Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ልማት ካለ ነፃነትና ፍትሕ ፋይዳ የለውም –ክፍል ሁለት

$
0
0

ከ ይኩኖ መስፍን

ቦስተን ሰሜን አሜሪካ

መልካም አስተዳደርና የፓለቲካ ምሕዳር

Justiceየሞያ ነፃነት በተገደበባት” ነፃ የፍትሕ” የዳኝነትና የዴሞክራሲ ተቋማት በሌሉበት! የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት በጠፋበት” በጋብቻና በዝምድና የተሳሰረ አንድ ፈላጭ ቆራጭ ፓርቲ የሀገሪትዋን ሁለንትናዊ ሰብኣዊ ማተሪያላዊና አእምራዊ ሀብት ተቆጣጥሮ ራሱ ሕግ አውጪ! ራሱ ሕግ ተርጓሚ! ራሱ ሕግ ፈፃሚና አስፈፃሚ በሆነበት” ባጠቃላይ ፍርሃት! ዱላ! ድሕነትንና ረሃብን እንደ የፓለቲካ መሳሪያ አድርጎ በመጠቀም ለያይቶና አደንቁሮ የሚገዛ አምባ ገነን መንግስት ባለበት ድሃ ሀገር የሚኖር ሕብረተሰብ ምን ያህል ለአፈና! አድልዎ! ጭቆና እና ዝርፊያ የተጋለጠ እንደሆነ መገመቱ አያዳግትም::

አብዛኞቻችን ከደርግ ውድቀት በሗላ በእርስ በርስ ጦርነት የደቀቀውን ሀገርና ህዝብ እፎይታ አግኝቶ በይቅርታ መንፈስ ሁላችንም በአንዲት እናት ሀገር ጥላ ስር ታቅፈን! ተቻችለን! ተፋቅረንና ተከባብረን በጋራ የምንገነባት አንዲት ዲሞክራሲያዊት እናት ሀገር ትኖራለች የሚል ነበር ተስፋችንና ምኞታችን፡፡ የህወሓት/ኢሕአዴግ ስርዓትም ካለፉት መንግስታት ተምሮ በሀገራችን ቢያንስ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሰረት ይጥል ይሆናል የሚል በጎ እምነትና ግምት ነበረን፡፡ በሂደት የሚታዩ አንዳንድ የልማት እንቅስቃሴዎችም እንደ መልካም ጅምር በመውሰድ” ነገር ግን በመልካም አስተዳድር! በፓለቲካዊ ምሕዳር! በምርጫና በሀገራችን ድሕንነት ዙሪያ የሚታዩ መሰረታዊ ችግሮች ዛሬ ነገ ይታረማሉ በማለት ዜጎች በተደራጀም ሆነ በተናጠል ላለፉት አሰርቱ ዓመታት ብሶታቸውን ሲያሰሙና አቤት ሲሉ ቆይቷል:: ይሁን እንጂ ሰሚ ጆሮ አልተገኘም::

ህወሓት/ኢሕአዴግ በትረ ስልጣኑን ከጨበጠና ካደላደለ በሗላ እሱም በተራው የጥፋት መንገድ በመከተል የህዝቡን የለውጥ ጥማትና የፍትሕ ተስፋ አጨልሞታል:: ትናንት በደርግ ቀይ ሽብር የተቀጣውና የደነገጠው ሕብረተሰብ ለውጥ ይመጣል ብሎ ሲጠብቅ ዛሬም በፀረ ሽብር አዋጅ እንዲገዛ! እንዲሸማቀቅና እንዲሰጋ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ትላንት ለዴሞክራሲና ለሰው ልጅ ነፃነት ሲባል የተከፈለውን ኩቡር የህይወት መስዋእትነት ተረስቶ ዛሬ የህወሓት/ኢሕአዴግ የአንድ ድርጅት አባልና ታማኝ ካልሆንክ በስተቀር የመደራጀት! የመናገር! የመስራት! ባጠቃላይ እንደ አንድ ዜጋ በህይወት የመኖር ነፃነትህን ተነጥቆ ለፍልሰት! ለእስር! አሊያም ለሞት ትዳረጋለህ፡፡ የተከበረና አኩሪ ባህል ያለው ጨዋ ህዝብ ዛሬ ወዳጅ” ማሀል ሰፋሪና ጠላት ብሎው በመፈረጅና በመከፋፈል አንዱ አንዱን የገዛ ወንድሙን በጎሪጥና በጥርጣሬ ዓይን እንዲተያዩ እየተደረገ ይገኛል፡፡ አንድ ዜጋ የተለየ ሃሳብ ወይም የሌላ ድርጅት አባል በመሆኑ ብቻ እንደ ነውርና እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ በህዝብ ፊት የተለያዩ አስነዋሪ የማስፈራሪያ ዘዴዎችን እየተጠቀሙ በተወለባት ምድር ሓፍረት እንዲሰማው” ከሕብረተሰቡ እንዲነጠልና እንዲሰጋ ከማድረግ ባሻገር ይባስ ብለው ሲሞት እንዳንቀበረው” እሳት እንዳናስጭረው” የሚል የወረደ ማሕበራዊ ውግዘትና ተፅእኖ እንዲፈፀምባቸዉ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ሌሎችም በዚሁ ፅሑፍ ለመጥቀሱ የሚከብድና የሚዘገንን ድርጊት በተለይም ለአርባ ዓመታት ያህል በአንድ ሞኖፓላዊ ድርጅት ህወሓት ተይዞ የሚገኘው የትግራይ ህዝብ ታሪኩንና መለያ ባህሉን (Indeginous culture) በጉልበት በማፈራረስ እና በመበረዝ በምትኩ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቅይጥና የተዳቀለ የካድሬዎች ግራ አስተሳሰብ እንዲተካ በማድረግ እርስ በርሱ እያናከሱ በላዩ ላይ ይህ ነው የማይባል ግፍ እየተፈፀመበት ይገኛል፡፡

