አቶ ልደቱ አያሌው፣ የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) መሥራች
አቶ ልደቱ አያሌው የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) መሥራች ናቸው፡፡ ኢዴፓን ለበርካታ ዓመታት የመሩት አቶ ልደቱ በአወዛጋቢው ምርጫ 97 የኢሕአዴግ ብርቱ ተፎካካሪ በነበረው የአራት ፓርቲዎች ጥምረት ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ በፓርቲያቸው ተወክለው ባሳዩት አመራር ዝናቸው ጫፍ ደርሶ ነበር፡፡ ይሁንና ከምርጫው በኋላ የቅንጅት አመራሮች ሲከፋፈሉ አቶ ልደቱ ላይ የተሰነዘሩት ወቀሳዎች ተቀባይነታቸው ላይ ጥያቄ እንዲነሳባቸው አድርገው ነበር፡፡ አቶ ልደቱ በእሳቸውና በፓርቲያቸው ላይ የቀረበው ወቀሳ አሉባልታ እንጂ ተጨባጭ መረጃና ማስረጃ የሚቀርብበት ሀቅ እንዳልሆነ በሚጽፏቸው መጻሕፍትና መጣጥፎች፣ ለተለያዩ ሚዲያዎች በሚሰጧቸው ቃል ምልልሶች ሲሞግቱ ቆይተዋል፡፡ አቶ ልደቱ እስከ 2003 ዓ.ም. በኢዴፓ ፕሬዚዳንትነታቸው በፖለቲካው መድረክ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ቢቀጥሉም፣ ከዚያ በኋላ ግን በመድረኩ ላይ ብዙም አይታዩም፡፡ የኢዴፓ መሪነቱን ለአቶ ሙሼ ሰሙ ያስረከቡት አቶ ልደቱ በእንግሊዝ ለንደን ዩኒቨርሲቲ በዴቨሎፕመንት ስተዲስ የማስተርስ ዲግሪ አጠናቀዋል፡፡ ከዚያ በፊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ ከእንግሊዝ መልስ ‹‹ቲያትረ ፖለቲካ›› በሚል ርዕስ ባለፈው ዓመት መጽሐፍ ማሳተማቸውም ይታወሳል፡፡ ‹‹በሕይወት እስካለሁ ድረስ ራሴን ከፖለቲካ ማግለል ፈጽሞ አይታሰብም!›› የሚሉት አቶ ልደቱ፣ የኢዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ባይሆኑም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በመሆን አሁንም የሚጠበቅባቸውን ተግባር እየተወጡ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ኢሕአዴግ የሠራውን በጎ ተግባር ዕውቅና በመስጠት እንዲሁም ያጠፋውንና ድክመት ያሳየበትን ጉዳይ በግልጽ በመጠቆም የሚተነትኑት አቶ ልደቱ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገዥው ፓርቲ ዋነኛ አጀንዳ የሆነው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ የሚሰማቸውንም አካፍለዋል፡፡ ሰለሞን ጎሹ በወቅታዊ ጉዳዮችና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ አቶ ልደቱን አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የመልካም አስተዳደር ችግር በስፋትና በጥልቀት የአገሪቱን ህልውና እየተፈታተነ ነው የሚል ግምገማ በራሱ በመንግሥት ቀርቧል፡፡ ብዙ የኅብረተሰብ ክፍሎችም በዚህ ይስማማሉ፡፡ ዋነኛው የልዩነት ምንጭ የችግሩ መነሻ ምንድነው የሚለው ነው፡፡ በእርስዎ ግምገማ የዚህ መጠነ ሰፊ ችግር ዋነኛ ምንጭ ምንድነው?
አቶ ልደቱ፡- አንዱ መግባባት ያቃተን በችግሩ ክብደት ላይ ነው፡፡ ኢሕአዴጎች እንደተባለው ችግሩ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ በከፍተኛ ዘመቻ ችግሩን ለመፍታት ቆርጠን ተነስተናል እያሉ ነው፡፡ በተቃዋሚዎች ዘንድና በአንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይኼ እንደ እውነት አልተወሰደም፡፡ ኢሕአዴግ እንደተለመደው ዘመቻ መልክ ቴአትር አሳይቶ የሚተወው የማስመሰያ እንቅስቃሴ ነው የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ እኔ ኢሕአዴግ ይኼ ችግር የህልውና ጉዳይ ነው፣ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው ብሎ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የቀልድ ነው ብዬ አላምንም፡፡ የምር ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ኢሕአዴግ የምር እየተንቀሳቀሰ ያለው ይኼ ችግር ሳይፈታ ከቀጠለ የሥርዓቱን ህልውና እንደሚፈታተንና አደጋ ላይ እንደሚጥለው ስለገባው ይመስለኛል፡፡ ሥርዓቱ ላይ ያለው አንዱም ችግር ይኼ ነው፡፡ ችግሮች ሳይጠነክሩ፣ ሳይሰፉና ሥር ሳይሰዱ ለሕዝብና ለአገር ጥቅም ሲባል በተገቢው ወቅትና ሁኔታ መፈታት ሲገባቸው፣ አንዳንድ ጊዜ ዘመቻዎቹ ጠንከር ብለው የሚመጡት በራሱ ህልውና ላይ ችግሩ ሲመጣ ነው፡፡ ይኼ ችግር የሥርዓቱን ህልውና ብቻ አይደለም የሚፈታተነው፡፡ አጠቃላይ የአገር ጥቅምና ደኅንነትን የሚፈታተን ጉዳይ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ማየት የነበረበት ከአገር ጥቅም እንጂ ከራሱ ጥቅምና ደኅንነት አንፃር መሆን አልነበረበትም፡፡ ዞሮ ዞሮ በዚህ ጉዳይ ላይ ኢሕአዴግ እየቀለደ አይደለም፡፡ እርግጥ በኢሕአዴግ በኩል መልካም አስተዳደር ምንድነው በሚለው ጉዳይ ላይ ልዩነት አለ፡፡ ከተለያዩ መድረኮች እንደተረዳነው በኢሕአዴግ አስተሳሰብ መልካም አስተዳደር የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ወደ መንግሥት ቢሮዎች አገልግሎት ፈልጎ ሲሄድ የሚገጥመው ውጣ ውረድና የመጉላላት ችግር ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡ በእርግጥም ይኼ አንዱ የመልካም አስተዳደር ችግር መገለጫ ነው፡፡
