Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የነፃነት – ቃና። (ከሥርጉተ ሥላሴ)

$
0
0

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.05.2014 (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)

pic2የነፃነት ቃና የነገሮች ሳይሆን ይልቁንም ሰው የመሆን ልዩ ቃና ነው። ቃና መሆን እራሱ ሲያንሰው ነው – ለነፃነት። ነፃነት ትርጉም ያለው መኖር ማለት ነው። መኖር ሲተረጎምም ነፃነት ማለት ይሆናል። ነፃነት እንደ ጎረቤት ሳይሆን እንደ እራስ ሆኖ መኖር የሚያስችል ቀለማም የመብት ባላቤትነት ልዩ እርስተ – ጉልት ነው። የህይወትም እርእስም። ነፃነት ውስጥን ፈቅዶ የመተርጎም አቅም ካለምንም ተጽዕኖ ወይንም ፈቃድ ሰጪ ኃይል ወደ ተግባር ለመተርጎም የሚያስችል የብቃት ብቸኛ ማውጫ ነው። ነፃነት እራስን እንደ ፈለገ ገልጦ አንብቦ መኖር ማለት ነው። እርግጥ ነፃነት ጣሪያና ግድግዳ አለው። መብትና ግዴታ። መብትን ለማግኘት ግዴታን መወጣት። ግዴታን ተወጥቶ የመብት ባለቤት መሆን። ቀደምቶቹ የመብታቸውና የግዴታቸውን ጣሪያና ግድግዳ በአግባቡ ስላወቁ ነፃነታቸውን ለማግኘት ተሰዉ። በነፃነታቸውም በሀገራቸው ዳር ደንበር በወጥ ማንነት ኮርተው ኖረው – አለፉ። ዬድርሻቸውን ዬተወጡት አይደለም እናት ኢትዮጵያን አፍሪካን በአለም የተበተነው የዘረ ጥቁር ተፈጥሮ በተግባር አነጠሩት። መወደሱን ለማንነት በፈቃድ ሸልመው ዙፋኑን ጭነው  -አነገሡት። ኑሯቸው ህይወት — ማለፋቸውም ሕይወት ሆነ። መፈጠርን – ተጠበቡበት። አይደለም ትናንት ዛሬም በራስ የመተማመን ጥገትን በውስጣችን በደማቸው አተሙ። – ብሩካኑ በኢትዮጵዊነት የተካኑ።

የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ጥሬ ሀብትን ብቻ ሳይሆን እርካሽ ጉልበትን ለማጋበስ አፍሪካን እንደ ቅርጫ በተከፋፈሉበት ዘመን አባቶቻችንና እናቶቻችን በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት ሰውነታችን ተከብሮ እንደ እራሳችን በጣዕማችንና በጠረናችን እንኖር ዘንድ አስቻሉን። ነፍሳቸውን ኤልሻዳይ አርያም ገነት ያስገባለን። አሜን!  የትጉኃኑን አቨውን ዘመን የባረከ አምላክ እኛምንም በበረከቱ ይጎብኘን። አሜን! የቀደሙት የኢትዮጵያ መሪዎች እርብኝነታቸው ከዘመኑ ብቃት በላይ ስለነበረ ከባርነት ያወጡን የነፃነት አባቶቻችንና እናቶቻችን ናቸው። ደግመው ወለዱን – ለክብር።

ኢትዮጵያ ሀገራችን በታላቅ ክብር ከአፍሪካ ተለይታ እንድትኖር ካደረጉት የተግባር ተጋድሎዎች አንዱ እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ የራሷ ብርቅና ውድ የፊደል ገበታ ያላት መሆኑ ነው። ይህ ዕጹብ ድንቅ ገቢራዊ ቅርስ እኛነታችን ከሰጡን ታላቅ ባላውለታዎቻችን ደምና አጥንት መስዋዕትነት ውስጥ የተገኘ ልዩ ጥሪታችን፤ የጋራ የመንፈስ ሃብታችን ድህነታችንም ነው። ምልክታችን፤ እኛነታችን ነው።

