Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በሙስና የተጠረጠሩት የደብረ ጽጌ ቅ/ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ዋና ጸሐፊ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋሉ

$
0
0

ሐራ ተዋሕዶ ብሎግ እንደዘገበው፦

  • በተጭበረበረ ውል ደብሩን ከ3 ሚልዮን ብር በላይ በማሳጣትና ሰነድ በማሸሽ ይጠየቃሉ
  • ከጥቂት የሙዳይ ምጽዋት ገቢ ምርመራ ብቻ ከ2 ሚልዮን ብር በላይ ጉድለት ተገኝቷል
  • የአብዛኛዎቹ የደብሩ ሕንጻ ሱቆች የኪራይ ውል በትክክለኛ ሰነድ የተፈጸመ አይደለም
  • ለማተሚያ ቤት አገልግሎት በተከራየው ክፍል በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የማይታወቅ ሞዴላሞዴል እንደሚታተምበት ተጠቁሟል
  • የፕሮቴስታንት ቤተ ጸሎት እንደሚያዘወትሩ የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋ

 

musnaበአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ዋና ጸሐፊ ዲያቆን ምሩፅ ትኵዕ በተጭበረበረ ሰነድ ከተፈጸመ የኪራይ ውልእና ለሒሳብ ምርመራ የሚፈለጉ የሙዳይ ምጽዋት የገንዘብ ቆጠራ ቃለ ጉባኤዎችን ከማሸሽ የሙስና ወንጀል ጋራ በተያያዘ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ፡፡

ዋና ጸሐፊው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ ሐምሌ ፲፪ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ረፋድ ላይ በደብሩ ጽ/ቤት ባሉበት ሲኾን ከዋና ጸሐፊው ጋራ በተጭበረበረው የኪራይ ሰነድና ውል ለደብሩ የሚገባውን ክፍያ ሳይፈጽሙ የግል ጥቅማቸውን አካብተዋል የተባሉ ሌሎች ሁለት የሕንጻው የንግድ ቤቶች ተከራዮችም በተመሳሳይ ቀን መያዛቸው ተመልክቷል፡፡

በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ቀን ጀምሮ በቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙት ዋና ጸሐፊው ዲያቆን ምሩፅ እና ሁለቱ ተጠርጣሪዎች፣ ሐምሌ ፲፮ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት መቅረባቸው ተገልጧል፡፡

ዋና ጸሐፊውና የጥቅም ተባባሪዎቻቸው ፈጽመውታል የተባለውን ማጭበርበርና ምዝበራ  የሚያረጋግጡ የሰነድ ማስረጃዎችና የሰው ምስክሮች እንዳሉት ለችሎቱ የገለጸው ፖሊስ፣ በዋና ጸሐፊው ላይ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብና የሰው ምስክሮችን ለማዘጋጀት የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ያቀረበችባቸው ክሥ እንደሌለና ከሣሻቸው እንደማይታወቅ በመጥቀስ የፖሊስን የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ በጠበቃቸው በኩል የተቃወሙት ዲያቆን ምሩፅ÷ የሰባት ቤተሰብ አስተዳዳሪ መኾናቸውን፣ የሚጠየቁትን ማስረጃ ቤተሰቦቻቸው እያቀረቡ መኾኑን፣ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሲውሉ ቢሯቸውን ለመዝጋት እንዳልተፈቀደላቸው እና ሐምሌ ፳፪ ቀን በደብሩ የቅዱስ ዑራኤል ክብረ በዓል በመኾኑ ሥራዎች እንዳይስተጓጎሉ በመጥቀስ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ጉዳያቸውን በውጭ መከታተል እንዲችሉ እንዲፈቀድላቸው አመልክተዋል፡፡ ዮሐንስ አይዳኝ እና ዓለም ፍሥሓ የተባሉት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው፣ እነርሱ ውል የያዙበት ሰነድ ከሌሎች ተከራዮች የተለየ እንዳልኾነ በመጥቀስ የዋስ መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡

የደብሩን ሕንጻ አራት የንግድ ሱቆች በተጭበረበረ ሰነድ በተፈጸመ የኪራይ ውል በመያዝ ሕገ ወጥ ጥቅም ሲያካብቱ ቆይተዋል ከተባሉት ሁለት ተጠርጣሪዎች ተፈላጊውን ማስረጃ መሰብሰቡን የገለጸው ፖሊስ÷ ተጠርጣሪዎቹ ለምርመራ ሥራው ጠቃሚ ማስረጃዎችን በመስጠት አደርገውታል ባለው መተባበር በዋስ ተለቀው በውጭ ኾነው ጉዳያቸውን መከታተላቸውን እንደማይቃወም፣ ዋና ጸሐፊው ዲያቆን ምሩፅ ግን የደብሩ ጽ/ቤት ሓላፊ በመኾናቸው በተለይ ከሒሳብ ምርመራ እንዳሸሿቸው የሚገመቱት የሙዳይ ምጽዋት ገንዘብ ቆጠራ ቃለ ጉባኤዎችእስኪገኙ ድረስ ‹‹ማስረጃ ያጠፋሉ፤ ምስክር ያባብላሉ›› በሚል የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሟል፡፡

ዮሐንስ አይዳኝና ዓለም ፍሥሓ የተባሉት ተከራዮች በብር 50 ሺሕ ዋስ እንዲለቀቁ ያዘዘው ፍ/ቤቱ፣ የዲያቆን ምሩፅን የዋስትና ማመልከቻ ውድቅ በማድረግና የፖሊስን የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጥያቄ በመቀበል ተጠርጣሪው ለሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም እንዲቀርቡ ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል፡፡

በቀደመው ዘገባችን እንዳስታውቅነው÷ ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት እና ከመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የተውጣጡ ልኡካንበደብሩ የፋይናንስ እንቅስቃሴና አሠራር ላይ ምርመራ እያካሄዱ ባሉበት ኹኔታ የደብሩ ዋና ጸሐፊ ዲያቆን ምሩፅ ትኵዕ በቁጥጥር ሥር የዋሉት፣ ከሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለፖሊስ በቀረበ ጥያቄ እንደኾነ ሲዘገብ፣ ይህም ዲያቆን ምሩፅ በጋብቻ ሰበብ ከአገር ለመውጣት እየተሰናዱ ለመኾናቸው ከመሰማቱ ጋራ ሳይያዝ እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡

St Urael Church YeHulegeb Agelgelot Hintsa

የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ሁለገብ ሕንጸ

ሐራዊ ምንጮች ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የደብሩ አካላት ለአብነት ካቀረቧቸው ማስረጃዎች እንደተረዱት፣ ዲያቆን ምሩፅ ከሁለቱ ተጠርጣሪ ተከራዮች ጋራ የተጭበረበረ የኪራይ ውል የፈጸሙት ነሐሴ ፳፬ ቀን ፳፻፫ ዓ.ም እና መስከረም ፲፭ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ነበር፡፡ በቤት ቁጥር 43 የተለየው የደብሩ ሁለገብ ሕንጻ ክፍል ለአኒሜሽንና ግራፊክስ ቴክኖሎጂ ማሠልጠኛ፣ በቤት ቁጥር 27 እና ቨረንዳ ቁጥር 4 የተለዩት የሕንጻው ክፍሎች ደግሞ ለዓለም ጠቅላላ ፋይበር ግላስ ሓላ/የተ/የግ/ማ ተከራይተዋል፡፡

ለአራት ዓመት የሚቆየው የኪራይ ውል የተፈጸመበት ሰነድ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ በኪራይ ውል አሰጣጥ/ውል ማራዘሚያ ከሚጠቀምበት ሕጋዊ ሰነድ የተለየና የውል መለያ ቁጥር የሌለው ነው፡፡ በሰነዱ ላይ የሚታየው ክብ ማኅተም የደብሩ ቢኾንም ቲተሩና ፊርማው ግን ውሉ ከመፈጸሙ በፊት ከአስተዳዳሪነት ሓላፊነታቸው የተነሡትና ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቀድሞው የደብሩ አለቃ ነው፡፡

