Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ነፃነት በቬሎ –በሠረገላ¡ ይቻል ይሆን? -ከሥርጉተ ሥላሴ

$
0
0

ከሥርጉተ ሥላሴ 30.03.2014 / ሲዊዘርላንድ ዙሪክ

በዬጊዜው እያሰገረ የሚነሳ ግርሻ መልስ ይሰጥበት ዘንድ ከህሊናዬ ጋር ተስማማሁ።

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ)

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)

ትናንት ዕለተ  ሰኞ 02.03.2015 ከፀሐፊ አቶ ክንፉ አሰፋ የተጻፈ ጹሑፍ አነበብኩኝ። ሚዛን የሚዳፋ ስለነበር ማንበብ፣ ማድመጥ ብቻ ሳይሆን አስቀመጥኩት። በመንፈሴ ባንክ። ከዚህ ባሻገር ከቀደሙት ሶስት ጹሑፎች በመነሳት የሚሰማኝን ከመግለፄ በፊት ከመጨረሻውና ከአራተኛው ሃሳብ ከጸሐፊ አቶ ክንፉ አሰፋ ልነሳ ወደድኩኝ። የሌሎችን ጸሐፍት በጥቅሉ እሄድበታለሁ። የማከብረውት ፀሐፊ አቶ ክንፉ ለመሆኑ ሱዳን ለኢትዮጵያ ምኗ ነበረች? አጋጣሚ ጠብቃ ለማጥቃት የማትዘናጋ የጉሮሮ አጥንት ነበረች። ነገር ግን በዘመነ ደርግ ሥርዓቱን የተጠላ ሁሉ የመሸገው ሱዳን ነበር። ሱዳንም የተፈለገውን ሁሉ ከአቅሟ በላይ አድርጋ ከብክባ ጎጆ አውጥታ አሁን ያለውን ምስቅልቅል ሁኔታ ሸልማናለች።

ወደ እለታዊ ኑሮ ስንመለስ ቀለል ያሉ ምሳሌዎችን ላንሳለዎት እንሆ ወደድኩኝ። በአንድ የህክምና ማዕከል ውስጥ መሳሪያዎች የጋራ ግን የተለያዩ ሃኪሞች በተለያዩ ህመሞች ልዩ ስልጠና ያደረጉ ይኖራሉ። አንድ በሽተኛ ወደ የወል የህክምና ማዕከሉ ሲሄድ ቀጥ ብሎ የሚሄደው ለህመሙ ቀጠሮ ወደ ሰጠው ሃኪም ይሆናል። ለበሽታው ኃላፊነት ከሚወስደው ሃኪም፤ ይህ ማለት የዓይን ከሆነ – ከዓይኑ፤ የጨጓራ ከሆነ — ከጨጓራው፤ የሳንባ ከሆነ ከሳንባ፤ ለራዲዎሎጂ ብቻ ከሆነም እንዲሁ። …  ሌላም ምሳሌ ልስጥ ፈርማሲ መዳህኒት ሊገዛ ሲኬድ ፈውስ የሚሰጡ፤ የሚያስታግሱ በርካታ መዳህኒቶች በብዛት ተደርድረዋል። እርሰዎ የሚገዙት ግን ለሄዱበት ጉዳይ ትእዛዝ የተሰጠበትን ወረቀት ሰጥተው መፈወሻውን ወይንም ማስታገሻውን ተቀብለው ይመለሳሉ እንጂ ያዩትን ሁሉ መዳህኒት አይሸምቱም። … አሁንም ሌላ ተጨማሪ ላንሳ … አንድ የገብያ አዳራሽ ይሄዳሉ የዓለሙ የምርት ውጤት ሁሉ ያለበት ነው። ሱቁ ምስቅልቅል ብሎ እደሳ ላይ ሊሆን ይችላል፤ እርሰዎ የሄዱት ግን አንድ የትራስ መብራት ከሆነ ያንኑ ገዝተው ይመለሳሉ፤ ሌሎችም ጉዳዮች ካሉበዎት የሚፈልጉትን ብቻ ይገዛዛሉ እንጂ የጭነት መኪና ተከራይተው ዓይነዎት ያዬውን ሁሉ ካልገዛሁ ብለው እንደማይገለገሉ እርግጠኛ ነኝ።

በሌላ በኩል ኃያላን መንግሥታትም ለኢትዮጵያ ቅን አስበው አይደለም የምንሰደድባቸው። ቁጭ ብድግ ብለን መኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ወድቀን እምንነሳው …. ቀን ለማሳለፍ ነው። አበው „የሚያልፍ ዝናብ አይምታህ ይላሉ“ ከዚህ አንፃር ይዩት ያቀረቡትን ትንተና። እኛ መጠጊያ ቢስ ነን። በሀገራችን በኢትዮጵያ የተሰደድን ውጪ ሀገርም ስደተኞች። ስለዚህ  መነሻችን ሆነ መዳረሻችን  ለእኛ ችግር ከቀረበው ጉዳይ ጋር በሚያያዙት መስመሮች ብቻ ነው አትኩሮት አድርገን ቀን ለመሳለፍ ጥግ የጠዬቅነው ….. እሺ  የእኔ ክብር።  ምርጫ የለም ማለት የለማኝ ተጓዳጅ አንሁን ማለት ነው። ጹሑፎዎት „ሰው መሆንን“ የሚጠይቅ ጉልበታም ስለሆነ መንፈስን አብዝቶ ይሟገታል። ነገር ግን ዛሬ ውጪ ግቢ ነፍስ ላይ ላለ ብሄራዊነት ለነፃነት ትግሉ ጠረን የሚመቹትን፤ ከጠላትን ሴራ ጋር የማይተባበሩትን ነጥቦች ላይ ማተኮሩ የነፃነት ትግላችን አቅም ፈተና እንዳይገጥመው ብቻ ሳይሆን አቅማችንም አይሻማም። በንፋስ ምችም ዝቅ ሲል ብሮንካይት ከፍ ሲል አስማ አያጠቃውም። ልብ ያለው ሸብ። ዋጥ አድርጎ የሚቻል በሽታና መከራ አለ። ስደተኝነት የስጋት ጥገኛ ነው። ነገም እንዳነሷቸው ዓይነት የወገን ጥቃቶች ኤርትራ ላይ ሊኖሩ እንደሚችሉ ይሰቡ እባከዎትን፤ በትሃ ጠጅ /አፍለኛ/ አይመረጠም ስለምን? ሆድ ስለሚነፋ፣ አፍለኛ እንጀራም እንዲሁ፤ ስለምን? ማር – ማር ስለሚል፤ ጀርባውም የእንጀራነቱን ቀለም ስለሚነሳው ከወጥ ጋር ስሙሙ ስለማይሆን። ስለዚህ ለአፍለኛ ጠጁም ሆነ እንጀራው ቀን ይተከልላቸዋል። አረብ ሀገር ወገኖች ይተማሉ። ከሞት ሸሽተው ወደ አልታወቀ ሞት፤ ሀገር ቤት የነፃነት ትግሉ ፓርቲዎች ከገዳያቸው – ከሚያሳድዳቸው፤ ከሚያሥራቸው ጋር አብረው በተፎካካሪነት ለመስራት ይተጋሉ፤ ከማህላቸው ተጠቂ እንዳለ አውቀው ይቀጥላሉ – በትጋት። ወያኔ የበጎ ህልም ጠላት እንደሆነ ጠፍቷቸው አይደለም በመከራ ውስጥ ኩራዝን ለማግኘት አሳር እንዲረማመድባቸው ፈቀዱ፤ ስለሆነም ፍላጎትን በማፍታታ ቀንን መተርጎም ግድ ይለናል።

