Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የልጅቷ እምባ –ከሳዑዲ አረቢያ መልስ – (እውነተኛ የወንጀል ታሪክ)

$
0
0

እመቤት ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገሯ በመመለሷ ደስተኛ ሆናለች፡፡ በ1993 ዓ.ም መስከረም ወር አካባቢ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ስትጓዝ መንገዱ አልጋ በአልጋ ሆኖላት አልነበረም፡፡ ከ10 ክፍል በላይ ልትቀጥለው ያልቻለችውን ትምህርት ትታ አዲስ አበባ ውስጥ መቀመጥ አልታያትም፡፡ የተወለደችውና ያደገችው ጅማ ቢሆንም ወደ አዲስ አበባ ከመጣች ግን ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ እናቷ ወታደር አባቷን ተከትለው ሸገር ሲገቡ እሷ በአያቷ እጅ ነው ያደገችው፡፡ አያቷ ከልጅነቷ ስላሳደጓት እናትና አባት ጅማን ለቀው ወደ አዲስ አበባ ለመክተም ጓዛቸውን ሲጠቀለልጁ ‹‹እሷን ከእኔ ነጥላችሁ ከወሰዳችሁ እናት አለኝ ብለሽ እንዳትመጪ- እንደሞትኩ ቁጠሪኝ›› ብለው ስለተማረሩ ነው እመቤት እዚያው እንድትቀር የተወሰነው፡፡ የመጀመሪያ ልጅ ብትሆንም ወትሮም ከእናትና አባቷ ይልቅ የምታውቀው የአያቷን ጣእም ነውና ከርሳቸው ተለይታ ወላጆቿን ተከትላ አዲስ አበባ መግባትን አልወደደችም፡፡ አድጋና ነፍስ አውቃ 8ኛ ክፍልን ስትጨርስ ግን አዲስ አበባ መጥታ መማር እንዳለባት የወሰነችው ራሷ ናት፡፡ አንድም ያሳደጓት አያቷ በድንገተኛ ህመም የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሳለች በማረፋቸው ሌላም አዲስ አበባ ገብታ ብትማር የተሻለ መሆኑን ስላሰበች እናትም ስለገፋፏት ነው ሸገር የገባችው፡፡
crime
ዛሬ 10ኛ ክፍልን ብታጠናቅቅም ከዚያ በላይ ለመግፋት የሚያስችል ነጥብ አልመጣላትም፡፡ ስለዚህ ስራ ከመፍታት ብላ በተለያዩ ካፍቴሪያዎች ውስጥ የአስተናጋጅነት ስራ ሞክራለች፡፡ ነገሩ ‹‹ከእጅ አይሻል ዶማ›› ሲሆንባት ነው ወደ ውጪ ሀገር ስለመጓዝ ማለም የጀመረችው፡፡ በወቅቱ በቀላሉ ልትጓዝበት የምትችልበት መንገድ የሃጂና ዑምራ ጉዞ ነው፡፡ አንድ ሰው በደላላ አግኝታ የእርሱ ሚስት እንደሆነች ተደርጎ በሙስሊም ስም ፓስፖርት ካወጣችና ኒካ ካሰረች በኋላ ፕሮሰሱ ብዙ አልቸገራትም፡፡ ከወላጆቿ አስቸግራና ራሷም ያጠራቀመችውን ገንዘብ ጨምራ በ6 ሺ ብር ወጪ ከሃጅና ዑምራ ተጓዦች ጋር ተቀላቅላ ዘይነባ በሚል ስም ሳዑዲ ገባች፡፡ አራት ዓመታትን ያሳለፈችው በተለያዩ ቦታዎች የቤት ሠራተኛ ሆና በማገልገል ነበር፡፡
ዛሬ አዲስ አበባ ስትመለስ የተሰማት ስሜት ልዩ ነበር፡፡ ወላጆቿን ማግኘቷና ታናናሽ እህትና ወንድሞቿን አድገው ማየቷ- ከዚህም በላይ የናፈቀችውን አገሯን ደግሞ ለመመልከት በመታደሏ ደስ ብሏታል፡፡ አመጣጧ ለእረፍት ሲሆን ከ5 ወር በኋላ በሌላ ወረቀት ወደ መጣችበት አገር ለመመለስ እቅድ ይዛለች፡፡

