ከፊልም ሥራ ጋር የተዋወቀችው ከ10 ዓመታት በፊት ቢሆንም በሙሉ ኃይሏና ጊዜዋ በኢንዱስትሪው ውስጥ ተጠቃሽ ባለሙያ የሆነችው ግን ከጥቂት ዓመታት በፊት ነው፡፡ 8 ለእይታ የቀረቡ ፊልሞች ላይ የተወነች ሲሆን ሁለቱ ደግሞ በቅርቡ ይወጡላታል፡፡ የአዱኒስ ድርሰት በሆነው በ‹‹መለከት›› ድራማ ዋና ገፀባህርይን ተላብሳ በመጫወቷም እናውቃታለን፡፡ የዛሬዋ እንግዳ ተዋናይት እና ሲቪል ኢንጂነር አዚዛ አህመድ፡፡
ጥያቄ፡- ስምሽና ሥራሽ ፊልምንና ድራማ ለሚከታተሉ አንባብያን አዲስ ባይሆንም አዚዛ አህመድ የትነው የተወለደችው?
አዚዛ፡- ጅማ ነው የተወለድኩት፡፡ እትብቴም የተቀበረው እዛው ነው፡፡ የልጅነቴን ጊዜ ጨምሮ የኖርኩት ደግሞ አዲስ አበባ ነው፡፡ ተመልሶ የመሄድ ዕድሉም ስላልነበረኝ ስለ ጅማ ብዙ የማስታውሰው ነገር የለኝም፡፡ በቅርብ እንደምሄድ ተስፋ አደርጋሁ፡፡
ጥያቄ፡- ፊልሙና ድራማው የሙሉ ቀን ስራሽ ነው?
አዚዛ፡- አሁን የሙሉ ቀን ሥራዬ ሆኗል፡፡ በፊት ግን ትምህርት ላይ ስለነበርኩ ወጣ ገባ እያልኩ ነበር የአርት ሥራዎችን እሰራ የነበረው፡፡
ጥያቄ፡- ምንድን ነበር የምትማሪው?
አዚዛ፡- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ነበርኩ፡፡ እሱን ስጨርስ ነው ሙሉ ለሙሉ ወደ አርቱ ፊቴን ያዞርኩት፡፡
ጥያቄ፡- ከሲቪል ምህንድስና ወደ ጥበብ ሽግግሩ አይከብድም?
አዚዛ፡- ደስ የሚል ሽግግር ነው፡፡ /ሳቅ…/ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሳለሁ ነው 1996 ላይ ጥበብ ጠራችኝ ብዬ በቴዎድሮስ ተሾመ፣ የተሰራውንና የቀዝቃዛ ወላፈን ቁጥር ሁለት ፊልም በነበረው ፍቅር ሲፈርድ ላይ የሰራሁት፡፡ ከጨረስኩ በኋላ አምስቱን ዓመት ትምህርቴ ላይ ትኩረቴን አድርጌ ከፊልሙ ኢንዱስትሪ ርቄ ቆይቻለሁ፡፡
ትምህርቱ ከባድ ነው፡፡ በዚህ በኩል ፊልሙም ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ውሳኔ ላይ መድረስ ነበረብኝ፡፡ ስጨርስ ግን ሙሉ ለሙሉ ወደ ጥበቡ ነው የገባሁት፡፡
ጥያቄ፡- ከነዛ ዓመታት በኋላ ስትመለሺ ዘርፉ በነበረበት ነው የጠበቀሽ? አልከበደሽም?
አዚዛ፡- በጣም አድጎ ነበር፡፡ በአጋጣሚ ፍቅርና ገንዘብ የተሰኘውን ፊልም ከሚሰሩ ልጆች ጋር ተገናኘሁ፡፡ የሶስት ሴቶችን ታሪክ ሲሰሩ አንዷን ካራክተር እኔ ወክዬ እንድጫወት ነበር የመረጡት፡፡ እኔም ታሪኩን ወድጄው ስለነበር በደስታ ግብዣውን ተቀብዬ በድጋሚ ወደ ፊልሙ ስራ ገባሁ ማለት ነው፡፡
ጥያቄ፡- ጎበዝ ተማሪ ነበርሽ?
አዚዛ፡- ምንም አልልም፡፡ ውጤቴም ለክፉ ሳይሰጥ ተመርቄያለሁ፡፡
ጥያቄ፡- አስተዳደግሽ አሁን ላለሽበት ቦታ አብቅቶኛል ትያለሽ?
