Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ስለ ቀድሞ ባልንጀራዬ በጣም በሥሱ (ደረጀ ሀብተወልድ-ኢሳት)

$
0
0

በጠጠሩ ምትክ፣ በወንጭፉ ፋንታ፣
የሳዖልን ካባ፣ ያለበሱት ለታ፣
ያኔ ጊዜ ነው ዳዊት ፣ላይድን የተረታ።

ከዳዊት ከበደ(አውራምባ ታይምስ) ጋር ያለን ወዳጅነት ከሀዳር ምስረታ ዋዜማ አንስቶ እስከ ቃሊቲ ይዘልቃል። በዚህ ረዥም ጊዜ ውስጥ ክፉውንም፣ ደጉንም አሳልፈናል። (…እንዳስፈላጊነቱና እንደሁኔታው እያደር የምንጫዎተው ነገር ሊኖርም፤ላይኖርም ይችላል።)
Dawit kebede
-ከእስር ከተፈታን በኋላ እኛ ስንሰደድ ዳዊት ፈቃድ አግኝቶ አውራምባ ታይምስን ጀመረ። በነጻ የተፈቱት ሢሳይ አጌናና እስክንድር ነጋ ፈቃድ ተከልክለው በይቅርታ የተፈታው ዳዊት ፈቃድ ያገኘበትን ምክንያት የሚያውቁት እግዜርና ፈቃድ ሰጪው አካል ቢሆኑም፤ ዳዊት አውራምባን በመጀመሩ ደስተኛ ነበርኩ። ለዚህም ነበር አውራምባን ሲያቋቁም በጋዜጣው እንድሳተፍ ሲጠይቀኝ በደስታ ፈቃደኝነቴን የገለጽኩለት። ቃል በገባሁትም መሰረት ጽሁፌን እንዳያትም “ማስጠንቀቂያ እስኪደርሰው ድረስ” ባመቸኝ ጊዜ “ይድረስ ለባልንጀራዬ” በሚል ርዕስ አልፍ አልፎ ጽሁፎችን ልልክለት ሞክሬያለሁ።

-ዳዊት ለሲፒጄ ሽልማት ሲታጭ እነ ቶም ሩድስ አስተያዬት ያሰባሰቡት ከሌላ አካል ሳይሆን ከእኛው ከኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ነው።በወቅቱ ከአንዳንድ የሥራ ባልደረቦቼ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ስንነጋገር ያስተዋልኩት ነገር ፤ እኔን ጨምሮ ሁላችንም የዳዊትን መሸለም በደስታና በጥሩ ጎኑ መመልከታችንን ነው። “ሲፒጄ አንድ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛን( የሥራ ባልደረባችንን) ለዚህ ሽልማት ማብቃቱ ፤ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች የሰጠውን ክብርና አትኩሮት ያሳያል ፤ ዳዊት ተሸለመ ማለት እኛ ተሸለምን ማለት ነው” የሚል ነበር የሁላችንም መደምደሚያ።ከዚህ ውጪ አንዳንድ ሰዎች እንዳሉት፦“እንዴት ሆኖ?፣በልምድም፣ በከፈሉት መስዋዕትነትም ሆነ በሙያው ከእርሱ የሚልቁ ጋዜጠኞች እያሉ ሲፒጄ እንዴት እርሱን ይመርጣል? ምናምን..” የሚል ክርክርም ሆነ ጥያቄ በአንድኛችንም አልተነሳም። ይህንን፤ ማለትም እርሱ ለሽልማት በመታጨቱ በሁላችንም ዘንድ ጥሩ መንፈስ የማደሩን ነገር ፤በሥሱም ቢሆን ለዳዊት ሹክ ያልኩት ይመስለኛል።

– በሽልማቱ ዋዜማ ለሲ. ኤን. ኤን በሰጠው ቃለ-ምልልስ፦ “ ስደትን በፍጹም እንደማይሞክረው ብቻ ሳይሆን፤ መሥራት ተስኖን የተሰደድነውን ባልደረቦቹን “በመሰደዳችን” ሸንቆጥ ያደረገን ዳዊት ፤ በሽልማቱ ማግስት ብዙም ሳይቆይ አንድ ቀን ምሽት ላይ ድንገት መሰደዱን ነገረኝ። ከነበረን ቅርበት አኳያ አሜሪካ እንደደረሰ ምሽት ላይ መጀመሪያ የሆነውን ነገር የነገረኝ ለኔ ነበር። ደነገጥኩ፣አዘንኩም። ከሱ መሰደድ በላይ አውራምባ ታይምስ መዘጋቷ፣በጋዜጠኞቹም ላይ ድንገት የመበተን አደጋ ማንዣበቡ ይበልጥ አሳዝነኝ።”አይዞህ!በርታ! ጠንክር!!” ብዬ ላጽንናው ሞከርኩ። ለጊዜው ከነበረበት ቦታ አኳያ ከዚህ በላይ ማውራት አልቻልንም።

ይሁንና፦”ይቅርታዬን በማንሳት የቃሊቲውን ፍርድ ሊያጸኑብኝ እንደኾነ መረጃው ደርሶኝ ነው የወጣሁት።” በማለት ለመሰደዱ የሰጠኝ ምክንያት ለረዥም ጊዜ ግርታ ሳይፈጥርብኝ አልቀረም። ምክንያቱም ዳዊት ከቅንጅት መሪዎች ጋር በይቅርታ ይፈታ እንጂ እሱና ሌሎች ሦስት ጋዜጠኞች የተፈረደባቸው አራት ዓመት አካባቢ ነው። አመክሮው ሲታሰብ፤ አንድ የአራት አመት ፍርደኛ እስር ቤት የሚቆየው 32 ወራት ነው። ይህ ማለት ወደ 20 ወራት የታሰረው ዳዊት ይቅርታውን አንስተው ፍርዱን ቢያጸኑበት እንኳ ሊታሰር የሚችለው ከ12 ወራት(አንድ ዓመት) አይበልጥም ማለት ነው። እንግዲህ እሱ ያለውን አምነን ብንቀበል እንኳ “እሞታታለሁ እንጂ ስደትን ፈጽሞ አማራጭ አላደርግም” ያለው ዳዊት የተናገረው ቃል በጆሯችን ማቃጨሉን ሳያቆም ለስደት የተነሳው አንድ ዓመት ላለመታሰር ብሎ ነው ማለት ነው። ? ? ? …እናም ተሰደደ፤ ስደትንም ለመደ።
-እያደር እየለመደ ሲመጣ አውራምባ ታይምስን ከዚህ ሆኖ ስለሚቀጥልበት ከተቻለ ደግሞ አብረን መሥራት በምንችልበት ሁኔታ መነጋገራችንን ቀጠልን።

ኢሳት ላይ በቶሎ ሥራ የመጀመር ፍላጎቱ ከአንዳንድ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ለጊዜው እደግመዋለሁ ለጊዜው ሳይሳካ ቀረ። ጥቂት እንዲታገስም ተነገረው።
-ይህን ተከትሎ አውራምባን ወደማስቀጠል ሀሳቡ በማዘንበሉ ከአርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በዬነ ጀምሮ- እንደ ሚዲያ እስከ ኢሳት ድረስ በዋሽንግተን ዲሲ የአውራምባን ምስረታ በማስተዋወቅና በመቀስቀስ በተቻለ መጠን ከፍተኛ ድጋፍ አደረጉለት። በኢሳት ራዲዮና ቲቪ ላይም እንግዳ ኾኖ እየቀረበ በአንዳንድ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አስተያዬቱን ሲገልጽም ቆዬ።
-በዚህ ሁሉ ሂደት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ወይም ከጧቱ አንስቶ እስከመጨረሻው ድረስ ዳዊት ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በተለዬ መልኩ ለዶክተር ብርሀኑ ፍቅር እንደነበረው ነበር የማውቀው። ዶክተር ብርሀኑም እንዲሁ ለዳዊት መልካም አመለካከት ያለው ሰው እንደኾነ ራሱ ዳዊት ያውቀዋል።
-ይህ በእንዲህ እንዳለ ዳዊት ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመመለሻው ዋዜማ በሚያወጣቸው ጽሁፎችና ቪዲዮዎች ድንገት ዶክተር ብርሀኑ እና ንቅናቄያቸው ግንቦት 7 ላይ መተኮስ መጀመሩ አስደነገጠኝ። ከጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባር ባፈነገጠ ሁኔታ ዶክተር ብርሀኑ ላይ ጥቃቱን አጠናክሮ ከፈተ።ይህ የዳዊት 380 ዲግሪ የመዞር ክስተት፤ በጊዜው እኛን ብቻ ሳይሆን በቅርብም፣በሩቅም የሚያውቁትን ሁሉ ማስገረሙ ይታወቃል።

ከዚያም አልፎ አውራምባ ላይ በሚያወጣቸው ጽሁፎች ሁሉ ኢሳትን- “የግንቦት ሰባት ልሳን” ማለት ጀመረ።

ይሁንና እሱ እንዳለው ኢሳት የግንቦት ሰባት ልሳን ቢኾን ወይም ኢሳት በግንቦት ሰባት ጫና የሚሽከረከር ቢኾን ኖሮ ዳዊት እስካሁን የኢሳት ሠራተኛ ሆኖ በቀጠለ ነበር። ዳዊት ኢሳት ላይ በቶሎ እደግመዋለሁ በቶሎ ሊሠራ ያልቻለው ከግንቦት ሰባት መሪዎች ይሁኝታ በመታጣቱ እንደኾነ አድርጎ ቢያስብም፤ ይህ አስተሣሰቡ ግን የመርጋ በቃናን አገላለጽ ልዋስና መት ፐርሰንት ስህተት ነው።

አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፦ዳዊት ኢሳት ውስጥ የመሥራት ፍላጎት እንዳለው የገለጸ ሰሞን ዶክተር ብርሀኑ ለሥራ ጉዳይ ወደ አውሮፓ መጥቶ ነበር። ዶክተር ብርሀን፣ፋሲል እና እኔ አንድ ምሽት ራት እየበላን ሳለ ዶክተር ብርሀኑ ዳዊት በኢሳት ለመሥራት መፈለጉን እንደገለጸለትና ቦታ ካለ ይቀጠር ዘንድ ለማኔጅመንቱ ግፊት እንድናደርግለት አጥብቆ ጠየቀን። በዚህም ሳያቆም የዳዊት ኢሳት ውስጥ መግባት ይኖራቸዋል ብሎ የሚያስባቸውን ጠቀሜታዎች ሰፊ ሰዓት ወስዶ በዝርዝር ነገረን።

ይሁንና ኢሳት ውስጥ ስለሚቀጠሩ ጋዜጠኞችም ሆነ ስለ ሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች የሚወስኑት ማኔጅመንቱና የኤዲቶሪያል ቦርዱ ናቸው ።ዶክተር ብርሀኑ ዳዊት በቶሎ ኢሳት ውስጥ ሥራ እንዲጀምር ፍላጎቱ ቢኾንም የሱ ድርሻ ሃሳብ ከማቅረብ የዘለለ አይደለም።እደግመዋለሁ፦በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ የሚሰጡት ማኔጅመንቱና የኤዲቶሪያል ቦርዱ በጋራ ነው።ይህን ፕሮፌሰር ብርሀኑም ያውቀዋል። ለዚህም ነበር ዶክተር ብርሁኑ ፦”እናንተ ለማኔጅመንቱ ሃሳብ ብታቀርቡ..” የሚል አስተያዬት ደጋግሞ ሢሰጥ የነበረው።

