ከየካቲት 1966 ጀምሮ አንዳዶች የሚድኸዉ መፈንቅለ መንግሥት፤ ሌሎች አዝጋሚዉ አብዮት፤ ሌሎች ደግሞ ግብታዊዉ ለዉጥ የሚሉት አብዮት የወደፊት ሒደት በግልፅ የታየበት፤ደርግ «ያለ ምንም ደም» ከሚለዉ መሪ መፈክሩ በታቃሮኑ መቆሙ የተረጋገጠበት፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዞም በደም «በጨቀየ» ጎዳና መደናበር የጀመረበት ወቅት ነዉ።
የዛሬ አርባ ዓመት በእዚሕ ሰሞን ለረጅም ዘመን ኢትዮጵያን የገዟት የንጉሠ-ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአዲሶቹ ወታደራዊ ገዢዎች የተረሸኑበት፤ በመረሸናቸዉ ኢትዮጵያዉያን በሐዘንና ደስታ ተቃራኒ ስሜት የቆዘሙበት ወር ነበር፤ ኅዳር 1967።
ከየካቲት 1966 ጀምሮ አንዳዶች የሚድኸዉ መፈንቅለ መንግሥት፤ ሌሎች አዝጋሚዉ አብዮት፤ ሌሎች ደግሞ ግብታዊዉ ለዉጥ የሚሉት አብዮት የወደፊት ሒደት በግልፅ የታየበት፤ ደርግ «ያለ ምንም ደም» ከሚለዉ መሪ መፈክሩ በታቃራኒው መቆሙ የተረጋገጠበት፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዞም በደም «በጨቀየ» ጎዳና መደናበር የጀመረበት ወቅት ነዉ።
ለዘወዳዊዉ ሥርዓት መፍረስ በተለያየ መስክ የተሠማራዉ የእዚያ ዘመኑ ኢትዮጵያዊ ትዉልድ በየፊናዉ ያደረገዉ ተቃዉሞ፣ አድማ፣ ሠልፍና አመፅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉ ሐቅ ነዉ።
ግን ያኔ የከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት ተማሪዎችን፤ መምሕራንና ምሁራንን ያክል በግንባር ቀደምትነት ለለዉጥ የታገሉና ሕዝብን ለለዉጥ የቀሰቀሱ ወገኖች ጥቂቶች ናቸዉ። ዘዉዳዊዉን ሥርዓት በመቃወም ለለወጥ ባንድ አብረዉ የታገሉት ኃይላት ግን ከለዉጡ ዋዜማ ጀምረዉ በተለያየ የፖለቲካ ፓርቲ በመደራጀት ጎራ ለይተዉ መሻኮት፤ መወጋገዝ፤ በስተመጨረሻዉም እስከ መገዳደል በደረሰ ቅራኔ ተወጠዋል።
እንዳድ ወገኖች የያኔዎቹ ወጣቶች የገቡበት ቅራኔ ኢትዮጵያን እስከ ዛሬ ለተረፋት ፖለቲካዊ ቀዉስ ዳርጓታል የሚሉ አሉ። ታሪኩ ረጅም፤ ክርክሩ ሠፊ፤ ሰበብ ምክንያቱም ዉስብስብ በመሆኑ በእዚሕ አጭር ዉይይት ገሚሱን እንኳን መዳደስ አንችልም። እንዲያዉ በደምሳሳዉ የእዚያ ትዉልድን ትዉስታ፤ ጉጉት፤ ዉጤት-ዉድቀታቸዉን፤ ተሞክሯቸዉ ላሁኑ ትዉልድ የሚኖረዉን አስተምሕሮ በጨረፍታ ለመቃኘት እንሞክራለን።
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
Source:-dw.de