Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በደቡብ ኮሪያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወቅታዊ መግለጫ፡ ያምማል! አፍንጫን ሲመቱት ዓይን ያለቅሳልና!

$
0
0

6 killo University
እኛ የኦጋዴን፣ የኣማራ፣የኦሮሞ፣የትግራይና የደቡብ ብሄር ተወላጆች ኣዲስ ኣበባን ለማስፋፋት በሚል ሽፋን በኣዲስ ኣበባ ዙሪያ የሚገኙ ድሃ የኦሮሞና ሌሎች ገበሬዎችን ግፍ በጥብቅ የምናወግዝ ሲሆን በቅርቡ በሃረማያ፣ በኣምቦ እና በሌሎች ኣካባቢዎች የሚኖሩ የኦሮሞ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደውን ግድያና በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ሊገልጹ በወጡ ተማሪዎች ላይ እየተወሰደ ያለውን የድብደባና የማጉላላት ዘመቻ በጥብቅ እናወግዘዋለን። ገዳዮቹም የጊዜ ጉዳይ እንጂ በፍትህ ፊት ቀርበው የእጃቸውን እንደሚያገኙ ኣንጠራጠርም።

እኛ ኢትዮጵያዊያን ልብ ልንል የሚገባው ጉዳይ ባለፉት ዘመናት እንደታዘብነው የኢህዓዴግ መንግስት ሲያሻው ብሄር እየለየ ሲያሻው በጅምላ ሰላማዊና ለውጥ ፈላጊ ዜጎችን ሲያሰቃይ ሲገድል ቆይቱኣል። ኣንዴ ኦሮሞን፣ ኣንዴ ደቡብ ሲዳማን፣ ኣንዴ ኣማራን፣ ኣንዴ ኦጋዴንን፣ኣንዴ ጋምቤላን ወዘተ ሲያጠቃ ተላላ ሆነን የተጠቃው ቡድን ብቻ ለብቻው ትንሽ ጮሆ ዝም ስለሚል የግፉ ጊዜ ሊረዝምብን ችሏል። ኣሁን ግን የኢትዮጵያ ህዝብ የመንግስትን የከፋፍለህ ግዛው ዘዴ ሊነቃበትና ኣፍንጫን ሲመቱት ኣይን ያለቅሳል እንደሚባለው ኣንዱ ሲጠቃ ሌላውም ሆ! ብሎ በመነሳት ይህንን ኣስከፊና በዓለም የሌለ ብሄርተኛ ኣገዛዝ ኣሽቀንጥሮ መጣል ይገባዋል።በሌላ በኩል የኦሮሞ ወገኖቻችን ያነሱትን የፍትህ ጥያቄ ለማጣመምና ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት የኢህዓዴግ ካድሬዎች ሊሯሯጡ እንደሚችሉ እየተገነዘብን ይህንን ጉዳይ የኦሮሞ ተማሪዎች ይስቱታል ብለን ኣናምንም። መንግስት በተለይ በኣሁኑ ሰዓት የቀለም ዓብዮት ሊነሳብኝ ይችላል የሚል ትልቅ ስጋት ስላለበት ህዝቡን በሃይማኖትና በብሄር በመከፋፈልና ከፍተኛ የሆኑ የፍትህና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በጋራ እንዳይነሱ ስለሚፈልግ ብሄርተኝነትንና ጠባብነትን ለብሶ እንደለመደው እያጋጨ በስልጣን ለመቆየት መፍጨርጨሩ ኣይቀርምና በማናቸውም ተቃውሞዎቻችን ውስጥ ለወያኔ እድል ፈንታ መስጠት የለብንም።

በሌላ በኩል ለውጥ ለማምጣት የሚታገሉ ዴሞክራት የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆኑ ኣንድ ብሄር ተለይቶ ሲጠቃ ሁሉን
የማንቀሳቀስና ለጋራ ትግል ቆራጥ የጥሪ ደወል የማሰማት ሃላፊነት ኣለባቸው ብለን በጽናት እናምናለን።

የጀግናው ብእረኛ እስክንድር ነጋ ነገር፣ በቅርቡ ደግሞ ወደ ዘብጥ የወረዱት የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ጉዳይ እንቅልፍ የነሳን ጉዳይ ነው። እነዚህ ወጣት የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን በሰፊው እስር ቤት የሚገኘውን የኢትዮጵያን ህዝብ የነጻነት እጦት ኑሮ ተምሳሊት ኣድርገው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ለጋ ወጣቶች ወደ እስር ቤት መውረዳቸው ከሰፊው እስር ቤት ወደ ጠባቡ መግባታቸውን ከማሳየቱም በላይ የታሰሩት ግለሰቦቹ ብቻ ሳይሆኑ ኣላማቸው በመሆኑ ሌላው የዞን ዘጠኝ እስረኛ የሆነው ኢትዮጵያዊ ሁሉ መንግስት የነጻነት ጥያቄውን ወደ ወህኒ መወርወሩን የሚያሳይ በመሆኑ ምን ያህል መንግስት በጭካኔ ስራው ሊቀጥል እንደ ወሰነ ያሳያል። በመሆኑም የነዚህ ወገኖች መታሰር፣ የፖለቲካው ምህዳር ምን ያህል እየጠበበ መምጣቱን፣ መንግስት ለህዝቡ ያለው ንቀት ጫፍ መርገጡን ያሳያል። በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በብሄርና በሃይማኖት ሳይከፋፈል የኦሮሞ ወገኖቻችንን ወቅታዊ ጥያቄና የጋዜጠኖቹን እስር ጉዳይ ወደ ኣጠቃላይ ፍትህና ዴሞክራሲ ጥያቄ ከፍ ኣርገን በያለንበት እንነሳ :: ዴሞክራሲና ፍትህ ሲሰፍን ጥያቄዎቻችን ሊፈቱ ይችላሉና ኢትዮጵያዊያን በጋራ ለለውጥ እንድንነሳ ወገናዊና ወንድማዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
የማትከፋፈል ኢትዮጵያን ለትውልድ እናሳልፋለን!
በደቡብ ኮርያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ድምጽ


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>