ከኢብራሒም ሻፊ
ከ10 ዓመታት በፊት ምርጫ ሲከወን አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ከአራት ዓመታት በፊት “በስብሰዋል” ብሎ ስላሰናበታቸው የትግል ግዜ ወዳጆቹ እና ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ ስለተፈጠረው የሰላም ድርድር እንዲሁም የፍትህ ሂደት እንጂ ምንም ያሰበው ነገር አልነበረም፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተገኝቶም ለሰበሰባቸው ምሁራን “ቀጣዩ ምርጫ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ ይሆናል፤ ለዚህም ቃል እገባለሁ” ሲል ምን ይመጣብኛል አላለም፡፡ የትግል ወዳጁ ገብሩ አስራት “ሉዓላዊነት እና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ” በሚለው መፅሐፋቸው ይህን በሚገባ ተረድተውት “የኢህአዴግ ተሃድሶ ተግባራዊ ይሆናል ብለው ተስፋ ያደረጉ በርካታ የአዲስ አበባ እና የሌሎች ዩኒቨርስቲ የቀድሞ እና የወቅቱ ምሁራን ወደ ምርጫው መጡ” በማለት በጥልቀት ያላሰበበት አምባገነኑ መለስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ስርነቀል ለውጥ ሊፈጥሩ የሚችሉ ሰዎችን ወደ ፖለቲካዊ ምህዳሩ ጋብዞ እንደነበር ያወሳሉ፡፡
በወቅቱ አምባገነኑ መለስ እንዳሰበው የምርጫ ውይይቱ እና ክርክሩ ከስርዐቱ መበስበስ እና መታደስ ጋር የተያያዘ አልነበረም፡፡ ስለ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መዘዞች፣ውጤት እና የፍትሕ ሂደትም ብዙ አልተነሳም፡፡ በቁንፅል በመገናኛ ብዙሐን ስለሚወሳው ሙስና እና ስርዐቱ ሙስናን ለማስወገድ በቁርጠኝነት አለመንቀሳቀሱ ላይም ብዙ አላጠነጠነም….ውይይቱ…..ክርክሩ፡፡ ይልቅ መንግስት ያልተዘጋጀባቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አፍጠው መጡ፣ የኢኮኖሚ ችግሩ ተነሳ፣ ችጋሩ እና ድህነቱ ተወሳ፤ የሀይማኖት ነፃነት ጥያቄዎች በረድፍ ይቀርቡ ጀመር፣ የኢትዮጵያን አንድነት የነቀነቀው “በልዩነት አንድነት” የኢህአዴግ ፖሊሲ ብዙ ጥያቄዎችን አንግቦ ብቅ አለ፡፡ ኦሮሞው የታለ የኢኮኖሚ እኩልነቱ የሚል ጥያቄን ሲያነሳ፣ አማራው እስካዛን ወቅት ለምን ነፍጠኛ እና የቀድሞ ገዢ መደቦች አካል ተደርጎ እንደሚወሰድ መጠየቅ ጀመረ፡፡ መንግስት ምሁራንን ከፊታቸው አድርገው ባልተዘጋጀበት ጥያቄ ያጣደፉትን ተፎካካሪ ፓርቲዎችን “ኢንተርሀሞይ” የሚል ኃይለ ቃልን ጭምር ተጠቅሞ ቢያስፈራራም ጥያቄው ገፋ፡፡ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ድጋፍ በአዲስ አበባ የወጣው ህዝብም ኢህአዴግ በምርጫው ተሸናፊ ሊሆን እንደሚችል የቅድሚያ ምስክርነትን ሰጠ፡፡ ስለዚህም አምባገነኑ መለስ ሊያሸንፍበት የሚችለውን አንድ ነገር ከምርጫው በኋላ ተጠቀመ፡፡ ህፃናትን ጭምር በጥይት አስደብድቦ ገደለ፣ ህዘብን በገፍ አሰረ፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን አመራሮችን ወህኒ ወረወረ፣ ጋዜጠኞችን እስር ቤት አጎረ፣ አሰደደ እንዲሁም እንዲዘጉ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡
ህዝብ በፍርሃት በተወጠረበት እና ነፍስ ውጪ፣ ነፍስ ግቢ በሚባልበት በዚያው ዓመት አምባገነኑ መለስ የስልጣን ዕድሜውን ማራዛሚያ ቀመርን ይቀምም ጀመር፡፡ አምሳያ አምባገነን ሀገራት እንዴት ስልጣን ላይ ረጅም እድሜን አስቆጠሩ? በተለይ የቻይናው ኮሚዩኒስት ፓርቲ ይህን ሁሉ ዘመን አንዴት ስልጣን ላይ መቆየት ቻለ? ብሎም የኩረጃ ፖለቲካውን ጀመረ፡፡ የበጎ አድራጎት ማህበራት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ህግ ወጣ፡፡ በርካታ ለእርዳታ፣ ፍትህ፣ ዲሞክራሲ፣ እኩልነት እና ሰብዐዊነት የቆሙ ተቋማት ተዘጉ ………ከኢትዮጵያም ተሰናበቱ፡፡ የፀረ-ሽብር ህግ ተብሎም በተረቀቀው ህግ ጋዜጠኞች፣ ተቃዋሚዎች እና የሰብዐዊ መብት ተሟጋቾች ኢላማ ተደርገው ለእስር ተዳረጉ፣ ተገደሉ እንዲሁም ተሰደዱ፡፡ የመገናኛ ብዙሓን መረጃ የማገኘት እና ነፃነት አዋጅ ተብሎም እጅግ አፋኝ ህግ ወጥቶም የህዝብ ድምፅ የሚባሉት ጋዜጦች እና መፅሔቶች ተዘጉ፡፡ ባለቤቶችን እና ጋዜጠኞቹን ማንገላታት፣ ማሰር፣ ማስፈራራት እና ሀሳዊ ፍርድ ቤቶች አቅርቦ ለረጅም ዓመታት ወህኒ መወርወር ተለመደ፡፡
የትኛውም ዓይነት ጥያቄ ሲቀርብ በኃይል መጨፍለቅ ምላሽ ተደርጎ ይወሰድ ጀመር፡፡ በጋምቤላ መሬቴን ተነጠቅሁ ያለን ገበሬ ያለ ርህራሄ መጨፍጨፍ በአምባገነኑ መለስ ትክክለኛ ተደርጎ ይወሰድ ጀመር፡፡ በኦጋዴን እና ሲዳም ለትንሽ ኮሽታ እናት፣ አባት፣ ሴቶች፣ ህፃናት ተገደሉ፡፡ አወሊያ አስተዳደራዊ ዝቅጠት ውስጥ ከገባው መጅሊስ ተላቆ የሙስሊሙ ይሁን፣ መንግስት በሀይማኖት ጉዳያችን ጣልቃ አይግባ እንዲሁም ሙስሊሙ በመስጂድ የሚመርጣቸው እውነተኛ የሀይማኖቱ ተወካዮችን እናግኝ ብለው ሶስት ቀላል ጥያቄዎችን ይዘው በመረጧቸው ኮሚቴዎች በኩል የቀረቡትን ሙስሊሞች “ኢስላማዊ መንግስት የመመስረት ሀሳብ አላችሁ” ብሎ ድራማ ሰርቶባቸው ወህኒ ወረወራቸው፤ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ሙስሊሞችም ህይወታቸውን ከፈሉ፡፡ የአዲስ አበባ ኦሮሚያ የተቀናጀ የጋራ ፕላን “ገበሬን በዝቅተኛ ገንዘብ አፍናቅሎ ድህነትን የበለጠ ያስፋፋል” ብለው የተቃወሙ የኦሮሚያ ሰዎችን እንደተለመደው ህፃን፣ አዛውንት፣ አሮጊት፣ ሴት ሳይመረጥ የጥይት እራት አድርጎ አለፋቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ውስጥ ሳይቀር እጁን አስገብቶ ህዝበ ክርስቲያኑን “በምን ታመጣለችሁ?” ደነፋባቸው፡፡
