- በደሴቶች ኦሎምፒክ ለመሳተፍ ይፈልጋሉ
የምናወቀው እግርኳስ በእጅጉ እየተለወጠ ነው፡፡ በዓለም እግርኳስ የቲኬት ዋጋ በእጅጉ እየናረ ነው፡፡ ቢሊየነር የክለብ ባለቤቶች ተጨዋቾችን ለማዘዋወር እና ለደመወዝ አስደንጋጭ የሆነ ከፍተኛ ገንዘብ እያወጡ ነው፡፡ ሆኖም በደቡብ አትላንቲክ ውቅያኖስ በሚገኙ ደሴቶች እግርኳስ የሚጠበቅበትን ስራ እየተወጣ ነው፡፡ ማህበረሰቦችን ወደ አንድነት ማምጣት፡፡
ሴንት ሄሌና በጣም የምትታወቀው ለፈረንሳይ የቀድሞ መሪ ናፖሊዮን ባናባርቴ የስደተኝነት መዳረሻ በመሆን ነው፡፡ ፈረንሳዊው 1821 ህይወቱ ያለው በዚህች ደሴት ነው፡፡ ደሴቷ ጠባብ ነች፡፡ የሴንት ሄሌና ህዝብ ቁጥር ከ4000 አይበልጥም፡፡ ይህ ቁጥር ይበልጥ መቀነሱ ደግሞ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ወጣቶቹ የደሴቷ ነዋሪዎች ለትምህርት እና ለስራ ወደ ብሪታኒያ እያመሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ብዙም አያስደንቅም፡፡ ምክንያቱም የሀገሪቱ ሠራተኞች ዓመታዊ አማካይ ደመወዝ 5500 ፓውንድ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም በርካታ ችግሮች ቢኖሩበትም ሴንት ሄሌና የእግርኳስ ሊግ አላት፡፡ የእግርኳስ ማህበርም እንዲሁ፡፡
የሴንት ሄሌን የእግርኳስ ሊግ በሜይ ወር ይጀመራል፡፡ የክሪኬት የውድድር ዘመን የሚጀመረው የሊግ ማብቂያ ላይ ነው፡፡ ሴንት ሄሌና የምትመራው በብሪታኒያ ነው፡፡ ሊጉ እጅግ ከባድ ፉክክር ይደረግበታል፡፡ ተመልካቾችም ሊጉን በትኩረት ይከታተላሉ፡፡ የ2014 ሊግ 12 ክለቦች ይሳተፉበታል፡፡ እስካሁን ድረስም ከፍተኛ ፉክክር እየተደረገበት ነው፡፡ ሪቨርስ እና ሀርትስ የተባሉ ክለቦች ለሻምፒዮንነቱ እየተፎካከሩ ነው፡፡ ያለፈውን የውድድር ዘመን ሻምፒዮኖቹ የሴንት ሄሌና ዋየርበርድስ ጥሩ ጊዜን እያሳለፉ ባይሆንም በሊጉ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ኮከብ ተጨዋቻቸው ጀንሰን ጆርጅ ደግሞ የከፍተኛ ጎል አግቢነቱን ደረጃ እየመራ ነው፡፡ እስካሁን 17 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡
ሴንት ሄሌና በኢንተርናሽናል እግርኳስ የመሳተፍ ህልም አላት፡፡ የደሴቷ እግርኳስ ማህበር ለ2011ዱ የደሴቶች ውድድር አንድ ቡድን ለመላክ አስባ ነበር፡፡ ውድድሩ የኦሎምፒክ መርህን የተከተለ ሲሆን በመላው ዓለም የሚገኙ ደሴቶች የሚሳተፉበት ነው፡፡ የ2011ዱ የደሴቶች ጨዋታዎች የተከናወነው በአይሰል ኦፋዌይት ነበር፡፡ እግርኳስ ማህበሩ 17 አባላት የያዘ ስኳድ ለመላክ እቅድ ነበረው፡፡ አምስቱ ከደሴቷ የሚመረጡ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ የሴንት ሄሌና ዝርያ ያላቸውን ተጨዋቾች ለማድረግ ታስቦ ነበር፡፡ ሆኖም ይህን እቅድ ማሳካት አልተቻለም፡፡ ህልሙ እውን መሆን ያልቻለው በፋይናንስ ችግሮች ምክንያት ነበር፡፡