አማርኛ ቋንቋ ቃናው ነፃነት፤ ጣዕሙ ደግሞ ታላቅ የዕውቀት ዘርፍ ነው። አያሌ ሰዎች የሚስማሙበት ቋንቋ መግባቢያ ነው ብለው ነው። ለእኔ መግባቢያ ብቻ ሳይሆን ቋንቋ የዕውቀት ዘርፍም ነው። ዬዓለም የመተንፈሻ ሳንባዋ ቋንቋ ነው። ቋንቋ ሙያም ነው። ባህልን ወግን ልማድን እምነትን ማንነትን ቀምሮ እራስን መግለጽ የሚያስችል የሀገር አንበደት ነው – ቋንቋ። የህዝብ ልሳን ነው። ቋንቋ ተቋምም ነው። እንደ ኢትዮጵያ ላላ ለታደለ ሀገር ደግሞ የነፃነት በኸረ ልጅ ነው።

አማርኛ ቋንቋ ያደገ፣ የሰለጠነ – ብልህ ወታደር ነው። እናት ሀገሩን ከነፃነት የታደገ ታላቅ ባለውለታም ነው። ጠላትን ቀጥቶ ለማንበርከክ ወጥ አንደበት ባይኖር ትጥቅና ሥንቁ፤ ፍላጎትና ራዕዩ የባቢሎን ግንብ በሆነ ነበር። ሥልጡኑ አማርኛ ግን ግዳጁን በከፍተኛ ደረጃ የተወጣ ሰማዕት፣ አርበኛና አደራ አውጪም ነው።

pic1አማርኛ ቋንቋ ፍሰቱ – ርባታው – ለዛው – ቃናው – ጣዕሙ – ዜማው – አወራረዱ ሳቢና አጓጒ ነው። አማርኛ ቋንቋ ውበቱ ልዩ ነው። ደማም – ዓይነ – ገብም። እያንዳንዱ ነጠላ ፊደል ቅርጽና ይዘታቸው ተደላድለው የተፈጠሩ እንደ አራስ ልጆች ታይተው የማይጠገቡ ብርቅ የዓይን አበባዎች ናቸው።  በሌላ በኩል አማርኛ ቋንቋ አንባሳደራችንም ነው። ከአፍሪካ የተለዬች ኢትዮጵያን ያደረጋት ታላቁ ሚስጥር ቀለማሙ የፊደል ገባታ ሥህናዊ ተፈጥሮ ነው። ለላቀው ብቃቱ ዘመንን እዬሸኜ ፈተናን እዬረታ፤ ጠላቶቹን እያስተማራ አምሮበት አለ። ባሰኜው ቀለም በሀገሩ ወግና ልማድ ትውፊትና ማንነት ፈክቶ  - አብቦ አለ። መፈጠርስ እንደ አንተ-  መኖርም እንደ አንተ – ማወቅም – ማደግም እንደ አንተ፤ መማርም መመራመርም እንደ አንተ -  ባለ ግራጫ ግን ሁል ጊዜም ዕንቡጥ።

የጹሑፌ መግቢያ ፎቶ በ2012 ዓለም ዐቀፍ የፊደላት ቀን ሲከበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተመረጡት ፊደላታ ጋር አማርኛ ቋንቋ ቤተኛ ሆኖ ፍላየሩ ውስጥ ነበር። ይህ ሁለተኛው ፎቶ ደግሞ እነዚህ የምታዮዋቸው ፊደሎች ለናሙና የተሰሩ ናቸው። ከተመረጡት ዬ17 ሀገሮች የፊደል ገበታዎች ውስጥ አንዱ የእኛው ጀግና ነበር። ይህ ለአንድ ወር በዘለቀው ኤግዚቪሽን መክፈቻ በር ላይ የነበረ ሲሆን „የገደል ማሚቶ“ በሚል እርእስ ሥር በተመረጡት ቋንቋዎች ተተርጉሞ በአንድ መጸሐፍና በድምጽም ንባቡ አብሮ ተያይዞ ቀርቦ ነበር። የአግዚቢሽኑ በር ሲከፈት ደግሞ ውስጡ  ሃብታችን በተሟላ መልኩ ነበር። ለዚህ ክብርና ዝና እንዲህ ያበቁን ኢትዮጵያዊነታችን እንድንሳሰለትና፤ እንድናደንቀው ያደረጉት ቀደመቱ ማስተዋሉን ፈጠሪ አምላካችን አብዝቶ የሰጣቸው ቀንዲሎቻችን ነበሩ።

„የእኛ ታሪክና የፖለቲካ ውጥንቅጥ“ ዲያቆን ኒቆዲሞስ እርቅይሁን ተችተው አኔን እንደጻፉኝ ኢትዮጵያዊነቴ ተጭኖኝ ሳይሆን ሙሉዑ ሰው እንድሆን በደም ፍሳሽና በአጥንት ክስካሽ የተሰጠኝ ውስጤ  - ብርቄም – የመኖሬ ስዋሰውም መኖሬም በመሆኑ ነው።

ለነገሩ እንደ ጸሐፊው አገላለጽ ወቀሰው ለእኔ ክብሬ በመሆኑ ለዚህ የወቀሳ ምስክርነት ላበቃኝ አምላክ ክብር ምስጋና ይግባው። እንኳንስና ይሄ በኢትዮጵያዊነቴ ምክንያት በድንጋይ ተደብድቤ እንድሞት ቢወሰንብኝ እዬዘፈንኩ የምቀበለው ስለመሆኑ የጹሑፌ ታዳሚነታቸውን ስለገለጹልኝ ለክቡርነታቸው ሆነ የእሳቸው ጹሑፍ ታዳሚ ለነበሩ ቅኑ ወገኖቼ አበክሬ በተደሞ መግለጽ እሻለሁ። አሁንም የሰው ሰው መሆኔን የሰጠኝ ኢትዮጵያዊነቴ ክብር -ምስጋናና – ልዕልና ለምንጊዜም እመኝለታለሁ።

pic3በተረፈ መልስ መጻፍ ያለስፈለገኝ ምክንያት ከቅርንጫፍ ጋር ሳይሆን እኔ ከግንዱ ጋር ስለሆነ ግብግቡ ግንዱን ወዳጄን ተክሌሻን እዬጠበኩ ነበር። እምለው ከኖረኝ የታናሼ ቃና የብዕር ውበት ግጥሜ ስለሆነ ደስ እያለኝ ከተክሌሻ ጋር እንጂ ከሌላ ጋር እእ! በተረፈ ሰማዕታት አማርኛ ቋንቋን እስከነ -ሙሉ ትጥቁ፤ እስከነ – ስንቁ ስለሸለሙኝም ዱዳ ሳልሆን ምንም እንኳን በሥነ -ንግግር ጥበብ  ዕድሉን አግኝቼ በሥልጣና ክህሎቴ ቢታገዝም በተፈጥሮዬም ብቁ ተናጋሪ፤ የወጣልኝ አድማጭ፤ ጸሐፊ፤ ገጣሚና ባለቅኔ እንዲሁም በትሁት እርግጠኝነት፤ በፈካ በራስ የመተማመን ስሜት እንዲኖረኝ አባቶቼና እናቶቼ ስለ አደረጉ አውዳቸዋለሁ፤ አከብራቸዋለሁ።  ስለዚህም በሙሉ ሰውነት አለምን በግልቡ ሳይሆን ከልቡ ገብቼ እንደፈትሽው በሚገባ ጠርበው ቀርጸውኛል። ጌጦቼ – ዋርካዎቼ  - ጉልላቶቼ ቀደምቶቹ የነፃነት ሊቀ – ሊቃውንታት።  http://www.ethiomedia.com/14news/our_complex_history.pdf

 

አሁን ወደ ቀደመው — ሁላችሁም እንደምታወቁት ሲዊዘርላንድ የሥራ ቋንቋዎች አራት ሲሆኑ ሶስቱ ጎልተው የወጡ በመሆኑ ዕርእሱ የአምርኛ ፊደል የሚለው በጀርመንኛ፤ በጣሊያንኛና በፈረንሳይኛ ሲሆን … በጎን ያሉት ደግሞ ሲጻፍ ከቀኝ ወደ ግራ እንደሆነ፤ ሲነበብ ከቀኝ ወደ ግራ ስለመሆኑና ከላይ ወደ ታችም እናት ፊደልን ማንበብ እንደሚቻል ተብራርቷል፤ ዝቅ ብሎ የእናት ፊደሎችና የልጅ ፊደላት እርባታን ለአብነት ተስርቷል። ከዚህ ባለፈ ስለ ቋንቋው አጠቃላይ ዜማዊ ድምጸት፤ ስለ ሰዋሰዋዊ ፍሰት፤ ግሳዊ እርባታ፤ የአናባቢና ተነባቢ ፊዳላት ጠባያት፤ በሌሎች ቋንቋዎች የሌሉ ፊደላትና የድምጽ ተዋፆዖ፤ የትውስትን ቃላትን ብቻ ስለሚያስተናግዱት ሁለት ፊደላት ማለትም „ጰ እና ፐ“ እና  የአማርኛ ቋንቋ ፍጥረቱ – እድገቱ – ደረጃውና የወደፊት ዕጣውን በሚመለከት ሰፊ ገለጻ / ፕረዘንቴሽንም / ነበር …. ይህ ብቃት ምንጩ የዛሬ አይደለም የትናንት ዓይነታ ሃብት እንጂ። አንገትን ቀና አድርጎ፤ ልብን ነፋ አድርጎ፤ እኛ አራሳችን የፊደል ገበታ አለን የሚስብል ጉልበታም ፕላኔት በመዳፋችን አለን። የማንም የትውስት ወይንም የብድር ያልሆነ፤ ተሸብቦ ወይንም ተሽበልብሎ ወይንም ተኮፋትሮ ወይንም ተትርትሮ ሳይሆን እራሱን ገልጾ፤ ብቃቱን ሊያሰጎበኝ የሚችል የሊቀ ሊቃውንታት ዕውቀት ጭማቂ ማለት አስችሎናል …. የነፃነት ባለቃናውን ዬአማርኛ ቋንቋ።

 

አማርኛ ቋንቋ ጥልቅ የመሆኑን ያህል አተረጓጎሙ እኔ ነኝ ካለ የቋንቋ ፊደላት ሆነ ሥርዓተ – ህግጋት ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ አንዳችም ነገር የለውም። የቀደሙት ከፊደል ቀረጻ ጀምሮ የሠሩለት ሥርዓት አማርኛን እራሱን አስችሎ ቀጥ አድርድርጎ አቁሞ ዓዕምድ እንዲሆን አስችሎታል። አማርኛ ቋንቋ ምርኩዝ – ከዘራ አይሻም። ወይንም ደንበር ዘለል ኩባንያዎች አይለማመጥም – ክፉሉ አይደለምና። ተፈጥሮውም አይፈቅድለትም። ነፃነትን አምጪው ኃይል እራስ በመሆኑ ይህንንም ጀግናው በቃና እና በቅኔ፤ ብብቃትና በስልት – ከውኖታል።

pic1

ሲወዘርላንድ በዙሪክ ክፈለሀገር ቪንተርቱር በሚባል ከተማ በቀን 2000 እንግዶችን በፍቅር የሚያስተናግደው የኢንተግሬሽን እና የህዝብ ቤተ መጸሐፍት የሚገኝበት ህንፃ ከሦስት መቶ ዓመት በላይ የኖረ በመሆኑ ካቩ ሆነ የጣሪያው እንጨት እንደተፈጠረ ውበቱ ከሩቅ ይጠራል። ከላይ ወደ ታች ፍላዬሩ ተሰርቶ ስለነበረ ታሪካዊ ህንጻ ጣሪያውንም ስለሚያሳይ እንዳለ ማቅረቡን መርጫዋለሁ።  „ወ ና ጀ“ ይታያሉ። ስታተልቁት ደግሞ ሌሎችም ይወጣሉ።

 

አማርኛ ያማረ የተዋጣለት ትዕይንታዊ ኪናዊ ቋንቋ ነው። አማርኛ ለፍቅርም ምቹ የሆነ ጣዕም አለው … ሥንኞቹ ዓይናማ ናቸው። ግጥሞቹ ኮልኮዮች ናቸው፤ ቅኔዎቹ ውስጥን ያስነብባሉ  - ርቀው ሊቅነትን ይሸልማሉ። ድርሰቶቹ ተሳለሙኝ ባዮች ናቸው። ተረትና ምሳሌዎቹ ዕውደት ይናፍቃቸዋል፤ ሥነ ቃሎቹ ትውፊትን ይጣራሉ። ቅጽል፤ መስተዋድድ፤ ተወሳከ ከግሥ፤ መስተጻምር ግሥ – ያነግሳሉ።  አደብ የገዛ አደብን ያበረከተ – እጬጌ!

