ሕልሜን ፍቱልኝ።
TPLF በአገሩ ሁሉ ለሚኖሩት ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ታላቅ ግብዣ አድርጓል። በዚህ ቤት ሁሌ ደስታ ነው ሁሌ ፌሽታ ነው። ለድግሱ የተጠሩት ሁሉን ማድረግ የሚችሉ፣ ባለብዙ ህንጻ ባሌቤቶች፣ የፈለጉትን የሚወስኑ፣ ራእይ አስፈጻሚ ናቸው። በሚሰሩት ስተት ንጉሱ ከመረጧቸው ከድግሱ ተጠሪዎች ውጪ ማንም ሊጠይቃቸው የማይችል፣ የሚሰሩትን ግፍዊ ስራ እንደ ጀብዱ ደጋግመው የሚናገሩ፣ በአዳራሹ ውስጥ ለተሰበሰቡት መገለጫቸው ነው። በዚህ መሃል ንጉሱ እንዲህ አሉ ለድግሱ ታዳሚዎች በአዳራሽ ውስጥ ላሉት። ህልም አልሜአለው ብለው ተናገሩ። ህልሜም ተፈጻሚነት እንዲኖረው ለድግሱ የተጠራችሁ ወዳጆቼ በሙሉ ሃላፊነት አለባችሁ ከአዳራሹ ውጪ ያልወጣ የንጉሱ ራእይ እንደፈለጉ ሊበሉ ሊጠጡ ለተመረጡት ተነገረ። ወዳጅ ዘመዶቻቸው የተጠሩት ሁሉ ገብቶአቸው ይሁን ሳይገባቸው በጭብጨባቸው አጸደቁላቸው። ሳይገባቸው ነገሮች እንዲወሰን የሚያደርጉ ሁሉ ታሪክ በኃላ በአጨብጫቢነታቸው እንደሚዘክራቸው ሊያውቁት ይገባል። ህዝቡም የማያውቀው ራእይ ይነገረው ጀመረ። አዲሱ ንጉሳችን የንግስናው ወንበር በጭንቀት ይሁን በኑዛዜ አልያም በራእይ ታይቶላቸው ወይም ግራ ገብቷአቸው ንግስናውን እንዴት እንደተሰጣቸው ባይገባንም ቅሉ ብቻ አዲሱ ንጉሳችን ንግግራቸውን ሲጀምሩ እንዲ አሉ። የቀድሞ ንጉሳችንን ራእይ እናስፈጽማለን። ይሄንን ቃል ደግመው ደጋግመው ይነግሩናል። በመቀጠልም በመቀባበል በተለያዩ ሚዲያዎች እና አጋጣሚዎች የቀድሞ ንጉሳችንን ራእይ እናስፈጽማለን ይሉ ጀመር የአዳራሹ ታዳሚዎች። ራእዩን ያዩትም ሳይነግሩን ሄዱ ራእዩም የተነገራቸው የድግሱ ታዳሚዎችም ስለራእዩ ምንነት ሳይገልጹልን ራእዩን ለማስፈጸም እሩጫ ሆነ። ለህዝባችን ይፋ ሆኖ ያልተነገረው ራእይ ምን ይሆን?
በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ብዙ ጥያቄዎች ተነሱ ጥያቄዎች በሙሉ በሚያለያይ እና ተቀባይነት በሌለው መልኩ በኃይል ተፈጻሚ ሆኑ። ገዳማዊያን ሳይቀሩ አለም በቃኝ ብለው አፈር ምሰው ጤዛ ልሰው ቅጠል በጥሰው ድንጋይ ተንተርሰው እግዚአብሔር በማመስገን የሚኖሩት ገዳማዊ አባቶች የግፍ በትር አረፈባቸው ታላቅ ተንኮል ተሰርቶባቸው በማያውቁት ነገር ባህታቸው ድረስ ሄደው ገፏቸው ደበደቧቸው። ይሄ ቦታ የናንተ አይደለም ልቀቁ ተብለው ተዘባበቱባቸው እውን በቤተ ክርስቲያን እና አለም በቃኝ ባሉት አባቶች ላይ የግፍ በትር ማሳረፍ እና ቤተክርስትያንን ማፍረስ ይሆን ራእዩ?