የሴንት ሄሌና እግርኳስ ማህበር በቅር ከዓለም አቀፉ የእግርኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ ጋር ግንኙነት ፈጥሯል፡፡ ሌላኛው በብሪታኒያ የተያዘው ጄብሪልተር የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር የፊፋ አባል የማይሆንበት ምክንያት እንደሌለ ያሳያል፡፡
ሆኖም የትሪስተን ዳ ኩንሃ ደሴት ጉዳይ ከበድ ይላል፡፡ በእሳት ጎመራ በፍንዳታዎች የምትታወቀው ደሴት ከሴንት ሄሌና 1600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ በትሪስተን ዳ ኩንሃ የሚገኙት ነዋሪዎች ቁጥር 300 ብቻ ነው፡፡ በአሳሹ ትሪስተኑ ዳ ኩንሃ ስም ለተሰየመችው ደሴት ነዋሪዎች እግርኳስ ዋነኛ የህይወታቸው አካል ነው፡፡ ስለ እግርኳስ አውርተው ከማይጠግቡት የደሴቷ ነዋሪዎች አንዱ ሊዮን ግላስ ነው፡፡ የደሴቷን የመጀመሪያ እና ብቸኛ የእግርኳስ ክለብ የመሰረተው ሊዮን ነው፡፡ ትሪስተን ዳ ኩንሃ ኤፍሲ ይሰኛል፡፡
‹‹የቴሌቪዥን ስርጭት በስፖርት ያለውን ፍላጎት በጨመረበት ወቅት የትሪስትን እግርኳስ ቡድን በ2002 ተቋቋመ›› ይላል ግላስ፡፡ ‹‹ለጉብኝት የሚመጡ ተጋጣሚዎችን ስናገኝ ከተቃራኒው ቡድን ጋር እንጫወታለን፡፡ በቅርብ ዓመታት ግን የመጡ ቡድኖች የሉም፡፡ ተጋጣሚዎች ስለሌለ ተጨማሪ ቡድኖችን ማቋቋም የሚችል አይመስለኝም፡፡ በዚያ ላይ ያለውን ቡድን ለመቀላቀል የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥም ቀንሷል፡፡ ትረስትን ዳ ኩንሃ ኤፍሲ በዓለም እጅግ ሩቅ ቦታ የሚገኘው ክለብ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምንም እንኳን ከዚህ በፊት ግጥሚያዎችን አድርገው ቢያውቁም (ከመርከብ ሰራተኞች ጋር ተጫውተው ያውቃሉ) ክለብ የሚገኝበት ቦታ ርቀት ጎድቷቸዋል፡፡ እንደ ሴንት ሄሌና ሁሉ ሊዮን ግለስም አንድ ቡድንን ወደ ደሴቶች ኦሎምፒክ ለመላክ ፈልጎ ነበር፡፡
‹‹እንደ ቡድን ወደ ደሴቶች ኦሎምፒክ ለመላክ ተወያይተንበት ነበረ፡፡ ነገር ግን ለጉዞው የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን አቅም አልነበረንም፡፡ ገንዘብ እና ዕድል ካገኘን ከፍለን ወደ ውጭ ሀገራት መውሰድ እንፈልጋለን›› እያለ ሊዮን ያሉትን ችግሮች ያስረዳል፡፡ ዕድል ግን አልቀናቸውም፡፡ ተጋጣሚ ማጣታቸው ቡድኑን ወደ መፍረስ ደረጃ ሊያደርሰው ተቃርቧል፡፡ አሁን ባለ አምስት ተጫዋቾች ቡድን ሆኗል፡፡ ‹‹የዓለም ጫፍ ላይ የሚገኘው ቡድን›› የሚል ትልቅ ስም ያለው ቡድን ቢሆንም እየተቸገረ ነው፡፡ ተጋጣሚ አልባ ቡድን፡፡
ሆኖም በሌላ 1600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ደሴት ሁኔታው የተለየ አይደለም፡፡ አሴንስን ደሴት 800 ነዋሪዎች ብቻ አሏት፡፡ አብዛኞቹ ነዋሪዎች ደግሞ የአሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ሴንት ሄሌና ዝርያ አለባቸው፡፡ ደሴቷ እንደ ትሪስተን ዳ ኪንሃ እና ሴንት ሄሌና የምትተዳደረው በብሪታኒያ ነው፡፡ በደሴቷ እግር ኳስ እጅግ ተወዳጁ ስፖርት ነው፡፡ አሴንስን የራሷ የእግርኳስ ሊግም አላት፡፡ ሆኖም በደሴቷ እግርኳስ ያለ ችግር አልቆመም፡፡ በደሴቷ ያለው ብቸኛው የእግርኳስ ሜዳ የተሰራው ከባህር ዳርቻ ጎን ነው፡፡ በጨዋታ ቀናት ኤሊዎችን ሜዳ ላይ መመልከትም የተለመደ ነው፡፡ ሜዳው ሣር የሚባል ነገር የለውም፡፡ ነገር ግን እንደ ሴቷ ጋዜጠኛ ካትሪን ሊዮን ከሆነ አዲስ ስታዲየም የመስራት እቅድ አለ፡፡
‹‹አዲስ ስታዲየም መገንባቱ አይቀርም፡፡ አሮጌው ደግሞ ለተወሰኑ ዓመታት ለመጫወት ያስችላል፡፡ ሎንግቢች የእግርኳስ ሜዳ ረጅም ታሪክ ስላለው ሰዎች ለመልቀቅ አልፈለጉም፡፡ አዲስ ስታዲየም ሲገነባ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ይችላል፡፡ ሌሎች ስፖርቶችንም ያስተናግዳል፡፡ በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ ስለሚሰራም ተማሪዎች በቀላሉ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ ገና በደሴቷ አብዛኛዎቹ ቋሚ ነዋሪዎች አይደሉም፡፡ የሚኖሩትም የሥራ ፈቃድ አውጥተው ነው፡፡ በመሆኑም በደሴቶች ኦሎምፒክ የሚሳተፍ ቡድን ማዘጋጀት ይከብዳል፡፡ ሊጉ ግን ተጠናክሮ ቀጥሏል››
የአሴንስን እግር ኳስ ሊግ ስድስት ቡድኖች ይሳተፉበታል፡፡ ኢንሲትዊነርስ፣ ቱ ቦትስ ዩናይትድ እና ያለፈው የውድድር ዘመን ሻምፒዮኖቹ ቪሲ ሚላን ከተፎካካሪዎቹ መካከል ናቸው፡፡ እግርኳስ እጅግ ተወዳጁ ስለሆነ የደሴቱ ጋዜጣ The inslander የጨዋታ ዘገባዎችንም ትንታኔዎች ይዞ ይወጣል፡፡ ሴንት ሄሌና ሴንቲነል የተሰኘው ጋዜጣ ደግሞ የአሴንሴን ሊግ የአንድ ገፅ ሽፋን ይሰጣል፡፡ የደሴቷ ነዋሪዎች በቁጥር ትንሹ ቢሆንም በየሳምንቱ ቅዳሜ ወደ ሎንግቢች ሜዳ ለጨዋታ ይሄዳሉ፡፡ ሜዳው በኤሊዎች ተሞልቶ ወይም የባህር ውሃ ርሶ ቢያገኙትም ከመጫወት እና ከመመልከት ወደኋላ አይልም፡፡
አሴንስን ደሴትን ለቅቀው ወደ ደቡብ አቅጣጫ ሲጓዙ የፎክላንድ ደሴቶች ያገኛሉ፡፡ ደሴቶቹ በእንግሊዝ እና አርጀንቲና መካከል አስከፊ ጦርነት የተካሄደባቸው ናቸው፡፡ የፎክላንድ ደሴቶች በደቡብ አትላንቲክ ውቅያኖስ ከሚገኙት ሌሎች ደሴቶች የሚለያቸው የራሳቸው ሊግ የላቸውም፡፡ ባለፉት 10 ዓመታት የደሴቶቹ እግርኳስን የሚያስተዳድረው የፎክላንድ ደሴቶች እግር ኳስ እየተዳከ ነው፡፡ በደሴቶቹ እግርኳስን የሚያስተዳድረው የፎክላንድ ደሴቶች እግርኳስ ሊግ በ2011 ሊጉን አፍርቶበታል፡፡ ለመወዳደር የቀሩት አራት ቡድኖች ብቻ ስለነበሩ ነው፡፡ በፎክላንድ ከሪኬት የበለጠ ተወዳጁ ስለሆነ የእግር ኳስ ፍላጎት መዳከም አንደኛው ምክንያት ነው፡፡ ሆኖም ሊግ ባይኖራቸውም ፎክላንድ በደሴቶች ኦሎምፒክ መሳተፋቸውን ቀጥለዋል፡፡ የፊፋ አባል የሆነውን ቤርሙዳ እና ከአውሮፓ እግርኳስ ማህበር አባል ጂብራለታር፣ እንዲሁም አይሰል ኦፍ ማን፣ ጉኤርንሴይ እና ግሪንላንድ ጋርም ተጫውተዋል፡፡ በውድድሩ ያላቸው ሪከርድ አስደሳች አስደሳች ባይሆንም በ2013 በብሪታኒያ በምትተዳደረው ቤርሙዳ በተዘጋጀው የደሴቶች ኦሎምፒክ ላይ ሶስተኛ በመውጣት የነሃስ ሜዳሊያ ተፋልመዋል፡፡ ነገር ግን በፊፋ ደረጃ መጫወት ለፎክላንድ ደሴቶች የማይችል ይመስላል፡፡ የፎክላንድ ደሴቶች እግርኳስ ሊግ ሊቀመንበር ማይክል ቤትስም የሚጋሩት ይህንን ነው፡፡ ‹‹እንደ አጋጣሚ ሆኖ በደቡብ አሜሪካ ባለው ፖለቲካ ምክንያት ፊፋን መቀላቀል አማራጭ አይደለም››
የፎክላንድ ህልም ግን እስከ አሁን መና አልቀረም፡፡ ሊጉ በአዲስ መስክ ተጀምሮ የተደራጀ እግርኳስ በደሴቶቹ እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡ የሊጉ አስተዳደር አርቴፊሻል ሜዳ ለማሰራት ከፎክላንድ መንግሥት ፈቃድ እየተጠባበቀ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ያሉት ሜዳዎች ለጨዋታ ምቹ አይደሉም፡፡ አስቸጋሪ ንፋስ እና እጅግ ቀዝቃዛው የፈረንጆቹ በጋ የሣር ሜዳዎችን ለረጅም ጊዜ እንዳይቆዩ እያደረጋቸው ነው፡፡
በኤሊዎች ጥላ ከሚጫወት ሊግ፣ በቅርብ ካለ ተጋጣሚያቸው 1600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ክለብ እና ለሶስት ዓመታት ይፋዊ የውድድር ግጥሚያን እስካላደረገ ክለብ የሚገኙት በእነዚህ የደቡብ አትላንቲክ ደሴቶች ነው፡፡