ታደሰ ብሩ
3. የትኛው የትግል ስትራቴጂ ይበጀናል? ለምን?
በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ የፓለቲካ ፓርቲዎች ከታወቁበት 1960ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ የፓለቲካ ፓርቲዎችን ካወዛገቡ ትላልቅ ርዕሶች አንዱ የትግል ስትራቴጂና ስልት ምርጫ ነው። ለምሳሌ ትጥቅ ትግልን እንደ ስትራቴጂ በመውሰድ ላይ ተስማምተው እያለ “የከተማ ትጥቅ ትግል” ወይስ “የገጠር ትጥቅ ትግል” በሚል የስልት ልዩነት የተፋለሱ፣ ከዚያም አልፎ የተገዳደሉ ድርጅቶችና ስብስቦች መኖራቸው የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው ። ዛሬም ፓለቲካችን ውስብስብ ችግር ውስጥ ካስገቡት ጉዳዮች አንዱ ወያኔን በማስወገድ አስፈላጊነት ላይ የሚስማሙ ድርጅቶች በስትራቴጂና በስልቶች ላይ ስምምነት የሌላቸው መሆኑ ነው።
የስትራቴጂ ምርጫ በንድፈ ሀሳብም በተግባርም ውስብስብ ሂደት ይጠይቃል። ከሁሉ አስቀድሞ በአማራጮቹ ዝርዝር ላይ መስማማት ያስፈልጋል። ቀጥሎ ደግሞ መመዘኛዎችን ማውጣትና በመመዘኛዎች ላይ መስማማት ያስፈልጋል። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ በመመዘኛዎቹ አለካክ (methodology) ላይ መስማማት ይጠይቃል። በመጨረሻም በውሳኔ ህግ (decision rule) ላይ መስማማት ይጠይቃል።
ነገሩን ለማሳጠር በአማራጭ ስትራቴጂዎች ዝርዝር ተስማማን እንበልና ከቀረቡት አማራጭ ስትራቴጂዎች የተሻለውን በምን መመዘኛ ነው የምንመርጠው ብለን እንጠይቅ። ለስትራቴጂ መረጣ ብዙ መመዘኛዎችን መዘርዘር ብንችልም በሶስት ዋና ዋና መመዘኛዎች ማጠቃለል ይቻላል። እነዚህም 1ኛ) ተስማሚነት (Suitability)፣ 2ኛ) ተፈፃሚነት (Feasibility)፣ እና 3ኛ) ተቀባይነት (Acceptability) ናቸው።
ተስማሚነትን በተመለከተ ቁልፍ ጥያቄ መሆን ያለበት “በአማራጭነት የቀረበው ስትራቴጂ እተፈለገው ግብ ያደርሳል ወይስ አያደርስም?” የሚለው ጥያቄ ነው። የዚህ ጥያቄ መልስ አሉታዊ ከሆነ አማራጭ ተብሎ የቀረበው ስትራቴጂ እውነተኛ አማራጭ አይደለም ማለት ስለሚሆን በዝርዝሩ መውጣት አለበት። ትንሽም እንኳን እድል ካለው በምርጫው ውስጥ ቆይቶ የሚከተሉት ጥያቄዎች መመለስ ይሆርበታል። ይህ ስትራቴጂ እኛ አገር ውስጥ ይሠራል ወይ? ግልጽ ነው ወይ? ለባህላችን፣ ለአኗኗራችን ተስማሚ ነው ወይ?
ተፈፃሚነትን በተመለከተ መጠየቅ ያለባቸው ጥያቄዎች የሚከተሉትን የመሰሉ ናቸው። ለስትራቴጂው የሚያስፈልገውን ግብዓት ማግኘት ይቻላል ወይ? ለምሳሌ ስትራቴጂው የሰለጠኑ ሰዎችን የሚፈልግ ከሆነ እነሱን ማግኘት ይቻላል ወይ? በርካታ ሰው በአንዴ “ሆ” ብሎ መነሳት የሚኖርበት ከሆነ ይህንን ማምጣት ይቻላል ወይ? ስትራቴጂው የሚፈልገው ድርጅታዊ ብቃት አለ ወይ? ስትራቴጂው የሚፈልገው አመራር አለ ወይ? የተፈፃሚነትን መመዘኛ በሁለት አንኳር ነጥቦች ማጠቃለል ይቻላል – ሀ) አዋጪነት – ምን ያህል ዋጋ ያስከፍላል? ለ) አስተማማኝነት – ስትራቴጂው የሚፈልገውን ግብዓት (ሰው፣ አመራርና ድርጅት) መፍጠር ይቻላል?
ተቀባይነትን በተመለከተ ደግሞ ስትራቴጂው በዋና ዋና ባለድርሻ አካላት “ፍትሀዊ ነው” ተብሎ ይታሰባል ወይ? ማኅበረሰቡ “መልካም” የሚለው ዓላማ “መልካም ባልሆነ” ስትራቴጂ ተግባራዊ ቢደረግ በዓላማውን መልካምነት ላይ ተጽዕኖ አለው? ለምሳሌ፣ አምባገነን አገዛዝን ኃላፊነት በሚሰማው አመራር መቀየር መልካም ነገር ነው። ይህ ሽግግር በሰላማዊ መንገድ ቢፈፀም እጅግ በጣም ጥሩ ነው። ሆኖም ግን ይህ ሳይቻል ቀርቶ አምባገነኑ አገዛዝ በጉልበት ተቀይሮ ኃላፊነት የሚሠማው አመራር ሥልጣን ላይ ቢወጣ ሽግግሩ የተደረገበት መንገድ በአዲሱ አመራር ተቀባይነት ላይ ያለው ተጽዕኖ ምንድነው? “መልካም” የሆነው ዓላማ ከሞራል አንፃር ተመራጭ ባልሆነ ስትራቴጂ አማካይነት ተፈፃሚ ሆኖ መልካምነቱን እንደያዘ ማቆየት ይቻላል ወይ?
ከላይ የተዘረዘሩት የስትራቴጂ አማራጮች በሙሉ የመጀመሪያውን የማጥሪያ ጥያቄ ማለፍ አለባቸው። የማጥሪያው ጥያቄ “ይህ ስትራቴጂ ወያኔን ማስወገድ ይችላልን” የሚል መሆን ይኖርበታል። ይሄንን ቁልፍ ጥያቄ በአዎንታ ያልመለሰ ስትራቴጂ ይሰረዛል። (ለመሰረዝ መቸኮል እንደሌለብን አስቀድመን ተናግረናል)። ይህንን መመዘኛ ያለፉ ስትራቴጂዎች ሁሉ በእነዚህ ሶስት መመዘኛዎች ሊለኩ ይችላሉ። ለምሳሌ ከላይ በምሳሌነት ያቀረብናቸውን አምስት ስትራቴጂዎች በሰንጠረዥ 1 በተመለከተው መሠረት ለምዘና ልናዘጋጃቸው እንችላለን።
ሰንጠረዥ 1 በዚህ ሁኔታ ከተጋጀ በኋላ በእያንዳንዱ መመዘኛ አንፃር ከ 1 -10 ወይም 1 -100 ውጤት ሰጥተን ደምረን የተሻለውን እንመርጣለን።
ሰንጠረዥ 1ን ለመሙላት ሰፊ ውይይት የሚጠይቅ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። የዚህ ዘዴ አንዱ ጥቅምም ሥርዓት ላለው ውይይት የሚያዘጋጅ መሆኑ ነው። ለምሳሌ ለባህላችን፣ ለአኗኗራችን ለታሪካችን ተስማሚ የሆነው ሰላማዊ ትግል ነው? ወይስ የትጥቅ ትግል? የሚለው ጥያቄ ብዙ የሚያወያይ ነው።
ወደ ስትራቴጂዎቹ እንመለስና ስትራቴጂ 1 ላይ እናትኩር። ሰላማዊና ህጋዊ ትግል እንደ ስትራቴጂ ተስፋ አለው ማለት ህወሓት የሚቆጣጠረው ፓርላማ ባወጣቸው ህጎች እየተገዙ፤ ህወሓት የሚቆጣጠረው ፍርድ ቤት የሚሰጠውን ውሳኔ እያከበሩ፤ በህወሓት ፓሊስና ጦር ሠራዊት ቁጥጥር ስር ተኩኖም ቢሆን ህወሓት የሚቆጣጠረው የምርጫ ቦርድ በሚያስተዳድረው ምርጫ ራሱ ህወሓትን ማሸነፍ ይቻላል ብሎ ማመን ነው። እኔ በበኩሌ ይኼ ተስፋ የሌለው ስትራቴጂ ነው ብዬ ስለማምን እሰርዘዋለሁ። የዚህኛው ስትራቴጂ መሰረዝ ደግሞ አራተኛውን ስትራቴጂ ማለትም “የትጥቅ ትግል እና ሰላማዊና ህጋዊ ትግል ማቀላቀል” የሚለው ላይም የጥያቄ ምልክት ያስቀምጥበታል፤ ወይም ከአቢይ ስትራቴጂነት “በዚህ ስትራቴጂ ከሚያምኑ ድርጅቶች ጋር እንደምን ያለ የወዳጅነት ግኑኝነት ይኑረኝ? ወደሚል የሕዝብ ግኑኝነት ስትራቴጂነት ያወርደዋል።
የኔ እምነት ለሚጋራኝ የቀሩት ስትራቴጂዎች ሶስት ብቻ ናቸው (ሰንጠረዥ 2 ይመልከቱ)። ለኔ ያሉኝ አማራጮች 2፣ 3 እና 5 ናቸው። እነሱም ስትራቴጂ 2: ሰላማዊ ሆኖም ግን ህገወጥ ትግል፤ ሰትራቴጂ 3: ትጥቅ ትግል፣ እና ሰተራቴጂ 5: ትጥቅ ትግል እና ሰላማዊ ሆኖም ግን ህገወጥ ትግል ተቀላቅሎ ። እያንዳንዱን ለየብቻ እያነሳን እንነጋገርባቸው።
3.1. ሰላማዊ ሆኖም ግን ህገወጥ ትግል እንደ ስትራቴጂ
ሰላማዊ ሆኖም ግን ህገወጥ ትግል እንደ ስትራቴጂ መውሰድ ማለት የአገዛዙን ህጎችንና ደንቦችን እየጣሱ “እምቢ አልገዛም” ብሎ በማመጽ ህወሓትን ከስልጣን ማስወገድ ይቻላል በሚል እሳቤ ላይ የተመረኮረዘ ነው። ይህ ስትራቴጂ ይበልጥ የሚታወቀው ሕዝባዊ እምቢተኝነት (Civic Disobedience) በሚል መጠሪያ ነው። ከዚህ በኋላ እኔም “ሕዝባዊ እምቢተኝነት” የሚለውን መጠሪያ እጠቀማለሁ።
በርካታ አምባገነን መንግሥታት በሕዝባዊ እምቢተኝነት መንኮታኮታቸው እውነት ነው። የቅርቦቹን ብቻ በምሳሌነት ብናነሳ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1980ዎቹ መጨረሻ የቀድሞ ሶቭየት ኅብረት ግዛቶች የነበሩ በኢስቶኒያ፣ ላትቪያና ሊቷንያ፤ በምሥራቅ አውሮፓ በፓላንድ፣ በቼክ ሪፑብሊክ፣ በስላቫኪያና በምሥራቅ ጀርመን፤ በእስያ በፊሊፒንስ እና በላቲን አሜሪካ ቮሊቪያ ውስጥ አምባገነን ሥርዓቶች ተንኮታኩተዋል። ከዚያም እአአ በ2003 ጽጌረዳማ አብዮት የሚል ስያሜ በአገኘው የጆርጂያ አብዮት፤ በ2005 “ብርቱካናማ አብዮት” የሚል ስያሜ የተሰጠው የዩክሬይን አብዮት፤ በ2005 “ሲዳር አብዮት” በተባለው የሊባኖስ አብዮት አገዛዞች ተቀይረዋል። ከዚያም በ2011 በቱኒዝያና በግብጽ “ጃዝሚን አብዮት” የተባለው ተካሂዶ የቤን ዓሊንና የሆስኒ ሙባረክ አገዛዞች ተወግደዋል። በመጨረሻም አምና በ2014 በቡርኪና ፋሶ በሁለት ቀናት አብዮት ከሃያ ዓመታት በላይ የተንሰራፋው አገዛዝ ተንኮታኩቷል። ከዚህ አጭር ዳሰሳ መረዳት እንደምንችለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ውጤታማ የሆነባቸው የቅርብ ጊዜዓት ምሳሌዎችም በሁሉም ክፍለዓለማት የሚገኙ መሆኑን ነው።
በአንፃሩ ደግሞ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ተሞክሮባቸው የከሸፉ ወይም በሕዝባዊ እምቢተኝነት ተጀምረው ወደ ትጥቅ ትግል የዞሩ ምሳሌዎችም አሉ። በሕዝባዊ እምቢተኝነት የቅርብ ጊዜ ምሳሌነት ሲወደስ የነበረው የዩክሬኑ ብርቱካናማ አብዮትም በየጊዜው እያመረቀዘ አገሪቷን ወደ መከፋፈል አድርሷት እስካሁንም መቋጫ አላገኘም። በ2011 በሊቢያ የተቀሰቀሰ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ወደ እርስ በርስ ጦርነት ተሸጋግሮ ኃያላን አገሮች ወደተሳተፉበት አውዳሚ ጦርነት ተሸጋግሯል። በሶሪያ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ዓለምን አደጋ ላይ ወደ ጣለ የእርስ በርስ ጦርነት ዘቅጧል። በየመን የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ወደ እርስ በርስ ጦርነት ተሸጋግሮ አገሪቷን እያወደመ ከመሆኑም በላይ የአካባቢው አገሮች ሳይቀር ወደ ጦርነት እየሳበ ይገኛል።
ከላይ ለስትራቴጂዎች መመዘኛነት ያስቀመጥናቸው ሶስት መለኪያዎች- ተስማሚነት (Suitability)፣ ተፈፃሚነት (Feasibility) እና ተቀባይነት (Acceptability) አንፃር ሕዝባዊ እምቢተኝነት በምን ሁኔታዎች እንደሚሠራ በምን ሁኔታዎች ደግሞ እንደማይሠራ በማጥናት ከሀገራችን ተጨባጭ እውነታ ጋር ማገናዘብ ይጠበቅብናል። ይህ ሰፊ ምርምር የሚጠይቅ ሥራ በመሆኑ በዚህ ጽሁፍ የማይሞከር ነው። ሆኖም ዝርዝር ትንተና ውስጥ ሳንገባ ጠቅለል ያሉ ሀሳቦችን መስጠት ይቻላል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ተከታታይ በሆኑ አምባገነን ሥርዓቶች ሲበደል ቆይቷል። ቢያንስ በሶስት ተከታታይ ሥርዓቶች በመልካም አስተዳደር እና በልማት ስም ሲሸነገል ቆይቷል። ጥቂት ትላልቅ፤ በርካታ ትናንሽ አብዮቶች የከሸፉበት ሕዝብ ነው። የህወሓት አገዛዝ በሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ቢቀየር ለውጡ የሚኖረው ተቀባይነት እና ከለውጡ በኋላ የሚመጣው መንግሥት የሚኖረው የሕዝብ ድጋፍ ከፍተኛ እንደሚሆን መገመት ቀላል ነው። ምንም እንኳን ማስተማመኛ ባይኖርም በእንዲህ ዓይነት መንገድ የመጣ መንግሥት ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚያደርገው ሽግግር በአንፃራዊ መልኩ ቀና ይሆንለታል ብሎ ተስፋ ማድረግ ይቻላል። በዚህም ምክንያት ሕዝባዊ እምቢተኝነት የሚኖረው ተስማሚነት ከፍተኛ ነው ብሎ ማመን ይቻላል።
ተፈፃሚነትን በተመለከተ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። እስካሁን ከታዘብነው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ውጤታማ በሆነባቸው አገሮች ውስጥ የሚከተሉት ሶስት ነገሮች ተሟልተዋል። (1) በራስ መተማመንን ያጎለበተ ሕዝብ፣ (2) አንፃራዊ ነፃነት ያላቸው ተቋማት እና (3) በብልሃት የተቀመሩ የትግል ስልቶች። እነዚህ ሶስት ነገሮች በአገራችን ተሟልተዋልን (ወይም በአጭር ጊዜ ሊሟየሉ ይችላሉን) ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ የሚያረካ አይሆንም።
በራስ መተማመንን በተመለከተ ሁኔታዎች በፍጥነት እየተቀየሩ ነው። የማኅበረሰቡን ጥቅምና ስሜት በከፍተኛ ሁኔታ የሚነኩ አጀንዳዎች ሲኖሩ ብዛት ያለው ሕዝብ አገዛዙን ለመጋፈጥ እንደሚደፍር በሙስሊም ወገኖቻችን የተራዘመ እንቅስቃሴና ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ በኦሮሚያ ላይ አይተነዋል። መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በተመሳሳይ ስሜት የሚያንቀሳቅስ ኮርኳሪ አጀንዳ ለማግኘት መጣር ይኖርበታል። ለዚህ ብዙ መሠራት አለበት።
አንፃራዊ ነፃነት ያላቸው ተቋማት ጉዳይ። በሕዝባዊ እምቢተኝነት አምባገነን አገዛዞች በተገረሰሱባቸው አገሮች ሁሉ የተወሰኑ ተቋማት አንፃራዊ ነፃነት ነበራቸው። ለምሳሌ በፓላንድና በቼክ ሪፑብሊክ የለውጡ ዋነኛ አራማጆች የሙያ ማኅበራት ነበሩ። እነዚህ የሙያ ማኅበራት አንፃራዊ ነፃነት ነበራቸው። በፓላንድ ከሠራተኛ ማኅበር በተጨማሪ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለነፃነት ትግል ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክታለች። በዩክሬንና በጆርጂያ ፓርላማዎች አንፃራዊ ነፃነት የነበራቸው በመሆኑ የሕዝቡን ትግል የሚደግፉ የፓርላማ አባላት ነበሩ። ዩክሬን ውስጥ የሕዝቡን ትግል በመደገፍ የተወሰኑ የፓርላማ አባላት ፓርላማው ውስጥ የረሀብ አድማ አድርገዋል። ጥቂት ቆይቶም አብላጫው የፓርላማ አባላት የትግሉ ደጋፊዎች ሆኑ። በቱኒዝያ፣ ግብፅና ቡርኪና ፋሶ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ሊሳካ የቻለው በኃላፊነት ስሜት የሚንቀሳቀስ አንፃራዊ ነፃነት ያለው የጦር ሠራዊት ስለነበራቸው ነው። በሶስቱም አገራት ጦር ሠራዊቱ የሕዝቡን ጥያቄ ደግፎ ተንቀሳቅሷል። በብዙዎቹ አገራት የፍትህ፣ የሚዲያ እና የአካዳሚያ ተቋማት አንፃራዊ ነፃነት ነበራቸው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ከዚህ በጣም የተለየ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ ትንሽ እንኳን የነፃነት ሽውታ ያለበት አንድም ተቋም የላትም። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የፍትህ አካላቱ፣ ሚዲያው፣ አካዳሚያው በአገዛዙ ከመታፈናቸው በተጨማሪ ዘረኛ በሆነ መንገድ በመደራጀታቸው አገራዊ እይታ እንዳይኖራቸው ተደርጓል። ሲቪል ማኅበራት ፈጽሞ እንዳይኖሩ ተደርጓል፤ ። የሃይማኖት ተቋማት የሥርዓቱ ተቀጥላ ተደርገዋል። ወያኔ በሲቪል ማኅበራት ላይ የዘመተው እንደማኅበረሰብ የመዝለቃችን ዋስትና የሆነው ማኅበራዊ ካፒታላችንን ለማጥፋት ነው። እናም ጉዳቱ የማኅበራቱ ተግባር መሰናከሉ ብቻ ሳይሆን በአባላቱ መካከል ሊዳብር ይችል የነበረዉ የመተማመን መጠን መጥፋቱም ጭምር ነው፡፡ ማኅበራዊ ካፒታልን ማውደም ግዑዝ ካፒታል (ለምሳሌ ድልድይን) ከማፍረስ እጅግ የባሰ ጉዳት ያስከትላል፡፡
ሕዝባዊ እምቢተኝነትን ውጤታማ ያደርጋሉ የሚባሉት ሶስቱም መሠረታዊ ግብዓቶች (በራስ መተማመንን ያጎለበተ ሕዝብ፣ አንፃራዊ ነፃነት ያላቸው ተቋማት እና በብልሃት የተቀመሩ የትግል ስልቶች) በተሟላ ሁኔታ አለመገኘታቸው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ብቻውን እንደ ስትራቴጂ ቢወሰድ እምንፈልገው ድል ያደርሰናል ብሎ ለማመን እንዳይቻል ያደርጋል። ስትራቴጂው ተስማሚ ቢሆንም ግብዓቶች ይጎድሉታል።
ለማጠቃለል፤ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እንደ ስልት ተስማሚነቱ (Suitability)እና ተቀባይነቱ (Acceptability) ከፍተኛ ነው፤ ተፈፃሚነቱ (Feasibility) ላይ ግን ጥርጣሬዎች አሉ። ይህ ስትራቴጅ ብቻውን ህወሓትን ጥሎ በምትኩ ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት እና ሀገራዊ አንድነቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለመገንባት ያስችላል ብሎ ማመን ይከብዳል።
3.2. ትጥቅ ትግል እንደ ስትራቴጂ
በአገራችን ታሪክ ውስጥ ጠመንጃና ስልጣን ከፍተኛ ቁርኝት አላቸው። አብዛኛዎቹ የስልጣን ሽግግሮች የተደረጉት በጠመንጃ ታግዘው ነው። ጦረኝነት ኢትዮጵያዊ ባህል ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠመጃንና ባለጠመንጃን ያወድሳል። ስለዚህም ትጥቅ ትግል እንደ ስትራቴጂ ምናልባት በልሂቃኑ ዘንድ ካልሆነ በስተቀር በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓይን የተቀባይነት ችግር የለበትም።
ተፈፃሚነትን በሚመለከት ደግሞ ወያኔ በትጥቅ ትግል የማይሸነፍበት ምክንያት የለም። ወያኔ የኃላያን አገሮች ድጋፍ ያለው መሆኑ፤ ጦሩን በዘረኛ መንገድ ማዋቀሩ እና በአለም ፓለቲካ የሽብርተኝነት ስጋት መኖሩ በትጥቅ የሚታገዙ የነፃነት ትግሎች የሚጠብቃቸው ተግዳሮት ቀድሞ ከሚታወቀው በላይ እንዲሆን አድርገዋል። ይህ ትግሉን ያከብደዋል እንጂ ወያኔ በጉልበት የማይሸነፍ ኃይል እንዲሆን አያደርገውም።
ተስማሚነትን በሚመለከት ግን ሁኔታው ለየት ይላል። “በጠመንጃ ወደ ስልጣን የመጣ ኃይል አገሪቱን ወደ ዲሞክራሲ ሊመራ ይቻላል ወይ?|” የሚለው ጥያቄ በቀላሉ የሚመለስ አይደለም። በዓለም ታሪክ ውስጥ በጠመንጃ ወደ ስልጣን መጥተው ወደ ሲቪል አስተዳደር (በአንዳንድ ሁኔታዎችም ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር) የተሸጋገሩ ሥርዓቶች አሉ። ኮሎምቢያ በ1957፣ ቬንዙዌላ 1958፣ ቦሊቪያ 1997፤ ስፔን 1931፣ ቱርክ 1960፣ ፓርቹጋል 1974፣ ጋና 1979፣ በቅርቡ በ2014 ግብጽን (ከመሀመድ ሙርሲ በኃላ የአብዱል ፈታ ኤል ሲሲ በመንፈንቅለ መንግሥት መምጣት) እና ሌሎች በርካታ ምሳሌዎችን በመዘርዘር መከራከር ይቻላል። ታሪክ፣ ዜጎችን ፈጅተው የመጡ አምባገነኖች ወደ ሲቪል አስተዳደር ሲቀየሩ አይታለች፤ በአንፃሩ ደግሞ በሰላማዊ መንገድ በሕዝብ ይሁንታ ወደ ስልጣን መንበር ወጥተው አስከፊ አምባገነን የወጣቸውን ታውቃለች። በክፋቱ የሚታወቀው የሂትለር ናዚ መንግሥት ወደ ስልጣን የመጣው በምርጫ ነው፤ ስታሊንም ሌኒንን ተክቶ እንጂ ገልብጦ የመጣ አይደለም። በሰላማዊ መንገድ የመጣ መንግሥት ዲሞክራሲያዊ መሆኑን ማረጋገጥ እንደማይቻል ሁሉ በጠመንጃ የመጣ ሁሉ አምባገነን ይሆናል ብሎ ማጠቃለል አይቻልም። ወሳኙ ነገር ለውጡ በመጣበት ወቅት ያለው የኃይል ሚዛንና የጠንካራ ተቋማት መኖር ወይም አለመኖር ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲ ተቋማት ይቅሩና አገራዊ ተቋማት እንኳን የሉም። አገራችንን እንደ አገር ሰብስበው የያዟት ተቋማት እየተዳከሙ ናቸው። ከአገራዊ ስሜት ጋር የሚፎካከር አካባቢያዊ ስሜት ፋፍቷል። ህወሓት በስልጣኑ ለመቆየት ሲል አጎራባች ማኅበረሰቦችን፤ የተለያዩ ሃይማኖት አማኞችን በአክራሪነት ስም ሲያጋጭ የቆየ በመሆኑ የትጥቅ ትግል ከቁጥጥር ካፈተለከ የት ሊያደርስ እንደሚችል መገመት ያስፈራል።
በዚህም ምክንያት የትጥቅ ትግል እንደ ስትራቴጂ ተፈፃሚ እና ተቀባይነት ያለው ቢሆንም ተስማሚነቱ አጠራጣሪ ነው።
3.3. ትጥቅ ትግል እና ሰላማዊ ሆኖም ግን ህገወጥ ትግል ተቀላቅሎ እንደ ስትራቴጂ
ከላይ ስለሕዝባዊ እምቢተኝነትና ትጥቅ ትግል የተገለፀውን በሰንጠረዥ 3 ተጠቃሎ ቀርቧል። በሰንጠረዥ 3 በግልጽ እንደሚታየው ሕዝባዊ እምቢተኝነትም ሆነ የትጥቅ ትግል ለየብቻቸው በስትራቴጂነት ሲቀርቡ የሚጎላቸው ነገር አለ።
ግባችን ወያኔን ማስወገድ ብቻ አይደለም፤ ከወያኔ በኋላ የምትኖረን ኢትዮጵያ ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት እና አገራዊ አንድነቷ የተረጋገጠ እንዲሆን እንፈልጋለን፤ የምንመርጠ የትግል ስትራቴጂ ወደዚህ የሚያደርሰን መሆን ይኖርበታል። አሁን ባለው ሁኔታ ሕዝባዊ እምቢተኝነትም ሆነ የትጥቅ ትግል ለየብቻቸው ወደዚህ ግብ ሊያደርሱን ይችላሉ የሚል እምነት የለኝም።
