( ዐባይ ዐሥራት፤ ጀርመን)
ስለኢትዮጵያ መንግሥት (ለዚያውም መንግሥት ከተባለ) ግብሩን አይተው የሚጠሉት ሰዎች ብዙ ስላሉት ያንኑ ጉዳይ መልሼ እዚህ ላይ መድገም አልፈልግም። በዚሁ መንግሥት የሚመስል ቅርጽ ባለው፤ ነገር ግን ባለጌና የመንግሥት መገለጫ ክብር በሌለው የአራት ኪሎው መንግሥት ተብዬ ላይ የሚጻፉ ብዙ አግባብነት ያላቸውና ክፋቱን እየመዘኑ በመጠን የለሽ ጥላቻ ተጽፈው የሚወጡት ጽሁፎችን ሳነብ ቆይቻለሁ።
እኔን ግን ለመጀመሪያ ጊዜ እንድጽፍ ያነሳሱኝ ምክንያቶች በጣም ያበሳጩኝና የኢትዮጵያ መንግሥት ለመባል የሚያስችል ማንነቱን አጥቼ ያየሁበት መንግሥታዊ ብልግናና ክብር የለሽ ተግባሮቹ ናቸው። እነዚህም አምስት እይታዎቼ መሬት ላይ በግልጽ የሚታዩ ሆነው ሳለ እንደብልግና የማይቆጥራቸው ነገር ክብር ሊሰጠው እንደማይገባ የሚያሳብቁበት ከበቂ በላይ ምክንያቶችን ለመጥቀስ በመፈለግ ነው።
1/ የመፍትሄ አፈላላጊ የእስልምና ኮሚቴዎችን በመለከተ
ባለጌው መንግሥት ከ17 የእስልምና መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ጋር በፌዴራል ጉዳዮች ክብር የለሽ መስሪያ ቤቱ በኩል የሃሳብ ልውውጥ በማድረግ ለጥያቄዎቻቸው መፍትሄ መስጠት እንዲቻል ለወራት ሲነጋገር መቆየቱ ሀገር ያወቀው፤ ጸሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው። በዓለማችን ላይ እየተሰከተ ካለው የአክራሪነት መንፈስ አንጻር አሸባሪነት የለም ወደሚል መደምደሚያ ባንደርስም ኢትዮጵያውያን ሙስሊም ኮሚቴዎችን ከንግግርና ከውይይት መድረክ ወደአሸባሪነት በአንድ ጊዜ የሚቀይራቸው አመክንዮ ለማቅረብ የባለጌነትን ጠባይ መላበስ ይጠይቃል። ኮሚቴዎቹ፤ ኮሚቴ መሆናቸው ከመነገሩና ከባለጌው መንግሥት ጋር መነጋገር ከመጀመራቸው በፊት አሸባሪ የተባለና በማስረጃ የቀረበ ክስ ሳይኖርባቸው ባለጌው እንዲሆኑለት የሚፈልገው ሳይሆን መቅረቱን ሲያረጋግጥ በእጁ ባለው የብልግና ህግና ጠመንጃ ታግዞ አሸባሪ ማለቱ የብልግናውና የክብር የለሽነቱ ልክ የት ድረስ እንደሆነ ከሚያሳይ በቀር የታሳሪዎቹን አሸባሪነት በጭራሽ ሊያረጋግጥ የሚችል አይደለም። ብልግና ቁጥር አንድ!
2/ አሸባሪነት እየተስፋፋ መምጣቱን እንደሽፋን በመጠቀም ሲያነጋግራቸው የቆያቸውን ኮሚቴዎች ፤ አሸባሪ ሆነው ቢገኙ እንኳን ካሰረ በኋላ በመደብደብ፤ በማሰቃየት፤ አንዳንዶቹንም በካቴና ጠፍንጎ በማስለፍለፍ በመከራ እሳት መጥበሱን ስመለከት ወደአእምሮዬ የመጣው ፤ ምንም ነገር በእጃቸው ያልያዙ፤ በእጁ ላይ የወደቁ፤ ከቃሊቲ የካቴና እስር ወጥተው መፈንቅለ መንግሥት ሊያደርጉ የማይችሉ ዜጎች ላይ ያንን መፈጸሙ በእውነት የአራት ኪሎው መንግሥት የመጨረሻ ባለጌና ክብር የሌለው/ በእነሱ ቋንቋ ሲገለጽ/ ወራዳና ባለጌ መንግስት ነው። ብልግና ቁጥር ሁለት!
3/ ወራዳው መንግሥት እንደተመኘውና ድንገት ከጠረጴዛው መዞ እንደለጠፈባቸው የአሸባሪነት ተግባር ኮሚቴዎቹ ለእሱ አሸባሪዎቹ ሆነዋል ብለን ብንቀበል እንኳን ብልግናውን መሸፈን የማይችል የወራዳነት ሥራውን ደጋግሞ ሲያሳየን እንመለከታለን። ሰዎቹ በባለጌው እስር ቤት ወድቀዋል። የባለጌው ፍርድ ቤትም የብልግና የፍርድ ሂደቱን ጀምሯል። ምን ሊወሰንባቸው እንደሚችል ህግ ተጠቅሶ ከመወሰኑ በፊት ይታወቃል። ባለጌው መንግሥት አሸባሪ የተባሉት ሰዎች ላይ በብልግናው ፍርድ ቤት የፈለገውን ውሳኔ ማስወሰን እየቻለ ወይም ማስወሰን ስገባው ብልግናው ለከትና አቅል የሌለው ስለሆነ «ጀሐዳዊ ሀረካት» የሚል ፊልም ራሱ ሰርቶ ፍርድ ቤቱ በአሸባሪዎቹ ላይ ምን ማስረጃ እንደሚያቀርብ፤ ምን ሊወስን
እንደሚችል በማሳየት ራሱ የታሳሪዎቹን መጨረሻ ለመናገር የቸኮለ ባለጌና የህግ እስረኛ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ የማይፈልግ ባለጌ መንግስት ነው። ከእንግዲህ ፍርድ ቤቱ የብልግናው አስፈጻሚ እንጂ አከራካሪ ሊሆን እንደማይችል ራሱ አሳይቶናል። ከእንግዲህ ፍርድ ቤቱ በነጻ ለቅቄአለሁ ካላለ በስተቀር በ5 ዓመት 10 ዓመት፤ እድሜ ልክና በሞት ቀጥቻለሁ ቢል የጀሀዳዊ ሀረካት ውጤት መሆኑን እንድንቀበል ራሱ በለቀቀው ፊልም ነገሮናል ማለት ነው። የብልግናው ፍርድ ቤት የብልግና ፍርድ እስኪሰጥ የማያስታግሰው እንዲህ ዓይነት ባለጌና ክብር የሌለው መንግሥት የትም ሀገር አላየንም። አምባገነኖች ወይ ግንብ አስደግፈው ይገድላሉ፤ አለበለዚያም ነፍሱ እንዳትወጣ ቁራሽ እየወረወሩ በእስር ያማቅቃሉ እንጂ እንዲህ ዓይነት በፍርድ ስም ብልግና በመፈጸም ጊዜያቸውን አያጠፉም። ብልግና ቁጥር ሶስት!
4/ ባለጌውና የመንግስትነት ክብር የሌለው ይኸው ወራዳ መንግሥት አሸባሪዎች ባላቸው ሰዎች ላይ ከፍርድ ውሳኔ በፊትና በፍርድ ሂደቱ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር በሚችል መልኩ አስቀድሞ ፊልም ሰርቶ በታሳሪዎቹ ማንነት ላይ የባለጌ አፉ በሆነው በቴሌቪዝኑ ሲለቅ አግባብነት ያለው ያህል ሳያሳፍረው፤ የሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ የፖለቲካና የሚዲያ ታሳሪዎች ሁሉ ይፈቱ ብለው ሲጠይቁ በፍርድ ሂደቱ ላይ ተጽእኖ ለማሳደር በማለት ማላገጡ በእርግጥም የብልግናው ጣሪያ የት ድረስ እንደሆነ ከሚያሳይ በስተቀር የሰማያዊ ፓርቲ ጥያቄዎች ከባለጌው መንግሥት የጂሀዳዊ ሀረካት ጋር በምንም ሚዛን የሚለካ አይደለም። ሰማያዊ ፓርቲ «መንግሥታዊ ሐረካት» የሚል ፊልም ሰርቶ በፈለገው ሚዲያ ቢያስተላልፍ ይህ ባለጌ መንግሥት ምን ሊል ነበር? ይህ ባለጌ መንግስት ራሱ በሌሎች ላይ ሲለጥፍ እንጂ እሱ የለጠፈውን ስም ማጥፋት ሲቃወሙ ዓይኑ ደም የሚለብስ ክብር የለሽ መንግስት መሆኑን አረጋግጧል። ብልግና ቁጥር አራት!
5/ የወራዳው መንግስት የተቀደደ ቁና የሆነው፤ አቶ ሼምየለሽ ከማል፤ የበረከትን መልእክት ተቀብሎ አረፋ እየደፈቀ የባለጌዎች መጫወቻ በሆነው ቴሌቪዥን ለመናገር ሲያቆበቁብ ቶሎ የመጣልኝ ነገር ባለጌዎች ምን ጊዜም ሌሎች የሚያውቁባቸው ስለማይመስላቸው ምን ዓይነት ብልግና ሊናገር ይሆን? ብዬ ነበር። እንዳልኩትም የፍርድ ሂደቱ ላይ ተጽእኖ ለማሳረፍ ሰማያዊ ፓርቲ ጀሀዳዊ ሀረካት ዓይነት ስራ ሰራ ለማለት ከመፈለጉም በላይ መንግስትና ሃይማኖትን ቀላቅሏል በማለት ሲዋሽ ታይቷል። አቶ ሼምየለሽ /Shameless Kemal/ የሚናገረውን የማያውቅ ሆኖ ሳለ እንዴት ዴኤታ ሊባል ቻለ?በወቅቱ የጠየኩት ጥያቄ ነው።
መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ፤ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ አይገባም ማለት ሃይማኖታዊ መብቴ ይከበርልኝ ብለው ባለእምነቶች አይጠይቁም ማለት አይደለም። ሃይማኖታዊ የመብቴ ይከበርልኝ ብሎ መጠየቅ በመንግስት ጉዳይ መግባት የሚሆነው በባለጌዎች ዘንድ እንጂ ህግ በሚያውቁ ዜጎች ፊት ሊሆን አይችልም። እስከሚገባኝ ድረስ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ አይገባም፤ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ማለት መንግሥታዊ ሃይማኖት አይኖርም፤ ወይም ሃይማኖታዊ መንግሥት የለም ማለት እንጂ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች ህገ መንግስቱ የሰጣቸውን ሃይማኖታዊ የመብት ጥያቄ አያቀርቡም ማለት አይደለም። አቶ ሼምየለሽ ከማል ግን የባለጌ መንግስት ውጤት በመሆኑ ዘወትር የሚያላዝንበትን የራሱን ህገመንግስት ትርጉም እንኳን በጭራሽ አያውቅም። ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ ላይ ሃይማኖታዊ ነጻነት ይከበር ብሎ መጠየቅ አይችልም? መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ገብቷል፤ ይህም ህገመንግስቱን የጣሰ ስራ ነው ብሎ መጮህ አይችልም ማለት ነው?
እንዴት ጣሰ? መቼ ጣሰ? ለሚለው የፓርቲው ጥያቄ መንግስት አግባብነት ባለው የመልስ አሰጣጥ ሂደት ላይ ምላሹን ከሚሰጥ በስተቀር በባለጌ ወንበር ላይ ተቀምጦ በቴሌቪዥን ማስፈራራት ተገቢ ነው?
ፖለቲካዊ ነጻነት ይከበር፤ ህገ መንግስታዊ ነጻነት ይከበር ብሎ መጠየቅ አይችልም ማለት ነው? ወራዳ መንግስት ወትሮውንም ውርደቱን ገላጭ ከሆነ ማንነቱ መውጣት ስለማይችል መብቴ ይከበር ብሎ መጠየቅን እንደወንጀል ይቆጥረዋል። መብት በተከበረበት ሀገርማ ጓንታናሞ ይዘጋ፤ ታሳሪዎቹ ወደአሜሪካ መደበኛ እስር ቤቶች ይዛወሩ እስከማለት ድረስ ድምጽ ማሰማት ይቻላል። በፍርድ ቤት የተያዘን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የተፈረደባቸው ሰዎች ይለቀቁ እስከማለት የመጮህ መብት የተከበረ ነው። ሌሎች ህግንና ህግን ብቻ መሰረት አድርገው በሚፈርዱ ሀገራት ሳይቀር ሰልፍ ማድረግ ከተቻለ በባለጌው የኢትዮጵያ መንግሥት ፍርድ ቤት ውሳኔማ እንዴት አብዝቶ አይጮህ? እውነት ለመናገር ርእዮት ዓለሙ የኢትዮጵያን ህዝብ አነሳስታ፤ ጠመንጃ ተሸክሞ የተጫነብንን የአራት ኪሎውን ባለጌ መንግስት ለመገልበጥ ስትሞክር ተገኝታ ነው የታሰረችው? የባለጌው ማኅበር አባላት ሳይቀሩ በዚህ የብልግና አባባል ያፍራሉ። መቼም ባለጌ ራስ እንጂ ሰብአዊ ኅሊና የለውም። መንግስታዊ ባለጌም ኅሊና ቢስ ነው። ክብር የለሽ መንግስት! ቃላችሁን ተውሼ፤ መልሼ ብነግራችሁስ? ወራዳ መንግስት!!!
( ዐባይ ዐሥራት፤ ጀርመን)