* 80 ሽህ ነዋሪ ባለበት ሃገር ከ130 በላይ ነዋሪዎች አልተገኘም ፣ ለምን ?ከ 80 ሽህ በላይ ነዋሪ እንዳለበት በሚገመተው የቀይ ባህር ዳርቻ ውብ ከተማችን ጅዳ 600 የኮሚኒቲውን መታወቂያ ያደሱ አባል አሏት፣ ትናንት ሃሙስ ህዳር 18 ቀን 2007 ዓም በተጠራው በስብሰባ የተገኘው በጣት የሚቆጠሩ አዳዲስ ነዋሪዎችንና ወደ መቶ የሚጠጉት ሰራተኞችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ130 ያልበለጠ ነዋሪ ነበር ። ነዋሪው በተለይም ወላጁ በዚህ ወሳኝ ቀን ዝር ማለት አልቻለም፣ ስብሰባውም እንደተለመደው በደንቡ መሰረት ” ምልአተ ጉባኤ አይሞላም ” ተብሎ ተበትኗል ! ይህ የነዋሪው ዝምታና ኩርፊያ መግለጫ ሽሽት የገዘፈው ችግር ማሳያ ከሆነ መልካም ነው ! ግን ነዋሪው ለምን ከወሳኙ ተሳትፎ ሸሸ ?
መቸም ያልተመቸ ነገር አለና ነዋሪው በአንድ ያደመ ይመስል ከመቅረብ መራቅን መርጦ ዝም ፣ ጭጭ ብሏል ። በተለይም የሶስት ሽህ ተማሪዎችን በጅዳ የኢትዮጵያውያን አለም አቀፍ ት/ቤት የሚያስተምረው ወላጅ ት/ቤቱን ለመታደግ የሚያስችለው የኮሚቲ መ/ቤት ሪፖርት ለመስማትም ሆነ ፣ አዲስ ምርጫ ለማካሔድ ፍላጎት አለማሳየቱን በውል ላጤነው ያሳስባል።
እኔ የማውቀው …
እኔ እስከሚገባኝ ልክና እስከማውቀው ነዋሪው ዝምታ ኩርፊያና ሽሽት መምረጡ በዓመት የሚከፈለው የአባልነት መዋጮ ከብዶት አይደለም። ጥቅማ ጥቅሙ ጎድሎበትም ከአባልነት የሸሸ ነዋሪ እንደሌለ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ ። ዳሩ ግና በቆንስሉም ሆነ በኮሚኒቲው ዙሪያ በማህበራዊ ችግሩ ፣ በመብት ማስጠበቁ እና በዙሪያው በሚሰጠው ግልጋሎት ነዋሪው ከፍቶታልና ሸሽቷል ፣ በውስጥም በውጭም አሰራሩ ተፈጥርቆ ወደ ቀናው ጎዳማ አልላወስ ያለው ትልቁ ማህበር እያደር መኮስመኑ ፣ በብቸኝነት በሚያስተዳድረው ካፊቴሪያ ፣ ሻንጣ ቅበላና በትምህርት ቤቱ በአደባባይ በሚታይ በሚሰማው ኢ ፍትሃዊ አካሄድ መደፍጠጡ ፣ የተቋሙ ሁለንተናዊ አገልግሎት አሰጣጥ እያደር መዝቀጥ ፣ ብሎም በማዕከሉ ግልጽነት የሌለው ተደጋጋሚ የተውሸከሸከ አካሔድ ነዋሪው ተስፋ መቁረጡ እውነት ነው! ይህ ሆነና እውነቱ ነዋሪው በነቂስ ዝምታ ፣ ኩርፊያ ሽሽት መምረጡን ነው የማውቀው …ሁሉም ትክክል ነው …
ከካፍቴሪያ እስከ ት/ቤቱ ችግር አለ ? …አዎ !
ቤቱ ፍትሃዊ ባልሆነ አሰራር ይሰራል? ቅጥር አሰራሩ በቤተሰብ የተጨማለቀ ነው ? …አዎ ! ቤቱ የአስተዳደር ብልሹነት የነገሰበት ነው ? …አዎ !
* ነባራዊ ሁኔታውን ያላገናዘበው የእኩዮች ዘመቻ …
ከትናንት ጀምሮ በአደገኛ መንታ መንገድ ስላለው የኮሚኒቲው መስሪያ ቤት ” ለምን የሰላ ሂስ ታቀርባላችሁ “,በሚል አንድምታ እዚህ ግባ የማይባል የስም ማንቋሸሽ ዘመቻም ተጀምሯል። የስም ማጥፋት ዘመቻው አቀንቃኞችም ሆኑ ኮሚኒቲውን ለዚህ የከፋ አደጋ የጣሉት የጥፋቱ ባለድርሻ አካላት ከቧልት ስድባቸው ተቆጥበው መመርመር ያለባቸው እውነታ ግን ” ኮሚኒቲውን ነዋሪው ለምን ሸሸው? ” የሚለውን ውሃ የሚያነሳ ጥያቄ ቢሆን ለሚያወዛግባቸውና ለሚያንቀዠቅዣቸው መልስና ለችግሩ መፍትሔ ማግኘት በቻሉ ነበር ።
ኮሚኒቲውን ህዝባዊነት አሳጥተው የአንድ ወገን መፈንጫ ለማድረግ ምላሳቸውን ብቻ አሹለው ለዲስኩር ፣ ለስድብ፣ ለድንፋታና ለከንቱ ውዳሴ የሚፏልሉት ወገኖች ይህን ደረቅ እውነት በትክክል መረዳት ቢችሉት መልካም በሆነ ነበር ። ግን አልሆነም ! አዙሮ ማየትን ለታደለ ትናንት ያየነውን ጨምሮ በተደጋጋሚ በኮሚኒቲው ምርጫ በግላጭ የታየው እውነታ የሚያሳየው ከዚህ ያለፈ እውነታን አይደለም ። ሌላው ቢቀር ወላጁ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ያለው የትምህርት ቤቱን ጉዳይ አሳስቦትና የራሴ ጉዳይ ነው ብሎ ለምን ንቁ ተሳትፎ አላሳየም? ለምንስ ስብሰባ አለ በተባለ ቁጥር በዙሪያው ዝር ማለት አልፈለገም ? ብለን መጠየቅ አለብን ፣ ከፍጹም የጎጥ ስሜት ፉክክር ወጥተን ፣ በቤተሰብ የተማከለውን ማዕከል ሰርተው ውለው እንዲገቡ የምንፈልጋቸው ቤተሰቦቻችን ከመከላከል የመነጨ ተራ ጉዳይ ወደ ጎን ትተን ለመሰረታዊ ችግሩና ለነዋሪው ዝምታ ኩርፊያና ሽሽት መልስ ልናገኝለት ይገባል። መፍትሔ እንኳ ማምጣት ቢገድ ትክክለኛ መልሱን ማወቅ ለቀጣዩ ጉዞ ይጠቅማል ። መልሱን ከተረዳችሁ ለምንወተውተው እውነት ምላሽ ማግኘት ነውና የነዋሪውን ችግር በመጠኑም ቢሆን እንድትረዱት ያደርጋችሁ ይመስለኛል !
ሃቅ ስንናገር የጥላቻ ዘመቻ ማቅናት የሚቀድማችሁ እነ እንቶኔ በግለሰቦች ማንነታችን ላይ ውርጅብኙን ትታችሁ በቀረበው አስተሳሰብ ዙሩያ ምላሽና መፍትሔ ሃሳብ አፍልቁ … እከችኋለሁ ! የቆማችሁት ለህዝብ ከሆነ አቅሙ እንኳ ባይፈቅድላችሁ በቅንነት ከተነሳችሁ አይገዳችሁም ” ሰው ለምን ዝም ይላል? “የፈራ ይመስል ” ሰው ለምን ይሸሻል? በማለት ራሳችሁን ጠይቁ ፣ አማክሩት ፣ አንክሮም ሰጥታችሁ ለሽሽቱ ምላሽ ብትፈልጉለት መልካም ነው …
* ሁለቱን መከራዎች እንዴት እንቻል …?
