Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Sport: ቬንገር በማባረር አልተቻሉም

$
0
0

በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ የሐምሌ እትም ቁጥር 53 ላይ ታትሞ የወጣ።

Arsene-wenger (1)ከባድ ሸክም ከአርሰን ቬንገር ትከሻ ተነሳ፡፡ በጣም ከባድ፤ ለዚያውም የ10 ሚሊዮን ፓውንድ ሸክም፡፡ ሴባስቲያን ስኩዊላቺ፣ ዴኒልሰን እና አንድሬ አርሻቪን ያለምንም ጥቅም ክለቡን በደመወዝ መልክ በዓመቱ በድምሩ 10 ሚሊዮን ፓውንድ ሲያስወጡ ኖረዋል፡፡ አሁን የአርሰናል ንብረት አይደሉም፡፡ ይህም ለደጋፊዎች መልካም ዜና ነው፡፡ ሆኖም ወሬው በእርግጥም መልካም እንዲሆን አሰልጣኙ 10 ሚሊዮን ፓውንድን መልሰው ለቡድኑ ማጠናከሪያ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ፈረንሳዊው ከዚህ ቀደም እንደሚያደርጉት የተሸረፈ እና የተቆጠበውን ገንዘብ ለማይወደደው የክለቡ ቦርድ አሳልፈው ከሰጡ የተጨዋቾቹ ሽያጭ የፈጠረው ደስታ ከደጋፊዎቹ ጋር አይቆይም፡፡

ይሁን እንጂ አርሰናል ለዓመታት ያለአግባብ ታቅፎ የያዛቸውን እና ላልተገባ የደመወዝ ወጪ የዳረጉትን ተጨዋቾች መሸኘት መጀመሩ እንደበጎ ጅምር ተወስዶለታል፡፡ በተለይ አሰልጣኙ እነዚህን ሂያጆች በአዳዲስ እና በተሻሉ ተጨዋቾች ካልተተኩ እርምጃቸው ሙሉ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ቬንገር ተጫዋቾችን ለመሸጥ ወይም በነፃ ለመልቀቅ አዲስ አይደሉም፡፡ ሆኖም ሰውዬው ምርጥ ተጫዋቾቻቸውን ከሸኙ በኋላ ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ያሉ ከዋክብትን ለመተካት ሲቸገሩ ኖረዋል፡፡ ለዓመታትም በተመሳሳይ መልኩ ተጉዘዋል፡፡

ቬንገር ዴኒልሰን ትቶት የሄደውን 50 ሺ ፓውንድ ሳምንታዊ ደመወዝ እንዲሁም የስኩዊላቺን 60 ሺ ፓውንድ እና የአርሻቪንን 85 ሺ ፓውንድ ተቀብለው አርሰናልን መጥቀም የሚችሉ ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች ማምጣት ይችላሉ፡፡ የዝውውር ሂሳቡን ትተን ስለደመወዝ ብቻ ካወራ አሰልጣኙ የሶስቱን ተሰናባቾች ገንዘብ ተጠቅመው ሁለት ትልልቅ ስም ያላቸው ተጨዋቾችን በ90 ሺ ፓውንድ ሳምንታዊ ደመወዝ ሊያስፈርሙ እድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ትልቅ ተጨዋች እና ሁለት ሌሎች የቡድኑን ጥልቀት እና ጥራት ከፍ የሚያደርጉ ከዋክብትን ደመወዝ ቀጥ አድርጎ ይይዝላቸዋል፡፡

አርሰን የማይጠቀሙባቸውን ተጨዋቾች መሸኘታቸው እና በሌሎች መተካታቸውን በጀታቸውን በተሻለ መንገድ እንዲጠቀሙ ከማድረጉም ሌላ የቡድናቸውን ጥራት በትልቁ ያሳድግላቸዋል፡፡ ቬንገር በግብ ጠባቂ ቦታ ወጣቶችን ቢይዙም አንዳቸውም በደጋፊዎች እምነት የሚጣልባቸው አልሆኑም፡፡ በኢምሬትስ ከቮይቾች ቼዝኒ እና ሉካስ ፋቢያንስኪ በመቀጠል የቡድኑ ሶስተኛ ግብ ጠባቂ የነበረው ቪቶ ማኖኔ ወደ ሰንደርላንድ ሲያመራ የተሸጠበት ዋጋ ይፋ ባይሆንም አርሰናል 2 ሚሊዮን ፓውንድ ሳያገኝበት እንዳልቀረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ መድፈኞቹ በንፅፅር ወጣት የሚባልን የ25 ዓመት በረኛ ቢያጡም የጣልያናዊው ክለቡን መልቀቅ ለሌላ ልምድ ያለው ግብ ጠባቂ በር መክፈቱ እርግጥ ይመስላል፡፡ በተለይ ከአርሰናል ጋር ድርድር ላይ መሆኑ የሚነገርለት ዡሊዮ ሲዛር ክለቡን ከተቀላቀለ ለሌሎቹ ሁለት ወጣት ፖላንዳዊያን ጥሩ ልምድ ሊያካፋል እና ቡድኑንም ወደ ውጤት ሊያመራ ይችላል፡፡

ሌላኛው የክለቡ ተሰናባች በኤምሬትስ ረጅም ጊዜ የቆየው ዮሀን ዡሩ ነው፡፡ ስዊዘርላንዳዊው ተከላካይ በተለይ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ከሁለት የካፒታል ዋን ግጥሚያዎች ውጪ በቋሚነት የጀመረው ግጥሚያ የለም፡፡ በጃንዋሪ ወደ ጀርመኑ ሆኖቨር በውሰት አቅንቶ 16 ጨዋታዎች ካደረገ በኋላ ክለቡ ዝውውሩን ቋሚ ለማድረግ ፍላጎት አሳይቷል፡፡ ሆኖም የ26 ዓመቱ ዡሩ ከሀኖቨር ይልቅ የክለቡን ተፎካካሪ ሀምቡርግን መቀላቀል የመረጠ ሲሆን አዲሱ ክለቡም አሁን ዝውውሩ በውሰት ውል ተይዞ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ በቋሚነት ሊገዛው እንደሚችል ተስማምቷል፡፡ ይህም በመሀል ተከላካይ ቦታ የስዋንሲውን አሽሊ ዊልያምስ ለማስፈረም ያለውን ፍላጎት ያጠናከርለታል፡፡

የ2012/13 የውድድር ዘመንን በውሰት ውል በጁቬንቱስ ያሳለፈው ኒክላስ ቤንድትነርም በኤምሬትስ እህል ውሃው አልቋል፡፡ በገዛ ፈቃዱ ወደ አርሰናል እንደማይመለስ በትዕቢት ሲናገር የቆየውን ዴንማርካዊ ደጋፊዎቹ ማየት አይሹም፡፡ ባለፉት ቀናት በወጡ መረጃዎች መሰረት የጀርመኑ ኢንትራክት ፍራንክፈርት በግዙፉ አጥቂ ላይ ያለውን ፍላጎት አጠናክሯል፡፡ የተጫዋቹ ወኪል ቶም ብሩክስም ‹‹አሁን ብዙ ባልናገር እመርጣለሁ፡፡ ሆኖም ዝውውሩ በቀናት ውስጥ እውን እንደሚሆን ተስፋ አለኝ›› ሲል ጉዳዩ እያለቀ መሆኑን አብራርቷል፡፡

ቬንገር ለወቀሳ ያደረገው ሌላኛው የቅርብ ጊዜ ግዢ ፖርክ ቹ ያንግ ኤምሬትስን እስከመጨረሻው የመሰናበቱ ነገር እርግጥ ይመስላል፡፡ ባለፈው ሳምንት በወጡ መረጃዎች መሰረት ክለቡ በደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ የዜግነት ግዴታውን እየተወጣ ያለውን ተጨዋች ሊሸኝ ወስኗል፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በውሰት ለሴልታቪጎ የተሰጠው እና በአርሰናል የሁለት ዓመት ቆይታው በሊግ ካፕ ቦልተን ላይ የተቆጠረችን አንድ ጎል ብቻ ያስመዘገበው እስያዊ አርሰናልን ለኪሳራ ቢዳርግም በደመወዝ መልክ ሊወጣበት ይችል የነበረውን 5.5 ሚሊዮን ፓውንድ ያድናል፡፡ በዚህ ሀሳብ የተስማሙ የሚመስሉት የቆረጡ መስለዋል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ተሰናባቾች በተጨማሪ በክለቡ እንዲቆይ የማይፈለገው አንድሬ ሳንቶስም በቡድኑ የሚሰነብትበት ምክንያት የለም፡፡ በጁን አጋማሽ በውሰት ከቆየበት ሀገሩ ብራዚል ሲመለስ ቅር መሰኘቱን በይፋ የገለፀው ፉልባክ ምናልባትም ወደ ቱርክ ሊጓዝ እንደሚችል ተነግሯል፡፡

ሳንቶስ በ2011 6 ሚሊዮን ፓውንድ ወጥቶበት ከፌኔርባህቼ ከመጣ በኋላ ለክለቡ 25 ጨዋታዎች ቢያደርግም በደጋፊዎቹ ልብ የሚያቆየው መልካም ትዝታ አላተረፈም፡፡ በእርግጥም ሳንቶስ ከአርሰናል በውሰት ከመልቀቁም በላይ በብራዚል ለግማሽ የውድድር ዘመን የቆየው ግሬሚዩም ተጨዋቹን ለማስፈረም ብቁ ነው ብሎ አለመመልከቱ ተከላካዩ በጭራሽ ለእንግሊዙ ክለብ እንደማይመጥን ይጠቁማል፡፡ አሁንም በዝውውር ገበያው ሳንቶስ ፈላጊ ማጣቱ ቬንገርን ቅር አሰኝቷል፡፡

እነዚህ ተጨዋቾች አርሰናልን ምን ያህል እንደጎዱት መመልከት ከባድ አይደለም፡፡ ሆኖም አሰልጣኙ የማይጠቀሙባቸውን እና የተጠቀሱትን ተጨዋቾች ጨርሰው ከሸኙ እንዲሁም ከሰሞኑ ሌሎቹን እንደተጠበቁ ያልሆኑ ሁለት ተጨዋቾች (ማርዋን ሻማክ እና ዠርቪንሆ) ሸጠው ገንዘብ ካገኙ ትልቅ ስራ እንደሰሩ ይቆጠርላቸዋል፡፡

እንደ እንግሊዙ ዴይሊ ሜይል ዘገባ ከሆነ የስፔኑ ክለብ ሌቫንቴ ሞሮኳዊውን ለመግዛት 1 ሚሊዮን ፓውንድ ለመክፈል ፈቃደኛ ነው፡፡ በ2010 ከቦርዶ በነፃ አርሰናልን የተቀላቀለው አጥቂ በመጀመሪያዎቹ አራት ወራት 10 ጎሎች አስቆጥሮ ተስፋ ቢያጭርም በቀጣዮቹ ጊዜያት ችሎታውን ብቻ ሳይሆን በራስ መተማመኑንም ጨርሶ አጥቶታል፡፡ ተጨዋቹ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በውሰት ውል ለዌስትሀም ቢጫወትም ምንም ተፅዕኖ መፍጠር ሳይችል ወደ ኢምሬትስ ተመልሷል፡፡ የሻማክን የሌቫንቴ ዝውውር ሊያደናቅፍ የሚችለው በአርሰናል ሊያገኘው የነበረው 65 ሺ ፓውንድ ሳምንዊ ደመወዝ ቢሆንም አጥቂው ደመወዙን ለመቀነስ የሚስማማበት እድል አለው፡፡

የአርሰናል ደጋፊዎች በቅርቡ ሰምተው ከተደሰቱባቸው ዜናዎች መካከል የዠርቪንሆ በማርሴይ መፈለግ ይገኝበታል፡፡ የፈረንሳዩ ክለብ ኮትዲቯራዊውን ቀድሞ ይጫወትበት ወደነበረው ሊግ ሊመልሰው ተዘጋጅቷል፡፡ ዠርቪንሆ በ2011 ከሊል ከመጣ በኋላ በአርሰናል ወጥ የሆነ አሳማኝ ብቃት ማሳየት እና ተመልካቾቹን ማሳን አቅቶታል፡፡ አርሰናል ከሁለት ዓመት በፊት 11 ሚሊዮን ፓውንድ የከፈለበት እና በ63 ጨዋታዎች 11 ጎሎች ያስቆጠረለትን አፍሪካዊ በኪሳራ ሊያጣው ፍላጎት ያለው ይመስላል፡፡

የ26 ዓመቱ ተጨዋች ከማርሴይ በተጨማሪ በቱርኩ ፌኔርባህቼ ቢፈለግም የፈረንሳዩ ክለብ ከሰሜን ለንደኑ ክለብ ጋር ድርድር ለመጀመር ቅድሚያውን ወስዷል፡፡

አርሰናል በክረምቱ ከዡሩ፣ ስኩዊላቺ፣ አርሻቪን፣ ዴኒልሰን እና ማኖኒ በተጨማሪ ቤንድትነር፣ ሻማክ፣ ፓርክ፣ ሳንቶስ፣ ባካሪ ሳኛ እና ፋቢያንስኪን ካሰናበተ በየሳምንቱ ወደ 700 ሺ ፓውንድ የሚጠጋ የደመወዝ ወጪ ያድናል፡፡ ይህ በዓመት ወደ 31 ሚሊዮን ፓውንድ ይጠጋል፡፡ ይህ ገንዘብ በአቡኑ የዌይን ሩኒ የማንቸስተር ዩናይትድ ደመወዝ እርሱን መሰል ሶስት ትልልቅ ተጨዋቾችን የዓመት ደመወዝ ይከፍላል፡፡ ተጨዋቾቹ መጠነኛ በሚባል ገንዘብ ቢሸጡ ደግሞ በግምት በድምሩ እስከ 28 ሚሊዮን ፓውንድ ያስገኛሉ፡፡ ይህ ገንዘብ ሩኒን ለመግዛት በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ በአጠቃላይ የሽያጩ እና የደመወዝ መጪው ለአርሰናል ሶስት ወይም ትልልቅ ተጨዋቾችን ገዝቶ ክለቡን ለዋንጫ እንዲፎካከር ያስችላል፡፡

የእንግሊዝ ጋዜጦች ቬንገር ለዝውውር 70 ሚሊዮን ፓውንድ እንደተፈቀደላቸው መዘገባቸውን ቀጥለዋል፡፡ ባለፉት ዓመታትም እንደዚሁ አርሰናል የተሻለ የዝውውር ገበያ እንደሚያሳልፍ እየተነገረ በዋዛ ያለፉ ጊዜያት ነበሩ፡፡ በእርግጥም ሰውየው የተባለው በጀት ካላቸው እና የማይጠቅሙ ተጨዋቾቻቸውን ሸኝተው ገንዘብ ማትረፍ ከቻሉ አርሰናልን ወደ አደገኛ ተፎካካሪነት ለመለወጥ አቅም ያገኛሉ፡፡

ሆኖም አርሰናል ተጨባጭ የገንዘብ ምንጭ አለው፡፡ ከፑማ ጋር ለአምስት ዓመት ከተፈራረመው ሪከርድ የትጥቅ ማቅረብ ስፖንሰርሺፕ ውል 170 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያገኝ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 20 ሚሊዮን ፓውንዱ በቅድሚያ ተከፍሎታል፡፡ በተጨማሪም ከኢምሬትስ አየር መንገድ ጋር ለአምስት ዓመት የፈረመው 150 ሚሊዮን ፓውንድ ትልቅ ገንዘብ አስገኝቶለታል፡፡ የስታዲየሙ ግንባታ ዕዳ በእጅጉ መቀነሱ ከግምት ሲገባ ቬንገር ለዝውውር በቂ ገንዘብ እንዳገኘ መገመት አሳማኝ ነው፡፡

ጋዜጦች ስለሚያወሩት የ70 ሚሊዮን ፓውንድ በጀት ማረጋገጫ ባይገኝ እንኳን ክለቡ ከተጨዋቾች ሽያጭ 28 ሚሊዮን ፓውንድ እና ከፑማ ቅድመ ክፍያ 20 ሚሊዮን ፓውንድ መቀበሉን ለተመለከተ በዚህ ክረምት ቢያንስ ቬንገር የዚህን ገንዘብ ድምር እንደሚያወጡ መጠበቅ ስህተት የለውም፡፡

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>