ልብ በሉ!! ተወልደን ባደግንበትና እትብታችንን በተቀበረበት መንደር ዛሬ ይህ ዓይነት የስነ ልቦና ጦርነት በያንዳንዳችን ቤት ቢደርስብን ምን ይሰማናል? ትላንት ጫካ ገብተው ስለ ነፃነት ሲዘምሩ! በሰማእታት ስም ሲምሉ! ለህዝብ ሲያስተምሩና በሽዎች የሚቆጠሩ ለጋ ወጣቶችን ቀብረው ስልጣን ላይ የወጡ የፓለቲካ መሪዎቹ ያ ሁሉ ለህዝብ የገቡበትን ቃል ረስተው ዛሬ ብዙሃኑን ለልመናና ለስቃይ ዳርገው እነሱ በሙሱና ሲጨማለቁ! ከሕግ በላይ በመሆን በህዝብ መብት ላይ ሲቀልዱ! በገዛ ወገናቸው ላይ ሲጨክኑና ሲያሰቃዩ በውል ስናይ እውነት ምን ይሰማናል? የህወሓት/ኢሕአዴግ ስርዓት የሁሉም ዜጋ ሕገ መንግስታዊ መብትና ደሕንነት ጠብቆ በእኩል ከማስተዳደር! ከመጠበቅና እንደ መንግስት ከመስራት ይልቅ ራሱን ታች ወርዶ ከሕብረተሰቡ ወይም ተቃዋሚ ናቸው ከሚላቸው ሰዎች ጋር የሚናቆርና የሚያውክ ከሆነ ህዝቡ ለማን አቤት ይበል?

ዛሬ የምንኖረው በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሰው ልጅ ከአካባቢው የእይታ አድማስ አልፎ ዓለምን መዳሰስ በጀመረበት” በተለይም ዴሞክራሲ” የሕግ የበላይነት” መልካም አስተዳደር” ሰብኣዊ መብትና የነፃነት ጥያቄዎች ድንበር አልባ (ዩኒቨርሳል) የሰብኣዊ ፍጡር እሴቶች በሆኑበት በሰለጠነ ዘመን ሆኖ ሳለ ነገር ግን ህዝባችን ብሎም ወጣቱ ትውልድ አደንቁረህ ግዛ በሚል የህወሓት/ኢሕአዴግ ያረጀ ያፈጀ ፈሊጥ ሳይወድ በግድ እንደ ወባ ክትባት የአንድ ፓለቲካዊ ቡድን ጠባብና ሞኖፓላዊ አስተሳሰብ ተሸብቦ እንዲያድግ የሚገደድበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ለሰሚ ብቻ ሳይሆን ለተመልካችም ግራ የሚያጋቡ የዘመናችን የሀገራችን እንቆቁልሽ ናቸው፡፡

የተከበራችሁ ውድ ኢትዮ}ያውያን ወገኖቼ ሆይ!!

በሀገር ቤት ቆይታዬ እስካሁን ድረስ በአእምሮዬ ውስጥ እየተመላለሱ የሚረብሹኝ ብዙ ነገሮችን ታዝቤያለሁ፡፡ ሁሉም ያየሁትንና የሰማሁትን የህዝቡን እሮሮ በዚህ አጭር ፅሑፍ ዘርዝሮ ለማቅረብ የሚከብድ ቢሆንም ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜኑ ክፍለ ሀገራችን በተለይም አርባ ዓመታት ያህል በአንድ ነፃ አውጪ ነኝ የሚል ፓለቲካዊ ድርጅት በህወሓት ሞኖፓላዊ አገዛዝ ወድቃ በአካባቢው ነዋሪዎች አጠራር የፓሊስ ግዛት (police state) እየተባለ የሚነገርላት ትግራይ ለወራት ያህል በቆየሁበት ጊዜ ያጋጠሙኝን አስደማሚና አስነዋሪ ነገሮችን ቢያንስ ሕብረተሰቡ ማወቅ አለበት ብዬ በማስታወሻዬ ዘግቤ ከያዝኩዋቸው አንዳንድ ነጥቦች ውስጥ ጥቂቶቹን ቆንጠር አድርጌ ላካፍላችሁ፡፡

ፍርሓት (ወኔ ሰላቢ በሽታ)

ህዝቡን አስደንግጦ! አስፈራርቶ! አሸብሮና ወኔ ሰልቦ መግዛት በደርግ ጊዜም የነበረ ቢሆንም የዛሬው ግን የረቀቀና ዓይን ያወጣ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ለኢትዮ}ያ ህዝብ ካወረሱትና ካበረከቱት ትልቁ ስጦታና ራዕይ “ፍርሃት” ነው፡፡ ፍርሃት በአሁኑ ጊዜ ህወሓት/ኢሕአዴግ ህዝቡን አንበርክኮና ፀጥ ረጭ አድርጎ በሀይል ለመግዛት የሚጠቀምበት ትልቁ የፓለቲካ መሳሪያው መሆኑን እኔ ከምናገረው በላይ ነው፡፡ ፍርሃት በሕብረተሰቡ ውስጥ ገብቶ ምን ያህል አስከፊና አስፈሪ ሁኔታ እንደፈጠረ በይበልጥ የተረዳሁት ዘመድ ጥየቃ ከቦታ ወደ ቦታ ስንቀሳቀስ በደረስኩበት ቤት ሁሉ የማገኛቸው ሰዎች አንዳንዶቹ በስጋትና በጭንቀት ተውጠው እንባ እየተናነቃቸው ሲነግሩኝ ውስጤ በጣም ይሰማኝ ነበር፡፡ አዎ!! ሁኔታውን በአካል ተገኝቶ ለተመለከተው ሰው እውነትም ባለቤት ያጣ ያልታደለ ህዝብ! ያልታደለች ሚስኪንዋ ድሃ ሀገር! የሚያሰኝ ነው፡፡