በእስልምና እምነት ላይ ብዙ ሴራ ተሰራ የእምነት መሪያቸውን እንዳይመርጡ የመለያየት ስራ ተደረገ ይመሩናል ያሉትን ትተው ያላሰቡት መሪ ሆኖ በግዳጅ ተጫነባቸው። የለም መሪዎቻችንን እኛ እንምረጥ ባሉት ህዝብ ላይና ጥያቄ ያነሱትን በሙሉ የግፍ በትር ያርፍባቸው ጀመረ። ድምጻችንን ስሙን መሪዎቻችንን እኛው እንምረጥ ያሉትን ህዝብ ላይ ጥያቄውን ከመመለስ ይልቅ የሃይል ዱላ ያሳረፉና ያሰቃዩ ቀጠሉ። እስልምናን መከፋፈል ይሆን እንዴ ራእዩ?
ነጻነት… ነጻነት… ነጻነት… ዲሞክራሲ… ዲሞክራሲ… ዲሞክራሲ…. ፍትህ… ፍትህ…. ፍትህ… ብለው በተናገሩት ነጻ ሰዎች ላይ ቤተሰባቸውን ማሰቃየት ከስራ ገበታቸው ማባረር የመሰብሰቢያ ቢሮአቸውን በሃይል መዝጋት ስቃይና እንግልት መጫን። ምን አልባትስ በነጻተት የሚናገር ህዝን እንዳይኖ ስለነጻነቱ የሚቆም ትውልድ እንዳይኖር ይሆን ራእዩ?
ወንድም ከወንድሙ አጠላልፎ ገንዘብ አምላኪ አድርጎ ትውልዱን መቅረጽ ለምን ተፈለገ?። ስለ ጥቅሙ እንጂ ስለ አገር ክብር ስለ ወገን በደል እንዳያስብ ተደርጎ ያስተምሩታል እንጂ ወደፊት አገሩ ከዚህ ትውልድ ብዙ ነገር እንደምትጠብቅ እና ሃላፊነት እንዳለበት እንዲነገረው ያልተፈለገበት ምን ይሆን ምስጢሩ? የወገን ፍቅር፣ ያገር ፍቅር፣ ከልቡ እንዲወጣ እና እንዳይሳልበት ተደርጎ ትውልድን ማስተማር የድግሱ ታዳሚዎች ምን ይሆን የሚያመጣላቸው ጥቅም? ። አንዱን ሃይማኖት ከሌላው ሃይማኖት ጋር የማጋጨት ስራን መስራት፣ በዘር፣ በጎሳ፣ በብሔር፣ እንዲጠላለፍ ሴራ ማሴር ትርፋቸው ምን ይሆን? ሲሻቸው ማሰር፣ ሲሻቸው ማሰቃየት፣ ሲሻቸው መግደል፣ ባጠቃላይ ህዝብ በሁሉም አቅጣጫ ሲበላላ፣ ሲጠጣላ፣ እና ሲሰቃይ ማየት ድንገት ይሄ ይሆን እንዴ ራእዩ?
ጥቂቶች ተፈርተው ብዙሃኖቹ ተሸማቀው ማኖር ይሆን ሃሳባቸው። ጥቂቶች ባለስልጣን ሆነው ህዝቡ ለባለስልጣኑ ተገዢ ማድረግ ይሆን እቅዳቸው። ጥቂቶች ሃብታም አድርጎ ብዙኃኑን አደህይቶ የጥቂቶቹን እጅ ጠባቂ ማድረግ ይሆን ፍላጎታቸው። ጥቂቶች ፈላጭ ቆራጭ ህዝብ ግን ተፈላጭ ተቆራጭ እንዲሆን ማድረግ ይሆን ትግላቸው። አገር የቤተሰብ መምሪያ እስከሚመስል ድረስ በአንድ ጎጥ መያዝ ይሆን ራእያቸው?
