ዛሬ 12 ሰዓት የጀመረው ምርጫ በወከባ ተጀምሯል፡፡ ኢህአዴግ ካድሬዎች መራጮቹን በመጠርነፍ እንዲመርጡ እያስገደዱ እንደሆነ አዲስ አበባ ውስጥ ከምርጫ ጣቢያ 03 የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ በዚሁ ምርጫ ጣቢያ የሰማያዊ ፓርቲ ታዛቢዎች እንዳይገቡ ታግደው በማርፈዳቸው ወረቀት ሳይቆጠር ምርጫው ተጀምሯል፡፡ በተመሳሳይ በወረዳ 15 ምርጫ ጣቢያ የሰማያዊ ፓርቲ ታዛቢዎች ‹‹አትገቡም!›› ተብለው ወከባ እንደደረሰባቸው የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ የሆኑት አቶ ተገኔ ጌታነህ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ወረዳ 6 ምርጫ ጣቢያ 20 መራጮች ጣት ላይ የሚደረገው መርገጫ ቀለም የሚለቅ እንደሆነ ታውቋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ታዛቢዎች ቀለሙ የሚለቅ መሆኑን ገልጸው ቃለ ጉባኤ እንዲያዝላቸው ቢጠይቁም የምርጫ አስፈጻሚዎቹ ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች የሰማያዊ ፓርቲ ታዛቢዎች በገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ደህንነቶች ወከባ እየደረሰባቸው እንደሚገኝና አንዳንዶቹ በወከባው ምክንያት በቦታው አለመገኘታቸውን ዕጩዎቹ ገልጸውልናል፡፡
ሲዳማ ቦርቻ ወረዳ ደግሞ 26 የሰማያዊ ፓርቲ ታዛቢዎች ታስረው የታዛቢነት መታወቂያቸውን እየመለሱ ሲለቀቁ፣ ሶስቱ መታወቂያን አልመልስም በማለታቸው አሁንም እንደታሰሩ ናቸው፡፡ በጉራጌ ዞን የም ልዩ ወረዳ ደግሞ 48 የሰማያዊ ታዛቢዎች በቁም እስር ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡
The post 48 የምርጫ ታዛቢዎች በቁም እስር ላይ ናቸው * 26 ታዛቢዎች ታስረው የታዛቢነት መታወቂያቸውን መለሱ appeared first on Zehabesha Amharic.