ከዚህ በመነሳት ጥያቄ ለመሰንዘር ግድ ሆነብኝ፡፡ “እናንተ ዜጎች አይደላችሁም ወይ? በሀገሪቱ ሕግ የለም ወይ? ለመንግስት አቤት የማትሉበት ምክንያት ለምንድን ነው? የተሰማችሁ ሀሳብ ሁሉ ለሚመለከተው አካል በግልፅ ለመናገርና ለመቃወም ለምን ትፈራላችሁ?” ብዬ ብጠይቃቸው የሰጡኝ መልስ የሁሉም ሃሳብ ተመሳሳይ ነው፡፡ “እኛ የሕግ ዋስትና የለንም፡፡ መንግስትም ራሱ ለሕግ ተገኝ ካልሆነ ለማን አቤት ይባላል” የሚል ነው፡፡

“ስማ ወንድማችን! እኛን የሚያስተዳድሩን እኮ መንግስት የላካቸው ካድሬዎችና ታማኞች ናቸው፡፡ በሕብረተሰቡ ዘንድ አፍ ጠባቂዎች እየተባሉ የሚጠሩ የተለያዩ የስለላ መረቦች በየመንደሩ በውስጣችን እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ለመቆጣጠር እንዲመቻቸውም ከላይ እስከ ታች ሕዝቡን አንድ ለአምስት አደራጅተውታል፡፡ ቀጥሎም የቤተ ሰብ ሸንጎ የሚባልም አለ፡፡ ከዚህም አልፎ የፌዴራል ፓሊስ! ያካባቢው ፓሊስ! ሚሊሻና የተለያዩ ስውር ታጣቂዎች ሁሉም በአብዛኛው ጊዜ የሚጠብቁት የህዝቡን ድህንነትና የዜጎች ህልውና ቅድሚ በመስጠት ሳይሆን የኛን ነፃ እንቅስቃሴ የሚገድቡና አፋችንን የሚጠብቁ ሀይሎችም ናቸው፡፡ ሌላ ቀርቶ በቤተሰብ መካከልም መተማመን የለም፡፡ ባል ካፈነገጠ በሚስቱ ወይም በዘመዶቹ ሚስት ካፈነገጠች ደግሞ በባልዋ ወይም በልጆችዋ እየገቡ ትዳር እንዲፈርስ ወይም እንዲካሰሱ ያደርጋሉ፡፡ ከተናገርክ ደግሞ አፍ እላፊ እየተባለ ከስራ ትባረራለህ! መሬትህን ወይንም ንብረትህን ትነጠቃለህ! በህዝብ ስም ከውጭ የሚመጣ እርዳታም እንዳታገኝ ይደረጋል! ከዚህም አልፎ እንደ ጠላት የተፈረጁ የተቃዋሚ ፓለቲካ ድርጅቶች ስም እየተለጠፈብህ የትምክህተኞች አቀንቃኝ! አሸባሪ ! ከሃዲ! ወዘተ በሚል ሰበብ ተከሰህ ወደ አቦይ ታአገስ (እስር ቤት) ትገባለህ፡፡ ከዚያ በሗላ ጠያቂ የለህም፡፡ ወይም ሀገር ለቀህ ትጠፋለህ አሊያም ትሰወራለህ፡፡ ባጠቃላይ ሌላ ሰው ወይም ሕብረተሰቡ ተቃውሞ ወይም የፍትሕ ጥያቄ እንዳያነሳ ለማድረግ እኔን አይተህ ተቀጣ የሚል ሌላ ስውር መልእክት በሚያስተላልፍ መልኩ ግፍ ይፈፀምብሃል፡፡

በዚህ ምክንያት የሆድ ቁስል ይዘን እያወቅን እንዳላወቅን አፋችንን ይዘን ዝም እንላለን፡፡ ለማንስ አቤት እንበል፡፡ ከጎጥ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ አመራር ያለው የካድሬና የስለላ ሰንሰለት ነው፡፡ እኛ እኮ በሀገሪቱ ሕገ መንግስት አለ ሲባል በወሬ እንሰማለን እንጂ ሕጉ ፈፅሞ እኛን አይመለከተንም፡፡ ሕግና ስርዓት ቢኖርማ እንዲህ አይሆንም ነበር፡፡ እኛ እኮ እስካሁን ድረስ የምንተዳደረው በትጥቅ ትግሉ ጊዜ ከነበረው የድርጅቱ ሕግና ስርዓት የተለየ አይደለም፡፡ ድሮ ሲያስተዳድሩን የነበሩት የህወሓት ካድሬዎች ናቸው አሁንም ከላይ እስከ ታች አፋችሁን ያዙ እያሉ እየኰረኰሙ እየገዙን ያሉት እነሱ ናቸው ሌላ አዲስ ነገር አልመጣም” እያሉ የነገሩኝ ብዙ ናቸው፡፡ በተለይም የቅርብ ዘመዶቼና ጓደኞቼ በጆሮዬ ሹክ እያሉ “ከሰው ጋር ብዙ አታውራ፡፡ ጠንቀቅ በል፡፡ ሲቪል መስለው ካድሬዎች ይከታተሉሃል፡፡” በማለት ምክር ይለግሱልኝ ስለነበር ከሌላ ሰው ቀርቶ ከቅርብ ዘመዶቼ እንኳን ሳይቀር ነፃ ሆኖ ለማውራት በጣም ከባድ ነበር፡፡

