Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Health: በወሲብ ወቅት ብልቴን ያቃጥለኛል፣ ያመኛል፣ ይቆስላል፣ ይላላጣል

$
0
0

እድሜዬ 25 ሲሆን የወንድ ጓደኛ አለኝ፡፡ ለአንድ ዓመት ያህል ጥሩ የወሲብ ግንኙነት ነበረን፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ አዲስ ነገር ተፈጠረ፡፡ በመጀመሪያ በግንኙነት ጊዜ ከእኔ ብልት የሚወጣው ፈሳሽ አይወጣም ነበር፡፡ ይህን ተመርምሬ መድሃኒቱን ተከታትዬ ለተወሰነ ጊዜ ተሻለኝ፡፡ ቀጥሎ የጓደኛዬ ብልት ብልቴ ውስጥ ሲገባ ያቃጥለኛል፣ ያመኛል፣ ይቆስላል፣ ይላላጣል፣… ለአንድ ዓመት እንደዛ ሆነብኝ፡፡ ከዛ ተመርምሬ ዶክተሩ (ሐኪሙ) ይህን ችግር ሊያስከትልብሽ የቻለው ማህፀንሽ ውስጥ ዕጢ ስላለ ነው አለኝ፡፡ ይህን እጢ ሳታስወጭ መፀነስ የለብሽም፡፡ ዕጢውን ካስወጣሽ በኋላም ለመፀነስ ሐኪምን ማማከር አለብሽ ተባልኩኝ፡፡ የኔ ጥያቄ ታዲያ፡-
1. ማህፀን ውስጥ ዕጢ ሊፈጠር የሚችለው እንዴት ነው?
2. በግንኙነት ጊዜ የሚቆስለው የሚላጠው ዕጢው ሲወጣ ይተውሻል ብላችሁ ታምናላችሁ?
3. ከቀዶ ጥገና በኋላ እንደፈለጉ ግንኙነት ማድረግ እና ያለስቃይ ልጅ መውለድ ይቻላል? ይህን ሁሉ የምላችሁ ፍቅረኛዬን ማጣት ስለማልፈልግ ነው፡፡ የማይሆን ከሆነ እወደዋለሁ ግን ምን ላድርግ? መልሳችሁን እጠብቃለሁ፡፡ S.K

ask your doctorየዶ/ር ዓብይ ዓይናለም ምላሽ፡ ውድ S.K ሰላምታሽ ደርሶናል እናመሰግናለን፡፡ የእኛም ሰላምታ ከመልካም ምኞታችን ጋር ይድረስሽ እያልን ዛሬ ያንቺን ደብዳቤ ለመመለስና አንዳንድ መረጃዎችን ላንቺ እንዲሁም ለሌሎች ለማድረስ ወደድን፡፡
በግብረስጋ ግንኙነት ወቅት ሆነም ከግንኙነት በፊት ወይም በኋላ በብልትና አካባቢው የሚሰማ ህመም በህክምናው Dys-pareunia በመባል ይታወቃል፡፡ የዚህ ህመም ስሜት ከመጀመሪያው የግብረ ስጋ ግንኙነት ጀምሮ የሚሰማ ወይም የግብረ ስጋ ግንኙነት ከመጀመሩ ከብዙ ጊዜያቶች ያለ ህመም ከቆየ በኋላ የሚመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የህመም ስሜት በማንኛውም ጊዜና ከተለያዩ ሰዎች ጋር በሚደረግ የግብረ ስጋ ግንኙነት ሲመጣ ወይም አልፎ አልፎ ሊከሰት የሚችል የበሽታ አይነት ነው፡፡
ምክንያቱም ከብልትና አካባቢው (ከማህፀን ጭምር) በሚኖሩ ችግሮች እና ከስነ ልቦና ችግር ጋርም የመያያዝ ባህሪ ሊኖረው ይችላል፡፡
ለዚህ ችግር ተጠያቂ ምክንያቶች ተደርገው የሚነሱ ጉዳዮች፡-
- የሴት ልጅ ግርዛት፣
- የማህፀን በሽታ (ኢንፌክሽን)
- ያረጡ ሴቶች
- የጭንቀት በሽታ
- የድብርት በሽታ፣ እና
- በልጅነት ዕድሜ የተከሰተ የፆታ ጥቃት ወይም አስገድዶ መደፈርን የመሳሰሉ ናቸው፡፡