መንግስት በዚህ ሁሉ ወንጀል ውስጥ ተዘፍቆ ግን ሁለት የይስሙላ ምርጫን አድርጎ ወደ ሶስተኛው ተጉዟል፡፡ እሁድ ግንቦት 16/2007 እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠርም ይኸው ምርጫ ተደርጓል፡፡ የ2000 የማሟያ ምርጫን 100% እንዲሁም የ2002 አጠቃላይ ምርጫን 99.6% አሸንፌያለሁ ብሎ ባደደባይ የሚደሰኩረው አምባገነኑ መንግስት ከሙስሊሙ፣ ክርስቲያኑ፣ ከሁሉም ዘር (የትጥቅ ትግል የጀመረበት ቦታን ጨምሮ)፣ ከወጣቱ፣ አዛውንቱ እና ሴቶች ጋር ተጋጭቶ፤ ሙስናው አይን አውጥቶ፣ በእግሩ ድሆ እና ቆሞ አፍጥጦ እየታየ፣ በየሳምንቱ እምባን የሚጋብዙ ኢትዮጵያዊ ነክ ዜናዎች እየተሰሙ ለምን ምርጫ ላይ ሙጭጭ ይላላ? የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡
የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ከ1997 ምርጫ በኋላ የኩረጃ ፖለቲካ ውስጥ የተፈቁት ሟቹ አምባገነን መለስ “እንዴት ብዙ መቆየት እችላለሁ?” ብለው ሲኮረጁ 66 ዓመታት የቆየውን የቻይናን አምባገነን መንግስት ብቻ አላዩም፡፡ 69 ዓመታት የቆየው የጆርዳን፣ 35 ዓመታት ያስመዘገበው የዙምቧቡዌ እንዲሁም 21 ዓመታት የዘለቀውን የቤላሩስ አምባገነኖችን ኮርጀዋል፡፡ እግረ መንገዳቸውንም የዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ የፖለቲካል ሳይንቲስቷ የዶክተር አንድሬያ ኬንዴላ-ታይለር እና የብሪጅዋተር ስቴት ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰሯን ኤሪካ ፍራንትዝ ጥናትን የተመለከቱም ይመስላሉ፡፡
ለሁለቱ እንስት ምሁሮች፤ እንደ ሟች መለስ ዜናዊ አይነት አምባገነን እና እንደ ኢህአዴግ አይነት የተጠላ መንግስት ዕድሜውን ማራዘም ከፈለገ ምርጫ አይነተኛ “መድኃኒት” ነው፡፡ ከምርጫ በተጨማሪ የውሸት (Pseudo) ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ዕድሜያቸውን ያረዝሙላቸዋል፡፡ በሚፈልጉት መጠን ለክተው የቆረጧቸው ተቃዋሚ (ተፎካካሪ) ፓርቲዎች የሚያጫውቷቸው ከሆነ ደግሞ ዕድሜያቸው መንግስታዊ “ማቱሳላ” መሆኑ አይቀርም ይባልላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች እንዳሉ ሆነው ዘንድሮ ምርጫን ያደረጉ አምባገነኖች እንደዚህ ናቸው፡፡ ዑዝቤክስታን፣ ሱዳን፣ ቶጎ እና ካዛክስታን ፖለቲካዊ አምሳያቸውን ከፈለጉ ኢትዮጵያን ማየት ይበቃቸዋል፡፡ ኢትዮጵያም እንዲህ የሆነችው እነሱን ኮርጃ ነው፡፡
እንደ ዶክተር አንድሪያ እና ረዳት ፕሮፌሰር ኤሪካ ገለፃ ለእንደ ኢትዮጵያ አይነቱ አምባገነን ምርጫ “ነፃ፣ ፍትሐዊ እና በውድድር የተሞላ” መሆኑ አያሳስባቸውም፡፡ እነርሱ የሚፈልጉት ዓመቱን ጠብቆ ምርጫ መደረጉ፣ በሚፈልጉት መጠን የተለኩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች መኖርን እና ስልጣናቸውን ህጋዊ (Legitimate) የሚያደርጉላቸውን ተቋማት ብቻ ነው፡፡ በተለይ ከቀዝቃዘው የዓለም ጦርነት በኋላ አምባገነኖች ይህን አሰራር በደንብ ተላምደውታል፡፡ ሁለቱ አንስት ምሁራን እንዳጠኑት ከ1946-1989 የአምባገነኖች አማካይ ዕድሜ 12 ዓመታት