(ዘ-ሐበሻ) በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርገው የሚኒሶታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ማህበር ነገ በሚኒሶታ የኦሮሞ ኮምዩኒቲ በጠራው ሰልፍ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያውያን ወዳጅ የሆነ በመገኘት አንባገነኑ የሕወሓት መንግስት ሰላማዊ ጥያቄ ባቀረቡ ዜጎች ላይ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች የወሰደውን የግድያ እርምጃ እንዲያወግዝ ጥሪ አቀረበ።
“አስቸኳይ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ! በሚኒሶታ ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያውያን ወዳጆች” በሚል የወጣቶች ማህበሩ በሶሻል ሚድያ፣ በቴክስት መልዕክት፣ በፖስተርና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እየበተነ ካለው በራሪ ወረቀት ላይ እንደሚነበበው “አምባገነኑ የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግስት ከዚህ ቀደም በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በኦጋዴንና በሌሎችም የኢትዮጵያ ከተሞች ሰላማዊ ጥያቄ ባነሱ ዜጎች ላይ ይወስድ የነበረውን በጥይት የመግደል ዘመቻ በመቀጠል ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ሰላማዊ ጥያቄ ያነሱ ተማሪዎችን ጥይት በመተኮስ መግደሉ ይታወሳል። በመሆኑም በሚኒሶታ የሚገኘው የኦሮሞ ኮምዩኒቲ ከሜይ 9 ቀን 2014 (May 9, 2014) ጀምሮ በሴንት ፖል ስቴት ካፒቶል ደጃፍ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ከጠዋቱ 9 ሰዓት ጀምሮ የጠራ በመሆኑ፤ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ጥቃት በጋራ እናወግዝ ዘንድ ሁላችሁም ተጠርታችኋል። ዝምታ በቃ! ጥይት በቃ!” ይላል።
በነገው ዕለት ሜይ 9 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 9 ሰዓት ጀምሮ በሚኒሶታ ስቴት ካፒቶል (Minnesota State Capitol፡ 75 Rev Dr Martin Luther King Jr Boulevard., St Paul, MN 55155) የሚጀመረው የተቃውሞ ሰልፍ ቀጣይነት እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን ሕዝቡ በነቂስ በመውጣት ድርጊቱን እንዲያወግዝ ማህበሩ ጥሪውን አቅርቧል።
ማህበሩ ከነገው ተቃውሞ በተጨማሪ “በቅርቡ የወያኔ ሰዎች በሚኒሶታ እናደርገዋለን ያሉትንና በአላሙዲ የሚደገፈው የስፖርት ፌስቲቫል ቦይኮት ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚገኙ” ገልጸው “ወያኔዎች ኢትዮጵያ ሰው እየገደሉ ሚኒሶታ መጥተው በደም ገንዘብ ጨፍረውብን አይሄዱም” በሚል መርህ እቅዳቸውን ለማክሸፍ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ በበተኑት ወረቀት ላይ ገልጸዋል።