አዚዛ፡- በጭራሽ እንዲሁ ዝም ብሎ ሚኒ ሚዲያዎች ላይ መካፈል፣ ፕሮግራሞች በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሲኖሩ ድራማዎችን መስራት ዕድሉ ነበረኝ፡፡ ከዛ በተረፈ ግን ቤተሰቤ ውስጥ ወደዚህ ሙያ እንድገባ የሚገፋፋኝ ሰው አልነበረም፡፡ ይበልጥ በትምህርቴ እንድገፋ ነበር ፍላጎታቸው፡፡
ጥያቄ፡- የፊልሙና የድራማው ዘርፍ አዳዲስ ተዋንያንን በደንብ ይጋብዛል?
አዚዛ፡- ኢንዱስትሪው በደንብ እየሰፋ ስለመጣ ዕድሉን የማግኘት ሁኔታው በዛው መጠን ትልቅ ነው፡፡ ደግሞም ብዙ አዳዲስ ፊቶችን በየጊዜው እያየን ነን እኮ፡፡
ጥያቄ፡- ሴት ተዋንያን ውበታቸውን በመጠቀም ፊልሞችን ይሰራሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ፊልሙን ፕሮዲውስ በማድረግ ወይም በሌላ መንገድ ተፅዕኖ በመፍጠር ነው ወደዚህ ስራ የሚመጡት ይሄ የኢንዱስትሪውን ዕድገት አይጎዳም?
አዚዛ፡- በቅድሚያ ፊልም ውበት ላይ ተመርኩዞ መሰራት አለበት የሚል እምነት የለኝም፡፡ እርግጥ ነው ጥሩና ሳቢ የሚባለው መልክ ቢኖርህና ፊልሙ ላይ በጥሩ ሁኔታ ብትተውን አይከፋም፡፡ ነገር ግን ያ መሰረታዊ ሊሆን አይገባም፡፡ የውጭ ሀገር ፊልሞችን ብትመለከት ፊልሙ የሚያጠነጥንባቸው ገፀ ባህሪያት የሚመረጡት፣ በዚህ መስፈርት ሳይሆን ስክሪፕቱ የሚፈልገው አይነት ሰው ሲሆኑ ነው፡፡ ያም ቢሆን የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚገባ እስከተወጡ ድረስ መልከኞቹንም ፊልሞቹ ላይ ብንመለከት ክፋት የለውም፡፡
ጥያቄ፡- በቅርቡ የወጣውን ሰኔ 30 የተሰኘውን ፊልም የማየት ዕድሉ ነበረኝ ጥሩ ሥራ እንደሆነ እኔ አምናለሁ፡፡ ፊልሙ ላይ የመሥራት ዕድል እንዴት አገኘሽ?
አዚዛ፡- ስለወደድከው ደስ ብሎኛል፡፡ ፊልሙ ላይ እንድሰራ ዕድሉን ያገኘሁት ዋጄ በሚባልና እስክሪፕቱን በፃፈው ሰው አማካኝነት፣ እንዳነብና አስተያየት እንድሰጥ በተጠየኩ ጊዜ ነው፡፡ ሥራውን እንደወደድኩት ስገልፅለት ከፕሮዲውሰሮቹና ዳይሬክተሩ ጋር ተገናኘሁ፡፡ እነሱም ከእኔ ጋር ለመስራት ፍላጎቱ ስለነበራቸው ወደ ቀረፃ ገባን፡፡
ጥያቄ፡- ሴት ተዋንያን ውበታቸውን በመጠቀም ፊልሞችን ይሰራሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ፊልሙን ፕሮዲውስ በማድረግ ወይም በሌላ መንገድ ተፅዕኖ በመፍጠር ነው ወደዚህ ሥራ የሚመጡት ይሄ የኢንዱስትሪውን ዕድገት አይጎዳም?
