ASback1647በተጠረጠሩበት የሽብር ድርጊት ወንጀል የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ‹‹መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ ተሰናብተዋል›› ቢላቸውም፣ ይግባኝ ተጠይቆባቸው በእስር ላይ ሆነው እየተከራከሩ የሚገኙት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት) ፓርቲ፣ የአረና ፓርቲና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች የነበሩት ሕይወታቸው አደጋ ውስጥ መሆኑን፣ ለይግባኝ ሰሚው ችሎት የካቲት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. አሳወቁ፡፡
አቤቱታቸውን ያቀረቡትና አመራሮች የነበሩት አቶ ዳንኤል ሺበሺ (አንድነት)፣ አቶ አብርሃ ደስታ (አረና) እና አቶ የሺዋስ አሰፋ (ሰማያዊ) ሲሆኑ፣ በተለይ አቶ ዳንኤል የተከሰሰበት ዋና ጉዳይ እንደማያሳስበው ገልጾ፣ ፍርድ ቤቱ እንዲያውቅለት የሚፈልገው ሕይወቱ አደጋ ላይ መሆኑ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ የታሰረው በኮንቴይነር ውስጥ መሆኑን፣ ምግብ እንዳይገባለት መከልከሉን፣ ዘመድም ሆነ ቤተሰብ እንደማይጠይቀውና ዛቻም እንደሚፈጸምበት ለይግባኝ ሰሚው ችሎት አመልክቷል፡፡ አቶ አብርሃና አቶ የሺዋስም ተመሳሳይ ድርጊት እየተፈጸመባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይግባኝ ሰሚው ችሎት የይግባኝ መዝገቡን ቀጥሮት የነበረው፣ ይግባኝ ባይ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በአመራሮቹ ላይ ያቀረበውና ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ተገኘ የተባለው ማስረጃ ዋናው እንዲቀርብ በሰጠው ትዕዛዝ ላይ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡ ነገር ግን በተመሳሳይ ቀን (ጥር 30 ቀን 2008 ዓ.ም.) ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፍትሕ ሚኒስቴር ለማዕከል መመርመርና ውሳኔ ማሰጠት ዳይሬክቶሬት፣ እንዲሁም ፍትሕ ሚኒስቴር ደግሞ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ወንጀል ችሎት በጻፉት ደብዳቤ መሠረት ውሳኔው ሳይሰጥ ቀርቷል፡፡
ብሔራዊ መረጃና ደኅነነት አገልግሎት በጻፈው ደብዳቤ እንደገለጸው፣ ከተቋሙ የተገኘውንና ተከሳሾቹን ያደረጉትን የመልዕክት ልውውጥ በሚያሳይ መልኩ ተስተካክሎ እንዲያቀርብ ተጠይቋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ሥራ የሚሠሩ አካላት ካለባቸው የሥራ ጫናና መደራረብ ምክንያት እንደማይችልና የአንድ ሳምንት ጊዜ ቢሰጠው ሠርቶ የሚያቀርብ መሆኑን ገልጾ ለሚኒስቴሩ መግለጹ ተነግሯል፡፡
ዓቃቤ ሕግም ይህንኑ ለፍርድ ቤቱ በደብዳቤ አሳውቋል፡፡ በዚህ ጊዜ አቶ ሀብታሙ አያሌው በፍርድ ቤቱ እምነት ማጣቱን ገልጾ እየተጉላሉ መሆኑንም ተናግሯል፡፡
ይግባኝ ሰሚው ችሎት ከሦስት ሳምንታት በፊት ያስተላለፈው ትዕዛዝ፣ ዓቃቤ ሕግ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እንዳገኘው የገለጸውን የኢሜል፣ የኢንተርኔትና የድምፅ ማስረጃ እንዳለ ዋናው (Original) እንዲቀርብለት ነበር፡፡ በመጨረሻ ፍርድ ቤቱ በተለይ በደል ተፈጽሞብናል ያሉትን ተከራካሪዎች፣ በሚመለከት፣ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር የካቲት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀርቦ ምላሽ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ በማስረጃው ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር