ለበርካታ አመታት ምናልባትም የአንድ ወጣት እድሜ እና ከዛ በላይ ለሆነ ጊዜ በብዛት የአልኮል መጠጦችንና ጠጥተው ወይም ሲጋራ አጭሰው ዛሬ ከእነዛ ደባል ሱሶች ተላቀዋል ።
በወጣትነት ተጀምሮ ለብዙ አመታት የቆየን ልምድ ወይም ሱስ በተለይም ደግሞ የአልኮል ሱሰኝነትን ማቆም እጅግ ከባዱ እና አስቸጋሪው ነገር ነው ። ይህን ተቋቁመው ከዚህ ሱስ ከወጡ እንኳን ደስ ያለዎት ።
ምክንያቱም በማቆምዎ እድሜ ልክዎን የሃኪም ደጅ እንዲጠኑ ከሚያደርግዎት ነገር በመጠኑም ተላቀዋልና ። የአልኮል መጠጦች ፤ የአዕምሮ ክፍልን ፣ ጉበትን ፣ ልብን ፣ የአንጀት ክፍልንና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ የማድረግ አቅም አላቸው ።
እንዳለመታደል ሆኖ ግን ብዙዎች ለማቆም ሞክረው የተወሰኑት ሲቀጥሉ አብዛኞቹ ግን ተመልሰው በመግባት እድሜ ልካቸውን የተበላሸ እና ምስቅልቅሉ የወጣ ህይዎት እንደሚመሩ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ ።
ከዚህ በታች ያሉት ደግሞ በከባድ ሁኔታ ለበርካታ አመታት በዚህ ሱስ ውስጥ አልፈው አሁን ከአልኮል መጠጦች የራቀ ህይዎት የሚመሩ ካሉ ትናንት ያበላሹትን ጤንነት ዛሬ እንዴት ማደስ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ናቸው ።
ለተጎዳው ሰውነትዎ የተመረጠ አመጋገብ ስርአት ቢኖርዎት
በርካታ የአልኮል ሱሰኞች ለሰውነት አስፈላጊ በሆኑ የምግብ እጥረቶችና አልኮል በሚያመጣው ተፅዕኖ ሰውነታቸው እጅግ የተጎዳና የተጎሳቆለ ነው ።
ሰውነትዎ ካጣው የተመጣጠነ የምግብ እጥረትና በአልኮል ምክንያት ከተፈጠረበት ጉዳት እንዲያገግም ካልረዱት ደግሞ ውጤቱ የከፋ ይሆናል ።
አልኮልን አብዝቶ መጠጣት በደም ውስጥ የስኳር መብዛትን ያስከትላል ፣ የልብና የአተነፋፈስ ስርአትን ያዛባል ፣ እጅግ የተጎዳና የተጎሳቆለ ገጽታ ፣ ለስኳር በሽታ ፣ ለካንሰር ፣ ላልተፈለገ እና ጤነኛ ላልሆነ የስብ ክምችት ፣ የስርአተ ምግብ ሂደት መዛባት እና ከፍተኛ ለሆነ የመርሳት ወይም የአዕምሮ መቃወስ ያጋልጣል ።
በርካቶች ከዚህ ደባል ሱስ ሲላቀቁ እንደ መርሻ ወይም መተኪያ ብለው የሚወስዷቸው ጣፋጭ እና አንዳንድ አነቃቂ ፈሳሾችን ነው ፤ ይሁን እንጅ ይህ ልማድ ከቀደመው ሱስ ያልተናነስ አደገኛ እና የማይመከር ነው ይላሉ የአሪዞናው ዶክተር ጆን ኒውፖርት ።
ከሰላሳ አመታት በላይ በተቋረጡ ሱሶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሰሩት እና ምርምር ያደረጉት ዶክተሩ ፤ መሰል መተኪያ መንገዶች ወደ ቀደመው ሱስ እንዲመለሱ በማድረግ ለአደገኛ በሽታ እና ህልፈት ያጋልጣሉ ።
ከዛ ይልቅ የሜዲትራንያን የአመጋገብ ስርአትን መከተሉ አዋጭ ነው ።
የጥራጥሬ ውጤቶችን ፣ ፍራፍሬዎች ፣ አትክልትቶችና በጥሬ ሊዘጋጁ የሚችሉ ቅጠላ ቅጠሎች ፣ በፕሮቲን የበለጸጉ ስራስሮችና ቦሎቄ ፣ ቅባት ያልበዛባቸው እና ብዙ እሳት ያልመታቸው ምግቦች በአመጋገብ ስርአትዎ ውስጥ መካተት አለባቸው ይላሉ።
ከሜዲትራንያን የአመጋገብ ስርአት ጋር ተዋህዶ ገበታ ላይ የማይጠፋው ቀይ ወይን ግን በዚህ ሂደት ውስጥ አላስፈላጊ እንደሆነም ነው ዶክተር ኒውፖርት የሚናገሩት ፤ ስለዚህም በንጹህ ውሃ እና መሰል ፈሳሾች ምግብዎን ቢወስዱት መልካም ነው።
በንጥረ ነገሮች የበለጸጉ ምግቦችን ለሰውነትዎ ቢመርጡ
ከነበሩበት ሁኔታ ተላቀው ወደ አዲስ ምዕራፍ ሲሸጋገሩ ለተጎዳው ሰውነትዎ የተመረጡና እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ምግቦችን መውሰዱ ዋስትና ይሰጥወታል ።
በዚህ በኩል እነዚህ ምግቦች ውጤታማ ናቸው ፤
ከስንዴ ዘር የሚገኙ ምግቦች ፤
እነዚህ የአሚኖ አሲድ አይነቶች ለሰውነትዎ ብርታትና ጥንካሬን ከመስጠታቸውም ባለፈ ፤ በሰውነትዎ ውስጥ አላስፈላጊ የሆነ የስኳር ፣ የአልኮል እና ሌሎች እጾችን ወይም መድሃኒቶችን ለማስወገድ ያግዙዎታል ።
ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ ፥ እነዚህ ደግሞ ከመጠን በላይ በወሰዱት የአልኮል መጠጥ የተጎዱ የሰውነት ክፍሎችዎን እንዲሁም በመጠጥ የተጎዳን የልብ ክፍልን እና የተዛባውን የስርአተ ምግብ መፈጨት ሂደትን እንዲስተካከል ያስችላሉ ።
ከዚህ ባለፈም ከመጠን በላይ በሆነ የአልኮል መጠጥ የተዛባውን እና የጠፋውን የማስታወስ ችግርን ለማስወገድ እና የአዕምሮ ክፍልዎ ያጣውን ነገር ለማስተካከልም ይረዳሉ ።
የአሳ ዘይት እና ዘቢብ ደግሞ በዚህ ይዘታቸው የበለጸጉ እና በቀላሉ ሊያገኟቸው የሚችሏቸው ምግቦች ናቸው ።
በቪታሚን ኤ የበለጸጉ ምግቦች ፥ በዚህ ይዘታቸው የበለጸጉ ምግቦች በጠጡት የአልኮል ብዛት በጉዳት የሳሳ እና ምናልባትም የተበላሸ አጥንትዎን እና ጥርስዎን የማገገሚያ ጊዜ ይሰጡታል ።
ከእህል በበለጠ አልኮልን ወስደው ላቋረጡ ጠጭዎች ቪታሚን ኤን መጠቀም ከካንሰርም ይጠብቃቸዋል።
ቪታሚን ቢ ፥ ይህ ደግሞ በመጠጥ ብዛት ደንዝዞ የነበረውን የሰውነትዎን የነርቭ ስርአት ለማስተካልና ንቁ ለማድረግ ያግዝዎታል ።
ከዚህ በተጨማሪም ሰውነትዎን ዘና በማድረግ እና ከድብርት በመከላከል ከአላስፈላጊ ጭንቀትና ወደ ነበሩበት ሱስ እንዳይመለሱም ያግዙዎታል ።
ቪታሚን ሲ ፥ በቀላሉ የሚያገኟቸው በቪታሚን ሲ የበለጸጉ ምግቦች ደግሞ አጠቃላይ የሰውነትዎን ሁኔታ ለማስተካል የሚረዱ ናቸው ፤ የተዛባውን የደም ዝውውር ስርአትዎንም ያስተካክላሉ ።
በአመታት የአልኮል ብዛት ከጥቅም ውጭ የሆነውን ጉበትም የተስተካከለ እና መደበኛ ስራውን እንዲሰራ ያስችሉታል ።
በቪታሚን ኢ የበለጸጉ ምግቦች ፥ እነዚህ ምግቦች በአልኮል ብዛት ለተዳከመውና ለተጎዳው ሰውነትዎ የተዛባውን የልብ ስርአት ለማስተካከልና የደከሙትን የሰውነትዎን የጡንቻ ክፍሎች በማበርታት የተስተካከለ ገጽታዎን ለመመለስ ያግዛሉ ።
አነቃቂ ነገሮችን አይጠቀሙ ፤
ምናልባት ጠዋት ሲነቁ አንድ ሁለት ሲኒ ቡና እና የሻይ መጠጦች መልካም ሊሆን ይችላል ። በካፌይን የበለጸጉ መጠጦች ሲበዙ ግን መዘዘኛ ናቸው እና እነሱን ባይጠቀሙ መልካም ነው ይላሉ ዶክተር ኒውፖርት ።
አብዛኞቹ ከአልኮል ሱስ ያገገሙ ሰዎች በካፌይን የበለጸጉ መጠጦችን አብዝተው ሲወስዱ ይታያል ፥ ይህ ደግሞ በደም ውስጥ ያለውን ስኳር በማብዛት ጤናዎን አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ይከተዋል ።
ከፍተኛ ጭንቀት ፣ የእንቅልፍ እጦት ፣ መቅበዝበዝ ወይም ድንገተኛ እና ያልታሰበበት የሰውነት እንቅስቃሴ እና ያልተለመደ እና ጤነኛ ያልሆነ የሽንት ብዛት ደግሞ በዚህ መልኩ የተጠመዱ ሰዎች መገለጫዎች ናቸው ።
ለዚህ ደግሞ የበዛ የቡና ፣ የስፕሪስ ፣ ለስላሳ መጠጦች ( እንደ ኮካ ኮላ ያሉ ) እንዲሁም ጣፋጭ ቼኮሌቶችን ባይጠቀሙ መልካም መሆኑን ይናገራሉ ።
ለሚያገግመው ሰውነትዎ አነቃቂ ነገር ወይም ካፌይን የሌለበት አረንጓዴ ሻይ ፣ ንጹህ ውሃ ከቻሉ የታሸጉ እንዲሁም በውሃ ቀጠን ያለ የፍራፍሬ ጭማቂዎችን መውሰዱም ይመከራል ።
የሲጋራ ሱስ ካለብዎት ያቁሙ ፥
የሲጋራ ሱስ ካለብዎት ሳያመነቱ ቢያቆሙት ይመከራል ። የአልኮል መጠጥ ሱሰኛ የሆኑ ሰዎች ካልሆኑት ይልቅ በከፍተኛ ሁኔታ ሲጋራ ያጨሳሉ ፤ እነዚህ ሰዎች ከአልኮል ነጻ ቢሆኑ እንኳን ከሲጋራ ሱስ ሲላቀቁ አይታይም ።
ሲጋራ ማጨስ አደገኛ ቢሆንም አልኮልን ለሚወስዱት ደግሞ ከመርዝም በላይ አደገኛነቱ ይጎላል ፤ ምክንያቱም በአልኮል ምክንያት በነርቭ ላይ አደጋ ከማስከተሉም ባለፈ የአዕምሮ የነርቭ ክፍሎችን ሙሉ በሙሉ ከአገልግሎት ውጭ ማድረግ በመቻሉ ነው ።
ሲጋራን ከአልኮል ጋር ሲወስዱ በሂደት በጭንቅላትዎ ውስጥ ያሉ የደም ማስተላለፊያ ቱቦዎች ላይ ጉዳት በማድረስ በጭንቅላትዎ ውስጥ በቂ የደም ፍሰት እንዳይኖርና ከዛ ጋር ተያይዘው ለሚመጡ እጅግ አደገኛ ሁኔታዎች ያጋልጣል ።
የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ብዙዎቹ ከአልኮል ሱሰኝነታቸው ቢላቀቁም ሲጋራ ማጨሱ ላይ ግን ያመነታሉ ፤ ካጨሱ ደግሞ ወደ አልኮል መመለስዎ አይቀርምና ተዳብለው ከሚጎዱዎት ለጤናዎ የሚበጅዎን ቢመርጡ መልካም መሆኑን ባለሙያዎቹ ይመክራሉ ።
መጠጡን ለማቆም ያደረጉት ጥረት ለሲጋራውም ይረዳዎታልና ይጠቀሙበት ፤ የህክምና ክትትል እና የባለሙያ ምክርም ይረዳዎታልና እሱን በማድረግ አደገኛውን ልማድዎን ያስወግዱት ።
ምንጭ ፥ ቦተም ላይን ሄልዝ