“የኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ህገ መንግስታዊ ጥያቄ በአንባገነናዊ ዙፋን ላይ ለመቀመጥ በሽምግልና ስም ለሚፈጸም ዉንብድና የሚቀርብ አይደለም። ግን ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች በዚያ ዙፋን ላይ የሚቀመጠዉን የፖለቲካ ሐይል አወዳድሮ የማጫረት ብቃት ብቻ ሳይሆን፤በዙፋኑ ላይ የሚፈልጉትን የማስቀመጥም የማንሳትም ሐይልም አላቸዉ!”
ከሳዲቅ አህመድ
የኢትዮጵያዉያንን ሰላማዊ ትግል በሐይል መቀልበስ ያልቻለዉ ህወሃት መራሹ መንግስት፤ ትግሉ ወደ ድል ደጃፎች የሚያደርገዉን ጉዞ ለማፋለስ የተለያዩ ሴራዎችን ያሴራል። ከነዚህም የተንኮል መንገዶች ዋነኛዉ በሰላማዊ ትግል ላይ የተሰማራዉን ሙስሊሙን ማህበረስብ ማከፋፈል፣የሰላም አምባሳደር የሆኑትን ኮሚቴዎችን ባደባባይ ባሸባሪነት እየፈረጀ…በምስጢር በጣም ድንቅ የሆኑ የኢትዮጵያ ልጆች መሆናቸዉን በመግለጽ በመንግስት ላይ የሚደረጉ ተቃዉሞዎች ቢረግቡ ሊፈታቸዉ እንደሚችልና ነገሮች ሁሉ ወደነበሩበት እንደሚመለሱ የዉሽት ቃልኪዳን ይገባል። ህወሃት በልማት ስም የሚቀርባቸዉ ወይም ከዲያስፖራ አገር በመግባት ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት ያላቸዉን ሰዎች በመደለል በአንድነት የሚታገለዉን ሙስሊሙን ማህበረሰብ እንዲሸረሽሩ ስዉር የማታለል ተልእኮም ይሰጣል።
አንባገነናዉያን እርቅና ሽምግልናን ከሚገቡበት አጣብቂኝ ለማምለጥ ከሚጠቀሙባቸዉ የማሳሳቻ መሳሪያዎች ዋነኛዎቹ ናቸዉ።ሐይልን ለህዝብ መስጠት የማይፈልግ አንባገነናዊ መንግስት በሽምግልና እና በእደራደራለሁ ማታለያ የአዞ እንባዉን እያፈሰሰ የሰላማዊ ትግል ትሩፋቶችን እንክት አርጎ እንደሚበላ ለማወቅ ብዙ ምርምር ባያሻዉም የአለማችንን ወቅታዊ ሁናቴዎችን ማጤን ብቻ ይበቃዋል። አወቀዉትም ይሁን ሳያዉቁት፣ መልካም ይመጣል ብለዉ በመታለል፣ በሰላማዊ ትግሉ በመዛል (በመዳከም) ነገሮች ወደነበሩበት እንዲመለሱ በመሻት፣ የተጀመሩ ኢንቨስትመቶች እንዲያልቁ ካልያም አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመጀመር መዉጫ ቀዳዳን ለሚፈልገዉ ህወሃት መራሹ መንግስት መዉጫን በነጻ ለመቸር (መዉጫን ጀባ ለማለት) የሚንደፋደፉ ወገኖች በየቦታዉ እየተታዩ ነዉ።
ትላንት በኢህአዴግ የተንገፈገፉ ዛሬ ከኢህአዴግ ጋር መሞዳመዱን ዲሞክራሲያዊ መብት እንደሆነ በድፍረት መግለጽ የጀመሩም አሉ። ኢትዮጵያዉያንን በጅምላ እያገላታ ያለዉን፣ ሙስሊም የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን አስሮ በምድራዊ ቸነፈር ያሰቃየዉን፣ቁርዓንና ሒጃብን ያቀጠለዉን፣ መስጊዶቻችንን የሚያፈርሰዉን፣መስጊዶቻችንን ወርሶ ካድሬ ሚሾመዉን፣ መጽሄት ጋዜጦቻችንን የዘጋዉን፤…ኡለሞች፣ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች ካገር እንዲሰደዱ ያደረገዉን ፣እምነትን ነጥቆ በአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ለማጥመቅ የሚዳክረዉን፣ በደም የተበከሉ እጆቹን በእምነት ተቋም ዉስጥ በማስገባት የአገርን ሉአላዊነት ለማናጋት ሌት ተቀን የሚሰራዉ ህወሃት መራሹ መንግስት ጋር መሞዳመዱ እንደመብት ከታየ…ከሐይማኖት በላይ የመንግስትን አጀንዳ ለማራመድ የሚቅበዘበዙ ጥቂቶች አንገዋሎ መለየቱና መቃወሙ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታ የሆነበት ወሳኝ አጋጣሚ ከፊት ለፊታችን ላይ ተጋርዷል።
“በረዶ አዘል የህወሃት የጥቃት ዶፍ ከመዉረዱ በፊት የአዞእንባ አልቃሹን ህወሃት እንጠንቀቀዉ!”
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች የሚደረገዉን ሰላማዊ ትግል ሙሉ ለሙሉ ቢደግፉም በጣት የሚቆጠሩ ጥቂቶች ግን ለህወሃት መራሹ መንግስት መዉጫ ቀዳዳን ይፈልጉለታል።የህወሃት መራሹን የማታለልና የማዘናጋት ሴራ ወደ መሬት ለማዉረድ የሚንቀሳቀሱ እነማን ናቸዉ?
· ከዲያስፖራ ወደ ኢትዮጵያ የሚመላለሱ የይስሙላ የኢንቨስትመንት ቀረቤታ ያለቸዉ ወይም ኢንቨስት ማረግ የሚፈልጉ ጥቂቶች
· ከባለስልጣናት ጋር ቀረቤታ ያላቸዉ ወይም ባለስልጣን ዘመድ የቤተሰብ አባል ያላቸዉ።ባሉበት የምቾት አለም ዉስጥ በሰላም መቀጠል የሚፈልጉ
· ከመንግስት ባለስልጣናት ሁሉም ነገር ወደነበረበት ይመለሳል ተብለዉ የዉሸት ቃል የተገባላቸዉ
· ዲያስፖራ በሚገኙ ኤምባሲዎች በልማት ስም በብሔር ብሔረሰቦች ጉዳይ ወጣ ገባ የሚሉ
· ከዲያስፖራ ወደ አገር ቤት ባጋጣሚ የሔዱና መሬት ላይ ያለዉን ተቃዉሞ እና የመንግስት በደል በሚገባ ያላጤኑ
· አገር ቤት ሆነው ያንባገነናዊዉ ስርዓት ተጠቃሚ የሆኑ፤ ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች የሚያደርጉት ሰላማዊ ትግል ያላቸዉን መረጋጋት እና ከስርዓቱ የሚያገኙትን ጥቅም የነካባቸዉ
· ከአንባገነናዊዉ ስርዓት ጋር ቁርኝት ያላቸዉና ከስርዓቱ የሚጠቀሙ፤ የሙስሊሞች ቅዋሜ ከገፋ ስርዓቱን ሊንደዉ ይችላል የሚል ፍራቻ ያለቸዉና ስርዓቱን ለማዳን የሚሯሯጡ
· ከሐማኖት በፊት የብሔር ጉዳይ የሚያስቀድሙና ብሔርተኛዉን መንግስት ማዳን የሚፈልጉ
· ህወሃት መራሹ መንግስት ከጥፋቱ ተምሮ እራሱን አሻሽሎ ይስተካከላል ብለዉ የሚያምኑ። ከተስተካከልም በተስተካከለዉ መንግስት ዉስጥ እራሳችንንም ጠቅመን ወገናችንን እንረዳለን ብለዉ በየዋህነት የሚያስቡ
· በማህበረሰቡ ዉስጥ ቦታ የነበራቸዉ ግን ከሰላማዊ ትግሉ ፍጥነት ጋር አበረዉ መጓዝ ያልቻሉ።በድምጻችን ይሰማ በህቡእ የሚደረገው ስኬታማ ትግል ተሰሚነትን የነጠቃቸዉ…የተሰሚነትን ቦታ ፈላጊዎች
· አፈንጋጮች፦ ከብዙሗን አመለካከት ዉጪ የራስቸዉን በጣም አናሳ ንኡስ ክፍል ለመስረት የሚጠሩ። ተምረናል፣አንብበናል በማለት የነርሱ አስተሳሰብ የላቀና የመጠቀ እነደሆነ በማሳየት፤ ብዙሃኑ የሚያደርገው ትግል የመንጋ(mob) ጥረት ነዉ ብለዉ የሚያጣጥሉ። ተግባር የለሽን (theory) ትግል በሞላቀቅና በፍልስፍና ለማስረጽ የሚሞክሩ ናቸዉ።
· አደገኞቹ፦ መንግስትን መቃመም፤ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ክልክል ነዉ የሚል ዲሞክራሲ ከሌለባቸዉ የአረብ አገራት የመጣ አመለካከትን (Dogma) ለመተግበር የሚሹ። እነዚህ አካላቶች ከጠላት ጋር ማበርን ተገቢ ነዉ የሚሉበት አጋጣሚ ስለሚኖር አደገኛነታቸዉን ከግምት ዉስጥ ማስገባቱ ግድ ይላል።
· የሚፈሩ፦ በመላዉ አለም በሙስሊሞች ላይ የሚደረሰዉን ጥቃት በማየት ‘የባሰዉን አታምጣዉ!’ በሚል እሳቤ ‘እስኪያልፍ ያለፋል!’ እያሉ በጭቆና ዉስጥ መኖር የሚፈልጉ።
· ግራ የተጋቡ፦ የሙስሊሙን ህገመንግስታዊ መብት መከበር ቢደግፉም፤ ህወሃት መራሹ መግስት በአወሊያ ያቋቋመዉ የስሙላ ቦርድና መጅሊስን አስመልክቶ ያደረገዉ የሐስት ምርጫ ለዉጥ ነዉ ብለዉ ማመካኛ(excuse) የሚሰጡ። በድንበር የለሹ የህወሃት ፕሮፓጋንዳ ግራ የተጋቡ።
· ጀዝባ እና ስራ ፈቶች፦ በሱስ የተጠመዱ፣ የኔ የሚሉት ስራ የለላቸዉ ማንኛዉንም መግስታዊ ሴራ በርካሽ ክፍያ ከመፈጽም ወደ ሗላ የማይሉ ናቸዉ። እነዚህ ግለሰቦች ዛሬን በልቶ ማደር እንጂ ነገን አርቀዉ መመልከት የማይችሉም ናቸዉ። በህገወጡ መጅሊስም ይሁን በመስጊድ ነጠቃ ወቅት የመንግስትን ሴራ ለማስፈጽም ያለ እፍረትና ፍርሃት ይንቀሳቀሳሉ።
የሌላ እምነት ተከታዮችን መላክ፦
መፍትሔዉ ያለዉ ህወሃት በቂሊንጦ እስር ቤት አስሮ በሚያሰቃያቸዉ የሰላም አምባሳደሮችና የሚሊዮኖች ወኪሎች ዘንድ መሆኑንን እያወቀ፤ ቀደም ሲል ህወሃት ከተቃዋሚዎች ጋር በነበረዉ ችግር አመርቂ የፖለቲካ ስራ ያሰራቸዉን ሰዎች ዛሬም የሙስሊሙን ሰላማዊ ትግል ለማሰናከል ሲጠቀምባቸዉ ይስተዋላል።ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ካለፉት የፖለቲካ ስተቶች የተማሩ በመሆናቸዉ ህወሃትን ያልተበላበትን እቁብ እንዲፈልግ እያሳፈሩት ነዉ።
‘ድመትን በር ዘግተህ አትደብድባት’ የሚለዉ አባባል በራሱ አንባገነናዊ የዞረ ድምር ለናወዘዉ ህወሃት መልስ ሰጪ ነው። የህወሃት መዉጫ ቀዳዳ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የጠየቀውን ጥያቄ ባግባቡ መመለስና መመለስ ብቻ ነዉ። ባቋራጭ የሚፈለጉ መዉጫ ቀዳዳዎች ሽንቁር (ክፍተት) ለመፈጠር ከሚደረጉ የጨቋኝ ፈላጭ-ቆራጮች ሴራ ቢሆኑ እንጂ ምንም ሊሆኑ አይችሉም። በርግጥ ህወሃት መራሹ መንግስት መፍትሔን የሚሻ ከሆነ እራሱ ወደ አዘጋጀዉ የማጎሪያ እና የማሰቃያ ቀዬ ወደሆነዉ ቂሊንጦ እስር ቤት ዝቅ ቢል መፍትሔን ያገኛል። ካልያ የድመቲቱ ተረት እዉን መሆኑ አይቀሬ ነዉ።
በርግጥ ድመቲቱ መዉጫ ቀዳዳ ስታጣ ልትቧጥጥ ልትቧጭር ትችላለች፤ በስተመጨረሻ ግን ያካባቢዉ ሰዉ ተሰባስቦ ያቺን መረን የለቀቀች ድመት በቁጥጥር ስር ያዉላታል። እነሆ የድመቲቱን መቧጨርና መቧጠጥ የቻለዉ ትዉልድ ትግላችን እስከድል ደጃፎች ድረስ በአላህ ፍቃድ ይቀጥላል እያለ ወደፊት እየገሰገሰ ነዉ።
ከልብ የሰረጸ ህዝባዊ እንቅስቃሴ አይቀለበስም።ተወልዶ፣ አድጎ፣ ጎርምሶ፣ ወጣትን የተላበሰዉ ሰላማዊ ንቅናቄ ጎልማሳ ሲሆን ብልሃትና ዘዴን ይቀዳጃል። ብልሃትና ዘዴን የተቀዳጀዉ ሰላማዊ ንቅናቄ ወሳኝ ለዉጥን ለማምጣት ስልታዊ ዝምታን፣ስልታዊ ማፈግፈግን እና ስልታዊ ቅኝትን ይጠቀማል። ጉዞዉ ረጅም መሆኑንን የተረዱት ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች የትግል ሐይልን ለመቀዳጀት ስልታዊ አካሔድን ሲመርጡ ስጋት የገባዉ ማፍያዉ ህወሃት ኮንደሚኒየም፣ መሬት እሰጣችሗለሁ በማለት የድለላ ተገባር ወደ ማህበረሰቡ የሚልካቸዉ የፖለቲካ ቤተ-ሙከራ የዋሃን ሰራተኞች መሰማራታቸዉ እየታየ ነዉ። እፈኝ የማይሞሉ የዋሃን ከህወሃት በላይ እምነታቸዉን በህዝበ ሙስሊሙ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ እና በድምጻችን ይሰማ ላይ ጥለዉ ቢረጋጉ መልካም ነዉ የሚልም ትችት ይሰነዘራል።
“ዝምታ ወርቅ ነዉ!” በኢንቨስትመንትም ይሁን በኮንዶሚኒየም ስጦታ ወይም በሌላ ጥቅም የተሸበቡ ሰዎች በዝምታ ልማታዊ ዜጎች መሆን ይችላሉ። ግን ድንበርን አልፈዉ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ደሙን ያፈሰሰበት ትግል ላይ በደም የተጨማለቀዉን የህወሃት እጅ ለማጠብ ደፋ ቀና የሚሉ ከሆነ…ከጨቋኝ ጋር በማበር ለሚመጣ ተጠያቂነት እራሳቸዉን ለምን ያጋልጻሉ የሚልም ጥያቄ ይነሳል።
ህዝብ በሰላማዊ ትግል የሚቀዳጀዉ ዉጤት ዘገምተኛ እና ዘለቄታዊ ነዉ። በዚህ እልህ አስጨራሽ የትግል ሒደት ዉስጥ ግዜ ዋነኛ መሳሪያ ነዉ። የግዜን መዝለግ ለራስ ጠቀሜታ እንዲዘነበል ለማደርግ አንባገነናዉያን የግዜን ስርቆት ይፈጽማሉ። ቀደም ሲል ግዜን ለመስረቅ ያደባዉ ህወሃት ህዝብን ያልማከለ የሽምግልና ሴራዉን ፈጽሞ አይደለም ሽምግልናዉ ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ለማሰባሰብ በሰሜን አሜሪካ የሚገኝ እደዣንጥላ የተዘረጋ ድርጅት መክኗል። አሁንም ዳግም ህወሃት በመደራደር ስም ያደመነዉ የጥቃት ደመና በረዶ አዘል ዶፉን ሊያዘንበዉ እየጠቋቆረ በመሆኑ ጥንቃቄ በሚያሻበት ወስኝ ወቅት ላይ እንገኛለን።
በጽናት መታገል እንጂ መለሳለስ አንባገነናዉያንን አያረግባቸዉም። ጫናዉ ግፊቱ ሊቀጥል ይገባል፤ ህወሃት መዳራደር ከፈለገ ከዲያስፖራ በልማትና በኢንቨስትመንት ስም ወይም በካንዳሚኒየምና መሬት ታገኛላቹ ድለለላ በመለመላቸዉ ግለሰቦች ሳይሆን፤ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ ተመርጠዉ ዛሬ ቂሊንጦ እስር ቤት ከሚገኙ ጀግኖች ጋር ነዉና ልብ ያለዉ ልብ ይበል።
“በረዶ አዘል የህወሃት የጥቃት ዶፍ ከመዉረዱ በፊት የአዞእንባ አልቃሹን ህወሃት እንጠንቀቀዉ!”