መግቢያ
ንቁ ፥ በሃይማኖት ቁሙ ፥ ጎልምሱ ጠንክሩ» /1ቆሮ16 ፥13/
በመላው ዓለም የምትገኙ ኦርቶዶክሳውያን የተዋሕዶ ልጆች ክርስቲያኖች እንደ ምን አላችሁ ። የእግዚአብሔር ጸጋና ሰላም ፥ ፍቅርና ርኅራኄ ይብዛላችሁ ። ብዙዎቻችሁ የቤተ ክርስቲያኔ ነገር ያገባኛል ያሳስበኛልም ብላችሁ ርትዕት ስለ ሆነች ሃይማኖታችሁ በዚህ ሰዓት የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ አክብራችሁ ስለ ተገኛችሁ የቤተ ክርስቲያን ራስ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ያክብራችሁ ።
ቅዱስ ጳውሎስ «ንቁ ፥ በሃይማኖት ቁሙ ፥ ጎልምሱ ጠንክሩ» ብሎ የሚመክረን መንፈሳዊ ንቃተ ሕሊናችንን ስሕተትና ኑፋቄን እንዲሁም የጥላቻን ወንጌል በሚሰብኩ በየዘመኑ የሚነሡ የሐሰት ሰዎች እንዳይዘናጋና በእነሱ ወጥመድ ውስጥ እንዳይጥሉን ነቅተን በሃይማኖት እንድንቆም ነው ። በቤተ ክርስቲያን መካከል ፍቅርና አንድነትን በማጥፋት ፥ ምእመናንን ከአባቶቻቸው ለማለያየት ምናምንቴ ሰዎችን በየጉባኤው እየላኩ አይሁድና ቢጽ ሐሳውያን ጉባኤውን እያወኩ ያስቸግሩት ስለ ነበር ንቁ ይላቸዋል። እንዲሁም በሀሰት ትምህርት ግራ እንዳይጋቡ በማሰብ በሃይማኖት ጸንተው ቁመው እንዲገኙ ቅዱስ ጳውሎስ “ንቁ” እያለ ምእመናንን ይመክራል ። በነቢያት ዘመን ነቢያተ ሀሰት የነቢያትን ትምህርት ያስተባብሉ እንደ ነበሩ ፣ በሐዋርያትም ዘመን ቢጽ ሐሳውያን የሐዋርያትን ትምህርት እየተቃወሙ ሕዝቡን ግራ ያጋቡ እንደ ነበር ፣ በዚህ ዘመንም ርቱዕ የሆነውን የቤ/ክ ትምህርትና ሥርዓት የሚቃወሙ ፣ የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ለመክፈል ታጥቀው የተነሡ ግለሰቦች ራሳቸውን አደራጅተው ቤተ ክርስቲያንን የሚፈትኑበት ዘመን ስለ ሆነ ነቅተን ቤተ ክርስቲያንን ልጠብቅ ይገባል ።
እኔ ዛሬ ይህንን መልእክት እንዳቀርብ ያስፈለገበት ምክያት ፣ በቅርቡ እንደ አዲስ ነገር ተደርጎ ራሱን «ማኅበረ ቅዱሳን» (ማቅ) ብሎ በሚጠራው ድርጅት በተሰማሩ የሐራ ጥቃ ሰባኪዎች አማካይነት የአርጋኖን ነገር በማንሣት ሕዝበ ክርስቲያኑን በውጭ አገር የሚገኙ አባቶች ኦርጋን ወደ የቤተ ክርስቲያን በማስገባት የቤተ ክርቲያናችንን ሃይማኖት እንዲለወጥ እያደረጉ ነው በማለት ፣ ቴሌ ኮንፈረንስ በማድረግ ሕዝቡን ግራ በማጋባት ላይ ስለሚገኙ ፣ ይልቁንም የታላቁን ሊቅ የብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ስም በማጥፋት የሐሰት ከሳሾች ሁነው ስለ ተገኙ ፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ እውነቱን እንዲረዳ ለማድረግ ነው ።
ምእመናን ! ይህ ዘመቻ የማኅበረ ቅዱሳን(ማቅ) መልእክተኞች ሁለተኛው ዙር ዘመቻ ነው ። በመጀመርያው ዘመቻ በውጭ ሀገር ያለችውን ቤተ ክርስቲያን በመከፋፈልና በሀገር ውስጥና በሀገር ውጭ የሚገኙ አባቶችን በማወጋገዝ ተጠናቆ ነበር ። የመጀመሪያውን ዘመቻ ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት 2003 እኤ ጀምሮ አካሂዶ ነበር ። አላማውም በሰሜን አሜሪካ በማኅበሩ የሚመሩ አብያተ ክርስቲያናትን ለመመሥረት ሲሆን ዘመቻውን ያጧጧፈው በውጭ ሀገር ያሉ አንድ አንድ አብያተ ክርስቲያናትን በኦርጋን መዘመራቸው ትክክል አይደለም ፤ በውጭ አገር ባለቺው ቤተ ክርስቲያንም የሚያስተምሩ መምህራን መናፍቃን ናቸው ፣ ሲኖዶስ በአዲስ አበባ እንጂ በአሜሪካ የለም ፣ ወዘተ እያሉ ነበር የዘመቱት ። በመጨረሻም በሀገር ቤት ያሉትን አባቶችና በውጭ ሀገር ያሉትን አባቶች ለማወጋገዝ እስኪችል ድረስ የተሳሳተ መረጃ አዲስ አበባ ላሉት አባቶች በማቀበል ትልቅ ሚና ተጫውቶ ችግሩ በልዩነት ቀጠለ ። ድርጅቱ የአዲስ አበባውን ሲኖዶስም አመራር አይቀበልም ። ነገር ግን በስደት የሚገኙትን አባቶች የሚዋጋው «እናት ቤተ ክርስቲያን» በሚል ስም ነው ። ግቡም የኢኦተቤክ አስተዳዳራዊ ሥልጣን መንጠቅ ነው።
ይሁን እንጂ “ማቅ” ከአራት ዓመት በፊት በአትላንታ ባደረገው ስብሰባ ከአሁን በኋላ በውጭ አገር የሚገኘውን ሲኖዶስና አባቶች መቃወሙ በሕዝብ ዘንድ እያስጠላን ስለመጣ አንደኛ የራሳችንን ቤተ ክርስቲያን እናጠናክር ። ሁለተኛ በሌሎችም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመግባት የአባልነት ክፍያ እየከፈልን ከሰበካ ጉባኤው /ቦርድ/ ውስጥ ገብተን በመከፋፈል ሕዝቡን ግራ በመለያየት ፥ ከቻልን ቤተ ክርስቲያኑን እንረከበዋልን ካልቻልን ሰላም እንነሳቸዋለን ብሎ የሰልፍ ስልቱን ቀይሶ ነበር ።
ከዛሬ ዓመት በፊት ደግሞ ሲያትል ላይ አዲስ እቅድ በመንደፍ አሁን በየቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ገብተው የሚታገሉ ተቃዋሚዎችን አፍረተናል ፤ በጀት በጅተን በውጭ ሀገር የሚያገለግሉትን ጳጳሳትና ካህናት የሚቃወም ንቅናቄ በመፍጠር ሕዝባቸው ዘንድ ተሰሚነት እንዳያገኙ በማድረግ ሕዝቡን አስደንግጠን ወደኛ እንዲመጣ ማድረግ አለብን ብለው ይኸውና በዓመቱ ድርጅቱ በገንዘብ የገዛቸውን ምናምንቴዎች አዝምቶ በመዋጋት ላይ ይገኛል ።
በመሆኑም ጦርነቱንም ለማፋፋም በዋናነት ምክንያት ያደረገው አረጋዊው አባት በሎሳንጀለስ ጥምቀት ላይ ስለ አርጋኖን ተጠይቀው የሰጡትን ማብራሪያ ነው ። ስለዚህ አርጋኖንን አስመልክቶ የተነሣውን ጥያቄ ምክንያት በማድረግ ጠቅላላ ስለ መዝሙር መሣሪያዎች ማብራሪያ ለመስጠት «መዝሙርና የመዝሙር መሣሪያዎች» በሚል ርእስ ይህ ጥናታዊ ጽሑፍ ተዘጋጀ ።
ይህ ጥናታዊ ጽሑፍ አርጋኖንን ለሚቃወሙ የቢጽ ሐሳውያን ‘ማቅ’ አባላት መልስ ለመስጠትበ2003 ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጅቶ የቅዱስ ሲኖዶስ ልሳን በሆነው ነጸንራቅ መጽሔት ላይ በ2005 የተሰራጨ ሲሆን ፥ እንደ ገና ከ10 ዓመታት በኋላ እንዳዲስ ጥያቄውን ስላነሡ የመጀመርያው ጽሑፍ ተሻሽሎ በ2016 እኤ እንደ ገና ለንባብ ቀረበ ።
በዚህ ርእስ ስለ ዜማ ስልት ስለ መዝሙር እና የመዝሙር መሣሪያዎች ስለ ቅዱስ ያሬድ መሠረታውያን የዜማ ስልቶችና ትርጓሜ ጠቅለል አድርጌ ለማብራራት ጥረት አደርጋለሁ ።
ዜማ ማለት ስልት ያለው ጩኸት ወይም በሥርዓት በደምብ የሚሰማ ድምጽ ፥ ሰሚውን የሚማርክ የሚመስጥ ፥ ለስሜት ትርጉም የሚሰጥ ድምጽ ማለት ነው ። ቀሌምንጦስ እና አርጋኖን የሚባሉት የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ፥ ዜማ ከሰው አንደበት የሚወጣ ብቻ ሳይሆን ከወፎች የምንሰማው መልካም ድምጽም ሆነ ከዜማ መሣሪያዎች ቅኝት የምንሰማው ድምጽ ዜማ እንደ ሆነ ፥ ዜማም እንዳለው ፥ ዜማም እንደሚባል ይናገራሉ ። የመጻሕፍቱ ቃል በግእዝ እንዲህ ይላል “አእዋፍ ዘሠናይ ዜማሆሙ ይሴብሕዎ በሠናይ ዜማ ወማኅሌት” ይህም ማለት “ዜማቸው ያማረ ወፎች በመልካም ዜማቸው ያመሰግኑታል” ማለት ነው ። እንዲሁም “ኅብረተ ዜማ ግእዝ እዝል ወዓራራይ ፥ ዝብጠተ መሰንቆ ወእንዚራ እለ ቦሙ ሠናይ ዜማ” ይላል ። ሲተረጐም “በግእዝ በእዝል በዓራራይ የዜማዎች ኅብረት ዜማቸው መልካም ከሆነ ከመሰንቆና ከእንዚራ መደርደር (መመታት) ጋር ያመሰግኑታል” ማለት ነው ። (ያሬድናዜማው)
ከዚህ በላይ እንዳየነው መልክና ስልት ያለው ጩኸት ሁሉ ዜማ አለው ፥ ዜማ ነው ፥ ዜማ ይባላል ።
ዜማን በሁለት ክፍል ማየት እንችላለን።
- መንፈሳዊ ዜማ
- ሕዝባዊ ዓለማዊ ዜማ
- መንፈሳዊ ዜማ
መንፈሳዊ ዜማ የምንለው በቤተ እግዚአብሔር እና እንዲሁም በዓበይት በዓላት በሕዝብ አደባባይ በእውነተኞች የዜማ ሊቃውንት በቅዱስ ያሬድ ደቀ መዛሙርት በድጓ በአቋቋም መምህራን የሚቀርብ እውነተኛው ያሬዳዊ የምስጋና ዜማ ነው ። /መዝ 5 ፥ 3 ። መዝ 62 ፥ 6 ። መዝ 11 8 ፥ 62/
ስልቱ የተወሰደው ምንጩና መገኛው መንፈሳዊ ዜማ ነው ። ነገር ግን ስሙ እንደሚያመለክተው የሚውለው እንደ ሕዝቡ ባሕልና ሥርዓት ለዘፈንና ለልቅሶ ለዋይታ ለሽለላ (ለጃሎታ) ለቅሮሮሽ (ቅርርቶ) ወዘተ ነው ። ሕዝቡ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆነ እንደ ሆነ “ሆ!” እያለም በሆታ ይዘምራል ። እግዚአብሔርንም ያመልክበታል ። ለምሳሌ በሀገራችን “ሆ! ነይ ነይ እምዬ ማርያም ፤ በወት ግባ በወት ያገራችን ታቦት ፤ ኤልያስ በሠረገላ ፤ ኧረሰይ አማኑኤል፤…” ሌሎችም በሕዝብ ዜማ የሚቀርቡ የበዓል የሕዝብ ዜማዎች ናቸው ። ዛሬ ዛሬ ግን ዳብሮና ሰፍቶ በልዩ ልዩ ሕዝባውያን ዘማሪዎች ተቀናጅቶ ሲዘመር ይታያል ። ደስ የሚያሰኝ ነው ።
