Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

መነገር ያለበት ቁጥር 7 የክፍፍላችን ገጽታ

$
0
0

በልጅግ ዓሊ

ባለፈው ዓመት ሃገራችንንም በሚመለከት አስደሳችም፣ አስከፊም፣ አስደናቂም፣ አናዳጅም ተግባሮች ተፈፅመዋል። አሮጌው ዓመት ለአዲሱ ዓመት ቦታውን ሲለቅ ፈጣሪ አምላክ አዲሱ ዓመት የሠላም፣ የፍቅር፣ የመግባቢያና ችግሮቻችንን ሁሉ የምንፈታበት ዓመት ይሁን ማለታችን አልቀረም። ግን የዚህ ምኞታችን ፍፃሜ ከቅርብነቱ ሩቅነቱ በክፍፍላችን ምክንያት የጎላ ነው። አንዳንዶቹ ቅራኔዎቻችንን መፍትሔ ለማግኘት ስናጠናቸው የችግሩን መንስዔ ለማግኘት እንኳን የተጠላለፉ በመሆናቸው በጣም የሚያስቸግሩ መሆናቸውን እንረዳለን። በትልቁ ፆም አጋማሽ ዕለት ጀርመን ፍራንክፈርት ላይ የተመለከትኩት ሁኔታ በእኔ ዘንድ በዓመቱ ከታዘብኩት ክስተቶች ውስጥ ከፍተኛውን ቦታ ይዟል። ይህ የክፍፍላችን አንዱ ገጽታ ነው።

ደብረ ዘይት . . . ግማሽ ፆም

ይህ የተፈጸመው የግማሽ ፆም ዕለት ነው። የዐብይ ጾም አጋማሽ። ዘወትር በዕለተ እሁድ የምናስቀድስባቸው ቤተ ክርስቲያኖች ፍራንክፈርት አካባቢ ይገኛሉ። ወደ ቤተ ክርስቲያኖቹ ለመሄድ ከየቦታው በባቡር የመጣው ሕዝብ ፍራንክፈርት ባቡር ጣቢያ በተመሳሳይ ሰዓት ይገናኛል። ከዚያም ሁሉም በአንድነት ከባቡር ጣቢያው ፊት ለፊት ከሚገኘው የከተማ ውስጥ የመንገድ ባቡሮችን(ትራም ወይም በጀርመን ስታራሰን ባን) ለመሳፈር እንሰባሰባለን። የተለመደው የዜጎቻችንን የፍቅር ሰላምታ ይቀጥላል።

ደህና ነሽ ፣ ደህና ነህ ? . . . ምነው ጠፋሽ ? ምነው ጠፋህ ? ትከሻ ለትከሻ መጋጨት . . . አምሮብኻል ምን ተገኘ ? . . . አምሮብሻል ? . . . እንዴ ልጅሽ አደገ አይደለም እንዴ? . . . ጎረመሰ እኮ ? . . . ትልቋ ልጅሽ? አልመጣችም እንዴ ? እንቅልፍ ይዞት አልመጣ አለች . . . የዘንድሮ ልጆች መች እሺ ይላሉ . . . ሥራ እንዴት ነው? ሃገርቤት ሄደህ ነበር እንዴ ? . . አዎ ሰሞኑን ነው የተመለስኩት . . እንዴት ፋሲካን ሳትውል? . . . ፍቃድ አልነበረኝም ፣ ቶሎ ተመለስኩ ። ሃገር ቤት እንዴት ነው?. . . ፆም ሃገር ቤት ነው እንጂ ፣ በዚያ ዓይነት ልዩ ልዩ የፆም ወጥ እየተፆመ፣ ፆም አይባልም.። እንደሱ ከሆነ ዘላለም በፆምኩ . . . ባክሽ አትስጎምዢኝ . . . ሰላም ነው ? . . ሰላም ነው ። .

ባቡሩን የምንጠብቅባት ትንሽ ደቂቃ ነች።“ፍቅር“ በጣም የበዛባት ትመስላለች። አንዱ ሌላውን አቋርጦ ሰላም ይላል፣ ጥድፊያም አለ፣ አንጠፋፋ እንገናኛ . . . የውሸት ቀጠሮም ብዙ ነው። ስልክ ቁጥር ሳይሰጣጡ እንደዋወል መባባሉም አለ. . . ። አንዳንዱ የድሮ ጓደኝነትን በማሰብ መፎጋገር ይመስላል። መቼን ያልጨመረው እንገናኛ የሚለው ቀጠሮ ለመገናኘትን ያለመፈለግን ያሳብቃል።

በዛች ትንሽ ደቂቃ ሁሉም ለሁሉም “ፍቅሩን“ ያሳያል። በአሁኑ ወቅት ዜጎቻችን ሳይነጣጠሉ በአንድነት የሚገናኙበት ቦታ ይህቺ ባቡር ጣቢያ ብቻ ትመስላለች ። ምንአልባት ከለቅሶ በስተቀር። ያውም አስከሬን ከቤት ከወጣ። ሠርግ እንኳን እንደ ድሮው አይደለም። የተወሰኑ የሚስማሙ ብቻ ናቸው የሚጠራሩት። ጎረቤት ስለሆንኩ ሠርግ እጠራለሁ ማለት አይቻልም። ለምሳሌ የወያኔ ተቃዋሚ ከሆንክና የኤምባሲ ሰዎች ከተጠሩ የመጋበዝህ ጉዳይ የመነመነ ነው። የወያኔ የዘር ፖለቲካ የሠርግ ግብዣ ላይ ብዙ ችግር ፈጥሯል። ለስደተኛነት የሰጠኸውን ምክንያትም ለሠርግ ጋባዥነትም ሆነ ተጋባዥነት ምክንያት ሊሆን ይችላል። ልደት፣ ክርስትና ሌሎችም ድግሶች ለዜጎቻችን መገናኛነታቸው ካከተመ ሰንብቷል። ለምሳሌ የዲያስፖራ “ኢንቬስተር“ መሰሉን ነው የሚፈልገው። “ከኢንቬስተርነቱ“ በፊት የነበሩትን ጓደኞቹን የረሳ ብዙ ነው።

የባቡር መምጣት የመለያየቱን ጊዜ እንደ ደረሰ አበሰረ። የሰላምታው ጥድፊያ በባቡሩ መምጣት ተቋረጠ። መጀመሪያ የመጣው 16 ቁጥር ባቡር ነበረ ። የተወሰኑት ዜጎቻችን ወደ ባቡሩ ገቡ ። ያ ደስ የሚል አንድነት ተበጠበጠ። በዚህኛው ባቡር የተጓዙት ወደ ማርያም ቤተክርስቲያን የሚሄዱት ነበሩ ። የፍራንክፈርቱ ማርያም . . . ከአዲስ አበባው ሲኖዶስ ጋር የተያያዘ ሲሆን አብዛኛው ተሳፋሪ ምንም እንኳን ወያኔን የሚቃወሙ የማርያም ወዳጆች ቢገኙበትም በመንግሥት ደጋፊነት የሚጠረጡሩ ናቸው። የታየው “ፍቅር“ ግን አልጠናም። እነርሱ ከሄዱ በኋላ ሐሜት ተጀመረ. . . ። ቀሪዎቹ ባንድነት ሆነን ቀጠለን። ጭውውቱ እንደገና ጦፈ።
– ዛሬ ማሪያም አትሄጂም እንዴ? . . .
– አይ ዛሬ ገብርኤል ነው የምሄደው።
– አንቺሽ ? እኔ መድኃኔዓለም ነው እኮ ሁል ጊዜ የምሄደው።
– ምን ልዩነት አለው ሁሉም ጋር ከልብ መፀለዩ ነው።
– አለው እንጂ አሁን ማርያም የሄዱት አታይም እንዴ ?
– ብዙዎቹ እኮ ሃገርቤት ቤት የሠሩ ናቸው ይባላል። ካለ ማርያም ሌላ ቤተክርስቲያን ከሄዱ ቤታችን ይወረሳል ብለው ይፈራሉ።
– ማነው ደግሞ የሚወርሳቸው? ይህ መንግሥት ተደራጅተሽ አትቃወሚ እንጂ ምን እንዳያደርግሽ ?
– ብዙዎቹ የሰሜን ሰዎች አይደሉም እንዴ ወደ ማርያም የሚሄዱት?
– እሱማ የታወቀ ነው ።
– ቄሱ ከሰሜን ናቸው እኮ።
– ለመሆኑ አሁን ሰላም ነው እንዴ ማርያም?
– የሙኒኩ (የሙንሽኑ) ቄስ መስፍን 150 ሽህ ኤሮ ከቦደሰ በኋላ እኚህኛውን ማን ተናግሯቸው። ይባስ ብለው ይህንን ሁሉ ገንዘብ የሰረቀውን ቄስ ታቦት አሽከሙት አይደለም እንዴ ባለፈው ጊዜ?
– እኛ ምን አገባን ፈጣሪ አምላክ ሁሉንም የሚመለከት ይፍረድባቸው እንጂ . . . ። ፈራጅ አንድ ፈጣሪ ነው። በእሱ ሥራ ገብተን መፈትፈት የለብንም። እኔ እንደሆንኩ የማራያም ቀን ማርያም፣ የገብርኤል ዕለት ገብርኤል፣ የመድኃኔዓለም ቀን መድኃኔዓለም እሄዳለሁ።

