ከመለስ ሞት በሁዋላ ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ከሌኒን ሞት በሁዋላ የነበረውን የሩስያ ሁኔታ ያስታውሰኛል። ሌኒን በቦልሼቪክ ፓርቲ ውስጥ የገዘፈ ስም ነበረው፣ በፓርቲው ውስጥ ያሰፈነው የዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነት አሰራር የምእራቡን ዲሞክራሲን ለማይቀበለው የኮሚኒስት ታጋይ ሁሉ የሚመች ነበር ፤ በዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነት መርህ መሰረት ማንም የድርጅቱ አባል የሆነ ሰው እንደልቡ መናገር ይፈቀድለታል፣ ውሳኔ ከተላለፈ በሁዋላ ግና ውሳኔውን ያለምንም ማቅማማት ይተገብራል። ሌኒን ሲሞት የሌኒንን ቦታ ለመያዝ ይቋምጥ የነበረው ስታሊን የመጀመሪያ እቅዱ ይህን የዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነትን አሰራር ማፍረስ ነበር። ስታሊን ተናግሮ የማሳመን ወይም አዳዲስ ሃሳቦችን የማፍለቅ ስጦታ ወይም ችሎታ አልነበረውም። ትሮትስኪን የመሳሰሉ፣ ከስታሊን የተሻለ አስተሳሰብ እና ብቃት የነበራቸው፣ ሰዎች የዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነትን አሰራር ተጠቅመው ወደ ስልጣን የሚመጡበት እድል ከፍተኛ ነበር፤ ስታሊን ይህንን አሰራር ካላስቆመው በስተቀር በክርክር የመሪነቱን ስልጣን ሊይዝ የሚችልበት እድል አልነበረውም፣ አፈረሰው።
ዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነትን ማፍረስ ብቻውን ለስታሊን በስልጣን ላይ መቆየት ዋስታና የማይሰጥ በመሆኑ ስታሊን የፓርቲውን መስራችና የአብዮቱ መሪ የነበረውን የሟቹን የሌኒንን ስም ለመጠቀም ወሰነ። የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ሌኒን የተለየ ፍጥረት እንደነበር እንዲሰብኩ አዘዘ፣ ዜና መክፈቻና መዝጊያው ሁሉ “በሌኒን ራእይ” የታጀበ ሆነ። ጎዳናው ሌኒን፣ ካፌው ሌኒን.. ሆስፒታሉ ሌኒን፣ መጸዳጃው ሌኒን፣ ሌኒን.. ሌኒን… ሌኒን… እነትሮትስኪ በሌኒን ሙት መንፈስ መነገዱ እንዲበቃ ቢወተውቱም ለእነስታሊን የሚያሳምን አልሆነም፣ እንዲያውም ሌኒን ወደ “ሌኒኒዝምነት” ከፍ አለ…። ስታሊን የሌኒን የሙት መንፈስ ብቻውን ለረጅም ጊዜ በስልጣን ላይ እንደማያኖረው የተገለጠት ዘግይቶ ነበር፤ ይህ መገለጥ እንደታየው ወዲያውኑ ተቃዋሚዎችን አንድ በአንድ ጨረሳቸው።
ከዚህ በሁዋላ ስታሊን አስገራሚ የሆነ የ5 አመታት የኢኮኖሚ እቅድ ነደፈ፣ አገሪቱን በከባድ ኢንዱስትሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ( 10 አመታት) ከምእራባዊያን ጎን እንደሚያሰልፋት ቃል ገባ ። ይህንን የሚቃወሙ ፖለቲከኞች ” ከሀዲዎች፣ ጸረ ልማት ሀይሎች” ተባሉ፤በመጀመሪያዎቹ 5 አመታት የስታሊን እቅድ ተሳካ። የአገሪቱ እንዱስትሪ በ2 አመታት ውስጥ በ300 ፐርሰንት አደገ ፤ ግብርናውም እንዲሁ ተመነደገ። ብዙም ሳይሄድ ነገሮች መቆም ጀመሩ፣ በተለያዩ ምክንያቶች። ከእነ አሜሪካ ቀድማ መንኮራኩር ( ስፑትኒክ) ለመጀመሪያ ጊዜ ያመጠቀችው ሩስያ ከ70 አመታት የተወለካከፈ ጉዞ በሁዋላ ተንገራግጫ ቆመች፤ ቆመች ብቻ አይደለም በማፊያዎች ተዘረፈች።
መለስ ዜናዊ ተቀናቃኞቹን ካስወገደ በሁዋላ የዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነትን አሰራር አሽመደመደው ( እነስየን ማለቴ ነው)፣ መድረክ አዘጋጅ፣ ተናጋሪ፣ ወሳኝ መለስ ብቻ ሆነ። ተቀናቃኝን ማጥፋት ብቻውን በስልጣን ላይ የመቆየት እድሜን አያረጋግጥምና መለስም እንደስታሊን የ5 አመታት የትራንስፎርሜሽን ረቂቅ መዝሙር ቀምሞ ብቅ አለ፣ ውጤቱን ሳያይም በድንገት አረፈ፣ እነሆ ኢህአዴግም በተራው የመለስን ራእይ አስፈጽማለሁ ብሎ ተነሳ ፤ የአንዱ ሞት ለሌላው የስልጣን ማራዘሚያ መቅስቀሻ በሚሆንበት ስታሊናዊ አሰራር መሰረት ፓርቲው መለስ ካለፈበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ “መለስ መለስ” ማለቱ ለራሱም እንኳ የሰለቸው አይመስልም፣ መቼ እንደሚያቆምም እግዚአብሄር ይወቅ።
የሌኒን የሙት መንፈስ ስታሊንን ረጅም ርቅት እንዳልወሰደው ሁሉ፣ የመለስም ሞት ኢህአዴግን ረጅም ርቀት አይወስደውም፤ ከተወሰኑ አመታት በሁዋላ መለስም ይረሳል( እስካሁንም ካልተረሳ ነው)። በመለስ መረሳት ጭንቀት ውስጥ የሚገባው ኢህአዴግ ምናልባትም ስታሊን ተቃዋሚዎቹን ለማጥፋት በሄደበት መንገድ ሊሄድ ይችላል፣ አዝማሚያውም ወደዛው ነው።
በመጨረሻም፣ የኢህአዴግ የ 5 አመታት የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን ፖሊስ ከስታሊን የመጀመሪያዎቹ የ5 አመታት የእድገት ፖሊሲ ጋር በብዙ ነገሮች ይመሳሰላል፤ የመመሳሰሉ ብዛት ደግሞ አወዳደቁንም እንዳይ ረድቶኛል፣ እግዜር ቢፈቅድ አንድ ቀን እመለስበታለሁ።
↧
ለመለስ ሙት አመት ማስታወሻ (ከፋሲል የኔአለም) ጋዜጠኛ
↧