Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ፕሮፌሰር መስፍንን ለቀቅ

$
0
0

ፕሮፌሰር መስፍንን ለቀቅ

አንተነህ መርዕድ

ህዳር 2014

በዙህ ጉዳይ ላይ ለመጻፍ በሁለት ምክንያቶች ከራሴ ጋር ብዙ ታግያለሁ። መጀመርያ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አይደለም ለራሳቸው፤ ለሌላም የሚተርፍ አንደበት አላቸውና ራሳቸው መልስ  ይስጡ በማለት ሲሆን ሁለተኛው ምክንያቴ ደግሞ ትልልቅ አገራዊ ጉዳይ እያለ በዚህ ጠባብ ነገር መጠመድ ለማን ይበጃል በሚል ነበር።በሁለቱም ትክክል አልነበርሁም። ፕሮፌሰር መስፍን በግል ደረጃ የወረደ እንቶ ፈንቶ መግባት ስብዕናቸው ስላልፈቀደ ንቀው መተዋቸው ትክክል ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ግለሰቦች ሆነ ቡድኖች ትልልቅ የአገር አድባሮችን ሲያዋርዱ በዝምታ መመልከቱም ተገቢ አለመሆኑን ተገንዝቤአለሁ።

Prof. Mesfin

አንድ ህብረተሰብ ከመካከሉ የሚወጡ ፋና ወጊ መሪዎችን በመንከባከብ፤ ሲሳሳቱ በማረም  ቢያሳደግ ለበለጠ ሰላምና ብልጽግና ያበቃዋል። ይህንን እውነት በበርካታ አገሮች አይተናል።በህይወት ሳሉ ተሞግሰውና ተከብረው፤ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን የበለጠ ለአገራቸው ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ሲበረታቱ፣ ከሞቱም በኋላ ሃውልትና መታሰብያ ተሰርቶላቸው ትውልዱ አርዐያቸውን እንዲከተል ይደረጋል። እንዳለመታደል ባለፉት አርባ አመታት በአገራችን በአምባገነን መሪዎችና አንዳንድ ወገኖች የተያዘው አደገኛ መንገድ የአገሪቱን ትልልቅ ሰዎች ማዋረድ፣ መሪና ምሳሌ የሚሆነን ማሳጣት ነው። በተለይም በአብዮቱ ዘመን የምስራቁን ርዕዮት በአገራችን ለመትከል ታጥቀው የተነሱ ወገኖች ትልልቅ ኢትዮጵያውያንን ኢላማ አድርገው እንደነበር የምንዘነጋው አይደለም። ብዙ ለአገራቸው አስተዋፅዖ ያደረጉ አዛውንትና ትልልቅ ዜጎች ራሳቸውን ትልቅ አድርገው በሚመለከቱና ትንንሽ ጭንቅላት ባላቸው ከንቱዎች ተሰድበዋል፣ ተዋርደዋልም። እነዚህ ብርቅ ኢትዮጵያውያን  ከትውልድ ትውልድ ሊተላለፍ የሚችል ስራቸው በሁሉም ልቦና ያለ ሲሆን ሰዳቢዎቻቸውና አዋራጆቻቸው ግን ያሰቡት ሳይሳካ መክነው ቀርተዋል።