ነገር ግን መልካም አስተዳደር የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄም ነው፡፡ በአጠቃላይ የመንግሥትንና የሕዝብን ግንኙነት የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ በምርጫ አማካይነት ከሕዝብ ጋር የገባውን ውል መንግሥት በአግባቡ እየተወጣ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ጥያቄ ነው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ፡፡ ገዥው ፓርቲ ግን የመልካም አስተዳደር ጥያቄን በዋናነት ከኢኮኖሚ ጉዳይ ጋር አስተሳስሮ ያያል፡፡ በዚህ መልኩ የሚደረግ ዘመቻ ችግሩን ከምንጩ ያደርቃል ብዬ አላምንም፡፡ ሁለተኛ በዚህ ጠባብ ማዕቀፍም ውስጥ ቢሆን የችግሩ መሠረታዊ ምንጭ ምንድነው የሚለው ላይ በግልጽ ውይይት ሲደረግበት አይታይም፡፡ እርግጥ ችግሩ ምን ያህል ከባድ እንደሆነና በሁሉም የአገሪቱ አካባቢ ያለ መሆኑ ላይ የፖለቲካ አመራሩ ስምምነት ላይ የደረሰ ይመስላል፡፡ ለምንድነው ይኼ ሥርዓት በዚህ መጠንና ሁኔታ የመልካም አስተዳደር ችግር ውስጥ የተዘፈቀው ብሎ መሠረታዊ የሆነውን ምክንያት ማወቅና ችግሩን ከምንጩ የማድረቅ አቅጣጫ ግን አይታይም፡፡ እኔ ከዚህ በፊት በጋዜጣችሁ ላይ ይኼ ዘመቻ የሚከሽፍ መሆኑ ከወዲሁ የታወቀ ነው ብዬ ለመደምደም ያስገደደኝ ይኼ ምክንያት ነው፡፡ ለእኔ ምንጩ የፖለቲካ ሙስና ነው፡፡ የኢኮኖሚ ሙስናው የፖለቲካ ሙስናውን ተከትሎ የመጣ ነው፡፡ ሥርዓቱ ለፖለቲካ ሥልጣን የበላይነት ብሎ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ሙስና የሚፈጽም በመሆኑ የኢኮኖሚ ሙስናው ይኼን ተከትሎ የመጣ ነው፡፡ በቢሮክራሲው ውስጥ የሚቀጠሩት ሰዎች በሙያ ብቃታቸው፣ በትምህርት ደረጃቸውና በሥነ ምግባራቸው አይደለም በዋናነት የሚመለመሉት፡፡ በዋናነት የሚቀጠሩት ለሥርዓቱ ባላቸው ታማኝነት ነው፡፡ ይኼ የፖለቲካ ውሳኔ ነው፡፡ የፖለቲካ ሙስናም ነው፡፡ ከሚኒስትር ጀምሮ እስከ ጥበቃና ፅዳት ሠራተኛ ድረስ ሰዎች የሚቀጠሩት በፖለቲካ ታማኝነታቸው ነው፡፡ የአገሪቱን ቢሮክራሲ የሚያመርቱት ዩኒቨርሲቲዎች ሲመረቁ ሳይሆን ገና ሲገቡ ነው ተማሪዎቹ የኢሕአዴግን የመታወቂያ ካርድ በእጃቸው የሚይዙት፡፡ ምክንያቱም በሥራ የመቀጠር ዋስትናቸው እሱ ነው፡፡ በዚህ መልኩ በፖለቲካ ሙስና የተሰባሰበ ቢሮክራሲ የኢኮኖሚ ሙስና ቢፈጽምና የመልካም አስተዳደር ችግር ውስጥ ቢዘፈቅ የሚደንቅ አይደለም፡፡
አንድ ሥርዓት የፖለቲካ የሥልጣን የበላይነቱን ለማስጠበቅ ብሎ ምርጫን የሚያጭበረብር ከሆነ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚያፍን ከሆነ፣ የሕዝብን ሰብዓዊ መብት የሚያፍን ከሆነ፣ የፕሬስ መብትን የሚያፍን ከሆነ፣ ይህን የሚያደርገው በካድሬዎቹ አማካይነት ነው፡፡ አባላቱ እንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ሙስና ሲፈጽሙ የማይቀጣ መንግሥት የኢኮኖሚ ሙስና ሲፈጸም ሊደንቀው አይገባም፡፡ በተለይ በዝቅተኛ እርከን ላይ ያሉ ካድሬዎች ናቸው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ዳታ የሚያዘጋጁት፡፡ የሚቀርበው ዳታ አለቆችን የሚያስደስት እንጂ እውነታውን የሚያንፀባርቅ አይደለም፡፡ የበላይ አመራሮች የሚቀርብላቸውን ዳታ እንዳለ በግርድፉ ከመቀበል ይልቅ ዳታ ኦዲት ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ለዓመታት ተከራክሬያለሁ፡፡ ይህ እንደ ጠቃሚ ሐሳብ አሁንም ድረስ አይወሰድም፡፡ እኔ ከ20 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሳትፎ ቢኖረኝም ይህ ካድሬ ይህን የፖለቲካ ሙስና ፈጽሟል ተብሎ ዕርምጃ ሲወሰድበት አላየሁም፡፡ አባላቱን ለመቅጣት አለመፈለግ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ጊዜ እነዚህ የፖለቲካ ሙስናዎች በመንግሥት ትዕዛዝ የሚፈጸሙ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በቢሮክራሲው ውስጥ የተሰባሰበውን ካድሬ ካየህ የሕዝብ አገልግሎትን አጀንዳ አድርጎ የተሰበሰበ ኃይል አይደለም፡፡ በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ በኢሕአዴግ ዙሪያ የተሰበሰበው ኃይል ጥቅም ፈላጊ ኃይል ነው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ሙስናን ስትዋጋ የኢኮኖሚ ሙስናን ማድረቅ አትችልም፡፡ ስለዚህ ይህን ችግር ለመቅረፍ መሠረታዊና ሥር ነቀል የሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት ማንነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህ ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፍትሐዊነት የአገሪቱን ሀብትና ሥልጣን ማከፋፈልን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ነገር ግን ይኼ አቅምን መሠረት ካደረገ ቢሮክራሲ ጋር አብሮ ይኼዳል?
አቶ ልደቱ፡- መሠረታዊው ነገር በአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ በቋንቋና በዘር ማንነታቸው ካደራጀህ ሌሎች ለሥራ፣ ለአስተዳደርና ለኢኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ሁሉ ወደ ጎን ይገፋሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር ከዚሁ የሚመነጭ ነው፡፡ ሰዎች ወደ አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት አገልግሎት ፈልገው ሲሄዱ ምን ዓይነት ተቋም አለ? ምን ዓይነት ሕግ አለ? ብለው አይደለም የሚሄዱት፡፡ ማን አለ? ብለው ነው የሚሄዱት፡፡ የራሴ የሚሉትን ሰው ነው ፈልገው የሚሄዱት፡፡ ይኼ በአብዛኛው የሚመዘነው በዘር ማንነትና በፖለቲካ አመለካከት መቀራረብ ነው፡፡ ይኼ ዜጎች በእኩል ዓይን የማይታዩበትን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ እኛና እነሱ የሚል አስተሳሰብ በየመንግሥት ተዋረድ ባሉ መዋቅሮች ውስጥ ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ምክንያት በተለይ በገጠር ወደ መንግሥት መዋቅር የሚመጣው ትምህርትና እርሻ ጠል የሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ በከተማም አብዛኛው ወደ መንግሥት መዋቅር ገብቶ ሲሠራ የምናየው ሰው መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥሮ መሥራት የማይችል፣ ወይም በግሉ ካፒታል ኖሮት መነገድ የማይችል፣ ወይም በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ መሥራት የማይችል ሰው ነው፡፡ እዚያ ውስጥ የሚገባው ለኑሮዬ የሚበቃ ጥቅምና ደመወዝ አገኛለሁ ብሎ ሳይሆን የሕግና የአሠራር ክፍተቶችን ተጠቅሜ ከኅብረተሰቡ ጉቦና የተለየ ጥቅም ተቀብሎ ኑሮዬን እደጉማለሁ ብሎ ነው፡፡ ሥርዓቱ የራሱን የፖለቲካ የበላይነት ለማስጠበቅ ታማኝ የሆነ፣ ጥያቄ የማይጠይቅና ታዛዥ የሆነ ቢሮክራሲ ነው መሰብሰብ የሚፈልገው፡፡ መንግሥት ይህን ችግር ለመዋጋት የሚያደርገው ጥረት ሁሉ በራሱ መዋቅር ተሸናፊ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ራሱን በራሱ ነው የሚታገለው፡፡
ሪፖርተር፡- አንዳንድ የፌዴራሊዝም ምሁራን ግን ማንነትን መሠረት ያደረገ የፌዴራል ሥርዓት አቅምን መሠረት ያደረገ ቢሮክራሲ ለማዋቀር ችግር እንደማይፈጥር ይከራከራሉ፡፡ የብሔር ተዋፅኦው እንዳለ ሆኖ በእዚያው ብሔር አባላት መካከል አቅምን መሠረት ያደረገ ምልመላ ማድረግ ይቻላል ሲሉም ይጠቁማሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ይስማማሉ?
አቶ ልደቱ፡- ይኼ አስተሳሰብ ችግር ውስጥ የሚገባው በክልሎች ደረጃ ነው፡፡ ለምሳሌ በአማራ ክልል በየቢሮክራሲው ተቀምጦ የመልካም አስተዳደር ችግር እየፈጠረ ያለው ከሌላ ብሔር የመጣው ሳይሆን ራሱ አማራው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በፌዴራል መንግሥት ደረጃስ?
አቶ ልደቱ፡- ችግሩ ሕዝቡን በማማረር ላይ ያለው በፌዴራል ደረጃ ነው? ከሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር የተገናኘው ችግር እየተፈጸመ ያለው በክልሎች ደረጃና ከሕዝቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባለው ቢሮክራሲ ነው፡፡ እላይ ያሉት ችግራቸው ተገቢ የሆነ የአሠራር ሥልት ዘርግተው ይህ የመልካም አስተዳደር ችግር መጀመሪያውኑ እንዳይስፋፋ አላደረጉም፡፡ መስፋፋት ሲጀምር ደግሞ በአጭሩ እንዲቀጭ ዕርምጃ አልወሰዱም፡፡ የአመራር ሚናቸውን በአግባቡ ባለመጫወታቸው ጉዳዩ አገራዊ ችግር እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ አለበለዚያ በራስህ ተወላጅ ስለተመራህ ብቻ ችግሩ አይቀረፍም፡፡ ለእኔ የብሔረሰቦችን መብት እያከበሩ ግን ደግሞ የአስተዳደር ሥራን በአቅም መሠረት እንዲያዝ ማድረግ የሚጋጭ ነገር አይደለም፡፡ ችግሩ የፖለቲካ ድርጅቶቹ ወደ ቢሮክራሲው እንዲመጣ የሚመለምሉት ሰው በብሔር ብቻ አይደለም በፖለቲካ ወገንተኝነትም ነው፡፡ በኦሮሚያ የኦሕዴድ፣ የኦነግ ወይም የኦፌኮ ደጋፊ የሆነ ሰው አለ፡፡ ሦስቱም ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ ወደ ቢሮክራሲው አንድ ሰው የሚመጣው በኦሮሞነቱ ብቻ አይደለም፡፡ በኦሕዴድ ደጋፊነቱ ነው የሚያመጡት፡፡ ነገር ግን ተገቢ የሆነ ሕግና ሥርዓት አስቀምጠህ ኃላፊነቱን በአግባቡ እስከተወጣ ድረስ የኦፌኮን አባል ቢሮክራሲው ውስጥ እንዲሠራ ብታደርገው ችግር የለውም፡፡ ፌዴራሊዝም ተግባር ላይ የሚውለው መብትን ለማክበር ብቻ አይደለም፡፡ የኢኮኖሚ ልማትን ለማሳደግና አስተዳደራዊ ፍትሕንም ለማምጣት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ጥቅም ላይ የዋለው በዋነኛነት አለ ተብሎ የታመነውን የብሔር ጭቆና የመፍቻ መሣሪያ ሆኖ ነው፡፡ ፌዴራሊዝም የመጣው ከዚህ ጥያቄ በፊት ነው፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ፌዴራሊዝም ሊፈታቸው የሚችላቸውን ሌሎች ጥያቄዎች ማስተናገድ አልተቻለም፡፡ ለምሳሌ የአስተዳደር አመችነትና የኢኮኖሚ ልማት ጉዳይ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ማግኘት ነበረባቸው፡፡ የብሔር ጥያቄም ስለመመለሱ አጠያያቂ ነው፡፡ ለምሳሌ በኦሮሚያ ከፍተኛ የሆነ የመብት ጥያቅ ይነሳል፡፡ በክልሉ ግን የፌዴራል አደረጃጀት ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ክልሉን የሚያስተዳድሩት የኦሮሞ ብሔር አባላት ናቸው፡፡ ችግሩን ግን ፈቱት ወይ? አልፈቱትም፡፡
ሪፖርተር፡- ከአመራር ዘይቤ አንፃር ኢትዮጵያ ከአቶ መለስ ሕልፈተ ሕይወት በኋላ መሠረታዊ ለውጥ አሳይታለች ብለው ያስባሉ?
