Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Health: የውሃ ምስጢሮች

$
0
0

‹‹እኔ እኮ አይጠማኝም››፤ ‹‹አያስመለክተኝም››፤ እንዲያም ሲል ‹‹ሰው እንዴት ባዶ ውሃ ይጠጣል?›› የሚሉ ሰዎች አጋጥመዋችሁ ይሆናል፡፡ እውነታው ወዲህ ነው፡፡ ፈሳሽ እየወሰዱ ያለ ምግብ ለሳምንታት መቆየት ይቻላል፡፡ የውሃ እጥረት ግን ከማናቸውም ንጥረ ምግቦች እጥረት በተለየ መልኩ በፍጥነት ህይወትን ያሳጣል፡፡ ያለ ውሃ ለ10 ቀናትም እንኳ በህይወት መቆየት አይቻልም፡፡ የሰውነታችን እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የውሃን ተሳትፎ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጠይቅ ነው፡፡ ይሁንና ስለ ውሃ አስፈላጊነት ብዙው ሰው በውል አልተገነዘበውም፡፡ እንዲያውም የንጥረ ምግብ ምድብነቱንም የሚጠራጠሩ ሰዎች አሉ፡፡ ውሃ የሚጠጡት ሊጠማቸው አለበለዚያ ምግብ ሲያንቃቸው ብቻ ነው፡፡
water for health
ከወንዶች የሰውነት ክብደት 60 በመቶ ከሴቶች ደግሞ 50 በመቶ ያህል ውሃ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሰውነት ውሃ መጠን ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ አንሶ መገኘቱ ስለ ስብ ክምችታቸው ነው፡፡ ውሃ እና ስብ አያጣጣሙም፡፡ በሰውነታችን ውስጥ ከ38-45 ሊትር የሚገመት ውሃ ይገኛል፡፡ አንጎል 78፣ ደም 83፣ ጡንቻ 75፣ አጥንት 22 በመቶ ውሃ ናቸው፡፡ ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ የሰውነት የውሃ መጠን እየቀነሰ፣ የሰውነት ስብ ክምችት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ፆታ፣ ዕድሜ፣ ውፍረት የመሳሰሉት ጉዳዮች የሰውነት ውሃ መጠንን እንደሚወስኑ ልብ ይሏል፡፡

ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን ፈሳሽ ፍላጎታችንን የምናሟላው ከምንጠጣው፣ ቀሪውን ሃያ ከመቶ የምናሟላው ደግሞ ከምንበላው ነው፡፡ አትክልትና ፍራፍሬዎች በርካታ ውሃን አዝለዋል፡፡ እንካችሁ ውሃ ከነሙሉ ትጥቁ ይሉናል፡፡ ለምሳሌ ሀብሃብ፣ ቲማቲም፣ ቆስጣ እና ሰላጣ 90 በመቶ ይዘታቸው ውሃ ሲሆን በአቅራቢያችን የሚገኘው ዋጋውም እየተወደደ ያስቸገረን የቫይታሚን ሲ አለኝታችን ‹‹ብርቱካን›› ደግሞ 87 በመቶ ውሃ ነው፤ በፕሮቲን ምንጭነታቸው የምናውቃቸው ሥጋ፣ ዓሣ፣ ዶሮ ሳይቀሩ ከግማሽ እስከ ሁለት ሦስተኛ ይዞታቸው ውሃ ነው፡፡

የውሃ ጠቀሜታ በሰውነታችን ውስጥ ለመጠጥ ፍጆታችን ውሃን እንምርጥ ዘንድ ያሉት ሳይንሳዊ መረጃዎች ግድ ይሉናል፡፡ ከዚህም ሌላ በርካሽ ዋጋ በየቦታው የምናገኘው ጥም ቆራች መጠጥም ውሃ ነው፡፡

ውሃ ማጓጓዣ ነው
ንጥረ ምግቦች እና ወሳኝ ማዕድናት በመላው የሰውነት ክፍሎች የሚዘዋወሩት፤ ቆሻሻ ተረፈ ምርቶች ከሰውነት የሚወገዱት በውሃ ተሸካሚነት ነው፡፡ ያለ ውሃ የሰውነት ዋና ዋና የስራ ሂደቶች ክፉኛ ይስተጓጎላሉ፡፡

ውሃ ማለስለሻ፣ ማለዘቢያም ነው
በውስጣዊ የሰውነት አካላት ዙሪያ የውሃ መኖር እንደ መከላከያ ግድግዳ በመሆን ከውጫዊ ድንገተኛ ጫና ይጠብቃቸዋል፡፡ የዚህ ጥበቃ ተጠቃሚ ከሆኑ የሰውነታችን ብልቶች ውስጥ አንጎል፣ አይን፣ እና ህብለ ሰረሰር ይገኙበታል፡፡
ውሃ በምራቅ እና በሌሎች የሰውነታችን ፈሳሾች ውስጥ በብዛት ስለሚገኝ የተፈጨ ምግብ በጉሮሮ ወርዶ ወደ አንጀት እንዲደርስ የምግብ ቧንቧን የማለስለስ ሚና ይጫወታል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ምራቅ የቀነሰባቸው ሰዎች ምግብ ለመዋጥ የሚቸገሩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ያሉ የአጥንት መገጣጠሚያዎች እንደልብ እንዲተጣጠፉ አሁንም ውሃ የራሱ ድርሻ አለው፡፡

ውሃ በሰውነት ውስጥ በሚካሄዱ ኬሚካላዊ ዑደቶች ንቁ ተሳታፊ ነው
የፕሮቲን እና የካርቦሃይድሬት ዑደት ልመት ውጤቶች የሰውነት ህዋሳት በሚጠቀሙበት መልኩ እንዲቀየሩ ውሃ የሚጫወተው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ እንደ ተረፈ ምርት ሆኖ ከሰው ሰራሽ ብክለት ነጻ የሆነ አንድ ብርጭቆ ያህል ውሃ በየቀኑ በዚህ መልኩ ይፈጠራል፡፡ እኛ እንገነዘበው ይሀናል እንጂ ህዋሳት ለዕለት ፍጆታቸው ፈጥኖ የሚያደርስላቸው በመሆኑ ውሃን በጉጉት ይጠብቁታል፡፡

ውሃ የሰውነት ሙቀትን ይቆጣጠራል
በጤና እንሰንብት ዘንድ የሰውነታችን ሙቀት ተገቢ በሆነ ልክ ተወስኖ መቆየት አለበት፡፡ የውጪው አየር ሙቀት ሲለዋወጥ የሰውነታችን ሙቀት አብሮ አይለዋወጥም፡፡ ይህም የሆነበት ዋናው ምክንያት ሰውነታችን አብዛኛውን እጅ ውሃ በመሆኑ፣ ውሃ ደግሞ በተፈጥሮው የሙቀት ለውጥ የሚያስተናግደው ዝግ ብሎና ተረጋግቶ ስለሆነ ሙቀትን አፍኖ ይይዛል፡፡
በሞቃታማ የአየር ንብረት ወቅት ከሰውነታችን ውስጥ የውሃ ትነት ይከሰትና አላስፈላጊ ሙቀት አብሮ እንዲወገድ ያደርጋል፡፡ በዚህም ላይ ላብ አለ፡፡ ሳናስተውለውም ቢሆን ቀንና ሌሊት ያልበናል፤ በተለይ በሞቃት የአየር ንብረት እና በከፍተኛ አካላዊ እንቅስቃሴ ወቅት የላብ መጠን ይጨምራል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ውሃ ቆዳችንን በማለስለስ ውበትን እንደሚያጎናፅፍ ይታወቃል፡፡ የስነ ቆዳ ውበት ባለሙያዎች መፍቀሬ ውበት ወይዛዝርት ደንበኞቻቸውን አበክረው የሚመክሩት ዘወትር ውሃ በበቂ ሁኔታ እንዲጠጡ ነው፡፡

የሰውነት ፈሳሽ ሚዛን መጠበቅ
ሰውነታችን በየቀኑ የውሃ ብክነት ከውሃ አወሳሰድ ጋር እንዲመጣጠን የሚያስችል ውስጣዊ አሰራር አለው፡፡ የፈሳሽ እጥረት ሲያጋጥም ኩላሊቶች መልኩ ቡናማ የሆነ መጠኑ ያነሰ ፈሳሽ በሽንት መልክ እንዲወገድ በማድረግ የሰውነት ፈሳሽን ይቆጥባሉ፡፡ በተጨማሪም አንጎላችን ዝም አይልም፤ የውሃ ጥምን በማወጅ ፈጥነን ውሃ እንድንጠጣ ያሳስባል፡፡ የፈሳሽ ሚዛኑ ወደ መበራከት ካመዘነ ኩላሊቶች የጠራ ሽንትን አብዝተው ያመርታሉ፡፡ አንጎል በበኩሉ ውሃ ጥምን ያነሳል፡፡

ውሃ ከሰውነታችን የሚወገድባቸው መንገዶች
በሚታይና በማይታይ መልኩ ውሃ ከሰውነታችን ይወጣል፡፡ ቆዳ፣ ኩላሊቶችና ሳንባዎች በውሃ መወገድ ሂደት ዋና ዋና ተሳታፊዎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ዝርዝሩን ቀጥለን እንመልከት፡፡

በቆዳ በኩል
የሰውነት ሙቀትን ለመቆጣጠር ከሚያስችሉ ዘዴዎች አንዱና ዋነኛው በቆዳ በኩል ውሃን ማውጣት ነው፡፡ ይህም እንደ አካባቢው የሙቀት መጠን እና እንደ አካላዊ እንቅስቃሴ ሁኔታ ይለያያል፡፡ በአማካይ በላብ በኩል የሚወገደው የውሃ መጠን 100 ሚሊ ሊትር ነው፡፡
በሞቃት አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ውስጣዊ የሰውነታቸውን ሙቀት ለመቆጣጠር ሲባል በቀን እስከ 2 እና 3 ሊትር የሚደርስ ላብ ሊያልባቸው ይችላል፡፡ ይህን የሚተካ ውሃ ካልተወሰደ የፈሳሽ ሚዛኑ እንደሚዛባ መገመት አያዳግትም፡፡ አድካሚ የሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ ከታከለበት ደግሞ ሁኔታውን ይበልጥ ያባብሰዋል፡፡
የሰውነት እንቅስቃሴ ከወትሮው በጨመረ ቁጥር የሰውነት ሙቀትም ይጨምራል፡፡ ታዲያ ተማሪው ሙቀት መወገድ የሚችለው በላብ አማካኝነት ነው፡፡ ከፍተኛ ደረጃ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የላብን መጠን 1 ሊትር በሰዓት ሲያደርሱት ይህ ድርጊት በሞቃታማ አካባቢ ከሆነ ግን በላብ የሚወገደው የውሃ መጠን 2 እና 3 ሊትር በሰዓት ሊደርስ ይችላል፡፡
በበሽታ ምክንያት የሚመጣ የሰውነት ትኩሳት ሌላው ላብ አምጪ ጉዳይ ነው፡፡ የሰውነት ሙቀት ከተለመደው በ1 ዲግሪ ሴልሽየስ ከጨመረ የላብ መጠን በግማሽ ሊትር ይጨምራል፡፡ ትኩሳት ላለባቸው ሰዎች ተጨማሪ ፈሳሽ እንዲወስዱ ሐኪሞች የሚመክሩት ለዚህ ነው፡፡
ላብ የሚታይ ነገር ነው፡፡ የማይታ ነገር ግን በቆዳ በኩል የሚባክን ውሃ አለ፡፡ ስለ እርሱ ጥቂት ላውጋችሁ፡፡ ውሃ ከቆዳችን ያለማቋረጥ በትነት መልኩ የሚወጣ ሲሆን መጠኑም በቀን 350 ሚሊ እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ የቆዳ ላይ ትነት እና ላብ አይገናኙም፡፡ አንድ አስገራሚ ማስረጃ ላቅርብ፡፡ ያለ ላብ አመንጪ ዕጢዎች የሚፈጠሩ ሰዎች አሉ፡፡ (እንዲህ ያለ ሰው ገጥሞኛል) ታዲያ ሰዎቹ በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነው ባያልባቸውም ሊከሰት ይችል የነበረውን ከፍተኛ የሰውነት ሙቀት መጠን በቆዳ ትነት አማካኝነት ይከላከሉታል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ምን ይውጣቸው ነበር?

በኩላሊቶች በኩል
ከሰውነት በኩላሊቶች አጣሪነት የሚወገደው የሽንት መጠን በሆርሞን ቁጥጥር ስር ያለ እና የሰውነት የፈሳሽ ሚዛንን ለመጠበቅ ሲባል ወቅታዊ ማስተካከያ የሚደረግበት ነው፡፡ ብዙ ፈሳሽ እየወሰደ የሚገኝ ግለሰብ ብዛት ያለው ጠራ ያለ ሽንት ሲኖረው በአንፃሩ የፈሳሽ አወሳሰዱ የቀነሰ ሰው የሚኖረው ሽንት መልኩ የደፈረሰ፣ መጠኑ ያነሰ ነው፡፡ ይህ ቀላል የሽንት ቀለምን የመለየት ዘዴ የሰውነት የፈሳሽ ሚዛንን ለመገምገምና የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ያስችላል፡፡ የሰውነት ፈሳሽ እጥረት ሲያጋጥም ኩላሊቶች ውሃን በመቆጠብ ስራ ይጠመዱና በሽንት መልክ እንዲወገድ የሚፈቅዱት የፈሳሽ መጠን ከግማሽ ሊትር አይበልጥም፡፡ በተቃራኒው ሰውነት በውሃ ብዛት ሲንበሸበሽ በቀን እስከ 20 ሊትር ውሃ በሽንት መልክ ማስወገድ እንደሚችሉ ያስመሰክራሉ፡፡ በአዘቦቱ ቀን የሽንት መጠን ከ1.3 እስከ 1.4 ሊትር ነው፡፡ ፕሮቲንና ጨው የበዛባቸው ምግቦች እንዲሁም የአልኮል መጠጦች ሽንትን በማብዛት ይታወቃሉ፡፡

በሳንባዎች በኩል
በአፍ እና በአፍንጫ ተስቦ የሚገባው አየር ከመተንፈሻ አካላት ስስ ልባስ በሚለገሰው እርጥበት ምክንያት ለውስጥ ሰውነት ወደ ሚስማማ እርጥበታማ አየር ይቀየራል፡፡ ውሃ ለእርጥበት መፈጠር ዋናው ግብዓት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ያለማቋረጥ በትንፋሽ የሚጠፋው የውሃ መጠን ከ350-400 ሚሊ በቀን ይገመታል፡፡
በትንፋሽ በኩል የሚወጣው የውሃ መጠን ያካባቢው አየር እርጥበት ሲቀንስ፣ ኤር ኮንዲሽነር ባለበት ክፍል፣ በተራራማ ቦታዎች፣ አይሮፕላን ውሰጥ እና በስፖርታዊ ልምምድ ወቅት ይጨምራል፡፡ እንደ አሁኑ ባለ ቀዝቃዛ ወራት በትንፋሽ የሚጠፋው ውሃ ይበራከታል፡፡ ለዚህም ነው በቅዝቃዜ ወቅት የአፍና አፍንጫ ውስጥ ድርቀትን የሚያስተናግዱት፡፡

በዓይነ ምድር በኩል
በቀን ከመቶ ሚሊ ሊትር ያልበለጠ ውሃ ከአይነ ምድር ጋር አብሮ ይወገዳል፡፡ ሰዎች እንደ ኮሌራ በመሰሉ አጣዳፊ የተቅማጥ በሽታዎች ሲያዙ ይህ አሃዝ በማይታመን መልኩ ወደ 1 ሊትር በሰዓት ሊያሻቅብ ሲችል አፋጣኝ የፈሳሽ መተካት ህክምና ካልተደረገ በአጭር ጊዜ ውስጥ ህይወትን ሊያሳጣ የሚችል ነው፡፡

ለውሃ እጥረት የተጋለጡ
ህፃናት

የማላብ ስርዓታችን ገና ስላልዳበረ ከፍ ያለ ሙቀት መቋቋም ይሳናቸዋል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፣ ለውሃ ጥም ስሜት እንደ አዋቂዎች ያለ አፀፋዊ ምላሽ አይሰጡም፡፡ አጣዳፊ ትውከትና ተቀማጥ ካጋጠማቸው ደግሞ ለሰውነት መሟሸሽ ፈጥነው ይጋለጣሉ፡፡
አረጋውያን

እንደ ወጣቶቹ ሰውነታቸው ውሃ ሲያጥረው ስለማይጠማቸው ለሰውነት መሟሸሽ ተጋላጭ ናቸው፡፡ ተደራራቢ በሽታዎች ለእነዚህም የሚወሰዱ መድሃኒቶች ካሉ የውሃ እጥረት ችግሩ ይባባሳል፡፡
ህፃናትና አረጋውያን በቂ ውሃ እንዲያገኙ ማስቻል ከቤተሰብ አባላት እንዲሁም ከህብረተሰቡ የሚጠበቅ በጎ ተግባር ነው፡፡

አትሌቶች

ከሌሎቹ ንጥረ ምግቦች ይልቅ የውሃ አወሳሰዳቸው ትኩረትን የሚሻ ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ውሃ ፈርጣማ ጡንቻዎቻቸውን ለማብረድ፣ የሰውነታቸውን ሙቀት ለመቆጣጠር ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ የውሃ እጥረት ስፖርታዊ ክንውናቸውን ክፉኛ የማወክ ዝንባሌ ሲኖረው መዘዞችም አሉት፡፡ ለምሳሌ አንድ አትሌት ከሰውነት ክብደቱ ከ2-3 በመቶ ያለው በላብ ምክንያት ቢቀንስ በአግባቡ ተልዕኮውን ማከናወን ይሳነዋል፡፡ የፈሳሽ ጉድለቱ ከ7-10 በመቶ ከደረሰ ግን ሰውነት ከአቅም በላይ በሀነ ግለት ይመታና ከዚህች ዓለም ስንብት ይሆናል፡፡ የማራቶን ሯጮች በአንድ ሰዓት ውስጥ እስከ 2.8 ሊትር የሚገመት ላብ ያልባቸዋል፡፡ በስፖርታዊ ልምምድም ሆነ በውድድር ወቅት ከሚከሰት ከፍተኛ የፈሳሽ እጥረት ለመከላል ከድርጊቱ አስቀድሞ (2 ብርጭቆ ውሃ ከ2 ሰዓት በፊት፣ 1 ብርጭቆ ውሃ ከ15 ደቂቃ በፊት)፣ በክንዋኔው ወቅት (በየ20 ደቂቃው ከግማሽ እስከ 1 ሙሉ ብርጭቆ) እና ከውድድሩም በኋላ በቂ ውሃ መጠጣት ያስፈልጋል፡፡
ከዚህም ሌላ ከቤት ውጭ ባልተከለለ ቦታ ቀኑን ሙሉ የሚሰሩ ሰዎች ለፈሳሽ እጥረት የተጋለጡ ናቸው፡፡ ሞቃትና ከፍተኛ የአየር እርጥበት ከልፋት ጋር ሲደመሩ የፈሳሽ እጥረቱን ያባብሱታል፡፡ እንዲህ ያሉ ሠራተኞች ከጎናቸው ውሃ ሳይለያቸው በመካከል ውሃ ቢጎነጩ መልካም ነው፡፡

ለምን ይጠማናል?
ሰውነታችን የውሃ ፈሳሽ እጥረት እንዳጋጠመው አብዛኛውን ጊዜ የሚያስታውቀው ጥምንን በማወጅ ነው፡፡ አንድ ሰው የጥም ስሜትም ሆነ የህመም ስሜት ሳይሰማው የሽንቱ መጠን ሳይቀንስ መልኩም ሳይደርስ የጠራ ከሆነ ግለሰቡ የፈሳሽ ሚዛኑ የተጠበቀ ነው ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ታዲያ ሁሌም እንዲህ አይሆንም፡፡ ልማድ አድርገነው ውሃ እስኪጠማን ድረስ ሳንጠጣ የምንቆይ ከሆነ አንዳንዴ ሰውነታችን የፈሳሽ እጥረት እንኳ ገጥሞት አንጎላችን ጥምን ሳያውጅ የሚቆይበት ጊዜ አለና በየጊዜው በቂ ውሃ መውሰድ የዕለት ተዕለት ተግባራችን ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይ ህፃናት፣ አረጋውያን፣ ስፖርተኞች፣ እና አትሌቶች የሰውነት ውሃ ፍላጎታቸው በጥም ላይ ሊመሰረት አይገባውም፡፡

በየቀኑ ምን ያህል ውሃ መጠጣት አለብን?

እያንዳንዱ ሰው በጤና ለመሰንበት በቂ ውሃ በየቀኑ መጠጣት ይኖርበታል፡፡ ይህ መጠን እንደሰውየው ዕድሜ፣ ፆታ፣ ጤና እና አካላዊ እንቅስቃሴ ሁኔታ ይለያያል፡፡ የአየር ሁኔታውም ተፅዕኖ አለው፡፡ በደምሳሳው ሲታይ ከባድ የሰውነት እንቅስቃሴ የማያደርግ፣ በምቹ የአየር ንብረት ያለ አንድ ጤናማ አዋቂ ሰው በቀን አነሰ ከተባለ 2 ሊትር (8 ብርጭቆ) አለበለዚያ 3.5 ሊትር (13 ብርጭቆ) ውሃ መጠጣት ሲያስፈልገው ካላቸው የስብ ክምችት የተነሳ የሴቶች የውሃ ፍላጎት ከወንዶቹ በአማካይ በ1 ሊትር ያንሳል፡፡
ውድ አንባብያን በቂ ውሃ የመጠጣት ልምድን ለማዳበር ከዛሬ ጀምሩ፤ በቀስ በቀስ የውሃ አወሳሰድን አጎልብቱ! ለዚህ እኔ ምስክር ነኝ፣ ከ2 ብርጭቆ ተነስቼ አሁን ላይ 13 ብርጭቆ ደርሻለሁ፤ ቤተሰቦቼም እንደኔ የመጠጥ ውሃ ይደፍራሉ፡፡

አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ከመደበኛው በታች የሆነ የፈሳሽ አወሳሰድ ስላለው በመለስተኛ የሰውነት መሟሸሽ ደረጃ ውስጥ እንደሚገኝ ይገመታል፡፡ ስር የሰደደ የሰውነት ፈሳሽ እጥረት ለኩላሊት ጠጠር እና ሌሎች መዘዞቹ እንደሚዳርግ የሞያ ተሞክሮዬ አስገንዝቦኛል፡፡ የህክምና መጻህፍት ከዚህ ጋር ይስማማሉ፡፡
በእነዚህና እነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ውሃ ለህይወታችን መሰረት ነው፤ ውሃ ህይወት ነው እላለሁ!
ቸር እንሰንብት፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>