የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ካቀረበባቸው ክስ በነፃ የተሰናበቱት የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊዎች የነበሩት አቶ ቃሲም ፊጤ፣ አቶ በቀለ ገብሬና አቶ ገብረየሱስ ኪዳኔ አዲስ ኃላፊነት ተሰጣቸው፡፡
አቶ ቃሲም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ የመሠረት ልማት ጉዳዮች አማካሪ ሆነው ሲሾሙ፣ አቶ በቀለ ደግሞ፣ የከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ተሾመዋል፡፡ አቶ ገብረየሱስ ቀድሞ በነበሩበት የመሬት አሰጣጥ ኦፊሰር ሆነው እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡
የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሦስቱን ግለሰቦች ወረዳ 17 ቀበሌ 19 ውስጥ ከሚገኝ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ጋር በተገናኘ በሙስና ወንጀል በመጠርጠር በቁጥጥር ሥር አውሏቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡
እነዚህ ኃላፊዎች ተጠርጥረው የተከሰሱት ቦታው ኢንጂነር ግርማ አፈወርቅ የተባሉ ግለሰብ መሆኑ እየታወቀ፣ በአካባቢው ባለሦስት ኮከብ ሆቴል ከገነቡ ባለ ንብረት ጋር ተመሳጥረው መሬቱን አሳልፈው ለመስጠት ለአስተዳደሩ የመሬት ሊዝ ቦርድ የተሳሳተ መረጃ አቅርበዋል በሚል ነው፡፡ ነገር ግን ባለሥልጣናቱ ባለፉት አሥር ወራት በእስር ላይ ሆነው የክስ ሒደቱ ቢቀጥልም፣ ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ተጠርጣሪዎቹ ድርጊቱን ፈጽመዋል ሊያስብል የሚችል ማስረጃ ስላልቀረበ በማለት በነፃ ማሰናበቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የፀረ ሙስና ኮሚሽን ይኼንን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ ቢጠይቅም፣ ይግባኝ ሰሚው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍርደኞቹ ሳይጠሩ ይግባኙን ሳይቀበል መዝገቡን መዘጋቱን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡
በዚህ መሠረት የቀድሞ ሠራተኞቹን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቀብሎ አዲስ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል፡፡ አቶ ቃሲም ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ግንባታ ፈቃድ ባለሥልጣን ኃላፊ ነበሩ፡፡ አቶ በቀለ ደግሞ የከተማ ማደስና መሬት ባንክ ኤጀንሲ ኃላፊ ነበሩ፡፡
ምንጮች እንደገለጹት አቶ ቃሲምና አቶ በቀለ ቀድሞ እንደነበራቸው ሥልጣን ውሳኔ ሰጪ ተደርገው ባይሾሙም፣ አሁን የተሰጣቸው ሥራ ግን ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡
አቶ ቃሲምና አቶ በቀለ በመሬት ዘርፍ ለረዥም ጊዜ የሠሩ ናቸው፡፡ በተለይ አቶ በቀለ በአቶ አርከበ ዕቁባይ ይመራ ከነበረው የከተማው አስተዳደር ቀደም ብሎ በተለያዩ የኃላፊነት ሥራዎች ላይ ሲሠሩ የቆዩ ናቸው፡፡ አቶ ቃሲም ደግሞ ከአቶ ኩማ ደመቅሳ የአስተዳዳር ዘመን ጀምሮ በመሬት ዘርፍ በኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩ ናቸው፡፡
Source: Ethiopian Reporter