ግርማ ሞገስ (girmamoges1@gmail.com)
እሮብ ሐምሌ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. (Wednesday, July 24, 2013)
የዜጎችን ፊርማዎች ማሰባሰብ የብዙ መቶ አመቶች ታሪክ ያለው ሰላማዊ ትግል ነው። የሚሊዮኖች-ድምጽ-ለነፃነት ዘመቻ አንዱ ግብ በኢትዮጵያ ሽብር ህግ ላይ ዜጎች ያላቸውን አቅዋም በፊርማቸው እንዲገልጹ ማድረግ ነው። እንደሚታወቀው አንድ መንግስት ዜጎቹን በሽብር ህግ የሚገዛው ከፖለቲካ ተፎካካሪዎቹ የተሻለ አሳብ በማቅረብ የህዝብ ድጋፍ ማግኘት ሲያቅተው ነው። የአዲስ አሳብ ምንጮቹ ሲደርቁበት ነው። የአሳብ ኪሳራ ሲደርስበት ፊቱን ወደ ሽብር ያዞራል። በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው ይኼው ነው። በፊርማችን አቅዋማችንን እንግለጽ።
አለም አቀፍ ሽብር ለመከላከል ነበር የኢትዮጵያ ፀረ-ሽብር ህግ የተደነገገው የሚለው ምክንያት ሃሰት ነው። የኢትዮጵያ ፀረ-ሽብር ህግ የተደነገገው አልቃይዳ እና ሌሎች አለም አቀፍ ሽብርተኞች ጥቃት ደርሶባቸው በሽሽት ላይ በነበሩበት ጊዜ ነበር። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ2001 ዓመተ ምህረት ማለቂያ ጀምሮ አሜሪካ እና ምዕራብ አውሮፓ በየአገራቸው ፀረ-ሽብር ህግ ሲደነግጉ አቶ መለስ ኢትዮጵያ አያስፈልጋትም ይል ነበር። ነገር ግን እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2005 ዓመተ ምህረት በኢትዮጵያ የተካሄደው ምርጫ (ምርጫ 97) አስደነገጠው። ሌላ ምርጫ 97 ቢደገም ስልጣን ከዕጁ ሊያመልጥ እንደሚችል ወለል ብሎ ታየው። በዚህን ጊዜ ነበር የመለስ ዜናዊ ህውሃት አለም አቀፍ ፀረ-ሽብር ህግ ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል ማለት የጀመረው። የፖለቲካ ባላንጣዎቹን ለመወንጀል እና ከስልጣን ፉክክር ሜዳ ለማስወጣት። ህዝብን በሽብር አስፈራርቶ እንደ እንሰሳ ለመግዛት።
ቀደም ሲል ቀጥተኛ የሽብርተኞች ጥቃት የደረሰባት እና በግንባር ቀደምትነት ፀረ-ሽብር ህግ ከደነገጉት አገሮች ውስጥ አንዷ የሆነቸው አሜሪካ ሳትቀር የኢትዮጵያን ፀረ-ሽብር ህግ ከመስመር የወጣ እና የፖለቲካ ተቃዋሚዎቹን ኢላማ ያደረገ መሆኑን ገለጸች። የኢትዮጵያ መንግስት ህጉን እንዲከልስ አሳሰበች። የአውሮፓ ህብረት፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂውማን ራይትስ ዋች፣ ድንበር የለሽ ጋዜጠኞች የኢትዮጵያን ፀረ-ሽብር ህግ ፀረ-ሰብዓዊ መብት እና ፀረ-ዲሞክራሲ ነው በማለት በአደባባይ ተቃወሙ። እንዲሻሻል ጠየቁ። ስመ ጥሩው ኢሰመጉም ተመሳሳይ ተቃውሞ እና ጥያቄ አቀረበ። በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ተመሳሳይ ተቃውሞ እና ጥያቄ አቀረቡ። ተቃውሞዎቹ እና ጥያቄዎቹ ዛሬም አላቋረጡም። የዛሬው የሚሊዮኖች-ድምጽ-ለነፃነት አገር አቀፍ ህዝባዊ እንቅስቃሴም የእነዚሁ አለም አቀፋዊ እና አገራዊ ተቃውሞዎች እና ጥያቄዎች ቅጥያ ነው።
የኢትዮጵያ ፀረ-ሽብር ህግ የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን የአገሪቱን ህገ-መንግስት ይፃረራል። ህጉ የተዘጋጀው አምባገነኖቹ ገዢዎች እንደፈለጉ መተርጎም እና ፖለቲካዊ ጥቃት መፈጸም እንዲችሉ ተደርጎ ነው። ህጉ በህገ-መንግስቱ ውስጥ የተዘረዘሩትን መብቶች ይሰርዛል። ጸረ-ዴሞክራሲ ነው። ጸረ-ነፃ ፕሬስ ነው። ፀረ-ነፃ ምርምር ነው። ፀረ- አዳዲስ አሳብ አፍላቂነት ነው። ፀረ-ሲቪክ ማህበራት ነው። የነፃነት አድማስ አፋኝ ነው። የዴሞክራሲ አድማስ አጥፍቷል። ነፃ ምርጫ ያደናቅፋል። እንደ ከብት መንጋ መገዛትን ህጋዊ ያደርጋል የኢትዮጵያ ሽብር ህግ። ባጭሩ ከአቀራረባቸው እና ከአፈጻጸማቸው በስተቀር የዛሬው የኢትዮጵያ ሽብር ህግ እና የትናንቱ የደርግ ሽብር ህግ ተመሳሳይ ናቸው። ሁለቱም ህጎች የዜጎችን የማሰብ መብት ሳይቀር የሚያስቀጣ ወንጀል ያደርጋሉ። ስለዚኽ የኢትዮጵያ ፀረ-ሽብር ህግ መሰረዝ አለበት። የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት አገር አቀፍ እንቅስቃሴ ግቡ ይኽን ህግ ለማሰረዝ እና የዚህ ህግ ሰለባ የሆኑትን ሰላማዊ ታጋዮች እና ጋዜጠኞ ማስፈታት ነው። በዚህ ሰላማዊ ትግል ብንሳተፍ የሚጠቀሙት በአገር ቤት ያሉት ወገኖቻችን ናቸው። የሚጠቀሙት በሽብርተኛነት የታሰሩት የድምጻችን ይከበር መሪዎች፣ የኢትዮጵያ ሰላማዊ ትግል መሪዎች እና ጋዜጠኞች ናቸው። የሚጎዳው ህውሃት ብቻ ነው።
በሽብርተኛነት የታሰሩት ሽብርተኞች አይደሉም። ላብራራ! ዛሬ የሽብርተኞች ባህሪ ብዙ የተጠና እና የተጻፈበት ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ በሽብርተኛነት የታሰሩት የሙስሊም እምነት መሪዎች እነ አቡበከር፣ የአንድነት ፓርቲ አባላት እነአንዱዓለም አራጌ፣ እነናትናኤል መኮንን እና ሌሎች፣ የኦፌዴን ም/ሊቀመንበር በቀለ ገርባ፣ የኦሕኮ ጽ/ቤት ኃሊፊ አቶ ኦሌባና ላሉሳ እና ሌሎች፣ እንዲሁም ጋዜጠኛቹ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት ዓለሙ የሽብርተኛነትን ባህሪ እና ታሪክ የላቸውም። ሌላ ማብራሪያ! ሽብርተኞች በአለማችን የፈጸሙዋቸውን አሰቃቂ የሽብር ተግባሮች ብናስታውስ ሽብር ለመፈጸም የተደራጀ የሰው ኃይል፣ የሰለጠነ ድርጅት፣ ሃብት፣ የጦር መሳሪያ፣ ሚስጥረኛነት (የድብቅ ስራ) እና በሽብርተኛ የፖለቲካ ትግል ባህል መጠመቅን ይጠይቃል። በሽብርተኛነት ህውሃት ያሰራቸው በሙሉ እንዲዝኽ አይነት የተደራጀ ኃይል የላቸውም። እስኪ አሁን በምን ሂሳብ ርዕዮት ዓለሙ ሽብርተኛ ናት ማለት ይቻላል? በከፊል እየሰራች በከፊል ትምህርት እና ተጨማሪ ድግሪ በማሳደድ ላይ ነበረች እንጂ የሽብር ድርጅት በመምራት ላይ እንዳልነበረች ይታወቃል። ያልፈቷትም ይቅርታ ጠይቂ ብለዋት ሳላጠፋ ይቅርታ አልጠይቅም በማለቷ ነው። በቀለ ገርባም ቢሆን ክብሩን ጠብቆ እያስተማረ በጎን ከፍተኛ ትምህርቱን የሚከታተል እና ቤተሰብ የሚያስተዳድር ሽብርን የሚኮንን ዜጋ ነበር። አንዱአለም አራጌ ደፋር የሰላማዊ ትግል ሐዋሪያ ነበር። እስክንድር ነጋም ሃሳቡን በአደባባይ ሲናገር የነበር የነፃ ፕሬስ ታማኝ ወታደር ነበር። መለስ ዜናዊን አምባገነን ለዴሞክራሲ እንቅፋት ስለሆንክብን ከስልጣን ውረድ ብሎ እዚያው አዲስ አበባ በይፋ የፃፈ ነው። በሽብር የታሰሩት በሙሉ አዲስ ሰላማዊ የትግል ባህል ለኢትዮጵያ ያበረከቱ ናቸው። በዚኽ አስተዋጽዋቸው ኢትዮጵያ ልትሸልማቸው እንጂ ልታስራቸው አይገባም። በሙሉ ሊፈቱ የገባል።
የህውሃት ካድሬዎች እስክንድር ነጋን ሽብርተኛ ለማስመሰል በህፃን ልጅ ፊት የሰሩት ድራማ እጅግ አሳፋሪ ነበር። ሽብርተኛ አስመስለው ሊያስሩት በመንገድ ላይ ሳለ ግርግር ሲፈጥሩ እስክንድር ነጋ ፍቅር የተባለውን የ5 አመት ልጁን ከትምህርት ቤት ወደ ቤት በማድረስ ላይ ነበል። እንደ ጥሩ ዜጋ አባት። እስክንድር ሲያዝ አብሮት የነበረው ፍቅር አባቱን ከፖሊሶች ለማስለቀቅ እያለቀሰ ፖሊሶቹን እግር እግራቸውን በእግሩ ሲመታ እንደነበር በሰፊው ተዘግቧል። ሽብረተኛው እስክንድር ሳይሆን ስብዕናቸው የተሟጠጡት የመለስ ዜናዊ መልክተኞች የህውሃት ካድሬዎች ናቸው። ከአይን ምስክሮች ባሻገር ወጣት ናፍቆት አባቱን ከፖሊሶች ለማስለቀቅ ያደረገውን ትግል የሚያሳይ ቪዲዮ ወይንም ፎቶ ቢኖር ከፍተኛ ታሪካዊነት እና የፖለቲካ ፋይዳ አለው።
ስለዚኽ በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ውስጥ በመካሄድ ላይ በሚገኘው አገር አቀፍ የሚሊዮኖች-ድምጽ-ለነፃነት ዘመቻ በመሳተፍ በኢትዮጵያ ፀረ-ሽብር ህግ ላይ ያለንን ተቃውሞ እንግለጽ። አለአግባብ የታሰሩትን ለማስፈታት በመንግስት ላይ ጫና እናድርግ። መሳተፍ ማለት ከሚከተሉት ሁለት ነገሮች ውስጥ አንዱን ወይንም ሁለቱንም ማድረግ ማለት ነው።
(1) www.andinet.org ድረ-ገጽ በመሄድ ፊርማችንን መስጠት፣
(2) እያንዳንዱን ህዝባዊ ስብሰባ እና ሰላማዊ ሰልፍ ዘመቻ ለማደራጀት ገንዘብ ስለሚያስፈልግ የገንዘብ እርዳታ ማድረግ፣
http://www.thepetitionsite.com/174/997/377/millions-of-voice-
ከፍ ብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ አንዱን ወይንም ሁለቱንም በማድረግ በሃሰት በሽብርተኛነት ታስረው አላግባብ እድሜያቸውን በእስር ቤት እንዲያባክኑ ለተገደዱት ለእነ አቡበከር፣ አንዱዓለም አራጌ፣ ናትናኤል፣ በቀለ ገርባ፣ ኦሌባና ላሉሳ፣ እስክንድር፣ ውብሸት፣ ርዕዮት እና ሌሎች የትብብር እጃችን እንዘርጋላቸው። በመንግስት ላይ ጫና በማድረግ ከእስረኞቹ ጎን መቆማችንን እንግለጽ። ኢትዮጵያ በመስራት ላይ ባለቸው አዲስ የዲሞክራሲ ጉዞ ታሪክ ላይ ማህተማችንን እናስቀምጥ!
በክፍል ሶስት እንገናኝ።
ክፍል ሶስት የሚሊዮኖች-ድምጽ-ለነፃነትን ከበካይ ተግባሮች ለመጠበቅ ያስችሉናል የሚላቸውን አሳቦች ለአንባቢያን በማቅረብ ዜጎች ውይይት እንዲከፍቱበት ይጋብዛል።