በቴሌቭዥን የሚተላለፉ መርሐ ግብሮች አነሰም በዛም በሕዝብ ላይ የሚፈጥሩት የእረጅም ጊዜ ተፅኖ ቀላል አይደለም።በተለይ በታዳጊ ወጣቶች እና ልጆች ላይ ለነገ እነርሱነታቸው የሚጭረው ስሜትም ሆነ አለማቸውን እና አካባቢያቸውን የሚመለከቱበት ዕይታ የጠበበ አልያም የሰፋ ወይንም የተንሸዋረረ የመሆን እድሉ ትልቅ ነው።እዚህ ላይ ወላጆች ለልጆቻቸው ከቴሌቭዥን መርሃ ግብር በኃላ የሚሰጡት የማስተካከያ ሃሳብ ወይንም ልጆችም ሆኑ ወጣቶች ጉዳዩን የሚያዩበትን እይታ ቀላል አይደለም።
የኢትዮጵያ ተለቭዥንን በሀገር ውስጥ የመረጃ ምንጭነት ተአማኒነቱ የወረደበትን ደረጃ ለመግለፅ ህዝቡ ”የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እውነት የምናገረው ሰዓት ብቻ ነው” የሚለውን አባባል መግለፁ ብቻ በቂ ነው።ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ በመገናኛ ብዙሃንነት የቆየ የቴሌቭዥን ጣብያ በእዚህ አይነት ደረጃ የወረደ የመረጃ ምንጭ መሆኑ እንደ ኢትዮጵያዊነት በጣም ያሳዝና።ዛሬ ቢልልን ኖሮ ኢቲቪ በመላው ዓለም ባሉ ከተሞች ወኪሎች በኖሩት እና በቀጥታ የሚዘግቡ ዘጋቢዎች በኖሩት ነበር። ይህ ደግሞ ከወጭም አንፃር ብዙ አለነበረም።ምክንያቱም በመላው ዓለም እንደመበተናችን በነፃ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ማግኘት ከባድ አይደለም።ነገር ግን አለመታደል ሆኖ አምባገንነት፣ጎሰኝነት እና ሙስና መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደጠረነፈ ሁሉ የኢትዮጵያ ቴሌቭዝንም አንዱ ሰለባ ነው።ኢትዮጵያውያን ግን በሀገር ቤት የታፈነ ድምፃቸውን በቸልታ አላዩትም።በጥቂቶች አስተባባሪነት የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን በመላው ዓለም እና በሀገር ቤት ላሉ ወገኖቻችን ብቸኛው ነፃ የመገናኛ ብዙሃን ለመሆን በቅቷል።
የእዚህ አጭር ማስታወሻ አላማ ስለ ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ታሪክ ለማውራት አይደለም።ስለሚያቀርባቸው ሳምንታዊ ድራማዎች ግን ትንሽ ማለት ፈለኩ።የቴሌቭዥን ድራማዎቹን ምግብ እየበላሁም ሆነ መንገድ ላይ ባለኝ ክፍት ጊዜ እመለከታቸዋለሁ።ይህንን የማደርገው መዝናኛ ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን አሁን ያለውን የሀገር ቤትን ማኅበራዊ፣ስነ-ልቦናዊ፣ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሁኔታ ስለሚያንፀባርቁልኝ ነው።የድራማዎቹን የመሃል እንቡጥ መልእክት ፈልፍላችሁ ለማግኘት ስትሞክሩ (በስድስተኛው የስሜት ህዋስ ማለቴ ነው) ብዙ ጠቃሚ እና ጎጂ ጎኖቹን ለማየት አያስቸግራችሁም።
በስድስተኛው የስሜት ህዋስ የሶስቱ ድራማዎች እይታ
እዚህ ላይ በቴሌቭዥን ከሚቀርቡት ድራማዎች ውስጥ የሁለቱ ማለትም ”ቤቶች” እና ”ሞጋቾች” ላይ የማነሰው የጠለቀ ሂስ አለመሆኑን እና ያንን ለማድረግ የሙያው ክህሎት እንደሌለኝ ለመግለፅ እፈልጋለሁ።ነገር ግን ድራማዎቹ በህብረተሰባችን ላይ ያላቸው አሉታዊ እና በጎ ተፅኖ ላይ ሃሳብ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
1/ ”ቤቶች” ድራማ
ይህ በየሳምንቱ ቅዳሜ ምሽት የሚቀርበው ድራማ በብዙዎች ዘንድ በአስቂኝነቱ የሚጠቀስ እና በርካታ ተመልካች ያለው መሆኑ ይታወቃል።አመታዊ ዝግጅቱን ሲያዘጋጅም የሚመለከቱት ተመልካቾች በርካታ መሆናቸውን ያሳያል።እንደ እኔ አስተያየት ድራማው ከማዝናናት ባለፈ ሊያስተምር የሚገባው በርካታ ነገሮች ይቀሩታል።በመጀመርያ ደረጃ ታሪኩ አንድ በግንብ በታጠረ ቪላ ቤት ውስጥ የሚኖር ቤተሰብ ዙርያ ያጠነጥናል።ቤተሰቡን መካከለኛ ገቢ ያለው ቤተሰብ ለማለት ይከብደኛል።ምክንያቱም መካከለኛ ገቢ የሚባለው ሕብረተሰብ አሁን በራሱ ጠፍቷል።ከሃያ ሶስት አመታት በፊት አንድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር መሬት ተመርቶ ቤት የመስራት አቅም ነበረው።ዛሬ ቤት ለመስራት ከፍተኛ ገቢ ካላቸው ውስጥ የሚመደብ ካልሆነ አይታሰብም።እናም ድራማው ውስጥ የሚተውኑት ቤተሰብ አባላት ቢያንስ ባለ ሁለት ሰራተኛ እና አንድ የጥበቃ ግለሰብ የሚተዳደሩ ናቸው እና መካከለኛ ከሚለው እናውጣቸው።እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ95% በላይ በእንደዚህ አይነት ኑሮ የሚኖር አይደለም።አዲስ አበባ ብቻ የግል መፀዳጃ የሌለው የሕዝብ ብዛት ከ70% በላይ እንደሆነ ከተገለጠ እሩቅ አይደለም።በመሆኑም ድራማው ተጨባጩን የሀገራችንን ሕዝብ ኑሮ አይወክልም።ይህ ግን ድራማውን ያስወቅሰዋል እያልኩ አይደለም።ጥቂቶችም ብዙሃኑ ግብር በሚከፍልበት ቴሌቭዥን እርስ በርስ ሲጨዋወቱ መመልከት በራሱ ድራማ ነውና።
በእዚህ ድራማ ላይ ”ይቤ” ገፀ ባህሪ ይዞ የሚጫወተው ወጣት የዩንቨርስቲ ተማሪ ለወጣቱ ምን ያስተምራል? ብዬ ስጠይቅ በገፀ ባህሩ ላይ ባብዛኛው አሁን በዘመነ ኢህአዲግ/ወያኔ አንድ የዩንቨርስቲ ተማሪ የሚኖረውን መልክ ይዞ ታገኙታላችሁ።ይቤ በድራማው ላይ ይጠጣል፣ይቅማል፣የተለያዩ የሴት ወዳጆች አሉት፣የሚናገረው የተደበላለቀ ማለትም ”ከአራዳ አነጋገር” እስከ እንግሊዝኛ የተደባለቁ፣ኢትዮጵያዊነት በሙሉ የጠፉበት ሆኖ እናገኘዋለን።በነገራችን ላይ ይቤ መሃንዲስ ነው እና የነገ ኢንጅነሮቻችን የሚቅሙ፣የሚያጨሱ ናቸው በመሆኑም መስርያቤቶች ከመሃንድሶች ጋር ሲሰበሰቡ የጫት በጀት መያዝ አለባቸው ማለት ነው።
ቤቶች ድራማ ሶስት መስተካከል ነበረባቸው የምላቸው አቀራረብ አይቼበታለሁ
የመጀመርያው በቅርቡ የታየው ነው ታሪኩ እንዲህ ነው።ሁለቱ የቤት ሰራተኞች ቡና እያፈሉ ሳሉ የቤት ጠባቂው ዘበኛ ያገኘውን ዱቄት መሰል ነገር ፍሙ ላይ ሲጨምሩት እና በቤቱ ውስጥ የነበሩት በሙሉ ሲሰክሩ ያሳያል።እንደ ድራማው አገላለፅ ለካ የጨሰው አደገኛ ዕፅ ነበር።ሙሉ ድራማው በወቅቱ ቀጥሎ ያሳየን ነገር ቢኖር አንድ እፅ የወሰደ ሰው ምን እንደሚታየው፣ለምሳሌ ድመት ዘንዶ እንደሚመስለው፣ሰዎች ትልቅ ሆነው እንደምታዩት በተግባር እያሳየ ትውልዱን አሰለጠነ።የሚገርመው ድራማው የእፅን አስከፊነት ሳይሆን አዝናኝነት ነው እስኪበቃን የነገረን።እፅ ያጨሱት በፖሊስ ሲያዙ እና ሲቀጡ ሳይሆን የአደገኛ እፅን አዝናኝነት ለታዳጊ ወጣት ሁሉ ተነገረው።ይህንን የተመለከተ ወጣት ”አንድ ቀን ልሞክረው” እንዲል አድረገው አቀረቡለት።ይህ ክፍል ከታየ ገና ወራት አልተቆተሩም።በአድዋ በዓል ላይ ሸለላችሁ ብሎ ያገደ ፖሊስ ያለው መንግስት በተለቭዝኑ የእፅ አወሳሰድ ስልጠና ሲሰጥ ማየት ያሳምማል።
ሁለተኛው፣ ቤተሰቡ ለሽርሽር ከሄደባቸው ቦታዎች አንዱ ቅዱስ ላሊበላን ያሳየናል።በቅዱስ ላሊበላ ቅፅር ውስጥ በአካል ቤተሰቡ ቆሞ የሚሰጠውን ገለፃ ያዳምጣል።በእምነት ቦታ በመሰረቱ የቀልድ ድራማ መስራት አስቸጋሪ ነው።ድራማው ላይ ግን ሃይማኖታውም ሆነ ታሪካዊ ገለፃ ሲሰጥ በመሃል የፌዝ እና የቀልድ ንግግሮች ይሰሙ ነበር።ይህ እንግዲህ በመሃል ከሚገባው የሳቅ ጋጋታ ጋር አብሮ ነው።የእምነት ቦታዎች የሚሰጣቸው ቦታ እና በአማኙ ዘንድም ሆነ በታዳጊ እና ወጣቶች ዘንድ የሚያሳድረው ተፅኖ ፈፅሞ አልተጤነም።ቅዱስ ላሊበላ ከመጎብኘቱ ባለፈ የከበረ ቀልድ የማይነገርበት ቦታ መሆኑን ማሰብ ተገቢ ነበር።በሌላ በኩል ግን የድራማው አላማ ሀገርህን እወቅ በሁሉም ቤተሰብ መለመድ አለበት የሚለውን ሃሳብ በማንፀባረቁ የሚደገፍ አይደለም እያልኩ አይደለም።ለእምነት ቦታዎች የማይባሉ ቀልዶች ቀላቀለበት እንጂ።
ሶስተኛው የድራማው አቀራረብ የገጠሩን የሀገራችንን ገበሬ ለከተማው ወጣት የሚስልበት የተሳሳተ አቀራረብ ነው።የቤቱ ዘበኛ ሁል ጊዜ እንቅልፍ በጣም ወዳጅ፣ምግብ የሚወድ፣ሥራ የማይወድ እና ግዴለሽ አድርጎ የሚስልበት ገፀ ባህሪ የኢትዮጵያን ገበሬ ፈፅሞ አይወክልም።የኢትዮጵያ ገበሬ እንቅልፍ የለውም ከማለዳ እስከ ምሽት ሲለፋ ውሎ ማታ የቀረውን ሥራ በመስራት የሚጠመድ፣ንቁ፣በሥራ የሚያምን፣ላመነበት የሚሞት እና ለወዳጁ ሟች ነው።ይህንን የህብረተሰብ ክፍል ነው እንግዲህ ለሕዝቡ ”ሎሽ ማለት ብቻ የሚወድ” ተብሎ የሚቀርበው።ይህ በእራሱ ከቀልድ ባለፈ ብዙ ማህበራዊ ነገሮችን የሚነካ ነው።በኮሜዲ ፊልሞች ላይ ገፀ ባህርያት የተለያዩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን እያነሱ ያስተምራሉ እንጂ በኢትዮጵያ ገበሬ ላይ የሚሳለቅ አቀራረብ ይዘው እና ከገበሬው የምንማረው እንቅልፍ ብቻ የመሰለ አቀራረብ ማንንም አይጠቅምም።
እዚህ ላይ የቤቶች ድራማን አንዳንድ ግድፈቶች እና ማስተካከል የሚገባቸውን አቀራረቦች ላይ ሃሳብ ለመስጠት ፍለግሁ እንጂ በደፈናው ድራማውን ለማጣጣል እንዳልተነሳሁ ይታወቅልኝ።ድራማ ከአዝናኝነቱ ባለፈ ወጣቶችን በስነ-ምግባር፣በሀገር ፍቅር ስሜት እና በቅን ለሀገር መስራትን የሚያስተምር ካልሆነ በሳቅ ማንከትከትን ብቻ አላማዬ ብሎ ከተነሳ ስለ እፅ አወሳሰድ የሚያሰለጥነን ከሆነ አደገኛ ነው።ላሰምርበት የምፈልገው ለሕዝብ የሚቀርቡ ድራማዎች በተለያየ ሙያ ላይ ያሉ አማካሪዎች ያስፈልጋቸዋል።ደራሲው ”ህዝብን ካሳቀ እና መንግስትን እስካላሳቀቀ ድረስ መንገዱ ሰላም ነው” በሚል አስተሳሰብ ብቻ አየር ላይ ማዋል የለበትም።
”ሞጋቾች” ድራማ
ከእዚህ በአንፃሩ በ”ኢቢኤስ”ቴሌቭዥን የሚቀርበው ”ሞጋቾች” የተሰኘው ድራማ ጥሩ፣አስተማሪ እና ትውልድን የሚያንፅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።ሞጋቾች በአንድ ሆስፒታል ውስጥ የሚሰሩ የህክምና ዶክተሮች እንዴት ህዝባቸውን በታማኝነት እንደሚያገለግሉ እና በማህበራዊ ኑሮአቸው ውስጥ የሚገጥማቸውን ተግዳሮት ያሳያል።የሞጋቾች ድራማ በፊልም አቀራረፅ እና የድምፅ ጥራቱ ብቻ ሳይሆን የመረጡት ሆስፒታል ተራው ሕዝብ የሚገለገልበትን እና እታች ያለው ሕዝብ የሚላቸውን አባባሎች፣ስሜቶችን ሁሉ የሚያንፀባርቅ አቀራረብ ይታይበታል።እዚህ ላይ ማስታወሻዬ አጭር ከመሆኑ አንፃር ባጭሩ ”ሞጋቾች”ድራማ ሶስት ነገሮችን ለአዲሱ ትውልድ እንደሚያስተምር ጠቅሼ ሃሳቤን ልግታ።
1/ ተምሮ በሀገር መስራትን እና ወገንን ማገልገልን
በድራማው ብዙ ክፍሎች ላይ የሚታዩት አቀራረቦች በዶክተር ደረጃ ያሉ የህክምና ባለሙያዎች ምን ያህል እታች ላለው ሕዝብ እንደሚጨነቁ እና ኃላፊነት እንደሚሰማቸው ያሳያል።
2/ የዩንቨርስቲ ሴት ተማሪዎች ጥንቁቅ እንዲሆኑ ይመክራል
የድራማው ዋና ገፀ ባህሪ በአንድ ወቅት የዩንቨርስቲ ተማሪ ሆና ሳላ አንድ ምሽት በተፈጠረ የምሽት ዳንስ ይመሽባትና ከሰው ቤት ታድራለች።ሆኖም በእዚችው ምሽት ተደፍራ ልጅ ትወልዳለች።ድራማው ባብዛኛው የወለደቻትን ልጅ አባት በመፈለግ ስትደክም ያሳያል።ይህ አሁን ላሉት ወጣቶች እያንዳንዱ ምሽት የምትሰራ ስህተት እና ከዋልጌ ተማሪዎች ጋር መግጠም የሚያስከፍለው ዋጋ ለአመታት የሚተርፍ መሆኑን ያሳያል።ይህም በተለይ ሴት ወጣቶች ጥንቁቅ እንዲሆኑ ይመክራል።
3/ በአንድ ወቅት ችግር ቢያጋጥምም መልሶ መነሳት እንደሚቻል ያስተምራል
የድራማው ዋና ገፀ ባህሪ ባንድ ወቅት ተደፍራ ልጅ ለመውለድ ተገደደች።ሆኖም ተመልሳ ጠንክራ በመማሯ ዛሬ ለህክምና ዶክተርነት በቃች።ይህ በራሱ የሚያስተምረው ትምህርት አለ።ወጣቶች ስህተት ላይ ሊወድቁ ይችላሉ ግን ከስህተታቸው ተመልሰው እንደገና ተነስቶ ለቁም ነገር መብቃት ነው ዋናው ቁም ነገር ይለናል የድራማው መልእክት።
ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ድራማዎች የረቀቀ የፕሮፓጋንዳ መስርያ አውድማ ወይንም የተበላሸ ትውልድ ማፍርያ ማሽን እንዳይሆኑ በስድስተኛውም የስሜት ህዋሳችንም መቃኘቱን አንርሳ።
ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
የካቲት 26/2007 ዓም (ማርች 5/2015)
The post የቴሌቭዥን ድራማዎች በስድስተኛውም የስሜት ህዋሳችንም መቃኘቱን አንርሳ; የትኞቹ ያስተምራሉ? የትኞቹ መታረም ይፈልጋሉ? ”ቤቶች” እና ”ሞጋቾች” ድራማ appeared first on Zehabesha Amharic.