ነዋሪው ሙሉ ባይባል ቢያንስ የኮሚኒቲው አባል የሆነው ከ80 ሽህ 600 ያልነው ንቁ አባል አኩርፎም በሉት ተማሮ ዝምታን መርጦ ሸሽቷል ! … በዝምታና ኩርፊያ ሽሽትን ለመረጠውን ውስን አባል ሳይሆን በነቂስ የጅዳ ነዋሪ መጻኤ ህይወት መሻሻል ” አሳስቧቸው”የኢህአዴግ አባላት በኮሚኒቲው ምርጫ ዙሪያ ሲመክሩ ነው የሰነበቱት ፣ ይህም በማድረግ በአዲሱ ምርጫ የራሳቸው የሚሉትን አካሔድ ለመከተል ተስማምተዋል። የአባልነት መብታቸውን ተጠቅመው በመምከር ማዘከራቸው ተቃውሞ የለኝም ። ኮሚኒቲውን ማስተዳደር ቢችሉ ከፖርቲው በመምጣታቸው ብቻም አልቃወማቸውም ፣ መስራት ከቻሉ ማህበራዊ ችግራችን ይቀርፋሉና መልካም ነበር ። ነገር ግን የስራ ክህሎትም ብቃት ሆነ የወገን ተቆርቋሪነት ስሜታቸውና የትጋታቸውን ልኬታ በተለያዩ አደረጃጀቶች ፣ ማህበራትና በራሱ በኮሚኒቲው ውስጥ እናውቀዋለን ፣ በተደጋጋሚ አይተነዋልና የድርጅት አባላቱን ኮሚኒቲን የመቆጣጠር አዝማሚያ አንደግፈውም ። የድርጅቶች ቀረቤታ ለጤና ነው የማንለው ኮሚኒቲው የቀረውን ሽርፍራፊ ነጻነት ተነጥቆ ስራ ሳይሰራ መልሶ አዘቅት የሚያገባ አካሔድ ብለን እንሰጋለንና ነው ! እናም ነጻነትም አጥተን ስራም ሳይሰራ ሁለት መከራ መሸከም ይከብደናልና …ተውን ! ….
* ተቋሙን ለማዳን ወሳኙ ተሳትፎ …
ነዋሪው ኮሚኒቲውን ለመታደግ ከወዲሁ ካልተጋ አደጋው ሃያል ነው። ምልአተ ጉባኤ ሳይሞላ ቀርቶ ለሶስት ሳምንት የተላለፈው ስብሰባም ሲቀጥል መከረኛውን ህግና ደንብ ይጠቀስና እንደለመድነው በመጣው ሰማንያና መቶ ሰው ምርጫ ከማድረግ የሚመልሰው እንደሌለ ልብ በሉ ! በዚህ ሁኔታ በዝምታ፣ ኩርፊያና ሽሽት ከነጎድን ተመልሰን ወደ መከራው አዙሩቱ እንደሚያስገቡን አትጠራጠሩ ! ዝምታን የመረጠውና የሸሸው ነዋሪ ምክንያት አለው ብንልና ብንዘረዝረውም ችግሩን ለመቅረፍ ዝምታ ፣ ኩርፊያና ሽሽቱ ግን አዋጭ አይደለም ። የኮሚኒቲው አባል በመሆን ንቁ ተሳይፎ በማድረግ ለውጥ ለማምጣት ይቻላል። ሰአቱ አሁን ብቻ ነው ! ሌላው ቢቀር በት/ቤቱ የሚያስተምር ወላጅ ብሶቱን ” እህ ” ብሎ ችሎ የኮሚኒቲው አባል በመሆን በነጻነት የሚፈልጋቸውን መምረጥ አለበት … በአደጋ ላይ ያለውን የትምህርት ተቋም ለጥቂት አፈ ቀላጤዎች በትጉህ ስራቸው ለማናውቃቸው የመንግስት ባለሟሎች ኮሚኒቲውን ማስረከብ የለበትም። በቀጣይም ለበከተው አስተዳደርና አሰራር ሲሳይ አድርጎ በራሱ ጉዳይና ቤት መሸሸቱ አዋጭ አይደለም !
ሲደቆስ ለከረመ ለባጀው ነዋሪ መሰረታዊ ችግር እንዴት መፍትሔ እናምጣ ?
እንደኔ እንደኔ …
ዝምታን ሰብሮ ፣ ኩርፊያን ድል ነስቶ ሽሽትን በማቆም ፣ የኮሚኒቲው አባል በመሆንና በመምረጥ የልጆቻችን ት/ቤት ላይ መወሰን ከቻልን ብቸኛ የተ/ቤታችን ባለቤቶች እንሆናለን ! ይህን እውን ለማድረግ አማራጩ ዝምታ ፣ ኩርፊያና መሸሸት ሳይሆን በቀጠይ ሶስት ሳምንት በተቀጠረው ስብሰባ ለመገኘት የኮሚኒቲው አባል በመሆን አደጋ ያንዣበበበትን ማዕከል መታደግ ይቻላል !
እስኪ ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
ህዳር 19 ቀን 2007 ዓም