አሁን ከሳምንት በፊት ወደ ጨርስኩት ሃሳብ ልመለሳችሁ። ከአንድ ወንዝ የተቀዱ የሚመስሉ ቀለሞችን ዘሀበሻ ላይ በተከታታይ አነበብኩኝ። ሦስት መንትዮሽ። መልካም ነው ሃሳብን ሳያሽጉ እንዲህ እንደ ወረደ በነፃነት መልቀቅ ማለፊያ ነው። የነፃነት ትግሉ ክፍለ አካል በዚህ መንፈስ ይቀጥል ዘንድ ነው ተስፋው ሆነ ራዕዩ። ስለዚህ ወገኖቼ የሚሰማቸውን – የሚያልሙትን ሆነ ተቆርቋሪነታቸውን በሰፊው ሂደውበታል። እንዲህ ፊት ለፊት ተገናኝተን ክርክር ማደረግ ቢቻል መልካም ነበር። ሃሳብና ሃሳብ ተቧክስው ዳኛው አሸናፊው መንፈስ እንጂ የካንጋሮ መሰል ወልጋዳ ሚዛን ባልሆነ ነበር። የሆነ ሁኖ ደንበር ከገፉት ቃሎች ውጪ ያለው መንፈስ ሁሉ ቀና ናቸው ሊያድጉ – ሊዳብሩ – ሊበረታቱ ይገባሉ። በተረፈ አድማጭ መርጦ መሸመትም መከዘንም ስለሚችል ይበይንበት እንላለን እኛ ከዚህ ከኮሽ አይሏ ቤተ – ጸጥታ ተሲዊዝዬ ያለነው ሥርጉተና ብዕሯ ….

ሦስትዮሾችን ደጋግሜ አነበብኩ። አዳመጥኳቸውም። የስሜቱ ድልድይ ያው የወንዝ ልጅነትን ያነባል። ነፃነት በቬሎ -በሠረገላ መንገዱን ጨርቅ ያድርግ ቢባል ከቶ እርግማን ይሆንብኝ ወይንስ ምርቃት። …. አይታወቅም። ለነገሩ ይህ የነፃነት ፍላጎት የሚባለው ሸንኮፉ ወይንስ ዘሩ ይሆን ያለው? …. ችግርን ውጦ፣ ችግርን አርግዞ፣ ችግርን ለመገላገል …. መርዝም ይበላል። አሁን እኔ እህታችሁ አልኳችሁ ዓይኔንም ሆነ ጥርሴን ያመኛል። እንዲያው ቅንጭብ አድርጌ ነው የምነገራችሁ። የጤናው ነገር የዚያን ያህል ነው። እናላችሁ የምር ከዓይኔ ስቃይ የጥርሴ ይሻለኛል። የጥርስን በሽታ የምታውቁት ታውቁታላችሁ የስቃዩን ምጥ፤ ግን ከዚህኛው የስቃይ ምጥ የዓይኑ ይብስብኝ እና ምነው ዓይኔን ትቶ ለዛሬም ሆነ ለሁልጊዜ ጥርሴ ቢሆን እላለሁ። በሽታ ምኑ ይመረጣል?! ዓይንም ጥርስም የዓይን አካል ናቸው። ግን ከበዛው ስቃይ ለአመልም ቢሆን የፋታ ጭላንጭል የሚታይበት ይሻላል በማለት  እንጂ የጥርሱም አይጣል አያድርስ ነው። ዓይንስ አንዱ ብቻ ነው። ጥርስ ግን 32 ክ/ጦር ያለው መሆኑ ብቻ ሳይሆን አዝማቹ ሻለቃ ምላስ አለ፤ ምስለኔው ትናጋም፤ ቁልቁለት ላይ ያለው የክ/ጦ ማዘዣ ጣቢያው ኮ/ ጉሮሮም አለ። ህም መግቢያውስ የደጀ ሰላሙ ሁለቱ ባሻዎች ባለ እርግብ ክንፎችም ቀኝና ግራዎችም እነ ከንፈርም …. ወዮ! … ድድ ድድ ድድ እነሱስ ሁሉም አብረው ነው የሚሾቁት። እነ አንጀትም ይንጫጫሉ ራህብ ፈጀን እያሉ ….  ይህም ሆኖ የጥርሱን ስቃይ እምርጣለሁ። ከልቤና ከእውነቴ ነው የምነግራችሁ። በተለይ ክረምት ዋናውን በር ክርችም አድርጌ ንፋስ እንዳይገባ አድርጌ መሄድ እችላለሁ፤ ዓይንን ግን እንዴት … ሞት ላይ ሆኖ ሠርግ፤ ጉሮሮ ማርጠቢያ በሌለበት ኬክ፤ ከፈን የሌለው ቬሎ፤ አህያ የሌለው ማርቸዲዝ ለሠርጉ ይመኛል። መመኘት መልካም ሆኖ ሳለ ለተስፋ ስንጥር ፈጥሮ እርሃብን ማባበስ ግን … አይገባም። ምን እንዲሆን እንደሚፈለግ አይገባኝም – ፈጽሞ። ይህቺ ቃሏ ጣፋጯ ነፃነት ስትደገም – ስትሰለስ ….“ እንዴት ብዬ ልምጣ ከፈለጋችሁኝ?“ ስትል ደግሞ በሠረጋላና በቬሎ ይሆናል መልሱ። ዘመናይነት በጣም የበዛ። ቅልጣን ነገር ….  ልቅቅ ያለ ይባል ይሆን?  ከጦርነት ምን ይተረፋል? አመድ ብቻ። ግን አማራጭ ከጠፋ ምን ይደረግ? ሞት የናፈቀው ሞትን የሠርጉ ያህል በፆም በፀሎት የሚለምን ፍጡር ምድር ላይ አለን። ጭብጡ። መንገድ ሲጣፋ፤ ጉም ተስፋን ሲያለብስ፤ እረመጡ ከሥጋ አልፎ መንፈስን ሲቀቅል …. ምስጥ ዘርን በዘረኝነት ትእቢት አመድ ሲያደርግ … ዝም ይሻላልን? እንዲያው ዝምም – ህም። ከቶ አንድነት ብሄራዊ ራዕይ ጠቀም ፓርቲ ጠበንጃ ቢያነሳ ሊፈረድበት ነውን?!

ናጋሳኪና ሄሮሽማ /ጃፓን/ –  አሜሪካ፤ ጀርመንና እንግሊዝ፤ እስራኤልና መላ ዓለም ምን እና ምን? ጃፓንና ቻይናስ። ሌላው ይቅርና ምስራቅ ጀርምንና ምዕራብ ጀርመን ምንና ምን ነበሩ? ወዳጅና ወዳጅ እንዳትሉኝ። የቅኝ ግዛት መስፋፋት – እና ተገዢዎችስ? አንደኛውም ሆነ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ሂደቱና ውጤቱ፤ የሶሻሊዝማና የካፒታሊዝም ዘመን ውጊያ ምንድን ናቸው? ኔቶና ዋርሶስ? ….. ዓለም ምህረትን የተማረባቸው፤ ዓለም ለቀጣይ ትውልዱ ቅራኔን ችግሮችን በፈርጁ ፈቶ ሰላምን ለማውረድ ሀሁ የቆጠረባቸው የፊደል ገበታዎች ናቸው። የዓለም አንዳዊነት ሃይማኖቶች ነበሩ ዘመናተ – ስቃዮች ማለትም ልቻል። በዬትኛውም ሁኔታ በደል፤ በደሉን ተከትሎ የሚመጡ ሰቆቃዎች፤ ግፎች ቢደመሩ 8ኛ 9ኛ 10ኛ ሌላ አህጉር ሊፈጥሩ የሚችሉ ዬህዝብ ዬሥልጣኔ ልዩ ማህለቅ በሆኑ ነበር፤ ግን ሆነን? አልሆነም። ዘመን የሚሰራቸው ወይንም የሚገነባቸው ታሪኮች መልካሞችንም ሆነ መልካም ያልሆኑትንም ነው። መልካም ያልሆኑት መልካም ካልሆኑበት ውስጠ – መሠረት ተነሰተው አስተምረው ፍቅርን ማምረት ካልቻሉ ከታሪክ ማህደር መሰረዝ አለባቸው እላለሁ – እኔው። እኔ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ሥልጣን ቢኖረኝ እማደርገው ይሄን ነበር። እራሱ አሁን ያለው የዓለም ክረት ፍጥጫ ከዘመኑ ጋር ቢታይ ባይ ነኝ። ስለምን? ነገ ዓለም ምደረበዳ የመሆን ዕድሏ ሰፊ ነውና …. ስጋት የዓለም ዜጎች የወል መለያ በሽታ …. መሆኑ በአሁኑ አያያዝ አይቀሬ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አካሚውም ተጠቂ ስለሚሆን ፈዋሽ አልባ ትሆናለች – ዓለም።

ከአህጉራችን ተነስተን ወደ አፍሪካ ቀንድ ከዛም ወደ መካከለኛው ምስራቅ አፍሪካ ስንሄድ እኛ ተግተን ልንሰራበት የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ ለአፍሪካ ቀንድ ሆነ ለመካከለኛው ምስራቅ የሰላማ ቀጠና ከማድረጉ ላይ ነው። ዕምነት ካለን የምንመራበት ቁራን ሆነ ወንጌል የተሠራልን ሰውን ሰው አውሬ  እንዲሆንበት ሳይሆን፤ ሰው ለሰው የተፈጠረ የመኖር ሚስጢሩ በመሆኑ የሚጣፍጠውም የሚያመረውን ተጋርቶ ቀጣይ ትውልድን በሰላም መገንባት ከመቻሉ ላይ ነው። አህጉራችን ደሃ ናት። አህጉራችን በድህነት ብቻ ሳይሆን በሥልጣኔ የተጎተተች ናት። የጦርነትም ቀጠና ናት። የአንባገነኖችም መፈንጫ ናት። ይህም ብቻ አይደለም ጥቁር በመሆናችን የወንጀሎች ሁሉ መፈጠሪያ ተደርገንም እንታያለን። ዲሞክራሲ ለእኛ የእንጀራ እናት ተድርጎ ስለሚወሰድ እንደ እንሰሳ ኑረን እንደ እንሰሳ እንድናልፍ ትውልድ ለትውልድ ውርርሱ – ሰቆቃ – ኋለቀርነት – ራህብ – በሽታ – መሃይመነት – ጦርነት -ችግር እንዲሆን ነው፤ እኛ የዛሬ ትውልድ ባለ ዕጣ ፈንታዎች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሰው በመሆናችን ብቻ ቢያንስ ለአህጉራችን ለእማማ አፍሪካ አንድ ደረጃ ከፍ ማለት ተግተን መሥራት ይኖርብናል። እንደ ፍቅር ምን ይመቻል? ፍቅር የመኖር ስበት የግንኙነት ሚዛን ጠባቂ ነው። አፍሪካ እንደ አውስትራልያ አህጉርና ሀገር ብትሆን አታልሙም። እኔ ግን ህልሜ ይህ ነው። እንኳስ የአንድ እናት ጡቶች ኤርትራና ኢትዮጵያ። የበደለ የከፋ የሚማረው እኛ ለማስተማር ስንዘጋጅ ብቻ ነው። ጸጸት የሚወለደው ከምህረት ነው። ከምህረት ደግሞ ትውልድ …. ፍቅር ሰላም ተስፋ ….. የልብ በር ምህረት ነው። ዋናው።

እኛ ባለንበት ትውልድ ከፍ ሳንል ሁልጊዜ ጎሮ ለጓሮ እንዳማን፤ እንደ ሰነጠርን፣ እንደ ተረተርን ቂም ጠንስሰን ቂም ደፍድፍን ቂም ጠምቀን ቂም ዘክረን መኖር ከመቃብር በታች እንጦርጦስ ነው ለእኔ። ሥልጣኔው የፈጠረልን መንገድ ድልድዩ ከቂም በቀል የጸዳ ይቅር ለእግዚአብሄር የሚያስባብል፤ የተጎዳ ተጠግኖ፤ አይዞህ ተብሎ ተደግፎ ነገን ማንጋት ነው። አዛውንትነት፣ ተመክሮ፣ ዕድሜ የትምህርት ደረጃ፣ መሰልጠን ሁሉ ለነፃነት መባተል ቀርቶባቸው ለነገር ድውለት ከሆነ ድካሙ ሁሉ የተቃጠለ ዘመን ይሆናል። ህግ ያጠናውም፤ ፍልስፍና ያጠናውም፤ ስፔስ ኢንጂነሪ ያጠናውም፤ ህክምና ያጠናውም መሬት ላይ ከእኔ ከማህይሟ ጋር እኩል ተሰልፎ አለማወቅን – ጭቅጭቅና ጠብን ፈልፋይ ነገርን ሲያድስ ሲሸነቁር ከዋለና ካደረ ላጠፋው የእውቀት ጊዜ ሆነ ላፈሰሰው መዋለ ንዋይ እንደ ተቃጠለ አውቆ ዘመንን ይቅርታ መጠዬቅ ያለበት ይመስለኛል።  ማደግ በፂም ወይንም በዲግሪ አይደለም። መሸበትም በጸጉር አይደለም። ማደግ ዘመኑ ለፈቀደው ጥያቄ እራስን አመቻችቶ ተዘጋጅቶ መጠበቅና ከራስ መጀመር ነው። አውንታዊነት በራሱ ሰላምና ጤና ነው። አሉታ ደግሞ በሽታ እና ጦርነት ነው። በግልም ኑሮም ቢሆን ጸጋቸው እንደ ተፈጥሯቸው ይሸረሽራሉ ወይንም ይገነባሉ። ግንባታው የታሪክ – የትውልድ – የዘመን – የትውፊት ተጠያቂነት ይመልሳል። ፍርሻው ደግሞ ሀገርም አህጉርንም ያሳጣል። ይህ ደግሞ እንደ ቀለማችን „ባሪያዎች ኒግሮዎች እንሰሶች“ እንደሚሉን ሆነን እንድንገኝ እኛ ፈቅደናል ማለት ነው። ፈርመናል ማለትም ነው።

ትብትብ ሌላውን ጠልፎ የሚጥል ይመስላል፤ መጀመሪያ የሚጥለው ግን እራሱን ነው። እኛ የትውልዱ አባል ስለሆን አልፈንበታል። እናውቀዋለን። ከቤተሰቡ በአንድም በሌላም መንገድ ያልሞተበት፤ ያልተሰደደበት፤ ያለተንገላታበት ሰው በነቂስ አይገኝም። የኛ የትግል ሚስጢር ለዲሞክራሲ ብቻ ሳይሆን ቀዳሚው ከወያኔ ሃርነት ትግራይ ባርነት ነፃ መሆን ነው። ከነፃነት በኋላ ደግሞ ለታላቁ ዴሞክራሲ። ግዴታችን በምድራችን በኢትዮጵያ በአህጉራችን በአፍሪካ ይህ ወጣት ትውልድ ያለበላውን ዕዳ የሚከፍልበትን መጋረጃ ቀዶ እንደ ተፈጥሯቸው ወጣቶች በዘመናቸው፤ ዘመናቸው የፈቀደላቸውን አድርገው ዘመኑንም በፍቅር መምራት ይችሉ ዘንድ ካለስጋት ይኖሩ ዘንድ ማሰናዳት ነበር። ቢያድለን። ለወጣቱ ትውልድ መከራ ሳይሆን፣ ስቃይ ሰይሆን የተረጋጋ ኑሯቸውን የመገንባት ድርብርብ ሃላፊንት አለብን – የቀደምነው። አንድ ትውልድ አለቀ። አንድ ትውልድ እንደ ተናከሰና እንደ ባከነ ወደመ። አሁን ደግሞ በዚህ ይቀጥል ነውን? …. በቀል በበቀል ይተጫጨድ ነውን? የኔዎቹ ክብረቶቼ ከልብ ሁናችሁ ብታስቡት የተሰደዱ ወገኖቻችን ትንፋሻቸው የጠብታ ጥግ ያገኙት ምን የዬት ሀገር ዜጋ ነን ብለው ኬዝ ቢሰጡ እንደሆነ ልባችሁ ያውቀዋል። ኢትዮጵውያን እንኳንስ መኖሪያ ፈቃድ ያላገኙት ያለን እንኳን በስውሩ የወያኔ ሴራ ተባባሪ ሃይላት መቀመጫ አለገኘነም። የሌላ ሀገር ዜግነትን መወሰድም አቅሙ ምን ያህል እንደሆነ አይታችሁታል። ….. ትንሽ እንደ እድሜያችን ሚዛን ይኑረን ….. ፍርድና ዳኝነት ደግሞ ሥልጣኑ የመዳህኒተአለም እንጂ የሰው አይደለም።

በሌላ በኩል የጋዜጠኛ ህጉ ደንበር አልተሰራለትም። አቅም ከኖረ የትም ቦታ የቀለም፤ የድንበር፤ የሃይማኖት ቦታ ሳይገድበው ዕውነትን ፈልጎ ለማግኘት የመረጃ ምንጭ ተግባሩን የመወጣት ሃላፊንት አለበት – ጋዜጠኛው። አይደለም ኤርትራ መሄድ ኤርትራ ላይ ኢሳት፤ ኢራቅ፤ እስራኤል፤ ደቡብ ኮርያ፤ አርንጀንቲና፤ ካሜሩን፤ ማዳጋስካር፤ ሜክሲኮ የኮርስፓንዳንስ ሠራተኛ ቢኖር ነውሩ ምኑ ላይ ነው? እንደገናም የፖለቲካ ጋዜጠኛ እንደ እስፖርት ወይንም እንደ ሞድ ወይንም እንደ ማህበራዊ ወይንም እንደ ሳይንስ  ጋዜጠኛ ሊሆን አይችልም። የሙያው ሥነ ምግባር ሆነ ተፈጥሮው አይፈቅድም። እንዲያውም የፖለቲካ ጋዜጠኞች የደህንነት፤ የህግ፤ የሰብዕዊ መብት አያያዝ ተጨማሪ ሥልጠና ቢሰጣቸው የሙያቸውን ሥነ ምግብር ምን ያደርገዋል? ይመጥነዋል። ማለት ልቅ ሳይሆን በልክ ጊዜን ያደመጠ፤ ወቅትንም ያጠመደ፤ ተስፋን የከበከበ፤ ጥንቃቄ የተካነው ግን ግነት ያልዘፈነበት ያደርገዋል። ወሳኝ ጥያቂዎች ዘመኑን የሚንዱ ከሆኑ፤ ለዘመኑ ትርፋማ ካልሆኑ መዘለል አለባቸው። ይህ ስልጠና ሲወሰድም አበክረው መምህራኑ የሚገልጹት ነው። በሌላ በኩል ሰው መብት አለው የሚፈልገውን የመወሰድ ወይንም የመተው። ማን በግድ ተሸከም ብሎ ያስገድደዋል። ለዛውም በብዙ ሁኔታ በህይወት ተቆርጦ ለተሄደበት ጉዞ ሃጢያቱ የኪሎ ማንጃሮ ተራራ ያህል መሆን። ቁስለት! …. ተጠልፈው ለበለሃሰብ ተሰጥተው ቢሆን ደግሞ ውዳሴው ድርሳን ይጻፍላቸው ነበር። ፎቶው ዝክረ ማህደር ይሆን በነበረ …. ተዛነፍ ፍላጎት – ነፃነትን የማለም አቅሙን እዩት – ቀጭጮ ታቱ ሲል …. ይቅር ይበለን አባቴ።

አንድ ጥግ ላጣ ተማላ ዜጋ፤ መሬት ላጣ ሥጋና ደም፤ ውሃ ጠምቶት ሲጠወልግ ቀና አድርጎ በአፉ ምራቅ ያረጠበ ማንም – ምንም ይሁን ለእኔ ጻድቅ ነው። ለነፃነት ካለ ደሞዝ በነፃ ወጣትነቴን፣ አዛውንት ወላጆቼን፣ ናፍቆቴን ኢትዮጵያን ትቼ ወይንም የኑሮ ጣዕሜን ሁሉ እሰጣለሁ ብሎ ለቆረጠ ጀግና ትንፋሽ ቢያጥረው፤ ቢቆስል፤ ተስፋ ቢያጣ ሜዳ ላይ በአፉ አፍንጫውን ምጎ ትንፋሽ የሚለግሰው ለእኔ የነፃነት ረሃቤ መልካሜ ነው። የጨነቀው፤ የቸገረው፤ ማጣፊያው ያጠረበት፤ መብራት የሌለው፤ የሀገር – የቦታ – የምቾት ሆነ የሰው ምርጫ ጥያቄው አይደለም። ለዛውም የሚያማርጡበት በሌለበት ሁኔታ። አንድ ነጭ ከመንገድ አግኝታችሁ አንዲት ከሚያወቃት ኢትዮጵያዊ ቋንቋ ያናግራችሁ። ምን የሰማችኋል? የሀገር ናፍቆት – ሰቅሰቅ አድርጎ ከአብራክና ከማህፀን የሚያስለቅስ ሰቀቀን ያለባችሁ ወገኖቼ። ዕውን በእውኔ ነውን? የሀገሬ ጠረን በዬት መጣ ብላችሁ ክፍትፍት ባደረገው፤ የስደት ንፋስ ብጥርቅርቅ ባደረገው መንፈሳችሁ ውስጥ አዲስ ሰናይ አይሰማችሁንም?! እኔ እውነቱን ብናገር„ በርቀት የቡናውን ጭስ ሸተትን፤ በርቀትም ሁመራ ማርያምንም አዬን። ሰቲት ሁመራ ሀገራችን ግን እንድንረግጣት ያልተፈቀደችልን“ ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን …. እኔ አለቀስኩኝ። እናቴ ተስላ ዬልቧን ያደረሰችላት ሁመራ ማርያም፤ ጀግና አርበኛ አባ ሻንቆ መለሰ ኃይሉ ከአርበኝነት መልስ ዬኢትዮጵያን ሰንድቅ ዓላማ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ከፍ አድርጎ በማህል አናቷ ሰቲት ሁመራ ላይ ያውለበለበባት፤ የአባቶቼ የቅድመ አያቶቼ አጽም እርስት፤ እኔም ለአቅመ ህይዋን ስደርስ ሄጄ ወገኖቼን ያደረጀሁባት ቦታ የትናንት የጎንደር ክ/ሀገር የዛሬ የወራሪውና የዘራፊው ዬወያኔ ሃርነት ትግራይ ዘራዊ አፓርታይድ አገዛዝ መፍንጫ ሰቲት ሁመራ – ተከዜ፣ አልፎም አብደራፊ አንዲያም ሲል ኡምናሃጅር ሽው – ውል – ንፍቅ አለኝ፤ ተባረክልኝ አባትዬ በመንፈሰም ቢሆን ለናፍቆቴ ወጌሻ ስለሆንከው …. ኑርልኝ። እና ሠራዊቶቻችን የእኛዎቹ የሀገራቸውን ጠረን በቅርብ እርቀት፣ የቋንቋቸውን ምት ላሂ በውስጡ፤ የባህላቸውን ጸዳል በምልዕት፤ የሃይማኖታቸውን ሥርዓት በተደሞ እንደ እራሳቸው በሚዳስሱበት ቦታ መገኘት አንዱ የመንፈስ ማስያዥ ህክምና ብቻ ሳይሆን መንገድ ጠራጊ እንዲሁም ጠባቂ፤ ከብካቢና አበረታች …. አፅናኝ የማሸነፊያ ኃይል ሰጪ አይደለምን?! ውትድርና እኮ ፈቅዶ ኑሮን ሳይሆን ሞትን በፈለገው ፎርምና ይዘት መቀበል፤ መከራን በድምጸ ሙሉ ውሳኔ በራስ ላይ መጫን ነው። ለዛውም በነፃ መሃያ አልቦሽ። …. እህት – እናት – ወገን – አበልጅ – ትዳር – ልጅ – ጎረቤት በቅርብ የለም። ግን ጣዕሙ አንድ የሆነ፤ ዘመን የለዬው መንትዮሾነት በፈቃደ እግዚአብሄር ሥነ ጥበብ እንዲህ ሲኮን አያጓጓም? ይህ እኮ የሰው  ሥራ አይደለም።

እኔም የእናት አባቴን ልጅ ወንድሜን ሃይልዬን የአጎቶቼ ልጆች ከሁሉም በላይ አብሮ አደጌ የትግል ጓዴ እንግዳወርቅ ተክሌ እንደ ወጣ ቀርቶብኛል። ይግደሉት – ይስቀሉት  – በቁም ከነህይወቱ ይቅበሩት አይተወቅም። እንግዳ ዋሾ ሜዳ፤ አንገረብ መስክ ኮኮች ወንዝ አብሮኝ የቧረቀ አብሮ አደጌ በኋላም ጓዴ ነበር። ዬእንግዳ ቤተሰቦቹ ትግረኛ ተናጋሪ ሲሆኑ ዬዬትኛው ስለመሆኑ አናውቀውም። እድገታችን ጎንደር ኢትዮጵያዊነት ብቻ ስለሆነ። እንጃ ለእኔ ልዩዬ ነበር። ከካኪ አቅም እንኳን የሥራ ልብስ አስቦ ገዝቶ የሚልክልኝ የልቤ አንጎል ነበር። ሌላው ባህርዳር ላይ በአድዋ ድል ዕለት የተወለደው— የባህርዳሩ አድዋስ …. ወፌ እያለ የሚያቀብጠኝስ። እዛው ነበር የቀረው። አድዋ ከህልፈቱ ጀምሮ ቢሮዬን እስከለቀቁበት ድረስ ፎቶው ፊት ለፊቴ ነበር፤ ከቤተሰቦቹም አንድም ቀን ሳልለይ ነበር …. የተለያዬነው። ስለምን? አንቱው ሙሁር እረሱን ለእናቱ የገበረ በላይ ነበርና። እልፍ ጀግኖች ዘመን ከቶ ሊተካቸው የማይችሉ ሳተናዎች …. አጥተናል፤ ይህ ብቻም ሳይሆን ሰማዕትነታቸው ዝክረ ቀብር ተበይኖበታል። አሁን ደግሞ ብሄራዊ ማንነት በተዳጠበት ዘመን የከፋ ችግር ወቅት ላይ ነን። ስለሆነም ችግርን ደፍሮ፣ ችግር ለመቀበል ወስኖ፣ በችግር ምሽግ ለብሰው መፍትሄ ለማፍለቅ፤ በችግር ድቅድቅ ብርሃን ለማዬት በምህረት ጎዳና መጓዝ ምኑ ነው ክፋቱ? የዘመንና እሰረኛውን መንፈሳዊ አኃታዊነት ችለን ይፍታህ ብለን የቅዱስ ሐዋርያውን ጳውሎስ ምግባር ብንወስድ እንጎዳ …. ይሆን?!

ለጥፋቱ ሁሉ የዘመኑ ታዳሚዎች ነንና ሁላችንም ከተጠያቂንት አንድንም። የበርሊን ግንብ ፈርሶ አንድ ያደረገ አምላክ ቢያንስ በገጽ ፍቅርን አቅንተን ፍቅርን ብንሸምት ምን ክፋት አለው? ጥላቻ እኮ ነው ሰላምን የሚያሳጣው – አሳማው። ፍቅር የሰላም ሸላሚ ነው። ሌላው እነዛ ቀንበጦች እነዛ ማገዶዎች ስለ እውነት የመሰከሩ፤ የማንዴላን ዓላማ የተከተሉ፤ የሃይማኖት ነፃነትን የጠዬቁ፤ የሰው ልጆችን መብት በሰላም እንጂ በጦር ሜዳ በሚገኝ ትርፍ መወራረድ የለበትም ጦርነት ከእንግዲህ በቃ ብለው ነጭ እርግብን ያፈኩ፤ ሰላምን በሰላም ብለው የተሟገቱ …. ሁሉንም ሞክረው ግን ቤታቸው በበላያቸው ላይ የፈረሰው የሃቅ ማህደር አገልግል ሲፈታ ምን ይለን ይሆን? „አንድነት“ ሥሙ እንኳን በሽታ ሆኖት የወያኔ ሃርነት ትግራይ ይሄው …. ያላችሁበት ሃቅ ነው። …. ሌላው የገረመኝ ደግሞ ለማመሳከሪያነት የቀረበችው ክብርት ዳኛ ብርትኩን ሜዴቅሳ መሆኗ ነው። ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ያጎናጸፋት መነሻ ቤቷ ቀስተ ዳመና ፓርቲ ነው። ድልድዮዋ ድግሞ ቅንጅት ሲሆን የልቅናዋ እርገቷ አንድነት ነው። ከእውነት ጋር ቡጢ መግጠም ትርፉ ምንም ይመስለኛል፤ የሚቻል ከሆነ አሁንም እኮ መሞከር ይቻል ይመስለኛል። የወንበዴው የወያኔ እግር ብረቱም፤ ዱላውም፤ ስጋቱም፤ መደፈሩም መታሰሩም በተጠንቀቅ ይጠብቃሉ – አሉ። በትጥቅ ትግሉም ቢሆን ኬኒያ፣ ጁቡቲ፣ ሱማሊያ፣ ሱዳን ክፍት ናቸው የሚችል መሞከር የአባት ነው። …… በስተቀር እዬጎረጎሩ – እዬቦረቦሩ የነፃነት ትግሉን አቅም መብላት ወይንም መንፈስን መስረቅ ጥቅሙ ለወያኔ እንጂ የቅንጣት ታክል የነፃነት ትግሉን አይጠቅምም – ወገኖቼ። ለተስፋችን ደመኝነትም ነው። የወያኔ ጀሌዎችና እና እኛ እኩል በአንድ መስመር ከሚያስገቡን ሃዲዶችና ባቡሮች እራስን ማግለል ብልህነት ይመስለኛል –  ቢያንስ ዝም። እኔ በጣም እርግጠኛ ነኝ ሰላማዊ ትግል እያሉ አንድነትን የደገፉ መስለው ግን ጉዳዩን ሲያራግቡ፣ ሲያሟሟቁ – ሲያጋግሉ የነበሩ አካላችን ከፈረሰበት ዕለት ጀምሮ ድራሽ አልባ እንደሚሆኑ ነው የማስበው። ስለምን? ድሮም የእኛ አልነበሩምና። እውነተኛው ቁም ነገር አንድነትንም ወደውት አልነበረም። መሸጎጫ እንጂ። አንድነት ለእኛ ለኢትዮጵያ ሴቶች ለትውልዱ – ትውልዳዊ ድርሻውን የተወጣ የመጀመሪያዋን ሴት የብሄራዊ ፓርቲ መሪ ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳን በአብላጫ ድምጽ የመረጠ ሆኖ የተገኘ የእኩልነት ማርዳችን – ጌጣችን ነበር።  በዐለም ዕውቅና ክብር ያላት ጋዜጠኛንም የፈጠረ። ተወዳጅ ተፈቃሪ መሪዎችን ያስገኘ። ግን ቀጠለን? አስቀጠሉትን? —– ይህን እንቆቅልሽ ከሌላ ጋር ሳይሆን ሁለት ሃሳቦችን ፊት ለፊት አቅርቦ ተጠዬቅ መቀመጥ ያለብን ይመስለኛል። ከሊቅ እስከ ደቂቅ። …. ስድቡም መቆም አለበት። ለዚህ ያልሆነ ሽበት – ጋዳ ነው ገደለ – ነገር። እንደ ዕድሜ፣ እንደ የዕውቀት ደረጃ እኛን መሃይሞችን በመሆን መብለጥ ያለባቸው ይመስለኛል … በፆም ግድፍት የሚያምራቸው ቀደምቶቹ – ደሞቼ።

ሌላው የገረመኝ ነገር። ለኤርትራ ሀገራዊነት ዕውቅና ተሰጠ ብለው የሚተቹ ወገኖች፤ ሰሞኑን የተከበሩ ፕሮፌስር  ተስፋ ጽዮን መድህኔ „“ ይሄውና ኤርትራ ሞተች ትግል ለሀገር ትንሳዔ“  ሲሉ አንድ ጹሑፍ አስነብበውናል። እርእሱ እራሱ „ሀገር“ ሌላ ቦታ ሳይኬድ ዕውቅና ነው። ገራሚው ነገር ኤርትራን እንደ ሀገር ተቀበለ ግንቦት 7 ብለው ናዳውን የሚለቁት ናቸው ፕ/ ተስፋ ጽዮንን ሲያደንቁ የማዳምጠው። እኔ ፕ/ በአካል አውቃቸዋለሁ። መቼም ሥርጉተ ቅመም ናት። 13 የምንቅናቅ /ንቅናቄ/ አንድ የግል ታጋይ በሦስት ቋንቋዎች /በትግረኛ – በአረብኛ – በእንግሊዘኛ/ በተዘጋጀው የጀብሃ መስራች አዛውንታት በተገኙበት ከመላ የዓለም ሀገሮች ብቻ ሳይሆን ከሁሉም አህጉራት የተሰበሰቡ የጀበሃ ደጋፊዎች፤ የሻብያ ተቃዋሚዎችን ጉባኤ በድንቅነት እንዲሳካ ካደረጉት ውስጥ አናቱ ናቸው – ፕሮፌሰሩ። የብቃታቸውንም ጥልቅነት በጣም ከውስጣቸው ነበር የተመለከትኩት። የሰከኑም ናቸው። ኤርትራ አለኝ ልትላቸው የምትችል ብቸኛ ሃብትም ናቸው። የእኔ ጉዳይ በእሳቸው አቅም – የተፍጥሮ ጸጋና ክብረት አይደለም። … አንዱ የሚደቆስበት ተመሳሳይ አመክንዮ ከሌላው ላይ ሲሆን ውዳሴ መሆኑ ነው የገረመኝ። … ሳልጠቅሰው የማላልፈው ሃቅ ግን የ13 ምንቅናቅ መሪዎች በጋራ ከአንጋፋ የጀበሃ መሥራቾች ጋር ስብሰባ በተለዬ አዳራሽ ተቀምጠው ነበር። እኔ ወደ አዳራሹ ስገባ በዛ ጀርጋዳ ቁመታቸው ተነስተው በመጎናጸፊያቸው እቅፍ ያደረጉኝ እንጃ ከአባቴ በስተቀር እንዲህ የሆነልኝ ንጹህ ልብ አልገጠመኝም። አይረሳኝም። በነፃ መሬታቸው መረጃ ቢያስፈልገኝ የምንቀሳቀስበትም ይለፍ ሰጥተውኝ ነበር። በቂ አድራሻም።

ለማንኛውም ዘመናይነት፤ ቅልጣን፤ ዝነጣ፤ ቅንጦት፤ ቅብጥና ቅልጥ ፍለጋ ነፃነትን በቬሎ – በሠረገላ የመመኘት ያህል ነው ለእኔ። ከሁሉ የሚከፋው ቀውስ የጎሳና የሃይማኖት ነው። በሁለቱም የተሰቀዘች ሀገር ላይ ሆነን እንደ ሃላፊነታችን ለቀጣዩ ሀገር እሰከ ዓይን ጥርሷ የማስረከብ ብሄራዊ ሃላፊነት እያለብን ግን ….?  ….. ዛሬ ስለቀረ ነው እንጂ ኤርትራና ኢትዮጵያ ከሀ እስከ ፐ ታላቅ ብሄራዊ ጉባኤ ላይ ተከታታይ ወርክሾፕ ሆነ ፓናል ዴስከሽን የማደረግ አቅም ነበረን። የማይታዋቅ ታሪክም፤ ያልተሰለጠነበት የፖለቲካ ዘርፍም አልነበረም። ሌላው ቀርቶ በዬሶስት ወሩ ይታተም የነበረው የፓርቲዬ የኢሠፓ ልሳን አካል „መስከረም“ መጽሔት እራሱ ተቋም ነበር። ለዚህ መሰሉ ታሪካዊ ትንታኔ አዲስ አይደለንም። እንኳንስ ተጫማሪ ኮርሶች ታክለው … ግን ዛሬ ላለብን የፋመ ረመጣዊ ችግር ይጠቅማልን? ነፍሰ ጡር ወገን አስፓልት ላይ፤ ቅድስት መነኩሴ አስፓልት ላይ፤ የገዳማት አበው በገዳማቸው፤ ሼኮች በመስጊዳቸው፤ ገበሬዎች በማሳቸው፤ ወጣቶች በገደል በቤንዚን እራሳቸውን በሚገድሉበት መራራ ዘመን ላይ፤ ወገኖቻችን ስቃይን እንደ ስቅለት ዕለታዊ ትንፋሻቸው በሆነበት ሁኔታ ላይ ብርንዶ፤ ጠጅ፤ ቁርጥ ያሰኘናል ለነፃነት ትግል —- ወይንስ ድንኳን ወይንስ ዲል ያለ ድግስ በአዳራሽ? ፍ – ቱ – ት —-

ለመሆኑ „የኤርትራ ጥያቄ እስከመገንጠል የማን ቅኝት ነበር“ ሌላም ሱማሊያ ኢትዮጵያን ገዝታ ብትሆን ምን እንመስል ነበር? የባድመ ጦርነትም ጊዜ ሻብያ እንዲቀጥል ያበረታታ አቋም ነበር „በወያኔ ጉድጓድ ሄዶ መሞት አይገባም“ የሚል። ሻብያ ባይገደብ ቢቀጥል ሚኒሊክ አደባባይ ሰንደቁን ቢያውለበለብ ተጨማሪ ከ74000 ዜጎቻችን በላይ ንብረት ቢወድም ዛሬ ያለው አቅማችን ምን ይመሰል ነበር? ገለጻውን በስማ በለው አልነበረም የሰማሁት እኔ ቁጭ ብዬ ፊት ለፊት ነው  የስብሰባው ታዳሚ ሆኜ ያዳመጥኩት። ለዛች ቅጽበት መርሁ ገዳይ ነበር። ለነገሩ አድማጭም አልነበረውም። ዛሬ ደግሞ ከጠላታችን ጋር ተወገነ ተበሎ ሌላ ጨዋታ …. ለመሆኑ ይህ ሃቅ ብቻውን በመጸሐፍ አሳትሞ የህዝብን መንፈስ በሃቅ ወተት መገንባት አያስችልምን? ምን ሲገድ … ግን ለዛሬ ይጠቅማልን? ይፈይዳል? ብናኝ ዕሴት አለውን? ከብጥብጥ ከአንባጓሮ ከመካሰስ በተረፈ ለዚህ በአናቱ ወያኔ ላንጠለጠለው ኢትዮጵያዊነት መኖር ይሆናል? አቻው ነውን? ቁስል እዬቀራረፉ መግል ማዝነብ ድምሩ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ሸኮናን ወይንም ዳልጋ ማድለብ ብቻ ነው የሚሆነው።

ስለዚህ የሚጻፋው በሉት፤ ፕሮፖዛል በሉት፤ ቃለ ምልልሱ በሉት ከላፍኩበት ህይወት ውጪ አይደለም – ለእኔ። ተዛነፉን በመሰሉና በልኩ በተሳፋ ጠርቦ ማስተካከል ይቻላል። ግን ለዛሬ ያ ሚዛን ጠበቂ ትንታኔ ጠቃሚ ነውን? ያ አቋም የወያኔ ንደት ያባብሰዋል ወይስ ይደግፋዋል – ኢትዮጵያንስ እንደ ሀገር ህዝብንም እንደ ማህበረሰብ ያድናልን? …. እእ …. ለወቅቱ የሚስማማ የአቅምን ድምጽ ማድመጥ ነው ብልህነት። የለማኝ ተጓዳጅ መሆንም አይገባም።  ውዶቼ – የኢትዮጵያን ህዝብ ብልህነት ህግነት፣ እውነትነት፣ ጥልቅነት በግልቡ አንዬው። ከእኛ በላይ ህይወቱ ዩንቭርስቲው ነውና ….. መምህራችንም ነው። እንክርዳድን – ከስንዴ፤ ፍሬን – ከገለባ የመለዬት አቅሙም አንቱ ነው። ይልቅስ እኛ ያለብን ግርድፍና ሽርክት ቁንጥንጥ ፍላጎቶች ገርተን ወይንም መልክ አስይዘን ለራህቡ እንድረስለት። ምስጋናውን ቀርቶ ቢያንስ በብልህነት ወቅቱን እናዳምጥ። በትውፊታችን የምናውቀው …. የማይቻል መከራ ለሌላው ሳይነገር እሬሳ ታቅፎ፤ ዕንባ ታምቆ፤ ብዙ ቀናት ከውርዴት ወይንም ከመጋለጥ የሚያድኑ መሰናዶዎች ይከወናሉ። ያዬነውም የሰማነውም ከቤተሰቦቻችን ትውፊቶች እነኝህን ይመስሉ …. ነበሩ። እባካችሁ ክብረቶቼ እናስተውል – ፉከራ አይደለም። ከልብ እንሁን፤ በፍላጎታችን ውስጥ መኖር ብቻ ሳይሆን የፍላጎታችን ስኬታማነት ሥነ – ህግጋትን እንመርምር ለማለት ነው። የብዕር አካላዊ እንቅስቃሴዎች የነፃነት ትግሉ ክንድን የሚያጠነክሩ እንጂ የሚያዝሉ መሆን አይኖርባቸውም – ፈጽሞ። ደግሞስ መጎረጃው መቼ ነው ይሆን የሚያቆመው?! ግንቦት 7 ከተፈጠረ ጀምሮ ይሄው ነው። ሌላ ተግባር ብንከውን ምን አለ? ሁልጊዜ በአንድ ፓርቲ ላይ ናዳ መለቅቅ … ለምን? ግራ ነገር። ማገርሸት – ማገርሸት – ግርሻው ደመ ከሴ ቢፈልግ ይሻለው በነበረ። የሆነ ሆኖ የማይጥመው አለማድመጥ – አለመተባበር – የራስን ተግባር በራስ ምርጫና መንገድ በበለጠና በቀደመ ሁኔታ መከወን … በቃ! ለነገሩ ከነፍሳቸው ያልተፈጠሩ አጀንዳቸው በራሳቸው ጊዜ ይከስማሉ …. አድራሻ አልቦሽ —- ናቸውና።

የጓጓለ ስጋቴን በተሰፋማ ዕይታ …..

  1. እንደ ድርጅት ሻብያ፤ እንደ መሪ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መፈንቅለ መንግሥት ቢደርስባቸው፤ ፓርቲያቸው ውስጥ አንጃ ቢፈጠር፤ ወይንም በሌላ ድርጅት – ድርጅታቸው ቢጠቃ እንደ ሰውም ቢያልፉ፤ የሥርዓት ለውጥ ሊመጣ ቢችል የኛዎቹ ተጠባባቂ ቦታ ብቻ ሳይሆን በአጭር ጊዜ ሠራዊቱን ከነንብረቱ ቦታ የማስለቀቅ ሁኔታን ቀድሞ ሊታሰብበት ይገባል። ከሥር ተከታታይነት አቅም ያለው ጣምራ ሥራ ሊሠራበት ይገባል እላለሁ።
  2. ሻብያ ከወያኔ ሃርነት ጋር ቢስማማስ? መጥፎዎችን አስቦ መዳህኒት አዘጋጅቶ በተጠንቀቅ መጠበቅ ያተርፋል እንጂ አያከስርም። በዚህ ዙሪያም የኢትዮጵያ ነፃ አውጪ ሠራዊት ኤርትራን የመልቀቅ ግዴታ ቢኖርብት መሸኛኘቱ በእኩልነት ላይ ተመስርቶ በምስጋና እና በፍቅር ይሆን ዘንድ ቅድመ ድርድርም ከሻብያ ጋር ማድረግ ይገባ ይመሰለኛል።
  3. ቃለ ምልሱን እንዳደመጥኩት ጭብጡ ጎጠኝነት ለኢትዮጵያዊነት አይበጅም ነው። እሰዬው ያሰኛል። ታዲያ ይህን መንፈስ ወደ ተግባር የመቀዬር የቀረበው መስመር ያለው በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እጅ ነው። በህግ ባያፈርሷቸውም ይህን ቀና መንፈስ በጎጥ ከተደራጁት፤ ድጋፍ በቀጥታ ከሚያገኙት አካላት መሪዎች ጋራ ቁጭ ብለው መከረው፤ ሰባራ ሰንጠራውን ደፍነው ወደ ብሄራዊነት ለማምጣት የቤት ሥራውን ሆነ ሃላፊነቱን ቢወስዱት መልካም ይመስለኛል። የመገንጠልን ሆነ በጎጥ የመደራጀትን ትርፍና ኪሳራ ከራሳቸው በላይ በህይወቱ የኖረ የለምና። „ታሪክ የለኝም“ ሲሉ አዳምጫለሁ። ምን አልባት በዚህ ዙሪያ በሚወስዱት ንጡር እርምጃ ታሪካቸውን ጸሐፊ ያገኝ ይሆናል።
  4. የጎጥ ድርጅት መንፈሶች በፍሬው ትንተና ሲኬድባቸው በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ጎጡ ሳይሆን፤ በጎጡ ውስጥ ነው ኢትዮጵያዊነት ያለው። ይህ ማለት ኢትዮጵያዊነት ደረጃው ከጎጡ በጣም የወረደ ነው። ስለዚህ ለነገ ጠንቅ ነው። ከዚህም በላይ ከእንግዲህ በኋላ የጎጥ መንፈስ አመክንዮ ዓለም አቅፍ ዕውቅና ድጋፍ አያገኝም። የአንድነት ሃይሉ ሥነ ልቦና ድል ላይ ነው በዓለም ዐቀፍ ደረጃ። በመሆኑም መሳሪያ ካነሱት ውስጥ ለዚህ ሃሳብ ቅርቡ የነገ የተስፋ ጥንስስና ጥግ አርበኞች ግንቦት በመሆኑ በመንፈስ፣ በአካል አጠናክሮ ከጎጠኞቹ አቅም ጋር የሚመጥን የግንባታ ሂደት መኖር ያለበት ይመስለኛል። በስተቀር ለነገም ጥላሸት የሚያመነጩ፣ ተስፋን የሚፈታተኑ ሁነቶች ጎልተውና ጉልበታም ሆነው ከወጡ አንጻራዊ አደጋ ሊኖረው ይችላል። ስለዚህ በኢትዮጵያ ሰንድቅዓላማ ሥር የተሰባሰቡት ካለ ጥያቄ፤ ካለ ቅድመ ሁኔታ በወጥ ፍላጎት ሥር መሰባሰብ አለባቸው ባይ ነኝ። ለዚህ ቀዳሚው የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር አብሪ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። የፕሬስ + የስፖርት ጋዜጠኛው ሆዅተ ብርሃን ጌጡ „የአፋሩ ቅኔ በእኔ ቅኝት“ የረቀቀ ሚስጥሩን በቅኔ ሲዘርፈው ይህን ማለቱ ብቻ ሳይሆን ከዚህ የዘለቀም ትርጉም አለው። ኢትዮጵያን ያለ ከአሸናፊው ማንነት ጋር መወገን አለበት ነው ሚስጢሩ። በተረፈ መሆንን በመከራ ሰሞናት የተረጎመውን የቀድሞው አንጋፋው ዬአርበኞች ግንባርን አመሰግናለሁ። መመካት ባይኖርም ኮራሁባችሁ። የተከበሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሲታሰሩ ባወጣችሁት ፈጣን መግለጫ ከሥሩ ያልኩት ነበር – ሁናችሁ አሳያችሁኝ።

ስንብት ይሁን መሰል። ወጣቱ ትውልድ በህይወት ያሉ እውነታዊ ምስክሮችን አይቶ የነፃነት ትግሉን በአቅም – በጉልበት – በመንፈስ – ሥነ ህሊናውን ሳይቀር ሸልሞ ዝንቅና ቅጥ አልቦሽ ሃሳቦችን ቀብራቸውን ማወጅ አለበት። እኔ ተማሪ እያለሁ „አትማሩ“ የሚል መርህ ነበር። „አትማሩ መርህ“ 40 ዓመት ለሥልጣን አልበቃም። 40 ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያ ያሉ የት/ ተቋማት፤ ዩንቨርስቲዎች፣ ኮሌጆች፤ ተቋማት፤ ቢዘጉ ኢትዮጵያ ምን ትመስል ነበር? በሙያው ይተዳደሩ የነበሩት ቤተሰቦችስ አዳራቸው ምን ይሆን ነበር? የኔ ጌጦች በተለይ ወጣቶች አስቡት። ስለዚህ በሰላማዊ ትግሉም ዘርፍ ቢሆን አሸናፊውን ማንነት ይዞ ወደ ተሰለፈው መትመም ግድ ይላል። ወደ ሰማያዊ ክተት ማለት ይገባል። በተረፈ ቀደምት ሰማዕታት ጀግኖቻችን አርበኞቻችን በአትዮጵያ ምድር ጦር፤ በባህር ኃይል፤ በአዬር ኃይል ተሰልፈው ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዕላዊነት የተሰውት ጀግኖቻችን ከንክብራቸው – አንረሳቸውም። ቀን ሲያልፍ ሁሉም ይሆንላቸዋል። የሚመረውም እያንገሸገሸው እንዲውጠው – ይገደዳል። ይህ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ የዜግነታችን የክብር ቀን ነውና። እያያችሁት ነው የሚጸዬፉት ስልጡኑ አማርኛ ቋንቋ ግራ ቀኙን እንዴት አሳምሮ አንበርክኮ እዬገዛ እንዳለ። ኢትዮጵያዊነት ሄኖክ ኢትዮጵያ ደግሞ አላዛር ናት። እግዚአብሄር ይስጥልኝ ዘሃበሻ ማህበራዊ ድህረ ገጽ – ኑሩልኝ። ለጹሑፌ ወርቅ ታዳሚዎችም መሸቢያ ሰሞናት ተመኘሁ – ከመንፈሴ ብሌን።

ቂም በቀል ዘር አክሳይ፤ ምህረት የርትህነት ውስጠ – ሲሳይ! የሥልጣኔም ስንቅ አቀባይ።

ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ከበቂ በላይ ነው!

ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ፤

ትውልዳዊ ድርሻችን በህብረትና በአንድነት እንወጣ!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ ኑሩልኝ – የኔዎቹ።

 

The post ነፃነት በቬሎ – በሠረገላ¡ ይቻል ይሆን? -ከሥርጉተ ሥላሴ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>