Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የኢትዮጵያ አፈር የጠራው ጠቢብ፣ የድሆች አባት ዶ/ር በርናርድ ተለየን ! -ነቢዩ ሲራክ

$
0
0
የማለዳ ወግ …የድሆች አባት ዶ/ር በርናርድ ተለየን !
* የኢትዮጵያ አፈር የጠራው ጠቢብ
*” ክብር ሞቱ ለሰማዕት ”
(ጸሐፊው ነብዩ ሲራክ)

(ጸሐፊው ነብዩ ሲራክ)

ዛሬ የምናዘክረው ሰው የኢትዮጵያ አፈር ፍቅር ጠርቶት ለጉስቁል ተገፊው ደሃ የሀገሬ ሰው ህይዎት ትንሳኤ ተግቶ ለውጥ ስላመጣ  ጠቢብ ነው። ዝካሬ ታሪኩ ቢያስተምረን ፣ አርአያ ሰብዕናው ግብአት፣ ተሞክሮ ቢሆነን ፣ ህይዎት ንብረቱን በእኛው ቀዬ ስላፈሱሰ ትጉት ሀኪም ነው ! ነፍሳቸውን ይማር ብለን ለሰሩት ስራ ክብር በመስጠት እናዘክራቸዋለን!  ዶክተር በርናርድ አንደርሰን ይባላሉ ! በርናርድ ዛሬ አይሰሙም ፣ አያዩንም …

የዶር በርናርድን እረፍት ያረዳችኝ መነኩሴዋ እናቴ ሀዘኑ ጎድቷት ” ልጀዋ ዋርካችን ተገረሰሰ እኮ ፣ የድሆች አባትና ጠዋሪ መድሃኒታችን አጣንኮ … ” ነበር ያለችኝ … ያልጠበቅኩት ነበርና ድንጋጤው መላ አካሌን ወረረው  ። የእንባ ሳግ እየተናነቃት ሃዘኗን ያጋራችን እናቴን ከማጽናናት ባለፈ ምንም ማለት አልተቻለኝም! እናም ስለ ጠቢቡን የድሆች አባት ዶር በርናርድ አንደርሰን ላዘክር በተጎዳ ስሜት ብዕሬን ሳነሳ ጠቢቡ በሰጡት የኑዛዜ ቃል መሰረት ቀብራቸው በሚወዷት ሀገረ ኢትዮጵያ ምድር ይሆን ዘንድ በተናዘዙት መሰረት ሊፈጸም ተቃርቧል ። ውድ ባለቤታቸው የአርበኛው ደራሲ ገሪማ ታፈረ ልጅ ከሲስተር እማዋይሽ ገሪማም  ከምድረ አሜሪካ የዶር በርናርድን ቃል ለመፈጸም ዛሬ እኩለ ቀን አ.አ ይገባሉ  !  ጥቂት ስለድሆች አባት በርናርድ አንደርሰን ላጫውታችሁ …

ዶር በርናርድን ሳውቃቸው  !

ከአራት አመት በፊት ጠቢቡ ወንድም አግኝቻቸዋለሁ  ።  ስለሚሰሩት በጎ አድታጎት  በቅርብ የሚያውቋቸው ስለደግነት ቸርነታቸው አውርተው የማይጠግቡ ወገኖችን አግኝቸ ብዙ ተነግሮኛል። ከዚህም ተነስቸ ጠቡቡን ወንድም በአንድ የራዲዮ ዝግጅት ከአንጋፋው የረጅም ጊዜ የጀርመን ራዲዮ ጋዜጠኛ ከተክሌ የኋላ ጋር በመሆን በአንድ ዝግጅት ለማቅረብ ጠይቄያቸው ነበር ። ዶር በርናርድ ግን ” ምኑን ሰርቸ ታሪኬ ይነገራል ! ” በማለት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ፋና ወጊና አርአያ ተግባራቸውን ለማስተዋወቅ አልተሳካልኝም ! ያም ሆኖ ጠቢቡ በርናርድ እና ባለቤታቸው ሲስተር እማዋይሽ ገሪማን  በኢትዮጵያ ባህል በተሽቆጠቆጠው ቪላቸውን ሲያስጎበኙኝ እዚህ  ስላደረሳቸው መንገድ አውግተናል ።   “አጴ ቴዊድሮስ በተወለዱበት እና ባቀኑት ሃገር የአህያ ግንባር የምታክል ማስታወሻና መዘከሪያ ቦታ እንዴት አይኖራቸውም?  ” በሚል ለቴዎድሮስ መታሰቢያ ሙዝየም ለማስፈቀድ ሲከላተሙ ያገኘኋቸው ከእውቋ ሀገር ወዳድ  ከወ/ሮ እማዋይሽ ገሪማ ጋር በመሆን የምድረ አሜሪካ የተደላደለ ኑሮ ስላፈናቀላቸው የእናት ኢትዮጵያ ፍቅር ፣ በታሪካዊዋ የጎንደር ከተማ  ስላሰሩት የአዛውኖቶች መጠለያ  ፣ ለህሙማን መርጃ ባቋቋመው የህክምና እርዳታ መስጫ ቦታና ያኔ ጅምር ስለነበረው የሆስፒታል ግንባታ መሰረት በሚጣልበት ማሳ ላይ ቆሜ ህልማቸውን አውገተውኛል ፣ ሃሳባቸውን ተጋርቻለሁ!