የማርያምን ቤተክርስቲያን ጉድ ስንሰማ ቆየን ። ሌላ ባቡር ደግሞ መጣ። የሚቀጥለው 11 ቁጥር ባቡር ነበረ። የተወሰኑ ዜጎቻችንን ተሳፈሩ። አሁን ደግሞ ሃሜቱ ተቀየረ። የማሪያሙ ቀርቶ የገብርኤሉ ተጀመረ።

– ድሮ እኮ ከእኛ ጋር ነበሩ። ከመድኃኔዓለም ተገንጥለው እኮ ነው ገብርኤልን ያቋቋሙት።
– እኚህ ወጣቱ መነኩሴ ለራሳቸው ሲሉ ነው እኮ የከፋፈሉን፣ እንጂ ሕዝቡማ አንድ ነው።
– ልክ ነሽ ።ብዙዎቹ እኮ አሁንም መድኃኔዓለም ይመጣሉ።
– ለመሆኑ ለምንድነው የተከፈሉት ?
– ለነገሩማ ገብርኤሎች ከሁለቱም ሲኖዶስ አንሆንም ብለው ነው ይባላል። ገለልተኛ ነን ባይ ናቸው። ግን ሕዝቡ ነው እንጂ ገለልተኝነትን የፈለገ፣ ወጣቱ መነኩሴ እንኳን እንጃ።
– አንድ ቀንማ እንደባለቃለን። ሕዝቡ አንድ ዓይነት አመለካከት ነው ያለው።
– የረባ ሽማግሌ ጠፍቶ ነው እንጂ ሊታረቁ የሚችሉ ነበሩ። ምንም ልዩነት የለንም።
– እግዜር የፈቀደ ቀን ይሆናል። መቼም እንዲህ ሆነን አንቀር።

ይህንን ስንባባል የእኛም 17 ቁጥር መጣና ተሳፈርን እና ወደ መድኃኔዓለም ጉዞ ጀመርን። በሌሎቹ ባቡሮች ስለኛ ምን እንደተባለ ባልሰማም፤ መባሉ ግን እንደማይቀር መገመት ይቻላል። ያው ወያኔዎች እንዳስወሩት ፖለቲከኞች ናቸው መባሉ አይቀርም። ምክንያቱም ወያኔን በቆራጥነት የሚታገሉ በዚህ ቤተክርስቲያን በብዛት ይገኛሉና ነው።

ገና አንድ የባቡር ማቆሚያ እንደ ሄድን አንድ የኛ ዜጋ ንብረት ከሆነው ቡና ቤት ፊትለፊት ደረስን። ቁጥራቸው በዛ ያሉ ዜጎቻችንን ቡና ቤቱ አድረው ሲወጡ በቡጢ እንካ ቅመስ ይባባላሉ። ጠርሙስ ከአንዱ ወደ ሌላው ይወረወራል ። ከቡና ቤቱ ውስጥ የሚወጡ ወጣት ሴቶች ይታያሉ ። እነርሱን የከበቡ ወጣት ወንዶችም አሉ። ልቀቁኝ፣ ልቀቀኝ ግልግሉ ብዙ ነው። ጃኬቱን ጥሎ ለጠብ የሚከንፍም አለበት። ጫማዋን አውልቃ በእጇ የያዘች ሴትም ትታያለች። አካባቢው ድብልቅልቅ ብሏል። ባቡሩ መብራት ይዞት ቆመ። እኛም የሚያሳዝነውን ትዕይንት ማየት ቀጠልን።

የፖሊስ መኪና ጩኸት በሩቅ ሲሰማ ጎረምሳው ተበታተነ።

ባቡር ውስጥ ያለነው ተሳፋሪዎች ጨዋታ ተቀየረ ።
– ፍራንክፈርት በጣም ተበላሸ እኮ ።
– ድሮኮ አበሻ እንደዚህ ዓይነት አሳፋሪ ተግባር አያደረግም ነበር ።
– ቆይ ታያላችሁ አሁን የጀርመን መንግሥት መቀበል ያቆማል።
– እነዚህ እኮ በሰሃራ በኩል የመጡት ናቸው ። እዚያ ያዩት መከራ ጨካኝ አድርጓቸዋል እኮ!
– ጥሩ ኮሞኒቲ ቢኖረን እነዚህ ልጆች መምከር ያስፈልጋል።
– ኮሚኒቲው እማ የወያኔ ሰው ነው የሚመራው ይባል የለም እንዴ?
– እኛ ጥለን ስለሄድንለት ነዋ ? ደግሞም አሁንም ደህና ደህና ሰዎች ኮምኒቲው ውስጥ አሉበት እኮ። ለወያኔ ጥለን አንሄድም ብለው የሚታገሉ።
– ሊቀመንበሩ ከወያኔ ኤምባሲ አይወጣም ነው የሚባለው።
– የስደተኛው ኮሚኒቲ መሪ ከወያኔ ጋር ምን ይሰራል?
– እረ ዝም በይ፣ ሃገር ቤት ትሄጂ የለም እንዴ?
– ብሄድስ ለእሱ ብዬ ልፈራ ነው እንዴ? አፍሽን ዝጊ።
– በይ ተይው ጎመን በጤና አለ አሉ ፀሐዬ። አሁን ደግሞ እዚያ ውስጥ ማን ገብቶ ይጨቃጨቃል። እንደፈለጉ ያድርጉት ።
– ከእነዚህ ከሚረብሹት መሸሽ ነው። አሉ አንድ ሸምገል ያሉ አዛውንት። አገላለፃቸው እውጭ ሆነው ጠቡን ሊገላግሉ ቢገቡ ግፍትሪያው የፈሩ ይመስል።
– እነዚህ የሚደባደቡት እኮ ድራግ (ዕጽ)ሽያጭ ውስጥ አሉበት እኮ ።
– ውይ በሞትኩት አበሻ ድራግ ውስጥ ገባ እንዴ ? አበሻ አለቀላት ማለት ነው ። አለች አንዷ አፏን በማጣመም ፣ እንደ ማሽሟጠጥ።
– ቆይ ታያላችሁ! ጀርመኖች ቀላል አይደሉም እየለቀሙ ነው የሚያስወጧቸው ። አለ አንዱ ።
– እኔ መቼም እነዚህ የጀርመን መንግሥት ሊያስወጣቸው ነው ቢባል እንደ ሳውዲ ጊዜ ሰልፍ አልወጣም። እነዚያ እኮ ምስኪኖች ናቸው።

በዚህ በዚያ ስናማም ስንታማም መድኃኔዓለም ደርሰን ልባችንን ለእግዚአብሔር ሰጠን። ቅዳሴው ላይ ምንድነው እንዚህ ወጣቶች እንዲህ ጨካኝ ያደረጋቸው ብዬ አሰብኩ።

ለነገሩ ሱዳንን ፣ሰሃራ በርሃን ፣ ሜዲትራንያንን ፣ የመጡበትን ጀልባ ፣ ከመስመጥ እንዴት እደተረፉ ላየ ሰው እነዚህ ወጣቶች እንዲዚህ ዓይነት ሁኔታ ላይ ቢገኙ ላይፈርድ ይችላል። ግን ሁኔታው ደግሞ የተለየ ነው። ሮማ ኮለንቲናና አነኒና የሚባሉ ሕንጻዎች ውስጥ ስለሚነሳው ጠብ የነገረኝ አንድ ወንድም ታናሽ ብዬ የምጠራው በሳህራ አቆርጦ ጣሊያን የደረሰ ወጣት ነበር። ምንድነው ዜጎቻችንን እንዲህ ጨካኝ ያደረጋቸው? ብዬ ለጠየቅሁት እንዲህ ብሎ አጫወተኝ።

“ወንድም ታላቅ አትሳሳት እዚህ የሚቧቀሱት ምን ዓይነት ፈሪ እንደሆኑ ልንገርህ አልችልም። እኔ ሱዳንም ሊቢያም አውቃቸዋለሁ። አንተም ቱኒዚያ፣ ጣሊያንና ጀርመን አይተሃቸዋል። ለመሆኑ ቱኒዚያ ውስጥ ሲጣሉ አይተሃል? ምን ያህል ተለዋዋጭ እንደሆንን መናገር ይከብዳል። ፈሪዎች ነን። እዚህ እንደ ጀግና ስንጣለዝ የምታየን ሊቢያና ሱዳን፣ በተለይ ሰሃራ ውስጥ ምን ያህል ቦቅቧቃ እንደሆንን ታውቀዋለህ። አንድ ዐረብ ሊቢያዊ መንገድ ላይ ሲደበድበን ችለን ነው የምንመጣው። የሴት ጓደኛችንን ዓይናችን እያየ ሲነጥቁን ዝም ነው የምንለው። ናይጀሪያዊው፣ ሱማሌው፣ ሌላው አፍሪካ ለመብቱ ሲታገል እኛ ግን ያ ሁሉ በደል ሲደርስብን ዝም ነው የምንለው። የኛ ጀግንነት የሚጀምረው ጣሊያን ላምባዱሳ ላይ ነው። ሕግ መኖሩን ስናውቅ ሕግ ለመጣስ አንደኞች ነው። ድብድባችን ደግሞ የሚጀምረው እርስ በራሳችን ነው። የምናሳዝን ሰዎች ነን። ለመተባበር አልፈጠረንም፣ ለመከፋፋል እንቸኩላለን ። አለኝ።

ይህ ሲጽፉት የሚከብድ እውነት ነው። በዚህ ዓመት ከፍራንክፈርት ከተማ ውስጥ በዜጎቻችን በሃያ ዓመት ከተሰራው ወንጀል በላይ ተሰርቷል። በሆላንድ ፣ በቅርብ በሙኒክ እና በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች የጦፈ ድብድቦች ታይተዋል። በኢጣሊያን በስደተኞች መኖሪያ አካባቢ በየቀኑ ድብድብ ይታያል።

በተለይ በአስቸኳይ ሃብታም ለመሆን ወጣቶቹ ካደረባቸው ፍላጎት አንጻር ብዙ ብዙ ወንጀሎችን እየተፈጸሙ ነው። ይህ ከዕጽ ጋር የተያያዘ ወንጀል ወጣቶቹ ከሃገር ቤት ጀምሮ የተማሩት እንደሆነም ይነገራል። ስለ ትምህርት ያላቸው አመለካከት የደከመ ነው። ሠርቶ ራስን ማሳደግ በአንዳንዶቹ መሃል ጥያቄ ውስጥ አይገባም። ዛሬ ወያኔ ከፈጠረብን ትልቁ ችግር አንዱ ይህ ነው።

እነዚህ በጣም ጥቂት የሆኑ ጋጠ ወጥ ወጣቶች ሕግ አክባሪዎች ናቸው ተብሎ ለእኛ የተሰጠንን ጥሩ ስም እያጠፉት ነው። ይህ ደግሞ የሃገሩ መንግስት በእኛ ላይ እንዲጨክን ሊያደርግ ይችላል። በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ንፁሃን እንደሚጎዳ ግልጽ ነው። ችግሩ ንጹሁን ከመጥፎው ከመለየቱ በፊት ኢትዮጰያውያን እንዲህ አደረጉ መባሉ ብቻ በጀርመኑ ሕብረተሰብ መካከል ጥላቻን ይፈጥራል። እነዚህ ሕግን ጥሰው ሃገርን የሚያውኩ ከስደተኛው መሃል በጣም ትንሽ ናቸው።

ይህ ነገር እየገፋ መጥቶ በዜጎቻችን ላይ ጉዳት ሲደርስ መቼም ዝም ብለን ላናይ እንችላለን። ምክንያቱም ንጹሃንም አብረው ስለሚጎዱ። ግን የምንከራከረው ለማን ነው? በፖለቲካ ምክንያት መጥተው ዕጽ ለሚሸጡ? ጠግበው በስካር በቡጢ ለሚዣለጡ? ወደፊት ክፉ ዘመን ሲመጣ ሰላማዊ ሰልፍ ውጡ እንዳንባል ፍራቻዬ ነው። ለምንስ ነው ሰልፉ? እነዚህ አንባጓሮ ፍለጋ ከሃገር የተሰደዱ ጋጠ ወጦችን በመደገፍ። ደግሞ በዚሁ ማሀል ስንት ሐቀኞች ደግሞ ይጎዳሉ። ከአሁኑ መምከር ፣ ሕግን መጣስ አስፈላጊ እንዳልሆነ ማስረዳት ያስፈልጋል። ይህ ከመድረሱ በፊት ሁላችንም በየአካባቢያችን እነዚህ ወጣቶች መምከር ይኖርብናል። በተለይ ድጋፍ የሚጽፉ የፖለቲካ ድርጅቶች ለማን ድጋፍ እንደሚጽፉ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ችግራችን ነውና ዝም ብለን ማየት አይኖርብንም። የሚቀጥለው ዓመት የተሻለ ይሁንልን ብለን ስንመኝ የክፍፍላችንን ገጽታዎችን ወደ ውስጥ ተመልክተን ራሳችን መፍትሄ መሻት ያስፈልጋል።

ስለ አንድነታችን የሚያስቡ ሁሉ በሰላም ይክረሙ!

beljig.ali@gmail.com

በልጅግ ዓሊ ፣
ፍራንክፈርት ፣
መስከረም 2007


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>