ዛሬ በህይወት የሚገኙትና በአዛውንት እድሜአቸው ደከመኝ ሳይሉ በተባ አንደበታቸው ጥልቅ የሆነ እውቀታቸውንና ተመክሮአቸውን ለወገን እያበረከቱ ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም  ብዙዎች የምንሳሳላቸውና የምናከብራቸው ቢሆንም ሁሉም ይወዳቸዋል ብለን አንጠብቅም። ሶስቱንም የአገራችንን   የአምባገነን ስርዓቶች አጥብቀው የታገሉ፣ ድፍረትና እውቀታቸው የመጠቀ፣ ለሃብት፣ ለስልጣን ሆነ ለግል ድሎት ቦታ የማይሰጡ፣ ትክክል ነው ብለው ያመኑትን ከመናገርና ከማስተማር ግንባራቸውን የማያጥፉ መሆናቸው ለብዙው ኢትዮጵያዊ እንደ አርአያ (ሮል ሞዴል) ሆነው እንዲታዩ ያደረጋቸውን ያህል በአንዳንዶች የአገርና የህዝብ ጠላት ሆነው እንዲታዩ ጥረት ይደረጋል። ይህ ትችቴ የፕሮፌሰር መስፍንን አንዳንድ ሃሳቦች በሃሳብነት የሚሞግቱትን ጨዋ ሰዎች አይመለከታቸውም። መስፍን ወልደማርያምን ፍጹም ናቸው የሚል ሃሳብ አይወጣኝም፣ እሳቸውም ይህንን እንደማይቀበሉ አምናለሁ። ትችቴ ፈረንጆች “ህፃኑን ከእጣቢው ጋር መወርወር” እንደሚሉት ሁሉ የፕሮፌሰሩን የተወሰነ ሃሳብ በስህተትነት ይዘው ጨዋነት በጎደለው ሰብዕናቸውን ለማጥፋት የዘመቱ ወገኖች ዓላማቸው አደገኛና አጥፊ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው።

የፕሮፌሰሩን አንዳንድ ሃሳብ የማይቀበሉ የተወሰኑ ግለሰቦች ጽሁፎቻቸውንና ንግግሮቻቸውን እየነቀሱ ጨዋነትና እውቀት ላይ የተመሰረተ ትችቶችን ማድረጋቸው ለብዙዎቻችን እውቀት መዳበርና የሃሳብ ጥራት ገንቢ ሚና ተጫውተዋል። ፕሮፌሰር  መስፍን ወልደማርያምም የምርምርና የእውቀት  ሰው በመሆናቸው ይህንን ዓይነት ትችት እንዲዳብር የሚስማሙበት ይመስለኛል። የብዙዎችን ላቆየውና በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ካንድ ወገን የሚሰነዘረው ከባህላችን ውጭ የሆነ ዓላማው ግልጽ ያልሆነ ስድ በሚያሰኝ የመንገድ አዳሪ ቋንቋ የስድብ ውርጅብኝ  በኒህ አዛውንት አባት ላይ ሲወርድባቸው ዝም ብሎ መመልከቱ ለህሊና ይከብዳል።

ነሃሴ 25 ቀን 2006 ዓ ም  “ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት”  በራሱና በሌሎችም ማህበራዊ ድረገፆች “ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በዐማራው ቁስል ላይ ጨው ነሰነሱ! የ<<ዐማራ የለም>> አቋም የክህደት ወይስ የመሳት?” በሚል ርዕስ የበተነው መግለጫ ተልዕኮው ምን እንደሆነ ያልለየና አሳዛኝ ነበር። በዚህ አምስት ገጽ በሞላ አማራው ላይ ስለደረሰ ግፍ በሚዘረዝር እውነትን ባዘለ ይዘቱ ላይ ተቃውሞ የለኝም። በመሬት ላይ ያለው ተጨባጭ እውነት ከዚያም የከፋ በመሆኑ ማንም ሊያደበዝዘው አይቻለውም። ነገር ግን በፕሮፌሰሩ ላይ የተሰነዘረው ቃል ተገቢ አልነበረም።

መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ትልልቅ ሃሳቦችንና ሰዎችን አኮስምኖና ገድሎ የራሱን ትልቅነት ለመገንባት ሲጥር ለመጀመርያ ጊዜ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን ነው በቴሌቪዥን ሊሞግት የሞከረው። ሁሉም እንደተከታተለው በክርክሩ ወቅት የመለስ ትንሽነት ነበር ጎልቶ የወጣው። በዚያ ውይይት ኢትዮጵያውያንን በጎሳ ከፋፍሎ ሊበትን ያሰበውን ዓላማ በመስፍን ወልደማርያም አፍ ላይ ሊያስቀምጥ ሲል “አማራ የሚባል ጎሳ የለም” ብለው በስሙ እንዳይነገድበት ያቀረቡት መከራከርያ እስከዛሬ ድረስ ወያኔ በሰፋላቸው የጎሳ እጀጠባብ ማጌጥ የሚፈልጉ ሁሉ የሚያመነዥኩት ሃሳብ ሆኗል። በቅርቡ ፕሮፌሰሩ በሸገር ሬድዮ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ይሄው ሃሳብ መደገሙ ካስቆጣቸው ወገኖች ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት አንዱ በመሆኑ ይመስላል ይህንን መግለጫ አይሉት ስድብ አሰራጭቷል። ባከታታይም የሞረሽ ደጋፊዎች ነን የሚሉትም ትኩረታቸው ቆምንለት የሚሉት አማራ ነፃ የሚወጣበትን መንገድ ከመሻት ፕሮፌሰሩን በመተቸት ተጠምደዋል።

ተደጋጋሚ የሆነ ከሃሳብ ይልቅ በግል ሰብዕና ላይ ያተኮረ ትችት አስነዋሪ ከመሆኑም በላይ ፕሮፌሰሩን በመሳሰሉ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚሰነዘረው ስድብ በአገር ላይ እንደሚሰነዘር ይቆጠራልና በዚህ መግለጫ ያነበብሁት ስድብ አሳዝኖኝ ከበርካታ ጓደኞቼም ጋር ተነጋግረንበት አልፈነው ነበር። እንዳጋጣሚ በፈረንጆች አቆጣጠር መስከረም 7 ቀን 2014 በቶሮንቶ ካናዳ የኢትዮጵያውያንን አዲስ ዓመት በክሪስቲ አደባባይ እናከብር ነበርና ብዙ ህዝብ በሚርመሰመስበት የደመቀ በአል መሃል የሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት መሪ የሆኑትን አቶ ተክሌ የሻውን አገኘኋቸው። ደስ ብሎኝ ራሴን ካስተዋወቅሁ በኋላ በወጋችን መሃል በቅርቡ ከወጣው መግለጫቸው አምስት ገጽ እውነት ውስጥ ጨዋነት የጎደለው ስድብ ተገቢ እንዳልነበር ነገርኳቸው። የሰማሁት መልስና ለፕሮፌሰሩ ያላቸው ጥላቻ አስደነገጠኝ። ለአማራው ህዝብ መብት ቆሜያለሁ ብለው አደባባይ የወጡ  እኒህ ሰው አንዱን ታላቅ ወገናቸውን በሰብዕናቸው ገብተው ሲዘልፉ መመልከት ዓላማቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሆኖ አገኘሁት። ስልሳዎቹ ውስጥ የሚሆኑ እኒህ አዛውንት ሌላው በእድሜ፣ በእውቀትና በተመክሮ ለሚበልጧቸው ክቡር ሰው የሚሰጠውን የጨዋ አማራ ባህል ከውስጣቸው አላየሁም። ስለሆነም ውይይቴን ብቀጥል የበለጠ ህሊና የሚያቆስል ነገር እንደምሰማ በመገመት ተሰናበትኋቸው። የመግለጫውን ስድቦች ነቅሼ ላቅርብላችሁ። (ሙሉውን ጽሁፍ ከሞረሽ ወይንም ከሌሎች ድረገጾች ፈልጋችሁ አንብቡ)

“…የፕሮፌሰር መስፍንም ክርክር ጭፍን ክህደት ወይም መሳት (መጃጀት) አልያም ቀቢፀ-ተስፋ የተሞላው ቁጭት ከመሆን አያልፍም።……ከመሳት (መጃጀት) የመነጨ ከሆነ ግን አያድርስ! እንዲህ እስኪሆንስ ፈጣሪን “አታቆዬን” ከማለት ሌላ ምን ይባላል።

“…ፕሮፌሰር መስፍን ክህደት የመታወቂያ ባህሪያቸው ስለሆነ…..”

