Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በመጨረሻ… ለጋዜጠኛ ዳርዮስ ሞዲ ህክምና መቶ ሺህ ብር ተሰጠ!

$
0
0
ዳርዮስ-ሞዲ

ዳርዮስ-Sep 6,2014

ኢ.ኤም.ኤፍ) አንድ ትውልድ ወደኋላ ከተሻገርን ጋዜጠኛ ዳርዮስ ሞዲን የማያውቀው የለም። በተለይም እ.ኢ.አ ግንቦት 13 ቀን፣ 1983 ዓ.ም. የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዘዳንት፤ ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም አገር ለቀው ሲወጡ ዜናውን ያነበበው ጋዜጠኛ ዳርዮስ ሞዲ ነበር። በሳምንቱ ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ… የጠመንጃ አፈ ሙዝ ግዳጅ ተጨምሮበትም ቢሆን ዜናዎች ያነብ እንደነበር ብዙዎች ያስታውሳሉ። ይህ እውቅ ጋዜጠኛ በህመም ላይ መሆኑ ከተነገረ ሰነበተ። ሆኖም የሰራበት ማስታወቂያ ሚንስትር መስሪያ ቤትም ሆነ ሌሎች በተፈለገው አቅም ሊደርሱለት አልቻሉም።

ከጋዜጠኞች አለምነህ ዋሴ በግሉ ያደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ ሌሎች የነጻ ፕሬስ ውጤቶች የዳርዮስ ሞዲን ህይወት ለመታደግ የየራሳቸውን ድርሻ ሲያበረክቱ ቆይተዋል። ሆኖም የሚፈለገውን ያህል ገንዘብ አልተገኘም ነበር። ትላንት ምሽት ላይ የሰማነው ዜና ግን ከሌላው ግዜ የተለየ እና “እፎይ” የሚያስብል ነው። አንጋፋው የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት ለጋዜጠኛ ዳርዮስ ሞዲ ህክምና የአንድ መቶ ሺ ብር እርዳታ ሰጥቷል። (በነገርዎ ላይ መድን ድርጅት በሚጠናቀቀው የኢትዮጵያ አመት፤ ለደንበኞቹ የ3 ትሪሊዮን የኢትዮጵያ ብር የመድህን ዋስትና ሸጧል። ይህም በታሪክ የመጀመሪያው ከፍተኛ ገንዘብ ነው።)

የጋዜጠኛ ዳርዮስ ሞዲ የቅርብ ሰዎች እንዳሉት ከሆነ፤ ይህ ገንዘብ ቀሪውን ህክምና እንዲያደርግ የሚረዳው ነው። መድህን ድርጅት እናመሰግናለን… ብለዋል። ጋዜጠኛ ዳርዮስ ሞዲም ምስጋና ያቀረበ መሆኑ ተያይዞ ተገልጿል። እንግዲህ ይንን መልካም ዜና ይዘን፤ ባለፈው ወር አዲስ ጉዳይ መጽሄት ሃምሌ 26/2006፤ በጋዜጠኛ እንዳለ ተሺ አማካኝነት ከዳርዮስ ሞዲ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ልንጋብዛቹህ ወደድን። እንዲያው ጋዜጠኛ ዳርዮስ ሞዲን እንድናስታውሰው ያህል ነው ቃለ ምልልሱን ያቀረብንላቹህ።

በጋዜጠኝነት ከ30 አመታት በላይ በብስራተ ወንጌልና በኢትዮጲያ ሬዲዮ ሰርቷል። በወቅቱ የነበሩ የሬዲዮ አድማጮች በተለየ የዜና አቀራረቡና ድምጹ ይለዩታል። በሰራባቸው አመታት ተደብድቧል፥ ታስሯል ከስራ መታገድ ሁሉ ደርሶበታል። ግና ይህን ሁሉ መስዋእትነት የከፈለበት ተቋም ዛሬ ላይ የአልጋ ቁራኛ በሆነበት ሁኔታ ከጎኑ ሊቆም አልወደደም፥ የጋዜጠኛውንም ችግር ለህዝብ ማሳወቅ የፈለገ አይመስልም፡፡ ይህ ሰው በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የልብ ህመም እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ ጋዜጠኛ ዳርዮስ ሞዲ ነው፡፡ ከዚህ የዘመን ባለውለታ ከሆነው ጋዜጠኛ ዳርዮስ ሞዲ ጋር በተክለሃይማኖት ጠቅላላ ሆስፒታል ለአንድ ሰአት ያህል ቆይተናል። ጋዜጠኛ ዳርዮስ ሞዲም ከህመሙ ጋር እየታገለ ቅን አንደበቱን አልነፈገንም፡፡ እነሆ ቆይታውን፡-


– ህመሙ የጀመረህ መቼ ነው?