እንዲህ እንዲህ እያልኩኝ ሃሳቤን የማወርደው ራእዩን ያዩት ባለራእዩ መሪ ራእያቸውን ሳያሳውቁን ስለሄዱ ነው። ራእዩም የተነገራቸው የድግሱ ታዳሚዎች የአዳራሹ ስብስቦች ምን እንደሆነ ባልነገሩን እና ባላሳወቁን ራእዩን አስፈጻሚ እንደሆኑ ደጋግመው ይነግሩን ስለጀመሩ ነው። ታዲያ እየተፈጸሙ ያሉት እነዚህ እና እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው። ንጉሱ ያዩት ራእይ ለህዝቡ ሳይነግሩ ለምን ሄዱ? ወይስ ጥሩ አማካሪ አልያም ጥሩ ወዳጅ አልነበራቸው ይሆን? ጥሩ አማካሪ አልያም ጥሩ ወዳጅ ቢኖራቸው ያዩትን ራእይ ሊፈቱት የሚችሉ በአገሩ እንዳሉ ይነግሯቸው ነበረ። ያሉት አማካሪ ጥሩ ስላልነበሩ እና የንጉሱን ህልም የሚፈቱትን የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረባቸው የሚመጣውንም ያለፈውንም እግዚአብሔር የሚገልጥላቸው እንቆቅልሽን የሚፈቱ በገዳም የሚኖሩትን መነኮሳት አባቶችን እንኳን አቅርቦአቸው ችግራቸውን ሊያስፈቱ ቀርቶ ገዳማቸው ድረስ ሄደው ማሰቃየትን ነው የመረጡት። ህልም ፈቺዎችን ኢማን ያላቸውን በአላህ መንገድ ያሉ ለአላህ የተገዙ ሼሆችን እያራቁ እና እያሰቃዩ መልካም ነገር መጠበቅ ከባድ ነው። ቅዱሳን አባቶችን ንጉሱ ካጠገባቸው ሊያቀርቧቸው ቀርቶ በገዳማቸው እና በመስኪዳቸው እንዳይኖሩ ታላቅ በደል እያደረሱባቸው ራእዩ እንዴት ሊፈታ ይቻላል? ማንስ ይፍታው?።
ንጉሱ ያዩትን ራእይ አዳራሽ ውስጥ የተሰበሰቡ የኔ ናቸው ያሉአቸው እንዲበሉ የተፈቀደላቸው በሙሉ ሊፈቱት አይችሉም። ታዲያ የንጉሱን ራእይ ማን ይፍታው? ግፍ ሲበዛ እግዚአብሔር እራሱ እንዲህ ይፈርዳል።
የእግዚአብሔር እጅ በግፈኖች እና በጨቋኞች ላይ ይወርዳል በእውነትም ፍርዱን እንዲህ ይፈርዳል።
ንጉስ ብልጣሶር ትልቅ ግብዛ አድርጎ ከመኳንቶችን ጋር ከሚስቶቹ ጋር ከእቁባቶቹ ጋር እየጠጣ እና እየጨፈረ ከእንጨት እና ከድንጋይ የተሰሩ አማልክትን ማመስገን ጀመረ። በዚህ ሰአት የሰው እጅ ጣት የንጉሱን አዳራሹን ጥሳ ገባች ግድግዳው ላይ ጽሁፍ ጻፈች። ንጉሱም የሰው ጣት በቤቱ ግድግዳ ላይ ስትጽፍ ተመለከተ። ያን ግዜ የንጉሱ መልክ ተለወጠ፣ ልቡ ታወከ፣ የወገቡ ጅማት ተፈታ፣ ጉልበቶቹም ተብረከረኩ። ንጉሱም አስማተኖች እና ጠቢባኖች ወደ ንጉሱ ይመጡ ዘንድ አዘዘ። ሁሉም ወደ ንጉሱ ቤት መጡ።ጽፈቱን ያነቡና ፍችውን ይነግሩት ዘንድ ተናገረ። ይሄን ጽፈት እና ፍቺውን የነገረኝን ሐምራዊ ግምጃ ይለብሳል በመንግስቴም ላይ ሶስተኛ ገዢ አድርጌ እሾመዋለው ብሎ ተናገረ። በግዛቱ ውስጥ ያሉት አስማተኞች፣ ጠቢባኖች ጽህፈቱን ሊያነቡት አልቻሉም ፍቺውንም ሊያውቁት አልቻሉም። የዚህን ግዜ ንጉሱ ደነገጠ ፊቱም ሲለዋወጥ ባዩት ግዜ መኳንቶቹም ደነገጡ። በአገሩ ጥሩ መካሪ አይጥፋ ጥሩም ወዳጅ አያሳጣን ይባላል። ንግስቲቷ የንጉሱንና የመኳንቶቹን ጭንቀት አይታ እንዲህ አለች። አሳብህ አያስቸግርህ ፊትህም አይለውጥ የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ያለበት ሰው በመንግስትህ ውስጥ አለ። ማስተዋልና ጥበብ በፊቱ የሆነ እውቀቱ ከእግዚአብሔር የተሰጠው ህልምህን የመተርጎም እንቆቅልሽን የሚገልጥ የታተመውን የሚፈታ ዳንኤል የሚባል ቅዱስ አለና እርሱ ሁሉን ይነግርሃል አለችው። ንጉሱም ተጨንቆ ስለነበረ በአስቸኳይ ይመጣ ዘንድ አዘዘ።
ዳንኤል ወደ ንጉሱ ቤት ገባ። ንጉሱም የጽህፈቱን ቃል ይፈታለት እና ይተረጉምለት ዘንድ ዳንኤልን ጠየቀው። ንጉሱ ለዳንኤል ሲናገረው በግዛቴ ያሉትን ጠንቋዮች፣ ጠቢባኖች፣ ፈላስፎች፣ እና ሟርተኖች ጭምር የጽህፈቱት ፍቺ ሊነግሩኝ አልቻሉም። አንተ ግን ሁሉን እንደምታውቅ ተነግሮኛል ጽህፈቱን አንብበህ ከፈታህልኝ ቀይ ግምጃ አልብሼህ በግዛቴ ሶስተኛ ገዢ አድርጌ እሾምሃለው አለው። ዳንኤልም ያንተን ቀይ ግምጃ እና ሹመት አልፈልግም። ስጦታህም በሙሉ ላንተ ይሁን ነገር ግን ጽህፈቱን አንብቤ ትርጉሙን እነግርሃለው አለው። ጽህፈቱ እንዲህ ይላል ማኔ ቴቄል ፋሬስ የሚል ሲሆን የነገሩም ፍቺ እንዲህ ነው።
ማኔ ማለት እግዚአብሔር መንግስትህን ቆጠራት ፈጸማትም ማለት ሲሆን።
ቴቄል ማለት በሚዛን ተመዘነች ቀላም ተገኘች
ፋሬስ ማለት መንግስትህም ተከፈለች ለመዶንና ለፋርስ ሰዎች ተሰጠች ማለት ነው። ብሎ ቅዱስ ዳንኤል ቃል በቃል ፈታለት። ንጉስ ብልጣሶርም እጅግ ተደሰተ ቀይ ግምጃም አልብሶት በመንግስቱ ላይ ገዚ አድርጎ ሾመው። ትንቢተ ዳንኤል ፭(5)+፲፫-፴ (13-30)
ከ- ከተማዋቅጅራ
Email- waqjirak@yahoo.com
The post ባለ ራእዩ መሪ ምን ይሆን ራእያቸው?። (ከ- ከተማዋ ቅጅራ) appeared first on Zehabesha Amharic.