አቶ ልደቱ፡- አቶ መለስ ካረፉ በኋላ በእርግጥም ለውጥ አለ፡፡ ምን ዓይነት ለውጥ ነው ያለው የሚለው እንደየአስተሳሰባችን ሊለያይ ይችላል፡፡ በእኔ በኩል ከአቶ መለስ ሞት በኋላ ከፍተኛ የሆነ የአመራር ክፍተት አያለሁ፡፡ አጠቃላይ የኃይል ማዕከሉ የት እንደሆነ የጠፋበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ ይኼ ስሜት የሚሰማው ከኢሕአዴግ ውጪ ለሆነው ሰዎች ብቻ አይመስለኝም፡፡ ኢሕአዴግም ውስጥ ራሱ ይኼ ግልጽ ያልሆነላቸው ሰዎች ያሉ ይመስለኛል፡፡ አቶ መለስ እያሉ በተለይም ከሕወሓት መከፋፈል በኋላ የፖለቲካ ሥልጣኑ ተጠቃሎ ሊባል በሚችል መጠን በእሳቸው እጅ ነበር፡፡ ከእሳቸው መሞት በኋላ በግለሰብ ደረጃ ያንን ሚና የተካ ሰው የለም፡፡ በቡድን ደረጃ ያ የኃይል ሚዛን ማን ላይ ነው ያለው የሚለው ግልጽ ሳይሆን የቀጠለ ነው፡፡ አሁን ኢሕአዴግ ሥልጣኑን እያጠናከረ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ያ ሒደት አልቆ ሥልጣን በአንድ ግለሰብ ወይም ቡድን በግልጽ ተይዞ አይታይም፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ መመርያዎች፣ ትዕዛዞችና ውሳኔዎች ከየት አቅጣጫ እንደሚመጡ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በይፋ መንግሥት አራምዳለሁ የሚለው አቋም ሌላ ነው፣ መሬት ላይ በተግባር ሲተረጎም የሚታየው ደግሞ ሌላ ነው፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ግጭቶች ተፈጥረው በሒደት አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን አሸናፊ ሆኖ መውጣት አለበት፡፡ እንደዚያ ዓይነት ሒደት አሁን ኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረ አልመሰለኝም፡፡ የሚፈጠርበት አዝማሚያ ግን ያለ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ለውጥ በተለይ በቅርቡ በአገሪቱ በተፈጠሩ ችግሮች እየጎላ የመጣው ጉዳይ በኢሕአዴግ ዘንድ አንድን ውሳኔ በደንብ ሳያጤኑ ወስኖ፣ ነገር ግን የሕዝብ ተቀባይነት ሲያጣ ወዲያው የመቀልበስ አሠራር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የውሳኔው ትክክለኛነት ላይ ማተኮር ሳይሆን ሕዝቡ ለውሳኔው ያለው አመለካከት ላይ የማተኮር አዝማሚያ ይታያል፡፡ ለዚህ እንደ አብነት በኦሮሚያ ማስተር ፕላንና በቅርቡ ደግሞ ከታክሲ ሾፌሮች ጋር በተያያዘ የተወሰኑትን ውሳኔዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ውሳኔ ወስኖ ተግባራዊ የማድረግ አቅም እያጣ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በቅርቡ በፓርላማ ባደረጉት ቆይታ የማንነት ጥያቄዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ተመልሰው አልቀዋል ብለዋል፡፡ ይኼ እንደ መሠረታዊ ለውጥ ሊወሰድ አይችልም?
አቶ ልደቱ፡- የጠቅላይ ሚኒስትሩን የፓርላማ ንግግር ተከታትየዋለሁ፡፡ እውነቱን ለመናገር ስሰማው ደንግጫለሁ፡፡ በእውነት ታስቦበት የተነገረ ንግግር ነው ወይስ በድንገት በስሜት የተነገረ ንግግር ነው የሚለውን እስካሁን መለየት አልቻልኩም፡፡ ታስቦበት የተነገረ ንግግር ከሆነ በጣም አከራካሪ ይመስለኛል፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ሕገ መንግሥቱ ከዚህ በኋላ የብሔር ብሔረሰቦች ችግር ተፈቷል አላለም፡፡ የሚፈታበትን አካሄድ አስቀምጧል፡፡ ሁለተኛ የማንነት ጥያቄ አንድ ወቅት ላይ ተነስቶ አንድ ወቅት ላይ ሙሉ በሙሉ ተፈቷል የሚባል አይደለም፡፡ በመቼውም ሁኔታና ጊዜ ሊከሰት ይችላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ያን የመፍቻ መሣሪያ ነው የሚሆነው፡፡ የማንነት ጥያቄ በውሳኔ ከዚህ በኋላ ተዘግቷል ሊባል አይችልም፡፡ አንዱ መጀመሪያም ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅና የፌዴራል ሥርዓቱ ሲዋቀር ግምት ውስጥ መግባት የነበረበት ይኼ ነው፡፡ የማንነት ጥያቄ አንድ ጊዜ ከቋንቋና ከብሔረሰብ ማንነት ጋር ከተያያዘ ማቆሚያ የሌለው እንደሆነ ግምት ውስጥ መግባት ነበረበት፡፡ ስለዚህ ይኼ ውሳኔ ራሱን ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አስበውበት ተናገሩ ብዬ አላምንም፡፡ አስበውበት የተናገሩ ከሆነና ከጀርባም የድርጅታቸው ውሳኔ ከሆነ ይኼ ትልቅ ለውጥና ሽግግር ነው፡፡ በፓርላማ እንደ ቀልድ ተነግሮ ብቻ መታለፍም የለበትም፡፡ ይኼ ለውጥ ለአገር ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም የሚለው ለውይይት ቀርቦ ሁላችንም ሐሳብ መስጠት ያለብን ይመስለኛል፡፡ ይኼ ኢሕአዴግን እንደገና የመፍጠር ጥያቄ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ ከዘመን መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የኢትዮጵያ ቢሮክራሲ መንግሥት ሊቋቋመው ያልቻለና መንግሥትን የማይፈራ ነው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ቢሮክራሲው ታማኝና ታዛዥ ነው እያሉ ነው፡፡ ይኼ እርስ በርሱ አይጋጭም?
