ነገረ ኢትዮጵያ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና የስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ህዳር 21/2007 ለሚያደርገው ስብሰባ የጻፈውን ማሳወቂያ ደብዳቤ አልቀበልም ማለቱን የትብብሩ ጸኃፊ አቶ ግርማ በቀለ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡
የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ህዳር 21 ለሚያደርጉትና መኢዴፓ ለሚያስተባብረው ስብሰባ ረቡዕ ህዳር 10 የፓርቲው ዋና ጸሃፊ አቶ ዘመኑ ሞላ፣ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ አይችሉም አያል እንዲሁም የድርጅት ጉዳይ ኃላፊው አቶ መሰለ እውኔ ደብዳቤ ይዘው ሄደው የነበር ሲሆን አቶ ማርቆስ ብዙነህ እና እሳቸውን ተክተው ሲሰሩ የነበሩት አቶ ፈለቀ ታመዋል በሚል የከንቲባ ጉዳይ የካቢኔዎች ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው ማሳወቂያ ደብዳቤውን አንቀበልም ማለታቸው ታውቋል፡፡
የመኢዴፓ አመራሮች ህዳር 10 ደብዳቤውን ለመስጠት በሄዱበት ወቅት ‹‹ዛሬ ደብዳቤውን አንቀበላችሁም›› ተብለው የነበር ቢሆንም ለህዳር 12 እንደሚቀበሏቸው እንደገለጹላቸው ይታወሳል፡፡ ይሁንና በትናንትናው ዕለት የመኢዴፓ ፕሬዝደንትና የትብብሩ ገንዘብ ያዥ አቶ ኑሪ ሙደሲር እንዲሁም የሰማያዊ ፓርቲ የፋይናንስ ጉዳይ ኃላፊ ደብዳቤውን ይዘው ቢሄዱም የከንቲባ ጉዳይ የካቢኔዎች ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው የእናንተን ደብዳቤ አንቀበልም እንዳሏቸው ታውቋል፡፡
የትብብሩ አመራሮች ደብዳቤውን የሚቀበላቸው ሲያጡ ጠረጴዛ ላይ ጥለውት የመጡ ሲሆን በፖስታ ቤት በሪኮመንዴ eg156846735et እንደላኩ አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡ የትብብሩ ፀኃፊ አክለውም ‹‹ይህ የሚያሳየው ስርዓቱ ሁሉንም ነገር ጠርቅሞ እንደዘጋና ለህዝባዊ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ያለውን ፍርሃት ነው፡፡ በመንግስት ገንዘብ የሚተዳደር መስሪያ ቤት በገዥው ፓርቲ መሳሪያ መሆኑን ያሳየ ነው፡፡ ሆኖም ግን ትግሉን ከመቀጠልም ሆነ ደብዳቤውን ከመድረስ አያግደውም›› ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህዳር 11/2007 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ ህዳር 7/2007 ዓ.ም ሰማያዊ ፓርቲ በማስባበር ሊያካሂደው የነበረው የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ፀረ ህገ መንግስታዊ ነው በሚል እርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