ኹኔታው የበለጠ ሊከፋ÷ እኒህ ሁለት ተከራዮች የደብሩ ሰበካ ጉባኤ የአካባቢውን የኪራይ ዋጋ ባማከለ አኳኋን በአዲስ መልክ ባስጠናው የኪራይ ተመንና አዲስ የውል ሰነድ መሠረት ውል እንዲያድሱ፣ በዚህ አግባብ የማይዋዋሉ ከኾነ ደግሞ ያለባቸውን ውዝፍ ዕዳ አጠናቅቀው የንግድ ቤቱን ለደብሩ እንዲያስረክቡ በወቅቱ አስተዳዳሪ በቆሞስ ፀባቴ መሓሪ ሀብቴ መጋቢት ፴ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ደርሷቸው የነበረ መኾኑ ነው፡፡ ‹‹ማስጠንቀቂያ በክቡር ቆሞስ ፀባቴ መሓሪ ሀብቴ ውል ደግሞ በአባ ተስፋ ማርያም መከናወኑ ግልጽ ጥፋት መኖሩን ያሳያል፤›› ይላል የኪራይ ውሎቹን አፈጻጸም ስሕተት ያጠናው የሰበካ ጉባኤው መንፈሳዊ አስተዳደር ያቋቋመው ኮሚቴ ያቀረበው ሪፖርት፡፡

ከተከራዮች ጋራ የጥቅም ተካፋይ በመኾን የተፈጸሙት የኪራይ ውሎች በሐሰተኛ ሰነድ መስጠታቸው የተረጋገጠባቸው ዋና ጸሐፊውና የቀድሞው የደብሩ ዋና ተቆጣጣሪ በሰበካ ጉባኤው ፊት ጥፋተኝነታቸውን አምነው ይቅርታ መጠየቃቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የይቅርታ ቤት ብትኾንም፡- የደብሩን ንብረትና የኪራይ ውሎች እየተከታተሉ ጥቅሙን ማስጠበቅ የሚገባቸው ዋናው ተቆጣጣሪ የተጭበረበረው ውል አዘጋጅና ምስክር በመኾን በፈጸሙት ጥፋት የአንድ ወር ደመወዛቸውን እንዲቀጡ፣ ሀ/ስብከቱም በዋና ጸሐፊው እና ዋና ተቆጣጣሪው ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወስድ፣ ተከራዮቹም በ30 ቀን ገደብ ውላቸው ተቋርጦና የሚፈለግባቸውን ውዝፍ ዕዳ ከፍለው ሱቆቹን እንዲያስረክቡት ጥር ፳፫ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም የደብሩ የሕግ ባለሞያ ባለበት በድጋሚ ተወስኖ እንደነበር ሪፖርቱ ያትታል፡፡

ይኹንና ዋናው ተቆጣጣሪ የተወሰነባቸው ቅጣት ሳይፈጸም ከነበደላቸው ወደ ሌላ ደብር በተመሳሳይ ሓላፊነት መዛወራቸውን፣ ተከራዮቹም አለመልቀቃቸውን ሪፖርቱ ገልጾ በዚህም ደብሩ በአዲስ መልክ ባስጠናው የኪራይ ተመን መሠረት ቢያንስ ከሚያዝያ ፳፻፬ ዓ.ም ጀምሮ ማግኘት የሚገባውን ከብር 2,637,603.30 /ብር ሁለት ሚልዮን ስድስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺሕ ስድስት መቶ ሦስት ከሠላሳ ሳንቲም/ ማጣቱን አስታውቋል፡፡

የቀድሞው የምሥራቅ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት በፋይናንስ አሠራርና በሕንጻው ኪራይ ዙሪያ ተፈጸመ የተባለውን ምዝበራ አጣርተው የሚያቀርቡ ልኡካንን ከአንድም ሁለት ጊዜ ልኮ የነበረ ቢኾንም ለማጣራቱ ሥራ ግንባር ቀደም ተባባሪ መኾን የነበረባቸው ዋና ጸሐፊው ዲያቆን ምሩፅ የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ ለማጣራቱ ሥራ ተባባሪ አልኾኑም፡፡ ዋና ጸሐፊው ለተመደቡት አጣሪዎች እንዲያቀርቡ ከተፈለጉት ማስረጃዎች መካከል፣ ከሐምሌ ፳፻፫ ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የሚገኘው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የያዛቸው የ22 ወራት 44 የሙዳይ ምጽዋት ቆጠራ ቃለ ጉባኤዎች/ቬርቫሎች/ ይገኙበታል፡፡

ዲያቆን ምሩፅ በሚያቀርቡት ‹‹ሕጋዊ እና በቂ ያልኾነ›› ምክንያት መጥፋታቸው ተገለጹት በእኒህ 44 የገንዘብ ቆጠራ ቃለ ጉባኤዎች መሠረት፣ ደብሩ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ  በመባዕ፣ ስእለት፣ በወርቅና በውጭ ምንዛሪ የተሰበሰበውን ሳይጨምር ከብር 12 ሚልዮን ብር ያላነሰ የሙዳይ ምጽዋት ገቢ ሊኖረው ይገባ ነበር፡፡ ለሐራዊ ምንጮች የደረሱት መረጃዎች ግን ደብሩ በአሁኑ ወቅት በባንክ ያለው ተቀማጭከብር 5 ሚልዮን የበለ እንዳልኾነ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ከዚሁ ብር 5 ሚልዮን ውስጥም 3.5 ሚልዮን ብሩ ካለፈው የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር የዞረ ነው፡፡ ይህም በወቅቱ የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ወደ ደብሩ ካዝና የገባው የሙዳይ ምጽዋት ገቢ ከ1.5 ሚልዮን ያለፈ እንዳልኾነ ያስረዳል፡፡

የሙዳይ ምጽዋቱ ገቢ ከሕንጻው ኪራይ እና ሌሎች የደብሩ የገቢ ምንጮች ጋራ ተደማምሮ በአጥቢያው ቋት መኖር ከነበረበት ሒሳብ ጋራ ሲነጻጸር በተጨባጭ ያለው መጠን በማነሱ የተደናገጡ የሰበካ ጉባኤ አባላት ተቆርቋሪ ምእመናንን በማስተባበር ለሀ/ስብከቱ አቤቱታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡ አቤቱታቸው በብዙ ጥረት ሠምሮ ከሀ/ስብከቱ እና ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተውጣጥቶ ወደ ደብሩ የተላከው መርማሪ ልኡክ የማጣራቱን ሥራ እየሠራ ይገኛል፤ ‹‹ያለቃለ ጉባኤ አንመረመርም›› በሚል ለተጠያቂነት ያስቸገሩት ዋና ጸሐፊው ዲያቆን ምሩፅም በሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጥያቄ በሕግ ጥላ ሥር ውለዋል፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት የሒሳብ ምርመራ ሥራቸውን የጀመሩት የሀ/ስብከቱ ልኡካን እስከ አሁን ባደረጉት ማጣራት ከሚፈለጉት 42 የገንዘብ ቆጠራ ቃለ ጉባኤዎች 14ቱን አግኝተዋል፤ ከዚህም ተቀባይነት ያገኙት ስድስት ቃለ ጉባኤዎች ብቻ ሲኾኑ ሌሎቹ የተጭበረበሩና በማስመሰል የተዘጋጁ መኾናቸው ታውቋል፤ መርማሪ ልኡኩ በስድስቱ ቃለ ጉባኤዎች ላይ ብቻ ተመሥርቶ ባደረገው ማጣራት ከብር 2.7 ሚልዮን በላይ የገቢ ልዩነት/ጉድለት እንደተመዘገበ መገለጹ የሰበካ ጉባኤውን አባላት አቤቱታ የሚያጠናክር እንደኾነ ተመልክቷል፡፡ የሙዳይ ምጽዋት ገንዘብ ከተቆጠረና አጠቃላይ ገቢው ከታወቀ በኋላ ወደ ሞዴል ፷፬ እንዲሰፍር ተደርጎ በገንዘብ ያዡ አማካይነት በሞዴል ፮  ተጠይቆ ወደ ባንክ ገቢ እንደሚደረግ ይታወቃል፡፡