ሕዝብ ከእግዚአብሔር የተለየ ከሆነ ግን በሕይወቱ ስለ አጋጠመው ገጠመኝ ስለ ሥጋ ፍላጎቱ ስለ ምኞቱ ይዘፍንበታል ። በሌላም መልኩ ደግሞ ስለ ሀገሩ ስለ ወገኑ ያለውን ፍቅር ይገልጽበታል ።
መንፈሳዊውም ሆነ ሕዝባዊው ዜማ በአንድ ነገር ይገናኛል ። መንፈሳዊው ዜማ የሥጋንም የመንፈስንም ጉድለትና ክብር ፣ ሞትና ሕይወት ፣ ጽድቅና ኲነኔ ፣ ሌላም ሌላም ሲገልጽ ። ዓለማዊው ዜማ በበኩሉ የዓለሙን ጉድለትና ምኞት ይገልጻል ። ሁለቱም የሰውን የውስጥ ስሜት በመግለጽ አንድ ይሆናሉ ። ይዞታቸውና መልእክታቸው ግን ፍጹም የተለያየ ነው ።
ከሰው ልጅ ስሜት አንጻር ዜማ ሲታይ ከገነት የተለየ ከእግዚአብሔር የራቀ የሰው ልጅ በመቆዘም በማንጐራጐር በደሉን ማሰብ ማንነቱን ማስታወስ ከእግዚአብሔር እርዳታ መጠየቅ ፥ ብሶቱንም መግለጽ የቻለበት መንገድ ነው ። ከዚያ በፊት ግን (ከስህተት በፊት) መታከትን ድካምን በማያስከትል የምስጋና ቃል ሕይወቱ የተመላ ነበር ። ከውድቀት በኋላ ግን እርዳታ ፈላጊ ሆነ ። ጩኸቱን እንደ ሀገሩ ልማድ እና እንደ ጸጋው መጠን በልዩ ልዩ ሥነ ዜማ ማቅረብ ጀመረ ። የተፈረደበትን ፍርድም ሆነ የተፈረደለትን በጐ ነገር በዜማ መግለጽ ጀመረ ። የዜማ መጻሕፍትም ዋና ማዕከላዊ አስተምህሮ የሰው ልጅ ሞትና ሕይወት ፣ የእግዚአብሔር ፍርድና ምሕረት ናቸው ።
ቅዱስ ያሬድ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የተማወቀ ፥ በቅዱሳት መጻሕፍት እውቀት የተራቀቀ ሊቅ ፣ በጸጋ እግዚአብሔር የተቃኘ ፥ በሥነ መለኮት አስተምህሮው የላቀ ፥ ምጡቅ ሰው እንደ ነበር ድርሰቶቹና የቤተ ክርስቲያን ታሪክም ምስክሮች ናቸው ። ቅዱስ ያሬድ ኅዳር 5 ቀን 534 ዓ.ም ከሰማይ ድምጽ ሰምቶ ሀብተ ዜማ ተሰጥቶት አፄ ገብረ መስቀል በመስከረም 25 ቀን 534 ዓ.ም ነግሠው እርሱ በኅዳር ከጣዕሙ ብዛት የተነሣ አጥንት የሚያለመልም ዜማ ደርሷል ።
ጥቅስ በግእዝ፤ “ወሰምዐ በህየ ቃለ እንዚራ ወቃለ አርጋኖን ወቃለ መሰናቅው እንዘ ይሴብሕዎ ወይዌድስዎ ወየአኲትዎ ለፈጣሬ ሰማያት ወምድር በስብሐት ወበማኅሌት በቅኔ ወበልዑል ዜማ ነግሀ ወሠርከ ይሴብሕዎ ለንጉሥ ዐቢይ በዓውደ መንበሩ ቅዱስ…አነ እነግረከ በዘትሌቡ ጸውዕ ስሞ ሐዲሰ ለእግዚአብሔር ዘውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ወትነስእ ማኅሌተ እም ዕሥራ ወአርባዕቱ ካህናተ ሰማይ በበዜማሁ ወይቤ ጐስዐ ልብየ…”
ትርጉም በአማርኛ፤ በዚያም የእንዚራን ፣ የአርጋኖን ፣ የመሰንቆን ድምጽን እንዲሁም ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ትልቁን ንጉሥ እግዚአብሔርን ጧትና ማታ በስብሐትና በማኅሌት በቅኔ ጧትና በሰርክ ከፍ ባለ ዜማ ካህናተ ሰማይ መላእክት በተቀደሰ ዙፋኑ ዙሪያ ሲያመሰግኑ ሰማ…እንግዲያውስ እኔ የምታስተውልበትን እነግርሃለሁ ። የእግዚአብሔርን አዲስ ስም ጥራ ። ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይም በየአይነቱ ዜማ ያለውን ማኅሌት ትማራለህ የሚል ቃል ሰማ … ልቤ መልካም ነገርን አውጥቶ ተናገረ።” ብሎ ተናገረ ፤ የዜማ ሐብትም ተሰጠው ። (ጥንታዊ ሥርዓተ ማኅሌት ዘአቡነ ያሬድ ሊቅ ገጽ 23-24) ተብሎ እንደተጻፈ።
ግእዝ፦ ግዕዝ ማለት የዜማ መጀመሪያ የመጀመሪያ ዜማ አንደኛ ቀዳሚ ማለት ነው
ዕዝል፦ ዕዝል ማለት በግዕዝ ላይ ታዝሎ ተደርቦ የሚዜም የሚዘመር ከባድ የበዓል የደስታ ቀን ዜማ ማለት ነው።
ዓራራይ፦ አራራይ የሚያራራ፤ ልብ የሚመስጥ ትዝታ ተመስጦ የሚያስከትል ዜማ ማለት ነው።
ቅዱስ ያሬድ በእነዚህ የዜማ ስልቶች ላይ ተመሥርቶ ስለ እግዚአብሔር መኖር ፣ ስለ ፍጥረተ ዓለም ፣ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ ፣ ስለ ምሥጢረ ሥጋዌ በአጠቃላይ ትምህርተ ሃይማኖትን ፣ ነገረ መለኮትን፣ ክብረ ቅዱሳንን መሠረት አድርጐ በሰፊው ዘምሯል ። አምስቱ የቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍትም (ድጓ ፥ ጾመ ድጓ ፥ ምዕራፍ ፥ ዝማሬ ፥ መዋሥዕት) የሚያረጋግጡት ይህንኑ ነው ።
1/ መለከት፦ ከቀንድ፣ ከብረት እና ከብር የሚሠራ የእግዚአብሔር ጉባኤ መጥሪያ ፥ ለመዘመሪያም የሚያገለግል መሣሪያ ነው ። አንዳንድ ጊዜ ቀንደ መለከት ይባላል ፣ ከቀንድ መሠራቱን ያመለክታል ። መለከትን ለመጀመሪያ ጊዜ የሠሩት የቃየል ልጆች ናቸው ። የተጠቀሙበትም መጀመርያ እነርሱ ናቸው ። በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምናነበው ለመጀመሪያ ጊዜ ከተማ የቆረቆሩ ፥ የተፈጥሮ ሕግን ሽረው ከአንድ በላይ ሚስት ማግባትን የጀመሩ ፥ የነፍሰ ገዳዩ እና የቀበዝባዛው ፥ የእግዚአብሔር ልጆች ከመባል የሰው ልጆች ለመባል ያበቃው የእርጉሙ የቃየል ልጆች ናቸው ። መለከትን የሠሩት በከተማቸው ሊዘፍኑበት ሊያንጐራጉሩበት ነበር ። ከእግዚአበሔር የተለየች በሕገ ተፈጥሮ /ሕሊና/ ላይ ያመጸች ፥ ሞት የተፈረደባት ሕይወታቸውን ለማባበል የዜማ ዕቃ ልዩ ልዩ ነገሮችን እየቀጠቀጡ ይሠሩ ነበር ። ምሥጢሩ ግን በደለኛው ማንነታቸው /ሕይወታቸው/ እርዳታ እየፈለገ ሰላም አጥቶ መቆዘምና ማንጐራጐር መጀመሩን ያመለክታል ። ዛሬም አንድ ሰው በሠራው ኃጢአት ምክንያት የሕሊና ሰላም እንደሚያጣ እና ሁከት እንደሚነግሥበት ። እነርሱም በአንደበታቸው ጩኸት ሊወጣላቸው ያቃታቸውን ከልባቸው የተረፈውን የውስጥ ጩኸት በመሣሪያ እየታገዘ ይወጣ ጀመር ።
እግዚአብሔር ሰውን ለምስጋና እንጂ ለዘፈን አልፈጠረውም ፤ የሚያዝነውም ሆነ የሚደሰተው የሚዘምረውም ሆነ የሚዘፍነው ሰው ያለው አንድ ስሜት ብቻ ነው ። ሰው በቅጽበት ልዩነት ሊሆን ይችላል እንጂ በአንድ ጊዜ ደስታ እና ኃዘን አይሰማውም ። ስሜቱ አንድ ብቻ ስለ ሆነ ግን እንደ ሁኔታው ስሜቱ ይለዋወጣል ። ሰይጣን የሰው ልጆችን የተፈጥሮ ጸጋ የሆነውን የምስጋና ስሜት በመለወጥ ለብሶት ጩኸትና ለዘፈን እንዲጠቀሙበት ገፋፋቸው ። ለእግዚአብሔር ክብር እንዳይዘምሩ በኃጢአት አውሮ ወንዱ ስለ ሴቶች ሴቶቹም ስለ ወንድ ማቀንቀን ጀመሩ ። የእግዚአብሔር ፍቅርም ክብርም ከነሱ ራቀ ። በመሆኑም በዓለም የሰው ልጆችና የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው በሁለት ሲከፈሉ መለከትን ሰርተው ይጠቀሙ የነበሩት የሰው ልጆች የተባሉ የቃየል ልጆች ነበሩ ። /ዘፍ 4 ፥ 21 ዘፍ 2 ፥ 6/
በኋላ ግን መለከት ለመንፈሳዊ አገልግሎት ዋለ ። የእግዚአብሔር ክብር ታወጀበት ። የቃየል ልጆችም የእግዚአብሔር ፍጥረቶች ናቸው ። አእምሮንም ሰጥቶ የፈጠራቸው እግዚአብሔር ነው ። ለሰይጣን የራሱ የሆነ ንብረት የለውምና የደከሙበት ዕቃ ለበጐ ዋለ ። ሰይጣን በእግዚአብሔር ፍጥረት በደል ቢሠራ ያሳዝናል እንጂ ፥ እግዚአብሔር በኃጢአት አልገዛልህም ያሉትን ቢገዛቸው የሚያስገርም አይደለም ፤ ንብረቱ ናቸውና ።
የመለከት አገልገሎት የተገለጸባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከዚህ የሚከተሉት ናቸው ። ዘኍ 10 ፥ 1-10 ። ኢያ 6 ፥ 20 ። 2ዜና 5 ፥ 12-13 ። 2ሳሙ 6 ፥ 15 ። 1ዜና 15 ፥ 28 ።
2/ በገና፦ አሥር አውታር ያለው የዜማ ዕቃ ነው ። ለመጀመሪያ ጊዜ የሠሩት የተጠቀሙበትም እንደ መለከት ዘፋኞች የቃየል ልጆች ናቸው ። ዘፍ 4 ፥ 21 ።
ለዘፈን ብለው የሠሩት የሰው ልጆች /የሥጋና የደም ሥራ የሚሠሩ/ ናቸውና ዘፈኑበት ። /ዘፍ 6 ፥ 2/
የእግዚአብሔር ልጆች ደግሞ ለመዝሙር ለምስጋና ተጠቀሙበት ፣ እኛም እንጠቀምበታለን ። ቁም ነገሩ ከሠሪዎቹና ከመሣሪያው ላይ ሳይሆን ከአጠቃቀሙ ላይ ነው ። ልዩ የመዝሙር መሣሪያም ሆነ ። ስለ በገና የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ። ዘፍ 4 ፥ 21 ።1ሳሙ 16 ፥ 16-23 ። 1ዜና 15 ፥ 21 ። መዝ 32 ፥ 2 ። ራእይ 5 ፥ 8 ።
3/ ክራር፦ የበገና ዓይነት የዜማ ዕቃ ነው ። የዘመናችን ክራር አምስት ወይም ስድስት የጅማት አውታሮች አሉት ። ክራርን በበገና ዓይን ካላየነው በቀር በክራር ሲዘመር እንደ ነበር ክራር የመዝሙር መሣሪያ እንደ ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር መሳሪያነት ጠቅሶት አናገኝም ። በስም ግን ጠርቶት ይገኛል ። ናቡከደነጾር ጣዖቱን ካሳጀበባቸው መሣሪያዎች አንዱ ክራር እንደ እንደ ነበረ በትንቢተ ዳንኤል ተጠቅሶ እናነባለን ። 3 ፥ 5-7 ።
ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ልሳን ሲናገር ሕይወት የሌላቸው መሣሪያዎች ሲቃኙ እንደ ቅኝታቸው ስሜት የሚሰጥ ድምጽ ይሰጣሉ ። እንዴት እናንተ በልሳን እንናገራለን እያላችሁ ትርጉም የለሽ ነገር ትናገራላችሁ ብሎ የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ግብዞች ባስተማረበት ክፍል ለምሳሌ ከጠቀሳቸው መሣሪያዎች ክራርና ዋሽንት ይገኙበታል ። 1ቆሮ 10 ፥ 7 ።
በተጨማሪም ክራር በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን /የአሁኑን ዘመን አይጨምርም/ የጐላ የመዝሙር ቦታ ተሰጥቶት አልተነበበም ። ይሁን እንጂ በክራር መዘመሩ በደል አይደለም ። ቤተ ክርስቲያን ግን ባትለየውም እውቅና አልሰጠችውም ። በአሜሪካ ያሉት አባቶች ጉባኤ ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ በኢትዮጵያ ያሉት አባቶች ጉባኤ ቅዱስ ሲኖዶስ በውሳኔው ውስጥ በተራ ቍጥር አልጠቀሰውም ።
4/ ዋሽንት፦እንደ ክራር ናቡከደነጾር ጣዖት ካሳጀበባቸው መሣሪያዎች አንዱ ነው። ዳን 3 ፥ 5-7። 1ቆሮ 14 ፥ 7 ።
ይሁን እንጂ ለሰይጣን ንብረት ስለሌለው እንደ አጠቃቀሙ ስለ ሆነ ለእግዚአብሔር ክብር መዋሉ ባይነቅፍም ቤተ ክርስቲያን ግን እውቅና ሰጥታ በዚህ አመስግኑ ብላ በውሳኔ አላስተላለፈችም ። ዋሽንት በሀገራችን ባሕል የሕዝብ መጫወቻ ነው ። በመሆኑም የከበረ ዕቃ ነው ።
5/ መቋሚያ፦ በቅዱስ ያሬድ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመዝሙር የዋለ የዜማ ማሣሪያ ፥ የመዝሙር መሳሪያ ነው ። የሚሠራውም ቀጥ ካለ እንጨት ሁኖ ጫፉ ላይ የቀንድ የብር የነሐስ የብረት የእንጨት መያዣ (መደገፊያ) ያለው ነው ። በመጽሐፍ ቅዱስ አልተጠቀሰም እግዚአብሔር በየዘመናቱ አዳዲስ ጸጋ ለሰዎች ስለሚሰጥ ለአባታችን ለቅዱስ ያሬድ የሰጠው ልዩ የማመስገኛ ዘንግ ነው ። መጽሐፍ ቅዱስ በመቋሚያ አመስግኑት አላለም ብለን የእግዚአብሔርን ጸጋ ልንቃወም አንችልም በየዘመኑ አዲስ ጸጋ የሚሰጥ እግዚአብሔር ነውና ። ቅዱስ ያሬድ በዚህ ዘመን ተነሥቶ ቢሆን ግን መቋሚያህን አስቀምጥ የሚሉ ከሳሾች በተነሡበት ነበር ።
6/ ከበሮ፦ፍጹም ለእግዚአብሔር ክብር የዋለ የመዝሙር ዕቃ ነው። ለድል ቀን መታሰቢያ ይመታ ነበር።ዘጸ 5 ፥ 20
ለእግዚአብሔር ክብር መዝሙር የሚቀርብበት መሣሪያ ነው ። መዝ 149 ፥ 4 ።
ለታቦት ክብር ይዘመርበታል ። 1ሳሙ 18 ፥ 6 ። 2ሳሙ 6 ፥ 5 ።
በአንጻሩም የእግዚአብሔር ሕዝብ እግዚአብሔርን ሲያመሰግንበትን ዓለም ደግሞ ወስዳ ትዘፍንበታለች ። ያ ግን የከበሮን አገልግሎት ክብር አይቀንሰውም ።
7/ ጸናጽል፦ ሁለት ዓይነት ጸናጽል አለ ። አንደኛው የማጨብጨቢያ ጸናጽል ናቁስ ይባላል ። እንደ መረዋ ያለ ነው ይላሉ አበው ። አሁን እኛ ዛሬ አንጠቀምበትም ፣ መሣሪያውም የለንም ። ሁለተኛው አሁን የምንጠቀምበት ዓይነት ጸናጽል ነው ። ከነሐስ ከብር ከወርቅ ይሠራል ። ጸናጽል የተቀደሰ የመዝሙር መሣሪያ ነው ። 2ሳሙ 6 ፥ 5 ። መዝ 150 ፥ 5 ። 1ዜና 13 ፥ 8 ። 2ዜና 5 ፥ 13 ። 1ቆሮ 13 ፥ 1 ።
8/ መሰንቆ፦ “ሰንቀወ” ሰነቃ ፥ ሞዘቀ ፥ መታ ፥ አስጮኸ ፥ ከረከረ ከመሣሪያው ጋር ጮኸ ፥ አዜመ ፥ ዘመረ ፥ ገጠመ ፥ አጉረመረመ ከሚለው የግእዝ ቃል የመጣ ነው ። ግሩም የሆነ የመዝሙር መሣሪያ ነው ። ኢሳ 5 ፥ 12 ። ኢዮ 21 ፥ 12 ። ኢሳ 23 ፥ 16 ። ሲራ 22 ፥ 6 ። ዮዲ 16 ፥ 1 ። መዝ ። 150 ።
9/ እንዚራ፦ “አንዘረ” መታ ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ይመስላል ። ግን አንዳንድ መጻሕፍት የሚመታ መሣሪያ ሳይሆን በእስትንፋስ የሚነፋ መሣሪያ እንደ ሆነ ያመለክታሉ ። የእንዚራን ትክክለኛ መልክ እስከ አሁን ማግኘት አልተቻለም ። አንድ አንድ አባቶች ደግሞ እንዚራ አኮርዲዮን ነው ይላሉ ። ለማንኛውም ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሷል ። “ሰብሕዎ በከበሮ ወበእንዚራ” መዝ 150 ።
ወአስተንፍሲ ውስተ አፉየ ከመ እኩን እንዚሁ ለበኩርኪ ። (አባ ጊዮርጊስ)
እለ ይነፍሑ እንዚራተ” (ፍትሐ ነገሥት 23 ቍ 8022)
ዛሬ ይህ ነው ተብሎ በቅርብ አግኝተን ባንጠቀምበትም እንዚራ አስደዳች የሆነ ድምፅ ያለው የመዝሙር መሣሪያ እንደ ሆነ እንማራለን እንገነዘባለን ።
10/ እምቢልታ፦ ታላቅ ዋሽንት ውስጡ ክፍት የሆነ የጥንት ዘመን ነገሥታት መኳንንት ደጃዝማች ብቻ ይጠቀሙበት የነበር ከቀርቅሐ ወይም ከሸንበቆ የሚሠራ ነው ። በብሉይ ኪዳን የታወቀ የመዝሙር መሣሪያ ነው ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎች ። 1ዜና 15 ፥ 28 ። ኢዮ 21 ፥ 12 ፤ 30 ፥ 31 ። መዝ 150 ፥ 4 ።
አሁንም በሀገራችን በትልልቅ አድባራት ለምስጋና ሲውል ይታያል ። የከበረ የመዝሙር መሣሪያ ነው ። ከዋሽንት ጋር ተመሳሳይነት ስላለው ዋሽንትም በእንቢልታ ዓይን ስለሚታይ ሳይሆን አይቀርም መዝሙር የሚቀርብበት ።
11) አርገኖን /ኦርጋን
በወርኃ ጥር በጥምቀት በዓል ላይ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ስለ አርጋኖን ተጠይቀው የሰጡትን መልስ መነሻ በማድረግ ማኅበረ ቅዱሳን ነኝ ብሎ ራሱን የሚጠራው የግለሰቦች ድርጅት ያሰማራቸውና ራሳቸውን መምህራን ብለው በሚጠሩ ግለሰቦች በኩል መልእክቱን አዲስ ትምህርት ወደ ቤተ ክርስቲያን ይግባ እንደ ተባለ አድርገው አባታችንን በመክሰስ ፣ በስደት የምትገኘውን የኢትዮጵያ ኦርቶ ዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመቃወም ምእመናንን ግራ ለማጋባት ጥረት አድርገዋል ። “የፈረንጅ መሣሪያ ወደ ቤተ ክርስቲያን በማስገባት አዲስ ሥርዓት እየሠሩ ስለ ሆኑ ተዋጉአቸው” ሲሉም ተሰምተዋል። «አዲስ ክርስቲያን ከጳጳስ ይቀናል» እንዲሉ ይህ ግብዝ ቡድን ራሳቸውን ለቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ አሳልፈው የሰጡትን ታላቅ አባት በማጣጣል እኔን ስሙኝ እነሱን ግን አትቀበሏቸው ሲል ማንነቱን ገልጧል ።
ይህ ቡድን ለቤ/ክ የማይታዘዝ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር አፍርሶ በራሱ መልክለመሥራት ሌትና ቀን በመሥራት ላይ ያለ ፤ የቤተ ክርስቲያንን ሀብተ ክህነት በማርከስየጀምላ ክህነት ፥ በገንዘብ በገዛቸው ሰዎች በኩል ለአባላቱ የሚያሰጥ፣ እንደ ስምዖንመሰርይ ጸጋ እግዚአብሔርን በገንዘብ ለመግዛት ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ መሆኑንበሀር ቤት የሚገኙ አባቶች በመናገር ላይ መሆናቸው ዕለት ዕለት የምንሰማው የቤተክርስቲያን አሳዛኝ ክስተት ነው ። ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግና ሥርዐት በመፍረስ አባቶችንም በመደፋፈር ታሪክ ይቅር የማይለው በደል እየሰራ መሆኑን ቤተ ክርስቲያን በመናገር ላይ ናት።[1]
ይህ ቡድን የቤተ ክርስቲያን ፈተና መሆኑ እየተገለጠ ባለበት በአሁኑ ወቅት የሕዝቡን ትኩረት ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመለወጥ አስቦ እየዘራው ያለ የሀሰት መልእክት ነው ። ሁላችን ልናውቅ የሚገባው ነገር ቢኖር ብፁዕ አባታችን ያስተላለፉት መልእክት ፣ ከዚህ ቀደም በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኖ ውሳኔው የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን በሆነው በነጸብራቅ መጽሔት በ2005 እ ኤ አቈጣጠር ታትሞ ለምእመናን የተዳረሰ ሲሆን ፤ አሁን እንዳዲስ ለም አነሣው?
በዚያውስ ላይ በሎሳንጀለስ ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶ ዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ላለፉት 30 ዓመታት በአርጋኖን እየተጠቀሙ እንዳሉ ያውቃል ፣ እንዴት አሁን እንደ አዲስ አድርጎ አባታችንን ለመክሰስ ተነሣ ? በስደት የሚገኙ አባቶች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በአርጋኖን እየዘመረች ሳለ፣ ይህ ቡድን ሳይፈጠር መሰደዳቸውን ያውቃል ፤ አርጋኖንን ከቤ/ክ አስወጥቻለሁና የእናንተም ሲኖዶስ ያጽድቅልኝ ብሎ አልጠየቀ። ለምን ከመሬት ተነሥቶ ይከሳል? ።
የአዲስ አበባው ሲኖዶስ በአርጋኖን ዘምሩ ብሎ ወስኗል በማለት በራሱ መጽሔት በሐመር ላይ የጻፈው ይህ ቡድን ፥ አርጋኖን የመዝሙር መሣሪያ መሆኑን ሳያውቅ ነውን ? [2] አሁን ለምን ሃይማኖቱን ካደ ? አሁን አሁን በነዚህ ሰዎች በኩል አርጋኖንን በተመለከተ ብዙ ነገር ሲባል እንሰማለን ።
ጥናቱም እነሆ !
