ናሽናል ኤርዌይስ 50 በመቶ ድርሻውን የሸጠው በኢትዮጵያ የመጀመርያው የግል የበራራ አገልግሎት በማቋቋም ወደ ሥራ ገብቶ ለነበረው የጎሽ አቪዬሽን ባለቤት ለአቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ናሽናል ኤርዌይስ በአሁኑ ወቅት አራት አውሮፕላኖችን በመከራየት በአገር ውስጥ የበረራ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝና በአትራፊነት የሚታወቅ ነው፡፡
በአቶ ዳዊትና በናሽናል ኤርዌይስ መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት የባለቤትነት ድርሻውን መስጠቱ የኩባንያውን አቅም በማሳደግ አገልግሎቱን ለማሳደግ ያስችለዋል ተብሏል፡፡ እንደ ምንጮቹ ገለጻ፣ አቶ ዳዊት ለ50 በመቶው የባለቤትነት ድርሻ ግዢ ምን ያህል ወጪ እንዳወጡ ባይገልጽም፣ ስምምነታቸውን በቅርቡ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አቶ ዳዊት፣ ጎሽ አቪዬሽንን በመመሥረት በአገር ውስጥ የበረራ አገልግሎት ጀምረው የነበሩ ቢሆንም፣ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት አገልግሎቱ መቋረጡ ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት መቀመጫቸውን ዱባይ ያደረጉት አቶ ዳዊት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ውስጥ የተሰማሩ ሲሆን፣ በተለይ በቅርቡ የራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ላይ 25 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ በመግዛት ከፍተኛ ባለአክሲዮን ሆነዋል፡፡
በዋናነት ግን ኢንቨስትመንታቸውን ዱባይ በማድረግ በአውሮፕላንና በሔሊኮፕተር የመለዋወጫ ዕቃዎች ቢዝነስ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በመድኃኒት አቅራቢነትም የሚታወቅ ኩባንያ ባለቤት ናቸው፡፡
በካፒቴን አበራ ለሜ የተቋቋመው ናሽናል ኤርዌይስ የመንገደኞች በረራ አገልግሎትን ጨምሮ የካርጎና የአየር አምቡላንስ አገልግሎቶችን በመስጠት በዘርፉ ልምድ ያለው ኩባንያ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2008 ጀምሮ በበረራ አገልግሎት ላይ የሚገኘው ይህ ተቋም፣ የዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት አባል ነው፡፡
Source:: Ethiopian Reporter