አማርኛ ቋንቋ እራሱን ሲገልጽ በነፃነት ነው። ነፃነቱን የሰጠው እሱ እራሱ ነበር። ነፃነቱን አምጦ አርበኞችን በአኃቲ ልቦና በፍቅር ገዝቶ ባዕቱን አስከብሮ እሱም ከበረ። ቋንቋው የሚርቅ ሳይሆን አቅርቦ እርስዎን እዬፈታተሸ እሱ ደግሞ በተራው በህግ ሥርዓቶቹ ይፈትሽዎታል። ዘንበል ያሉ ግድፈቶችን ትህትናን ለግሶ እያባበለ፤ እያቆላመጣ ያስተምራል።

pic4ባልተወለዱን፣ በቀለም በማንገናኛቸው ዘንድም እንዲህ ይወደዳል። ተከብሮ ያስከብራል። አንገትን ቀና አድርጎ ማንነትን ያበራል። አማርኛ  የኢትዮጵያ ሀገራችን የወል ሃብትና መግለጫ ነው። ንብረትነቱ ግላዊ ሳይሆን እናት ሆዱ በመሆኑ ሁላችንም በእኩልነት ያለአድሎ ያስተናግዳል። ግንኙነታችን የሰመረና ያማራ እንዲሆን ይጓጓል። በዬትኛውም ዘመን የተነሱ ቅኝ ገዢ ፍላጎቶችን ሰብሮ – አዋርዶና – አሳፍሮ የመለሰ የጀግኖች ቁንጮ ነው። ፍላጎታቸውንም አባክኖ ውኃ የበላው ቅል አድርጎታል – አርበኛው።

አማርኛ ቋንቋ በዘመነ ወያኔ በክፉ አይን የሚታይ፤ ስር በሰደደ ጥላቻ ጦርነት የታወጀበት፤ ፍዳውን የከፈለ፤ በረቀቀ ሆኔታ ታቅዶ ሞት የተበዬነበት ነበር። ግን አልሆነም። ወያኔ በፈለገ መልኩ አጠቋቁሮ፤ በባሩድ አቃጥሎ ሊደምስሰው ቢሻም እንሆ ተወደደ ተከበረ ተፈቀረ – ነገም። አማርኛ ቋንቋ ዘመኑ የፈቀደለትን ሥልጣኔ የተቋደስው ከሰማይ በወረደ መና አልነበረም። እሱም ታግሎ ደምቶና ተሰውቶ ነው። ስለዚህ የለመደውን መሰዋዕትነት እንደ ዘምኑ ማስተናገድ የመቻል ሙሉ አቅምና ሥነ – ተፈጥሮ አለው። ለዚህም ነው ገደልነው ሲሉ እያተ የሚሄደው፤ አጠፋነው ሲሉ እያበለ የሚገኘው፤ ደመሰስነው ሲሉም ቀድሞ ድል ላይ የሚፈርሸው፤ ሊከተክቱት ባዘጋጁት ገጀሞ እንሱን እዬከሰከሰ የሚያሸንፋቸው። ወያኔ ሰው በማያውቀው ደረጃ በጣም ብዙ ነገሮች ነው በአዲስ አባባ ዩንቨርስቲ እንዲከስሙ ያደረገው። ግን ሥራዬ ብለን ተግተን የምንታገልለት ኃይሎች ስላላን ምን አልባት አንድ ቀን የአፈኑት የኢጎ አርበኞች ሲበኑ ሌላም ታእምር ወያኔ ያያል።

አዎን ቋንቋችን አማርኛ ማደግ ስላለበት ዘመኑን የቀደሙ ተግባራት ተከውነውበታል። ትናንት ሲዊዘርላንድ ላይ ጄኔባ ድብልቅ ያሉ ሁለት ፍሬ መጸሐፍቶች፤ ቪንተርቱር ላይ ሙዚዬም ቤተ መጸህፍት ሁለት የአዲስ አባባ ዩንቨርስቲ የሥነ ቃል ጥናታዊ ወረቀቶችና አንድ የሥነ ቃል  መጸሐፍ ብቻ ነበሩ። ዛሬ ግን 6 ጊዜ አስተውሉ 6 ጊዜ በሲዊዝ ብሄራዊ  የኢንተግሬሽን ቤተ መጸሐፍት ብሄራዊ ጉባኤ ስለ አማርናኛ ቋንቋ የአዋቂዎችና የልጆች መጸሐፍት ፍላዬሩን በሀገሬው ቋንቋ እራሳቸው ሰርተው ማብራሪያ ተስጥቶበታል። እናም አብዛኞቹ የኢንተግሬሽን ቤተ መጸሐፍት አዲስ መምሪያ ከፍተው በፍቅር እያስተናገዱት ይገኛል። ትግሉ ይቀጥላላ ውጤቱም ይታፈሳል ……

ሌላም ይታከል – በሥነ ሥርአት፣ በንድፍ የተሰሩት ግጥሞች በቂ ጊዜ ተስጧቸው ለኤግዚቢሽን በቅተዋል። አለ ሌላም ቤተ መጸሐፍት ታዳሚዎቻቸውን የአማርኛ ቅኔ ሲዘረፍ በጣዕማዊ ቃና አስኝቷቸው ውሎ አበሉን ትራንስፖርቱን ክፍለው ቁጭ ብለው አዳማጡት። ይደገምልን እያሉ፤ በመጨረሻም „ የምሽት ማህሌት“ ሲሉ አደነቁት።

 

ግን ምን ያደርጋል? እንዲህ በሰው ሐገር የሚደከምለት ወያኔም በአንጡራ ጠላትንት ፈርጆ የሚደቁሰው አማርኛ ቋንቋ ንዑድ መንፈስን የሰነቁትን ማዬትም መስማትም አንሻም ሲሉ የኢጎ አርበኞች በዬኑበት።  አዎን! በ2013 የካቲት 4 ሲዊዘርላንድ ጄኔባ ላይ የኢሳት ፈንድ ራይዚንግ ነበረ። እንዲሸጥ በጊዜ ተጠዬቀ። ፈቃዱን ማግኘት አልተቻለም። ማስታዋቂያ ብቻ መናገር ይቻላል ተባለ። ይህ ስለተባለ ገንዘብ – ጊዜ  - ጉልበት ፈሶ ከእያንዳዱ ለናሙና 3 ሲደምር 18 መጸሐፍት 4 ሰአት ተጓዙ ወገኖቻቸውን ሊዩ – ጓጉ። ያው ከወገኖቹ ጋር ውስጥ ባይፈቀድላቸውም ውጪ ኃይለኛ በረዶ ነበር እንሞክራለን አለችኝ ክብሬና እህቴ ወ/ሮ ምስራቅ መንገሻ ይዘን ሄድን። ይህም አልሆነም። በቃ ይህ ነው የነፃነት ትግል።

እህቴ አረረች ማስታገስ ስለነበረብኝ ወቅቱ ያልነበረውን አዲስ ፕሮጀክቴን ነገርኳትና እንድትረሳው አደረኩኝ። እኔን ነፃ ሊወጣ በተደራጀ ሚዲያ ላይ የነፃነት ቃና ውበት ታሸገ። እኔን ግን አስቆመኝ?! እእ! አንድ ወንድሜ በጥልቀት ያውቃል። እንዲያውም ተጨማሪ ገንዘብ ላኩ „ እንቅልፍ አልባዋ ሥርጉተ ሥላሴ“ እስከ ማለት ያስቻለው የማይታይ ተግባር ከወንኩ። የወጣው ገንዘብ ቀላል አልነበረም። በወቅቱ ዓይኔን ኦፕራሲውን አድርጌም ስለነበር ያልተጋባ እርምጃ ነበር የወሰድኩት። ግን አረመኔዎች ናቸው። ትንሽ ብጣቂ አንጀት ያልሰራላቸው። አሁን ወያኔ ቢሆን ስንቱን ባል ነበር። ለእነዚህ በነፃነት ሀገር ነፃነቴን ለሚነጥቁ  — ለሚጨፈልቁ – ለሚረማማዱበት —- ሰዎች ፍርድና ዳኝነትን ከጌጦቼ ስለላ የቤተ ሥራውን ለእናንተ ልስጥ። አይካድ ነገር ሶስት እህቶቼ – ተሳትፈውበታል። ያውም እኮ እኔ ከሞት የተረፍኩ ነገ ምን ሊሆን እንደሚችል የማላውቅ ነኝ። አይታፈር ስሞትላቸው ለቀብር ይመጡ ይሆናል። „አሻም“ አልፈልግም።

ህም!  እንኳንስ 18 መጸሐፍት ከሁለት ኪሎ በላይ በሃኪም የተከለከልኩ ነኝ። ክብሮቼ  እናት ሆዱ ሁነና ግፍና በደሉን መርምሩት። እግዚአብሄር ይመስገን። አሁን ማስታወቄውን በብላሽ ኢትዮ ሚዲያና ሞረሽ ወገኔ ሠሩት፤ ከዚህ በኋለ ሊንኩን ወገኖቼ በሙሉ እዬተሻሙ ተረባረቡበት። ጭንቀት ነበረኝ አዲስ ሥራ ስለሆነ እንዳልዘረፍ። አሁን ግን መንፈሴ አረፈ።  ዘሃበሻም ማህበራዊ ድህረ ገጽ ደግሞ ቀዳ እያደረገ ልሳኑን በፍቅር ተቀበለ። በጉልበተኛ አቅመ ቢስ ኢጎ ታፍኖ የነበረው በር ቧ አድርጎም ከፈተለት። እንዲህ ተገናኝ እንጂ ተለያይተን እኮ ነበር። ከ2009 እስከ 2014 ብዙ ነው መርግም። ግን ተቻለ። እጅግ አመስግናችኋለሁ። ነፃነትን በእናንተ አዬሁኝ። ለዛውም ለሴት! ድንቅ ነው። ተመስገን! እንኳንም 2011 አልሞትኩኝ።

 

የሰማይን ጸጋ መገደብ አይቻልም – ፈጽሞ። ሥጦታው የመዳህኒት ነውና። የተዘጋ ተከፈተ። ማን ያውቃል ነገ እናንተን ሊይ ወደ እምትኖሩበት ባዕት ብቅ ይል ይሆናል። ሲዊዞች ጣዕሙን የሚለኩትን እናንተም ትቋደሱት ይሆናል። ተክሌሻ ወንድምአለም እዬሰማህ ነው? ለመሆኑ አለህ ከእኔ ጋር ነህን? መቼም እኔ ካለአንተ ብዕር አይሆንልኝ። እስቲ አንድ መላ በል አባቱ። መቼም እኔና አንተ ፍቅር በፍቅር ሆነናል። አንድ ጊዜ የዶር/ አረጋይ መጸሐፍን ተሳታፊው ምጥጥ አደረገላቸው ስትል ትንሽ ዜና ቢጤ አኮምኩመህን ነበር። እዚህ ደግሞ ግልምጫውም ጥፊውም ተችሎም ጋዳ ነው – ተራራ። ገደሉኝ ስልህ! በሽታሽቶ።


ሲዊዝ የአንድነት ድጋፍ ድርጀት እናት ድርጅቱ እውቅና እንዲሰጠው ያልታከተ በሳል ጥረት አድርጎ አልተሳካለትም። ሲዊዝ ውስጥ ያለው ትሬኮላታ ታገለው። በመጨረሻ አባላቱ ተዘርፈው የሀቅ አርበኞች ተገፈተሩ። ሲዊዝዬም ከአንድነት ረድኤት ውጪ ሆነች። ሥርጉተን የተከላት ኢሠፓ ፓርቲዋ ነው። ያበቀላት ደግሞ ገበረመድህን በርጋ ነው። ገብረመድህን በርጋ ማለት ጎንደርን ፓሪስ የማድረግ ንዑድ አቅም፤ ኢትዮጵያን የመሥራት ጥልቅ ጥበብ የነበረው፤ ትውልድ ሊተካው ከቶውንም የማይችል የድርጅት ናሙና  ነበር። ስለሆነም ሥርጉተን ጠቅላል አድርጎ ቆሻሻ ውስጥ መጨመር አይቻልም ቁርጠችሁን እወቁ – ።

ቅኑ ጎጄ ወንድሜ መከፋትህን ጥቃቴ ውስጥህ እንደ ገባ ጥቅምት 12.2013 ዙሪክ ላይ ሳገኝህ  በአይኔ አይቻለሁ። ዬአንተን ፈቃድ ስለሟላሁ፤ ሁለት ጊዜ ሙሉ በራሴ ወጪ ፍርንከፈርት አማይን በግንቦት 7 ስብሰባ መገኘቴ የተከለውን ቋሳ በምልሰት ትመረምረው ዘንድ በአጽህኖት አሳስብኃለሁ። ለእኔ አይደለም ለነፃነት ትግሉ አይበጅም። አፋፍ ላይ የተንጠላጠለ፤ በብዙ ዝንቅ ፍላጎት የታመለ ስሜት ይዘን የታላቋን ኢትዮጵያን ህልም መመኘትም ጅልነት ይመስለኛል።

ሌላው አስደሳቹ ዜና ስለ ፍቅር ሥርጉተ እምትለው ስለነበራት አሁንም 7ኛው መጸሐፏ መንገድ ላይ ነው //// 8ኛውም እርማት ላይ ነው – ይቀጥላል በዚህ በያዝነው አምት //// ሌላም ስለ አማርኛ ቋንቋና ስለ ኢትዮጵያ መታዳም ሰሞኑን ትንሽዬ ቀዳዳ አግኝቻለሁ። ተመስገን! እግዚአብሄር አብሮ ካለ ሁሉም አለ። የሰማይን መክሊት ከቶ ማንም ሊገድበው አይችልም …. ገና ያፈራል  - ይጎመራል። ወርቅ ይፈልቃል እንጂ አይማርትምና። አማርኛ ቋንቋ ቤቱ ውስጥ ሆኖ ውስጥነቱን ያዘራል። ሥርጉተም ትግሏን በመቀጠል ታንቆጠቁጠዋለች። የተደራጀው አደራጅ ግጥሙ ነውና።

 

የሚገርማችሁ ነጮቹ ይወዱታል አብሶ ለፊደልና ለተስፋ መጸሐፍት  ፍቅራቸው ጥልቅ ነው። ስለሆነም በጉባኤዎች፤ በኤግዚቢሽኖች በገለጣ ጣቢያዎች ከነፃነት – ቃናችን ጋራ ይገናኛሉ – እኛስ ነው ጥያቄው? ግን 613 ግጥሞችን በሶስት መድብል በአንድ ጊዜ አፍ ባላው የመቃብር ኑሮ  - ያሳተመ ሰምታችሁ ታውቃላችሁን? ሥርጉተ በ2010 አድርጋዋለች። በ2012 በአንድ አመት ብቻ ሶስት መጸሐፍትን አሳትማለች። የሥርጉተ ሥላሴ የመንፈስ ሰብል።“ ይህቺን ቃል ጉግልን ብታጎርሱት ይነግራችኋል። ጉግል ጉቦ ይወዳል። ታዲያ ጉርሻው እንደ „ባለታክሲው ፊልም“ በቢላዋ እንዳይሆን አደራ! ብረት ግጥሙ አይደለም። በዘንካታ እጣት። ጉግልንም ባህላችን እናስተምረው – ይሁን በሉ።

 

እንደ መደምደሚያ – ቋንቋ ሰው ሰው የሚሸት ቃና እና ናርዶስ አለው። ቋንቋ ጌጥ ነው – ልዩ። ውስጥን የሚሳይ ዘመናዊ መስታውት ነው። ስለ ውስጥ የሚናገር ርትዑ ነው። ቋንቋ ከተናጋሪው ቀድሞ ተናጋሪውን የማንበብና የመተርጎም ጸጋ አለው። ቋንቋ ንዑድ መንፈስ ስላለው ርህርህናው ጥልቅ ነው – እርግብ። እኔ „እኔን“ ከምገልጸው በላይ በተብራራ መልኩ አማርኛ ቋንቋ „እኔን“ ተርጉሞኛል ብል ግነት አይደለም።

 

የኔዎቹ ጨረስኩኝ። ዕለተ ሃሙስ ያው በተለመደው ጊዜ የቻላችሁ አዬር ላይ፤ ያልቻላችሁ ደግሞ አርኬቡ ላይ ግንቦት 8. 2014 እንገናኝ። www.tsegaye.ethio.info Tsegaye – Radio Lora Aktuelles ወይንም www.lora.ch.tsegaye ብዕሬን ብቻ ሳይሆን እኔን እህታችሁን ናፍቆት ብትክትክ አድርጎ ሲነዳድለኝ ታዳምጣላችሁ። ጀግኖቻችንም አብረን እናከብራለን። ጀግናን አብረን እንናፍቃለን …. እሺ ….. መልካም የንባብ ጊዜ ሰንበት ተመኘሁላችሁ እኔ ሎሊያችሁ ሥርጉተ ሥላሴ።

 

  • ፎቶዎቹ የተገኙት ከሲዊዞች ጋራ ስለተሰራ ነው እንጂ በተለያዬ ሁኔታ ከኢትዮጵውያን ጋር የተሰሩ ቪዲዮዎች ፎቶዎች ማግኘት አልቻልኩም – እንኳንስ አኔ በሚቀርቧቸው ሰዎች እንኳን ተሞክሮ አልተቻለም – ጉበልበተኞች። ተዳፈን። እረመጥ ነው ፍሞ ያበስላለ …..

 

 

ነፃነት የገባው ማንነት ለነፃነት ክብር አለው። ግን ማንነቱ እራሱን ማግኘት ከቻለ ብቻ!

 

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>