Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የጃኪ ጎሲ የሰሜን አሜሪካ የሙዚቃ ኮንሰርቶች የሕግ ጥያቄዎች አሉበት፤ ይሳካ ይሆን? አላሙዲ ከጃኪ ጀርባ አለ?

$
0
0

የምነው ሸዋ ኢንተርቴይመንት ባለቤት ሸዋ ኢተና የጃኪ ጎሲን የሙዚቃ ኮንሰርት በሰሜን አሜሪካ ለማየት ለሚጠባበቁ ወገኖች ጥሪ አቀረበ። ከዚህ ቀደም የስራ ፈቃድ አውጥተንለት ወደ ሰሜን አሜሪካ እንዲመጣ ጉዳዩን ጨርሰን ኮንሰርት እስከመሰረዝ ደርሰናል፤ በዚህም ኪሳራ ደርሶብናል በሚል የሚከሰው የሸዋ ኢንተርቴይመንት በተለይም በቅርቡ ዋሽንግተን ዲሲን ጨምሮ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ድምጻዊው ኮንሰርት ያቀርባል ብለው ሰዎች ገንዘባቸውን እንዳያፈሱ ጥሪውን አቅርቧል። “ጃኪ ባለን ስምምነት መሰረት [ከሌላ ሰው ጋር] (ምንም ዓይነት ኮንሰርት) መስራት አይችልም” የሚለው ሸዋ “በጃኪ ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ ሕዝቡ እንዳያዝን” ይላል። የሸዋ ባለቤት ከኢትዮቲብ ድረ ገጽ ጋር ካደረገው ቃለ ምልልስ እናስቀንጭብዎ እና አወዛጋቢው ጃኪ በድጋሚ በማወቅም ይሁን በማያውቀው መንገድ ከሌሎች ጋር ስለመላተሙ የሚዘግበውን ጽሁፍ ከታች አቅርበናል። ከዚህ ቀደም ጃኪ ለዘ-ሐበሻ ‘ከምነው ሸዋ ጋር ምንም ስምምነት ኖሮኝ አያውቅም” ሲል መናገሩ አይዘነጋም።

የድምፃዊ ጃኪ ጎሲ ያሜሪካ ዝግጅት ለ 2ኛ ጊዜ ውዝግብ አስነሳ

ይህ በጃኪ ኮንሰርት ዙሪያ ተክደናል የሚሉ ወገኖች ያሰራጩት መረጃ ነው።

ድምፃዊ ጃኪ ጎሲ በጥቂት ነጠላ ዜማዎቹ ከፍተኛ ዝናን ያገኘ ወጣት ድምፃዊ ነው። ጃኪ ጎሲ የኢትዮጵያን ባህላዊ የአዘፋፈን ስልቶች ከዘመናዊው ሙዚቃ ጋር የሚያዋህዱ ማራኪ ስራዎቹ በህዝብ ዘንድ እጅግ ፈጣን እውቅናን አጎናጽፈውታል። ይህ ወጣት ድምፃዊ በኢትዮጵያ የሙዚቃ አለም ገና ከጅምሩ የደረሰበት ደረጃ ወደፊት ብዙ ሊሰራና ከፍተኛ ዝናን ሊጨብጥ እንደሚችል አመላካች ነው።

ከዚህ በፊት እንደሚታወቀው ድምፃዊ ጃኪ ጎሲ ከምነው ሸዋ ኢንተርቴይመንት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ውዝግብ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ይታወቃል። ጃኪ ጎሲ በ2012 በፈረንጆቹ አቆጣጠር በሰሜን አሜሪካ ሃገራት ሊያደርጋቸው የነበሩ የሙዚቃ ኮንሰርቶች በዚህ ውዝግብ ምክንያት በመሰረዛቸው ብዙ አድናቂዎቹን እንዳሳዘነ ይታወሳል።

jacki gosseeበጃኪ ጎሲ ዙሪያ ከዚህ በፊት የተፈጠረው ውዝግብ ብዙ ኢትዮጵያውያን አድናቂዎቹን ማስከፋቱ የሚያሳዝን ክስተት ሆኖ ሳለ፤ ዘንድሮም በዚሁ አርቲስት ዙሪያ በሌሎች የኢንተርቴንመንት ስራን በሚሰሩ ሁለት ድርጅቶች መካከል በድጋሚ የተፈጠረው የሚያስገርም ውዝግብ የበለጠ ህዝብን የሚያሳዝን፣ የድምፃዊውንም ስምና ዝናን የሚያጎድፍ፣ እንዲሁም በዙሪያው አብሮ ለመስራት ሽር ጉድ የሚሉትን ፕሮሞተሮች ስምና ስብእናን ከጥርጣሬ ውስጥ የሚከት በመሆኑ፤ በጉዳዩ ዙሪያ ላሉ አካላትና ለአንባቢያን ግንዛቤ ማስጨበጥ አስፈላጊ ነው።

ነገሩ እንዲህ ነው፤ ኢቫንጋዲ ፕሮደክሽንና ማሂ ፕሮደክሽን በሰሜን አሜሪካ አትላንታ ከተማ የሚገኙ ሁለት የኢንተርቴንመንት ስራን የሚሰሩ ድርጅቶች ሲሆኑ፤ የሺ ማርት ደግሞ በዚሁ በአትላንታ የሚገኝ የሃበሻ ሱቅ ነው። ድምፃዊ ጃኪ ጎሲ በሰሜን አሜሪካ ኮንሰርቶች ለማዘጋጀት ከየሺ ማርት እና ከኢቫንጋዲ ፕሮደክሽን ጋር በመሆን በጋራ ስምምነት ያደረጉ ሲሆን፤ ይህንኑ ለማስፈጸምላለፉት ሁለትአመታት ወደ ሰሜን አሜሪካ ለመግባት የሚያስችለውን ፕሮሰስ ለመጨረስ ሙከራ በማድረግ ላይ ቆይቷል። ሆኖም በኢቫንጋዲ ፕሮደክሽን አማካኝነት እየተሞከረ የነበረው የፕሮሰስ ሂደት ሳይሳካ በመቅረቱ ምክንያት፤ኢቫንጋዲ ፕሮደክሽን ከሌላ አካል እርዳታ አስፈልጎት ነበር።

በዚህም መሰረት ኢቫንጋዲ ፕሮደክሽን እዚሁ አትላንታ የሚገኘውን ማሂ ፕሮደክሽን የአርቲስት ጃኪ ጎሲን የቪዛ ፕሮሰስ እንዲያስጨርስለት በመጠየቅ፤ ስምምነት አድርጎ ነበር። ስምምነቱን ባጭሩ ለመግለጽ ያክል፤ ማሂ ፕሮደክሽን የድምፃዊ ጃኪ ጎሲን የቪዛ ፕሮሰስ ካስጨረሰ ድምፃዊው በሰሜን አሜሪካ ከሚያደርጋቸው ኮንሰርቶች ውስጥፕሮደክሽኑ በሚመርጠው አንድ ቦታ ላይ ድምፃዊ ጃኪን ሊያሰራ፤ ኢቫንጋዲ ፕሮደክሽንም ቃሉን አክብሮ ይህንኑ ሊያስፈጽም ነበር።

እንደ ማሂ ፕሮደክሽን መረጃ ከሆነ በዚህ ስምምነት መሰረት ማሂ ፕሮደክሽን የድምፃዊ ጃኪ ጎሲን የቪዛ ፕሮሰስ አስጨርሶ ድምፃዊው ወደ ሰሜን አሜሪካ የሚያስገባውን ቪዛ በእጁ እንዲገባ አድርጓል። ነገር ግን ኢቫንጋዲ ፕሮደክሽን የገባውን ቃል አክብሮ መፈጸም ሲገባው፤ ማሂ ፕሮደክሽን ያደረገውን ውለታ እንደማያውቅና የድምፃዊ ጃኪ ጎሲ የቪዛ ጉዳይ ያለቀው በሼክ ማሃሙድ አል አሙዲን በኩል እንደሆነ በመናገር ላይ ይገኛል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ማሂ ፕሮደክሽን በተፈጠረው ሁኔታ ስለተበሳጨ ጉዳዩን ወደ ፍርድቤት ለመውሰድ በዝግጅት ላይ እንደሆነ ይናገራል።

(ከዚህ ቀደም የተሰረዘው የጃኪ ኮንሰርት ፍላየር)

(ከዚህ ቀደም የተሰረዘው የጃኪ ኮንሰርት ፍላየር)

እዚህ ላይ በጣም የሚገርመው ጉዳይ ድምፃዊ ጃኪ ጎሲ በኢቫንጋዲ ፕሮደክሽንና በማሂ ፕሮደክሽን መካከል ስምምነቱ ሲደረግና የቪዛ ጉዳዩ ያለቀው በማሂ ፕሮደክሽን በኩል መሆኑን እያወቀ ችላ በማለቱ ምክንያት ለሁለተኛ ጊዜ ውዝግብ ውስጥ መግባቱ ነው። ጥፋተኛው ማንም ሆነ ማን፤ የዚህ ፅሁፍ ዋናው አላማ ድምፃዊ ጃኪ ጎሲን ጨምሮ ሶስቱም አካላት ውዝግቡ የሚያስከትለውን መዘዝ ከወዲሁ ተገንዝበው በቶሎ መፍትሄ እንዲያበጁለት በአፅንዖት ለማስገንዘብ ነው።

በመጨረሻም ፅሁፋችንን ላነበቡና ሃሳባችንን ለተጋሩ ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋናችንን እያቀረብን፤ የምንሰናበተው ይህንን ጎጂና ደስ የማይል ውዝግብ በተመለከተ፤ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት የሚሰጡትን መልስ ጨምሮ፤ ሰፋያለ መረጃ በቅርቡ ይዘን እንደምንቀርብ ቃል በመግባት ነው::
——————————–

አንባቢያንስ ምን ትላላችሁ? ይህ ተወዳጅ ድምጻዊ እንደዚህ ያሉ ውዝግቦች ውስጥ መግባት ነበረበት ወይ? አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ካወጣው 4 ዘፈን አኳያ ይህ ሁሉ ነገር ይገባዋል ወይ? በሌሎች ወገኖች እንደሚከሰሰው አላሙዲ ጋር ስሙ መያያዙ በልጁ የወደፊት ሥራ ላይ የሚፈጥረው ነገር ይኖራል? አስተያየታችሁን ጻፉት።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles