* ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ በሚቆጣጠረው መከላከያ ሰራዊት ውስጥ እርስበርስ አለመተማመንና ጥርጣሬ አይሏል፡፡
* የህወሓት አገዛዝ ከሱዳን ጋር የተፈጠረውን ወታደራዊ ግጭት የህዝቡን ትኩረት ሊያስቀይርበት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡
* የህወሓት አገልጋይ የሆኑ “የአማራ ክልል” ባለስልጣናት ወደ ወልቃይት ሄደው በአካል ህዝቡን እንዲያነጋግሩ ከህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት ቀጭን ትዕዛዝ መተላለፉ ታወቀ፡፡
አርበኞች ግንቦት 7 ድምጽ ራድዮ እንደዘገበው
ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ በሚቆጣጠረው መከላከያ ሰራዊት ውስጥ እርስበርስ አለመተማመንና ጥርጣሬ አይሏል፡፡
በከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች ማለትም በጀነራል ሳሞራ የኑስ ቡድን እና በሌ/ጀነራል አብረሀ ወ/ማርያም ቡድን መካከል ተፈጥሮ የቆየው ጎራ ለይቶ መሰላለፍና አንዱ ቡድን ሌላኛን ለማስወገድ የሚያደርገው ፍትጊያ በእጅጉ ከሯል፡፡
በመሆኑም አለመተማመኑ ስር ሰዶ እስከ ታች ድረስ በመውረዱ በተዋጊው ሰራዊትና በአዛዦቹ፣ በአዛዦችና በአዛዦች፣ በአዛዦችና በህወሓት ባለስልጣናት፣ በተዋጊውና በተዋጊው እንዲሁም በተጨማሪ ባጠቃላይ በትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እና በሌሎች ቋንቋዎች ተናጋሪዎች መካከል ከፍተኛ ጥርጣሬ ነግሷል፡፡
ለህወሓት ታማኝና ቅርብ ነው የሚባለው አግአዚ ኮማንዶ ጦርም ባለመተማመኑ ማዕበል ተመትቶ መሰረቱ ተናግቷል፡፡ በዋና አዛዡ መቶ አለቃ ታፈሰ እና በምክትሉ ሻለቃ ባሻ ሰለሞን ኃ/ማርያም የሚመራው አንድ ሻምበል የአግአዚ ጦር ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ግንኙነት ፈጥሯል በሚል ጥርጣሬ መሽጎ ከቆየበት ሁመራ አካባቢ ዲማ የተባለ ቦታ ወደ ኋላ 30 ኪ.ሜ እንዲያፈገፍግ ተደርጎ ኩሃጂ ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
የህወሓት አገዛዝ ከሱዳን ጋር የተፈጠረውን ግጭት የህዝቡን ትኩረት ሊያስቀይርበት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡
የሱዳን መከላከያ ሰራዊት ድንበር ጥሶ ወደ ኢትዮጵያ የጠረፍ መንደሮችና እስከ መሀል ከተሞች ዘልቆ እየገባ በህዝብ ላይ ጭፍጨፋ እና የንብረት ውድመት በተደጋጋሚ እየፈፀመ መመለሱ ያስቆጫቸው አንዳንድ የህወሓት መራሹ መከላከያ ሰራዊት አባላት የአዛዦቻቸውን መመሪያ በመጣስ የፈፀሙት አፀፋዊ ጥቃት ያስከተለውን ግጭት በመንተራስ የህወሓት አገዛዝ ቅጥረኛ ካድሬዎች ሱዳን በጉልበት የወሰደችብንን መሬት ልናስመልስ ስለሆነ እርዱን በማለት ህዝቡን እየሰበኩ ከተጀመረው የነፃነት ትግል ለማዘናጋት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡
በተጨማሪም ካድሬዎቹ ሱዳን እና ኤርትራ የኢትዮጵያን መሬት ወረዋል የሚል ምክንያትና የገንዘብ መደለያ በማቅረብ ከመከላከያ የወጡ የቀድሞ አባላትን እንዲመለሱ በመማፀን ላይ ናቸው፡፡
የህወሓት አገልጋይ “የአማራ ክልል” ባለስልጣናት ወደ ወልቃይት ሄደው በአካል ህዝቡን እንዲያነጋግሩ ከህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት ቀጭን ትዕዛዝ መተላለፉ ታወቀ፡፡
ከአርበኞች ግንቦት 7 ጎን በመሰለፍ ለነፃነቱ እየተዋደቀ የሚገኘው እና “ክልል ሶስት እና ክልል አንድ የሚባል አናውቅም እኛ የጎንደር በጌምድር ተወላጅ ኢትዮጵያዊያን ነን” በማለት ለህወሓት ዘርን መሰረት ያደረገ አስተዳደር አልገዛም ብሎ በአንድነት የተነሳው የወልቃይት ህዝብ በህወሓት ህልውና ላይ ከፍተኛ ስጋት በመደቀኑ ነው የአማራ ክልል የህወሓት አገልጋይ ባለስልጣናት ወደ ቦታው ሄደው ህዝቡን በአካል በማግኘት ሰብከው ሃሳቡን እንዲያስለውጡና እንዲማፀኑም ጭምር በጌቶቻቸው የታዘዙት፡፡