ለመሆኑ ዶር በርናርድ አንደርሰን ማናቸው?

በሃገረ ጃማይካ ካትሪን ደብር ተብላ በምትታዎቅ አንዲት መንደር እ.ጎ.አ መስከረም 21 ቀን 1944 ዓም ህጻን በርናንድ አንደርሰን  ከአርሶ አደር ወላጆቹ ተወለደ።  የበርናንድ ህይዎት በጃማይካዋ የካትሪን ትንሽ የገጠር መንደር መጀመሩ እንጅ ከዘር ማንዘሩ ርቆ በሌላ የአለም ጫፍ ካለችው ኢትዮጵያ ጋር በፍቅር ተቆላልፎ ህይወቱን ያሳልፋል ብሎ የሚገምት አልነበረም ። ገና ከልጅነት ህይዎቱ ጀምሮ ብሩህ አዕምሮ የታደለው በርናንድ በካሪቪያን ውስጥ አንጋፋ በሆነው የዎልማር የወንዶች ት/ቤት ተግቶ በመመማር ወደ ተሻለ ደረጃ መሸጋገር ጀመረ ፣ ከዚያም ጉዞውን ቀጠለ … የተሻለ እውቀት ጥም እያንገበገበው ወደ አደገችው ምድረ አሜሪካ አቀና ፣ በትምህርቱ በመግፋት እ.ጎ. አ 1960 ዎቹ መጀመሪያ በዋንሽን ግተን ዲሲ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በህክምና ሳይንስ የመጀመሪያውን የባችለር ዲግሪ ሲቀዳጅ በከፍተኛ ማዕረግ ነበር ።  ለጎልማሳው በርናንድ በከፍተኛ የህክምና ተቋማት የላቀ ውጤት ማምጣት ተራ ትምክህት ሆኖ ሳይገታው የተሻለና የላቀ ፣ ከፍ ያለ ትምህርት የመቅሰም ህልምን ሰንቆ የማታ ትምህትቱን በመከታተሉን ገፋበት ። ይህንንም ህልም በአጭር ጊዜ ታጥቆ ለስኬት አደረሰው ። እ.ጎ. አ በ1970 ዎቹ በርናንድ በከፍተኛ ማዕረግ የዶክትሬት ማዕረግ ተመረቀ !

የዚያ ደርባባ ጎልማሳ ዶር ማንነት የተገነባው ከመደበ ኛው እውቀት ባለፈ አብሮት ከተቆራኘ ሰብዕና እንደነበር የሚያውቁት ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ ። ዶር በርናርድ አንደርሰን በሙያው ያጡ የነጡ፣ ጉስቁል ፣ምንዱባንን ለመርዳትና ለመደገፍ ቆርጦ ተነሳ ፣ ከምንም በላይ ደግሞ እንደ ቃል ኪዳን አድርጎ የያዘውን ተተኪ ፍለጋና ተተኪን ማፍራት ነበርና ድሎት ሳያታልለው ያደገ የተመነደገችውን ምድረ አሜሪካ ለቆ ወደሚያውቀው የድሆች ምድር አቀና  !  ወደ ጃማይካ ኪንግስተን …

ጃማይካ ኪንግስተን …

ህልሙን ለማሳካት ወደ ትውልድ ሃገሩ ጃማይካ ተመልሶ በወቅቱ ታዋቂ ከነበረው የኪንግስተን የህዝብ ሆስፒታል ስራውን ጀመረ ። የቀዶ ጥገና ጥበብ ባለሙያው ጎልማሳ ሃኪም ቅድሚያ የሰጠው በድህነት የሚማቅቁ ወገኖቹን መታደግ ነበር ፣ በህክምና ድጋፉ ፣ በተጓዳኝ ጥናትና ምርምሩ አንቱ በሚያሰኘውን ተመክሮ ራሱን እያጎለበተ ጉዞ የጀመረው ሃኪም በህክምና ድጋፍ ከመስጠት ርቆ ሔዶ በመምህርነት ሙያው ተተኪ ትውልድን የማነጽ ህልሙን አሳካ ። በዚህም ጉዞው ዶር በርናርድ አንደርሰን ለሃገሩና ለወገኑ ይህ ነው የማይባል አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ቻለ  !

ከጃማይካ መልስ በዋሽንግተን …

የጃማይካ ኪንግስተን ተልዕኮውን በሚገባ ከውኖ አቅፋ ደግፋ እውቀት ወደ መገበችው ሀገረ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ተመለሰ ። ዶር በርናርድ ለዚህ ላበቃው ዩኒቨርሲቲ ከእለትጉርሱ ያጠራቀመውን ከ100 ሽህ የአሜሪካ ዶላር የለገሰ ፣ ለሚሰረሰው በጎ ስረሰ ከመደሰተረ ውጭ ፣ መወደስ የማይሻ ሰብአዊም ነበር ።
ዶር በርናርድ ከጃማይካ መልስ እንደ አቻ የሙያው ባልደረቦቹ  ሃብት ንብረት የሚያካብትባቸው ሆስፒታሎ ች በከፍተ ኛ ገንዘብ ሊቀጥሩት ሲሻሙ አሻፈረኝ አለ።   ጥቅም ፍለጋ መማሰኑን ” ወዲያልኝ ” ብሎ ፣  የጤና ከለላና ሽፋን የሌላቸው ፣ በድንገተኛ አደጋ ተጎድተው ህይዎታቸው አጣብቂኝ የገቡትን የስልጡኑ ሀገር ተገፊ ምንዱባን መታደግ ወደ ሚችልበት በዲሲ ጄኔራል ሆስፒታል በአነስተኛ ደመወዝ ተቀጥሮ መስራት ጀመረ ።  በሙያው ተግቶ ፣ በሰብዕናው ጸንቶ ፣ ባሳየው ስኬትም በአጭር ጊዜ አንቱታን በማግኘቱ የሆስፒታሉ ሊቀመንበርና የቀዶ ጥገናው ክፍል ዋና ዳይሬክተር ለመሆን በቃ !  በአስተዳደር እና በሙያው ክህሎት የዲሲ ጀኔራል ሆስፒታል ከፍ ወዳለ ደረጃ ያደገው በዶር በርናርድ አንድሰን አመራር እንደነበር ዝክረ ታሪኩ ያስረዳል። ዶር በርናንድ ሆስፒታሉን ከማስተዳደር ጎን ለጎን የግል ክሊኒክ በድሆቹ መኖሪያ አቅራቢያ በዲሲ ሮድ አይላንድ መንገድ በመክፈት ፣ ለቻሉት በአነስተኛ ክፍያ ፣ ያልቻሉትን በነጻ በማከም ግልጋሎት ይሰጥም ነበር ።

የዶር በርናርድ አፍሪካና ኢትዮጵያ ትስስር …

በቀጣይ ዝካሬ ዶር በርናርድ ስነሳ እንደ አባት አቅርቤ ፣ እንደ ታላቅ ትጉህ ጠቢብ አንቱ እያልኩ መተረኬ ይገባኛል ፣ መልዕክቴ ከገባችሁ ለእኔ ያ በቂ ነው!  ብቻ ያገሬ ሰው ዶር በርናርድን  “የድሆች አባት ” ስላለበት አንድምታ ዘልቀን እናወጋለን …

ታህሳስ 24, 2007  ዓም ይህችን አለም የተለዩን ያልተጨበጨበላቸው ፣ ያልተነገረላቸው የኢትዮጵያ ወዳጅ ጃማይካዊ አሜሪካዊ ዶር በርናርድ የምናዘክረው በታላቅ  ክብር ነው  !  “ዶር በርናርድ ጉስቁል ምንዱባን ን ስትደግፍ ኖረሃልና ሞትህ የክብር ሞት ነው  ! ” ክብር ሞቱ ለሰማዕት ”  በሚል ታህሳስ 29 ቀን 2007 ዓም እኩለ ሌሊት በዋሽንግተን ዲሲ በተደረገ ሰፊ የጸሎትና የዝክር ስነ ስርአት ቤተሰብ ፣ ወዳጅ ዘመድና አድናቂዎቻቸው በተገኙበት የክብር ስንብት አድርገው በርናንድ በድናቸው እንዲያ ርፍ ወደ ፈቀዱባት ቅድስት ሀገረ ኢትዮጵያ በክብር ተሸኝተዋል ! በዚሁ ፕሮግራም ከተሰራጨው ዝክረ ህይዎት ያገኘሁትን መረጃ በቀጣይ እንደሚሆን አድርጌ የምናየው ይሆናል !

ለመላ ቤተሰብ ለወዳጆቻቸውና ለአድናቂዎቻቸው መጽናናትን እመኛለሁ  !  ለሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪው የድሆችን አባት ፈጣሪ በቀኙ ያሰረቀምጣቸው ዘንድ የዘወትር ጸሎቴ ነው  ! ነፍስ ይማር  !

ነቢዩ ሲራክ
ታህሳስ 30 ቀን 2007 ዓ.ም


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>