ምርጫ ቦርድ ማንም ይዘዘው ማንም ወይም በግል ተነሳሽነት እያደረገ ያለው ነገር የኢትዮጵያን የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ከምን ጊዜውም በለይ ወደኋላ ለመመለስ እንደሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊረዳው ይገባል፡፡ ምርጫ ቦርድ ምርጫ እንዲያሰተዳድር በተሰጠው ኃላፊነት የፓርቲዎች አስተዳደሪ ለመሆን እየቃጣው ያለ ተቋም ነው፡፡ ስናከብረው ለመከበር ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ለዚህ ተቋም መጠናክር የበኩላችንን መወጣት አለብን ብለን የተነሳን ፓርቲዎችን ጭምር እየገፉ አለቆቹን ለማስደሰት ደም ተግቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህን የሚያደርጉትን ሰዎች ደግሞ በህዝብ ፊት ለብይን እንዲቀርቡ በግልፅ ማጋለጥ ይኖርብናል፡፡
ትላንትና ዶ/ር አዲሱ በሚዲያ ቀርቦ የተናገረው በምንም መልኩ አንድነትን አይመጥንም፡፡ የተቀሩት የቦርድ አባላትም ይመጥነናል ካሉ ትዝብት ላይ ይወድቃሉ፡፡ የምርጫ ቦርድ አባላት ሳያገባቸው እንፈትፍት ሲሉ መፈተፍቱን ለእኛ ተዉልን ነው ያልናቸው፡፡ ዶ/ር አዲሱ በሚዲያ የቦረድ ውሳኔ ሊሆን ይችላል ብሎ ካቀረበ በኋላ ዛሬ ታህሳስ 28 2007 ቦርድ ተሰብስቦ ውሳኔ ሰጥቶዋል፡፡ ይህን ውሳኔ እንገራችሁ ብለው በስልክ ከጠሩን በኋላ የአንድነት ፓርቲ የወረዳ አባላት የሆኑትንም በተመሳሳይ መልክ ጠርተው ነበር፡፡ ለነገሩ ይህ አካሄድ አንድነትን ስለማይመጥን በፅሁፍ እንዲገልፁልን ነግረናቸው ተመልሰናል፡፡ ለማንኛውም ዶ/ር አዲሱ የሰጠው መግለጫ ይህ መግለጫ እንዲሰጥ የወሰኑትን ጨምሮ ለተቀሩት የቦርድ አባላት ያላቸውን ንቀት የሚያሳይ ነው፡፡ ቦርዱ ተሰብሰቦ ምንም ዓይነት ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት ውሳኔውን ሚዛን የሚያሳጣ መግለጫ ለመስጠት ምን እንዳጣደፋቸው መገመት ቀላል ነው፡፡ በልባቸው የሚደግፉትን ፓርቲ ለማንገስ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው፡፡
ልክ የዛሬ አምስት ዓመት አንድነት ላይ ተመሳሳይ ግብ ግብ ተፈጥሮ ነበር፡፡ የዚህ ተልዕኮ ፈፃሚዎች ዛሬ ላይ ሆነው ምን እንደተጠቀሙ ሲያሰላስሉ ምን እንደሚሰማቸው ባላውቅም ዛሬ በዚህ ተግባር ላይ የተሰለፉት አባላት ደግሞ ምን እንደሚያደርጉ መጠበቅ ነው፡፡ ለመማር ያልተፈጠረን ሁሉ ምንም ማድረግ ይቻላል? ማንም ተላላኪና ላኪ ሆኖ ቢያገለግልም ዛሬ የተሰማኝ ነገር አንድነት በምርጫ ለመሳተፍ ሲወስን እንደዚህ ዓይነት ተቋማት በምን ያህል ደረጃ ለመዋረድ ዝግጁ እንደሆኑ ለመረዳት የሚያስችል ነው፡፡ አሁንም ትግሉ መራራ፣ የሚያስከፍለው መስዋህትነትም ውድ ሊሆን እንኳን ቢችል የአንድነት አባላት በድል እንደሚወጡት ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ እሩቅ እንደሆነ አውቀን ለጀመርነው ትግል አቋራጭ እንደማንፈልግ መግለፅ ይኖርብናል፡፡
ውድ የአንድነት አባላት ለቀጣይ አንድነት ከምርጫ ቦርድ አሻጥር ለማላቀቅ ለምናደርገው ትግል ቀበቶ ጠበቅ ነው፡፡ ከሰማይ በታች አንድነት ለመፍታት የማይችለው ፈታኝ ነገር ምርጫ ቦርድም ሆነ በውሰጥችን ያሉት ዙንቢዎች ሊያቀርቡ አይችሉም፡፡ ጎበዝ ጠንከር ነው፡፡
ታሪክ ለመስራት እንዘጋጅ – አቶ ተክሌ በቀለ የአንድነት ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር
አንድነት ፓርቲ የኢህኣዴግን ምንነት ላላመኑ ወገኖች ለማጋለጥ በትጋትና በስሌት ሲሰራ ቆይቷል፡፡እየሰራም ነዉ፤እዚህ ደርሷል፡፡ “የሆደ ሰፊዉን ምርጫ ቦርድ” ሆድ በገሃድ አጋልጧል፡፡በነአሞራዉና ወዲ ቐሺ(በተጋሩ ሁሉ) ትግልና ሞት የሚቀልዱትን በህዝብ ፊት ወጥተዉ ዛሬም እንዲዋሹና ለኢትዮጵያችን የፖለቲካ ታሪክ እነማን ምን እንደሆኑ አንድነት ፓርቲ የበኩሉን ሚና ተጫዉቷል፡፡ ለኔ ከባድመ ዉሳኔና ልህዝቡ በወቅቱ ከተነገረዉ ጋር ይመሳሰላል፤ይጠጋጋል፡፡ኢህኣዴግ ምርጫዉን እንደማይፈልገዉ፤ከፈለገዉም ለተለመደዉ ቀልዱ ከነማን ጋርና በምን ሁኔታ እንደሚፈልገዉ ፓርቲያችን ሶስተኛዉን (የአዉሮፓና አሜሪካ ታዛቢዎች የሌሉበት ምርጫ መሆኑን፤የህዝብ ታዛቢዎች የተበላሸ የምርጫ ሂደትና ፓርቲዎችን የማፈራረስ/የማዳከም ስራዎች) ነጥብ አስመዝግቧል፡፡