አዚዛ፡- በቅድሚያ ፊልም ውበት ላይ ተመርኩዞ መሰራት አለበት የሚል እምነት የለኝም፡፡ እርግጥ ነው ጥሩና ሳቢ የሚባለው መልክ ቢኖርህና ፊልሙ ላይ በጥሩ ሁኔታ ብትተውን አይከፋም፡፡ ነገር ግን ያ መሰረታዊ ሊሆን አይገባም፡፡ የውጭ ሀገር ፊልሞችን ብትመለከት ፊልሙ የሚያጠነጥንባቸው ገፀ ባህሪያት የሚመረጡት፣ በዚህ መስፈርት ሳይሆን ስክሪፕቱ የሚፈልገው አይነት ሰው ሲሆኑ ነው፡፡ ያም ቢሆን የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚገባ እስከተወጡ ድረስ መልከኞቹንም ፊልሞቹ ላይ ብንመለከት ክፋት የለውም፡፡
ጥያቄ፡- ከአርቲስት ሽመልስ አበራ (ጆሮ) እና ሰለሞን ሙሄ ጋር ነው ፊልሙ ላይ የተወንሽው፣ ከአንጋፋና ወጣት ተዋናዮች ጋር መስራት ምን አስገኝቶልሻል?
አዚዛ፡- በጣም ነው ደስ የሚለው፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ ከአንጋፋ ተዋናዮ ጋር የመስራት ዕድል በተደጋጋሚ ጊዜ አግኝቻለሁ፡፡ ከእነሱ ጋር ስትሰራ ለወደፊት ስራህ ስንቅ የሚሆንልህ ልምድ ታገኛለህ፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል እሱ የነበሩበትና ዛሬ እኛ ያለንበት ዓለም የተለያየ ነው፡፡ ካገኘሁት ጥሩ ልምድ ባሻገር የእውነት ሁለቱም ጥሩ ሰዎች ናቸው፣ ጥሩ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት፡፡
ጥያቄ፡- ስንት ተከፈለሽ?
አዚዛ፡- ስነ ስርዓት! (ረዥም ሳቅ) አዚዛ ውድ ነች በማስባል ስራ ልታሳጣኝ ነው?
ጥያቄ፡- በመጀመሪያ የፊልም ስራሽ ስንት አገኘሽበት?
አዚዛ፡- መጀመሪያ 5 ሺ ብር ነበር ከፍቅር ሲፈርድ ፊልም የተከፈለኝ፡፡ ከዛ ቀደም ማስታወቂያ ላይ ወይም በሌላ አጋጣሚ ስክሪን ላይ የመታየት ዕድል አልነበረኝም፡፡ ስለዚህ ጥሩ ፍራንክ ነበር ለእኔ፡፡ ቴዎድሮስም ይህቺ ልጅ ታድጋለች ብሎ ነበር፤ ያን ማድረጉ ለዛም አመሰግናለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ምን አደረግሽት ብሩን?
አዚዛ፡- ብዙ ነገር ላይ አውያለሁ፡፡ እንደዛስ ሆኖ መቼ በቀላሉ አለቀና? ብትኖር አበድርህ ነበር፡፡ ምን አለፋህ በወቅቱ የተማሪ ሃብታም ሆኜ ነበር፡፡
ጥያቄ፡- ትልቁ ክፍያሽስ?
አዚዛ፡- በቅርቡ ለሚወጣው ፊልም ጥሩ ብር ተከፍሎኛል፡፡
ጥያቄ፡- እስካሁን ስንት ፊልሞች ላይ ተሳትፍሽ? ፊልሞቹ እነማን ናቸው? ይበልጥ የደከምሽበትና የምትወጂውንም ንገሪኝ?
አዚዛ፡- 8 ፊልሞች ላይ እስካሁን ሰርቻለሁ፡፡ ‹‹እንዳባባሉ ሁሉም ልጆቼ ናቸው›› ማለት ሳይሆን፣ በሁሉም ፊልሞች ውስጥ የተወንኳቸው ገፀ ባህሪያት የተለያዩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለእኔ ሁሉንም ማወዳደሩ ከባድ ነው፡፡ እስካሁን የተወንኩባቸው ፊልሞች ፍቅር ሲፈርድ፣ ፍቅርና ገንዘብ 1 እና 2፣ እኔ ፕሮዲውስ ያደረኩት ጢባጢቤ፣ ሰኔ 30፣ የጥቁር ፈርጥ፣ ሳላ ይሰኛሉ፡፡ አሁን ደግሞ ሁለት ፊልሞችን እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡
ጥያቄ፡- የፊልሞችን ጥራት ለመጠበቅ አንድ ተዋናይ በዓመት ምን ያህል ፊልሞች ላይ መተወን ይኖርበታል ትያለሽ?