በመጨረሻም የኤዲቶሪያል ቦርዱና ማኔጅመንቱ በመነጋገር ዳዊት ከኢሳት ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ጋር በተጣጣመ መልኩ ከፈለገ በትግረኛ አለያም በአማርኛ በሳምንት አንድ ጊዜ የሚተላለፍ የራሱን ፕሮግራም እንዲያዘጋጅ ስምምነት ላይ ተደረሰ። ይህም ውሳኔ በቅርቡ ካሉት ጋዜጠኞች በአንድኛው እንዲነገረው ተወሰነ።ይሁንና ዳዊት ውሳኔውን ሳይጠብቅ ተነስቶ ወደ አሪዞና አቀና። ውሳኔውን ሳይጠብቅ ወደ አሪዞና የሄደው፦ “ለምን ቶሎ ሥራ አልጀመርኩም? ሆን ብለው ነው እያሹኝ ያሉት” ከሚል ኩርፊያ ተነስቶ እንደሆነ እጥረጥራለሁ። ምክንያቱም ዳዊትን ለረዥም ጊዜ እንደማውቀው በባህርይው ቶሎ ተናዳጅና ችኩል ነው። ሀቁ ይኼው ነው። ይህ እኔ አሳምሬ የማውቀው እውነት ነው። ምናልባት ሌላ የማላውቀው ነገር ኖሮ አሳንሸው ይሆናል እንጂ አልጨመርኩበትም።ጓደኞቼም፣ ዳዊትም ምስክሮች ናቸው።ከነሱ በላይ ደግሞ ህሊና አለ።

ዳዊት ግን ይህን እውነታ አልተቀበለውም፤ወይም አላመነውም።በቶሎ ሥራ ያልጀመረው የግንቦት ሰባት መሪዎች በተለይም ዶክተር ብርሀኑ “እንድሠራ ስላልፈለገ ነው” ብሎ ያስብ ነበር። ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ተቋማት -በሰዎች(በግለሰቦች) ከሚሽከረከሩበት ባህል ውስጥ የወጣን ከመኾናችን አንጻር ዳዊት ይህን በማሰቡ አልተደነቅኩም።ምናልባት እኔም በሱ ቦታ ብኾን እንዲህ ላስብ እችል ይሆናል። ይህ አስተሣሰቡ ግን ስህተት እንደኾነ በወቅቱ ነግሬዋለሁ።

አይገርምም? ዶክተር ብርሀኑ “እባካችሁ አስገቡት?” እያለ ይማጸናል-ዳዊት “እንዳልገባ ያደረገኝ እሱ ነው”ብሎ ያስባል።

ዶክተር ብርሀኑ ሁሌም በአንድ ባህርይው ያሳዝነኛል። ያም ባህርይው ማናቸውንም ሰው በሙሉ ልቡ ማመኑ ወይም ለጥርጣሬ ጥቂት ቦታ እንኳ አለማስቀረቱ ነው። ዳዊት እሱ ላይ አነጣጥሮ መጻፍ እስኪጀምር ድረስ ዶክተር ብርሀኑ ዳዊት ኢሳት ውሥጥ እንዲሠራ ሀሳብ ማቅረቡን አላቆመም ነበር። ያ ብቻ አይደለም፤ ዳዊት እንደ ግለሰብ በእርሱ፣ እንደ ድርጅት በሚመራው ንቅናቄ ላይ አነጣጥሮ በተደጋጋሚ መጻፉን ተከትሎ ብዙዎች “ሰላይ”የሚል ስም ሢሰጡት እሱ ግን ይህን አይቀበልም። “ዳዊት ወደ አሜሪካ ሢመጣ አገኘዋለሁ ብሎ የጠበቀውን ነገር ባለማግኘቱ ነው በእልክ ወደ ሌላ አቅጣጫ የገባው” ብሎ ነው የሚያስበው። ከዚህ ውጪ ለሚጻፍበት ነገር ብዙ ትኩረት አይሰጠውም።
-ለህይውቱ ሰግቶ የተሰደደው ዳዊት በክብር አገር ቤት ተመለሰ። በ”ስደቱ” ዋዜማ “ለስድብ የተፈጠሩ ጥንዶች” ብሎ ከጻፈባቸው፣ እንዲሁም የሱን ዋና አዘጋጅ ውብሸ ታዬን ካሣሰሩት ከነ ሚሚ ስብሀቱ ካምፕ ጋር በይፋ ተቀላቀለ።

በአውራምባ ምክንያት ከህጻን ልጁ ተለይቶ የታሰረው ውብሸት ግን እስካሁን በቂሊንጦ እየማቀቀ ይገኛል።

-ከሰሞኑ ዶክተር ብርሀኑ ነጋ ወደ ግንባር ማቅናቱ ይፋ ከሆነበት ዕለት አንስቶ ዳዊት ዕረፍት አጥቷል። “ ጩኽ! ጩኽ! ተሳደብ! ተሳደብ!” ብሎታል።ከዛሬ ነገ ንዴቱ በርዶለት ወደ ኅሊናው ይመለሳል የሚል ተስፋዬን ሁሉ ጨርሶ ገደል ከቶታል።

-ዳዊት ያሰባሰበው መረጃ አለቀ መሰል አሜሪካ በነበረበት ወቅት በዶክተር ብርሀኑ ልጆች ምርቃት ሥነ-ስርዓት ላይ በእንግድነት ተጋብዞ የተገኘበትን ቤተዘመዳዊ የግብዣ ሥነ ስርአት በቪዲዮ ቀርጾ እነሆ ገጹ ላይ ለብዶታል። “የእውነት ታጋዮች ይህን ይመስላሉን?” በማለትም ሊሳለቅ ሞክሯል። ቪዲዮው የሚያስተላልፈው መልዕክት ግን እሱ ካሰበው በተቃራኒው ነው።ቪዲዮውን ያዩ ሰዎች ሁሉ ዶክተር ብርሀኑ የአሁን ለደረሰበት ውሳኔ ይበልጥ አድናቆታቸውን ሢሰጡ ነው ያደመጥኳቸው።

ስዬ አብርሀ በአንድ ወቅት ባቀረቡልን ጽሁፍ፦ “አሁን ያሉትን የኢህአዴግ ደጋፊዎችና አባሎች አስተሣስሮ ያቆማቸው እህል ውሀ ነው” ማለታቸውን አስታውሳለሁ። ትክክል ነው። ህወሀት-ኢሃዴግን በአባልነትም ሆነ በደጋፊነት ከከበቡት መካከል ብዙዎቹ -በቃኝ በማያውቀው ሆዳቸ ተሸንፈው እንጅ በድርጅቱ ዓላማ አምነውበት እንዳልሆነ ግልጽ ነው።ለነሱ የመጨረሻ ግባቸው እየበሉና እየጠጡ መኖር ነው።እነ ዶክተር ብርሀኑ ደግሞ “ ህዝባችን በመከራ፣ ሀገራችን በጭቆና በተያዙበት ወቅት በምቾት መኖር ዕረፍት አይሰጠንም” ብለው በረሀ ወረዱ።ይህ የዶክተር ብርሀኑ ውሳኔ ለሀወሀት-ኢሃዴጎች እብደት ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም በነ ሆዶሙ አምላኮሙ እና-በነ ዶክተር ብርሀኑ መካከል ሰፊ የአስተሣሰብ ልዩነት አለ።ይህ ልዩነት በአልዓዛርና- በሀኬተኛው ባለጸጋ መካከል እንዳለው ገደል ይሰፋል ብል አጋነንክ እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ። አዎ!ለኮንዶሚኒየምና ለ40 በ 60 ህሊናቸውን ሸጠው በወገን ስቃይ ለሚቀልዱ ሰዎች- እነ ነዶክተር ብርሀኑ ለነጻነት ሲሉ የተደላደለ ኑሯቸውን ትተው የመከራ ጽዋን ለመጎንጨት ወደ ቀራኒዮ መጓዛቸው ፈጽሞ ሊገባቸው አይችልም። የዶክተር ብርሀኑ ውሳኔ ትልቅና ጥልቅ ትርጉም ያለው በመከራና በስቃይ ውስጥ እየማቀቀ ለሚገኘውና ከፍትህ ጎን ለቆመው ብዙሀኑ ኢትዮጵያውዊ ነው።(እቀጥላለሁ)


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>