የዚህን በሽታ ምክንያቶች ዘርዘር አድርገን ስንመለከት ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች በሆኑ ሴቶች ላይ Vestibulsodyria የተባለው የበሽታ አይነት ሲሆን ከ50 ዓመት በላይ በሆኑት ላይ ደግሞ የብልት መሳሳት (Vulvavaginal atrophy) ይህንን የህመም ስሜት በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ያስከትላሉ፡፡
ተራ በተራ የዚህን በሽታ ምክንያቶች እስከ ህክምናቸው ስናይ፡-
1. Vaginismus:- የዚህ ችግር መንስኤ አንዲት ሴት የብልቷና አካባቢ ጡንቻ ሳታስበው በሚፈጠርባት መኮማተር የሚያስከትለው ነው፡፡ ለዚህ ችግርም የስነ ልቦና ችግር እንደ ምክንያት ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ የዚህች ሴት የብልት አካባቢ በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት በሚነካበት ወይም የወንዱ ብልት ወደ ብልቷ ሊገባ ሲል የብልቷ ጡንቻዎች ይኮማተራል ወይም ይወጣጠራል፡፡ በዚህም የህመም ስሜት ይፈጠራል፡፡ የብልቷ ይወጣጠራል፡፡ በዚህም የህመም ስሜት ይፈጠራል፡፡ የብልቷ አካባቢም ሳይነካ ይህ ችግር ሊታይ ይችላል፡፡ ህክምናውን በተመለከተ ቀስ በቀስ የብልትና አካባቢውን ጡንቻዎች አዕምሮን በማዘዝ ለማላላት በመሞከር የሚደረግ የህክምና አይነት ነው፡፡ በዚህም የብልትን ጡንቻዎች ወይም በብልት አካባቢ የሚገኙ ጡንቻዎች ቀስ በቀስ በአዕምሮ እንዲታዘዙ ማድረግ ስለሚቻል በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት የህመም ስሜትን መቆጣጠር ይቻላል፡፡
ሌሎች ህክምናዎች ደግሞ Sex therapy የሚባለው የህክምና አይነት ሲሆን ህመሙን ለማለዘብ ጓደኛሞች ቀስ በቀስ ግብረስጋ ግንኙነቱን እንዲያላምዳት ማድረግ ነው፡፡ በዚህም ጊዜ የጓደኛዋ ብልት ቀስ እያለ ወደ ብልቷ እንዲገባ በመርዳት በሂደት የሚከናወን ድርጊት ሲሆን ወንዱም ያለመ ሰላቸት የሚያከናውነው መሆን ያለበት የህክምና አይነት ነው፡፡
በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት የሚወሰድ የጡንቻን መላላት የሚያመጣውን መድሃኒት መጠቀም ሌላው አማራጭ ነው፡፡ ይህንንም ከሐኪም ጋር በመወያየት መጠቀም ይቻላል፡፡
2. Vulvar vestibulodynia:- ይህም ችግር ልክ እንደ ከላይ እንዳለው አይነት በሽታ ሲሆን ምክንያቱ ግን ተደጋጋሚ የብልት ኢንፌክሽን ወይም አደጋ የሚያስከትለው የበሽታ አይነት ነው፡፡ ህመሙ የሚመጣው የብልት አካባቢ ሲነካ ብቻ ነው፡፡ የላይኛው ግን ሳይነካም ሊመጣ ይችላል፡፡