ብቻ ነበር፡፡ ሆኖም ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በኋላ ይህ አማካይ ዕድሜ ወደ 20 ዓመታት ከፍ ብሏል፡፡አምባገነኖቹ ዕድሜያቸውን ለማርዘም ምርጫ፣ ህግ፣ ደንብ፣ ስርዐት ይሏችኋል፡፡ እናም የሚፈልጓቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሏቸው፡፡ ይህ ዲሞክራሲያዊ ጭምብልን ያላብሳቸዋል፡፡ ዓለምዓቀፍ እና የሀገር ውስጥ ተቀባይነትን (Legitimacy) በግድ ይወስዱበታል፡፡ “የተረጋጋ መንግስት አለኝ፤ በሀገሬ መጥታችሁ ኢንቨስት አድርጉ” ብለው ይቀሰቅሱበታል፡፡ በርካሽ የቸበቸቡትን የሰው ጉልበት፣ መሬት፣ የንግድ ዘርፍ እና የንግድ ተቋምን ከግምት ሳያስገቡ ዜጎቻቸው ላይ “እድገት” ብለው ያላዝኑበታል፡፡ እንዲሁም ወደ ምዕራባዊያን ሀገራት ለጉብኝት ሲያቀኑ ስለ ኮሞዩኒዝም መውደቅ፣ ስለ ምርጫ እና ሊብራሊዝም ማበብ ሊደሰኩሩም ይችላሉ፡፡ የይስሙላ ምርጫን አድርጎ ሳያስበው እና ሳይዘጋጅበት በህዝብ አመፅ እውነተኛ ውድቀት ውስጥ ከተዘፈቀው የሲሪላንካው ማሂንዳ ራጃብካ መንግስት ውጪ በቅርብ አምባገነኖችን ምሉዕ በሙሉ በውሸት የተገነባው ምርጫቸው ጥሏቸው አያውቅም፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም መተማመኛው ይሄው ነው፡፡ ሟች አምባገነኑ መለስ የሁለቱ እንስት ጥናትን ተመልክተው ከ1951-1989 አምባገነኖች ከተቃዋሚ ፓርቲ ጋር በአማካይ ጭማሪ ስድስት ዓመታት፤ ሳያሰልሱ ምርጫን ካደረጉ ጭማሪው 12 ዓመታት እንደሚኖሩ ይህ ቁጥር ግን ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በኋላ አምባገነኖች ከተቃዋሚ ፓርቲ ጋር በአማካይ 14 ዓመታት፤ ግዜን ጠብቀው ምርጫን ካደረጉ ግን 22 ተጨማሪ ዓመታት ሊቆዩ እንደሚችሉ አምብበውም፤ ስለዚህም ምሉዕ በሙሉ የውሸት ምርጫ ማድረግን ያዋጣኛል ብለው ተቀብለው ይሆናል፡፡ ለኢህአዴግ ከሙስሊሙ ጋር ቢጋጭ፣ በክርስቲያኑ ሀይማኖታዊ ጉዳዮች እጁን ቢያንቦጫርቅ፣ የትጥቅ ትግል የጀመረበት ቦታ ዘር ሳይቀር “ጠላሁህ” ብሎ ጠብመንጃ ቢያነሳበትም፣ ወጣቱ ጠልቶት በገፍ ስደትን ቢመርጥም፣ እስር ቤቶች ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በተያዙ እና በታሰሩ ሰዎች ቢሞሉም፣ ህዝብ በሹክሹክታ አምባገነንት በቃኝ ቢል፣ በሀገሪቷ ብሶትን የሚያሰማ አንዲትም ጋዜጣ ይሁን መፅሔት ባይኖርም፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ባለዝና ሰዎች እና ምሁራን በፍርሃት ተሸብበው አጎብዳጅ ቢሆኑም፤ ምርጫው ይደረጋል፡፡ ምክንያቱም “ምርጫው እድሜ ማራዘሚያ መድኃኒቱ” ነው፡፡ ህዝብ ይህን ምርጫ ታኮ ልተንፍስ ካለም ከእንሰሳ ብዙም የማይለዩ ለመግደል ብቻ የሰለጠኑ፣ ቀጭን ትዕዛዝ ተቀባዮች ይላኩበታል፡፡
The post እውን የዘንድሮው ምርጫ ፍታሀዊ ነውን? – ምርጫ እንደ ዕድሜ ማራዘሚያ appeared first on Zehabesha Amharic.