አዚዛ፡- መወሰን ከባድ ነው፡፡ ዝም ብለህ ያገኘኸውን ከመስራት በተቻለ መጠን፣ የተለያዩ ገፀ ባህሪያት በመምረጥ መስራት የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ገደቡን ግን ሁሉም ሰው አቅሙን ታሳቢ በማድረግ ነው የሚወስነው፡፡ እኔ ጥሩ ታሪክ ካገኘሁ ሙያውን የምወደው ስለሆነ ጊዜዎቼን አጣብቤ መስራት እችላለሁ፡፡ ነገር ግን ይሄን ያህል ብሎ ቁጥር ማስቀመጥ አይቻልም፡፡ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ፊት በፊልም ውስጥ መመልከታችን ብዙ ሰው ስሌለን ነው፡፡
ጥያቄ፡- ወደ ፊልም ስራ ስትገቢ የቤተሰብ ጫና አልነበረብሽም?
አዚዛ፡- በጣም ነበረብኝ፡፡ በተለይ አባቴ ደስተኛ አልነበረም አሁንም፡፡ ምናልባት ወደፊት በስራዎቼ ማሳመን ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ ቀሪ ቤተሰቦቼ ግን ስራዬን ይወዱልኛል ያበረታቱኛል፡፡
ጥያቄ፡- ወደፊት በፊልም ኢንዱስትሪው ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ የመፍጠር ዕቅድ አለሽ?
አዚዛ፡- አቅሙ ቢኖረኝ እና የፊልሙን ኢንዱስትሪ በሁሉም ዘርፍ ማሳደግ ብችል፣ አሻራዬን ጥዬ ባልፍ እመኛለሁ፡፡ እንደ ብዙዎቹ ባለሙያዎች፡፡ ትልልቆቹ ሆሊውድ እና ቦሊውድ የመሰሉ የፊልም ኢንዱስትሪዎች ከምንም ተነስተው ነው ዛሬ የሁሉንም ዓይን መግዛት የቻሉት፡፡ ቀደም ሲል እነዚሁ ኢንዱስትሪዎች እኮ ብዙ የሚተቹና እንከን የሞላባቸው የፊልም ስራዎችን ሲያመርቱ መቆየታቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ እኛም በዚሁ መንገድ አንድ ቀን ከምንፈልገው ደረጃ ላይ እንደምንደርስ እምነት አለኝ፡፡ የዚህ ጉዞ አካል መሆን ደግሞ እፈልጋለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ተመልካቹ አሁንም የፊልም ባለሙያውን እየመራው ነው ብለሽ አታምኚም?
አዚዛ፡- ነበር ብል ይሻለኛል፡፡ ምክንያቱም ያንን አካሄድ ሰብረው የወጡ ፊልሞችን መመልከት እየቻልን ነው፡፡ በአንድ ወቅት የኮሜዲ ስራዎች ብቻ ነበር በተመልካቹ የሚመረጡት፡፡ ነገር ግን እንደ ረቡኒ፣ ቀሚስ የለበስኩ ለታ፣ የሎሚ ሽታ እኔም የተወንኩበት ሰኔ 30ን ስትመለከት፣ በሌላ አቅጣጫ የቀረቡ ስለሆነ አሁን ላይ የፊልም ኢንዱስትሪው ተመልካቹን መምራት ጀምሯል ማለት ያስደፍራል፡፡
ጥያቄ፡- መለከት ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ በመሪ ተዋናይነት እሰራሽ ነው፣ ገጸባሃሪዋ ድራማውም ተስማምተውሻል?
አዚዛ፡- በጣም ደስ የሚል ድራማ ነው፡፡ የእኔ ታሪክ ባይሆንም በእውነተኛው ዓለም እየኖርኩት ያለውን ህይወት ነው ድራማው ላይ እየሰራሁ ያለሁት፡፡ አዚዛ ዋና ህይወት አላት፣ ከዛ በተረፈ ደግሞ አርቲስት ናት፣ ያንን ድራማ ውስጥ እያየሁት ስለሆነ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ አብረውኝ የሚሰሩት ተዋንያንም ብዙ እንድተጋ የሚያደርጉኝ ሰዎች ስለሆኑ ተመችቶኛል፡፡
ጥያቄ፡- በቅርቡ በልዩ ሁኔታ ቀለበት አስረሻል፣ ወደ አዲስ ህይወት ለመግባት እየተዘጋጀሽ ነው ምን ይመስላል ዝግጅት?
አዚዛ፡- ሄሎም ይባላል ጓደኛዬ… ለረዥም ዓመታት በጓደኝነት አብሮኝ የነበረ ሰው ነው፡፡ በቅርቡ በሰርግ ለመጋባት እየተዘጋጀን ነው፡፡ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
ጥያቄ፡- አዚዛ ምን አይነት ባህሪ ነው ያላት? ቁጡናት ይሉሻላ?
አዚዛ፡- አንተ ነህ ያልከው፡፡ አዚዛ እንዲሁ በመሳቅ ነው የምትታወቀው፡፡ እንደውም ካልሰማህ ከአባይ በኋላ በሳቅ ውስጥ የሚገኘው የአዚዛ እምባ ነው የሚገደበው ተብሏል፡፡
ጥያቄ፡- ተስፋ የምትጥይባት ተዋናይ አለች?
አዚዛ፡- አዚዛ አህመድ (ረዥም ሳቅ) ራሴ ላይ ተስፋ ብጥል ምን ክፋት አለው?
ጥያቄ፡- ምንም ክፋት የለበትም እሱስ፡፡ መብቴ ፊልሞች ላይ እንዲሳካልኝ አስተዋፅኦ አድርጎልኛል ብለሽ ታስቢያለሽ?
አዚዛ፡- አይመስለኝም፡፡ አዚዛን ለፊልም ስራ ሲመርጧት በውበቷ ነው ብዬ አላስብም፡፡ የሚመረጡ ሰዎች ውበት አንዱ መለኪያቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ከዛ በተረፈ ግን መስራት ትችላለች ብለው ያስቡበት ቦታ ላይ ካስት እንደሚያደርጉኝ ነው የማውቀው፡፡
ጥያቄ፡- በፕሮዲውሰርነት መሳተፍሽ ነግረሽል ፊልም የማዘጋጀት ፍላጎቱ አለሽ?
አዚዛ፡- ዝም ብሎ ሁሉንም መነካካት እንዲሆንብኝ አልፈልግም፡፡ እኔ ዳይሬክት ባደርጋቸው ብዬ ያዘጋጀኋቸው ስራዎች አሉኝ፡፡ ነገር ግን በደንብ ጎበዝ ሆኜ ካልሆነ በቀር ነካክቼ ብቻ ማለፍ አልፈልግም፡፡ ስለዚህ የተወሰኑ ጊዜዎችን በትወናው መቆየት እመርጣለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ተሰጥኦው የሌላቸው ሰዎች የጥበብ ስራ ውስጥ መግባታቸው ችግር የለውም?
አዚዛ፡- ፊልም ወይም ድራማ ለመስራት ገንዘብ ማውጣት ብቻውን በቂ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች፣ ከዛ በተረፈ ከሰዎች ጋር ባላቸው ቀረቤታም ፊልም ወይም ድራማ መስራት ቀላል የሚመስላቸው የሉም ማለት አይቻልም፡፡ እነዚህ ሰዎች ከትንሽ ጊዜ በኋላ ኢንዱስትሪው ውስጥ አናያቸውም፡፡ ይሄ ደግሞ ራሱን መሰረት ያስያዘ ባለሙያ እንዳንመለከት ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ችግር ይሆናል፡፡
ጥያቄ፡- በምህንድስናው ሙያሽ ትሰሪበታለሽ?
አዚዛ፡- ወደፊት፡፡ ምክንያቱም ብዙ ለፍቼበታለሁ፡፡ እንደውም በቅርብ ጊዜ ሁለተኛ ዲግሪ የመቀጠል ፍላጎት አለኝ፡፡
ጥያቄ፡- ስክሪፕት ትመርጫለሽ?
አዚዛ፡- ተመሳሳይ የሆኑ ገፀ ባህሪያት ላይ መስራት ስለማልፈልግ በተቻለ መጠን እመርጣለሁ፡፡ ትላንት ሰኔ 30 ላይ የታየችውን አዚዛ ሌላ ፊልም ላይ መድገም አልፈልግም፡፡ ከዛ ባለፈ ግን የፀሐፊው ማንነት ለእኔ ቦታ የለውም ጥሩ ስራ እስከሆነ ድረስ፡፡
ጥያቄ፡- አመሰግናለሁ፡፡
The post ‹‹በእውነተኛው ዓለም እየኖርኩት ያለውን ህይወት ነው ድራማው ላይ እየሰራሁ ያለሁት›› ተዋናይትና ሲቪል ኢንጂነር አዚዛ አህመድ appeared first on Zehabesha Amharic.