ህክምናውም የግብረስጋ ከመፈፀም በፊት (ከ10 ደቂቃ በፊት) እና ከፈፀሙም በኋላ የሚቀባ ቅባት በመጠቀም ከህመሙ መላቀቅ ይችላል፡፡ የዚህ ቅባት ስም ዛሎኬን ይባላል፡፡ ወይም ከዚህ ላቅ ያሉ የመድሃኒት አማራጮችን በመርፌ የሚሰጥ መድሃኒት በባለሙያ እርዳታ በብልት አካባቢ በመወጋት ህመሙን መቀነስ ይቻላል፡፡ ይህም በመጀመሪያው ቀን፣ ከሳምንት በኋላ እንደገና ከ15 ቀን በኋላ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ሌሎችም መድሃኒቶች ስለሚኖሩ በዚህ አይነት በሽታ የተጠቁ ሴቶች የማህፀን ሐኪምን እርዳታ መጠየቅ አለባቸው፡፡
ተጨማሪ ምክሮች፡-
- የብልትን አካባቢ ንፅህና መጠበቅ፣
- ላላ ያለና አለርጂ የማይፈጥር ፓንትና ልብስ ማድረግ፣ ከጥጥ የተሰራ ቢሆን ይመረጣል፡፡
- ሽታ፣ ቀለማቸው የሚለቅ፣ ኬሚካል ያላቸውን ልብሶች አለመልበስ፣
- የብልትን አካባቢ ሊጎዱ የሚችሉ እንቅስቃሴዎች ለምሳሌ ብስክሌት መንዳት ማቆም፣
- የብልት ፈሳሽ የሚያስቸግራቸው ሴቶች ፓድ ከማድረግ የውስጥ ሱሪያቸውን ቶሎ ቶሎ መቀየር ይጠበቅባቸዋል፣
- የብልት አካቢን ሞቅ ባለ ውሃ መዘፍዘፍና በተለይም የብልት አካባቢ ድርቀት የሚታይባቸው ከሆነ፣
- የግብረ ስጋ ግንኙነት በሚደረግበት ጊዜ የአትክልት ዘይት መቀባትም ድርቀቱን ሊያስወግድ ይችላል፣
- የተሰባበረ በረዶ በላስቲክ በማድረግ ብልት ላይ ማድረግ ከግብረ ስጋ ግንኙነት በኋላ የሚከሰተውን የብልት ማቃጠል ሊያስወግድ ይችላል፡፡
- Oxolate የተባለውን ቅመም የያዙ ምግቦችን ለምሳሌ ፍራፍሬዎች አትክልቶችንና ጥራጥሬዎችን ከምግቦቻቸው ላይ መቀነስ፡፡
1. Vulvovaginal atrophy (የብልት መሳሳት)
ይህ ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት ወይም ባረጡ ሴቶች ላይ ይታያል፡፡ ምክንያቱም ኤስትሮጅን የተባለው ሆርሞን እጥረት ሲሆን፣ በዚህ እጥረት የብልት አካባቢ ቅባት ይቀንሳል፡፡ ስለሆነም የብልት አካባቢ መድረቅ ይከሰታል፡፡ በዚህም የተነሳ በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ህመም ይሰማል፣ የብልት አካባቢ ያቃጥላል፣ የብልት መቁሰልና ከግንኙነትም በኋላ መድማት ይታያል፡፡ የኤስትሮጅን ቅባት በቀን አንድ ጊዜ ለአራት ሳምንታት መቀባት ያስፈልጋል፡፡
2. በቂ የብልት ቅባት አለመኖር
በቁጥር 3 እንዳየነው ሆኖ አንዳንድ ጊዜ ከ50 ዓመት በታች በሆኑ ሴቶች ላይ የሚታይና በቂ የስሜት አለመነሳሳት፣ ከጓደኛ ጋር በተለያየ ምክንያት አለመጣጣም ወይም ያልተፈታ የስነ ልቦና ችግር ሲኖር የአንዳንድ መድሃኒቶች የጎንዮሽ ችግሮች (የደም ግፊት፣ የድብት በሽታ መድሃት እና ሌሎችም) ይህንን ችግር ያስከትላሉ፡፡
መፍትሄዎቹ በመጀመሪያ ደረጃ ያሉትንና አጋላጭ ችግሮችን ማስወገድ ከግብረ ስጋ ግንኙነት በፊት የሚደረግ የፍቅር ጨዋታ ያስፈልጋል፡፡
3. የፊኛና የኩላሊት ኢንፌክሽን ሲኖር፡- በባለሙያ እርዳታ በመታገዝ ህክምና ማድረግ
4. የብልት ኢንፌክሽን ሲኖር፡- የብልት ፈንገስ በሽታ ወይም ሌላ የብልት በሽታ መኖር፣ የብልትና አካባቢው ፈሳሽ መኖር፣ መቁሰል፣ ማቃጠል፣ ማሳከክ ሌሎችም ምልክቶች ይኖራሉ፡፡ ህክምና ሳይደረግ የሚፈፀም ግንኙነት ህመም ያስከትላል፡፡ በባለሙያ እርዳታ ህክምና ማድረግ ለበሽታውም ለህመሙም መፍትሄ ያስገኛል፡፡