አቶ ልደቱ፡- አይጋጭም፡፡ ሥርዓቱ ቢሮክራሲውን ሲያሰባስብ የራሴ የሚለው ጥቅም እንዲያገኝ ፈልጎ አይደለም፡፡ መንግሥት የራሴ የሚለው የፖለቲካ ጥቅም ስላለው ነው፡፡ እኔን የሚመስል፣ የእኔን አስተሳሰብ የሚደግፍና ለእኔ ታማኝ የሆነ ቢሮክራሲ አሰባስቤ የፖለቲካ የበላይነቴን አስጠብቄ እቀጥላለሁ ብሎ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ዓይነት ሠራዊት ሲፈጥር ነገ ከነገ ወዲያ የራሱን ጥያቄ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ማሰብ ነበረበት፡፡ የኢኮኖሚ ጥቅም መፈለግ የሚጀምረው ኋላ ላይ ነው፡፡ አሁን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሙስናው ተመጋጋቢ ሆነዋል፡፡ ተቃራኒ በመሆናቸው ጦርነት ውስጥ ናቸው፡፡ አንድ ሰው ሙስና ውስጥ የሚገባው ደሃ ስለሆነ አይደለም፡፡ ይበልጥ ሙስና ውስጥ የሚገባው ሙስናውን ማጣጣም ከጀመረ በኋላ ነው፡፡ ከሥር ከመሠረቱ የመልካም አስተዳደር ችግርን ነቅሎ የሚጥል ዘመቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ችግሩ መዋቅራዊ መሆኑን አምኖ መቀበል ይጠይቃል፡፡ በለብ ለብ ዘመቻ አሸናፊ የሚሆነው ቢሮክራሲው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም መቀጣጫ እንዲሆኑ የተወሰኑ ሰዎች ሲታሰሩ አይተናል፡፡ ችግሩ ግን አልተፈታም፡፡ የቢሮክራሲው ኃይል አሁን ገዝፏል፡፡ ቢሮክራሲውና ሙስና አሁን አንድ ሆነዋል፡፡ ሙስናን ብታቆም ቢሮክራሲው በደመወዝ ብቻ ሊተዳደር አይችልም፡፡ ጥሎት ስለሚወጣ መንግሥት ተንገራግጮ ይቆማል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ችግር ለመፍታት አንደኛ ሁሉን አቀፍ የሆነ መፍትሔ መፈለግ አለብህ፡፡ ዋናው የፖለቲካ መፍትሔ ነው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ይኼ ቢሮክራሲ ራሱን፣ ቤተሰቦቹን፣ ልጆቹን የሚያስተምርበትና የሚመግብበት ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም እንዲያገኝ ማድረግ አለብህ፡፡ የሥርዓቱ አብዛኛው አካል ተበክሏል፡፡ ይኼን አካል ቆርጦ መጣል ቀላል ውሳኔ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ አማራጭ የለም፡፡ ይኼንን የተገነዘቡ የኢሕአዴግ አመራሮች ያሉ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ከችግሩ ጋር ደግሞ እጅና ጓንት የሆኑና የተያያዙ አካላት አሉ፡፡ አንዳንዳቹ እኮ የኢሕአዴግ ድርጅቶች በትክክል በሙስና የተዘፈቀ ሰው ሁሉ ይጠየቅ ቢባል ድርጅቶቹ እንደ ድርጅት ሊፈርሱ ይችላሉ፡፡ የሚያስከትለው የፖለቲካ ጣጣ ሊኖር ይችላል፡፡ ግን ደግሞ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ግን ይጠይቃል፡፡
ሪፖርተር፡- በኢሕአዴግ ዲስኩር ውስጥ ፓርቲው ራሱን የሚያስተዋውቀው ለሕዝብ ጥቅም የሚኖሩና ለዚህ ዓላማ መስዋዕት ለመሆን ዝግጁ በሆኑ አባላት እንደተሞላና ጥቂት ከዓላማው ውጪ የሚሠሩ አባላትን የማክሰም ብቃት እንዳለው ነው፡፡ በሌላ በኩል ሙስናን ለመዋጋት ከአስተዳደራዊና ከሕጋዊ ዕርምጃዎች ይልቅ ፖለቲካዊ መፍትሔዎች በቅድሚያ መወሰድ እንዳለበት የመንግሥት የፖሊሲ ሰነዶች ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች አብረው የሚሄዱ ናቸው?
አቶ ልደቱ፡- ሁለቱም የመፍትሔው አካል ናቸው፡፡ ተቀናጅተው ተግባራዊ መሆን አለባቸው፡፡ ኢሕአዴግ የሚታገለው አንደኛውን ነጥሎ ለመፈጸም ነው፡፡ ነገር ግን በኢሕአዴግ ዙሪያ የተሰባሰበው በትክክል የአገር ፍቅር ያለውና ለሕዝብ አገልግሎት ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ዕውቀቱን መስዋዕት ለማድረግ የተሰባሰበ ኃይል ነው ወይ? በዚህ መንፈስ ወደ ኢሕአዴግ የተቀላቀሉ ሰዎች የሉም ልል አልችልም፡፡ በተለይ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ይኼን ዓይነት አመለካከት ይዘው የገቡ ሰዎች አሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ግን አሁን ይኼ ሥርዓት በሥልጣን ላይ ከ20 በላይ ዓመታት ከቆየ በኋላ በዙሪያው ያሰባሰባቸው ኃይሎች እነማን ናቸው የሚለውን ካየን ግን በትክክል ለሕዝብ አገልግሎት የቆሙ አይደሉም፡፡ ያለ ምንም ማጋነን ከ95 በመቶ በላይ የሆነው ኅብረተሰብ ለዚያ ብሎ የተሰባሰበ አይደለም፡፡ ከአምስት ወይም ከስድስት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የሙስና መጠን በጣም ዝቅተኛ ነበር፡፡ አሁን ለማመን በሚከብድ መጠን ጨምሯል፡፡
ሪፖርተር፡- ከቀድሞ መንግሥታት በተቃራኒ ኢሕአዴግ የዘረጋሁት የአስተዳደር መዋቅር 1 ለ 5ን ጨምሮ በእያንዳንዱ ቤት የሚደርስ ነው በማለት በኩራት ይገልጻል፡፡ ከዚህ አንፃር ይህን ለአገሪቱ ህልውና የሚያሰጋ ችግር እስካሁን እንዴት ሳይገነዘበው ቀረ?
አቶ ልደቱ፡- ችግሩን ከተገነዘበው ቆይቷል፡፡ በመሠረቱ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ የመዋቅር ማሻሻያ ያልተሞከረበት ጊዜ የለም፡፡ ከፍተኛ የሆነ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ የተባለው ዛሬ አይደለም፡፡ በሌላው አገር አንድ ችግር ተፈጠረ ብሎ ከሥልጣን የሚለቅ ሚኒስትር የተለመደ ነው፡፡ መንግሥት በአግባቡ ሥራዬን አልተወጣሁም ብሎ ሲያስብ የመተማመኛ ድምፅ ይጠይቃል፣ ሕዝበ ውሳኔ ያደርጋል፡፡ ይኼ የሚያሳየው ችግሩ ከፍተኛ ከሆነ የፖለቲካ ህልውናህን ሊፈታተን እንደሚችል ነው፡፡ ኢሕአዴግ ግን የራሱን የፖለቲካ የበላይነት አስጠብቆ ነው ችግሮችን መፍታት የሚፈልገው፡፡ የፖለቲካ ህልውናውን የሚነካኩ ከሆነ ሊነካቸው አይፈልግም፡፡
ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመቅረፍ የተለያዩ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ለዚህ የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉት እንደ ፓርላማ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ እንባ ጠባቂ ተቋምና ሚዲያ የራሳቸው ሚና እንደሚኖራቸው ተገልጿል፡፡ እስካሁን የተወሰዱትን ዕርምጃዎችና የተቋማቱን ሚና እንዴት ያዩታል?
አቶ ልደቱ፡- ይኼን ችግር በብቃት ለመዋጋት ነፃ የሆኑ ተቋማት ያስፈልጉ ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተቋማት የተፈጠሩት የፖለቲካ ወገንተኝነት ባላቸው ወገኖች ነው፡፡ ነፃ ሆነው ሥርዓቱ አቅጣጫ ሲስት የሚገዳደሩና የሚጠይቁ ሰዎች አይደሉም በተቋማቱ የተሰባሰቡት፡፡ የፖለቲካ ታማኝነት መመዘኛ ሆኖ የሥርዓቱ ደጋፊና ታማኝ የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ተቋማቱ አሁን ነፃነት አላቸው ማለት አይቻልም፡፡ በሥርዓቱ ውስጥ ያለውን ችግር ታግሎ ለመፍታት የሚያግዝ ጉልበት አላቸው ማለት አይቻልም፡፡ መንግሥትን ከጥቃት የሚከላከሉ ናቸው፡፡ የእኔ ጠላት ናቸው የሚላቸውን አካላት እንዲያጠቁለት የተቋቋሙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ጥርስ የሌለው አንበሳ ሆነዋል፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከተቋቋመ በኋላ ሙስና እየጨመረ ነው የመጣው፡፡ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተቋቋመ በኋላ የኅብረተሰቡ የሰብዓዊ መብት ችግር የበለጠ እየተባባሰ ነው የመጣው፡፡
ሪፖርተር፡- ባለፈው ግንቦት ወር በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ መቶ በመቶ ያሸነፈው ገዥው ፓርቲ፣ በጥቂት ወራት ልዩነት ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተቃውሞ ሲነሳበት እንዴት አዩት?
አቶ ልደቱ፡- ኢሕአዴግ መቶ ፐርሰንት እንዳሸነፈ በምርጫ ቦርድ ሲነገረው መደሰት ሳይሆን መደንገጥ ነው የነበረበት፡፡ ምክንያቱም የተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብና የፖለቲካ ቅራኔ ባለበት አገር አንድ ፓርቲ በብቸኝነት ከቀበሌ እስከ ፓርላማ ያለውን መዋቅር መቶ በመቶ አሸንፎ የሚይዝበት ሁኔታ የለም፡፡ መቶ በመቶ አሸንፏል ከተባለ በኋላ እንደዚህ ዓይነት በጣም ከፍተኛ የሆነ የኅብረተሰብ ብሶቶችና ግጭቶች መፈጠራቸው የምርጫው ውጤቱ በፍፁም ነባራዊ ሁኔታውን የማይገልጽ መሆኑን ነው የሚያሳየው፡፡ ኢሕአዴግ ቆም ብሎ ማሰብ ያለበት አሁን ነው፡፡ መቶ ፐርሰንት የምርጫ ውጤት የሚያሳየው በኢትዮጵያ ውስጥ የሐሳብ ብዝኃነት ቦታ ማጣቱን ነው፡፡ ብዝኃነት የሚገለጸው በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በብሔረሰብ ማንነት ብቻ አይደለም፡፡ እንዲያውም በዋናነት ብዝኃነት የሚገለጸው በአስተሳሰብ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እየነገረና እየተሳበበ ያለው፣ በተግባር እየዋለ ያለው የአንድ ፓርቲ ብቸኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሌሎች አስተሳሰቦች ተደፍቀዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ብሶቱን፣ ተቃውሞውንና ቅሬታውን የሚገልጽበት መድረክ አጥቷል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በተፈጠረበት አገር አሁን የምናያቸው ዓይነት አላስፈላጊ የሆኑ ግጭቶች መከሰታቸው ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ደረጃና በማንፈልገው መጠን በአገሪቱ ውስጥ ግጭቶች እየታዩ ያሉት በዋናነት የአስተሳሰብ ብዝኃነት በመታፈኑ ነው፡፡ መንግሥት ሁለት ወዶ ሊሆን አይችልም፡፡ በአንድ በኩል ሰላማዊ መድረኩን ሙሉ በሙሉ ዘግቶ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አመፅን መዝጋት አይቻልም፡፡ የአመፅን መንገድ መዝጋት የሚቻለው ሰላማዊ መድረኩን በመክፈት ነው፡፡ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ቁልፉ ጥያቄ የአስተሳሰብ ብዝኃነት አለመከበር ነው፡፡ በቅርቡ ትልቅ ችግር ውስጥ የገቡት እንደነ ግብፅ፣ ሊቢያና ሶሪያ ያሉ አገሮች ራሳቸውን ለረጅም ዓመታት ከለውጥ አርቀው ነበር፡፡ የአስተሳሰብ ብዝኃነትን ማስተናገድ አቅቷቸው ነው መጨረሻ ላይ ወደማይፈለግ ግጭትና ብጥብጥ የገቡት፡፡ ይኼ ችግር የማይፈታ ከሆነ የኢትዮጵያም ዕጣ ፈንታ ወደዚያ ነው የሚያመራው፡፡
ሪፖርተር፡- በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ መጀመሪያ ሲነሳ መንግሥት የውጭ ፀረ ሰላምና ፀረ ልማት ኃይሎች እጅ ነው ብሎ ነበር፡፡ አሁን ግን ችግሩ በዋነኛነት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች እንደሆነና እነዚህ ኃይሎች የማቀጣጠል ሚና መጫወታቸውን የሚገልጽ ነው፡፡ በእርስዎ ግምገማ የውስጣዊና የውጫዊ ምክንያቶች ድርሻ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ልደቱ፡- በዋናነት ችግሩ የተፈጠረው ውስጥ ባለው ሁኔታ ነው፡፡ ሕዝቡ ውስጥ ባለ ተጨባጭ ብሶት ነው፡፡ ነገር ግን የዚህን ጉዳይ መገለጫዎች ስናይ ብቻውን የቆመ ነው ማለት አይቻልም፡፡ እነዚህን ብሶቶች ከጀርባ ሆነው ለራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ የሚጠቀሙባቸው የውጭ ኃይሎች የሉም ማለት አይቻልም፡፡ ግን እነዚህ ኃይሎች ይህን ዕድል ያገኙት የውስጡን ችግር በአግባቡ፣ በተገቢው ጊዜና ሁኔታ ለመፍታት ስላልተቻለ ነው፡፡ መነሻው ግን የአገር ውስጡ ችግር ነው፡፡ የውጭ ኃይሉ የተመቸ ሁኔታ አግኝቶ ይህችን አገር ወደ መጥፎ አቅጣጫ እንዳያስገባት መፍትሔው ማውገዝና ፕሮፖጋንዳ አይደለም፡፡ መፍትሔው ውስጥ ላለው ኅብረተሰብ ብሶት መነሻ የሆነውን ችግር ከምንጩ ማድረቅ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጥቂቶችን ጥቅም ለማስከበር የቆሙና የሕዝብ ፍላጎትን መሠረት አድርገው የማይሠሩ ናቸው ሲል ሁሌም ይተቻል፡፡ በቅርቡ በተከሰተው የተቃውሞ እንቅስቃሴም አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የውጭ ኃይሎችን አጀንዳ ለማስፈጸም ተንቀሳቅሰዋል ሲል ከሷል፡፡ ችግር ላይ ያለችውን ኢትዮጵያን ለመታደግ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን ሚና ሊጫወቱ ይገባል?