the alleged underground printing house

ሞዴላሞዴሎች በድብቅ ይታተሙበታል የሚባለው ማተሚያ ቤት

የደብሩ ሰበካ አስተዳደር ጉባኤ የተጭበረበረውን የኪራይ ውል እንዲያጣራ ያቋቋመው ኮሚቴ ከዘረዘራቸው የውል አሰጣጥ ችግሮች መካከል÷የውል ጊዜያቸው አልቆ በአዲሱ ውል ያልገቡ፣ ፈጽሞ ውል የሌላቸውና ኪራይ የማይከፍሉ፣ በውላቸው የጊዜ ገደብ ያልተቀመጠላቸውና ያልታደሰላቸው፣ ውል ኖሯቸው ክፍያ የማይፈጽሙ /ውዝፍ ያለባቸው/ እንዳሉ መጠቀሳቸው በመርማሪ ልኡኩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብታቸው ለማስጠበቅ ለፍ/ቤቱ ሲናገሩ እንደተደመጡት፣ ከ40 ያላነሱት የሁለገብ ሕንጻው ክፍሎች የኪራይ ውል ሰነዶች እነርሱ ውል ከያዙበት ሰነድ ጋራ ተመሳሳይ ስለመኾኑ የተናገሩት ቃል ቸል ሊባል አይገባም፡፡

ከሁለቱ ተጠርጣሪ ተከራዮች አንዱ ለማተሚያ ቤት አገልግሎት በተከራዩት ክፍል፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቤተ ክርስቲያንን ንብረትና ገንዘብ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠርባቸው ሞዴላሞዴሎች በድብቅ እንደሚታተሙባቸው በስፋት እየተወራ ነው፡፡ የምስጢር ኅትመት የኾኑት እኒህ ሞዴላሞዴሎች ግን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ቁጥጥር በትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ብቻ መታተም ያለባቸው ናቸው፡፡ እንደ አንዳንድ ምንጮች ጥቆማ ከኾነ ይህ ክፍል ‹‹ሞዴል ፴ እንደማያውቀው››ና ጨርሶ ኪራይ እንደማይከፈልበት መነገሩ ያሳስባል፡፡ የሀ/ስብከቱ ልኡክ የሒሳብ ምርመራ ሥራ ይህን ጉዳይ በሚገባ እንደሚዳስስ ይጠበቃል፡፡

በአጠቃላይ በገቢ አቅሙና ደረጃው ከሀ/ስብከቱ ዐበይት አድባራት በቀዳሚነት በሚጠቀሰው በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የፋይናንስ እንቅስቃሴ ላይ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የወሰደው ርምጃ በሀ/ስብከቱና በሌሎች አድባራት ለተንሰራፉት ሙሰኞች/መዝባሪዎች መልእክት የሚያስተላልፍና እንደ አገባቡም የሕግ ተጠያቂነቱ መቀጠል ያለበት ነው፡፡

በሌላ በኩል ከሚያዝያ ፳፻፫ ዓ.ም ጀምሮ የደብሩ ዋና ጸሐፊ በመኾን ተዛውረው የመጡት ዲያቆን ምሩፅ በአዋሬ አካባቢ የሚገኝና ‹‹ብርሃነ ኢትዮጵያ›› ተብሎ የሚጠራ የፕሮቴስታንት ቤተ ጸሎት እንደሚያዘወትሩ ለሐራዊ ምንጮች ተያይዞ ከደረሰው የቪሲዲ ማስረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በቪሲዲው ‹ዲያቆን› ምሩፅ በቤተ ጸሎቱ ከተሰበሰቡት ሰዎች ጋራ ቆመው ‹ሲዘምሩ› ይታያል – ከቤተ ክርስቲያን እየጎረሱ ወደ መናፍቃን መዋጥ፡፡ የዲያቆን ምሩፅን በለምድ የተሸፈነ ፕሮቴስታንታዊነት የሚያጋልጠው ቪሲዲ የሚሰጠን ፍንጭ አዘውትረን እንደምንለው በቤተ ክህነታችን ውስጥ ሙስናና ኑፋቄ ያላቸውን ትስስር ነው፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>