5. በወሊድ ጊዜ የሚደረግ የብልት መቆረጥ ወይም መለጠጥ በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ህመም ሊያመጣ ይችላል፡፡ ይህም ችግር በቀዶ ጥገና መስተካከል አለበት፡፡
6. የማህፀን ዕጢ፡- የማህፀን ዕጢ ያላቸው ሴቶች ከሌላቸው ሴቶች ጋር ሲነፃፀሩ በግንኙነት ወቅት የህመም ስሜት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በተለይ ትልቅ የሆነና በማህፀን ጀርባ አካባቢ የወጣ ዕጢ ከሆነ የማህፀን ዕጢውን ማውጣት ከዚህ ችግር ያድናል፡፡
7. የስነ ልቦና ችግር ያላቸው ሴቶች በዚህ ህመም ሊጠቁ ይችላሉ፡፡ በተለይ የተቃራኒ ፆታ ጥቃት ከደረሰባቸው፣ በቂ እውቀት (ስለ ግንኙነት) የሌላቸው ከሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ስለ ግብረ ስጋ ግንኙነት የተሳሳተ ግምት ካላቸው ለዚህ ሰዎችም የስነ ልቦና ህክምና፣ የግብረ ስጋ ግንኙነት ምን እንደሆነ የሚ ሰጥ ትምህርት፣ የፆታ ትምህርት፣ እና ሌሎችም ያስፈልጋቸዋል፡፡
ውድ ጠያቂያችን የማህፀን ዕጢ የሚፈጠርበት በውል የታወቀ ምክንያት ባይኖርም ከቤተሰብ በዘር የሚወረስና በአንዳንድ ምክንያቶች ጤነኛ የነበሩት የማህፀን ሴሎች ወደ ዕጢ ይለወጣሉ፡፡ እነዚህ ዕጢዎች የተለያዩ ምልክቶች ሊያሳዩን ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ለረጅም ጊዜ ወይም ብዙ የወር አበባ መፍሰስ፣ ወደ ታች የሚጫን ስሜት ወይም የህመም ስሜት መኖር፣ ከእርግዝና ጋር የሚከሰቱ ችግሮች ለምሳሌ በመጀመሪያው 3 ወራት ውስጥ የደም መፍሰስ መኖር፣ የእንግዴ ልጁ ከማህፀን ግድግዳ መለየትና እርግዝናው ላይ ችግር ማስከተል፣ በምጥ ጊዜም ምጡ ከጠናና የሚያስቸግር መሆንን ያመጣል፡፡ እነዚህ በእርግዝና ጊዜ የሚመጡ ችግሮች እንደ ማህፀን ዕጢው ትልቅነትና ያለበት ቦታ ይወሰናል፡፡ በተለይ የእንግዴ ልጁ በዕጢው ላይ ካለ ችግሩ ይከፋል፡፡
የማስወረድና ልጅ የመውለድ ችግር በማህፀን ዕጢ ምክንያት ሊመጣ የሚችለው ዕጢው የማህፀንን የውስጥ ክፍል አቀማመጥ ሲያዛባው ነው፡፡ ስለዚህ ዕጢውን ማስወገድ (በቀዶ ጥገና) ከላይ የጠቀስናቸውንና ሌሎችንም ችግሮች እንዳይኖሩ ያደርጋል፡፡
ውድ ጠያቂያችን፡- በአጠቃላይ በግንኙነት ወቅት የሚደርስብሽ ችግር የሚመጣው በዚህ በማህፀን ዕጢ ብቻ ላይሆን ስለሚችል ተጨማሪ የባለሙያ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የቀዶ ጥገና ከተደረገ ያለ ስጋት ግንኙነት ማድረግ ይቻላል፡፡ ልጅ መውለድም እንደዚሁ፡፡ S


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>