ታምሩ ጽጌ
-በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማስተር ፕላኑን ተቃወሙ
-ከአዲስ አበባ አዳማ በአዲሱ መንገድ ግራና ቀኝ መሬት መሸጥ ቁጥጥር ሊደረግበት ነው
አዲስ አበባ ከተማና በዙሪያዋ የሚገኙትን አምስት ልዩ የአሮሚያ ዞን ከተሞች ሰበታ፣ ቡራዩ፣ ሱሉልታ፣ ለገጣፎና ገላን አጠቃሎ በተሠራው ማስተር ፕላን ላይ መግባባት ባለመቻሉ ግምገማዊ ውይይት በማድረግ የመግባቢያ ፊርማ ለማድረግ የተጀመረው ስብሰባ ሳይጠናቀቅ መቋረጡን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
መጋቢት 19 ቀን 2006 ዓ.ም. የልዩ ዞኑና የአዲስ አበባ ከተማ ተወካዮች በማስተር ፕላኑ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት የተሰበሰቡ ቢሆንም፣ በተሠራው ማስተር ፕላን ላይ አንድ ዓይነት አቋም ሊይዙ አለመቻላቸው ታውቋል፡፡ ከአንዳንድ ተሳታፊዎች መግባባቱን ወደኋላ ሊመልሱ የሚችሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በመነሳታቸው፣ በዕለቱ ይካሄዳል ተብሎ በነበረው የጋራ ውይይት ላይ ልዩነት መፈጠሩን ምንጮች አስረድተዋል፡፡
በአዳማ በተደረገው ውይይት በልዩ ዞኖቹ በኩል የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አብዱልአዚዝ መሐመድና አዲስ አበባን በመወከል ከንቲባ ድሪባ ኩማ በጋራ ውይይቱን የመሩት ቢሆንም፣ በውይይቱ የተሳተፉ የተለያዩ ቢሮ ኃላፊዎችና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ባነሱዋቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምክንያት በዕለቱ ሊቋጭ ዕቅድ ተይዞለት የነበረው ግምገማዊ ውይይት ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን መሠረት ያደረገ የጋራ ማስተር ፕላን አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት፣ የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ልማት ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ፣ ከስምንት ዓመታት በላይ ጥናትና ውይይት ከተደረገበት በኋላ፣ ማስተር ፕላኑ ተሠርቶ መጠናቀቁንና በመጪው ግንቦት ወር ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡
ፕሮጀክቱ በ1996 ዓ.ም. በቀድሞው ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ መጠንሰሱን የሚናገሩት ምንጮች፣ ለፕሮጀክቱ መጠንሰስ ዋና ምክንያት የሆነው በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙት የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ታሳቢ ያደረገ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
በተሠራው ማስተር ፕላን ላይ ሁለቱ ወገኖች ተወያይተውና ተፈራርመው ለመለያየት በአዳማ ያደረጉት ስብሰባ በተለይ በአንዳንዶቹ የውይይቱ ተሳታፊዎች ያልተጠበቀ ጥያቄና አስተያየት ግራ የተጋቡት አቶ ድሪባ፣ ስብሰባውን ለመገናኛ ብዙኃን ዝግ በማድረግ ውይይቱን መቀጠላቸውን ምንጮች አስረድተዋል፡፡
ጥያቄዎቹና አስተያየቶቹ የተነሱት ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ባሉ ግለሰቦች በመሆኑ፣ ምናልባት ስለማስተር ፕላኑ በቂ ግንዛቤ እንዳልተፈጠረ በመገንዘብ እንደገና ግንዛቤ ለማስያዝ ስብሰባው በዝግ እንዲካሄድ ሳይደረግ እንዳልቀረ ምንጮች ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡
ማስተር ፕላኑን በሚመለከት መጋቢት 19 ቀን 2006 ዓ.ም. አዳማ ላይ ተደርጎ የነበረው ግምገማዊ ውይይትና ይፈጸማል ተብሎ የነበረው የስምምነት ፊርማ ለምን እንደተቋረጠ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳዊት ንጉሴ፣ ስብሰባው ተደርጎ እንደነበር አረጋግጠው፣ በወቅቱ መፈራረሙ የቀረው ስምምነት ጠፍቶ ሳይሆን፣ ለሁለት ቀናት ይደረጋል የተባለው ግምገማዊ ውይይት በአንድ ቀን እንዲያልቅ በመደረጉና ጊዜ ባለመብቃቱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ማስተር ፕላኑ አዲስ በመሆኑ መረጃ የሚፈልጉ ወገኖች እንደነበሩና ጥያቄ ማንሳታቸውን የገለጹት አቶ ዳዊት፣ አንዳንድ ግለሰቦች፣ ‹‹አዲስ አበባ ኦሮሚያን አስፋፍታ ልትይዝ ነው፣ ወደ ኦሮሚያ ምድር ልትስፋፋ ነው፤›› የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ መያዛቸው፣ ለጥያቄያቸው በቂ ምላሽ እንደተሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በበላይ አመራሮችና በቦርድ የሚመራ በመሆኑ፣ በሁሉም ነገሮች ላይ ስምምነት ላይ ተደርሶ ፕሮጀክቱ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሆነና ምንም ዓይነት ችግርና አለመግባባት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡
ልዩ ዞኖቹን ያጠቃለለውን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲዎች ተቃውመዋል፡፡ ፓርቲዎቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ‹‹ፊንፊኔ የኦሮሚያ ዋና ከተማ መሆኗ በሕገ መንግሥታችን ተደንግጎ እያለና በሕገ መንግሥት አንቀጽ 49(5) ላይ በጉልህ ኦሮሚያ ከፊንፊኔ አስተዳደር ልዩ ጥቅም ይከበርላታል በሚል ቢደነገግም፣ መንግሥት በተገላቢጦሽ በፊንፊኔ ዙሪያ ያሉትን ከተሞች በልማት ሰበብ በፊንፊኔ ሥር ለማዋል የሚያደርገው የረቀቀ ተንኮል ሕገ መንግሥቱን የሚስ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የኦሮሞ ሕዝብ ሳይወያይበት፣ ሳይመክርበትና ምክንያቱን ሳይረዳ በሁለቱ ወገኖች ውሳኔ ብቻ መደረግ ስለሌለበት ድርጊቱ በአስቸኳይ እንዲቆምም ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል፡፡
በማስተር ፕላኑ 85 በመቶ የሚሆነው መሬት ለግብርና የሚውል ሲሆን፣ 15 በመቶ የሚሆነው ለመኖርያ ቤት ግንባታ የሚውል ነው፡፡ በአጠቃላይ በማስተር ፕላኑ ክልል ውስጥ 13 ሚሊዮን ሕዝብ ይኖራል ተብሎ ሲገመት፣ ስምንት ሚሊዮኑ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ እንደሚኖሩ፣ በነበረው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እስከ 55 ፎቅ ብቻ መገንባት ይቻላል የሚለው ተነስቶ ከዚያም በላይ መገንባት እንደሚቻል ታውቋል፡፡
ማስተር ፕላኑ የሚያቅፋቸውን ልዩ ዞኖች በተለይም ከአዲስ አበባ አዳማ በተሠራውና በቀጣይም በሚሠራው ዋና መንገድ (ኤክስፕረስ ዌይ) ግራና ቀኝ ያሉ መሬቶች በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ሕገወጥ በሆነ መንገድ እየተቸበቸቡ መሆኑን ተከትሎ፣ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ መወሰኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አብዱልአዚዝ መሐመድ ትዕዛዝ ምንም ዓይነት የመሬት ሽያጭ በሕገወጥ መንገድ እንዳይካሄድ ለማድረግ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ ትዕዛዝ መተላለፉ ተገልጿል፡፡
Source: Ethiopian Reporter