የሃሳብ ነፃነትና መደራጀት

የሃሳብ ነፃነትና መደራጀት በሕገ መንግስቱ ሰነድ ቁልጭ ብለው ከተቀመጡት መሰረታዊ” ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ መብቶች ከወረቀት አልፈው በመሬት ላይ አይታዩም፡፡ ሕጉ ለባለሰልጣናት እንጂ ለሰፊው ህዝብ ባዕድ ነው፡፡ ሕጉ የአንድ ድርጅት የበላይነት ጠባቂና መሳሪያ እንጂ የህዝቡንና የሀገሪትዋን ሉአላዊ ክብር የሚጠብቅ ሞሶሶ አይደለም፡፡ ሕጉ ሌሎችን በተለይም በጠላትነት ለሚያዩዋቸው ተቃዋሚ ድርጅቶችን ለመምታት” ለማሳደደድ” ለማሰርና ለማዳከም የሚጠቀሙበት ትልቁ መሳሪያ እንጂ ለእኩልነትና ለፍቅር የቆመ አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር የዳኝነት” የፍትሕ” የምርጫና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት የአንድ ድርጅት አገልጋይና መሳሪያ በሆኑበት” ባጠቃላይ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ኢሕአዴግ የተለየ ሃሳብ ያላቸውን ዜጎች እንደባላንጣ ፈርጆ ሰበብ አስባብ እየፈለገ በመምታት ራሱን አውራ ፓርቲ ነኝ ብሎ የሰየመ አምባ ገነናዊ ስርዓት በነገሰበት ሀገር ስለ የሃሳብ ነፃትነትና መደራጀት ብሎ ማንሳት አይቻልም፡፡ በተለይም አሁን ከአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት በሗላ ብሶበታል፡፡ በተለይም የመለስ ራእይ ወራሽ ነን የሚሉ ቡድኖችና ባለስልጣናት ራሳቸው በራሳቸው መተማምን አቅቷቸው ሁሉም ነገር በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ስር መሆን አለበት በሚል ጭፍን አስተሳሰብ ላይ በመመስረት ያለ ምሕረት እየጠረጉ ወደ ፍፁም ጠቅላይ (ቶታሊቶሪያን) የሆነ ስርዓት ተሸጋግሯል፡፡

ከዚህ በመነሳት ዛሬ በሀገራችን ሰላማዊና ሕጋዊ የትግል መንገድ ተከትለው ሕጋዊ ፈቃድ አውጥተው በመንቀሳቀስ ላይ በሚገኙ ተቃዋሚ የፓለቲካ ድርጅቶች ላይ እየደረሰ ያለው አፈናና ወከባ ይህን ነው ብሎ ለመናገር ይከብዳል፡፡ ባንድ በኩል ፈቃድ እየሰጠ በሌላ በኩል ደግም ህገ መንግስት የሰጣቸውን መብት እንዳይጠቀሙ በመከልከልና ብሎም በመገደብ መፈናፈኛ አሳጥቷቸዋል፡፡ ከህዝብ ጋር እንዳይገናኙ” አባላት እንዳይጠጉዋቸው” ህዝባዊ ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደርጉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መሰናክል በመፍጠር የተለያዩ ፀረ ዴሞክራሲና ኢፍትሓዊ የሆኑ እርምጃዎች እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ሕብረተሰቡን በተለይም አዲሱ ትውልድ ለለውጥ ሊያነሳሱ ይችላሉ ብሎው የሚገምትዋቸው በአመራር ላይ የተቀመጡ ወጣት ምሁራን ላይ ሆን ብሎው በማነጣጠር በፀረ ሽብር አዋጅ እያመኻኙ ማሰር ስራዬ ብሎው ተያይዞውታል፡፡

ድርጊቱ ደረጃው ይለያይ ይሆናል እንጂ በሁሉም አካባቢ በሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ የሚፈፀም ቢሆንም በተለይም ዓረና ትግራይ በሚባል በትግራይ ውስጥ በህግ ተፈቅዶለት በሚንቀሳቀስ ድርጅት ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍ እንደ ምሳሌ ወስደን ብናይ በመላ ሀገሪቱ ያለው አስከፊ የፓለቲካ ደባብ ትክክለኛ ገፅታ ማሳያ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ድርጅቱ በይፋ በሕግ ከተቋቋመ ጀምሮ አቅሙ በፈቀደው መጠን ይንቀሳቀሳል፡፡ ድርጅቱ የተፈጠረበት ሁኔታ መለስ ብለን ስናይ ትግራይ “የተለየ አመለካከት የያዘ ትግርኛ ተናጋሪ ቀርቶ የተለየ መልክ ያላት ወፍ እንኳን ዘወር አትልበትም በማለት ለአርባ ዓመታት ያህል የህወሓት ትልቁ መደበቂያ ምሽግና ብቸኛ የጓሮ አትክልት ሆኖ በቆየው ምድር ላይ” በመሆኑ ለዓመታት ያህል ስር የሰደዱ የተለያዩ የመጨቆኛ መረቦችንና ሞኖፓላዊ አስተሳሰቦችን ሰብሮ የመርፌ ቀዳዳን የምታህል መንገድ አልፎ በምትኩ ዴሞክራሲያዊና የሰለጠነ ራእይ ይዞ ወደ ሕብረተሰቡ ለመግባት ምን ያህል አስቸጋሪና ውስብስብ ትግል የሚጠይቅ መሆኑን ለመገመቱ አያዳግትም፡፡

