ቀጥሎ ያለው አጭር መልዕክት ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በእስር በሚገኝበት ቃሊቲ ለተገኘው የነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር የገለጸው መልዕክቱ ነው፤ እንዲህ ቀርቧል፡፡
‹‹ነገሮችን ማወሳሰቡ ለማናችንም አይጠቅምም፡፡ ደግሞ በማናቸውም መልኩ የተወሳሰበ ችግር በመካከላችን ያለ አይመስለኝም፤ የለምም፡፡ እኛ እንደ ሀገር እና ህዝብ ከልዩነታችን ይልቅ አንድነታችን ይልቃል፡፡ ጥልቅ የሆነ ትስስሮሽ በመካከላችን አለ፡፡ በመነጣጠልና የህዝብ ተቆርቋሪዎችን በማሳደድ ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ የሚሮጡትን ወደጎን መግፋት ይኖርብናል፡፡ ከምንም በላይ ህዝብ እና ሀገር ይቀድማል፡፡
‹‹አሁን እዚህ እስር ቤት ውስጥ ስላለው ነገር ብነግርህ ብዙ ጊዜ ልወስድብህ እችላለሁ፡፡ ነገር ግን ፈረንሳያውያን አንድ አባባል አላቸው፤ ‹ፊቴን፣ አካባቢየን ካየህ በቂ ነው፣ ነገሮችን ከእኔ እና አካባቢየ ላይ ማንበብ ትችላለህ› የሚል ነው አባባሉ፡፡ እዚህ ግቢ ስትገባ ያለው ሁኔታ ደስ እንደማይል ማንበብ አያቅትህም፡፡ ብዙ ነገሮች አሉ፣ ጊዜ ጠብቀው ይፋ ይሆናሉ፡፡
‹‹እንደ እናንተ ሁሉ ሰዎች መጥተው ሲጠይቁኝ ደስ እሰኛለሁ፡፡ ለምሳሌ በዛሬው የእናንተ መምጣት ምክንያት ለ15 ቀናት ያህል ተረጋግቼ እሰነብታለሁ፡፡ ትልቅ የሞራል ስንቅ አለው፡፡ እንዳልኩህ ግን መሰረታዊው ጉዳይ በሀገር ደረጃ ያለውን ትስስሮሽ ከችግሮቻችን መውጫ መንገድ አድርጎ መጠቀም መቻሉ ላይ ነው፡፡ ይህ ነው የሁላችንንም ተስፋ ወደ እውነታ የሚለውጠው፡፡ ስለ ወደፊቱ ማሰብ ይኖርብናል፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታ ወደ ተሻለ ነገር መለወጥ አለበት፡፡
↧
Article 2
↧