አቶ ልደቱ፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ መንግሥት ዝም ብሎ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጅምላ አጀንዳ የለሽ አድርጎ ከማየት፣ ፀረ ሕዝብና ፀረ ልማት አድርጎ ከማየት የተለየ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች አሉ ብሎ መውሰድ የተሻለ ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ደግሞ አነሰም አደገም የሚወክሉት ኅብረተሰብ መሬት ላይ አለ ማለት የተሻለ ነው፡፡ ይህን ኃይል የሚያስተናግድ ሥርዓት መገንባት ግድ ነው፡፡ ኢሕአዴግ አማራጭ እኔ ብቻ ነኝ ብሎ የትም ሊሄድ አይችልም፡፡ የተለያዩ የኅብረተሰቡን ፍላጎት የሚወክሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች የሚወከሉበት መድረክ ያስፈልጋል፡፡ በፖሊሲ ውሳኔና በሕግ ማውጣት ጉዳይ ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ተቃዋሚዎች እስካሁን የሄዱበትን አስተሳሰብ መፈተሽ አለባቸው፡፡ አካሄዳቸውን ማስተካከል አለባቸው፡፡ በሰሞኑ ግርግር እንኳን ስናይ ግርግሩ ወዴት ያደርሰናል? የግርግሩ መነሻ ምንድነው? ተጠያቂው ማነው? ብለው ሳይገመግሙ የተፈጠረውን ችግር ሁሉ ለማባባስና በዚህ ግርግር የመንግሥት ለውጥ እንዲመጣ ሲጠብቁ አይተናል፡፡ ይኼ ስህተት ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰከን ብለው አጀንዳቸውን ከሕዝብና ከአገር ጥቅም ጋር አያይዘው መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ እንቅስቃሴያቸውም ሰላማዊና ሕጋዊ መሆን አለበት፡፡ መንግሥትንም በምክንያት መተቸት አለባቸው፡፡ አስተሳሰባቸው ከመንግሥት ለውጥ ጋር ሁልጊዜ መንጠልጠል የለበትም፡፡ ተጨባጭ የሆነ የፖሊሲ አማራጭ ይዘው ቀርበው መንግሥት የመሆን ዕድል እንኳን ባያገኙ፣ በመንግሥት ላይ ትርጉም ያለው ተፅዕኖ አሳድረው የፖሊሲ ለውጥ ማሻሻያ እንዲመጣ ማድረግ አለባቸው፡፡ የዚህ ዓይነት ባህል ካላቸው ብቻ ነው በሒደት በኅብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት እያገኙና እምነት እያገኙ ወደ መንግሥትነት ደረጃ የሚበቁት፡፡
ሪፖርተር፡- ፓርቲዎ ኢዴፓ አላምደዋለሁ የሚለውን የሊበራል አስተሳሰብ ለጥቂቶች ጥቅም የቆመና ኢትዮጵያዊ መሠረት የሌለው አድርጎ ገዥው ፓርቲ ያቀርበዋል፡፡ ይህን አቀራረብ እናንተ እንዴት ነው የምታዩት?
