(ዘ-ሐበሻ) በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች በተለይም በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው የኃይል እርምጃ ይቁም ሲል ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉአላዊነት ፓርቲ አስታወቀ። ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ “በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ በመንግስት ኃይሎች እየተወሰደ ያለው የኃይል እርምጃ ያውግዛል።” ብሏል።
“ለማንኛውም የህዝብ ጥያቄ መልሱ ግድያ ሊሆን እንደማይችል ያምናል።” ያለው ዓረና “የኢህአዴግ መንግስት የህዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ መፍትሔ ከማፈላለግ በኃይል ለመጨለቅ መሞከሩ ካለፈው የደርግ ስርዓት መማር አለመቻሉ ያሳያል።” ብሏል።
“ኢህአዴግ ህዝብን ማስተዳደር ባለመቻሉ ምክንያት የህዝብን ተቃውሞ እያየለ በመሄዱ ስልጣን ለህዝብ የሚያስረክብበት መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል።” የሚለው መግለጫው ሰሞኑን እየወሰደው ያለው የኃይል እርምጃ ባስቸኳይ እንዲያቆም ጠይቋል።
“መላው የትግራይ ህዝብ ከተጎጂዎች ጎን እንዲሰለፍና የኢህአዴግን የኃይል ተግባር በግልፅ እንዲያወግዝ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።” ያለው ዓረና ህይወታቸው ባጡ የኦሮሞ ተማሪዎች የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን ለመግለፅ እንወዳለን።” ብሏል።