ነገረ ኢትዮጵያ
‹‹ችግሮች በአስቸኳይ ካልተፈቱ ለበላይ አካል እናሳውቃለን›› ፈትያ የሱፍ
‹‹ችግሮቹ ውጫዊ ናቸው›› አቶ ሽመልስ ከማል
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል እና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህልና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፈትያ የሱፍ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዙሪያ እየተወዛገቡ እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
አቶ ሽመልስ ከማል የፕሬስ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ሲሆኑ፣ ላለፉት አራት አመታት ድርጅቱ በተለያዩ ችግሮች ተዘፍቆ እያለ በቦርድ ሰብሳቢነታቸው ችግሮቹን መፍታት የነበረባቸው ቢሆንም ተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎችን ችላ በማለት ድርጅቱ ከእነ ችግሮቹ እንዲዘልቅ አድርገዋል በማለት የባህልና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፈትያ የሱፍ ተናግረዋል፡፡ ሰሞኑን የ2007 የበጀት እቅድን ለመገምገም በተገናኙበት ወቅት የፕሬስ ድርጅት ቦርድ እና አስተዳደር በበርካታ ችግሮች ዙሪያ ወቀሳ እንደደረሰበትና ችግሮቹ እንዲፈቱም ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠ በራሱ ድርጅት እየታተመ የሚወጣው ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ በቅዳሜ እትሙ አስነብቧል፡፡
በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የአስተዳደር ብልሹነት መኖሩን የተናገሩት ፈትያ የሱፍ፣ ‹‹በራሱ ድርጅት በችግር የተተበተበ ጋዜጠኛ እንደምን የሌሎችን ድርጅቶችና ግለሰቦች የአሰራር ችግሮች ሊያጋልጥ ይችላል?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አክለውም በተደጋጋሚ ችግሮቹ ለድርጅቱ አስተዳደር በሰራተኞች ሲቀርቡለት የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ እያለ ማለፉን የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ አውስተዋል፡፡
ፈትያ የሱፍ እንደሚሉት የፕሬስ ድርጅት ቦርድ እና አስተዳደር ችግሮቹን በአስቸኳይ የማይፈታ ከሆነ ወደሚመለከተው ከፍተኛ አካል ለማስተላለፍ ከውሳኔ ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡
የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል በበኩላቸው የድርጅቱ ችግሮች ውጫዊ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ድርጅቱ የበጀት ችግሮች እንዳለበት ያወሱት አቶ ሽመልስ፣ በተጨማሪ ግን በድርጅቱ ላይ መጥፎ እይታ ያላቸው እና መጠቀሚያ ለማድረግ የሚፈልጉ አካላት በሰራተኞች ስም አላማቸውን ለማስፈጸም የሚሯሯጡ ወገኖች አሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
‹‹የግል እና የመንግስት ሚዲያ ይለያያሉ፤ በአመለካከት፣ በአሰራርና በጥራት ልዩነት አላቸው›› በማለትም ሰራተኞቹ ፕሬስ ድርጅት እንደ ግል ሚዲያ ሊሰራ እንደማይችል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰብስቤ ከበደ እና አቶ ሽመልስ ከማል ከፍተኛ የሆነ የጥቅም ትስስሮሽ እንዳላቸው የሚገልጹት የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች፣ በዚህ ትስስራቸው የተነሳም የአቶ ሽመልስ ከማል ባለቤት ያለምንም ውድድር በድርጅቱ በጋዜጠኝነት ተቀጥራ ምንም ስራ ሳትሰራ ደመወዝ ትወስድ እንደነበር፣ በኋላ ግን ‹ስራውን አልቻልኩትም› በሚል ከድርጅቱ እንደወረጣች ይናገራሉ፡፡
አቶ ሰብስቤ ከበደ በሰራተኞች ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው እና በተለያዩ ስብሰባዎች በይፋ ‹አልቻልክም ድርጅቱን ልቀቅ› ተብለው በሰራተኞች እንደተነገራቸው ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ግን ከአቶ ሽመልስ ከማል ጋር ባለቸው የጥቅም ትስስር በስልጣናቸው እስካሁን እንደሚገኙ፣ ይህም ድርጅቱን እና ሰራተኞችን እየጎዳ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