* በአጠቃላይ አንድ አመት ከሶስት ወራት ተቆጥሯል።
– በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ የት የት ህክምናህን ተከታተልክ?
* በመጀመሪያ በጳውሎስ ሆስፒታል ለአንድ ወር ያህል ታከምኩ። እንደገና በሽታው ሲያገረሽብኝ በአንድ የግል ሆስፒታል ተመላልሼ ከታከምኩኝ በኋላ ተሽሎኝ ለተወሰነ ጊዜ እንቅስቃሴ ሳደርግ፥ እንደገና አገርሽቶብኝ የካቲት 12 ሆስፒታል ህክምና ለማግኘት ስሄድ፥ አገልግሎት ሊሰጡኝ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ሲቀር ቀጥታ አሁን ወዳለሁበት ሆስፒታል አርብ ሐምሌ 18 ቀን 2006 አ.ም ሕክምናዬን መከታተል ጀመርኩ።
– ለአንድ አመት ከሶስት ወር ያህል ስትታመም ከጎንህ ማን ነበር?
* ቤተሰቦቼ፥ የሚያውቁኝ ሰዎችና ጓደኞቼ አብረውኝ ናቸው።
– የእድሜህን ግማሽ ያህል የሰራኸው ማስታወቂያ ሚኒስቴር ይመስለኛል፡ ይህ ድርጅት በአሁን ሰአት በአንድ የአለም ዋንጫ እስከ 30ሚልየን ብር ገቢ እያስገባ፥ አንተን ለመርዳት ወይም ያለብህን ችግር ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ ያልፈለገው ለምን ይመስልሃል?
* በጣም አስቸጋሪ ጥያቄ ነው። እንኳን መርዳት መኖሬን የሚያውቁ አይመስለኝም። እባክህ በዚህ ዙሪያ የምታነሳው ጥያቄ ካለ ቢበቃ ይሻላል።
– አንድ ሰው አቅሙ እስከፈቀደ ድረስ አንድን ተቋም አገልግሎ፥ አሁን አንተ እንደደረሰብህ አይነት ሕመም ሲገጥመው ያ ተቋም ከጎኑ ቆሞ አለሁልህ ካላለው፥ ሌላውን በዚህ ስራ ውስጥ እንዲያልፍ ለመምከር ያበረታታል?
* ይሄም ሌላኛው አስቸጋሪ ጥያቄ ነው። አንዳንዶች ለተወሰነ ጊዜ በጋዜጠኝነት ሙያ ያገለግሉና ቀንቷቸው የስኬትን ቁልፍ የሚጨብጡ አሉ። እንደ እኔ አይነቱ ደግሞ ሌሎች መውጫ በሮችን መመልከት ባለመፈለግ ብቻ፥ ስጋውን የሚያስደስትበት ገንዘብ ሳያገኝ እድሜው ገፍቶ፥ በችግር ተጠልፎ የሚወድቅበትን ይመርጣል። ብቻ ዋናው ነገር እከሌ በዚህ ቢያልፍ ጥሩ ነው፥ አይደለም የሚለውን ሁሉም በግሉ ቢያየው እመርጣለሁ።
– ያንተ ስሜት ግን ምንድነው የሚነግረን?
