Birhanu

ከቦሩ በራቃ
የቀድሞው የኦነግ ቃል አቀባይ  *

የኣርበኞች ግንቦት7ቱ ሊቀመንበር ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ድርጅታቸው በጠራው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ያደረጉትን ንግግር ዩቲዩብ ላይ ገብቼ በቀጥታ ተከታትየዋለሁ። ሌሎችም በቀጥታ ገብተው እንዲከታተሉት ብዬ ሊንኩን በፌስቡክ ገጼ ላይ ሼር ኣርጌው ነበር። በተለይም ከሁለት ወር ተኩል በላይ ሳይቁዋረጥ እየተካሄደ የሚገኘውን የኦሮሞን ህዝብ የጸረ ጭቆና ኣመፅ በተመለከተ ሊቀመንበሩ በሚናገሩት ላይ ትኩረት መስጠቴ ኣልቀረም። በዚህ ጉዳይ ላይ እንደማናቸውም የኦሮሞ ወገኖቼ የተለየ ትኩረት እንዲሰጥ ያደረገኝ ነገር ግልጽ ነው። በኦሮምያ የተጀመረውን የኣንገዛም ለወያኔ ንቅናቄ ኣርበኞች ግንቦት ሰባት እንደ ድርጅት እንዴት እንደሚመለከተውና ምናልባትም ይህ ታሪካዊ ንቅናቄ ድርጅቱ ቀደም ሲል በሚታወቅባቸው የብሄር ማንነት ኣመለካከቶች ላይ የተሻለ ግንዛቤ ፈጥሮ እንደሆን ለመረዳት ነበር።

ቦሩ ቦራቃ ከ 2012-2014 የኦነግ ቃል አቀባይ የነበሩ ናቸው::

ቦሩ ቦራቃ ከ 2012-2014 የኦነግ ቃል አቀባይ የነበሩ ናቸው::

ግንቦት 7 ከቀደሙት ድክመቶቹ ትምህርት ይቀስም ይሆናል ብለው ተስፋ የጣሉበት ኣንዳንድ ወገኖች ነበሩ። በተለይም ከኦሮሞ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ሳንካ ፈጥሮ የቆየውን የፀረ ብሄር ማንነት ኣቅዋሙን ያለሳልስ ይሆናል ብለው የገመቱ ኣንዳንድ ሰዎችን ኣውቃለሁ። ነገር ግን እኔ እንደ ኣንድ የቀድሞው የኦነግ ኣመራር ኣባል በዶክተር ብርሃኑ ንግግር ውስጥ ያየሁት ለውጥ የለም። ድርጅቱ ዛሬም የብሄር ማንነትን እንደ ኣፍራሽ ፖለቲካ መመልከቱን እንደቀጠለ በሊቀመንበሩ ንግግር በሚገባ ተንጸባርቁዋል። በዚህ ላይ ዶክተር ብርሃኑ ሲናገሩ ‘የዘውግ ማንነት’ ፖለቲካን የወለደው የዴሞክራሲ እጦት ስለሆነ ዴሞክራሲ ከሰፈነ ‘የዘውግ ፖለቲካ’ ተወግዶ ወደ ዜግነት እኩልነት ፖለቲካ መሸጋገር እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጠዋል።

ቀጠሉና ደግሞ ትንሽ ይሄንን ኣቅዋም የሚቃረን የሚመስል የዶሮና የኣንቁላል ምሳሌ ኣመጡ። እሳቸው ሁል ጊዜ ‘ዘውግ’ እያሉ የሚጠሩትን የብሄር ማንነትን የፈጠረው ጭቆና መሆኑን ሲያወሱ ቆዩና መልሰው ጭቆናውን የወለደው ደግሞ ራሱ የብሄር ማንነት ፖለቲካ ይመስል ሲሸወዱ ያዝናቸው። ከዶሮና ከእንቁላሉ የትኛው ቀድሞ እንደመጣ የሚያስረዳ ግልፅ መልስ እንደሌለ ሁላችንም እናውቃለን። ስለሆነም ከጭቆናውና ከብሄር ማንነት የትኛው ቀድሞ እንደተከሰተ መግለፅ ላይቻል ነው ማለት ነው። እንዲህ ያለውን ያንድ ትልቅ ድርጅት መሪ ግራ መጋባት ምን ብለን እንደምናልፈው ለጊዜው ኣይገባኝም።

ግልፅ መሆን ያለበትን ነገር ግን ሳላሰምርበት ማለፍ ኣልፈልግም። የብሄር ማንነት ፖለቲካ ሁል ጊዜ የጭቆና ኣገዛዝ ሰለባ ከመሆን የሚፈጠር ኣድርጎ ማየት ስህተት ነው። በርግጥ ጭቆና ሲበረታ ራስን ለማዳን ሲባል ጭቆናው ያነጣጠረበት የህብረተሰቡ ክፍል በብሄር ማንነቱ ተሰባስቦ መታገል ተፈጥሮኣዊ የሰው ልጅ ባህርይ ነው። ነገር ግን ሁል ጊዜ የብሄር ማንነት ፖለቲካ የሚመነጨው ከጭቆና ኣገዛዝ ወይም ከዴሞክራሲ እጦት ነው ብሎ መደምደም ኣደገኛ ነው። የብሄር ማንነት ጭቆና ኖረም ኣልኖረም የማይለወጥ ማንነት ነው። በቅኝ ግዛት ዘመን በብሄራቸው ተደራጅተው ሲታገሉ የኖሩ የኣለማችን ህዝቦች ነጻነት ከተጎናፀፉ በሁዋላም በብሄራቸው ማንነት ፀንተው ጎልብተው ቀጠሉ እንጂ ብሄራዊ ማንነታቸውን ከጭቆናው ድርቶ ጋር ኣውልቀው ኣልጣሉትም። በብሄራቸው ማንነት ኮርተው ራሳቸውን እያስተዳደሩ ናቸው። ኦሮሞም ሆነ ሌላው ብሄርም እንዲሁ ነው። ኦሮሞ በጭቆና ኣገዛዝ ስር ከመውደቁ በፊትም ኦሮሞ ነበረ። በኦሮሞነቱ ነበር ራሱን ሲገልጽ የኖረው። ጭቆና ስር ከወደቀ በሁዋላ ያመጣው የብሄር ማንነት ኣይደለም። ነገም ከጭቆናው ኣገዛዝ ሲላቀቅ ኦሮሞነቱን ኣውልቆ ኣይጥልም። ይህ ግልጽ መሆን ኣለበት። ይህ እውነታ የማይዋጥላቸው ወገኖች ካሉ ምንም ልንረዳቸው ኣንችልም።

ትናንት በዋሽንግተን ዲሲ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በጠሩት ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያውያኑ ለኦሮሞ ወንድም እህቶቻቸው ትግል ያላቸውን አጋርነት ያሳዩበት ሁኔታ በፎቶ

ትናንት በዋሽንግተን ዲሲ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በጠሩት ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያውያኑ ለኦሮሞ ወንድም እህቶቻቸው ትግል ያላቸውን አጋርነት ያሳዩበት ሁኔታ በፎቶ

እንደ ኣርበኞች ግንቦት ሰባቱ ሊቀመንበር ቁንፅል ኣቁዋም ከሆነ ወያኔ በጋራ ትግል ከተወገደ በሁዋላ ኦሮሞው ኦሮሞ ነኝ ብሎ ራሱን መጥራት ኣቁሞ ‘ኢትዮጵያዊ ነኝ’በሚለው ኣመለካከት ብቻ እንዲጸና ይፈለጋል። ይህ ደግሞ ከቶ ሊሆን ኣይችልም። የሊበራል ዴሞክራሲ ሃዋሪያ የሆኑት እነ እንግሊዝ እንኩዋን የብሄር ማንነትን በቱባው ዴሞክራሲያቸው ስኬት ማስቀረት ኣልቻሉም። እንደዛ ቢሆንማ ዛሬ ዩናይትድ ኪንግዶም መባል ባላስፈለጋቸው ነበር። ኢንግሊሽ፣ ዌልሽ፣ ስኮትሽና ኣይርሽ እያሉ በብሄራቸው ማንነት፣ በቁዋንቁዋቸውና በጂኦግራፊያዊ ኣሰፋፈር መሸንሸን ባላስፈለጋቸው ነበር። የዴሞክራሲያቸው መዳበር ይበልጥ የብሄር ምንነታቸው ኣስከበረው እንጂ ኣልናደውም። ከኣንድ ኣመት ገደማ በፊት በስኮትላንድ የተካሄደውን የራስን እድል በራስ የመወሰን ውሳኔ ህዝብን ማስታወስ ብቻ ለዚህ ሃቅ በቂ ምስክር ነው። ለኢትዮጵያ ኣንድነት ከማንም በላይ እንቆረቆራለን የሚሉት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ከኣለማችን ፖለቲካ ልምድ መቅሰም ኣይፈልጉም። በሚመኙትና በለመዱት የጭለማው ዘመን ሁዋላ ቀርና ነውረኛ የፖለቲካ ኣመለካከት ብቻ ህዝቦችን ሸብበው መቀጠል ያልማሉ። ይህ ደግሞ ከምንም ከማንም በላይ እንቆረቆርላታለን ለሚሉዋት የኢትዮጵያ ኣንድነት ኣደገኛ ነው።

ፅሁፌን የምቁዋጨው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ሌሎች ከኦሮሞ እኩል ተነስተው ላለመታገላቸው እንደ ምክንያት ያስቀመጡትን ኣንድ ስህተት በማረም ይሆናል። የኦሮሞ ህዝብ የረጅም ጊዜ ትግል ሂደት ኣካል የሆነውና ባሁኑ ወቅት የወያኔን ስርኣት ከመሰረቱ እየነቀነቀው የሚገኘው የኦሮሞ ፕሮተስትስ እነ ግንቦት ሰባትን ጨምሮ ለሁሉም የዛች ኣገር ፖለቲካ ያገባናል ለሚሉት ሃይሎችና ህዝቦች የትግል ጥሪ ኣስተላልፏል። ጥሪውን በመከተል በመግለጫ ደረጃ ከሞላ ጎደል ሁሉም ደግፏል። ነገር ግን ከኦሮምያ ውጪ ኣይን የሚሞላ ንቅናቄ እንዳልታዬ ግልፅ ነው። ለዚህ ደግሞ ራሳቸውን መጠየቅ ያለባቸው የነዚያ ወገኖች መቀስቀሻ መዘውር በእጃችን ይገኛል የሚሉት እንደ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ያሉት የፖለቲካ መሪዎች እንጂ ትንቅንቅ ላይ ያለው የኦሮሞ ህዝብና ኤሊቶቹ ኣይደሉም። ዶክተር ብርሃኑ ዲሲ ላይ ድርጅታቸው በጠራው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ሲናገሩ ኦሮሞዎቹ ተነስተው ሌላው ከነርሱ ጋር ባለመነሳቱ ‘ኦሮሞ ብለን በመነሳታችን ለካስ ብቻችን ነን እንዴ?’ ብለው ራሳቸውን እንዲጠይቁ ይጠቅማቸዋል የሚል ኣይነት መልእክት ያዘለ ኣባባል ተጠቅመዋል።

ይሄኛውም ኣባባላቸው ግዙፍ ስህተት መሆኑን ላስረዳ። ኦሮሞዎች በታሪክ ትልቅ ስፍራ የተሰጠውን ይህንን ትግል ለሶስተኛ ወር እስከዛሬ ሳያቁዋርጡ ሲቀጥሉ ሌሎች ከኛ ጋር ኣልተነሱምና ምን ይሻለናል ብለው ጉልበታቸው ኣልዛለም። በሌሎች ኣለመነሳትም ተስፋ የሚያስቆርጣቸው ምንም ነገር የለም። በርግጥ ሌላውም ህዝብ ከኛ ጋር ቢነሳ እሰዬው ነበር። የሁሉም መተባበር የድሉን ጊዜ ያቃርባልና። ሌሎች ባለመነሳታቸው ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ከሂደቱ ኣልተገታም ኣይገታምም። የኦሮሞ ህዝብ ሌሎችም የኣገሪቱ ህዝቦች ተመሳሳይ የጭቆናና የዘረፋ መዋቅር ስር መሆናቸውን ኣሳምሮ ይረዳል። ኦሮምያ ውስጥ ወያኔ ድል ከተደረገ ለተቀሩት ክልሎችም የትግል መንገዱን ጠርጎላቸው መክፈል የሚጠበቅባቸውን መስዋእትነት ያቀልልላቸዋል። ያ ማለት ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ ዛሬ ለብቻውም ቢሆን እየከፈለ ያለው መስዋእትነት ከራሱ ኣልፎ ለሌሎችም ህዝቦች ክብር መጎናፀፍ የጎላ ድርሻ እያበረከተ ነው ማለት ነው። ወያኔን ማዳከም ቢያቅተውም እንኩዋን (ነገር ግን በግልፅ እያዳከመው ነው) እንደብዙህነቱ የትግል ፋና ወጊነቱን ሚና መጫወቱ ለራሱ እንደ ጉልህ ድርሻ ተደርጎ መመዝገብ የሚገባው ነው ብዬ ኣስባለሁ።

ዶክተር ብርሃኑ ይህንን ሃቅ መገንዘብ ኣቅቶኣቸው ኣልያም እያወቁት ነገሩን መጠምዘዝ ፈልገው እንደሆነ ኣልገባኝም። የገቡኝ ኣንድ ሁለት ነገሮች ግን ኣሉ። የመጀመሪያው ዶክተሩ የኦሮሞ ልጆች ኦሮምያን ከጭቆና ኣገዛዝ ለማላቀቅ እስከምን ድረስ ቆርጠው እንደተነሱ ኣለመረዳታቸው ነው። የትግል ኣጋር ቢመጣም ባይመጣም ኦሮምያ የለኮሰችው የትግል ችቦ እንደሰደድ እሳት ክልሉን ኣዳርሶት ጨቁዋኞችን ኣጋይቶ ማስወገዱ ኣይቀሬ መሆኑን የተረዱት ኣይመስለኝም። ሁለተኛው ሊቀመንበሩ ያልተረዱት የሚመስለኝ ነገር በኦሮምያ ትግሉን እያቀጣጠለ ያለው የፖለቲካም ሆነ የህብረተሰቡ ክፍል እሳቸው ለማስቀመጥ ኣንደሞከሩት ፅንፈኛና ፅንፈኛ ያልሆነ እየተባለ የተከፋፈለ ኣይደለም። በዚህ መልኩ ተከፋፍሎ ኣንዱ ሲታገል ሌላ ዳር ቆሞ የሚመለከት ሁኔታ ኦሮምያ ውስጥ የለም። ትግሉ የኦፒዲኦ ኣባላትን ሳይቀር ያሳተፈ ሁሉ-ኣቀፍ የኦሮሞ ህዝብ ትግል እንጂ ፅንፈኛውን ኦሮሞ ኣግልሎ በለዘብተኞች ብቻ የሚካሄድ ተብሎ የሚገለፅ ትግል ኣይደለም። ኦሮሞውን ፅንፈኛና ለዘብተኛ ብሎ መከፋፈልም ጊዜ ያለፈበት የከፋፍለህ ግዛ ስልት ኦሮምያ ውስጥ ተቀባይነት የለውም።