አቶ ልደቱ፡- የግራ ፖለቲካ አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ማቆጥቆጥ ከጀመረበት ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ የሊበራል አስተሳሰብ ቦታ እያጣ ነው የመጣው፡፡ በጣም ፅንፈኛ የሆነ ወይ ከእኔ ነህ ወይ ከእነሱ ነህ የሚል የፖለቲካ ባህል ነው የሰፈነው፡፡ ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ አይቶ ሚዛናዊ አስተሳሰብ መያዝ ነውር እየሆነ የመጣበት ባህል ነው የተስፋፋው፡፡ ገዥው ፓርቲ የግራ ፖለቲካ ውጤት ነው፡፡ የሊበራል አስተሳሰብ በዓለም ገዥ የሆነ አስተሳሰብ ነው፡፡ ዛሬ የምንቀናባቸውና ዕርዳታ እንዲሰጡን የምንለምናቸው የሊበራል አስተሳሰብ የሚያራምዱ ናቸው፡፡ የሊበራል አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝባዊ መሠረት እንዳለው ወይም እንደሌለው ሊረጋገጥ የሚችለው ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ስታካሂድ ብቻ ነው፡፡ የሊበራል አስተሳሰብ የሚያራምድን አካል እንደ ሕዝብ ጠላት ፈርጀህ፣ መድረክ አሳጥተኸው፣ አምቀኸው፣ ሐሳቡን ለኅብረተሰቡ እንዳይሸጥ አድርገህ አይጠቅምም ማለት ዋጋ የለውም፡፡ ሁለተኛ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሊበራል አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይሆናል ብለን አናምንም፡፡ የሊበራል አስተሳሰብ በሩቅ ግብ እንደርስበታለን ብለን የምናምንበት ነው፡፡ በሒደት የሚመጣ ነው፡፡ ነገር ግን እዚያ ለመድረስ ከአሁኑ ነገሮች መጀመር አለባቸው፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢዴፓ የሚያነሳውን ሐሳብ ሁሌም ሲያጥላላ ነው የኖረው፡፡ ነገር ግን ይኼ ስህተት እንደሆነ የሚያሳዩ ከወቅታዊ የአገራችን ሁኔታ ጋር የተያያዙ ሦስት ምሳሌዎችን ላንሳልህ፡፡ ከኢኮኖሚ አንፃር ደግመን ደጋግመን ስንናገር የነበረው መሠረታዊ የሆነ መዋቅራዊ ሽግግር በኢኮኖሚያችን ካልተፈጠረና በአስቸኳይ ከእርሻ ጥገኝነት ራሳችንን ካላወጣን ያለው ኢኮኖሚ ዝናብ ቀጥ ቢል ችግር ውስጥ እንደሚገባ ነበር፡፡ ዘንድሮ የታየው ይኼ አገር አሁንም በምግብ እህል እንኳን ራሱን እንዳልቻለ ነው፡፡ ሁለተኛ ፌዴራሊዝም የአገሪቱን የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ ፈቷል፣ ከዚህ በኋላ አንድነታችን የበለጠ ጠንክሯል ተብሎ ሲነገር ነበር፡፡ እኛ ስንል የነበረው ይኼ የፌዴራሊዝም አደረጃጀት በዋናነት ትኩረት ያደረገው ልዩነት ላይ ስለሆነ በሒደት የኅብረተሰቡን አንድነት እያላላው እንደሚመጣ ነበር፡፡ ግጭት እያዳበረ፣ ጤናማ ያልሆነ ፉክክርን ያዳብራል ነው ስንል የነበረው፡፡ አሁን መንግሥት እያስተናገደ ያለው ምንድነው? በብዙ የአገሪቱ አካባቢዎች በታሪክ አይተነው የማናውቀው ግጭት ነው የተከሰተው፡፡ ሦስተኛ ከመሬት ጥያቄ ጋር በተያያዘ መሬት በመንግሥት እጅ መያዙ ለኅብረተሰቡ ነው የሚጠቅመው ሲባል ነበር፡፡ በኦሮሚያ ተቃውሞ ገበሬው እያነሳ ያለው ጥያቄ ምንድነው? መንግሥት ያላግባብ መሬታችንን እየነጠቀና እየሸጠ እሱ እየከበረ እኛ ግን እየደኸየን ነው በሚል ነው ተቃውሞውን ያቀረበው፡፡ እኛ ስንከራከር የነበረው የመሬቱ ባለቤት የሕዝቡ እንዲሆን ነው፡፡ ገበሬው በመሬቱ ላይ የመሸጥ፣ የመለወጥ፣ የማከራየት መብት ኖሮት ጥቅም ያግኝ እያልን ነው ስንከራከር የነበረው፡፡ ስለዚህ ስናነሳቸው የነበሩ ችግሮች ሁሉ አሁን ችግር መሆናቸው ጎልቶ እየታየ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በኦሮሚያ የተነሳው ተቃውሞ በተወሰነ መልኩ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ከምታገኘው ልዩ ጥቅም ጋር ተያይዟል፡፡ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ጋር ያላት ግንኙነት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠበትን መንገድና አተገባበሩን እንዴት ያዩታል?
አቶ ልደቱ፡- በእኛ እምነት ሕገ መንግሥቱ ብዙ ክፍተቶች አሉት፡፡ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ ነውር አይደለም፡፡ 25 ዓመት ከተጓዘ በኋላ ይኼ ሕገ መንግሥት ያሉበት ክፍተቶች ምንድን ናቸው? መቀየር ያለባቸው ነገሮች አሉ ወይ? ብሎ መገምገም አለበት፡፡ አሁን ግን ሕገ መንግሥቱ እንደ መለኮታዊ ሰነድ ነው እየታየ ያለው፡፡ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ጉዳይ አንዱ ክፍተት ነው፡፡ በግልጽ ባለመቀመጡ ብዥታ ፈጥሯል፡፡ የጥቅም ግጭትም ፈጥሯል፡፡ ትልቅ የፖለቲካ ጉዳይም እየሆነ ነው፡፡ ለአገርና ለሕዝብ በሚጠቅም መልኩ ግልጽ መደረግ አለበት፡፡ ካስፈለገም እስከ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ድረስ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ወደፊት ሊመጡ የሚችሉ ችግሮች ተጢነው አይደለም ሕገ መንግሥቱ የተረቀቀው፡፡ በወቅቱ ኢሕአዴግ ይዞት የነበረው አስተሳሰብ ነው በቀጥታ ወደ ሕገ መንግሥትነት እንዲቀየር የተደረገው፡፡ የብዙ ፓርቲዎች አስተሳሰብ ምን እንደሆነ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ፣ በቂ የሆነ ውይይት ተደርጎ የተዘጋጀ ሰነድ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥት ግን በባህርይ መሆን ያለበት እንደዚያ ነው፡፡ ይኼን በሒደት ማስተካከል አስፈላጊና ወቅታዊ ነው፡፡ ከመሬት ጥያቄ፣ ከአዲስ አበባና ኦሮሚያ ግንኙነትና የፌዴራል አደረጃጀቱ እስከ መገንጠል ጥያቄ ድረስ ጋር በተያያዘ ያለው አንድምታ በደንብ በድጋሚ መዳሰስ አለበት፡፡ አንዳንዶቹ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች ኢትዮጵያን እንደ እስራኤልና ፍልስጤም ሁኔታ በሩቅ ሒደት ውስጥ የሚያስገቡ ናቸው፡፡ ወደዚያ አቅጣጫ ከመግባታችን በፊት ቆም ብለን ማሰብና የአጠቃላይ ሕዝቡን ስምምነት ያገኘ ሕገ መንግሥት ማግኘት መቻል አለብን፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ተገቢውን ትኩረት ማግኘት አለበት፡፡ ነገር ግን አስተማማኝ በሆነ አቅጣጫ ውስጥ እንዲቀመጥ የሚያደርግ መፍትሔ መሰጠት አለበት፡፡
ምንጭ – ሪፖርተር
The post ‹‹በአገሪቱ ውስጥ ግጭቶች እየታዩ ያሉት በዋናነት የአስተሳሰብ ብዝኃነት በመታፈኑ ነው›› appeared first on Zehabesha Amharic.