አርጋኖን እና ስያሜው
አርጋኖን በግእዝ
ኦርጋኖን በግሪክ
አርቀኑን በዓረብኛ
ዑጋብ በዕብራይስጥ
ኦርጋን በእንግሊዝኛ [3]
ኦርጋኖን/church organ፦ የመዝሙር የማኅሌት የዘፈን የዜማ ዕቃ ነው ። አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌም ኦርጋንን ከነሥዕሉ በግእዝ መዝገበ ቃላታቸው ላይ አስቀምጠውታል።
አርጋኖን /ኦርጋን/ የተሠራው ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ በናይል /በአባይ/ ወንዝ አጠገብ በእስክንድርያ በአንድ ግሪካዊ ዝርያ ባለው ሰው ነው ። የተሠራበት ዘመንም ከክርስቶስ ልደት በፊት (በብሉይ ኪዳን ዘመን) ሦስት ዓመት ቀድሞ ነው ። ስለዚህም ስለ ኦርጋኖን /ኦርጋን/ ታሪክ የተጠና ጥናት እንዲህ ይላል ። ኦርጋን /አርጋኖን/ ቀስ በቀስ እያደገ እየተቀናጀ ይምጣ እንጂ ከጥንት ጀምሮ ነበር ። በኋላ ግን ልዩ ልዩ ክፍል ያለው፦ “mouth organ, pipe organ, etc…” እየተባለ የሚጠራ እንዲሁም church organ የሚባለው ልዩ መሣሪያ ከጥንት ጀምሮ እንደ ነበረ ታሪክ ያሳያል ። “Greek engineer working in Alexandria in the third century BC….Which the organ was known in red, beginning in the Nile Delta region around Alexandria….’’[4]
ጥናቶች ሁሉ እንደሚያመለክቱት ኦርጋን /አርጋኖን/ ጥንታዊ የዜማ ዕቃ ነው ። በዘመናችን ያሉ አንድ አንድ ሰዎች በዘመናዊ መሣሪያ አንዘምርም ለማለት ከሚጠቅሷቸው ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች “ምዕራባዊ ነው” እና ‘ዘመናዊ ነው’ የሚሉ አስተሳሰቦች ሲሰነዝሩ ይሰማሉ ። በመሠረቱ በመቼም ይሠራ የትም ይሠራ አንድን ነገር ለመቀበል የሚከለክል የቤ/ክ ቀኖና የለም ። ግን ታሪክ እንደሚያስረዳው ምዕራቡ ዓለም ለእድገቱ የሚጠቅሙትን ጥበቦችና ግኝቶች ከግሪክ እና ከአፍሪካ ለቃቅሞ ሲወስድ አብሮ የወሰደው መሣሪያ ነው እንጂ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሠራው አባይ ወንዝ አጠገብ ነው ።
ሮም በወደቀች ምሥራቅ ኤሮፕ ባደገች ጊዜ በቢዛንታይን ዘመነ መንግሥት እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን ከመከፋፈልዋ በፊት በቈስጠንጢኖስ ዘመነ መንግሥት አርጋኖን /ኦርጋን/ ልዩ የእግዚአብሔር ስም መቀደሻ ፥ የዲያብሎስ ድል መንሻ ፥ የመዝሙር መምነሽነሽያ መሣሪያ እንደ ነበር ጥናቶች ያሳያሉ ። የእኛ አባቶች እነ ቅዱስ ያሬድ እነ አባ ጊዮርጊስም ስለ አርጋኖን /ኦርጋን/ ጣዕም ብዙ ዘምረው ጣዕሙን ተናግረው በመጻሕፍቶቻቸውም ጽፈው ምሳሌም መስለውበት እናገኛለን ። የቤተ ክርስቲያን ታሪክና መጽሐፈ ስንክሳርም ያመሰክራሉ።
የቅዱስ ያሬድ እና ፥ የአባ ጊዮርጊስ ምስክርነት
- ቅዱስ ያሬድ ስለ አርጋኖን /ኦርጋን/ ምን አለ ?
የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት መልካም ነገርን ሁሉ በምሳሌ ይጠቀሙበታል ። አባታችን ቅዱስ ያሬድ ወንጌላዊ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድን እያስታወሰ በዘመረበት ክፍል ፥ የቅዱስ ዮሐንስን አስተምህሮ ጣዕም የቃሉን መዓዛ ለመግለጽ ከተጠቀመባቸው አንዱ አርጋኖን /ኦርጋን/ ነው ። ለምሳሌ እመቤታችንን ቅዱስ ኤፍሬምና አባ ሕርያቆስ በመሰንቆ በጸናጽል በበትረ አሮን እየመሰሉ እንደ ተናገሩት ያለ ነው ።
ጥቅስ በግዕዝ ፥
- ሰባኬ ወንጌል ዮሐንስ አርጋኖነ ትንቢት ዘይደምጽ ለቤተ ክርስቲያን ።
ትርጉም ፥
ሰባኬ ወንጌል ዮሐንስ ለቤተክርስቲያን መልካም ድምጽ የምትሰጥ ፥ በትምህርትህ የምትመስጥ የቤተ ክርስቲያን አርጋኖን /ኦርጋኖን/ ነህ” ። ይላል ቅዱስ ያሬድ ። [5]
ጥቅስ በግዕዝ
- ከመ ዝብጠተ መሰንቆ አርጋኖን ስብሐቶሙ ለእሙንቱ ካህናት”
ትርጉም
የካህናቱ ምስጋና መሰንቆ አርጋኖን ሲመታ እንደሚመስጠው ድምጽ ነው” ይላል ቅዱስ ያሬድ ። [6]
ከዚህ በተጨማሪ ቅዱስ ያሬድ ለመጀመሪያ ጊዜ ዜማን ሲደርስ በተመስጦ ከሰማቸው የዜማ ድመሣሪያ ድምጾች አንዱ የአርጋኖን /የኦርጋን/ ድምጽ እንደ ነበር ገድለ ቅዱስ ያሬድ ይናገራል ።
ጥቅስ በግእዝ፤
- ወሰምዐ በህየ ቃለ እንዚራ ወቃለ አርጋኖን ወቃለ መሰናቅው እንዘ ይሴብሕዎ ወይዌድስዎ ወየአኵትዎ ለፈጣሬ ሰማያት ወምድር በስብሐት ወበማኅሌት በቅኔ ወበልዑል ዜማ ነግሀ ወሠርከ ይሴብሕዎ ለንጉሥ ዐቢይ በዓውደ መንበሩ ቅዱስ.።
ትርጉም በአማርኛ፤
በዚያም የእንዚራን ፥ የአርጋኖን ፥ የመሰንቆን ድምጽ እንዲሁም ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ትልቁን ንጉሥ እግዚአብሔርን በስብሐትና በማሕሌት (በቅኔ) ከፍ ባለ ዜማ ጧትና በሰርክ በተቀደሰ ዙፋኑ ዙሪያ ሲያመሰግኑ ሰማ…” [7]
ከዚህ በላይ እንዳየነው አርጋኖን ከጥንት ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን የነበረ አሁን ግን ስሙን እንጂ መልኩን ፣ ዜናውን እንጂ ግብሩን ባለማገናዘብ በአርጋኖን እንዘምራለን “በኦርጋን” አንዘምርም የሚሉ ሰዎች ተነስተዋል ። አነጋገራቸው በከበሮ እዘምራለሁ “በድራም” አልዘምርም ፤ ውኃ እጠጣለሁ “ዋተር” አልጠጣም እንደማለት ነው ። አርጋኖን ኦርጋን ነውና ።
- አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ስለ አርጋኖን /ኦርጋን/ የተናገሩት ምንድን ነው?
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ጥንት ለኮመልዝ ይባል በነበረው ዛሬ ወሎ ክፍለ ሀገር አማራ ሳይንት ልዩ ስሟ ሸግላ ከሚባል ቦታ ነው የተወለዱት ። አባታቸው ሕዝበ ጽዮን እናታቸው እምነ ጽዮን ይባሉ ነበር ። በትምህርት በገዳማዊ ሕይወት አድገው ብዙ መጻሕፍት ጽፈዋል ። ከመጻሕፍቶቻቸው መካከል “አርጋኖን” እና “እንዚራ ስብሐት” የሚባሉት ይገኙባቸዋል ። እነዚህ መጻሕፍት በመዝሙር መሣሪያዎች የተሰየሙ ናቸው። በአጠቃላይ አባ ጊዮርጊስ ከአሥር በላይ መጻሕፍት ደርሰው ተጋድሏቸውን ፈጽመው በ1413 ዓ.ም አርፈዋል ። አባ ጊዮርጊስ ከተነሡበት ዘመን ትንሽ ቀደም ብሎ በአስረኛው ምእተ ዓመት የኦርጋን አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን በሰፊው ይሰጥበት የነበረበት ዘመን ነበር የአርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዲክሽነሪ ስለ አርጋኖን በሰጠው ሐተታ ላይ ይናገራል ።[8]
አባ ጊዮርጊስም የአርጋኖኑን ድምጽ እያስታወሱ ስለ እመቤታችን ምስጋና ሲያዘጋጁ በዘመናቸው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጣዕም ያለው ውዳሴ ይቀርብበት በነበረው የመዝሙር መሣሪያ በአርጋኖን /በኦርጋን/ መስለው የምስጋናውን ጣዕም እንደ አርጋኖን ድምጽ ለዛ ያለው እንዲሆን በማሰብ መጽሐፉቸውን አርጋኖን ብለውታል ። እመቤታችንንም በአርጋኖን /ኦርጋን/ መስለዋታል ። አርጋኖን የተሰኘውንም መጽሐፋቸውን መጻፍ ሲጀምሩ እንዲህ ይላሉ፥
ጥቅስ በግዕዝ
- “ንጽሕፍ እንከ ዘንተ መጽሐፈ ዘይሰመይ አርጋኖነ ውዳሴ ወመሰንቆ መዝሙር ወእንዚራ…”
ትርጉም
“የምስጋና አርጋኖን የመዝሙር መሰንቆ እንዚራም የሚባል ይህንን መጽሐፍ መጻፍ እንጀምራለን….” ብለው መጽሐፉን ጀምረዋል ። አርጋኖን መሰንቆ እንዚራ የሚባሉት የማመስገኛ መሣሪያዎች ጣዕም ያለው ድምጽ እንደሚሰጡ አባ ጊዮርጊስ የደረሱት የጸሎት መጽሐፍ ነፍስን የሚያስደስት በመሆኑ መጽሐፉን አርጋኖን /ኦርጋን/ መሰንቆ እንዚራ በተባሉ መሣሪያዎች መስለው ተናግረዋል ። (አርጋኖን ዘሰኑይ ገጽ 9) እንዲሁም ሊቁ ስለ አርጋኖን የሚከተለውን አብራርተዋል።
ጥቅስ በግዕዝ
- “ወከማሁ ሊተኒ ርድአኒ ለወጢነ ጽሒፈ ውዳሴሃ ለመርዓተ አብ ወአሠልጥነኒ ካዕበ ለፈጽሞቱ ወለከናፍርየኒ ወአፉየ ረስዮን ከመ አርጋኖን ወኃይለ መንፈስ ቅዱስ ይዝብጦን ዘበልሳን ከመ ይንብባ ዘይኤድሞሙ ለሰማዕያን ወረስዮ ለአፉየ ከመ መሰንቆ ወድኅንጻ መንፈስ ይጉድኦ ከመ ይንቁ ሐዋዘ ወይሰንቁ ምዑዘ ። ወእለ ያጸምኡ ይኩኑ ፍሱሐነ በሰሚኦቱ ፥ ይትመሰጥ ህሊናሆሙ ላእለ ወአኮ ታህተ ፣ የሐልዩ ጽድቀ ወአኮ ኃጢአተ ፥ የሐልዩ ንጽሐ ወአኮ ርስሐተ ፥ የሐልዩ ይዋሄ ወአኮ ጽልሁተ ፥ የሐልዩ ትሕትና ወአኮ ትዕቢተ ፥ የሀልዩ ፍቅረ ወአኮ ቅንአተ ፥ የሐልዩ ልባዌ ወአኮ እበደ ፥ የሐልዩ ክብረ ወአኮ ኀሳረ ፥ የሀልዩ ዘኢይማስን ወአኮ ዘይማስን ፥ የሐልዩ ዘኢይበሊ ወአኮ ዘይበሊ ፥ የሐልዩ ዘበሰማያት ወአኮ ዘበምድር…” ።
ትርጉም ፤ “የአብ መሽራ የሆነችውን (የድንግልን) የምስጋና መጽሐፍ መጻፍ እንድችል እርዳኝ ። ለመፈጸምም እንድበቃ ሥልጣኑን ስጠኝ ። ከንፈሮቼን እና አንደበቴን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በልዩ ቋንቋ ሰሚዎችን ደስ የሚያሰኝ ነገር ይናገሩ ዘንድ እንደ አርጋኖን /ኦርጋን/ አድርግልኝ ። አንደበቴም እንደ መሰንቆ መልካም ሁኖ ይዘምር ዘንድ ምዑዝ ጣዕም ለዛ ያለው ድምጽ ይሰጥ ዘንድ ድኅንጻ መንፈስ /የመንፈስ ቅዱስ ቅኝት እንደ መሰንቆ አንደበቴን ያጫውተው ይምታው ። አርጋኖን /ኦርጋን/ መሰንቆ ሰሚዎቻቸውን ደስተኛ እንደሚያደርጉ እነርሱን የሰሙ በመሣሪያዎቹ ድምጽ እንደሚመሰጡ ፣ ይህንን የእመቤታችንን ውዳሴ የሚሰሙ ኅሊናቸው ይማረክ ። ኃጢአትን ያይደለ ጽድቅን ያስቡ ፥ ርስሐትን ያይደለ ንጽህናን ያስቡ ፥ ቅንአትን ያይደለ ፍቅርን ያስቡ ፥ ስንፍናን ያይደለ ጥበብን ያስቡ ፥ ውርደትን ያይደለ ክብርን ፥ የሚያልፈውን ያይደለ የማያልፈውን ፥ የሚያረጀውን ያይደለ የማያረጀውን ፥ በምድር ያለውን ያይደለ በሰማይ ያለውን ያስቡ….’ ማለት ነው ። [9]
አባ ጊዮርጊስ ከዚህ ሌላም መሰንቆ የሚሰነቃ መሣሪያ ለመሆኑ ፥ እንዚራ ደግሞ የድምጽ ፣ የእስትንፋስ መሣሪያ ስለ መሆኑ አርጋኖን /ኦርጋን/ ደግሞ በእጅ የሚነቃቃና የሚቃኝ የጣት መሣሪያ ለመሆኑ በልዩ ልዩ ስልት እሴብሕ ጸጋኪ በተባለው የዘወትር የቤተ ክርስቲያን ጸሎት ላይ ተናግረዋል ። ለምሳሌ፦
ሀ) ስለ መሰንቆ እንዲህ አሉ ፥
ጥቅስ በግእዝ “ምንት ረባሑ ለመሰንቆ ለእመ አልቦ ዘይሰነቅዎ”
ትርጉም
“የሚሰነቃው ፥ የሚመታው ፥ የሚከረከረው ፥ የሚሞዝቀው ከሌለ የመሰንቆ ጥቅሙ ምንድን ነው” ይላል ። ለዚህም የተጠቀሙት የግእዝ ቃል “ሰንቀወ” ሰነቃ መሰንቆ መታ የሚለውን መሆኑን ልብ ይሏል።
ለ) ስለ እንዚራ ደግሞ እንዲህ አሉ።
ጥቅስ በግእዝ “ወምንተ ይደምጽ ንቃወ እንዚራ ዘስቁል ለእመ ኢተነፍሐ በድርገታተ ማኅሌት” ይላል
ትርጉም
- “የተሰቀለው እንዚራ በአንድነት ካልተነፋ የእንዚራ ድምጽ እንዴት ሊሰማ ይችላል?” ማለት ነው ።
ከዚህ ላይ እንዚራ የእስትንፋስ መሣሪያ ለመሆኑ አባ ጊዮርጊስ “ለእመ ኢተነፍሐ” ብለው ነፍሐ (ነፋ) በሚል ገላጭ አንቀጽ ስለ ገለጹት የሚነፋ ልዩ መሣሪያ መሆኑን ልብ ይሏል ። ድርገታተ ማኅሌት ማለት ደግሞ በዜና መዋዕል እንደ ተጻፈው ልዩ ልዩ የመዝሙር መሣሪያዎችን የሚጫወቱ ሰዎች በኅብረት በሚያቀርቡት የዜማ ድግስ ላይ እንዚራ የእስትንፋስ መሣሪያ ሁኖ የሚቀርብ የድግስ አካል መሆኑን ያመለክታል ።
ሐ) ስለ አርጋኖን /ኦርጋን ደግሞ እንዲህ ብለዋል
ጥቅስ በግእዝ
- “በነቀልቃለ ስብሐት ሑኪዮ ለአርጋኖነ ኅሊናየ ከመ ኢያርምም እም ስብሐታተ ፍቅርኪ” ይላል ።
ትርጉም “የፍቅርሽን ምስጋና ከማቅረብ አንደበቴ ዝም እንዳይል አርጋኖን /ኦርጋን/ ኅሊናዬን (ልቤን) በምስጋና ስሜት ንውጽውጽታ አንቀሳቅሽው/አነዋውጭው” ማለት ነው ።
“ነቀልቃል” የወጣበት “አንቀልቀለ” የሚለው የግእዝ ግሥና “ሑኪዮ” የሚለው አንቀጽ አርጋኖን /ኦርጋን በጣት እንቅስቃሴ ወይም ንውጽውጽታ መልካም ድምጽ የሚሰጥ መልካም የዜማ የመዝሙር መሣሪያ መሆኑን ስሙን ከነግብሩ ከነአፈጻጸሙ የሚገልጽ ነው ።
ከዚህ በላይ እንደተመለከትነው በጥንታዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአርጋኖን /ኦርጋን/ አገልግሎት የነበረ ለመሆኑ ማስረጃ ነው ። ዛሬም ቤተ ክርስቲያን የመዝሙር መሣሪያዎችን ስትቈጥር አርጋኖን ብላ በቋንቋዋ ኦርጋንን አብራ በውሳኔዋ ውስጥ ጠቅሳዋለች ። [10]
የዓለም ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደ ሚነግረን፣ ቤተ ክርስቲያን ካቶሊክ ኦርቶዶክስ ተብላ ከመለያየቷ በፊት በሠለስቱ ምዕት ዘመን አርጋኖን ወይም “ቸርች ኦርጋን” የሚባለው የቤተ ክርስቲያን አይነተኛ የመዝሙር መሣሪ እንደ ነበር ይናገራል ።[11] “ወሪድየ ብሄረ ሮሜ ለቤተ ክርስቲያን ርኢክዋ = ሮም ወርጄ ቤተ ክርስቲያንን አየኋት” ሲል የዘመረው ቅዱስ ያሬድ ስለ አርጋኖን ጣዕም በድርሰቱ መስክሯል ።
በዘመነ ሰማዕታትም አርጋኖን የታወቀ የመዝሙር መንፈሳዊ መሣሪያ ነበር ። ስለዚህም «ወበህየ ሰምዑ አርጋኖነ ወብዕዛ ወይቤሉ ምንትኑ ዘንሰምዕ» «በዚያም የአርጋኖንና የብዕዛ ድምጽ ሰሙ ፤ የምንሰማው ምንድነው አሉ» በማለት እንደ ተናገሩ በመጽሐፈ ስንክሳር ተጽፎአል ። [12]
ኢትዮጵያ ሀገራችን የዛሬን አያርገውና ከነአውሮፓ በፊት የሠለጠነች ፥ ግሪክን ግብጽን በሥልጣኔ የምትመስል ሀገር ስለ ነበረች የአርጋኖን /ኦርጋን/ አገልግሎት በኢትዮጵያ የታወቀ እንደ ነበር የሚያጠራጠር አይደለም ። የተፈጠረው እራሱ አባይ ዳር ነውና ። ግን ደሃን ሲያጣ ማንም አይወደውምና ታሪኩን ሁሉ ባዕዳን ስለወሰዱት እንኳን አርጋኖን መሰንቆው ሁሉ ከዕቃ ቤት ስለ ተባረረ እኛም የኛ ሳይመስለን ፥ ምእራባውያንም የኛ ነው ለማለት ሲከጅሉ ይታያል ። ግን ምሁራን አልተቀበሏቸውም ። በጥናታቸውም አፍሪካዊ የአባይ ዳር ግኝት የዜማ ዕቃ እንደ ሆነ ጽፈዋል ።
በዚህ ድርጅት (ማቅ) ውስጥ የሚገኙ አንድ አንድ ዓይነ ልቡናቸው የተያዘባቸው ሰዎች ተነሥተው ቤተ ክርስቲያንን ግራ ለማጋባትና የያዘችውን ለማስጣል ደፋ ቀና ማለት ከመጀመራቸው ቀደም ሲልም አርጋኖን /ኦርጋን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልዩ የምስጋና የቅዳሴ የውዳሴ መሣሪያ ሁኖ በታላላቅ አድባራት እግዚአብሔር ሲመለክበት ቆይቷል ።
ዛሬ ዛሬ ግን ቤተ ክርስቲያንን የምስጋና መሣሪያዋን እኛ እናውቅልሻለን ፤ በዓለም የምንዘፍንበት ይህ ስለ ሆነ ይህንን ለዘፈን ተዪልን ፤ ዝም ብለሽ ተቀመጭ ብለው ባላዋቂ አንደበታቸው ቤተ ክርስቲያንን በማውገዝ አርጋኖን እንዳይዘመርበት ሲያከላክሉ በአርጋኖን /ኦርጋን/ መዘመር እንደ አንቀጸ ሃይማኖት ታይቶ ሊቃውንቱ በጨዋዎቹ ፤ ጳጳሳቱ በነጋዴዎቹ ሲወገዙ መስማት እየተለመደ መጥቷል ።
በመሠረቱ በኦርጋን መዘመር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፣ በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፣ በአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፣ በሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና በህንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በአለም በሚትገኝ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የተለመደ የነበረ ያለ ነው ። አሁን አሁን ግን የኛዎቹ ቢጽ ሐሳውያን ቤተ ክርስቲያን ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እንኳ ለ40 ዓመታት ያህል በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣በግቢ ገብርኤል፣ በልደታ ለማርያም፣ በዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ እግዚአብሔርን ስታመልክበት ከኖረች በኋላ ማኅበርተኞች ለግላቸው በግላቸው ለቢዝነስ ያቋቋሙትን ማኅበር ይጻረርብናል ብለው የገመቱትን እና እንደ ጐባን ያዩትን ሃይማኖተ አበውን እና የቅድስት ሥላሴን ሰንበት ትምህርት ቤት ለማጥፋት ከተጠቀሙባቸው መንገዶች እንደ አንድ አማራጭ አድርገው የወሰዱት በኦርጋንን ይዘምራሉና መናፍቃን ናቸው ብሎ መክሰስን ነበር ። ይህ ራሱን የቻለ ታሪክና ምክንያት ያለው በመሆኑ ወደፊት እንመለከተዋለን።
- የጥንት መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ምስክርነት
ልዩ ጥቅስ
ግእዝ ፥ “ሰብሕዎ በከበሮ ወበትፍሥሕት
ሰብሕዎ በአውታር ወበእንዚራ”
አማርኛ ፥ በከበሮና በዘፈን አመስግኑት
በአውታርና በእምቢልታ አመስግኑት…። መዝ 150 ፥ 4 ።
English
“Praise Him with tumbrel and dance praise Him with stringed instruments and organs” ። Psalm 150:4 …King James Version
በዚህ ትርጉም ላይ የምንማረው ነገር ኦርጋን የመዝሙር መሣሪያ መሆኑን ነው ። ነገር ግን ሁላችን እንደምናውቀው ብዙ አይነት መሳሪወችን የያዘ የዜማ መሳሪያዎች ምዕላድ በመሆኑ ከዚህ ላይ በውስጡ ካሉት መሳሪዎች ንዱን በግእዝ እንዚራ በአማርኛ እንቢልታ የተባለውን መሳሪያ ነው አርጋን ያለው። ያ ማለት ግን አርጋኖን ማለት እንዚራን ብቻ ነው የሚወክለው ማለት አይደለም። እንዚራንም ስለሚያጠቃልል ነው እንጅ ። [13] ይህም ታሪካዊ የትርጉም ስራ አራጋኖን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያለውን ቦታ ያሳያል።
- በአርጋኖን ላለመዘመር የፈለጉ ሰዎች የሚያቀርቧቸው ምክንያቶችና መልሶቻቸው
- «አርጋኖን የመጽሐፍ ስም ነው እንጂ የመዝሙር መሣሪያ አይደለም» ይላሉ
ይህ አባባላቸው ግን ቀድመው በመጽሔታቸው ከጻፉት ጋር ከመጋጨቱም በላይ ካለማወቅ ወይንም ኅሊናን በመሸንገል የተሰነዘረ ሐሳብ ነው ። ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ዘንድ የታወቀና የተወደደ የመዝሙር መሣሪያ እንደ ሆነ በቅዱስ ያሬድ ድርሰት ፣ በአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ድርሰት ፣ በመጽሐፈ ስንክሳር ተጠቅሶ እንደሚገኝ በዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ ውስጥ እናሳያለን ።
ሌላው የማኅበሩ ተናጋሪ ደግሞ አርጋኖን ድምጽ እንጂ የመዝሙር መሣሪያ አይደለም ይላል ። [14] አርጋኖን ድምጽ እንጂ መሣሪያ አይደለም የሚል የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ የለም ። ለምን እንደ ሰናዖር ሰዎች ቋንቋቸው ተደበለቀ ?