ሀገራዊ ተቋማት የሌሉ በመሆናቸው የመብት ጥያቄዎች ሀይማኖታዊ ወይም ክልላዊ ብቻ ሆነው እንዳይቀሩ፤ የመብት ጥያቄዎች በቂ ምላሽ የሚያገኙት የፓለቲካ ሥርዓቱ ሲለወጥ እና ዲሞክራሲያዊ አመራር ሲሰፍን እንደሆነ ሰፊ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት በኢትዮጵያዊያን የተገነባ ነገር ግን በህወሓት የሚመራ ነው። ሠራዊቱ አመራሩን አስወግዶ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንዲቆም የሚረዳው አካል ያስፈልጋል። እነዚህን ወሳኝ ተግባራት ለመከወን ነው የታጠቀ ሕዝባዊ ኃይል የመኖሩ አስፈላጊነት ጎልቶ የሚወጣው።
“ትጥቅ ትግል እና ሰላማዊ ሆኖም ግን ህገወጥ ትግል ተቀላቅሎ እንደ ስትራቴጂ” ተብሎ የተገለፀው በአጭሩ “ሁለገብ የትግል ስትራቴጂ” የሚባለው ነው። ”ሁለገብ የትግል ስትራቴጂ” ሕዝባዊ እምቢተኝነትና የትጥቅ ትግል (ሕዝባዊ አመጽ) ተደጋግፈው እንዲሄዱ የሚያደርግ ስትራቴጂ ነው።
ነፃና አገራዊ ተቋማት ባለመኖራቸው ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት በመሙላት ረገድ እና ወያኔ በሕዝብ ላይ ያሰፈነውን ፍርሀት ለመግፈፍ የታጠቀ ሕዝባዊ ኃይል ከፍተኛ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። የሕዝባዊ እምቢተኝነት መኖር ሕዝብ የትግሉ ባለቤት እንዲሆን ያደርገዋል። “ሁለገብ ትግልን” ስትራቴጂ አድርገን ከወሰድን “ሕዝባዊ እምቢተኝነት” እና “ሕዝባዊ አመጽ” ወደ ስልትነት ይወርዳሉ። ይህ ማለት ወደተፈለገው ግብ የሚደረሰው ስትራቴጂው በሙሉ በተግባር ላይ ሲውል ነው እንጂ አንዱ ብቻውን ተግባራዊ ሲሆን አይደለም ማለት ነው። ሁለገብ ትግልን እንደስትራቴጄ ከመረጥን ሕዝባዊ እምቢተኝነትንም ሕዝባዊ አመጽንም ማደራጀትና መምራት ይኖርብናል፤ ከዚህም በላይ ሁለቱን ማቀናጀት ይገባናል።
በሁለገብ የትግል ስትራቴጂ ላይ የሚቀርቡ ሁለት ዓይነተኛ ትችቶች አሉ።
አንዱ የአመጽ ትግልን እና ሰላማዊ ትግልን ማደባለቅ አይቻልም፤ “ውሀና ዘይት” ናቸው የሚል ነው። እርግጥ ሁለቱ የትግል ስልቶች በሚፈልጉት የሰው ዓይነትም ሆነ አደረጃጀት የተለያዩ ናቸው። ይህ ማለት ግን እያንዳንዳቸው በየሚፈልጉት አደረጃጀት ተደራጅተው ሊደጋገፉ አይችሉም ማለት አይደለም። በመሠረቱ እስካሁን የሚታወቁ የነፃነት ትግሎች እና አብዮቶች ሁሉ ምጣኔዓቸው ይለያይ እንጂ የሕዝባዊ እምቢተኝነትና የሕዝባዊ አመጽ ድብልቆች ናቸው። ደቡብ አፍሪቃን ከአፓርታይድ ነፃ ያወጣው ትግል ሁለቱ ስልቶች ተደጋግፈውበታል። በምሥራቅ አውሮፓና በሰሜን አፍሪቃ የተካሄዱ የለውጥ እንቅስቃሴዎችም ቢሆኑ አመጽና እምቢተኝነት የተደባለቀባቸው አሊያም የተፈራረቁባቸው ነበሩ። እንዲያዉም ዛሬ ያለውን የሰሜን አፍሪቃና መካከለኛ ምሥራቅ ሁኔታ ስናጤን ለማስተዋል ከምንገደዳቸው መራር ሀቆች አንዱ በሕዝባዊ እምቢተኝነት አምባገነን አገዛዞች ተገርስሰው በምትካቸው ደካማ መንግሥታት ወደስልጣን ከመጡ የተራዘመ ቀውስ ሊከተል የሚችል መሆኑ ነው። ይህ እውነታ ከመጀመሪያው የተደራጀ ሕዝባዊ ኃይል መኖር አስፈላጊነትን ያጎላዋል።
ሁለተኛው ትችት ደግሞ “የትጥቅ ትግል መኖር አምባገነኞች ወታደራዊ ኃይላቸውን እንዲጠቀሙ መንገድ ይከፍትላቸዋል በውጤቱም የበርካታ ሕዝብ ሕይወት አደጋ ላይ ይወድቃል” የሚል ነው። ሁለገብ ትግል እንደትግል ስትራቴጂ በአማራጭነት የሚወሰድባቸው አገሮች ውስጥ ያሉ መንግሥታት ሠራዊታቸውን በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ከማዝመት የማይመለሱ እንደ ህወሓት ዓይነት ያሉ አገዛዞች ናቸው። እነዚህ አገዛዞች የበዛ ጥፋት የሚያደርሱት ራሱን መከላከል የማይችል ሆኖም ግን ጠንክሮ የሚታገል ተቃዋሚ ሲገጥማቸው ነው። እንደዚህ ዓይነት አገዛዞች በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ከመተኮስ የማይመለሱ በመሆናቸው በመለሳለስ ኪሳራ ማስቀነስ አይቻልምበመሠረቱ እኛም አገር ቢሆን ሰላማዊ ትግልና የአመጽ ትግል የሚያስከፍሉት ዋጋ መሳ ለመሳ ሆኗል ።
“ሁለገብ ትግል” ራሱ የብዙ ስትራቴጂዎች ጥቅል ስያሜ መሆኑ ማስታወስ ይበጃል። ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች “ክብሪቱን አንዴ ለኩሱልን እንጂ ከዛ ቀጥሎ ያለውን ለኛ ተውልን ይላሉ” ይህ አነገጋር ወደ ስትራቴጂ ሲመነዘር የሚከተውን ይመስላል: ህወሓት ከስልጣን የሚወገደው ሕዝባዊ አመጽና ሕዝባዊ እምቢተኝነት በፈረቃ በተግባር ላይ በሚወሉበት ሁለገብ ትግል ነው። የፈረቃው ቅደም ተከተልም በመጀመሪያ ሕዝባዊ ኃይል ወታደራዊ እርምጃ ይወስዳል፤ በዚህ የተደፋፈረው ሕዝብ በሥርዓቱ ላይ በማመጽ ወያኔን ያስወግዳል፤ ጊዜዓዊ የሽግግር መንግሥትም ይቋቋማል። ሌሎች ሰዎች ደግሞ “እናንተ ከዳር እኛ ከውስጥ እናጣድፈዋለን” ይላሉ። ይህ አባባል ወደ ስትራቴጂ ሲመነዘር የሚከተለውን ይመስላል: ህወሓት ከስልጣን የሚወገደው ሕዝባዊ አመጽና ሕዝባዊ እምቢተኝነት በአንድነት በተግባር ላይ በሚወሉበት ሁለገብ ትግል ነው፤ ዳር አገር ትጥቅ ትግል መሀል አገር ደግሞ ሕዝባዊ እምቢተኝነት፤ ሁለቱን ተደጋግፈው ወያኔን ያስወግዳሉ፤ ጊዜዓዊ የሽግግር መንግሥትም ይቋቋማል። እንዲህ እያልን ከሁለገብ ትግል ብዙ አማራጭ ስትራቴጂዎችን ማሰብ እንችላለን። ከዚህም ሌላ ምን ያህል አመጽ ምን ያህሉስ እንቢተኝነት መደባለቅ ይኖርበታል የሚለው ራሱ ቁጥር ስፍር የሌላቸው አማራጮችን ይዞ የሚመጣ ነው። ከላይ እንደተገለፀው የትግል ስትራቴጂ መረጣ የአንድ ወቅት ሥራ የማይሆነው አዕምሮዓችን በአሠራን መጠን አማራጮችን እያሰፋን የምንመጣ በመሆኑም ጭምር ነው።
ሁለገብ የትግል ስልት ሲባል ሁለቱም ማለትም ሕዝባዊ እምቢተኝነትንና ሕዝባዊ አመጽን አቀናጅቶ መምራት የሚመለከት መሆኑ ግንዛቢ ሊያገኝ ይገባል። በሁለገብ ትግል ውስጥ የገባ ድርጅት በሁለቱም ሜዳዎች መጫወት ይኖርበታል። እኔ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ወይም ሕዝባዊ አመጽ ብቻቸውን እንደስትራቴጂ ከተመረጠ የምንፈልገው ቦታ አያደርሱንም፤ ሁለቱ ሲቀናጁ ግን በአንዱ የጎደለው በሌላው ተሟልቶ ስትራቴጂውም የተሟላ ያደርገዋል የሚል እምነት አለኝ።
4. ማጠቃለያ
በዚህ ጽሁፍ ውስጥ “የትግል ስትራቴጂ” እና “የትግል ስትራቴጂ መረጣ” ሲባል እኔ የምረዳውን ለማካፈል ሞክሬዓለሁ። “ሁለገብ ትግል” እንደ ትግል ስትራቴጂ ምን ማለት እንደሆነ እና ለምንስ ለኢትዮጽያ ተመራጭ ነው ብዬ እንደማምን የግሌን አስተያየት አቅርቤዓለሁ። ይህ ጽሁፍ ሁለገብ ትግል ለኢትዮጵያ ይበጃል የምንል ሰዎች ቢያንስ ሳናስብበትና ሳንጨነቅበት በግልብ የወሰነው ጉዳይ አለመሆኑ ያስረዳል ብዬ አደርጋለሁ።
The post የትግል ስትራቴጂ ምንነት እና የትግል ስትራቴጂ መረጣ (ክፍል ሶስት: የመጨረሻ) appeared first on Zehabesha Amharic.