* ይሄን ያህል አመት ለማስታወቂያ ሚኒስትር በማገልገሌ የተሰማኝ ነገር የለም። ቁጭትና ሐዘን የሚሰማኝ በግሌ ነው፡፡ ከእኔ ጋር ይሰሩ የነበሩ ሰዎች የት እንደደረሱና ምን እንደያዙ አውቃለሁ። ግን ለምን እዚህ ቦታ ደረሱ፥ ለምን ይሄን አገኙ ብዬ አልከፋም፥ እንደውም ደስ ይለኛል እንጂ። አንዳንዴ ደግሞ የራሴ ጥፋት እንደሆነ ተቀብያለሁ።
– ምንድነው ያንተ ጥፋት?
* ጥፋቱ አንድ መስመር ከያዝኩ አለቅም ማለቴ ነው። ቢሆንም የሚቆጨኝ አይደለም።
– ምን ያህል አመት በጋዜጠኝነት መያ አገለገልክ?
* ከ1964 አ.ም ጥቅምት ጀምሮ ጡረታ እስከወጣሁበት እስከ 1994 አ.ም የጋዜጠኝነት ስራን ሰርቻለሁ።
– ማስታወቂያ ሚኒስትር በመስራት ጥሩ ስም አግኝተሃል። ነገር ግን በሕይወቴ አሳጣኝ የምትለው ምንድነው?
* በጣም ግሩም ጥያቄ ነው። ተቋሙ ለኔ ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ከላይ እስከታች ላለ ሰራተኛ በሬዲዮም በዜና አገልግሎት ስም አግኝተናል። ያ ስምም ስለሚለጠፍብህ በውጭ ሰዎች እንደ ልዩ ነገር ትታያለህ፡፡ ይሄ ደግሞ አንተ ወደህ ወይም ጠይቀህ የምታመጣው ሳይሆን፥ ከስራው ባህሪ አንጻር ማንኛውም እዚያ ተቋም የሚሰራ ሰው የሚያገኘው ክብር ነው። ግለሰቡ ያን ቦታ ስለሚያውቀው “ለማያውቁሽ ታጠኚ” እንደሚባለው አይነት ነው። የውጪ ሰው ግን አንተ ሁሉ ነገር የተሟላልህና አንዳንዱ ደግሞ እንደመሪ ጓደኛ አድርጎ ይመለከትሃል፡፡ ስም ታገኛለህ ይሄ አይካድም። እርግጥ ጎረምሳ ሳለን ደስ ሊለን ይችል ይሆናል፡፡ እንዲህ ስትሆን ደግሞ ስም ባይኖር ይሻላል ማለት አይቀርም። ቅርብ ጊዜ ከአንድ ግለሰብ ጋር ዘመዴ ቤት ሄጄ፥ “አንተ ብዙ ሰዎች እያወቅህ ለምንድነው ስራ የማታስቀጥረኝ?” ብለውኛል፥ እኔ በውስጤ እንኳን ለሰው ለራሴም አልሆንኩ ብያለሁ።
– ከአንተ በኋላ የመጡ ጋዜጠኞች ሕይወታቸውን በተሻለ ለመምራት በማስታወቂያ ስራ ላይ ተሳትፈዋል። አንተ አሪፍ ድምጽ እያለህ ወደዚህኛው ሰፈር መምጣት ያልፈለከው ለምንድነው?
* በዚህ በኩል ወጣቱን ትውልድ አደንቃለሁ። ሙያውን ይቀስማል፥ ሙያውን ከቀሰመ በኋላ እዚያው ተጋግሮ ተለጥፎ አይቀርም። የራሱን የግል አማራጮች ይፈልጋል፡፡ እኔና የኔ ትውልድ አንድ ተቋም ውስጥ ከገባን በኋላ ወደሌላ መመልከት አይመቸንም ነበር። ማንም ነባር ጋዜጠኛ ብትጠይቅ እንደተጎዳ ፥ እንደተበደለና የሚፈልገውን አላማ ከግብ እንዳላደረሰ ያውቃል። ምክንያቱም የጋዜጠኝነት ስራን መልቀቅ ማለት የህይወት መጨረሻ መስሎ ስለሚታየው ነው፡ ይሄ በነባሩና በአሁን ጋዜጠኞች መካከል ያለው ልዩነት ነው። ማስታወቂያ ያልከኝ እንኳን ያኔ አሁንም መስራት አልፈልግም።
-ለምን?
*እኔ ለረዥም አመታት ዜና ነው ስሰራ የቆየሁት። ዜና ደግሞ በባህሪው ለእውነት የተጠጋ ነው። በዚህ ስራዬ ደግሞ ሶስት መንግስታት ተመልክቻለሁ፡፡ ወደድኩም ጠላሁም በሶስቱም የአገዛዝ ዘመናት የመሪዎቹን ስም የመጥራት እድል ነበረኝ። እንደ መንግስት ቅጥረኛ ጋዜጠኝነቴ ሳገለግል፥ ይሄ ክብርና ጥቅም አለ ተብዬ ሳይሆን ለሚከፈለኝ ደመወዝ፥ ይሄንን አገልግሎት ስጥ ተብዬ የተቀመጥኩ ሰው ነኝ። ስለዚህ እኔ ያንን እንደ ክብር አየዋለሁ። ታዲያ ያንን የሚሰራ ሰው ወርዶ ስለ ክብሪት፥ ስለ ሻማ… ማስታወቂያ መናገር፥ ለእኔ በጣም ስግብግብነትና ራስን ማውረድ ሆኖ ነው የሚሰማኝ።
– ግን እኮ ማስታወቂያ ራሱን የቻለ ሙያ አይደል እንዴ?
* ሙያ መሆኑንማ አልክድም። ጋዜጠኛ ሆኜ እውነቱን ስዘግብ የኖርኩ ሰውዬ የሌለ ነገር መቀባጠር አልፈልግም። በእርግጥ ገንዘብ ሊገኝበት ይችላል፥ ገንዘብ ማግኘት አልጠላም። ግን ገንዘብን በአግባቡና ክብር ባለው መንገድ እንጂ ራሴን አውርጄ አልመኘውም፥ ተመኝቼውም አላውቅም።
– ያንተን መርህ እንደ ሙያ ታማኝነት ማየት ይቻላል?
* ልታየው ትችላለህ።
– ይሄ እኮ የሚያሳየን ለሙያህ ምን ያህል ታማኝ እንደሆንክ ነው?
* በዚህ አልስማማም። ሌላው ደግሞ አጭበርባሪ ነው ሊል ይችላል። አስተያየቱ የአድማጭና የተመልካች ነው እንጂ እኔ ጥሩ ነኝ ብዬ ብናገር ላልሆን እችላለሁ። መጥፎ ነኝ ብል ተቃራኒ ምላሽ ሊገጥመኝ ይችላል።
– መዝናናት ታበዛ ነበር?
* በእርግጥ እስካለሁ በማገኘው ነገር ልደሰት የምል ሰው ነበርኩ። ለምን እከሌ ወደላይ ወጣ ብዬ የምቃጠል ሳልሆን ደስታ የሚሰማኝ ሰው ነኝ። ቅናትንም መንፈሳዊና ተፈጥሯዊ ብላችሁ ለሁለት ከፈላችሁት መሰለኝ!? ለእኔ ግን አንድ ናቸው።
– እንዴት አንድ ናቸው?
* ለእኔ ምንም የሚለያዩበት ነጥብ አላገኘሁባቸውም። ራስን ቆንጆ ለማድረግ ነው መንፈሳዊ ቅናት የሚባለው እንጂ እኔ አንተን ለምን አገኘ? ካልኩ በኋላ ከምቀኛ ውጪ ሌላ ቃል መጠቀም አልፈልግም።
– ጡረታ እስጀወጣህበት ድረስ ደመወዝህ ስንት ነበር? * ደመወዜ 1650 ብር ነበር። ጡረታ ስወጣ 760ብር አገኛለሁ።
– መቼስ በዚህ ገንዘብ የተሟላ ኑሮ እንደማትኖር ይታወቃል፡ ታዲያ ማነው የሚደግፍህ?
* አንዳንድ የሚያውቁኝ ግለሰቦች በሚችሉት መጠን ይረዱኛል። አሁን ለምሳሌ ተክለሃይማኖት አጠቃላይ ሆስፒታል በሰዎች ድጋፍና ጥያቄ ነው የገባሁት።
– በነጻ ሕክምና ማለት ነው?