ሌላው ሰባኪያቸው ደግሞ አርጋኖን ወይም ኦርጋን ንዋየ ማኅሌትን የሚወክል ስያሜ በመሆኑ በኪንግ ጀምስ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሷል ይላል ። ይህም ከላይ ከጠቀስነው ተናገሪ ይለያል ። [15]
በድፍረት ኃጢአት ወድቀው ሌላውን ከሚበክሉ እርገጠኞች ባልሆኑበት ነገር ላይ ተነሥተው ሕዝበ ክርስቲያንን ከማሳሳት ይልቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ቢጠይቁ አይሻልም ነበርን ? ። ነገር ግን ጥንታውያን የብራና መጻሕፍቶቻችን የሚመሰክሩት አርጋኖን የሚጣፍጥ ድምጽ የሚሰጥ የመዝሙር መሣሪያ መሆኑን ነው ። ነገር ግን ስለ አርጋኖን የሚናገሩት ሰዎች የግእዝን ቋንቋ ባለመረዳታቸው ምክንያት የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ሕዝቡን ግራ ያጋባሉ ።
ከዚህ የሚከተለውን ጥናታዊ ጽሑፍ ስለ አርጋኖን ማቅረብ ያስፈለገበት ምክንያት ፣ ቤተ ክርስቲያን አርጋኖንን የመዝሙር መሣሪያ የምትለው ከጥንት ጀምሮ ሀብቷ ስለ መሆኑም ከቤተ ክርስስቲያን መጻሕፍት ፣ ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፣ ከመዛግብተ ቃላት የተገኘውን መረጃ ለምእመናን ግልጽ ለማድረግ ነው ።
የፈለገ ያለመሣሪያ ሊዘምር ይችላል ። በመሣሪያ ሊዘምር የሚፈልግን ደግሞ እኔ እቃወማለሁና አትዘምር ማለት ተገቢ አይደለም ። “የሚበላው የማይበላውን አይንቀፈው” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ አንዱ ሌላውን ሳይነቅፍ በፍቅር መኖር ሲቻል ፣ በአርጋኖን የሚዘምሩ አብያተ ክርስቲያናትን መኮነን ትልቅ ስሕተት መሆኑን ለማሳየት ነው
- “በኦርጋን ዳዊት አልዘመረም ። ሁሉ ተገልጾለት ትንቢት ሲናገር ወደፊት ኦርጋን እንደሚሠራተገልጾለት ትንቢት አልተናገረም” ይላሉ ።
እንደነዚህ ሰዎች ሃሳብ በዳዊት ዘመን ባልነበረ መሣሪያ ወይም ዳዊት እንደ ምሥጢረ ሥጋዌው ሁሉ ትንቢት ባልተናገረበት መሣሪያ መዘመር መጠቀም ስሕተት ነው ። በመሠረቱ ነቢያት ኃላፍያት (ያለፉትን) መጻእያት (የሚመጡትን) ሁኔታዎች ተገልጸውላቸው መናገራቸው እውነት ነው ። ግን ሃብተ ትንቢታቸው የተመሠረተው መንፈሳዊ ነገር በሚከናወንባቻው መሣሪያዎች ላይ ሳይሆን በምሥጢረ ሥጋዌ በክርስቶስ ቀዳማዊ እና ዳግማዊ ምጽአቶች ላይ በአጠቃላይ በብሉያትና በሐዲሳት በተጠቀሱት ተስፋዎች ላይ የተመሠረተ ነው ።
ይህንን ዓይነት ነገር የሚናገሩ ሰዎች በስልክ እንደሚያወሩ ፣ በመኪና እንደሚሄዱ ፣ በኢንተርኔት እንደሚገናኙ ፣ በአውሮፕላን ፣ እንበሚበሩ ዳዊት ትንቢት ስላልተናገረ እነዚህን ነገሮች መጠቀም የለባቸውም ማለትነው ። በእርግጥ እነሱ ቤተ ክርስቲያንን ከምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ለይተው ስለሚመለከቷት የእነርሱ ክርስትና ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ቅጽር ውስጥ ስለ ሆነ ነጠላውም መንፋሳዊ መስሎ መታየቱ ከዚያው ከቤተ ክርስቲያን በቻ በመሆኑ ውጪ እንዘፍንበታለን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እናመልክበታለን እንደሚሉ ጥርጥር የለውም ።
ሌላው ቅዱስ ያሬድ በመቋሚያ የዘመረው ዳዊት ስለ መቋሚያ ትንቢት ተናግሮ አይደለም እግዚአብሔር ገልጾለት ነው እንጂ ። አንድ አንድ ጊዜ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኦርጋን አልተጻፈም ይላሉ ። ስለ መቋሚያስ የት ተጽፏል በዋሽንት ዘምሩ የሚልስ የት ይገኛል ? መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወት መልእክት ላይ የተመሠረተ መጽሐፍ ነው ። እግዚአብሔር ወደ ፊት አዲስ ነገር በሰው ሕይወት ስለማይሠራ እንዳትጠቀሙ አላለም ። መጽሐፍ ቅዱስ በአርጋኖን አትዘምሩም አላለም ። የቤተ ክርስቲያን ሥርዓትም በአርጋኖን /ኦርጋን/ እንዳይዘመር አይከለክልም ። አትዘምሩ የሚል ሳይሆን ዘምሩ የሚል ሥርዓት ነው ቤተ ክርስቲያን ያላት ። ከጥንት ጀምሮ ኦርጋን የቤተ ክርስቲያን መሣሪያ ነውና ።
- “የዘፈን መሣሪያ ስለ ሆነ አንዘምርበትም” ይላሉ ።
ምነው ታዲያ መለከት በገና ክራር ለዘፈን በዘፋኞች የተሠሩ ለሥጋ ፈቃድ የተቀጠቀጡ የዘፈን ዕቃዎች የጣዖት ማጀቢያዎች አልነበሩምን ? በመሠረቱ ችግሩ ከዕቃዎቹ ላይ ሳይሆን ከተጠቃሚዎቹ እና ከአጠቃቀማቸው ላይ ነው ። እግዚአብሔር ለምስጋና እንጂ ለዘፈን ስላልፈጠረን በኦርጋን ልንዘምርበት እንጂ ልንዘፍንበት አይገባም ። ቤተ ክርስቲያንም ለዘፈን እውቅና አትሰጥም ። እነ ከበሮም እነ መሰንቆም እኮ ጠጅ ቤት ስለ ገቡ አንዘምርባቸውም ልንል ነው ?
- “ባህላችን አይደለም የምዕራባውያን መሣሪያ ነው” ይላሉ
በመሠረቱ ኦርጋን /አርጋኖን/ አፍሪካዊ ግኝት የቤተ ክርስቲያን ሃብት ቀደም ሲል እንደተመለከትነው እነ ቅዱስ ያሬድ ጣዕሙን ያደነቁት ፤ እነ አባ ጊዮርጊስ የተመሰጡበት ፤ በኢትዮጵያ ጥንታዊ የሥልጣኔ ዘመን የማኅሌት ሀብት ንብረት ሁኖ የነበረ ፤ እነ መሰንቆ እነ በገና እነ መለከት ከዕቃ ቤት ሲሰደዱ አብሮ ወጥቶ የቀረ ፥ ስሙ በዜማና በጸሎት መጻሕፍት እየታወሰ የሚገኝ ጥንታዊ የቤተ ክርስቲያን ሀብት እንደ ሆነ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ምስክሮች ናቸው ።
በመሆኑም ምዕራባውያን ክእስክንድርያ ወሰዱት እንጂ እኛ ከእነርሱ አላመጣነውም። ግን እነሱ ከአፍሪካ ወስደው አሳድገው ንብረታቸው አስመሰሉት ። በጥቁር ሕዝብ ላይ ነጮች የፈጸሙትን ግፍ ያየ ያነበበ ወጣት ሀብቱን በባሪያ ፈንጋዮች ዓይን በመመልከት ፈራው ። «እባብ ያየ በልጥ በረየ» እንዲሉ ። ያ ግን ያላደገ አስተሳሰብ ውጤት እንጂ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ታሪክና ሥርዓት የኦርጋንንም የመዝሙር መሣሪያነት የሚያጠፋ አይደለም ። ለዚህም ከዚህ በፊት ያነበብነው መረጃ በቂ ነው ።
- “ከበሮን ጸናጽልን እና መቋሚያን ከቤተ ክርስቲያን ለማጥፋት ነው” ይላሉ
የሚያሳዝነው ሰው ስላማያውቀው ነገር ሲናገር መሰማቱ ነው ። ለመሆኑ ማነው ስለዚህ ነገር ሊያስብ የሚገባው ? በእርግጥ ማንም እንደ ክርስቲያንነቱ ማሰብ የሚገባውን ማሰብ ይችላል ። ግን ከላይ የተጠቀሱትን የመዝሙር መሣሪያዎች ድርሻ የሚወስድ አይደለም ። ለሁሉም ጊዜ የአጠቃቀም ስልት መፍጠር ስለሚቻል እና ስለ ተቻለ የመሰንቆ መኖር ከበሮን እንደማያጠፋ የኦርጋንም መኖር ሌሎቹን መሣሪያዎች አያጠፋም ።
በተለያዩ ጊዜያት ወደ ቤተ እግዚአብሔር የገቡ ንዋየ ቅድሳት የየራሳቸው ድርሻ እና ጥቅም አላቸው። አንዳቸው ያንዳቸው መተኪያ እንዲሆኑ የተመሪጡ አይደሉም ። እነዚህን ንዋየ ቅድሳት ሁሉንም ለተዘጋጁበት አገልግሎት ለተመረጡበት ሥራ ስንጠቀምባቸው በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ። ለምሳሌ ዛሬ በመሰንቆ መዝሙርን ስናጅብ መሰንቆው የጸናጽልን ወይም የከበሮን ቦታ እንዲወስድ የተመረጠ ዕቃ ሁኖ አይደለም ። ሁኖም ግን ምክንያቱ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለመሰንቆ የራሱ ድርሻ ስላለው ለዚያ ተፈልጐ ነው ። እንደዚሁም ኦርጋንም /አርጋኖንም/ ከበሮንና ጸናጽልን እንዲያስቀር ወይም እንዲተካ የታሰበ ሳይሆን የተሠራበትን የራሱን ጥቅም እንዲሰጥ ለማድረግ ነው እንጂ ። ቤተ ክርስቲያን በብሉይ ኪዳን መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 5 ፥ 11-14 እንደ ተጠቀሰው በጸናጽል ፥ በመሰንቆ ፥ በበገና ፥ በዜማም ዕቃ ሁሉ የሠለጠነ የመዘምራን አካል ኖሯት እነዚህን ሁሉ አስማምታ የእግዚአብሔርን ስም እንድትቀድስበት ልዩ ልዩ የመዝሙር መሣሪያዎችን ያዘች እንጂ አንዱን በአንዱ ለማጥፋት አይደለም ።
- “የባሕር ማዶ መሣሪያ ነው” ይላሉ”
መልሱ አይደለም ነው ። አለመሆኑን ከዚህ ቀደም አይተናል ። ቢሆንስ በሃይማኖት የተቀበልናቸው ነገሮችን ከአካባቢ እና ከቀለም ጋር ማዛመድ የዘመናችን ፖለቲካ ነው እንጂ ክርስቲያናዊ ነገር አይደለም ። ቤተ ክርስቲያንም ዓለም አቀፋዊ (እንተ ላዕለ ኲሉ)ናት ። መጽሐፍ ቅዱስ በጥቁሮች ስላልተጻፈ አንቀበልም ልንል ነውን ? ይህ ዓይነቱ መንፈስ ከእግዚአንብሔር አይደለም ።
- “ቅርሳችንን ለመጠበቅ ነው” ይላሉ
ቤተ ክርስቲያናችን ለሰዎች መዳን ለክርስቲያኖች እውነተኛ ሕይወት እድገት ያዋለቻቸው ነገሮች ከጊዜ በኋላ በሚያምኑትም በማያምኑትም ሕዝቦች ዘንድ የባህል መግለጫዎች መሆናቸው እውነት ነው ። ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ከሆኑ ሀብቶችዋ አንዱ አርጋኖን እንደ ሆነ በሚገባ ተመልክተናል ። ስለዚህ በአርጋኖን መዘመር ሀብትን መጠቀም እንጂ ወደ ቤተ ክርስቲያን አጥፊ ነገርን ማስገባት አይደለም ። አንድ አንድ ጊዜ ደግሞ ዘመናዊ መሣሪያ ስለ ሆነ አንጠቀምም ይላሉ ። ጥንታዊነቱ አጠያያቂ ባይሆንም በዘመናዊ መሣሪያ መጠቀምም ስህተት አይደለም ።
ቤተ ክርስቲያን ያላትን ጠብቃ እንዲሁም ምእመናን ሕይወታቸው በምስጋና የሚሞላበት ፤ አእምሮአቸው በመዝሙር የሚደሰትበት ፤ የእግዚአብሔርን ክብር የሚገልጹበት ለበጐ የሚውል ነገርን በየጊዜው እግዚአብሔር ለሰዎች ከሰጠ ትጠቀምበታለች ። የኤሌክትሪክን መብራት መጠቀም ፣ ስልክን ፣ ሬዲዮን ፣ ልዩ ልዩ የኢንፎርሜሽን መሣሪያዎችን ዓለም ለፖለቲካዋ እና ለሥጋዊ እርባና ስትጠቀም ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ለበጐ ትጠቀምበታለች ። ወንጌል ታስተምርበታለች ። እንደዚሁ ሁሉ የመዝሙር መሣሪያም ለእግዚአብሔር ክብር ቢውል ምናልባት ሜልኮል በመቃብር ውስጥ የወለደቻቸው ፥ የመዝሙር ጠላቶች ፥ ዘማርያንን ዘፋኝ ባዮች ፥ የዳዊት ተቃዋሚዎች ካልሆኑ በቀር ምንም የሚከለክል መጽሐፍ በቤተ ክርስቲያናችን የለም ። ዘምሩ የሚል ግን ሞልቷል ።
በመሠረቱ ሕይወት የሚድንበት ከሆነ ፥ የክርስቶስ ወንጌል የሚገለጥበት ፥ ዘፋኝ ተለውጦ ዘማሪ የሚሆንበት መሳሪያ ፥ እንዲሁም ጥንታዊ የዜማ ዕቃ ሲሆን ፥ በኦርጋን ላይ ለምን ያላዋቂ አውጋዦች እንደ ተነሡ ግልጽ አይደለም ። ቅዱስ ዳዊት ግን ባለን ነገር ፣ ኃይል ፣ ጥበብ ሁሉ እግዚአብሔርን እንድናመልክ ፈቅዷል ። በዘመኑ የነበሩትን የዘፈን ዕቃዎች ዘምሮባቸዋል ። በአዲስ ቅኔ ፣ ድምጽ ባለው የመዝሙር ዕቃ ሁሉ እግዚአብሔርን እንድናመልክ ተናግሯል ። መዝሙር 150ን በሙሉ ያንብቡ ። በዳዊት ዘመን ቢገኝ ዳዊት የእግዚአብሔር ሰው ስለ ሆነ ይዘምርበት ነበር እንጂ ዝፈኑበት አትዘምሩበት አይልም ነበር ።
- “የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አይደለም” ይላሉ ።
በአርጋኖን /ኦርጋን/ መዘመር የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አይደለም ብሎ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነበት ጊዜ እና ዘመን የለም ። በአንጻሩም በአርጋኖን እንድንዘምር ቅዱስ ሲኖዶስ ያልወሰነበት ጊዜ የለም ። ቤተ ክርስቲያን የዜማ ዕቃዎችዋን ስትቈጥር ከአባቶችዋ እንዳገኘችው አርጋኖንን ከተራ ቍጥር ያወጣችበት ጊዜ የለም ። ለዚህም የነሱ ሐመር መጽሔት ሳትቀር ምስክር መሆኗን አይተናል። አርጋኖን ኦርጋን መሆኑን ማስተዋል ደግሞ የእኛ ድርሻ ነው ። ይኸውም ሊታወቅ በአዲስ አበባ ያሉ አባቶችም ሆነ በአሜሪካ ያሉ አባቶች በአርጋኖን እንዲዘመር ፈቅደዋል ። በየውሳኔዎቻቸው ዝርዝር ላይ ይህንን ሳይጠቅሱ ያለፉበት ጊዜ የለም ። ችግሩ የቋንቋ እንጂ የምሥጢር አይደለም ።
በመሠረቱ የአርጋኖን /ኦርጋን/ ታሪካዊ አመጣጥ ጥንታዊና በመንፈሳዊው ዓለምም ትልቅ መንፈሳዊ መሣሪያ መሆኑን ተመልክተናል ። በጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም እንደ ሌሎች አኀትአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ከጥንት ጀምሮ የአርጋኖን /ኦርጋን/ አገልግሎት የነበረና ያለ መሆኑን ከእነ ቅዱስ ያሬድ ፥ ከእነ አባ ጊዮርጊስ ድርሰቶች ፥ ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፥ ከጥናት ጽሑፎች ፥ ከልዩ ልዩ መዝገበ ቃላት ተረድተናል ። በእኛ ቤተ ክርስቲያን የአርጋኖን አገልግሎት እንደ ከበሮው ፥ እንደ መቋሚያው ፥ እንደ ጸናጽል እስከ አሁን በቅርቡ በቤተ ክርስቲያን ሲዘመርበት በሰፊው አላየንም ማለት ከሆነ ጥያቄያቸው ፥ ቤተ ክርስቲያን ካሳለፈቻቸው ፈተናዎች ሊያጠፏት ተነሥተውባት ከነበሩ ጠላቶቿ ከነዮዲት ጉዲት ፥ ከእና ግራኝ አህመድ ፥ ከነ ድርቡሽ ፥ ወዘተ የተነሣ ብዙ የጥበብ የበረከት መጻሕፍቶችዋ ጠፍተዋል ። አርጋኖን ብቻ ሳይሆን የመዝሙር መሣሪያዎቿ ሁሉ ተቃጥለዋል ። እንደ መሰንቆ ፥ እንደ በገና ፥ ዋሽንት ፥ እንደ እንዚራ ያሉት ሁሉ ከቤተ ክርስቲያን ዕቃ ቤት ተሰደው ቀርተዋል።
እንዚራ እና አርጋኖን ደግሞ በመጻሕፍት ብቻ ስማቸው እየታወሰ ቤተ ክርስቲያንም የመዝሙር መሣሪያዎችዋ እንደ ሆኑ እያስተማረች መልካቸውንና ስማቸውን ለማዛመድ እስክትቸገር ድረስ ከቤተ ክርስቲያን እርቀው ቆይተዋል ። ይህም አያስገርምም ። ዛሬ እነዚህ የዜማ ዕቃዎች ብቻ ሳይሆኑ በመሰንቆ በእንዚራ በበገና መዘመርም በመጽሐፍ እንጂ በግብር በማኅሌት አገልግሎት ሲሰጥ አይታይም ። ግን መጻሕፍቱ ሁሉ ይመሰክሩላቸዋል ። ይልቁንም መሰንቆ ከዕቃ ቤት ወጥቶ የአዝማሪ መሣሪያ ሁኖ ሲኖር ዛሬ አልፎ አልፎ በአንዳንድ ዘማሪዎች በኩል በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እየሰጠ ይታያል ። ነገም ሌሎቹ እንዲሁ ሊመለሱ ይገባል ። በክፉ ዘመን ያጡትን ንብረት እንደ ጠፋ ይቅር ማለት ተገቢ አይደለምና ። ለምሳሌ ፥ እንኳንስ ይሄን ነባሩን ነገር ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ከሆነ ሁሉን ማድረግ ይገባል ።
ቀድሞ ወንጌል እንደ አሁኑ ማታ ማታ ሥራዬ ተብሎ አይሰበክም ነበር ። አሁን ግን ያ ሁኗል ። ባህላችን አይደለም አንልም ። ቀድሞ የወጣት ሰንበት ትምህርት ቤት አገልግሎት አልነበረም ። ዛሬ ግን አለ። ባህላችን አይደለም አንልም ። ጠቃሚ ነውና ። የአርጋኖን አገልግሎት ግን ከዚህ ሁሉ በተለየ መንገድ የነበረ ፥ ግን በችግር ዘመን የቀረ ነው እንጂ አዲስ ነገር አይደለም ። ይኸውም ሊታወቅ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወርቃማው ዘመን በሚባለው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ከ1940ዎቹ ጀምሮ ከዚም በኋላ እስከ 1988 ዓም ድረስ በቤተ ክርስቲያን ሲዘመርበት ቆይቷል ። አኮርዲዮን እንዚራ ነው ብለው አበው ስለ ተቀበሉት በአክሱም ጽዮን ፥ በተድባበ ማርያም ፥ በቆማ ፋሲለደስ ፥ በደብረ ብርሃን ሥላሴ ጐንደር ፥ በማኅደረ ማርያም ደብረታቦር መድኃኔዓለም ፥ እንደ ነበረ አባቶቻችን የዓይን ምስክሮች ናቸው። ይህንን ሁሉ ያተትኩት በኦርጋን መዘመር ጥንታዊ ሥርዓታችን ነው ፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ ለቅዱስ ያሬድ ዜማ በጣም ተስማሚ ፥ ለሊቃውንቱ ለዛና ጉሮሮ የዜማ ስልት የሚስማማ አብሮ የሚሄድና የሚንቆረቆር በመሆኑ ፣ ከማንም የበለጠ የቅዱስ ያሬድ የዜማ ሀብት ላላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክትስቲያን ፥ በጣም የሚጠቅም ልዩ ሀብት ነውና የሚጠቀሙበትን መቃወም አይገባም ለማለት ነው ።
- “አርጋኖን ኦርጋን አይደለም” ይላሉ ?
ስሕተት ነው- የግእዝ መዝገበ ቃላት በግልጥ አርጋኖን ምን ማለት መሆኑን በሥዕል ሳይቀር አስቀምጦታል ። በግእዝ መዝገበ ቃላት ስሙ ከነትርጉሙ ሥዕሉ ሳይቀር ተሥሎ እናነባለን ። ይህንንም በዝርዝር ተመልክተናል ። ከዚህም በተጨማሪ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም ሰዎች በጣታቸው የሚጫውቱበት መሣሪያ መሆኑን አመልካች በሆኑ የግእዝ አናቅጽ ገልጦታል ።
- አርጋኖንን የቀድሞው ሊቀ ሥልጣናት በኃይል ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገቡት በኋላ ግን ቅዱስ ሲኖዶስ ከቤተ ክርስቲያን አስወጣው ይላሉ?
አርጋኖን ወደ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የገባው በእርግጥ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መሆኑ እውነት ነው ። ነገር ግን ቅዱስ ሲኖዶስ ሳያውቅ ሳይሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቅዶ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ እስከ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በቤተ ክርስቲያን ሰፊ አገልግሎት ሲሰጥበት እንደ ነበር ብዙዎቻችን እናውቃለን ።
አቡነ ጳውሎስም ከተሾሙ በኋላ የመጀመሪያወቹን ኤጲስቆጶሳት ሲሾሙ ቅዳሴው በአርጋኖን ታጅቦ እንደ ነበር ይህ ጸሐፊ የዓይን ምስክር ነው ። በኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክ ታሪክ የመጀመሪያ የሆኑት የአማርኛ መዝሙራት በያሬዳውያን ሊቃውንት ተዘጋጅተው ከኖታው ጋር በመጽሐፍ መልክ በሊቃውንት ጉባኤ ተመርምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ መታተሙን የታተሙት መጻሕፍትና ዛሬም በሕይወት የሚገኙት የመጻሕፍቱ ደራሲዎች ምስክሮች ናቸው ።
ምናልባት ማኅበርተኞቹ ሲኖዶስን መስማትና መከተል ስለማይፈልጉና ለቅዱስ ሲኖዶስም ካላቸው ንቀት የተነሣ እንደማያይ እንደማይሰማ በመገመትና በንቀት የተነሰነዘረ ነገር ነው ። እስኪ ማን ይሙት የኤጲስቆጳሳት ሢመትና ሢመተ ፓትርያርክ በሚከናወንበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል 1940ቹ ጀምሮ እስከ 1986 ዓ/ም ቤተ ክርስቲን ስትገለገልበት ፣ ስታወድስበት ሲኖዶስ ሳያውቅ ነው ማለት ከስድብ የከፋ ስድብ አይደለምን ? ንጉሡ ከተገደሉ ፥ ሊቀ ሥልጣናቱም ከታሰሩ በኋላስ አርጋኖኑ መቸ አገልግሎቱ ተቋረጠ ? ። ታሪክ ይታዘባልና ወንዶሞቻችን በቤተ ክርስቲያን ላይ የሐሰት ምስክር ባይሆኑ መልካም ነው።
- “በአርጋኖን መዘመር መናፍቅነት ነው” ይላሉ ።
ትክክል አይደለም ፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚያስረዳው ፣ በሠለስቱ ምዕት ዘመን ፣ በዘመነ ቈስጠንጢኖስ /በቢዛንታይን ዘመነ መነግሥት/ ቤተ ክርስቲያን ትጠቀምበት የነበረ ነው ። አኀት አብያተ ክርስቲያናትና ሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት ይዘምሩበታል ።
በአርጋኖን መዘመር ያስፈለገው በእኛና በፕሮቴስታንቶች መካከል ያለውን አጥር አፍርሶ አንድ ነን ለማለት ነው ይላሉ ።
ሐሰት ነው ለምሳሌ በሀገራችን የምትገኝ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የእኛን ያሬዳዊ መዝሙርና የእኛን ዜማና የመዝሙር መሣያ ነው የምትጠቀመው ፣ ግን ከእኛ ጋር አንድ አላደረጋትም ። ግብጾች አርመኖች ሶርያዎች ካቶሊኮች ኦርቶዶክሱ ዓለም በሙሉ በአርጋኖን ይዘምራሉ ፕሮቴስታት ጋር አንድ ለመሆን መንገድ ለመጥረግ ፈልገው ነውን ? አይደለም ። አንድን ቤተ እምነት ከሌላው ቤተ እምነት የሚለየው ትምህርተ ሃይማኖት /ዶግማ/ ነው እንጂ የመዝሙር መሣሪያ አይደለም ። ነገር ግን የእኛ የቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪዎች በጉልበት እንጂ በእውቀት ፣ በጠብ እንጂ በፍቅር ፣ ባለመቀበል እንጂ በመቀበል ፣ በመበተን እንጂ በመሰብሰብ ስለማያምኑ ነው ።
- “አንድ አንድ ሰዎች ሲኖዶስ ሳይወስን አንድ አባት ተነሥቶ በአርጋኖን ዘምሩ ብሎ ማወጅቀኖናዊነት አይደለም ፣ ቀኖናዊነት ከሌለ ኦርቶዶክሳዊነት የለም” ይላሉ ። በአርጋኖን እንዲዘመር የሀገር ቤቱ ሲኖዶስም የውጭ አሀገር ሲኖዶስም የከለከበት ወቅት የለም ።የአዲስ አበባው ቅዱስ ሲኖዶስ በ1986 ዓ/ም በግንቦት ወር ባደረገው ጉባኤ «በዋሽንት ፥ በከበሮ ፥ በጸናጽል ፥ በመሰንቆ ፥ በበገና ፥ በእምቢልታ ፥ በአርጋኖን ብቻ እንድንጠቀም አዝዟል» ይላል ። [16]
ከዚያ ቀጥሎ ማቅ አቋሙን ሲገልጥ «ከዚህ ወጥቶ በኦርጋን ልዘምር የሚል ካለ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባል አይደለም ይላል ። ከዚህ የምንማረው ቤተ ክርስቲያን አርጋኖንን ከመዝሙር መሣሪያዋ ውስጥ ማጠቃለሏን ነው ።
ነገር ግን የቤተ ክርስቲያንን ልሳን የማያውቀው ማቅ አርጋኖን ኦርጋን መሆኑን ባለማወቅም ይሁን በክፋት ውሳኔውን የሚጻረር ቃል ማስተላለፉን ልብ ይሏል ። እንዲሁም የማቅ አቋም በአርጋኖን /ኦርጋን/ መዘመር አንቀጸ ሃያማኖት ሁኖ ሰውን ከቤ/ክ እንደሚለይ ያሚያምን የቤተ ክርስቲያን እዳ መሆኑን ነው ። ኦርጋኖን ጠቅላላ የመዝሙር መሣሪያዎችን የሚወክል በመሆኑ መሣሪያ ለማለት በመዝሙረ ዳዊት 150 ላይ ተጠቀሰ እንጂ አንድ አይነት መሣሪያን አያመለክትም ይላሉ ።
ይህ አያጣላንም ፣ አርጋኖን ብዙ መሣሪያዎችን የያዘ ብዙ አይነት ድምጽ የሚሰጥ መሣሪያ ስለ ሆነ ነው ።
- በአርጋኖን በመዘመሩ ምክንያት አስቷቸው ወደ መናፍቃን የገቡ አሉ ። [17] የሚለው የማቅ ሰባኪ አባባል እውነትነት አለውን ?
የለውም ። ማኅበረ ቅዱሳን በዱላ ደብድቦ በር አዘግቶባቸው ፍትሕ አጥተው መጥፋታቸውን ረስተውት ይሁናል ። በእውነት የቤተ ክርስቲያን ልጆች ወደ መናፍቃን ያፈለሳቸው የዚህ ቡድን ዱላ ነው እጂ አርጋኖን አልነበረም ።
ማጠቃለያ
ምክንያታዊና መጽሐፋዊ የሆነውን ነገር እስካልተከተልን ድርስ መቼም ቢሆን መነቃቀፉ አይቆምምና ። በቡድን መነዳቱን ትተን የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ምን ይላሉ ። አባቶቻችንስ ምን ይላሉ እንበል ።ከመፍረድ በፊት መስማትና ማየት ይቅደም ፣ በፈረድንበት ፍርድ የሚፈረድብን ስለ ሆነ ።
መነቃቀፉ ቀርቶ የምንነጋገርበትን ርእስ በተመለከተ መጻሕፍትን መሠረት አድርገን የጋራ መድረክ ተፈጥሮ መነጋገር ሲገባ ፣ ለምን በዓለም መድረክ ቤተ ክርስቲያንን እየነቀፉ ምእመናንን እያሳፈሩ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እየናዱ መኖርን እንደ ፈቀዱ አይታወቅም ።
አርጋኖን የመጽሐፍ እንጂ የመሣሪያ ስም አይደለም ማለት ትክክል ነውን ?
ትክክል አይደለም ።
አርጋኖን ድምጽ ነው እንጂ መሣሪያ አይደለም ማለት ትክክል ነውን ?
ፈጽሞ ትክክል አይደለም ።
አርጋኖን ኦርጋን አይደለም ማለትስ ምክንያታዊ ነውን ?
ምክንያታዊ አይደለም ።
በኦርጋን መዘመር ኢቀኖናዊነት ነው ማለት ተገቢ ነው ?
ተገቢ አይደለም ።
በኦርጋን የዘመሩም ሆነ ያዘመሩ የሃያማኖት ሕጸጽ አለባቸው የሚለው የማኅበረ ቅዱሳን ሰባክያን አቋም ትክክል ነውን ?
ፈጽሞ ትክክል አይደለም ።
ለቤተ ክርስቲያን የሚያስብ ሁሉ በጳውሎስ ዘመን እንደ ነበሩት ቤተ ክርስቲያንን ይበጠብጡ እንደ ነበሩ ፥ ቅዱስ ሉቃስ «ምናምንቴዎች» ብሎ እንደ ጠራቸው አይሁዳውን ቢጽ ሐሳውያን ፣ ቤተ ክርስቲያንን ሰላም ለሚነሡት ግለሰቦች ላስተላልፈው የምፈልገው ነገር ከዚህ የሚከተለውን ነው ።
መደማመጥ ይኑር ። አባቶችንም ምእመናንንም ግራ አታጋቡ ። ለሕዝቡ ሰላም አስቡለት እንጂ የግል ችግራችሁን የቤተ ክርስቲያን ችግር አድርጋችሁ አታቅርቡ ። የመደብ ትግሉ ከአውደ ምሕረት ይወገድ ። የሥጋ የሥራ መስክ በቤተ ክርስቲያን ለመፍጠር ሥጋውያኑም መንፈሳውያን ነን በሚል ፍጹም በቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ባልተገለጠ የድፍረት ሥራ በመሥራት ለዕለታዊ ጥቅምና ክብር ብላችሁ ቤተ ክርስቲያንን አትውኳት ። ዐይነ ልቦናችሁ ይብራ ። ሌሊቱ አስተሳሰብ ጐህ ይቅደድበት ። ጨለማ ይወገድ አለማወቅም ይራቅ ። ሞቱ ሕይወት ሕይወቱም ሞት ፣ ጽድቁ ኃጢአት ኃጢአቱም ጽድቅ መስሎ አይታያችሁ ።
ተስማምተን ተሰብስበን በፍቅር እናምልክ እንዘምር ። ክርስቶስ ለሞተለት ሕዝብም እናስብለት ። በተራ ውዝግብ ቤተ ክርስቲያንን የሁከት አደባባይ አታድርጓት ። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያንን አሥራት ጅራፏን ከቤተ ክርስቲያን ነጥቀው ቤተ ክርስቲያንን በገንዘቧ የሚገርፏት የጥቅም እና የንግድ ሐዋርያት አገልግሎት ይቁም እንላለን።
የዳዊት ልጆች ሆይ ፥ ሜልኮልን አትስሟት ። ዝም በሉ ብትል ወይም ብትስቅባችሁ ሜልኮል ዓለምን እርሷት ። ዝም ብላችሁ ዘምሩ ። እሷም ትመክናለች ። የንጉሡ የክርስቶስ አባት የሆነው የሰሎሞን እናት እንዳትሆንም በምክንያት ትቀጣለች ። ወደ መቃብር ትወርዳለች ። ከክርስቶስ ቤተሰብ ቍጥርም ውስጥ አትገባም ። ግብዝነቷ ያጠፋታል ።
ጥቅም ያሳወራት ያሰከራት የአንድ አንድ ክርስቲያን መሰል ቢጽ ሐሳውያን ወጣቶች ልብ ሜልኮልን ደስ ባይላትም ቤተ ክርስቲያን በሚቻላት መንገድ ሁሉ ፈጣሪዋን ታመልካለች ። ለምስጋና ተፈጥራለችና ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ……. አሜን
በመጋቤ ሐዲስ መምህር ልዑለ ቃል አካሉ
www.zenatewahedo.org
[1] አቡነ ማትያስ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የትምህርት ተቋማት ያስተላለፉት ደብዳቤ ላይ እነዚህ ነጥቦች ሁሉ ተጠቅሰዋል።
[2] ሐመር ኅዳር/ታኅሣስ 1995 የታተመው የማቅ መጽሔት ገጽ 39
[3] የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የግእዝ መዝገበ ቃላት ይመልከቱ ገጽ 239
[4] (Organ History page 2-5) 641
ዓዲ http://faculty.bsc.edu/jhcook/orghist/history/hist001.htm
[5] ዚቅ የጥር ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ እስመ ለዓለም ።
[6] አርያም ዘቅዱስ ያሬድ የማክሰኞ ገጽ 152
[7] ጥንታዊ ሥርዓተ ማኅሌት ዘአቡነ ያሬድ ሊቅ የሚለውን መጽሐፍና ገድለ ያሬድን ተመልከት
[8] Orhtodox Dictionary of The Christian Church page 1192
[9] መጽሐፈ አርጋኖን ገጽ 11-12 ይመልከቱ
[10] ሐመር ኅዳር/ታኅሣሥ 1995 የታተመው የማቅ መጽሔት ገጽ 39
[11] Orhtodox Dictionary of The Christian Church page 1192
[12] ስንክሳር መስከረም 18 ወበዛቲ ዕለት ገብረ ተአምረ ቶማስ ከሚለው ላይ ተመልከት ።
[13] «በስመ ማኅደር ይጼዋእ ሀዳሪ ወበስመ ኅዳሪ ይጼዋእ ማኅደር » እንዲል።
[14] ዳንኤል ክብረት ከሐራ ጥቃዎች ጋር ካደረገው ቃለ መጠይቅ የተወሰደ
[15] ዐባይነህ ካሴ ከሐራ ጥቃዎች ጋር ካደረገው ቃለ መጠይቅ የተወሰደ ።
[16] ሐመር ኅዳር/ታኅሣሥ 1995 የታተመ የማቅ መጽሔት ገጽ 39
[17] ቀሲስ ደጀኔ በኢንተርኔት ካሰራጨው ጽሑፍ የተወሰደ