ሕዝቡ ከዳር እስከዳር በምሬት ተነስቶ በወያኔ ላይ የሚሰነዝረውን ጡጫ እያበረታ ነው:: ወያኔም በበኩሉ “ተመጣጣኝ ርምጃ” በሚለው ጥቃት በርካታ ዜጎችን ተኩሶ እየጣለ ነው:: ለአመታት ተደክሞ በብዙ ወጪ የተገነቡ ፋብሪካወችና ድርጅቶች በአንድ ቀን እሳት እንዳልነበሩ እየሆነ ነው:: ልቡ በክፋት ለተደፈነው ወያኔ ይህ ሁሉ የሚያሳስበው አይመስልም:: እንዲያውም አለመረጋጋቱን አጥብቆ የሚፈልገው ይመስላል:: የወያኔ አውራወች ችግሩን የሚያባብስ ርምጃ ሲወስዱ እንጅ መፍትሄ ለመፈለግ ሲሰሩ አይታዩም:: እንቅስቃሴው የፈጠረው አንድ በጎ ነገር ቢኖር ወዲያና ወዲህ ሆነው በጠላትነት እንዲተያዩና እንዲጠፋፉ ሸር ሲጎነጎንባቸው የነበሩ ጎሳወች ልዩነታቸውን አጥብበው: ጥላቻቸውን ፍቀው በአንድነት መሰለፋቸው ነው:: ለብዙ አመታት ፊት ተዟዙረው የነበሩት ስልጤወችና ጉራጌወች ይቅር ተባብለዋል:: በጥርጣሬ ይተያዩ የነበሩት ኦሮሞወችና አማራወች “በወያኔ ተንኮል ነቅተናል!” ብለው እጅ ለእጅ ተያይዘው በአንድነት ቆመዋል:: ይሁን እንጅ የወያኔ ቅጅ የሆነው ኦነግ (በስም ብዙ በባህርይ ግን አንድ የሆኑ የኦሮሞ ድርጅቶች) የሚባለው ድርጅት ሰዎች ይህን የሕዝቦች አንድነት አጥፍተው በምትኩ ክፍፍልን እና ጥላቻን ለመትከል ከፍተኛ ደባ እየፈጸሙ ነው::
አቶ ጃዋር መሀመድ ሰሞኑን የተናገረው ነገር በጣም የሚረብሽ ነው:: ይህን ሰው ባልተገራ አንደበቱ ምክንያት ብዙወች ይንቁታል:: የሚናገራቸው ነገሮች የተቀመጠበትን የሀላፊነት ቦታም ሆነ የአንድ ጤነኛ ሰው ባህሪን የሚመጥኑ እንዳልሆነ ነው የሚነገረው:: ጃዋር የክርስቲያኖቹን አንገት ለሜንጫ ከተመኘ ጀምሮ በብዙወች ዘንድ ጥላቻን ያተረፈ ሰው ሆኗል:: ይህ ሰው የፖለቲካ ድርጅት አባል እንዳልሆነ ይናገራል:: ይሁን እንጅ የሚያራምደው ሀሳብ ያለጥርጥር ደም ከጠማቸው የኦነግ አባላት ውስጥ አንዱ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው::
ኦነግ የወያኔን እና የሻእቢያን እቅድ ለማስፈጸም በመቆም እጅግ ብዙ አማራውችን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለ ሀላፊነት የማይሰማው አሸባሪ ድርጅት ነው:: በንጹሀን አማሮች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ መቸም ቢሆን ታሪክ የሚዘነጋው አይሆንም:: አማራወች በኦሮሞወች ላይ ከ120 አመት በፊት ፈጽመውታል በተባለው በሬ-ወለድ ጭፍጨፋ መነሻ በዚህ በሰለጠነ ዘመን የአሁኑን አማሮች በበቀል የፈጀ እጅግ የተበላሸ ኋላቀር ድርጅት ነው:: ይህ በሻእቢያ እገዛና ኢትዮጵያን እንደሀገር ማየት በማይፈልጉ ሀይሎች የተቋቋመው ድርጅት የሀገራችንን ታሪክ ለማበላሸት እና አንድነቷን አደጋ ላይ ለመጣል እረፍት አጥቶ ግፍ ሲፈጽም ኖሯል:: ለኤርትራ መገንጠል: ለኢትዮጵያ ታሪክ መጉደፍ: በኢትዮጵያውያን መሀል ልዩነት እና ጥላቻ ስር መስደድ: ለአማሮች መጨፍጨፍ እና ሀገራችን ለጥቃት ተጋላጭ እንድትሆን በማድረግ በኩል ጉልህ ድርሻ አበርክቷል:: ኦነግ ዛሬም እንኳ ከጥፋቱ ሊመለስ የማይፈቅድ ድርጅት መሆኑን በአቶ ጃዋር በኩል አስረግጦ እየነገረን ነው::
አቶ ጃዋር የፖለቲካን ሀ – ሁ ሳይረዳ የፖለቲካ ተንታኝ እና አክቲቭስት የሚል ስም የተሰጠው አፉ እንዳመጣ የሚናገር ያልበሰለ ሰው እንደሆነ ብዙወች ይስማማሉ:: ለነገሩ ኦነግ ውስጥ ምራቁን የዋጠ አስተዋይ ሰው ማግኘት ከባድ ሳይሆን አይቀርም:: አቶ ጃዋር ስለኦሮሚያ የሽግግር ጊዜ ሰነድ ሲያወራ: ስለኦሮሚያ ከፖለቲካ ነጻ የሆነ የጦር ሰራዊት ምስረታ ደረቱን ነፍቶ ሲናገር የኦሮሚያን ነጻ ሀገር አይቀሬነት እያረጋገጠልን መሆኑ ነው:: ይህ ግለሰብ የኦነግን ትንፋሽ ሳይይዝ በራሱ ጊዜ ፈጥሮ ያወራል ማለት አይቻልም:: ኦነግ አሁንም የኢትዮጵያን ሕዝብ መጠፋፋት እያወጀልን ነው:: በሰላምና በፍቅር አብሮ የኖረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በሸር ለያይቶ በመሬት ይገባኛል ጥያቄ እርስ በርስ ሊያጫርስ በጽናት ቆሟል:: አቶ ጃዋር የተናገረው ነገር በተሳሳተ መልኩ እንደተተረጎመ አድርጎ በዘሀበሻ ላይ ጽፎ ያስነበበን ጽሁፍ ያንኑ የኦነግን አላማ በድጋሚ የሚያረጋግጥ ነበር:: ደስ ሲላቸው የብሔር-ብሔረሰቦች መብት የሚከበርባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በጋራ መስርተን በአንድነት እንኖራለን የሚሉት ኦነጎች ብዙም ሳይቆዩ ‘በኢትዮጵያ ውስጥ እንቀጥል ወይስ የራሳችን ሀገር እንመስርት?’ በሚለው ጉዳይ ላይ የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ነው ሊወስን የሚችለው ብለው እውነተኛ ፍላጎታቸውን ያወጡታል:: አቶ ጃዋር ስለመከላከያ ሰራዊት ምስረታ ሲያወራ ምን ለማለት እንደፈለገ የማይገነዘብ ሰው አይኖርም:: በክልል ወይም በክ/ሀገር ወይም በአካባቢ በአንዲት ፌደራላዊት ሀገር ውስጥ ከሌሎች ጋር አብሮ የሚኖር ሕዝብ የአካባቢ ፖሊስ እንጅ መከላከያ ሰራዊት ሊኖረው አይችልም:: መከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ በሀገር ደረጃ የሚቋቋም ወታደራዊ ሀይል ነው::