* እንግዲህ ስፖንሰር እንደሚያደርጉኝ ነው የሰማሁት። ከዚያ ውጪ የማውቀው ነገር የለም።
– በ1978 አ.ም ዜና ስታነብ የፕሬዝዳንት መንግስቱ ሃይለማርያምን ስም በክብር ባለመጥራት የደረሰብህ ችግር እንደነበር ይነገራል እስቲ አጫውተኝ?
* በወቅቱ መንግስቱ ለጉብኝት ውጪ ይሄዳል። ዜና መሰራት ስለነበረበት ሰራነው። መጀመሪያ አርእስተ ዜናውን አነበብኩና ወደ ሃተታው ስገባ እውነቱን ለመናገር ነገሮች ሁሉ ተምታቱብኝ። ድንጋጤና ፍርሃቱ መጣብኝ። መጀመሪያ የፈለገ ነገር ይመጣል እንጄ አነባለሁ ብዬ ወስኜ የነበርኩ ሰው ማንበብ ስጀምር አንዴ ሻለቃ፥ አንዴ ኮሎኔል፥ ሌላ ጊዜ የደርግ ጸሃፊና መንግስቱ እያልኩ ያልቀባጠርኩት ነገር የለም። ይሄ ከሆነ በኋላ ስልክ ተደወለ፡- <<ሰውዬው አብዷል? ምንድነው የምትሰሩት? እንደውም ጥፋተኞች እናንተ ናችሁ፥ ማይክራፎኑን ለምን አትዘጉበትም?>> ብለው ስልኩ ተዘጋ፡፡ ከቢሮ ስወጣ ማስታወቂያ ሚኒስትር በታንክና በመትረየስ ተከቦ ሳይ ደነገጥኩ። ያዙኝና ለሁለት ቀን ያህል አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ የቁም እስረኛ አደረጉኝና ተፈታሁ። ከዚያ ለስድስት ወር ያህል ከስራ ታገድኩ። በኋላ ጠበቃ ይዤ ተከራከርኩና በመጨረሻ ለጊዜው የማላስታውሰው ቅጣት ተጥሎብኝ ወደ ስራ እንድመለስ ተደረኩኝ።
– በጋዜጠኝነት ቆይታህ በሰራኸው ዜና ተቀይሞ ቡጢ የሰነዘረብህ ሰው አላጋጠመህም?
* እንደ ምሳ ባይሆንም የቁርስ ያህል ትንሽ ቀምሻለሁ።
– የአቶ ገዳሙ አብርሃምና የአንተ ጭቅጭቅ ምን ነበር?
* ምንም ነገር የለም። አቶ ገዳሙ በወቅቱ የመምሪይ ሃላፊ ነበር። እኔ ደግሞ ዋና አዘጋጅ ነበርኩ፡፡ ስለዚህ ምንም ቅርበት በሌለበት ደግሞ ጭቅጭቅ አይኖርም።
– ከሌለ ሰራተኛው በሙሉ ለአቶ ገዳሙ የገንዘብ መዋጮ ሲያዋጣ አንተ አይመለከተኝም ለምን አልክ?
* ነገሩ ምን መሰለህ፥ አቶ ገዳሙ ወደ ሌላ መስሪያ ቤት በሹመት ስለሚዘዋወሩ የስንብት ግብዣ በሚል ገንዘብ ይዋጣ ተባለና መሰብሰብ ተጀመረ። አቶ ገዳሙ በጋዜጠኛነት ሙያ በወቅቱ ማንም የሚያህለው አልነበረም፡፡ አስተዳደሩ ላይ ግን በጣም ተንኮለኛ ነበር። የሰው ምንም ጥሩ ነገር አይታየውም። አንዴ ከጠመደ ደግሞ የማይለቅ “አልቅት” አይነት ነገር ነው። የመዋጮ ወረቀት እኔ ጋር ሲመጣ እሺ “0.10 ሳንቲም ጻፊ” አልኳት። ሰብሳቢዋ በድንጋጤ አይን ታየኛለች። ያዋጡትን ሰዎች ዝርዝር ስመለከት ደግሞ አትክልተኛና ዘበኛ ከ20-30 ብር ድረስ መዋጮ ከፍለዋል። ምክንያቱም ገዳሙ የሚፈራ ሰው ነበር። በኋላ ግን ያዋጣነውን መዋጮ ከተመለከቱ በኋላ <<አቅም ስለሌላችሁ መዋጮ አያስፈልግም>> በሚል በደብዳቤ አሳወቁ፡፡ እኔ የተመለከትኩት እንደ ሽሙጥ ነው።
– በአባትህ ኢራናዊ ነህ። አንተ ያለ ስሜት ምንድነው?
* እኔ ተወልጄ ያደኩት አዲስ አበባ ነው። ስለዚህ ስለማላውቀው ሃገር ብትጠይቀኝ ምንም መናገር አልችልም። ኢትዮጲያዊነቴን ከምንም ጋር አላወዳድረውም።
– ግንቦት 13 ቀን 1983 አ.ም፥ ኮ/ል መንግስቱ ሃገር ጥለው ወደ ሐራሬ በሄዱ ጊዜ ማእረጋቸውን ትተህ ማንበብህ ይታወሳል፡፡ ለምን በዚያ መልክ ማንበብ ፈለክ?
* በወቅቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የመጣው ዜና፥ ለሕዝብና ለእርሳቸው ደህንነት ሲባል ከአገር እንዲወጡ ተሸኝተዋል የሚል ነበር። ዜናውን ይዞ የመጣውም የወቅቱ ምክትል ሚኒስትር የነበረው መርእድ በቀለ ነበር። በነገራችን ላይ መርእድ በቀለና እኔ አንድ ትምህርት ቤት ነው የተማርነው በጣም ጥሩ ጓደኛዬ ነው፡፡ ጠራኝና “ተሸኝቷል የሚለውን አንብበው ግን ራሱን እንዳታነበው አሻሽለው” ብሎኝ ሊሄድ ሲል፥ “እንግዳው ከሄድክ ሌላውን ዜና እንጂ ይሄንን አላሻሽለውም” አልኩት። “ግዴለህም አንተ የመሰለህን ነገር ስራ” አለኝ። እኔ እንዲያውም እንደ ቀልድ <<ብላቴ የሚገኘው ማሰልጠኛ እሄዳለሁ ብለው አውሮፕላን አስገድደው ወደ ሐራሬ ፈርጥጠው ሄደዋል>> ብዬ ሰርቼ ሰጠሁት። <<በቃ ይሄማ ጥሩ ነው አንብበው>> አለኝ። <<መርዴ ትቀልዳለህ?>> ስለው “አንብበው” የሚል ምላሽ ሰጠኝ፡፡ “ፈርምበት” አለኝ። “እኔ ፈረምኩ አልፈረምኩ ምክትል ሚኒስትር አይደለህ እንዴ?” አልኩት። “አንብበው” አለኝ ገባሁና አነበብኩት።
– ከአነበብከው በኋላ ያገኘኸው ምላሽ ምን ነበር?
* በወቅቱ የተለያየ ስሜት አስተናግጃለሁ፡፡ አንዳንዱ ልክ ነህ ሲለኝ ሌላው ደግሞ ቆይ ጠብቅ ብሎ ይዝትብኝ ነበር።
– አሁን እድሜህ ስንት ደረሰ?
* አሁን 66 አልፌ 67 ልረከብ ነው፡፡
– ስንት ልጆች አሉህ?
* ሰባት ልጆች አሉኝ።
– እንደው ሞት ላንተ ምንድነው? ሞትስ ትፈራለህ?
* ሞት ያለና ሁልጊዜ አብሮ የሚኖር ነው። ስለዚህ ሞት ያሰኘው ጊዜ ይመጣብሃል። በሌላ ጊዜ ደግሞ አስፈራርቶ ይሄዳል። ሞት ከማንኛውም ተፈጥሯዊ ከሆነ ጋር አብሮ ያለ ስለሆነ በበኩሌ ምንም አያስፈራኝም።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles