ፈኢዝ መሀመድ ለታሪክ ምሁሩ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል፣ ለኡስታዝ አህመድ ሙስጠፋ፣ እንዲሁም ለኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ምስክርነቱን ሰጥቷል!
ማክሰኞ ታህሳስ 28/2007
የህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎቻችን ችሎት ከግንቦት 5/2006 ጀምሮ አቃቂ ክፍለ ከተማ በሚገኘውና በተለምዶ ‹‹08 አዳራሽ›› ተብሎ በሚጠራው ቦታ የመከላከያ ምስክራቸውን ማስደመጥ ከጀመሩ በኋላ የፍርድ ሂደቱ ሰሚት አካባቢ በሚገኘው በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት እንዲከታተሉ ሲደረግ የቆየ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በዚሁም መሰረት ከግንቦት 5/2006 ጀምሮ የመከላከያ ምስክራቸውን ሲያስደምጡ የቆዩ ሲሆን የዛሬውን ጨምሮ በአጠቃላይ 153 ምስክሮችን አስደምጠው የሰው የመከላከያ ምስክሮቻቸውን በዛሬው ዕለት አጠናቅቀዋል።
በዛሬው ችሎት ምስክርነቱን ለሶስት የኮሚቴው አባላት የሰጠው ፈኢዝ ሙሀመድ ሲሆን የመጀመሪያውን ምስክርነቱን ለታሪክ ምሁሩ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል አሰምቷል፡፡ አቃቤ ህግ በኡስታዝ አህመዲን ጀበል ‹‹ኢሜል ውስጥ አገኘሁት›› ብሎ ያቀረበው መረጃ እርሱ የጻፈው እንዳልሆነ ያስረዳው ፋኢዝ ሙሃመድ የተባለውን ኢሜል ለኡስታዝ አህመዲን የላከለት ራሱ መሆኑን እና ኢሜል ያደረገውም ከሰለፊያ ጋዜጣ፣ ከኢቲቪ፣ እንዲሁም ከተለያዩ ጋዜጦችና መፅሄቶች ያገኘውን መረጃ መሆኑን ገልጿል፡፡ ከላካቸው ጽሁፎች ውስጥም በወቅቱ የመጅሊስ አካላት ሲናገሩ የነበሯቸውን ንግግሮች እና መጅሊስ የአህባሽ ስልጠና መስጠቱን የሚያመለክቱ መረጃዎች መኖራቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
ፋኢዝ ቀጣይ ምስክርነቱን የሰጠው ለኡስታዝ ካሚል ሸምሱ እና ለኡስታዝ አህመድ ሙስጠፋ ሲሆን ኡስታዞቹ ለስሜት አለመገዛትን፣ እውቀት በኢስላም ያለውን ቦታ እና ሃይማኖታዊ መቻቻልን እና እኩልነትን አስመልክቶ ከሰጧቸው ትምህርቶችና ስለጠናዎች ጋር በተያያዘ የቀረበባቸውን ክስ በማስመልከት ክሱን አስተባብሎ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ከአቃቤ ህግ ለቀረበለት መስቀለኛ ጥያቄም በአግባቡ መልስ ሰጥቷል።
በዛሬው ዕለት ለውድ ኮሚቴዎቻችን ሊመሰክር የነበረው ሁለተኛ ምስክር ላፕቶፕ ኮምፒዩተሩ ከማዕከላዊ ስላልመጣ የቪዲዮ ማስረጃ በሚያቀርቡበት ወቅት አብሮ ምስክርነቱን እንዲሰጥ ትዕዛዝ የተሰጠ ሲሆን የሰው ምስክርነት የማሰማት ሂደቱም ዛሬ ማብቃቱ ታውቋል፡፡ ውድ ኮሚቴዎቻችን ቅሬታዎች እንዳሉባቸው በማሳወቅ አቤቱታ ለማቅረብ ያደረጉት ሙከራም ‹‹በቢሮ በኩል ቀርባችሁ አስረዱ›› በሚል ተቀባይነት አለማግኘቱ ታውቋል፡፡
ቀጣዩ ቀጠሮ የፊታችን ሰኞ ጥር 4/2007 ነው።
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!