የ1997 ዓ.ም ሀገር አቀፍ እና ክልላዊ ምርጫን ተከትሎ ቅንጅት አሸንፏል ብለው ያመኑት የተቃዋሚ ኃይሎች ሕብረት አመራሮች ለዴሞክራሲያዊ ስርአት የሚታገሉ መሆኑን እረስተው በምርጫ ውድድር ያሸነፈው ቅንጅት ላይ ዘምተው እንደነበር የሚረሳ አይደለም:: በውድድር ያሸነፈውን ስልጣን ትቶ ሁሉንም የሚጋብዝ የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት በቅንጅት ላይ ጫና ሲያደርጉ የነበሩት ተቃዋሚወች ፍላጐታቸው የተከፈተው የሰላማዊ እና የዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ስርአት እውን በመሆኑ ተደስተው ዴሞክራሲያዊ ስርአቱ እንቅፋት እንዳይገጥመው በመከላከል ወደተሻለ የእድገት ደረጃ እንዲሸጋገር ለማገዝ ሳይሆን ስልጣን ለመጋራት ነበር:: ማንም ይሁን ማን በሕዝብ እስከተመረጠ ድረስ የሕዝብን ውሳኔ አክብሮ መቀበል የዴሞክራሲያዊ ስርአቱ አንድ መገለጫ መሆኑን ረስተው በሕዝብ ፈቃድ የተመረጠው ቅንጅት ላይ የጥላቻ እና የምቀኝነት ዘመቻ ሲያካሂዱ ወያኔን ጭራሽ እንደሞተ ቆጥረውት ነበር:: ከዚህ ሁሉ በኋላ ሞቷል ተብሎ የታሰበው ወያኔ በራሱ መንገድ ተጉዞ ሁሉንም በሚፈልገው መልክ ሲያስተካክል ተቃዋሚ ድርጅቶች ከርስ በርስ ንክሻ ወጥተው እንደለመዱት በየፊናቸው በወያኔ ላይ መጮህ ጀመሩ::
የዛሬው የኦነግ የጦር ሰራዊት ምስረታ ዕቅድ የመነጨውም ወያኔ እየሞተ ነው ከሚለው የተሳሳተ ስሌት የተነሳ ነው:: አሁን በየአካባቢው እየተደረገ ያለው አመጽ የወያኔን ቀብር አቅርቦታል ብለው ያመኑት ኦነጎች እውነተኛውን ፍላጎታቸውን አውጥተው ኦሮሚያን ብቻ የሚመለከት የሽግግር መንግስት ምስረታ ሰነድ ለማዘጋጀት እና የመከላከያ ሰራዊት ለመገንባት እየተዘጋጁ እንደሆነ እየነገሩን ነው:: ይህ አካሄዳቸው ትግሉን ምን ያህል ሊጎዳው እንደሚችል የተገነዘቡት አይመስልም:: በመጀመሪያ ደረጃ ወያኔ እነርሱ እንደሚያስቡት ሊሞት በጣዕር ላይ ያለ ድርጅት አይደለም:: ሌላው ደግሞ ወያኔ ‘ጉድጓዱ የተማሰ ልጡ የተራሰ’ ነው ብለን ብናስብ እንኳ የኦሮሚያ መንግስት ምስረታ ሀሳብ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ ፍቱን መፍትሄ አይደለም::
በየጊዜው እንደምናየው በኦሮሚያ የሚደረጉ የሕዝብ አመጾች የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ሳይሆን የኦነግን ባንዲራ በመያዝ የሚደረጉ ናቸው:: የኦነግ ሰዎች ሲያወሩ ኢትዮጵያን እና ኦሮሚያን ለያይተው ነው:: ሌሎቻችንም ብንሆን ይህን አባባል የለመድነው ይመስላል:: ኢትዮጵያውያን እና ኦሮሞወች በየተቃውሞ መድረኩ የየራሳቸውን ባንዲራ ይዘው ጐን ለጐን ሲሰለፉ እያየን ነው:: ኦነግ የኦሮሚያን ካርታ ካወጣ ብዙ አመታትን አስቆጥሯል:: የኦሮሚያን የሽግግር መንግስት ሰነድ ለማርቀቅ እና የመከላከያ ሰራዊት ለመገንባት እንደታቀደም እየሰማን ነው:: የቀረው የወያኔን ውድቀት ተከትሎ የኦሮሚያን ነጻነት ማወጅ ብቻ ነው::
“ብቻ ወያኔ ይውደቅ” የሚሉ ኢትዮጵያዊያኖች የኦነግን አደገኛና አፍራሽ አካሄድ እየተገነዘቡ አይመስልም:: ይህ የተዛባ አመለካከት በፍጥነት ሊታረም ይገባል:: መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የኦነጎችን እና የወያኔን አፍራሽ እንቅስቃሴ በእኩል በንቃት በመከታተል የሚሸርቡትን ሴራ ማክሸፍ ይኖርበታል:: የኦነግ ያፈጠጠ ፍላጎት ኦሮሚያን ከኢትዮጵያ መገንጠል ነው:: ይህ የመገንጠል መዘዝ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መሀል ከፈጠረው ውድመት ሽህ ጊዜ ለሚበልጥ ጉዳት የሚዳርግ: ክልሉን የጦር ቀጣና ለማድረግ በሚያስቡ ታሪካዊ ጠላቶቻችን የተሰላ ተንኮል ነው:: ከኢትዮጵያ የመቶ አመት የቤት ስራ ውስጥ አንዱ የሆነው የኦነግ እንቅስቃሴ ካልተነቃበት ሊታረም የማይችል ጥፋት የሚያስከትል ይሆናል::
አንዳንድ የአማራ አክቲቭስቶች የኦነግን የነጻ ሀገር ምስረታ ፍላጎት እንደአደጋ አለማየታቸው ገርሞኛል:: ለመሆኑ ኦነግ ነጻ ኦሮሚያን እንደሀገር መመስረት ቢፈልግ የቱን ይዞ የቱን ትቶ ነው? አማራው ራሴን ችየ ሀገር እመሰርታለሁ ቢልስ የትኛውን የሀገሪቱ አካባቢ ይዞ ነው:: “ብቻ ወያኔ ይውደቅ!” የሚለው አባባል ፍጹም የተሳሳተ ነው:: ኦነግ የራሱ ካርታ እንዳለው ከዚህ በፊት ባወጣቸው ሰነዶች ላይ አይተናል:: ኦሮሞወች ነጻ ሀገር ለመመስረት ከፈለጉ ይህን ፍላጎታቸውን ማንም ሊያዳፍነው አይችልም ብለው የሚሉት ሰዎች ምን እያሰቡ ነው? በዚህ ሰነድ ላይ ተስማምተዋል ማለት ነው? ወይስ የኦነግን ጉዳይ በይደር ትተን ወያኔን ከስጣልን ካስወገድን በኋላ እንመለስበታለን ተብሎ ታስቦ ነው?
ከኦነግ ጀርባ የተሰለፈ ጠንካራ ኃይል መኖሩ መዘንጋት የለበትም:: አሁን እየተደመጠ ያለው የግብጽ መንግሥት ለኦነግ ማንኛውንም ድጋፍ ለማድረግ ቃል እንደገባ ነው:: ግብጽ የኢትዮጵያን መዳከም እና መከፋፈል አጥብቃ የምትፈልግ መቸም ቢሆን የማትተኛልን ታሪካዊ ጠላታችን ናት:: ኦነግ ስለወደፊቱ መጨነቅ የሚፈልግ ድርጅት አይደለም:: ወያኔ በበኩሉ ለብዙ ሽህ አመታት ኢትዮጵያን በደምና በአጥንቱ አስከብሮ ያቆየውን የአንድነት ኃይሉን አከርካሪ መስበሩን በኩራት ነግሮናል:: በዚህ የዱርየ ስራቸው የሚኩራሩት የወያኔ አመራሮች የአንድነት ተሟጋቾችን አዳክመው ሀገራችንን ለጥቃት ማጋለጣቸውን የሚያስተውሉበት ዐዕምሮ ያልታደሉ መሆናቸውን አስመስክረዋል:: ወያኔ ብሔር-ብሔረሰቦችን ለማፈን ከላይ ያስቀመጣቸውን የድርጅት አመራሮች እና ሰራዊቱን ተማምኖ ሕዝብን ንቋል:: በበብሔር-ብሔረሰቦች መሀል መተሳሰብ እንዳይኖር አድርጎ በመሀከላቸው የጥላቻ ዘር ሲዘራ ኖሯል:: ከአማራ ክልል እና ከአፋር ክልል ቆርሶ በጉልበት ወደትግራይ በማካለሉ ከአጐራባች ክልሎች ጋር ጠብ ፈጥሯል:: ኢትዮጵያ ብትፈራርስ ወያኔም ሆነ የትግራይ ሕዝብ እንዴት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ አይታወቅም:: “ብልህ የአመቱን ሞኝ የእለቱን” የሚለው አባባል ጊዜው አልፎበት በአዲሱ ፋሽን ሁሉም የእለቱን ናፋቂ ሆኗል:: ነገ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን እያሉ የሚጨነቁ ሰዎች ግን አልጠፉም:: አንዳንዴ ለምኑም ግድ የሌላቸው ሰዎች ያስቀናሉ:: ዞሮ ዞሮ በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ላለውና ወደፊት ለሚመጣው ችግር በዋናነት ተጠያቂው ትግራይ-ወለዱ ወያኔ ነው::
የሰው ልጅ ትልቁ ጥንካሬ ተስፋ ነው:: እና አሁንም ከችግር የመውጫ መንገዶች ጨርሰው አልተዘጉም ብለን ተስፋ እናድርግ:: የአንዳንድ ሀገር ወዳድ ወገኖች የመንፈስ ጥንካሬ የሁላችንም ተስፋ ነው:: ስለሀገር እና ስለሕዝብ አብዝተው የሚጨነቁ ሰዎች ደከመን ሰለቸን ሳይሉ መፍትሄ ለማምጣት የሚያደርጉት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት:: ያለፈውን እና አሁን ያለውን ሁኔታ ገምግሞ የወደፊቱን ለመተንበይ ለአንዳንዶቻችን ከባድ ሊሆን ይችላል:: እኔ እራሴ ደርግ ከወደቀ በኋላ እንኳ የደርግን ውድቀት አምኘ መቀበል አቅቶኝ ከዛሬ ነገ ተመልሶ ይመጣል እያልሁ ሳስብ ነበር:: የወቅቱን ሁኔታ በጥሞና መገምገም ለቻለ ኢትዮጵያን የገጠማት ፈተና እጅግ ከባድ መሆኑን ይረዳል:: አይመጣም ያልነው የሚመጣበት አይሆንም ያልነው የሚሆንበት ብዙ አጋጣሚ አለ:: ፈረንጆች Expect the worst የሚሉት ለቀልድ ሳይሆን መጥፎ አጋጣሚ ከመጥፎ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ከመልካም ሁኔታ መሀልም ሊከሰት እንደሚችል ግንዛቤ ተይዞ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ሲመክሩ ነው:: ስለዚህ እያንዳንዷን ርምጃ በጥንቃቄ ካልተራመድናት በሆይ ሆይታ የሚደረግ ጉዞ ከድጡ ወደማጡ ሊከተን ይችላል:: የሚያሳስበን የአሁኑ ችግር ብቻ ሳይሆን የወደፊት ኑሯችንም ጭምር ነው::
ትንሳኤ ለኢትዮጵያ!