ወደ ጠንካራ ሀገራዊ ድርጅት መፈጠር እንደ መሳለል ሆኖ ያገለግላል ተብሎ በሚሊኖች ዘንድ ተስፋ የጣለለት ዓረና በትግራይ አማራጭ ፓርቲ በመፈጠሩ የሚያስደነግጣቸውና እንደ ትልቅ ስጋት የሚያዩት የህወሓት መሪዎች ብቻ አይደሉም፡፡ ሌሎችም የኢትዮ}ያ መፈራረስና ጥፋት የሚመኙ በተለይም በትግራይ በትግራይ ምድር ላይ ኢትዮ}ያዊነት ማንነትና ሀገራዊ ራዕይ የሰነቁ ለህዝቦችዋ አንድነትና ክብር የሚሟጎቱ ሀገር በቀል ብሄረተኞች እንዳይበቅሉ የሚሰጉ እንደ ሻዕቢያና ጀሌዎቻቸው የመሳሰሉት ሀይሎች ይህቺን ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም በማለት ዓረና ትግራይን ከእንጭጩ ለማጥፋትና ለማዳከም የዘወትር ተግባራቸውና ሕልማችው መሆኑን ህዝቡ ከጥዋቱ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ሌላውን ትተን በቅርቡ የብዙሃን መገናኛዎችንና ማህበራዊ ድህረ ገፆችን እየተጠቀሙ በዓረና አባላትና መሪዎቹ ላይ የተቀናጀ ጥቃት ለመፈፀም ምን እያሉ እንደሆነ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ የሚገርመው አንዳንዶቹ እንዲያውም ለነገሩ ለይስሙላ ተቃዋሚዎች ነን ይበሉ እንጂ በተግባር ሲታይ ስውር አጀንዳቸው ከህወሓት/ኢሕአዴግ በላይ ዓረና ትግራይን እንደስጋት የሚያዩት መሆናቸውን በግልፅ የሚያመላክት ነው፡፡ ሆኖም ሀቁ “እኛም አውቀናል ጉድጓድ ጭረናል” እንደተባለው ሁሉ ጭቆና ያንገሸገሸው ህዝብ ነፃ እስካልወጣ ድረስ ይቅርና የወሬ ጋጋታ ሚሊዮን ጦርም ቢሰለፍ ከመታገል ወደሗላ ሊመልሰው የሚችል ምድራዊ ሀይል እንደማይኖር ሊያውቁት በተገባ ነበር፡፡

ከዚህ የተሳሳተ አመለካከትና ግምት በመነሳት በተለይም በመንግስት በኩል የዓረና ትግራይ ፓርቲ አባላት ለሆኑ ዜጎች የሚደርስባቸው ጫና” ግፍና አፈና ለመቀበል አይደለም ለማሰብም በጣም ያስቸግራል፡፡ ካድሬዎቹ ራሳቸው ከሳሽ” ራሳቸው መስካሪ” ራሳቸው ዳኛና አሳሪ እየሆኑ ማሰቃየት” ከህብረተሰቡ እንዲገለሉ ማድረግ” ከስራ ማባረር” ሀገር ያፈራውን ጥቅማ ጥቅም መከልከል የተለመደ ስራ ሆኗል፡፡  የትምክህት ሀይሎች አመለካከት አራማጆች” እንዲሁም በነሱ አጠራር አሸባሪዎችና ታሪካዊ ጠላቶቻችን ናቸው ከሚሉዋቸው ጋር በማዛመድ ተላላኪዎችና ወኪሎች ናችሁ” በመባል እየተወነጀሉ አብረው የጥቃቱን ሰለባ እንዲሆኑ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህ የተነሳም ማሕበራዊ ቀውስና ጫና እየደረሰባቸው ያበዱ ወይም የት እንደገቡ የማይታወቁ የድርጅቱን አባላት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ በዚህ ዓይነት በተመሳሳይ እየተከሰሱና እየተጠረጠሩ ቤታቸው የፈረሰ ቤተሰብ” የተፋታ ትዳርና ሳይወድ በግድ ከሞቀ ቤቱና ከቀዩ እየፈለሰ ወደ ስደት የሚጎርፈው ወጣት ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ለአብነት የሚከተሉትን ግለሰቦች የደረሰባቸው ግፍ እንመልከት፡፡

  • መምህር ሀይሌ አሰመኽኝ የሚባል የህወሓት የቀድሞ ታጋይ የነበረና በሗላም በባድመ ጦርነት የቀኝ እጁን ተቆርጦ ወደ ቤቱ የተመለሰው ወገን የአረና ትግራይ አባል በመሆኑ ብቻ በአካባቢው ካድሬዎች በተደረገበት ክትትልና ወከባ ምክንያት እንዲያብድ ተደርጎ አሁን የት እንዳለ አይታወቅም፡፡ ቤተሰቡም ድርብ ድርብርብ ሃዘን ሆኖባቸው እያለቀሱ ይገኛሉ፡፡ በሸራሮ ከተማም በተመሳሳይ አካሃን አቶ ፍፁም ያሃንስ በሚባል ወገናችን በደረሰበት ተፅእኖ አብዶ የከተማው ህዝብ መቀጣጫ ሆኖ ይገኛል፡፡

 

  • በዛና ከተማ እና አካባቢዋ በጣም ታዋቂ የነበረው የድሮ የህወሓት ታጋይ ዛሬ የአረና አባል በመሆኑ ብቻ ካድሬዎቹ ሲከታተሉት ከቆዩ በሗላ እሱን የሚያጠቁበት የተለያየ ምክንያት በመፈለግ በቤተሰቡ ላይ ጫና በመፍጠርና በመካከላቸው ጣልቃ በመግባት የገዛ ዘመዶቹና ቤተሰቦቹ ሳይቀሩ እንዲከሱት እና ተባባሪ እንዲሆኑ በማድረግ በደረሰበት ተፅእኖ ከቤቱና ከቀዩ እንዲባረር ተደርጎ አሁን አዲስ አበባ ይገኛል፡፡ ይህንን እውነታ በግልፅ የነገረኝ ስሙን እንዲጠቀስ ያልፈለገው የመንግስት ሰራተኛ የሆነው የራሱ ወንድም ነው፡፡

 

  • ሌላ አንድ ወጣትም ተመሳሳይ ፈተና ገጥሞታል፡፡ ልጁ የአረና አባል አይደለም፡፡ ነገር ግን አንድ ቀን ወጣቱ ከአንድ የአረና ትግራይ አባል በመንገድ ተገናኝተው ቆሞው ሲያወሩ እንደአጋጣሚ ሆኖ ሌላ አንድ የሚያውቀው ልጅ ሰላም ብሎት አብሮት ትንሽ መንገድ ይጋዛል፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በሗላ ልጁ ወደ ስራ ቦታው ሄደና ገና ስራ ከመጀመሩ በፊት ለካስ መረጃ ተላልፎ ቆይቷል በአስቸካይ አስተዳደር ጋር ይጠራል እና ይገባል፡፡ ሃላፊውም “ከመቼ ጀምረህ ነው የአረና ትግራይ አባል የሆንከው?” ብሎ ድንገተኛ ጥያቄ ይጠይቀዋል፡፡ “የማናውቅ እንዳይመስልህ እውነቱን አውጣ” ብሎ ያስፈራራዋል፡፡ ልጁም በድንጋጤ የአረና አባል እንዳልሆነ ቢገልፅለትም ሃላፊው በፍፁም ሊቀበለው አልቻለም፡፡ እናም ከዛ በሗላ ከባድ ማስጠንቀቅያ ተሰጥቶት ወደ ስራው ተመልሷል፡፡

የልጁ አባትም አብረውት በዚሁ መስሪያ ቤት ውስጥ በዘበኝነት ተቀጥረው ይሰራሉ፡፡ አባትየውም በተመሳሳይ ተጠርተው ልጃቸው ዓረና እንደሆነ እና ስራቸው አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ተነግረዋቸው እሳቸውም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶዋቸው ወደ ስራቸው ይመለሳሉ፡፡ ሁለቱም ማታ በቤት ከተገናኙ በሗላ አባትየው ልጃቸውን ቁጭ አድርገው የዓረና አባል መሆኑን እና አለመሆኑን ሲጠይቁትና ሲመረምሩት አመሹ፡፡ እሱም እንዳልሆነ ገለፀላቸው፡፡ በመጨረሻ አባትየው “በል ስማ ከዚህ በሗላ የአረና ትግራይ አባል ሁነህ ካገኘሁህ ግን ሰው ያላደረገውን ባንተ ላይ አደርጋለሁ” አሉት፡፡  ልጁም ገርሞት “ምን ታደርጋለህ አባዬ” ብሎ ሲጠይቃቸው እገድልሃለሁ አሉት በገዛ ልጃቸው፡፡ ይህን ቃል የነገረኝ ራሱ ልጁ ከጋደኞቹ ፊት ቁጭ ብለን ስናወራ ነው፡፡  ልጁ አሁን በአዲስ አበባ ከተማ በደህና ቦታ ተቀጥሮ እየሰራ የሚገኝ የመንግስት ሰራተኛ ነው፡፡ አሁን ልጁ ለስርዓቱ ያለውን ታማኝነት ለመግለፅና እንዲሁም ከአባቱ ጋር ተግባብቶ ለመኖር ሲል በማያምንበት ጉዳይ በየቀኑ ህወሓትን ደግፎ በየፌስቡኩ ሲሳደብ ይውላል፡፡

አብርሃ ደስታ

ለረጅም ጊዜ በቅርብ ርቀት ሲከታተሉት ከቆዩ በሗላ የመንግስት ጣት ተቀስሮባቸው የስርዓቱን የአፈና ሰለባ ከሆኑት ሰላማዊ ታጋዮች አንዱ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፓለቲካ ሳይንስ መምህር የሆነው ወጣት አብራሃ ደስታ ነው፡፡ ከመታሰሩ ጥቂት ቀናት በፊት በስልክና በአካል በመቐለ ከተማ ተገናኝተን አብረን ቁጭ ብለን በሰፊው እንድናወራ እና ይበልጥ ማንነቱን እንዳውቀው እድል አግኝቼ ነበር፡፡ አብራሃ በፅሁፍ እና በአካል ስታየው በጣም ይለያያል፡፡ ከምጠን በላይ ትሁት” ሕግና ስነ ስርዓት አክባሪ ሰው ነው፡፡ ረጋ ብሎ የመናገር እና የማስረዳት ችሎታው ከፍተኛ ነው፡፡ ተግባቢ ነው፡፡ አድማጭ ነው፡፡ በፍፁም አይጠጣም አያጤስም፡፡ ለስላሳ ይደግማል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ማሕበረሰብ ዘንድም በስራ ችሎታቸውና በሞያ ብቃታቸው ከሚደነቁትና ከሚከበሩት ሰዎች አንዱ ነው፡፡

አብርሃ ደስታ ለሰላማዊና ሕጋዊ ዴሞክራሲያዊ ትግል ያለው ፅናትና እምነት በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባርም በሄደበት ሁሉ በህዝባዊ ስብሰባም ሆነ በግል ሲወያይ በሰላም ታግሎ እንዴት ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ሲያስተምር ቆይቷል፡፡ በስብሰባ በህዝብ ፊት ቀርቦ የማሳመን ችሎታውም ከሞያው ብቃት ተዳምሮ ዘመን የፈጠረው ታጋይ እየተባለ በብዙዎቹ ዘንደ ይነገርለታል፡፡ ብቃቱንና ፅናቱን የቀድሞ የአረና ትግራይ አመራር የነበረው እና በሀገራዊ ምርጫ ዋዜማ ባልታወቀና በረቀቀ ሁኔታ በጭካኔ የተገደለው የወጣቱ ታጋይ አረጋዊ ገብረዮሐንስ ወኔ ወራሽ ነው እየተባለ ይነገርለታል፡፡

አብርሃ ደስታ ህወሓትን በሃሳብ እንደተሸነፈና ከመሳደብ” ከማሸበርና በጉልበት ከማሰር በስተቀር በህዝብ ፊት በአደባባይ ቆሞ በሀገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ በግልፅ ለመወያየት የሞራል መሰረትና ብቃት የሌለው የበሰበሰ ድርጅት መሆኑን በግልፅ ይናገር ነበር፡፡ይህም ህወሓቶች የተለየ ሃሳብ ይዞ በግልፅ መወያየት ያልለመዱት የፓለቲካ ባህል ስለሆነ እንደድፍረት በመቁጠር ጥርስ ተነክሶበት ከቆየ በሗላ እንደተለመደው አብርሃ ደስታን የሚያጠምዱበት ቀንና አጋጣሚ ሲከታተሉና ሲጠብቁ ከርሟል፡፡

በመጨረሻም ከትግል አጋሮቹ ጋር ቁጭ ብለን እያወራን እያለ ስለ የስርአቱን ምንነት” ያለው ክፋትና አፈና ከባህሪያቸው ጋር አያይዞ ብዙ ዝርዝር ነገሮች አወሳልን፡፡ ስለራሱ የግል ጉዳይም በማንሳት ከአንድ የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ጋር የዶክትሬት ፕሮገራም ይከታተል እንደነበረ እና በማያውቀው ሁኔታ ስለተቋረጠ ወደ ሚመለከተው አካል ሄዶ መማር እንዳልቻለ ነገረን፡፡  ለምን እንደተቋረጠ ቢጠይቅም ባለስልጣኑ በፌዝ “አንተ ስለ ትምህርት ታወራለህ፡፡ ያንተ መማር ይቅርና ሌሎቹ ካንተ ጋር ሰላምታ የሚለዋወጡ ሰዎችም ጭምር አደጋ ላይ ናቸው፡፡” ብሎ እንደ መለሰለት ነገረን፡፡ ከዚያቺ ደቂቃ ጀምሮ አብርሃ እንደሚያስሩት አስቀድሞ ያውቅ ነበርና ቁጭ ብለን በጋራ ስናወራ የአብርሃ ደስታን ፓለቲካዊ ብስለት ከሚናገራቸው ቃላት በላይ ከፊቱ የሚነበበው ልበ ሙሉነት” የአላማ ፅናትና ድፍረት ይታይበት ነበር፡፡ እንደሚያስሩት እያወቀ ምንም የፍርሃት መንፈስ ወይም ስጋት አይታይበትም፡፡ እኔም ገረመኝ፡፡ ለማመንም ከብዶኝ ነበር፡፡

አዎ!! በኔ እምነት በማስረጃ ላይ የተደገፈ ነገር ካለ አንድ ሰው ሕግ ፊት መቅረብ የለበትም የሚል ጭፍን እምነት የለኝም፡፡ ነገር ግን ዜጎች የተለየ እምነት ስለያዙ ብቻ ለአንድ ድርጅት የፓለቲካ ጠቀሜታ ተብሎ (politicaly motivated) ወይም በቂም በቀል (Revenge) ተነሳስቶ በሰላማዊያን ዜጎች ላይ የሚፈፀም የስም ማጥፋትና የክስ ሂደት ድራማ ግን ሕገ ወጥ ድርጊት ብቻ ሳይሆን በኢትዮያዊነታችን የርህራሄ ባህላችንም አኳያ ሲታይ ኢሰብኣዊነት” ከሃላፊነትና ከስነ ምግባር ውጭ ስለሆነ አልደግፈውም ብቻ ሳይሆን መወገዝ ያለበት ነው፡፡

በዚሁ መለኪያ በአብርሃ ደስታ ላይ የተፈፀመ እንግልትና እስር ሲታይ ከነ ብርቱኳን ሜደክሳ እና ሌሎች በቃሊቲና በማእከላዊ እስር ቤቶች ታጉረው ከሚገኙ የህሊና እስረኞች የሆኑት ወጣት ፓለቲከኞች ወንድሞቻችን ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ የክሱ ቀደም ተከተልና አካሄድ ስናየው ሕጋዊ መሰረትና እውነትነት የሌለው መሆኑን የሚያሳየው መጀመሪያ እንደ እንስሳ በጉልበት መደብደብ” ከዚያ በሗላ ማሰር” ከተደበደቡና ከታሰሩ በሗላም ከዳኝነት በፊት ከሰብኣዊ አያያዝ ውጭ ለፐሮፓጋንዳ ጠቀሜታ ሲባል በቪድዮ እየቀረፁ ለፓብሊክ ማጋላጥ፡፡  ከዚያም ቀጥሎ ለይስሙላ ማስረጃ ፍለጋ መሄድ ሲሆን የመጨረሻ ዕድላቸው ደግሞ በወህኒ ቤት እንዲበሰብሱ ወይም የይቅርታ ወረቀት እንዲፈርሙ በማድረግ የትግል ወኔያቸው አኰላሽቶ መልቀቅ ነው ፡፡ ይህ የዜጎች ሰብኣዊ ክብርና ሕገ መንግስታዊ መብት የሚዳፈርና የሚፃረር” ከአንድ መንግስት ነኝ ከሚል አካል የማይጠበቅ ሕገ ወጥ ተግባር ከመሆኑም በላይ ኢትዮ}ያ የፈረመችባቸው ዓለም አቀፍ የሰብኣዊ ፍጡርና የሕግ እስረኞች አያያዝ ሕግጋትም የሚጥስ ነው፡፡

 

አብርሃ ለምሳሌ ያህል ጠቀስኩት እንጂ በሌሎች ክፍላተ ሀገር በወጣት ታጋይ ወንድሞቻችን ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃም አላማው ተመሳሳይ ነው፡፡ በኢትዮ}ያ በሀገር ደረጃ የትግል አንድነት እየተፈጠረ ከሄደና ወጣት ምሁራን ወደ ትግሉ እየተቀላቀሉና የፓለቲካ አመራሩን እየተኩ ከሄዱ ለህወሓት/ኢሕአዴግ ትልቅ ስጋትና የፓለቲካ ኪሳራ ነው ከሚል ስሌት የመነጨ የፍርሃት እርምጃ መሆኑን ያዳባባይ ሚስጢር ነው፡፡

የሚገርመው ግን ህወሓቶችና ኢሕአዴጎች በወገን ላይ አፈናና ግፍ መፈፀማቸው ብቻ አይደለም፡፡  ነገር ግን አምባ ገነኖች የህዝብ እሮሮና ብሶት የዶሮን ያህል ግምት ሳይሰጡ በሰራዊት ጉልበት” በጦር መሳሪያ ጋጋታና ክምር ተማምነው ግለሰቦችንና ታጋዮችን ባሰሩና ጭቆናውን እያከረሩ በሄዱ ቁጥር የህዝቡን ልብ የበለጠ እንዲሸፍትና ሽዎች ታጋዮች እንዲፈልቁ ያደርጋል እንጂ ትግሉን ማዳፈን እንደማይቻል ካለፈው ታሪክ ሳይማሩ አሁንም ተመሳሳይ ድራማ መስራታቸውን ነው፡፡ እንዲህ ከቀጠለ ደግሞ ወደዱም ጠሉም ዕድሜያቸውንም በዚያው መጠን እያጠረ መሄዱ የማይቀር ተፈጥራዊ ሂደት መሆኑንም በውል ሳይገነዘቡ መቅረታቸው ነው የሚያሳዝነው፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን የመልካም አስተዳደር እጦት መንሲኤያቸው ሁሉም ከአንድ ወንዝ የሚቀዱ ናቸው፡፡ ይህ ማለት በሀገሪቱ ውስጥ ካለው ጠባብ የፓለቲካ ምሕዳር የሚመነጩ ናቸው ማለት ነው፡፡ የህወሓት/ኢሕአዴግ ስርዓት የህዝቡን መሰረታዊ ችግሮች ሊፈታ የማይችል” ዴሞክራሲያዊ ባህርይ የሌለው” መሰረቱን የተናደና የተፋለሰ ፓሊሲ የሚከተል በመሆኑ ብቻ የሚመነጩ ችግሮች ናቸው፡፡ መፍትሔውም የግለ ሰዎች መቀያየር ሳይሆን መሰረታዊ የአስተሳሰብ” የፓሊሲና የስርዓት ለውጥ ያስፈልገዋል ብዬ በፅኑ አምናለሁ፡፡ በኔ እምነት ማን ስልጣን ላይ ወጣ አይደለም ችግሬ፡፡  ዋናው ቁም ነገሩ ማን ምን ዓይነት ለህዝብ የሚጠቅም የፓለሲ ለውጥ ይዞ መጣ ነው መመዘኛዬ፡፡

ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ

ከላይ በመጠኑም ቢሆን የጠቀሱኳቸው ነጥቦች ብዙዎቻችሁ እንደምትጋሩ እምነቴ ነው፡፡ በተለይም እኔም ባልሳተፍኩበት በዚሁ ዓመት አጋማሽ ላይ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ያዘጋጀውን ፌስቲቫል ለመካፈል ከዲያስፓራ ወደ ትግራይ ክልል ሂዳችሁ በነበረበት ጊዜ ባለስልጣናቱ የህዝብ አዛኝ መስለው ለመታየት ሲሉ ቃጤማ አንጥፈው ለመቀበል ሙከራ ቢያደርጉም የህዝቡን እሮሮና መከራ ግን ለመሸፈን ስላልቻሉ በሕብረተሰቡ ውስጥ ማለት በመሬት ላይ ያለውን እውነታ ተገንዝባችሁ በየስብሰባውና በተናጠል ሲቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎች የብዙዎቻችን ጥያቄ መሆናቸውን እገነዘባለሁ፡፡ በተጨማሪም ሰሞኑን በዓይጋ ድህረ ገፅ ላይ አባይ ወልዱ ሙሱናን በሚመለከት ሁለት ሽሕ ለሚሆኑ ካድሬዎች ሰብስቦ ያቀረበውን ካንገት በላይ ንግግር አስመልክቶ ህዝቡ የሚሰማውን ሃሳቡ እንዲሰጥ ተብሎ በተከፈተው የአስተያየት አምድ ላይ ከተሰጡት በመቶ የሚቆጠሩ አስተያየቶች ውስጥ አብዛኞቹ ቀደም ብዬ በክፍል አንድ ያቀረብኩትን ፅሑፍ በበለጠ የሚያጠናኩሩልኝ ሆነው በማየቴ ትእዝብታችን ብቻ ሳይሆን ብሶታችንም አንድ ዓይነት መሆኑን ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ የተሰጡ አስተያየቶችም በህዝባችን ላይ የተጫነው ሸክምና የተጋረጠው ቁስል በብዙዎቻችን ሆድና አእምሮ ውስጥ የታመቀ ብሶት ገንፍሎ እንደወጣ የሚያሳይ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ የጊዜ ጉዳይ እንጂ በልቡ የሸፈተ ህዝብ እንዳለ ቁልጭ አድርጎ የሚያመላክት ነው፡፡

አዎ!! የቀረቡት ወርቃማ አስተያየቶች” ጥያቄዎችና የለውጥ ፍላጎቶች ሁሉ ትልቅ ትርጉም ያላቸው ቢሆኑም ውጤት የሚኖረው በአግባቡ ተገንዝቦና አጢኖ መልስ ለመስጠት የሚችል የሚሰማ ጆሮ” ከጊዜው ጋር የሚመጥን አእምሮ” የህዝብንና የሀገርን ጉዳይ የሚያስቀድም ዴሞክራሲያዊ ተፈጥሮ ሲኖር ብቻ መሆኑን የግድ ይላል፡፡ ይህ ባለቤት ያጣ ሚስኪን ህዝባችን ከአፈና” ከፍርሃት” ከፍልሰትና ከውርደት ተላቆ የነፃነት አየር የሚተነፍስበት ስርዓት እንዲፈጠር ሁላችንም የሃሳብ ልዩነታቸንና ሕብረ ቀለማችንን እንደ ውበትና ፀጋ ተቀብለን በሚያገናኙን ጉዳዮች ዙሪያ ለጋራ ችግር በጋራ ለመፍታት ተባብረን መቆምና መጮኽ እንዳለብን ጊዜውም ራሱ እየተናገረ ነው፡፡

ቸር ይግጠመን

የዛሬው ፅሑፌ በዚሁ ይጠቃለላል፡፡ በሚቀጥለው የመጨረሻው ክፍል 3 ፅሑፌ የአቶ መለስ ዜናዊ አምልኮ በሕብረተሰቡ ዘንድ እየፈጠረ ያለው የስነ ልቦና ጫናና ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮችን በማካተት ይቀርባል፡፡

 

sgbtsait@gmail.com

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>