በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
ሀምሌ 1/2007 ዓ.ም ጎንደር ከተማ ውስጥ በፖሊስና ደህንነቶች ታፍኖ የታሰረው የሰማያዊ ፓርቲ አባል መምህር አለላቸው አታለለ የት እንደሚገኝ ለማወቅ እንዳልቻሉ ቤተሰቦቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ በጎንደር መምህራን ኮሌጅ የአይ ሲቲ መምህርና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ የሆነው መምህር አለላቸው አታለለ ሀምሌ 1/2007 ዓ.ም ወደ ደብረታቦር ተወስዶ በደብረታቦር ከተማ አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ እንደነበር መረጃ ደርሷቸው ታሰረ የተባለበት ቦታ ድረስ ሄደው ቢጠይቁም እንደሌለ ተነግሯቸዋል፡፡ ሌሎች እስር ቤቶች ውስጥ ቢያጠያይቁም ሊያገኙት እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡
መምህር አለላቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ ከቤተሰቦቹ ጋር ሳይገናኝ የቆየ ሲሆን ከሳምንት በፊት ወደ አዲስ አበባ ተወስዷል በመባላቸው አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ እስር ቤቶች ውስጥ እስከ ዛሬ ሀምሌ 18/2007 ዓ.ም ቢጠይቁም እንደሌለ ተነግሯቸዋል፡፡