ጊዜዋን ከወላጆቿና ከምታውቃቸው ጓደኞቿ ጋር እያሳለፈች ነው፡፡ አዲስ አበባ ከገባች ከ15 ቀናት በኋላ ነበር ወደ ጅማ ሄዳ ዘምድ ወዳጆቿን ለመጠየቅ የተነሳችው፡፡ እናቷ አብረዋት ሊሄዱ ከተነሱ በኋላ የግል ጉዳይ ስለገጠማቸው በሌላ ቀን ሊመጡ ተነጋግረው ነው ብቻዋን የተጓዘችው፡፡ ለዘመድ አዝማድ የሚሰጡትን ስጦታዎችና የገዛቻቸውን ነገሮች ይዛ በአውቶብስ ወደ አባ ጅፋር ሀገር ጉዞ ጀመረች፡፡ ይህ ጉዞ ለእመቤት ዘመዶቿንና የናፈቋትን ጓደኞቿን የምታይበት ብቻ ሆኖ አልቀረም፡፡ በመንገዱ ላይ አጠገቧ ተቀምጦ ከነበር አንድ ሰው ጋር ለመተዋወቅ እድል ፈጥሮላታል፡፡

ጋሻው በዚያን ዕለት ወደ ጅማ የሚጓዘው ከአዲስ አበባ በስራ ምክንያት ተቀይሮ የሄደ የልብ ጓደኛ ሀገሩን እንያይ ባቀረበለት ግብዣ መሰረት ነው፡፡ ስለሆነም ጅማ ላይ ተጨማሪ ጓደኛ ልትሆነው የምትችል ልጅ ሲያገኝ ስለሀገሩም ስለራሷም አንዳንድ ነገሮችን እየጠየቃት ተግባብተው ነው መንገዱን የጨረሱት፡፡ በጉዟቸው ላይ እመቤት ለጋሻው ሁሉንም ታሪኳን ነግራዋለች፡፡ ከውጪ መምጣቷንና ቤተሰብ ለመጠየቅ የምትሄድ መሆኑን ጭምር፡፡ ለረጅም ጊዜ የሚተዋወቁ ያህል ብዙ የተጨዋወቱትና ስለራሳቸው መረጃ የተለዋወጡት የጉዞ ጓደኞች አጋጣሚውን ወደውታል፡፡ እመቤት በተለይ ረጅሙን ጉዞ የሚያቀልላት አጫዋች በማግኘቷ ተደስታለች፡፡ እሱም በልጅቷ ውበትና ሳቂታነት ተማርኳል፡፡ ጅማ ሲገቡ ደግሞ መገናኘት የሚችሉበትን ዕድል አመቻችተው ነበር የተለያዩት ስልክ ተለዋውጠዋል፡፡ እመቤትን አውቶብስ ተራ ሲጠብቋት የነበሩት ዘመዶቿ ሲቀበሏት ጋሻውን ጓደኛው መጥቶ ወስዶታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የተገናኙት ሁለቱ ሰዎች ከዚያን ቀን ጀምሮ አንዳቸው ለሌላኛቸው አስፈላጊ ሰዎች መሆናቸው እስኪሰማቸው ድረስ ቅርርባቸው ጠንክሮ ነበር፡፡

ጅማ መንገዱ ላይ የተጀመረው ትውውቅና በዚያች ከተማ ያሳለፏት የጥቂት ቀናት የጓደኝነት ቆይታ የተጠናከረው አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ ነው፡፡ ጋሻው ለእመቤት በጣም ጥሩ ሰው ሆኖ ነው የቆየው፡፡ እመቤት በጋሻው ጥሩነት፣ አሳቢነትና መካሪነት እንዲሁም የልቧን ልታጫውተው የምትችል ሁነኛና ቁም ነገረኛ ሰው መሆን በጣም ነበር የተደሰተችው፡፡ በየዕለቱ እየተደዋወሉና በየዕለቱ እየተገናኙ ግንኙነታቸውን ከተራ ጓደኝነት ወደ ፍቅር አሳደጉት፡፡ እመቤት ጋሻውን ወዳዋለች፡፡ ለረጅም ጊዜ የምታውቀው ያህል አክብራዋለች፡፡ በተለይ ለርሷ አሳቢነቱና በማንኛውም ሁኔታ በህይወቷ ውስጥ ጠቃሚ ሰው መሆን እንደሚችል በሚሰጣት አክብሮትና ፍቅር ማረጋገጥ መቻሉ የዚህችን ወጣት ልብ በቀላሉ ለመግዛት አስችሎታል፡፡

አንዳቸው ስለሌላቸው የሚያውቁት አንዳች ነገር የሌለ እስኪመስል ድረስ የየግል መረጃዎቻቸውን ሁሉ ተለዋውጠዋል፡፡ እመቤት የምታውቀው ጋሻው ብዙ ጊዜ ትዳር ለመመስረት ሞክሮ ያልተሳካለት በሚያከብራቸውና ሁሉን ነገር በሰጣቸው ሴቶች የተከዳ ከአንዴም ሁለቴ ህልሙን በናዱበት ፍቅረኞቹ የተጎዳ መሆኑን ነው፡፡ እርሱ ጥሩ ሆኖ ሳለ ያጋጠሙት ሴቶች ታማኝና የትዳር ሰው ለመሆን ባለመቻላቸው ውስጡ እጅግ መጎዳቱን በዚህ የተነሳም ከዚህ ወዲያ ፍቅር የሚለውን ነገር ፈጽሞ እንደማይሞክረው ለራሱ ቃል ገብቶ የነበረ ሰው መሆኑን ነው የምታውቀው፡፡ በመሀል ከእርሷ ጋር ሲተዋወቅ ከዚህ ጥርጣሬ ጋር ሆኖ ስለነበር ደጋግሞ በእርግጥም ልቡን እንደማታደማውና ያለፉት ያስቀየሙትን እንደማትደግመው እየመላለሰ ጠይቋት ያረጋገጠ በመሆኑ በነገራት ታሪክ ላይ አንዳች ጥርጣሬ አላደረባትም፡፡ እሷም የምትፈልገው ታማኝና ቃሉን አክባሪ እንዲሁም ለጊዜያዊ ግንኙነት ሳይሆን ለዘላቂ ትዳር ራሱን ያዘጋጀ ሰው ስለሆነ በዚህ በኩል እንደ ተሳካለት አምናለች፡፡ አንዳቸው ለሌላቸው እግዚአብሔር የጣለላቸው ገፀ በረከት መሆናቸውን አምነዋል፡፡ በተለይ እመቤት የወደፊት የትዳር አጣማጇን ባግኘቷ ውስጧ በደስታ ሰክሯል፡፡ ጥሩ ጊዜ አሳለፉ- በፍቅር እንዲህ ልቧ በመጥፋት የመጀመሪያዋ የሆነው እመቤት ጋሻውን ወደደችው ብቻ ሳይሆን አመለከችው ማለት ይቀላል፡፡ የቅርብ ጓደኛዋ አምሳለ እንዳለችው የሁለቱ ፍቅር እመቤት ጋሻው ያላትን ሁሉ ከመፈፀምና እያንዳንዱን እንቅስቃሴዋን ከእርሱ ፍላጎትና ጥያቄ ጋር የማጣጣም ባህሪ ከማዳበር ባለፈ ለጋራ ኑሮ ጎጆ እስከመቀለስ እቅድ አድርሷቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ታዲ እመቤት ጋሻውን እንጂ አካባቢውን አታውቀውም፡፡

በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ በአክርቴክትነት እንደሚሰራ፣ ጦር ኃይሎች አካባቢ ከእናቱ ጋር እንደሚኖርና የሚያስተምራቸው ሁለት ታናናሾች እንዳሉት፣ አባቱ መሞታቸውን፣ እናቱ ዘወትር እንዲያገባ እንደሚጨቀጭቁት እሱ ደግሞ የቤተሰቡ ነገር እንደሚያስጨንቀው ነው የነገራት፡፡ አምሳለ በዚህ ሁለት ወር ጊዜ ውስጥ እመቤት ስለ ጋሻው ያወራችው ነገር ሁሉ እውንት ስለመሆኑ ከእርሷ ውጪ ለሌላ አካል መረጃ ስለሌላት ጓደኛዋ ያለቻትን አምና ከመቀበል ውጪ አማራጭ አልነበራትም፡፡ ጋሻው አንድም ሰው ለመተዋወቅ ስለማይፈልግና ‹‹ጓደኛ ፍቅር ያደፈርሳል እንጂ አይጠቅምም›› የሚል አቋም ስለነበረው እመቤት ጓደኛዋን ልታስተዋውቀው- አምሳለም በዚህ አጋጣሚ ጋሻውን ልታየው አልቻለችም፡፡ ስለዚህ ስለርሱ የምትሰማው እመቤት በምትነግራት ወሬ ነው፡፡

በዚህ ሁኔታ ላይ ሳሉ እመቤት ቲኬቷ የሚቃጠልበት ጊዜ ደረሰ፡፡ በ3 ወር ውስጥ ለመመለስ ይዛ የነበረውን እቅድ ለማክበር አልቻለችም፡፡ ጋሻውን ተለይታ መሄድ የማይሆን ሆነባት፡፡ ናፍቆቱን የምትችለውም አልመሰላትም፡፡ በዚህ ሳቢያ መወሰን አቅቷት መዋለል ጀመረች፡፡ በዚህ በኩል ጋሻው ተመልሳ እንዳትሄድ ይወተውታታል፡፡ በተለይ ደግሞ በፍቅር መካከል የሚፈጠር ክፍተት ለችግር እንደሚዳርግ በመንገር መለያየታቸው ክፉ ነገር ይዞ እንደሚመጣ ያስረዳታል፡፡ በሌላ በኩል ቤተሰቦቿ እዚህ መቀመጥ እንደሌለባት ይወተውቷታል፡፡ በተለይ አዲስ ባመጣችው ባህሪና ሁሌም ውጪ ውጪ በማለቷ ገንዘቧን እያባከነች መሆኑ የተሰማቸው እናቷ ቶሎ ወደመጣችበት እንድትመለስ ይጨቀጭቋት ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ያሸነፈው ሃሳብ የጋሻው ሆነ፡፡ እመቤት ወደ ውጪ ተመልሳ የመሄድ ሃሳቧን ሰረዘች፡፡ አሁን ሙሉ ምርጫዋና የወደፊት እቅዷ በጋሻው እጅ ገብቷል፡፡

አብሮነት

ሁለቱ ጥንዶች በተዋወቁ በ6ኛው ወር ነው አብረው የመኖር ሃሳብ ያመጡት፡፡ ጋሻው እመቤትን ቤት ተከራይተው መኖር እንደሚገባቸው ይወተውታት ያዘ፡፡ አራት ዓመት ሰርታ ያመጣችውን 78 ሺ ብር ህይወታቸውን ለመመስረት ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ይጨቀጭቃት ጀምሯል፡፡ እመቤት በዚህ ፍጥነት የጠየቃትን አብሮ የመኖር ጥያቄ ለመመለስ ተቸገረች፡፡ በተለይ የጓደኛዋ ተደጋጋ ማስጠንቀቂያ ከቤተሰቦቿ ጋር የፈጠረችው ግጭት ጥቂት ወደ ራሷ እንድታስብ ቢያደርጋትም ከጋሻው ግን የበለጠባት የለም፡፡ ጋሻው የባንክ ቡኳን እሱ ጋር አስቀምጦ ገንዘብ ማውጣት ስትፈልግ ብቻ እንድታወጣ ለማንም ቤተሰብን ጨምሮ ገንዘብ እንዳትሰጥ አድርጓታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመስሪያ ቤት ማህበር ያለው መሆኑንና ለዚያ ቅድሚያ ክፍያ 30 ሺ ብር እንደሚያስፈልግ ነግሯት አውጥታ ሰጥታዋለች፡፡ ከዚህ በኋላ ቢቸገሩ 2 ዓመት ብቻ መሆኑን ገልፆላጽ አሁን ግን ቤት ተከራይተው ቢኖሩና ጋብቻቸውን በሚመቻቸው ጊዜ ቢያደርጉት የተሻለ መሆኑን አሳምኗታል፡፡ እመቤት ይህን ሁሉ ስታደርግ ያማከረችው አንድም ሰው እንደሌለ ስታውቅም ሁሉንም እርግፍ አድርጋ ተወቻቸው፡፡ ሁለት ክፍል ያላት አነስተኛ ቤት ተክለሃይማኖት አካባቢ ተከራዩ፡፡ ለቤቷ የሚያስፈልገውን ዕቃ በሙሉ ከ15 ሺ ብር በላይ አውጥታ የገዛችው እሷ ናት፡፡ በአንድ ግቢ ውስጥ ያለው ቤት ከርሷ ጋር ሌሎች ሁለት ተከራዮችን የያዘ ነው፡፡ መንደር ውስጥ ለውስጥ የገባ ቢሆንም ቤቱን ግን ሁለቱም ወደውታል፡፡ ጋሻውና እመቤት አብረው መኖር የጀመሩት በዚህ ሁኔታ ነው፡፡ የእመቤት ቤተሰቦች የልጃቸውን ከጉዞ መቅረትና ወንድ ወድዳ ቤት ተከራይታ መውጣት ፈፅሞ ያልደገፉት ነገር በመሆኑ በተለይ አባቷ አይኗን ሊያዩት እንደማይፈቅዱ ተናግረዋል፡፡ እሷም በፍላጎቷ ማንም መግባት የሌለበት መሆኑን በመግለፅ ነው ከቤት የወጣችው፡፡ እናትየው ግን አላስችል ስላላቸው በተደጋጋሚ ጊዜ ደውለውላት አልፎ አልፎ አባቷ በሌሉ ጊዜ እየመጣች ታያቸዋለች፡፡ ጋሻው ቀን ቀን ወደ ስራ ብሎ ይሄድና ምሽት ላይ ይመታለ፡፡ አብሯት ያድራል፡፡ ህይወታቸውን መምራት ጀመሩ፡፡ ሁለት ወር ያህል ከኖሩ በኋላ ለምን እንደማይጋቡ ደጋግማ ትጠይቀው ነበር፡፡ በዚሁ ላይ አንድም ቀን ጓደኞቹንና እናቱን ሊያስተዋውቃት ያለማሰቡ ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ መጣር ጀመረች፡፡ ጋሻው እሷን ለሁሉም የሚያስተዋውቃት ድንገት ሁሉንም ሊያስደንቅ በሚችል ሁኔታ እንደሆነ እስከዚያው ግን አንድም ሰው እንዲያውቅበት የማይፈልገው ፍቅራቸው የሰው አፍ ውስጥ እንዳይገባ ፈልጎ መሆኑን በመንገር ይሸነግላት ነበር፡፡

በሌላ በኩል ያስቀመጠችው ገንዘብ በየጊዜው እየተመዘዘ ማለቁም እመቤትን አስጨንቋታል፡፡ ብዙ ገንዘብ ወጪ አድርጋ ቤቱን ማቋቋሟ ሳያንስ በሰበብ አስባቡ ገንዘብ እንድትሰጠው የሚጠይቃትን ጋሻውን ማስተናገድ በዝቶባታል፡፡ የወሰደው 30 ሺ ብር ሳያንስ የተለያዩ ምክንያቶች እየፈጠረ ገንዘብ ከባንክ እንድታወጣ ያደርጋት ነበር፡፡ የቤት አስቤዛ የምትገዛው እሷ ናት፡፡ እሱ ለጊዜው እናትና ታናናሾቹን እየረዳ በመሆኑ መስመር እስኪያሲዛቸው እንድትታገሰው ነግሯት ስለነበር ልትጫነው አልፈለገችም፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜም ቤቱን እንድትሞላው- ሁሌም ደግሳ እንድትጠብቀው- ሁሉም ቢራና ወይን ከቤት እንዳይጠፋ መፈለጉ የልጅቷን የገንዘብ አቅም አመናመነው፡፡ ሶስት ወር ሲያልፋት ቢያንስ ቀለበት ማሰር እንዳለባቸው ትወተውተው ጀመረ፡፡ ለዚህም ምላሻ አላጣም፡፡ ቀለበት ማድረግ ብቻውን ዋጋ የሌለው መሆኑንና በቅርቡ ጋብቻቸውን መፈፀማቸው ላቀር ሌላ ወጪ መፍጠር የሌለባቸው መሆኑን ይነግራታል፡፡ ሁሌም ለምትጠይቀው ጥያቄ አሳማኝ ምላሽ አያጣምና በተቻለ መጠን እሱን ለማስቀየም ለማትፈልገው እመቤት ነገሩን በትዕግስትና በተስፋ መጠበቅ ብቻ ነበር አማራጯ፡፡

6 ወራት 1998 ጥቅምት

እመቤት ጓደኛዋን ፈለገቻት፡፡ በጋሻው የተነሳ የራቀቻትን ጋሻው ፈጽሞ እንዳታገኛት ብሎ ያለያያትን ጓደኛዋን ፈለገቻት፡፡ አሁን ነገሮች በፈለገችው መንገድ እየተጓዙ አይደሉም፡፡ በባንክ አካውንቷ የቀራት ገንዘብ 20 ሺ ብር ብቻ ነው፡፡ በ6 ወር ውስጥ ከ50 ሺ ብር በላይ አውጥታለች፡፡ ይህን ገንዘብ ለማግኘት 4 ዓመት ፈጅቶባታል፡፡ ጋሻው ገንዘብ የሚበቃው ሰው አይደለም፡፡ ተቃውሞ ስታቀርብ ሁሌም ያኮርፋል፡፡ ከእኔ ገንዘብሽን ታስቀድሚያለሽ ይታላል፡፡ በዚህ ትሳቀቃለች፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የገንዘቡ ማለቅ አያሳስበውም፡፡ ህይወታቸው የሚመራው በርሷ ገንዘብ ሳይሆን በርሱ ደመወዝ እንደሆነ ደጋግሞ ቢነግራትም አንድም ቀን ሻሽ እንኳን ገዝቶላት አያውቅም፡፡ ውጪ ከርሷ ጋር ለመታየት ይፈራል፡፡ ጓደኞቹን፣ እናቱን አካባቢውን አያስተዋውቃትም፡፡ አብረው የሚወጡት ምሽት ላይ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ቀን ቀን ስራ እያለ ከእሁድ እስከ እሁድ ቤት አይገኝም፡፡ ምሽት ላይ ነው አብሯት የሚሆነው፡፡ እሷ ጋር ሲመጣ ሞባይሉን ያጠፋዋል፡፡ በየ15 ቀኑ ፊልድ እያለ ለአንድ ሳምንት ቆይቶ ይመለሳል፡፡ በእነዚያ ጊዜያት ሁሉ ስልኩ ይዘጋል፡፡ ከኔትዎርክ ውጪ ስለሆንኩ ነው ይላታል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ፀባዩ እየተለወጠ መጥቷል፡፡ እንዳትጸንስ ሁሌም ቢሆን ያስጠነቅቃታል፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ልቧ ውስጥ ከፊል ጥርጣሬ እያሳደረባት ሲመጣ ጓደኛዋን ፈልጋ አግኝታ አዋየቻት፡፡

አሁን ከእንቅልፏ መባነን ጀመረች፡፡ ጓደኛዋ ሊሆን ይችላል ያለችውን ነገር ሁሉ ነገረቻት፡፡ ይህ ሰው ምናልባት እያጭበረበራት እንደሆነ ለማወቅ ማድረግ ያለባትን ሁሉ አስረዳቻት፡፡ በተለይ እሰራበታለሁ የሚልበትን መስሪያ ቤት በመጠየቅ እንድትተባበራት አማከረቻት፡፡ በዚህ መልኩ እመቤት በጋሻው ላይ ጥናት ማድረግ ጀመረች፡፡ አድርጋ የማታውቀውን ነገር ማድረግ ጀመረች፡፡ ጋሻው ለሽንት ከቤት ሲወጣ ቦርሳውን መበርበር ጀመረች፡፡ የመስሪያ ቤት መታወቂያ የለም፡፡ ነገር ግን የአንዲት ሴት ፎቶ ግራፍ አለ፡፡ በግምት 2 ዓመት የሚሆነው ወንድ ልጅ ያቀፈች ወጣት ነች፡፡ እመቤት ደነገጠች፡፡ ነገር ግን ምናልባት ዘመዱ ልትሆን ትችላለች ብላም አሰበች፡፡ የቀበሌ መታወቂያውን አየችው፡፡ ነዋሪነቱ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 18 ውስጥ መሆኑን ይናገራል፡፡ ከቤተሰቦቼ ጋር ጦር ኃይሎች እኖራለሁ ያለው ሀሰት መሆኑን ጠርጥራለች፡፡ ይህን አድራሻ በወረቀት ላይ መዘገበችና ያዘች፡፡ በማግስቱ ለጓደኛዋ ነገረቻት፡፡ ቀስ በቀስ ጋሻው እውነተኛ ሰው እንዳልሆነ ለመረዳት የቻለችበትን መረጃዎች አገነች፡፡ ስልኩን ሳያይ አውጥታ በውስጡ የተቀዱትን የቪዲዮ ምስሎች ተመለከተች፡፡ በፎቶ ግራፍ ላያ ያየቻትን ሴት አይነት ሴት አለች፡፡ አንድ ህፃን ልጅ በተደጋጋሚ ጊዜ ተቀርጿል፡፡ ደነገጠች፡፡

ጓደኛዋ ይህን ካወቀች በኋላ እመቤት ጋሻውን ማውጣጣት እንዳለባት አሰበችና ተመካከሩ፡፡ አንደ ቀን ጋሻውን ‹‹ለምን ከሰዎች ጋር እንደማታስተዋውቀኝ ገብቶኛል፡፡ ልጅና ትዳር እንዳለህ ደርሼበታለሁ፡፡ ስለዚህ ገንዘቤን መልስልኝ›› እንድትለው ነገረቻት፡፡

ህዳር 17/1998

ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ላይ በር ተንኳኳ፡፡ ቀኑን ሙሉ ቤት ተቀምጣ በሃሳብ ስትብሰከሰክ ለዋለችው ለእመቤት ይህ ምሽት የመጨረሻ ነው፡፡ ውስጧ ተበሳጭቷል፡፡ የተለየ ስሜት ተሰምቷታል፡፡ የመከዳት ስሜት ተሰምቷታል፡፡ በሀሰት የሚሸነግላት፣ የሚያታልላት ልቧን በሰረቀበት የማባበያና የማሳመኛ ቃሉ ሌላ እንዳታስብ አድርጎ አዕምሮዋን የጋረደባት እጅግ ስለምትወደውና ሌላ ለማሰብ ራሷን ስላላዘጋጀች ነበር፡፡ አሁን ግን ቆም ብላ ስታስብ የሆነው ሁሉ ተረት ተረት መስሎ ታያት፡፡ ስለዚህ ዛሬ እውነቱን የምታውቅበት ዕለት ነው፡፡ ጋሻው ወደ ቤት ገባ፡፡ እንደተለመደው እቅፍ አድርጎ ሳማት፡፡ መጠት መጠጥ ሸቷታል፡፡ ለምን እንደመጣ ጠየቀችው፡፡ የሆኑ ከውጭ የመጡ የመስሪያ ቤት እንግዶችን ሲያስተናግድ ቢራ መጠጣቱን ነገራትት፡ ከዚህ በኋላ ነበር ጦርነቱ የተጀመረው፡፡

ስራ የሌለው መሆኑንና እስካሁንም የተጫወተባት እንደሚበቃ ነገር ግን የወሰደባትን ገንዘብ ሁሉ እንዲመልስላት ካልሆነ ግን ለሚስቱ እንደምትደውልላት አስጠነቀቀችው፡፡ ቱግ አለ፡፡ ይህ ወሬ ያወራላት ሀሰተኛ እነርሱን ለመለያየት የፈለገ ሰው መሆኑን ነገራት፡፡ ነገር ግን እራሷ ማወቋንና ከሞባይሉ ውስጥ ያየችውን ቪዲዮ እንዲሁም ቦርሳው ውስጥ ያየችውን ፎቶግራፍ ሁሉ ነገረችው፡፡ ቦርሳውን ከፍቶ እንዲያሳያትና ሞባይሉንም አውጥቶ ቪዲዮውን የማን እንደሆነ እንዲገልፅላት ጠየቀችው፡፡ ተቆጣ፡፡ የእርሱን ሞባይልና ቦርሳ ለመጎርጎር ፈፅሞ መብት የሌላት መሆኑንና ቢያደርገውም የሚያገባት ነገር የሌለ መሆኑን ገለፀላት፡፡ ፀብ ተቀሰቀሰ፡፡ እመቤት ህይወቷን ማበላሸቱንና ከዚህ በኋላ ምንም አይነት ግንኙነት እንዲኖራት የማትፈልግ መሆኑን ነግራ ሌላ ግንኙነት እንዳለው ያንንም የሰራትን ሄዳ በመንገር እንደምትበጠብጥበት ስትነግረው አነቃት፡፡ መታገል ጀመሩ፡፡
እመቤት ራሷን መቆጣጠር ተስኗት መጮኽ ጀመረች፡፡ ልትቧጭረው ፈለገች፡፡ እሱም ይደብድባት ነበር፡፡ በመጨረሻ ላይ ባላሰበችው ሁኔታ አጠገቧ ያገኘችውን የኒኬል ብርጭቆ ወርውራ ስትመታው እጇን ጠምዝዞ ጣላት፡፡ አጠገቡ ያገኘውን የሽንኩርት መክተፊያ ቢላዋ ሲይዝ ልትቀማው ታገለችው፡፡ በጩኸት ሰው መጣራት ጀመረች፡፡ አፏን አፍኖ ወደ ታች የሰነዘረው ቢላዋ ዘወር ስትል ትከሻዋ ላይ ተሰካ፡፡ ጮኸችና ወደቀች፡፤ ግርግሩን የሰሙ ሰዎች ተሯሩጠው ወደበሩ ሲደርሱና እሱ ከፍቶ ሲወጣ አንድ ሆነ፡፡ ድንገት መሬት ላይ ወድቃ በደም ተበክላ ያዩዋት የቤቱ አከራይ ‹‹ገድሏታል›› ብለው ሲጮኹ ጋሻው ከአካባቢው ተፈትልኮ ጠፋ፡፡ ሰዎች በዚህ ምሽት ተሯሩጠው ቢፈልጉትም ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ እመቤትን ከወደቀችበት አንስተው በኮንትራት ታክሲ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወሰዷት፡፡ ሐኪሞች በድንገተኛ ክፍል ከእጇ ላይ የሚፈሰው ደም ከቆመላት በኋላ አልጋ አስያዟት፡፡ ህይወቷ ተርፏል፡፡

ከሳምንት በኋላ
ፖሊስ በደረሰው መረጃ መሰረት ባደረገው ማጣራት ጋሻው የሚኖርበትን አድራሻ ከእመቤት ጓደኛ አግኝቷል፡፡ በስልኩ ሲደወል ስልኩ የተዘጋ መሆኑን ቢገልፅም ፖሊስ ግን የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ይዞ ያለበት በአድራሻ ድረስ ሄዶ ቤቱን አገኘው፡፡ የሚኖርበት ቤት ውስጥ አያቱ አሉ፡፡ ሰሞኑን መጥቶ እንደማያውቅ የሄደበትን እንደማያውቁ ተናገሩ፡፡ ጋሻው ስራ የለውም፡፡ አልፎ አልፎ ደላልነት ይሞክራል፡፡ ከአንዲት ሴት ወልዶ እሷ አሁን አረብ አገር እየሰራች ነው፡፡ ተጋብተው ይኖሩ የነበረ ሲሆን እሷ ወደ ውጭ ስትሄድ ነው ወደ አያቱ ቤት የተመለሰው፡፡ ልጁን እያሳደገ ነው፡፡ ልጅቷ ከዓመት በኋላ ተመልሳ ትመጣለች፡፡ ህጋዊ የጋብቻ ወረቀትም ነበረው፡፡

ከ15 ቀናት ክትትል በኋላ ፖሊስ በጥቆማ ምሽት ላይ ወደ ቤቱ ሲመጣ ጋሻውን በቁጥጥር ስር አዋለው፡፡ በወቅቱም የእመቤትን የባንክ ደብተር ካስቀመጠበት እንዲያመጣ አደረገው፡፡ በመግደል ሙከራ ወንጀል ክስ የቀረበበት ጋሻው ከዚህ በተጨማሪም በማታለልና በማጭበርበር የሰው ገንዘብን ለራስ ጥቅም በማዋል ተከሷል፡፡ በህይወት የተረፈችው እመቤት ጋሻው እስር ቤት ከገባ በኋላ የሆነውን ነገር ሁሉ አረብ አገር ላለችው ሚስቱ ስልኳን ፈላልጋ ደውላ ነግራታለች፡፡ ልጅቷ ባለችበት ሆና ጋሻው የሚባል ባል እንደሌላትና አገሯም እንደማትመጣ ልጇን ግን እንደምትረዳ ለቤተሰቦቿ ነግራቸዋለች፡፡ ቤተሰቦቿም የተፈፀመውን ታሪክ አውቀዋል፡፡ ጋሻው በፈፀመው ወንጀል እስር ቤት ቢገባም እመቤት ከአካል ጉዳት ባሻገር የማይጠገን የህሊናና የሞራል ጉዳት ደርሶባታል፡፡ ከቤተሰቦቿ ጋር አብራ መኖር ብትጀምርም የጥፋተኝነት ስሜቱ ጠንቶበት ነበርና ከጓደኛዋ ጋር መኖር መርጣለች፡፡ በፍርድ ቤት የጋሻው ጉዳይ በመታየት ላይ ሳለ ነበር ወደ ውጭ ሃገር የተመለሰችው፡፡ የቀራትን 20 ሺ ለዚሁ ፕሮሰስ አውላ ሌሎች ብዙ ዓመታትን ጉልበቷን እየገበረች ብር ለማጠራቀም ይህችን ሀገር ጥላ ሄደች፡፡ አምሳለ እመቤት ተመልሳ ወደዚህች አገር ትመለሳለች የሚል ተስፋ የላትም፡፡ ምናልባትም ዛሬም ድረስ ይህችን አገር አላየቻት ይሆናል፡፡ አጭበርባሪው ግለሰብ ግን በወህኒ ቤት ለሰራቸው ተደራራቢ ወንጀሎች ፍርዱን እየተቀበለ ነው፡፡ ምናልባት ሚስቱ ስትመጣ በጋብቻ ላይ በመማገጥ ወንጀል ክስ ልትመሰርትበት ወይም ህሊናው ይቅጣው ብላ ልትተወው ትችል ይሆናል፡፡ ያ ታሪክ ዛሬ ቀላል ቢመስልም በተጎጂዎቹ ሴቶች ላይ የጣለው ጠባሳ ግን ምናልባትም የህይወት ዘመናቸውን ሙሉ ይከተላቸው ይሆናል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles