የሐራ ተዋሕዶ ዘገባ፦
ፓትርያርኩ የማኅበራት ገንዘብ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ገቢ ኾኖ በማእከል ካልተመራ በሚል ከማኅበራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጋራ የሚቃረን ግትር አቋም ይዘው ውለዋል፡፡
አቋማቸው ተቀባይነት ካላገኘ ስብሰባውን ለመምራት እንደሚቸገሩ በመግለጽ ምልአተ ጉባኤን ለማስገደድ ያደረጉት ሙከራ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ጽኑ አቋም ሳቢያ አልተሳካላቸውም፡፡
ጉዳዩ ‹‹ከአዲስ አበባ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ጋራ ብዙ የሠራኹበትና የደከምኩበት ነው፤ በቀላሉ የምተወው አይደለም›› በሚል ከአክራሪነት ጋራ የተገናኘ ጽሑፍ ሲያነቡ ውለዋል፡፡
ከተጀመረ ስድስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ በዛሬ፣ ጥቅምት ፲፯ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ሙሉ ቀን ውሎው፣ የ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. ሕገ ቤተ ክርስቲያን ለማሻሻል በቀረበውና የልዩነት አቋም በተያዘባቸው የረቂቁ አንቀጾች ላይ ጠንካራ ውይይት ሲያደርግ አምሽቷል፡፡
የማሻሻያ ረቂቁ፣ ባለፈው ዓመት ግንቦት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ኹለተኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብስባ ወቅት አንቀጽ በአንቀጽ ከተወያየበት በኋላ ተጨማሪ እርማትና ማስተካከያ አድርጎ ለአኹኑ ምልአተ ጉባኤ እንዲያደርስ የሠየመው ስድስት አባላት ያሉት የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሊቃውንትና የምሁራን ኮሚቴ ያቀረበው ነው፡፡
የማሻሻያ ረቂቁንና በኮሚቴው አባላት መካከል የልዩነት አቋም የተያዘበትን ቃለ ጉባኤ ባለፈው ቅዳሜ ከቀትር በፊት ውሎው የተናበበው ምልአተ ጉባኤው፣ ለዛሬ በቀጠረው መሠረት ነው ፍጥጫ የተቀላቀለበት ውይይት ሲያደርግ የዋለው፡፡
የልዩነት አቋሞች የተያዘባቸው ነጥቦች፡-
የሊቃነ ጳጳሳትን ተጠሪነት(ዝውውር እና ምደባ)
የማኅበራትን ተጠሪነትና የገንዘብ እንቅሰቃሴ ማእከላዊነት
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አመራር የተመለከቱት ይገኙበታል፡፡
ከስድስት የኮሚቴው አባላት መካከል በሦስቱም ነጥቦች ላይ የልዩነት አቋማቸውን በቃለ ጉባኤው ያስመዘገቡት የፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ናቸው፡፡ ልዩ ጸሐፊው ከአምስቱ የኮሚቴው አባላት ተለይተው በያዙት አቋም÷ የሊቃነ ጳጳሳቱንና የማኅበራትን ተጠሪነትን ለቅዱስ ሲኖዶስ የሚያደርጉት የረቂቁ አንቀጾች ለፓትርያርኩ ይኹን በሚል እንዲተኩ፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት እንደኾነ የሚገልጽ በረቂቁ ያልነበረ አንቀጽ በግልጽ እንዲቀመጥ ተከራክረዋል፡፡