በዚህ ሂደት ላይ ሰፊ እዉነታ ለህዝብ ይቀርባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ከምርጫዉ ቦርድ መጋረጃ ካሉት ወገኖች ጋር በሃሳብ እየተሸነፈ ግን ተሳትፎዉ ያለተቋረጠ አንድ ከፍተኛ አመራር እንዳለ እናዉቃለን፡፡ሁሉን ነገር በደንብና በመርህ የምንሰራዉ ለኢህኣዲግ/ምርጫ ቦርድ ካለን ፍርሃት ሳይሆን ለወደፊቱ ለምናስተዳድረዉ ህዝባችንና ለኢትዮጵያችን ፖለቲካ ክብር ስንል ነዉ፡፡እናም ከደንብ ወጥተን የሰራነዉ ክዋኔም በግፍ የገፋነዉ አመራርም፤አባልም የለም፡፡በመቻቻል መንፈስ ዲሰፒሊን ተጥሶም እንዲጓተት ተደርጓል፡፡ይህንንም የኢህኣዴግ ተባባሪነት ለታሪክ አስቀምጠነዋል፡፡
ምርጫ ቅንጦት ሆኖብን፤የተከበሩ እየተባሉ ለመጠራት ሳይሆን እፊታችን ላይ ያለ እድልና ስልትም ስለሆነ አንድነት ፓርቲ መጪዉን ምርጫ የምር እንዲሆን ወስኗል፡፡ ኢህኣዴግ ደግሞ ማበላሸቱን ተያያይዞትል፡፡ምርጫ በአምባገነን ቡድኖች ለሚገዙ አገራት ለለዉጥ እንዱ ስልት እንጂ ብቸኛዉ አለመሆኑ ይታመናል፡፡ፓርቲያችን ለለዉጥ ተደራጅም ይላል፡፡እዉነተኛ ፓርቲዎች ከምርጫዉ ባሻገር ላለዉ ግብ እንዲዋሃዱና እንዲተባበሩም ጥሪ አቅርቧል፤ስልቶችን ለማቀራረብም እየጣረም ነዉ፡፡የአንድነት ኣባላት በያለንበት ድርብ ሃላፊነት አለብን፡፡ለአንድነት ሃይሎች ስልቶቻችን ሁሉ በማቀራረብ የተጀመረዉ የስልጣን ሃይሎችን እያራገፉ ትግሉን በሰለጠነና አንድነቱን በጠበቀ መልኩ የማስቀጠልና ልዩነቶችን በማቻቻል ሰፊ መሰረት የማንበር ሃለፊነት አለብን፡፡ ታሪክ ለመስራት እንዘጋጅ፤ፊታችንን ወደ ዋናዉ ግብ እናድርግ፤ከሃዲዱ አንወርድም!
አሁን አንድነት ግልፅ ጦርነት የታወጀበት ይመስላል – አቶ ኪዳኔ አመነ – የመድረክ ወጣት አመራር
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በተመለከተ ብዙ እየሰማን ነው፡፡ ፓርቲው ራሱን የማፅዳት ሃላፊነት ከተወጣ በኋላ ገዢው ፓርቲ ጥርሱን የነከሰበት ይመስላል፡፡ ብዙ ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ በምርጫ ቦርድ ጥያቄ መሰረት ጠቅላላ ጉባኤ በድጋሚ እስከማድረግም ደርሰዋል፡፡በኔ እምነት አንድነት ፓርቲ በበኩሉ ብዙ ርቀት የሄደ ይመስለኛል፡፡ ትእግስታቸው አደንቃለሁ፡፡ ፓርቲው በውስጡ ከጥቂቶች በቀር በዙዎቹ ቁምነገር የሚያስቡ የምናከብራቸውና የምንወዳቸው ጥሩ ሰዎች አሉት፡፡ ትርጉም ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ጥቂት ፓርቲዎች አንድነት አንዱ ነው፡፡ እናም በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ና እውነተኛ ፍትህ ለማምጣት የአንድነት መኖር ከፍተኛ ትርጉም አለው፡፡ ፓርቲው የአንድነት ፓርቲ አባላትና የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሣይሆን የራሳችን አቋምና መስመር ይዘን በሌላ ፓርቲ ያለን ሰዎች እንኳ አንድነት እንዲኖር አጥብቀን እንፈልጋለን፡፡ ወደፊት አንድነትም እኛም ቤታችን እያፅዳን መንገድ ላይ መገናኘት አለብን፡፡
ያኔ ብቻ ነው ኢትዮጵያን የምናድናት፡፡ እንዳንራመድ ቀይዶ የያዘን ገመድ እየበጣጠስን፤ ፀረ-ለውጥና አድሃሪ አቋምን እየመከትንና እያፀዳን የዴሞክራሲ እና የሉዓላዊነት ፍለጋው ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
አሁን አንድነት ግልፅ ጦርነት የታወጀበት ይመስላል ፡፡ አንድነቶች አሁን ነው የፖለቲካ ፅናታቸው በጥበብ ማሳየት ያለባቸው፡፡ ወንድሞቻችን በርቱ!!!