“….ከክህደት ባህሪ በተጨማሪ በዕድሜ መግፋት ምክንያት የመጣ፣ የኋላን ያለማየት እና የመሳት አባዜ የገጠባቸው መሆኑን የሚያመለክት ነው።….”

(ስርዞቹ ለአፅንዖት የተጠቀምሁባቸው የእኔ ናቸው)

ስድቦቹ ሲጠቃለሉ ሁለት ፀያፍ ጽንሰ ሃሳብ ይዘዋል፤ ክህደትና መሳት(መጃጀት)

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን በክህደት መክሰስ በጣም የሚያሳዝን ነው። መስፍን ወልደማርያም ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ወላይታ፣ አገው፣ ጃንጂሮ፣ ጉሙዝ ሳይሉ ርሃቡን፣ ጥማትቱን፣ ስቃዩን፣ እስሩን፣ ግድያውን፣ ግርፋቱን፣ እንግልቱን በጠረጴዛ ዙርያ ውይይትና መግለጫ በማውጣት ሳይሆን ውስጡ ሆነው የታገሉትና የሚታገሉትም። ስቃዩን በአካልም በመንፈስም የሚጋሩት ጀግና ናቸው። ያውም እንደ እኔ የወያኔ ጫና ወላፈኑ ሲዋጀው ነፍሱን በጨርቁ ቋጥሮ፣ ጅራቱን ቆልፎ ከአገሩ የሸሸ ይቅርና፤ አገር ውስጥ ዳፋውን እየተጋቱ ያሉትም መስፍን ወልደማርያምን በክህደት አይወነጅሉም። እዚህ ሆኖ ማቅራራትና እዚያ ሆኖ ህዝብ መሃል እየኖሩ፣ እየተለበለቡ፣ እየታሰሩ  መታገል የብርሃን ዓመት ያህል ይራራቃልና። ርቆም ቢሆን ትግልያስፈልጋል ብሎ ላመነ ትግሉን በእውነትና በጨዋነትየተመራ ቢያደርገው የተመረተ ያደርገዋል።

የትግራይና የወሎ ህዝብ በርሃብ ሲረግፍ ሁሉም ጭንቅላቱን አሸዋ ውስጥ እንደከተተ ሰጎን አንገቱን በደፋበት በዚያ ፈታኝ ወቅት ህይወታቸውን አዳጋ ላይ ጥለው የደረሱላቸውና ዓለም እንዲያውቀው ያቀናበሩት ፕሮፌሰር መስፍን መሆናቸውን መካድ ነው ከሃዲነትሊሆን የሚችለው። የዐማራ ነገድ አለ የለም የሚል እንቶ ፈንቶ ለፖለቲካ ነጋዴዎች እንጂ ለመስፍን ወልደማርያም ሆነ ለዐማራው አንዲት ነገር አይፈይድም።

ለነገሩማ ታምራት ላይኔ፣ ተፈራ ዋልዋ፣ አዲሱ ለገሰ፣ በረከት ሲሞን፣ ደመቀ መኮንን፣ አለምነው መኮንን….አማራው አለ ይላሉ እኮ! የሚያዋርዱት፣የሚገድሉትና የሚያስገድሉት ደግሞ እነሱ ናቸው። ተግባር እንጂ መናገር ማንነትን የማያሳይ ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች ጥሩ ምሳሌዎች በመሆናቸው፤ የሚለፈልፉትን ሁሉ ማመን ከባድ የሚሆነው ለዚህ ነው። ዲያቪሎስም ከወንጌል ይተቅሳል ይላሉ በመኖር ተመክሮ የበሰሉ ዘመዶቻችን።

በደኖ፣ አርባ ጉጉ፣ ጋምቤላ፣ አሶሳ፣ ጎንደር አደባባይ ኢየሱስ ወዘተ…አማራው ሲጨፈጨፍ በእውቀታቸው፣ በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸው የደረሱለት፤ በአገርም በዓለምም የሞገቱት፣ ባቋቋሙት የኢትዮጵያ ሰብዐዊ መብት ጉባኤ (ኢሰመጉ)ና በግላቸው የደከሙትን ብርቅዬ ታጋይ ሲደክሙ ከጎናቸው ያልነበሩ በከሃዲነት ሊወነጅሏቸው የሚያስችል የሞራል ብቃት ያለ አይመስለኝም። ሙሾ ማውረድ ለእንደኔ አይነት ደካሞች ቀላል ነው። በተለያየ መንገድ ደም መላሽ የሆኑትን ጀግኖችና ትልልቆችን በመጥለፍ ጀግናና ትልቅ መሆን የሚገኝ የሚመስላቸው አይጠፉም። ከዚህ በፊትም ነበሩ። የኋላ ኋላ መጋለጡ ግን የማይቀር እውነት ነው።

ወያኔ ኢትዮጵያን ለመበተን በመድረክ ሲያውጅ፤ ይህንን ዘረኛና ከፋፋይ ዓላማ በብቸኝነት የተቃወሙት ታላቁ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ነበሩ። በዚያም አልቆም ብሎ በአማራው ላይ እልቂት ሲታወጅና ሲታረድ ያ ትልቅና ኩሩ ህዝብ መገደል የለበትም ብለው ከፊት የቆሙትና ለመስዋዕት የቀረቡት የቁርጥ ቀን ልጅ አስራት ወልደየስ ናቸው። ወያኔ ደመኛ ጠላት አድርጎ ሊያጠፋቸው ሲነሳ እንዲወግራቸው ደንጋይ ሲያቀብሉ የነበሩት “ለአማራ ቆሜአለሁ” ብለው ብቅ ሲሉ ደግሞ ታሪክና ህዝብ በትዝብት እየመዘገበ መሆኑን ሊዘነጉት አይገባም። ፕሮፌሰር አስራትን ወያኔና ደጋፊዎቻቸው በአካል እንዲጠፉ አድርገው ይሆናል፤ በስራቸው በህዝብ ልብ ላይ መሆናቸውንና ባለታሪክነታቸውን የሚያጠፋ የምድር ሃይል አይኖርም። በተመሳሳይ ሁኔታ የመስፍን ወልደማርያምን ስራና ትልቅነት ደካሞች የሚያጠፉ መስሏቸው ከሆነ ከታሪክ ሊማሩ ይገባል።

 2

( ሰዳቢዎቻቸው ይህን እስኪመስሉ በእስር ካንገላታቸው ወያኔ የሚለዩት በምን ይሆን?አክባሪዎቻቸውም ይሸልሟቸዋል)

መስፍን ወልደማርያም ትናንት ለነበረው አምባገነን መንግስት ካድሬ ሆነው አገልግለው ዛሬ ታጋይ ሆነው ብቅ ያሉ ሳይሆን አሁን ከእንቅልፋቸው ባንነው “አማራ ተበደለ” ብለው ከሚጮሁ ወገኖች በፊት በተደጋጋሚ አምባገነን ስርዓቶችን ተጋፍጠው ህዝቡ መራቡን ያጋለጡ፣ ለእርዳታ ማንም ሳይደርስ የደረሱ፤ ታሰረ፣ ተገረፈ፣ ተገደለ የተባለውን ቀድመው በመገኘት የታደጉ የተግባር ሰው ስለሆኑ በጠረጴዛ ዙርያ ለሚታኘክ የብሄር ብሄረሰብ ቲዎሪ ጊዜ የላቸውም። ስብዕናቸውና ትልቅነታቸው ወደዚህ ትንንሽ ነገር አይመራቸውም። አማራው ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ራሱን በመስዋዕትነት ካስቀመጠበት ልዕልና አውርዶ በጠባቡ የብሄር ስልቻ ውስጥ ለመክተት የሚታገሉ ወገኖች አላማቸውን በጨዋነት ማስረዳት እንጂ በተራ ብልግና ትልልቆችን ማዋረድ “የቆሙለት” የአማራው ባህልም አይደለም።

ሌላው ፀያፍ የሆነው ሁለትኛው ስድባቸው መስፍን ወልደማሪያምን የሳተ (የጃጀ) በሚል ለማዋረድ የሰነዘሩት ስድባቸው ነው። ምን ዐይነት ጤነኛ አዕምሮ ያለው ነው በጎንደር፣ በጎጃም፣ በወሎ፣ በሸዋ የሚገኝ አማራ ብቻ ሳይሆን ሌላውም ኢትዮጵያዊ ፊት እድሜ የጠገበን የአገር አዛውንት የጃጀ ብሎ ደፍሮ የሚሳደብ? ጃጅተውስ ቢገኙ ምን ነውር አለው? በአባቱ ገበና የሚስቅ ምን ዓይነት እርጉም ነው? እንደ አገሬ ደንጋይ ምንም ሳይሰሩ ተጎልተው የሸበቱ ሠርቶና ደክሞ ያረጀን፣ የጃጀን ይንከባከቧል እንጂ አደባባይ ለስድብ ያቀርቧል?

የሚገርመው መስፍን ወልደማርያም ለመጀመርያ ጊዜ መለስ ዜናዊን ስለ አማራው የተከራከሩት የዛሬ ሃያ ሶስት ዓመት በግምት በአሁኑ ሰዓት አቶ ተክሌ የሻው ባሉበት እድሜ ላይ ሆነው ነው። የዛን ጊዜ መስፍን ወልደማርያም ይህንን ሃሳብ የተናገሩት አርጅተውና ጃጅተው ነው ከተባለ አቶ ተክሌ የሻው ሆኑ ጓደኞቻቸው ተስፋ የላቸውም ማለት ነው። ይህንን ስድብ የጻፉት ሆነ መግላጫ ሆኖ እንዲወጣ ያደረጉት ጃጅተዋል ማለት ነው። በእነሱ አባባል ከሆነ ማለቴ እንጂ እኔ ማንንም በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረ ሰው በእድሜውና በጤናው የመሳለቅ ብልግና ነውርነቱን እየሰማሁ ነው ያደግሁት። ነገር ግን መስፍን ወልደማርያም  በአሁኑ እድሜአቸው እንኳ ከነአቶ ተክሌ ሺህ ጊዜ የሰላ አዕምሮ እንዳላቸው አውስትራልያ ሰሞኑን ያወያዩአቸውን ኢትዮጵያውያንን በመጠየቅ መረዳት ይችላሉ። ወይንም ፕሮፌሰሩ በየቀኑ በብሎጋቸው የሚያሰፍሩትን ማንበብ አለባቸው። አንድ ኢሜል መመለስ ባህል ማድረግ አቅቶን በምንደፋደፈው ደካሞች መካከል ቀን በቀን የዓለምን ሁኔታ እየተከታተሉ ብዙዎቻችንን እያስተማሩ ያሉ አዛውንት ጃጅተዋል ማለት ምን ተፈልጎ ነው? በነፃው ዓለም ትልልቅ ከተሞች ሃያ ሰው አሳምኖ መሰብሰብ የማይችሉ ሰዎች የመስፍን ወልደማርያምን አዕምሮ ለመመዘን ሲሞክሩ ያሳዝናል። ባዶ በርሜል ብዙ ይጮሃል ብለው ይሆናል መስፍን ወልደማርያም መልስ ያልሰጧቸው። እውቀት በተግባር ይፈተኗል። ለአማራው አለህ የለህም የሚለው ቀረርቶ ጀሮው ጫፍ አይደርስም። የመንዝ አማራ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሃረጉን ቢስብ እንደማይጠቅመው አሳምሮ ያውቃል። እንዳይገደል፣ እንዳይታሰር፣ እንዳይዘረፍ በተጨባጭ የሚከላከልለት እንጂ በስሙ የንግድ ፈቃድ አውጥቶ የሚነግድበት አይደለም የሚፈልገው። ስለፕሮፌሰር መስፍን ገድል ብዙ የሚያውቁ፣ አብረው የሰሩ፣ ሃዘናቸውንና ድካማቸውን የተካፈሉ ዝም ብለው በተቀመጡበት ሰዓት አላስችለኝ ብሎ ለፈለፍሁ እንጂ ታሪክና በርካታ አዋቂዎች እየታዘቡ እንደሆነ አውቃለሁ።

ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በእግዜብሄር አምሳል የተፈጠረ ሰው ክቡርነቱ እንጂ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ወላይታ… የሚለው የታፔላ ስም መቀነስ መጨመሩ ፋይዳ አይሰጣቸውም። ለከፋፋዮች፣ ለፖለቲካ ነጋዴዎች፣ የማንነት ቀውስ ውስጥ ለተዘፈቁ ከንቱዎች ይጠቅም ይሆናል። እየጠቀመም ነው።

አፄ ቴዎድሮስን፣ አፄ ዮሃንስን፣ አፄ ምንይልክን፣ ንጉሥ ተክለሃይማኖትን፣ ቀዳማዊ ኃይለስላሴን፣ ንጉሥ ጦናን፣ አሉላ አባ ነጋን፣ በላይ ዘለቀን፣ ሱልጣን አሊሚራህን፣ አባ ጅፋርን፣ ጄኔራል ጀጋማ ኬሎን፣ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን፣ ባሮ ቱምሳን፣ ተስፋዬ ደበሳይን፣ አብርሃም ደቦጭን፣ አበበ አረጋይን፣ ሌንጮ ለታን፣ ጄኔራል ከማል ገልቹን፣ አንዳርጋቸው ጽጌን፣ እስክንድር ነጋን…ወዘተ እነዚህን ሁሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች በሰብዕናቸውና በኢትዮጵያዊነታቸው እንጂ በጎሳቸው፣ በቋንቋቸው  እየከፋፈለ  የሚያይ ሳያረጅ የጃጀ፣ እውቀት ሳይገበይ የሳተ፣ ያለዚያም የፖለቲካ ንግድ ፈቃድ አውጥቶ የሚሮጥ ሸፋጭ ነው።

ትችቴን አንድ የውጭ አገር ፀሃፊ የኢትዮጵያውያንን  ጨዋነት በገለጸበት ታሪክ ልደመድመው ወደድሁ። የጎደለን እውነተኝነትና ጨዋነት ስለሆነ። ጸሃፊው ኢትዮጵያ ከጣልያን ጋር ስትዋጋ ከጎኗ ተሰልፎ ብዙ መስዋዕት የከፈለውና ያየውንም እውነት የመሰከረው አዶልፍ ፓርለሳክ ነው። “የሃበሻ ጀብዱ” በሚለውና ተጫነ ጆብሬ መኮንን  በተረጎሙት ገጽ 111 ላይ እንዲህ ይቀርባል።

በአድዋ ጦርነት ጊዜ አምባላጌን ይዟት ለነበረው የጣልያን ሻለቃ ቶለሲን ራስ መኮንን እንዲህ ብለው ነበር።

“ውድ ወዳጄ ሻለቃ ቶለሲ፤ ጀግንነትህንና ቆራጥነትህን አውቃለሁና አከብርሃለሁ። አደንቅሃለሁ።ይሁን እንጂ በዚህ ጦርነት ትሸነፋለህ። ስለዚህ አምባላጌን ለቅቀህ ወደ መቀሌ ሽሽ። እንዲህ በሰላም አምባላጌን ለቅቀህ ከወጣህ ጦርህ እንደታጠቀ ወደ መቀሌ ሸሽቶ ያለችግር እንደሚገባ ቃሌን እሰጥሃለሁ። ወዳጄ ቶለሲ ያለህን ጦር አውቃለሁ። እኔ አስር እጥፍ ጦር አለኝ። እና ኋላ በወታደሮቼ ብትገደል ልቤ ያዝናልና እባክህ አምባላጌን ለቅቀህ ውጣ።” ብለው መልዕክት ቢልኩበትም፣ ሻለቃ ቶለሲ “ከአለቆቼ ተጨማሪ ትዕዛዝ ካላገኘሁ አምባላጌን መልቀቅ አልችልም” ብሎ የራስ መኮንን ልመና ባለመቀበሉ ራስ መኮንን ሁለተኛ ጊዜ ለሻለቃ ቶለሲ መልዕክት ሲልኩ እንዲህ ብለው ነበር።

“ነገ ማለዳ ጦሬ ይዘምትብሃል።አሁንም ደግሜ ላሳውቅህ። ጦርህን ይዘህ ሂድ። ልቤን አታሳዝነው።” ሻለቃ ቶለሲ በድጋሚ የራስ መኮንንን ደግነት ባለመቀበሉ የራስ መኮንን ጦር የሻለቃ ቶለሲን ጦር ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀር አጨደው።

በኋላ ራስ መኮንን የሻለቃ ቶለሲን ሬሳ አስፈልገው ወታደሮቻቸውን ለአንድ ጀግና በሚገባው ክብር እንዲቀበር አዘው ዐይናቸው ያዘለውን እንባ ለመዋጥ ሺጣጣሩ ታይተዋል። እንግዲህ እንዲህ ዓይነት የጦር መሪ ያፈራችውን ሃገር ነበር ጣልያኖች ዛሬም ያልሰለጠነች አረመኔ ሃገር አድርገው በመላው ዓለም ጉራቸውን የሚነፉት።”  ብሏል።

ከመቶ ዓመት በፊት በአድዋው ጦርነት አገርን ለወረረና ለተዋጋ ጠላት አባቶቻችን የሰጡትን ክብር እንኳ ለመሰል ዜጋችን መስጠት ሲሳነን የሚያሳዝን ነው። ለዚህ ፈረንጅ የኢትዮጵያውያንን ጨዋነት ለማወቅና ለመመስከር ኢትዮጵያዊ ሆኖ መወለድ ሆነ ማደግ አላስፈለገውም። ንፁህ ህሊናና ብሩህ አዕምሮ ብቻ ነው የሚጠይቀው። ህሊናችን በአድርባይነት፣ በምቀኝነት፣ በንዋይና በስልጣን ስስት ከጨቀየ የምንናገረውና የምናደርገው ሁሉ አገርና ህዝብን መጉዳቱ አይቀርም። መልካም ዛፍ በፍሬው ይታወቃልና ከምንናገረው የበለጠ የምናደርገው በማንነታችን ላይ ምስክር ሆኖ የኖራል።

አገራችን መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት። አደገኛ አጥፊዋም በስልጣን ላይ ያለው ዘረኛ አምባገነን ስርዓት ነው። የትግሉ አቅጣጫ ሁሉ ስርዓቱን ለመቀየር  ተባብሮ በመታገል የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን መገምባት ሊሆን ይገባል። በጎንዮሽ ጦር እየሰበቁ ወገንን ለመውጋት ጊዜና ጉልበት ማባከኑ ቢያበቃ መልካም ነው። ድክመቶችም ካሉ በጨዋነት እየተመካከሩ ማረም ከኪሳራው ትርፉ ያመዝናል። ፕሮፌሰር መስፍንን ጭቃ ላይ ለመጎተት ህሊና ያልዳኛቸውን ዛሬ ስለሚሉትና ነገ ስለሚያደርጉት እንዴት እንመናቸ? በመተሳሰብና በመመካከር ወደጋራ የአገር ጥላት ማተኮር ይሻላል በማለት ቁጭቴን ለመግለጽ በመሆኑ ሃሳቤ የሚያስቀይማችሁ ካላችሁ አስቀድሜ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ከተሳሳትሁም ለመታረም ዝግጁ ነኝ።

ቸር እንሰንብት

ኢትዮጵያን ተባብረንና ተከባብረን ካጥፊዎቿ እናድናት

ጸሃፊውን በ amerid2000@gmail.com ማግኘት ይቻላል


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>