Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all 15006 articles
Browse latest View live

መላቀቅ የለም –ከአንተነህ መርዕድ

0
0

DD give upበዚች ቅፅበት፣ አንድ ቃል ተናግራቸሁ በማትጨርሱባት ደቂቃ፤ በወያኔ አልሞ ተኳሾች፤ በመላዋ ኦሮምያ፣ ጎንደርና ኦጋዴን ንፁሃን እየተገደሉ ነው። በዚችው ደቂቃ አፄ ዮሃንስና አባቶቻችን የወደቁባት መሬት በወያኔ ለሱዳን ተሰጥታ፤ አገራችንን አናስነካም ያሉ ጀግኖች ከወያኔና ከሱዳን በሚተኮስ ጣምራ ጥይት እየወደቁ ነው። በዚችው ደቂቃ ከአስራ አምስት ሚሊዮን የበለጡ ኢትዮጵያውያን አስፈሪውን ርሃብ ያለማንም እርዳታ ተጋፍጠውት ሮጠው ያልጠገቡ ልጆቻቸው እቅፋቸው ላይ ለዘለዓለሙ እያሸለቡ ነው። ከማምረቻ ፋብሪካዎች በላይ በበዙ ግልፅና ድብቅ እስርቤት ሺዎች እየማቀቁ ነው። ይህንን ሁሉ ግፍ የሚሠራው ዘረኛ ወያኔ እንደድሮው አፍኖ የሚገዛበት አቅም አጥቶ የመጨረሻ ኃይሉን እየተጠቀመ ሲሆን ህዝቡም ግፉ ሞልቶ በመፍሰሱ ከአሁን በኋላ እንደድሮው ላለመገዛት ቆርጦ መውጣቱን ከአሁኑ ድርጊቱ የበለጠ ማረጋገጫ አያስፈልግም።

ይህንን ህዝባዊ ትግል ወደ ዘላቂ ድል ለመቀየር አስተውሎ መራመድን ይጠይቃል። ተደጋጋሚ ድሎቹ የተነጠቁበት ህዝብ ተስፋ ባለመቁረጥ እንደገና ሲነሳ ዳር ቆሞ የሚታዘብና የሚያሽሟጥጥ አቅም ያለው ኢትዮጵያዊ የተረገመ ነው። በተለይም በሌለ አቅሙ ያስተማረህ/ሽ ምን ዓይነት እንቅልፍ አሁን ይወስድሃል/ሻል?? ትግሉ ብዙ ፍልስፍናና ምርምር የሚጠይቅ አይደለም። ዋና ዋና መሰረታዊ ጥያቄዎች እንዲፈቱ ማለም ብቻ ነው። የተነሳው ህዝባዊ አመፅ መልኩን እንዲይዝ አጀንዳውን ማስፋትና አገራዊ ማድረግ ወደ ዘላቂው መፍትሄ ያደርሳል። በመላ ኦሮምያና በጎንደር የተነሳው አመፅና በግፍ የሚፈሰው ደም ለተወሰነ ቦታ ሳይሆን ለአገር ነውና መስዋዕታቸውን ከፍተኛ ዋጋ ልንሰጠው ይገባል። የነሱን ትግል መላ ኢትዮጵያዊ እንዲቀላቀል የትግሉ ዓላማዎች አገራዊነትና ጥልቅ መሆን ስለሚገባቸው በነዚህ ዓላማዎች ዙርያ እንታገል። ህዝቡም እነዚህን ዓላማዎች እንዲያሳካ አቅጣጫ ይውጣለት።

  • የዜጎች ግድያና እስራት በአስቸኳይ ይቁም፤ ፈፃሚዎችም ለፍርድ ይቅረቡ!
  • ሁሉም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ይፈቱ!
  • የኢትዮጵያ ሉዐላዊነትና ድንበሯ ይጠበቅ!
  • መሬት የዜጎች እንጂ የአምባገነኖች የግል ንብረት አይደለም! መሬት ላራሹ ! የከተማ መሬት ባለቤትነት ይከበር!
  • የመፃፍ፣ የመደራጀት፣ የመሰለፍና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ያለገደብ ይከበር!
  • የመከላከያ፣ የደህንነትና የኤኮኖሚ ተቋማት ከጠባቡ ህወሃት እጅ ይውጡ!
  • ሁሉንም ያካተተ የሽግግር መንግስት ይቋቋም!
  • አገሪቱ ላይ እስካሁን የተፈጠሩትን ችግሮች መርምሮ የወደፊቷን፣ የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን ለመግንባት የሚያስችል ብሄራዊ እርቅ ይጀመር!
  • በርሃብ የተጠቁ ወገኖቻችንን በአስቸኳይ ለመርዳት የሚያግዝ ገለልተኛ አካል ይፈጠርና አፋጣኝ ህይወት አድን ሥራ ይቀናበር!
  • አገር ውስጥ ያሉ ሆኑ ውጭ የሚገኙ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶችና ንቅናቄዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በህዝባቸው ጉዳይ ላይ በአስቸኳይ ተገናኝተው ለመፍትሄው በጋራ መሥራት ይጀምሩ!

እነዚህ ከላይ የተቀመጡ ዓላማዎች ሁሉን የሚያጋሩ ይመስለኛል። የሚጨመሩም ካሉ ጨምሮ ህዝቡ በትልልቅ አላማዎች ዙርያ እንዲታገል የመምራትና የማስጨበጥ ሃላፊነት ያለባችሁ ወገኖች በዚህ ዙርያ ድከሙ። በየቦታው የተጀመሩ ትግሎችና ድሎች በሁሉም ይዳረሱ።

ኢትዮጵያን እግዜብሄር ይታደጋት!

ለልጆቿም ጥንካሬና አንድነትን ይስጥ!

 

The post መላቀቅ የለም – ከአንተነህ መርዕድ appeared first on Zehabesha Amharic.


እኔም ወያኔአዊ ብሆን እንደነሱ አስብ ይሆንን?  -ከተማ ዋቅጅራ

0
0
ከተማ ዋቅጅራ

ከተማ ዋቅጅራ

ሁሉም ኢትዮጵያዊ እየተናገረ  ያለው ከራሱ በላይ የአገሩ ጉዳይ ስለሚያሳስበው ነው። ከቤተሰቡም የበለጠ አገሩን ስለሚወድ ነው። ከዘሩ የላቀ ኢትዮጵያ አገሩ ስለሚበልጥበት ነው። አገር ማለት የእናት ናት የአባትም መገኛ ነው። አገር ማለት የሚስትህ ናት  የባልሽም መኖሪያ ነው። አገር ማለት ወልደህ ምትክህን የምታይባት ደስታህንም የምትገልጽበት የነገ ተስፋህ ልጅህ የሚኖርበት ነው። አገር ማለት የሁል ግዜህ እስትንፋስህ ለደቂቃም ልታጣው የማትችል አየርህ ነው። አገር ማለት ለህይወትህ ወሳኝ የሆነ ውሃህ ማለት ነው። አገር ማለት ደስታህ ሁለመናህ ነው። ስለዚህ ማንም ቢሆን በአገሩ አይደራደርም ምክንያቱም አገር የለህም ማለት እነዚህ  ሁኑ ነገር የሉህም ማለት ነው። አገር ከሌለህ አንተ  የትም ብትሄድ ስደተኛ ነህ። ሙሉ መብትም የለህም ሁለተኛ ዜጋ ትሆናለህ። በነጻነት የማትኖር በነጻነት የማትናገር በደስታ ህይወትህን የማትገፋ የፍቅር ርሃብተኛ ሆድህ ቢጠግብም አእምሮህ ሁል ግዜ ባዶነት የሚሰማህ የሩቅ ናፋቂ በቁጭት ኗሪ ማለት አገር የሌለው ሰው ነው። ሁላችንም እየተናገርን ያለነው ይህቺን ውድ የሆነች በምድር ላይ ልንኖርባት የተፈቀደልን አገራችንን ከራሳችን በላይ ወደናት ሁሉም በነጻነት በእኩልነት ይኖርባት ዘንድ አንድነት ይሻለናል ፍቅር ይበጀናል የምንለው አንዱ አንዱን አይበድል በዘር የተመረኮዘ ስልጣን በዘር የተመረኮዘ ጥቃት በዘር የተመሰረተ ክብር አይኑር የምንለው። በኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ብቻ ባለሙሉ መብት ባለቤት ባለሙሉ ስልጣን ባለስልጣን እንደየችሎታቸው በህዝብ ተመርጦ ይሰጣቸው የምንለው። ሁል ግዜም አትከፋፍሉን አትለያዩን ብለን የምንጮኸው የመጮህ ሱስ ኖሮብን አይደለም የምንናገረውም የመናገር አባዜ ተጠናውቶን አይደለም። ብቻ ሊያመጣ የሚችለውን ከባድ አደጋ ተረድተን እንጂ።  ሁሉም በዘር የሚደራጅ ሆኖ ከቀጠለ የአገራችን ሁኔታ ቅርጿን እንዳትቀይር በመስጋት እንጂ። እንዲ ስለሆነ እንዲ በመሆኑ በቀላሉ አሸናፊ እንሆናለን ብሎ ያሰበ ካለ እሱ የዋህ ብቻ ነው እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል ጉዳይ ይሆናል አርፎ የተኛውን ሰው በግድ ቀስቅሰነው አስነስተነው በኋላ ማብረጃው እንዳይቸግረን በማሰብ እንጂ። ለዚህም  እራሱን ለጥፋት  ያዘጋጀው እና ኢትዮጵያንም ለማጥፋት እየሰራ ያለው ወያኔ ነው። በኢትዮጵያ  ህዝብ ላይ እንደዚህ አደጋ እያመጣ እያየው ኢትዮጵያን ለማጥፋት እንደሚሰራ እያወኩኝ ወያኔ ብሆን እውን እደግፍ ነበረን?

ዛሬ ሁላችን አወቅን ወያኔ ስለ አገር ክብር የለውም ስለ ሰው ህይወት ግድ የማይሰጠው ግዜ በሰጠው ስልጣን ተጠቅሞ ወገኖቻችንን በጥይት ሲፈጅ በጋንቤላ፣ በአኝዋክ፣ በወለጋ፣ በአንቦ፣ በአርባ ጉጉ፣ በበደኖ፣ በባሌ፣ በአርሲ፣ በአዲስ አበባ፣ በወሊሶ፣ በጎንደር፣ በጎጃም፣ በሐረርጌ፣ በወሊሶ በሁሉም አቅጣጫ ኢትዮጵያዊያንን ያለ ርህራሄ ዜጎችን ሲገድል ግፉ ያማረረው ህዝብ ሰቆቃው የበዛበት ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ወጥቶ ሲቃወም ወያኔዎች ግን በአለም አገር ቤትም እንዲሁም በአለም ዙሪያ ያሉት ይቀልዳሉ ይሳለቃሉ አርፈው አይቀመጡም ነበረ ጥጋብ ነው እንዲህ የሚያደርጋቸው ዲሞክራሲ ስለተሰጣቸው ነው የሚረብሹት ብለው ጣታቸውን ወደሚሞተው ወደሚጨቆነው ህዝብ ይጠቁማሉ። እውነት እኔም ወያኔ ብሆን ግፈኛ እና ገዳይ መንግስትን በመደገፍ እንደነሱ አስብ ይሆንን?

ዛሬ ወያኔ የተባለው ቡድን እርስ በራሳችን እንድንፋጅ እያደረገን ነው። አንዱ ብሔር ከሌላው ብሔር በጠላትነት እንድንተያይ እያደረገ ነው። ይሄ ደግሞ በርዋንዳ እንደተደረገው የዘር ጭፍጨፋ ያመራናል ይሄ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በቶሎ የሚቆም ጉዳይ አይደለም ስለዚህ በአገራችን ይሄ እንዳይሆን ሁላችንም በጋራ በአንድነት እንቁም ጠላታችን ህዝብ ሳይሆን ወያኔ የተባለው ቡድን ነው እየቀሰቀሰ ያለውን የዘር ግጭቶችን እንቃወማለን ሲባል። እድሜ ለወያኔ የብሔር ብሔሮችን መብት አመጣ እድሜ ለወያኔ ሁሉም በቋንቋው እንዲናገር አደረገ። የተረሱ ብሔሮችን ያስታወሰ ለሁሉም እኩልነት ያመጣ ይሉናል። እኔም ወያኔ ብሆን እውን እንደነሱ አስብ ይሆንን?

ዛሬ ወያኔ ኢትዮጵያን የምትባለው አገር እያፈረሰና እየበታተኑ ነው  ይሄ ድርጊት ዝም ብሎ መመልከት አደጋ ስላለው ለግዜአዊ ስልጣን ብላችሁ ልጆቻችሁ  እና የልጅ ልጆቻችሁ የሚሮሩበትን አገር አታጥፉ ለልጆቻችሁም መከራን እና ስቃይን አታስቀምጡ ሲባል። እድሜ ለወያኔ አገር እየለማች ያለው እና በእድገት ጎዳናላይ ያስቀመጣት እንደውም 11% ያሰደገው ወያኔ ነው ይሉናል። ስለ እውነት እኔም ወያኔ ብሆን  የጥፋትን ሃሳብ እድገት ብዬ እናገር ይሆንን?

ውድ የትግራይ ልጆች እኛ እያለቀስን ያለው ለግዜው ወያኔ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሰውን  በደል በመቃወም ነው። የእንባችን ፍጻሜ ግን ለእናንተ ነው። ዛሬ አብዝተን የምንጮኸው ወደፊት በትግራይ ተወላጆች ላይ ሊከሰት የሚችለውን ሳስብ ወደፊት ሊመጣባችሁ የሚችለውን ነገር ሳልም ስለ እናንተ አለቅሳለው። ወደፊት ኃዘናችሁ ልክ የለውም ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ሲገደል ሲሰቃይ ዳር ቆማችሁ ታላግጡ ነበር ከዛም አልፎ እየሰለላችሁ አሳልፋችሁ ለእስር እና ለግድያ ታበቁ ነበር  ለ25 አመት ህዝባችን ቢታገሳችሁም ከመረዳት ይልቅ ዝምታን እንደ ፍራቻ ቆጠራችሁ  አርፎ የተኛን አንበሳ ነካክታችሁ ቀሰቅሳችሁት አሁን ሁሉንም ነገር የሰራችሁትን ስራ የእጃችሁን የምታገኙበት ሰዓት መጣባችሁ። ዛሬ በኢትዮጵያ  እየተሰራ ያለው ነገር ትግራይን አንደኛ የማድረግ ስራ በሰፊው ይሰራል የትግራይ ተወላጆች በአንደኝነት ዜግነት ተሰላፊዎች ናቸው ስራ የሚያገኝት ቅድሚያ እነሱ ስልጣን የነሱ መሬት በሰፊው የሚሰጠው ለነሱ በዚህ የተነሳ የትግራይ ክልል፡-

በጨርቃጨርቅ አምራች ከኢትዮጵያ አንደኛ፡- ትግራይ

በብረታ ብረት ምርቶች ትልቁ የማሽነሪው ባለቤት አንደኛ፡- ትግራይ

በመኪና ሞተር አምራችነት ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ፡- ትግራይ

የባለ ብዙ ድርጅት ባለቤቶች አንደኛ፡- ትግራይ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሙሉ አንቀሳቃሾች፡- ትግራዮች

መከላከያውን እና የደንነቱ ዋና ዋና ሰዎች፡- የትግራይ ሰዎች

የሚሞቱት፣ ከቦታቸው የሚፈናቀሉት፣ ስራ የሚያጥቱት፣ የሚሰደዱት፣ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ

በዚህ የተነሳ የግዜአዊ ተጠቃሚነታቸውን በማየት የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጣውን ተቋውሞውን እኩልነት ነጻነት እያለ ድምጹን ሲያሰማ እስከዛሬ ድረስ የትግራይ ተወላጆች እኛ ልማት ላይ ነን ከማለት ውጪ የኢትዮጵያ ህዝብን ችግር የተመለከት የለም። ወያኔንም የሚቃወምም አላጋጠመኝም። በዚህ የተነሳ በኢትዮጵያ የጨቋኙ ስርአት በግልጽም በተዘዋዋሪም ደጋፊዎች ናችሁ ማለት ነው። ስለዚህ ወያኔ ሲጠፋ ያኔ ለናንተ ነው የማዝነው እና የምናለቅሰው።ሁሉም ክልሎች የማንንም እርዳታ ሳይፈልጉ ባላቸው የተፈጥሮ ሃብት መልማት እና ማበብ መስራት እና ማደግ ይችላሉ የትግራይ ግን የተፈጥሮ አቀማመጧ አይፈቅድላትም ስለዚህ  ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ጋር በፍቅር መኖር ነበረባቸው። ፍቅር ብቻ ነው ሊያኖራቸው የሚያስችላቸው። ይሄንን ፍቅር፣ አብሮ የመኖሩን፣ የመተሳሰብ፣ የመዋደድን ድልድይ ወያኔ 25 አመት የጥላቻ  እና የመለያየት ስራዎችን በመስራት ሰብረውታል። የኢትዮጵያው ህዝብ የትግራይ ጠላት አድርጎ  በመሳል ወያኔ ከሌለ ትግራይ የለችም በማለት እየሰበከ ክፉ ልብ እንዲይዙ አድርጓል።ወያኔ ስልጣንን ለማራዘም የትግራይን ህዝብን መደበቂያ ማርደጉን ይታወቃል ይሄንን ደግሞ  ከሌላው ኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አብራችሁ ወጣችሁ መቃወም ይገባችኋል። ነገ ለሚፈጠረው ነገር ማሰቡ መልካም ነው። ወደልቦናችሁ ተመልሳችሁ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በፍቅር እንድትኖሩ እና ወያኔን ከጉያችሁ በማውጣት ኢትዮጵያን እንዳትጠፋ አብራችሁ ከሁሉም ህዝብ ጋር ትቆሙ ዘንድ የመጨረሻው ደውል ተደውሎላችኋል ደውሉን መስማት የእያንዳንዱ የትግራይ ህዝብ ጉዳይ ነው።

ከተማ ዋቅጅራ

15.12.2015

Email –waqjirak@yahoo.com

 

 

The post እኔም ወያኔአዊ ብሆን እንደነሱ አስብ ይሆንን?  -ከተማ ዋቅጅራ appeared first on Zehabesha Amharic.

Sport: የፕሪሚየር ሊጉ ‹‹ክስተት›› ቡድን –ሌይስተር ሲቲ

0
0

city
ሼይላ ኬንት ባለፉት 40 ዓመታት የሌይስተር ሲቲን ትጥቅ በማፅዳት ሥራ ተጠምዳ ቆይታለች፡፡ በእነኚህ አራት አስርት ዓመታት ሌይስተር ሲቲ እንደ አሁኑ ስኬታማ ሆኖ ተመልክታ አታውቅም፡፡

የአሰልጣኝ ክላውድዮ ሪኒዬሪ ቡድን ከቅዳሜው ጨዋታ በፊት በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ተቀምጦ ነበር፡፡ ይህንን የውድድር አመቱ መጀመሪያ ድረስ ማንም አስቦት አያውቅም ነበር፡፡

‹‹ባለፉት 40 ዓመታት ያመለጠኝ ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ናቸው›› ይላል ጨዋታዎች ብቻ ናቸው ይላል ከ1971 ጀምሮ በሌይስተር ሲቲ በእግር ኳስ ተጨዋችነት እንዲሁም አሁን በአምባሳደርነት እየሰራ የሚገኘው አለንቢርቺናል፣ ‹‹እዚህ በነበረኝ ቆይታ 24 በሚደርሱ የቀብር ስነ ስርዓቶች ላይ ተሳታፊ ነበርኩኝ፡፡ የዓለማችን እድለኛ ሰው እንደሆንኩኝ መናገር አለብኝ፤ በክለቡ ቆይታዬ ምርጥ የምባል እግርኳስ ተጨዋች አልነበርኩም፡፡ በርካታ ጨዋታዎች አልተጫወትኩም፡፡

‹‹እዚህ በነበርኩበት ወቅት አስደሳች ጊዜያትን አሳልፌያለሁኝ፣ በአሁኑ ሰዓት ክለባችንን በአምባሳደርነት መምራቴ ያስደስተኛል ሆኖም ከተጫዋችነት ዘመኔ ይልቅ በአምበሳደርነት ያገለገልኩበት ዘመን የተባለ ነው፡፡
የእግርኳስ የስኬት አንዱ ምስጢር በጋራ አብሮ የመስራት ባህልን ማዳበር ነው የፅዳት ክፍሉ የዚህ አንድ አካል እንደሆነ ይታወቃል፡፡

‹‹ይህ ወቅት በሁሉም ዘንድ የሚወደድ ነው›› ችላለች የክለቡን ትጥቅ ፅዳት የምትቆጣጠረው ቬይላ፣ ‹‹ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ እናት ላይ የተቀመጥነው መቼ ነበር? በአሰልጣኝ ማርቲን ኦኔይል ዘመን በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ ሆነን ፈፅመናል፣ ሆኖም ይህ አሁን የምንገኝበት ደረጃ የምንጊዜውም ምርጡ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ክላውዲዮ መጥቶ ሄሎ አለን፤ ከጣልያን ቼኮሌት ይዞልን መጣ፤ ጎክሃን (አንላር) ወደዚህ እንዲመጣ አደረገ፡፡ አጋጣሚው በጣም አስደሳች ነበር››

በሌይስተር ሲቲ አመጋገብ በጥንቃቄ እና ሳይንሳዊ ግብአቶችን ያሟላ ነው፤ ‹‹ለረጅም ዓመታት ውጣ ውረዱን ተመልክቻለሁኝ›› ይላል ለረጅም ጊዜ በምግብ ባለሙያነት ለክለቡ ያገለገለው ጋሪ ፔቶን፣ ‹‹አሁን በምንገኝበት ደረጃ ለመብቃት ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፈናል›› ይላል፡፡ ለረጅም ጊዜ በምግብ ባለሙያነት ለክለቡ ያገለገሉት ጋሪ ፔቶን፣ ‹‹አሁን በምንገኝበት ደረጃ ለመብቃት ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፈናል፣ የገንዘብ ችግር ተፅዕኖ አሳርፎብንም ነበር፡፡ ይህ ሁሉ አልፎ አሁን ያለውን ነገር ስመለከት የኩራት ስሜት ይሰማኛል››
በሜዳ ውስጥ የተጨዋቾች ታታሪነት በጣም ይገርማል፡፡ ተጨዋቾቹ በልምምድ ሜዳ ላይ ከመደበኛው ልምምድ ውጭ ተጨማሪ ሥራዎችን ይሰራሉ፡፡

‹‹በአሁኑ ሰዓት በክለቡ ውስጥ ያለው ስሜት ያስደስታል›› ይላል የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዳኒ ሲምፕሰን፣ ‹‹ሁሉም ተጨዋቾች ከመደበኛው ልምምድ ውጭ ተጨማሪ ልምምድ እንሰራለን፤ እግርኳስ ከአእምሮ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አሁን በጥሩ ስሜት ላይ እንገኛለን ነገር ግን አንድ ቦታ ላይ መቆም አንፈልግም››
ለሌይስተር ሲቲ ውጤታማ ጉዞ አንዱ ምስጢር ክላውዲዮ ራኒዮሪ እንደሆኑ ጥርጥር የለውም፣ ጣልያናዊው አሰልጣኝ ለእንግሊዝ እግርኳስ አዲስ አይደሉም፤ በቼልሲ አስደሳች ጊዜያትን አሳልፈዋል፤ በአገራቸው ጣልያን፣ ፈረንሳይ (ሞናኮ)፣ የግሪክ ብሔራዊ ቡድንን እና ስፔን አሰልጥነዋል፡፡

‹‹በእግር ኳስ ማሸነፍ፣ መሸነፍ እና አቻ ውጤቶች ቢኖሩም ተጨዋቾቼ በተመሳሳይ የአዕምሮ ጥንካሬ እንዲጫወቱ ስነግራቸው ቆይቻለሁኝ›› የሚል አስተያየትን የሚሰጡት ራኒዮሪ ‹‹በጭራሽ መዘናጋት አልፈልግም፣ ተጨዋቾቼ ከተዘናጉ ቡድኑ ሌይስተር ሲቲ እንዳልሆነ እነግራቸዋለሁኝ፣ እነርሱም ቢሆኑ ይህንኑ ጠንቅቀው ያውቃሉ›› በማለት ሁልጊዜም ቢሆን በተነቃቃ መንፈስ የሚጫወት ቡድን እንዲኖራቸው ያላቸውን ፍላጎት ጠቁመዋል››

በቼልሲ ሳሉ አፈራርቆ የማጫወት ፖሊሲን ይከተሉ የነበሩት ራኒዮሪ በሌይስተር ሲቲ አቀራረባቸው ተቀይሯል፤ (የማንቸስተር ዩናይትዱን ጨዋታ ሳይጨምር) ባለፉት 13 ጨዋታዎች ከቋሚ ተሰላፊዎች ዘጠን ያህሉ ዘጠኝ እና ከዚያ በላይ ጨዋታዎችን ፈፅመዋል፡፡

የቋንቋ ጉዳይ ሌላው ጥያቄ የሚነሳበት ነገር ነው፤ በቼልሲ ሳሉ በዚህ ረገድ ይቸገሩ የነበሩት ጣልያናዊ አሰልጣኝ አሁን በሌይስተር ሲቲ ስኬታማ ሆነዋል፡፡

‹‹በቼልሲ ሳለሁኝ ሁሉም ነገር የሚከናወነው በአስተርጓሚ ነበር፤ ያ ጊዜ ጋስ ፓዬት፣ ማርሴይ ዴሳይ እና ጂያን ፍራንኮ ዞላ በአስተርጓሚነት ያግዙኝ ነበር፤ አሁን ይህ እንደ አንድ ችግር አይነሳም ይላሉ የ64 ዓመቱ አሰልጣኝ፡፡

ባለፈው ዓመት ላለመውረድ ሲጫወት የነበረው ሌይስተር ሲቲ ዘንድሮ ፍፁም ተሻሽሏል፤ ራኒዬሪ እንኳን በዚህ ደረጃ የሚገኝ ክለብ በአደረጃጀቱ ተገርመዋል፡፡ ያም ቢሆን ግን በሌይስተር ሲቲ ስማቸው ልቆ የሚነሳውን ናይጅል ፔርሰን መርሳት አይገባም፡፡

‹‹በዙሪያዬ የሚገኙ ስታፎችን ስመለከት እገረማለሁኝ፣ የአካል ብቃት አሰልጣኞችን፣ የምልመላ አቅማችን፣ የቪዲዮ ትንታኔ… ሁሉም ነገር አስገራሚ ነው›› የሚል መረጃን የሚሰጡት በአሰልጣንነት የ30 ዓመት ልምድ ያላቸው ራኒዬራ ናቸው፤ ‹‹ሁሉም ነገር የተሟላ ከሆነ ለምን መቀየር ያስፈልገኛል፤ በአጠቃላይ ደስተኛ ነኝ››
ረዳት አሰልጣኙ ስቲቭ ዋልሽ ካለ ልዩ ተሰጥኦ ተጨዋቾችን ይመለምላል፤ ሪያድ ማህሬዝ አንዱ ነው፡፡ ለአማካይ ክፍሉ ጉልበት እና ኳስን በመንጠቁ ረገድ ምርጥ የሆነው ጓጎሎ ካንቴ ሌላው የሚጠቀስ ተጨዋች ነው፡፡

‹‹በዚህ አይነት መልኩ ምን ያህል ርቀት እንደምንጓዝ የማውቀው ነገር የለም፣ በአሁኑ ሰዓት የሚበርሩ ተጨዋቾች አሉን፤ ባለፉት 50 ዓመታት ከማውቀው ምርጥ የምልመላ ክፍል አለን፤ ነገሩ አስደሳች ነው›› ይላል አለን ቢርቼናል፡፡

The post Sport: የፕሪሚየር ሊጉ ‹‹ክስተት›› ቡድን – ሌይስተር ሲቲ appeared first on Zehabesha Amharic.

ኦሮሞው ኢትዮጵያዊ ያነሳውን የትግል ችቦ ሌላው ኢትዮጵያዊም ተቀብሎ ያበራል! –ገለታው ዘለቀ

0
0

 

nega 2የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ከዚህች ከኣዲስ ኣበባዋ የመሬት ነጠቃ ጥያቄ በጅጉ ገዝፎ የሄደ ነው። ከፍተኛው ጥያቄ የመልካም ኣስተዳደር ጥያቄ ነው። በመጀመሪያ ህወሃት ይህን ዘረኛ ፖለቲካውን ተሸክሞ ኣዲስ ኣበባ ከገባ በሁዋላ በተለይ ኦሮሞንና ኣማራን ጸጥ ኣድርጎ ለመግዛት የተጠቀመው ዘዴ በነዚህ ክልሎች ውስጥ ከታች እስከ ላይ ያሉትን ባለ ስልጣናት በኣልተማሩና የማስተዳደር ችሎታ በሌላቸው ነገር ግን ታዛዥ ብቻ በሆኑ ሰዎች መሙላት ነበር።  ወያኔዎች ይህን ያደረጉበት ምክንያት ህወሃት ይዞት የተነሳው ጥያቄ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የዴሞክራሲ  ጥያቄ ባለመሆኑና ዋናው ዓላማው የሆነ የራሱን ክብ ለመጥቀም በመሆኑ እነዚህን ክልሎች ኣፍኖ የሚይዝለት ኣስተዳደራዊ መዋቅር ስላስፈለገው ነው። ህወሃት ያሻውን ያደርግ ዘንድ “የራሴ”   የሚለውን ክብ ለመጥቀም ይችል ዘንድ በየክልሉ የራሱን መጠቀሚያዎች መፈለግ ስለነበረበት ነው። በነዚህ ክልሎች ሰው በባትሪ ተፈልጎ የሚሾመው ህወሃት የኣሳቡ እስኪሞላ ድረስ ፈረስ የሚሆኑትን ሰዎች በማግኘት ላይ የተመሰረተ ነበር። የማይጠይቅ፣ የሚፈራ፣ ለጥቅም የሚንበረከክ፣ እውቀት የሌለው፣ በባትሪ እየተፈለገ የሚሾመው ህወሃት ቀድሞ ላሰበው የግል ጥቅም ስራው ኣንድ ራሱን የቻለ ስትራተጂ ኣድርጎ ስለወሰደው ነው።  ውሎ ሲያድር ይህ ስትራተጂ ምን ኣመጣ? ከባድ የመልካም ኣስተዳደር ችግር በተለይ በኦሮምያና ኣማራ ክልሎች  ኣመጣ። የበቁ የነቁ የኦሮሞ ተማሪዎች ወይ በኦነግ ወይ በተቃዋሚ እየተፈረጁ ተወገዱ። የኦሮሞ ህዝብ ልቡ ኣዘነ። የተማሩ ልጆች እያሉኝ፣ ጥሩ ጥሩ ማስተዳደር የሚችሉ ልጆች እያሉኝ ለምን እንዲህ ኣደራጋችሁኝ? እያለ ኣነባ።  ኣማራው ኣካባቢም እንደዚሁ ታዛዡን እየፈለጉ ሲሾሙ በክልሉ ቀልጣፋ ኣገልግሎት ጠፋ፣ ህዝቡ ወደ ወረዳ ወደ ክልል ወደ ዞን ሲሄድ የሚያገኛቸው ባለስልጣናት ችግሩን የማይረዱ ኣንዳንዴም በሚያሳፍር መልኩ ህዝቡ የሚለው እንኳን የማይገባቸው ሆነው ተገኙ። ተራው ሰው  የበለጣቸው መሪዎች በየቦታው በመኖራቸው ህዝቡ ከኣመራር ኣካላቱ የሚጠብቀው ነገር ጠፋ። በተለይ የነዚህ የሁለቱ ክልሎች  ትልቅ ችግር ይሄ ነው። ህወሃት እነዚህን ክልሎች ከቀጣበት መንገድ ሁሉ በጣም ኣስከፊው ቅጣት ይሄ ነው። በራሳቸው ልጆች በጃዙር ቀጣቸው።  በርግጥም ልጆች እያሏቸው  የተማሩትን የተሻሉትን እያባረረ በማይሆኑ ሰዎች እንዲተዳደሩ መደረጉ ትልቅ ቀውስን ኣምጥቷል። ህወሃት እነዚህ ሰዎች መሳሪያው ስለሆኑና እላይ ቆልለውት እየሰገዱለት ስለሚኖር ደስ ብሎታል። የመጣው ማህበራዊ ቀውስ ግን ልክ የለውም። ይህ ችግር በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ቢታይም በኦሮምያና በኣማራ ግን የከፋ የከፋ ሆኖ ይታያል። በኣንዳንድ ቦታዎች ህወሃት ስልጣን ሲይዝ የወረዳ ሊቀመንበር የሆኑት ህወሃት ከመምጣቱ በፊት ችሎታ የሌላቸው ጥሩ ምግባር ያልነበራቸው ወዘተ ነበሩ። እነዚህን ሰዎች እየሰበሰበ የቀበሌ ምክር ቤት፣ የወረዳ ምክር ቤት፣ የክልል ምክር ቤት እያለ ነው ይሾም የነበረው። ህዝቡ ለጊዜው ይስቅ ነበር። ይሁን እንጂ  መራራው እውነት ግን እነዚህ ሰዎች የዚህን ህዝብ እጣ ፈንታ የሚወስኑ ስለነበር ሳቁ ወደ ኣዘን በፍጥነት ተቀየረ። ኣንዳንድ ለምልክት ከየብሄሩ ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ደግሞ ህወሃት በኣጃቢ ስም የቁም እስር ኣስሯቸው የህወሃትን ፍላጎት እያስፈጸሙ እንዲኖሩ ተደርገዋል።ይህ ችግር ለብዙ ኣመታት ሲቆይ የመልካም ኣስተዳደር ብሶቱን ኣበዛና እነሆ ዛሬ ህዝቡን በእንባ ኣራጨ።

 

ኣንዱ የዛሬው የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የሚያስተዳድሩትን ህዝብ ጥለው ህወሃትን ቆመው የሚያበሉ የክልሉን ኣስተዳዳሪዎች ማውገዝ፣ ህወሃት የፈጠረው ይህ ራስ ወዳድና ስግብግብ ፖለቲካ እንዳስቆጣቸው ለመግለጽ፣  ለውጥን ለመሻት ነው። ሌላው ጉዳይ  ደግሞ ከመልካም ኣስተዳደሩ ችግር በተጨማሪ ኣጠቃላይ የፖለቲካው ኣወቃቀር ህዝቡን ግራ ግብት ኣደረገው። በተፈጥሮ ሃብት፣ በባህል፣ በፖለቲካ ተሳትፎዎች ግልጽ የሆነ ስምምነት የለም። ይሄ ጉዳይ ከፍተኛ ማህበራዊ ምስቅልቅል ኣመጣ። ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመን ስትኖር ኣንዳንድ ክፉ ትውስታዎች(memories) ነበሯት፣ ብዙ መልካም ትዝታዎችም(good memories) ነበሯት።  የህወሃት ፖለቲካ የቆመው ግን መጥፎዎቹን ትዝታዎች(bad memories)  እየመረጠ በነዚያ ላይ ነው ቤቱን የሰራው።  ነገር ግን ፖለቲካ ዓላማው በጎ ለውጥን ማምጣት በመሆኑ ለማህበረሰብ ለውጥ እንደ ኤነርጂ ኣድርጎ ሊጠቀምባቸው የሚገባው ጥሩ ጥሩ ትዝታዎችን በማጉላት ነበር። የኛ ፖለቲካ ግን በተቃራኒው መጥፎ ትዝታዎችን  በማጉላት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠረው ኤነርጂ ኔጌቲቭ እንዲሆን እየታገለ ነው።ታዲያ ፖለቲካ በመጥፎ ትዝታዎች ላይ ሲቆም ኣንዱ ውጤት ይህ ነው። ቡድኖችን ማጋጨት፣ ብሄራዊ ማንነትን ማኮሰስ ፣ ኣገርን ማስጠላት ስደትን ማብዛት ነው። ይህ ጉዳይ ህዝቡን ውስጡን ጎድቶታል። ፖለቲካ በመልካም ትዝታዎች ላይ ቆሞ እነሱን እያራገበ መጥፎዎቹን ሊያርምና ሊክስ ነበር የሚገባው። ኣለመታደል ሆነብንና የህወሃት ፖለቲካ መጥፎዎቹን እያራገበ፣ ማራገብ ብቻ ሳይሆን ማጣፈጫ  ጨው ጨመር እያደረገ  የውሸት ታሪክ እየጻፈ ኣበላሸው።  ይህ ጉዳይ በጣም ጎድቶናል። ትልቅ ብሄራዊ ስብራትም ኣመጣ።

 

 

ኣሁን የህዝቡ ጥያቄ የለውጥ ጥያቄ ነው። ድሃው ህዝብ በቃል የሚገልጻቸውና የማይገልጻቸውን  ውስብስብ ችግሮቹን  በማስተር ፕላኑ  ለመግለጽ ይሞክር እንጂ ብሶቱ የትየለሌ  ነው። ትልቁ ብሶት የተበላሸውን የሶሺዮ ፖለቲካ ስርዓት እንዲለወጥ ከመፈለግ ነው። ህዝቡ ለውጥ ያለ ልክ ተርቧል። ጥያቄው ይሄ ነው።ወለጋ ውስጥ ያለውን ኦሮሞ፣ ምእራብ ሃረርጌ ያለውን ኦሮሞ ወዘተ…. ገንፍሎ እንዲነሳ ያደረገው ጉዳይ የመልካም ኣስተዳደር እጦትና ይህን ተከትሎ የመጣው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግፎች ናቸው።

 

ታዲያ የህዝቡ ጥያቄ የለውጥ ይሁን እንጂ በዚህ የለውጥ ወራት ጊዜ የትግላችንን ፍሬ ሊለቅሙ ከሚጣደፉ ወያኔዎች መጠንቀቅ ኣስፈላጊ ነው። በሃገራችን የሚመጣው ለውጥ ግዙፍ ለውጥ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን እንደገና ኣፍርሶ የሚሰራ መሆን የለበትም። ኢትዮጵያን እንደገና የሚያንጽ ስራ ነው የሚያስፈልገው። ስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ኣንድነት ኪዳን ውስጥ ልንገባ ይገባል። ይህ ማለት ኢትዮጵያን በመገንጠል ሪፈረንደም ወይም በሌላ መንገድ ኣፍርሰን እንደገና እንስራ ወይም እንገነጣጠል ማለት ኣይደለም።  ኢትዮጵያን እንደዚህ ለማሳብ ኣይቻልም። ኢትዮጵያ ውስጥ ግልጽ የሆነ የቡድኖች የድንበር ክልልም የለም። እነዚህ ኣሁን ያሉት ዘጠኝ ክልሎች ትናንት ወያኔ የፈጠራቸው፣   እንዳሻው የሰራቸው ናቸው። ኢትዮጵያ ስትፈጠር ዘጠኝ ክልል ነበረች የሚል ታሪክ የለም። ወያኔ በፈጠረው ኮራብትድ ክልል የመገንጠል ሪፈረንደም ኣይሰራም። ኣገራችን  ኣንድ ናት። የተቀየጠው ህዝብ ብዛት ከብሄሮች ቁጥር በልጧል። ወያኔ እንደሚለው ሳይሆን የጋራ ግዙፍ ታሪኮች ኣሉን። የጋራ ሃብት ኣለን። ወንዞቻችን የተፈጥሮ ሃብቶቻችን የጋራ ናቸው።ኣንዳንድ የወያኔ ኣባላት ከዚህ በፊት ጥለውት የነበረውን የመገንጠል ጥያቄ ዛሬ የኦሮሞ ህዝብ ሲነሳባቸው ሊያነሱ ይችላሉ። ኣምነውበት ባይሆንም ለጊዜው መሸሸጊያ ይሆነናል ከሚል ትግራይን ለመገንጠል ያስቡ ይሆናል።  ይህን የሚያደርጉት ደግሞ በቀጥታ ኣይደለም። እንዲህ ኣይነት የህዝብ ተቃውሞ ሲነሳ ይህንን ትግል ሃይጃክ በማድረግ ሊሆን ይችላል።   በመጀመሪያ ኣገሪቱን ኣፍርሰው፣ በተለይ ኣማራውንና ኦሮሞውን ኣባልተው ነው የሚሄዱት። የመገንጠል ጥያቄው  ከሌላ ብሄር እንደመጣ ኣድርገው ሌላውን ብሄር በየቤትህ እደር ኣይነት ከበተኑ በሁዋላ የሚያስቡትን ለማድረግ ይሞክሩ ይሆናል። ከዚህ በፊት ኣንስተውት ጥለውት የነበረ ጥያቄ ቢሆንም ወያኔ ኣይታመንምና ይህን ብንገምት ኣይፈረድም። ሃያ ኣምስት ዓመት ሲዘርፉ ቆይተው ኣሁን የመገንጠል ነገር ቢያመጡ ፍጻሜው ምን ይሆናል? የሚለውን ጥያቄ እናዘግየውና እንደዚህ ሊያስቡ ስለሚችሉ ለዚህ ፍላጎታቸው የኦሮሞም ህዝብ ሆነ የኣማራ ወይም የደቡብ እንዲሁም ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመች ኣይሆንም። የኦሮሞ ጥያቄም ሆነ የሌላው ህዝብ ጥያቄ የለውጥ፣ የመልካም ኣስተዳደርና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ናቸው።

 

 

የለውጡ ጥያቄ ኢትዮጵያን እንደገና የማነጽ ስራ ነው። ኢትዮጵያን እንደገና ማነጽ ማለት እኛ በቋንቋ የተለያየን ቡድኖች ኣብረን ስንኖር የኣንድ ቡድን የበላይነት ሳይኖር እንዴት ኣብረን በእኩልነት እንኑር?  እንዴት ኣድርገን ያለንን ባህል በኣንድ በኩል ወደ ላይ እያሳደግን በሌላ በኩል ወደ ጎን እየተማማርን እንኑር?  የቋንቋ ሃብቶቻችንን እንዴት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንጠቀም? እንዴት ኣድርገን የተሻለ ብሄራዊ ማንነት እንገንባ? በኣካባቢያችን ያለውን የተፈጥሮ ሃብት እንዴት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንጠቀም? ፖለቲካዊ ኣሰላለፋችን እንዴት እናድርገው? በሚሉ ጉዳይች ዙሪያ የመግባቢያ ኣሳብ ማምጣትና በዚህ ስምምነት ላይ መተዳደር ማለት ነው መስማማት ማለት::  ኢትዮጵያን እንደገና ማነጽ ማለት ወደፊት ለቡድኖች ሁሉ እኩልነትን የሚያመጣ ኣሳብ ማመንጨትና በዚያ ላይ ኣቋም ይዞ ኣዲሲቷን ኢትዮጵያን መገንባት ነው። በመሆኑም የለውጡ ጥያቄ ሰፊ ነው። ኢትዮጵያውያን ለውጥ ሲያነሱ ኣገራቸውን ለማፍረስ ኣይደለም። ኢትዮጵያ ማለት ኦሮሞ ነው። ኦሮሞ ማለት ኢትዮጵያ ናት። የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ነው። ስለሆነም የኦሮሞን ጥያቄ እንደግፋለን። ለውጥ ይምጣና የተሻለ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ማእቀፍ ውስጥ እንግባ። ሁላችን የኦሮሞ ወንድሞቻችንን ጥያቄ ደግፈን ለመልካም ኣስተዳደርና ለዴሞክራሲ እንታገል። በትግላችን ላይም ሆነ በውጤቱ ላይ በኣንድም በሌላም መንገድ ለወያኔ መሰሪ ዓላማ እድል ፈንታ ኣንሰጥም።ኦሮሞው ኢትዮጵያዊ ያነሳውን የትግል ችቦ ሌላው

ኢትዮጵያዊም ተቀብሎ ያበራል!

 

 

እግዚኣብሄር ኢትዮጵያችንን ይባርክ

 

ገለታው ዘለቀ

geletawzeleke@gmail.com

The post ኦሮሞው ኢትዮጵያዊ ያነሳውን የትግል ችቦ ሌላው ኢትዮጵያዊም ተቀብሎ ያበራል! – ገለታው ዘለቀ appeared first on Zehabesha Amharic.

“በኦሮሚያ ክልል እየሞቱ ያሉት አማሮች ገዳይ ወያኔ ነው ፤ አማራው ከኦሮሞው ጋር መተባበር አለበት”–ከቤተ አማራ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ

0
0

bete amahara

ቁ፡ 1 12/14/2015

በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ከቤተ አማራ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ

የአማራ ህዝብ ጀግኖች አባቶቹና እናቶቹ ከሌሎች አገር ወዳድ ወገኖች ጋር በመሆን ከመሰረቷት ብሎም በተከታታይ የደም እና የአጥንት ዋጋ ከፍለው ጠብቀው ካቆዩአት የገዛ አገሩ ለዘመናት በተሸረበ ሴራ ወደ ጎን በሃይል ተግፍትሮ የዜግነት መብቱን ከተገፈፈና በተከታታይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ሰለባ ከሆነ እነሆ 25 አመት ሊሞላው ነው። እስካሁን የተደረገው ግፍ አልበቃ ብሎ የዘር ማጥፋቱ እርምጃ በተፋጠነ ሁኔታ ሌት እና ቀን እየተሰራበት ይገኛል። የዚህ እኩይ አላማ ጠንሳሽ እና አስፈጻሚ በዋነኝነት አሁን አገሪቱን በመምራት ላይ ያለው ህወሀት ሲሆን በሂደት የሴራው ተካፋይ የሆኑ ብዙ ጥቅመኛ ቡድኖች ከጎኑ እንደተሰለፉ የሚታወቅ ነው። በዚህም ምክንያት ንጹሃን የአማራ ልጆች በጅምላ ተጨፍጭፈዋል፤ ተፈናቅለዋል፤ አገር ጥለው ተሰደዋል፤ ሀብት ንብረታቸውን ተዘርፈዋል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ መሬታቸው በየጊዜው እየተቆረሰ ላጎራባች ክልሎች እና ለሱዳን እየታደለ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ አማራ በአሁኑ ሰአት እንደህዝብ ከፍተኛ የሆነ እና አሳሳቢ የህልውና አደጋ ተጋርጦበት ይገኛል፡፡ የቤተ አማራ ንቅናቄ (ቤአን) የአማራውን ሰፊ ህዝብ ከዚህ ለአመታት እየተፈጸመበት ካለው ግፍ እና ከተደገሰለት ዘር ማጥፋት ዘመቻ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መላው የአማራን ህዝብ በማንቀሳቀስ የሚገላገልበትን መንገድ በመሻት አበክሮ በመስራት ላይ ይገኛል። ስለሆነም የቤተ አማራ ንቅናቄ ማእከላዊ ኮሚቴ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በጥልቀት ከገመገመ በኋላ ይህንን ባለ አራት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡

የአማራን ህዝብ እና መሬትን በተመለከተ

ወያኔ ገና የስልጣን በትሩን በጨበጠ ማግስት የወልቃይት እና የራያን አማሮች አጥፍቶ በተረፉት ላይም በግድ እንግዳ ባህል ጭኖ ለም መሬቶችን ሲወር ተው ባይ አካል በማጣቱ ተሟሙቆ ቋራን እና አርማጭሆን ብሎም ሰፊውን እና ታሪካዊዉን ጎንደርን አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ በማይሞሉ ቅማንት ወገኖቻችን ስም አካሎ ቀስ ብሎም ወደ “ታላቋ ትግራይ”ለመጠቅለል ታላቅ ሴራ በመሸርብ ወንድማማች የሆነውን ህዝብ እያጫረሰ ይገኛል። በመቀጠልም አማራን አሳንሶ እና አደህይቶ ከጥቅም ውጭ ለማድረግ ታሪካዊና ለም የጎንደር መሬቱን ለሱዳን ለማስረከብ ጫፍ ላይ ደርሷል። በዚህ ጉዳይ ላይ የሰፊው አማራ አይኖች ጎንደር ላይ እንዲያተኩሩ ግድ የሚልበት ወቅት ላይ ነን፡፡ በጎጃም፤ በወሎ፤ በሸዋ፤ እንዲሁም በመላ ኢትዮጵያ እና በአለም ዙሪያ ያሉ አማሮች ጉዳዩን በአንክሮ እና በእልህ ሊመለከቱት ይገባል፡፡ ዝርፊያውን ለማክሸፍም የተቀናጀ ህዝባዊ እርምጃ ያስፈልጋል፡፡ ቤአን ይህን ትግል ለማስተባበር እና ግቡን እንዲመታ ለማድረግ ታከተኝ ሰለቸኝ ሳይል በሙሉ አቅሙ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን እየገለፀ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለ ማንኛውም አማራ ሁሉ የአያት ቅድመ አያቶቹን ወሰን ላለማስደፈር እንዲታገል ጥሪውን ያቀርባል፡፡
በጎንደር እየተፈጸመ ስላለው የህዝብ እልቂት በተመለከተ

ግፈኛው የወያኔ አገዛዝ በተለያዩ የኢትዮጵያ ቦታዎች ዜጎች ላይ አማራ በመሆናቸው ብቻ ተደጋጋሚ ጥቃትና የዘር ማጥፋት ሲያካሂድ መቆየቱ አለም ያወቀው ጸሃይ የሞቀው ሃቅ ነው፡፡ ለዚህም በመተከል አካባቢ የተፈጸመው ግፍ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ሲሆን በአሁኑ ስዓት ደግሞ በጎንደር ልዩ ልዩ ቦታዎች የአማራን ደም እያፈሰሰ ዘሩን በማጥፋት ላይ ይገኛል ። በተያያዘ መልኩ አማራና ቅማንት በሚል አንዱን ህዝብ ለሁለት ሰንጥቆ እርስ በእርስ እያጫረሰው መሆኑ የአማራን ህዝብ ሰቆቃ እጥፍ ድርብ አድርጎታል ፡፡ ከዛም አልፎ ከቀናት በፊት ወደር በሌለው ጭካኔ እስረኞችን በጎንደር በአታ ወህኒ ቤት እና አንገረብ ላይ በሰራው አዲስ ተጨማሪ ማጎሪያ በእሳት አቃጥሏል፡፡ እነዚህን እስረኞች ከውስጥ በእሳት ከውጭ በጥይት አረር ቆልቷቸዋል፡፡ ይህም በናዚ ዘመን ከተፈጸመው የሰው ዘር እልቂት የከፋ ዘግናኝ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ እንቅስቃሴን በተመለከተ

የቤተ አማራ ንቅናቄ (ቤአን) አሁን በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተፈጠረው ችግር ምንጭ የወያኔው መንግስት ገና በጫካ ውስጥ እያለ የተጠናወተው የመሬት ዝርፊያ እና ወረራ አባዜው ነው ብሎ ያምናል። የመሬት ዝረፊያና “ፖቴንሻል ትሬት” ቅነሳ ዋና ዓላማው የሆነበትም ምክንያት ካለበት የአናሳነት ስሜት በመነሳት ተቀናቃኞቹን በሃይል እና በኢኮኖሚ ለማዳከም ነው፡፡ እጁን የፈታውም የአማራውን መሬቶች በመውረር እንደሆነ ይታወቃል። ወልቃይትን፤ ራያን እና መተከልን ከአማራ ወስዶ በጎሳ ቡድንተኝነት ለተሰባሰቡ የግፍ አገዛዙ አባላት ማከፋፈሉ የሚታወስ ነው፡፡ ይህንን የመሬት ወረራ ጥሙን ለማርካት ሲል የአዲስ አበባ ከተማ ማስፋፊያ ማስተር ፕላን እያለ በዙርያው ያሉ የኦሮሞ አርሶ አደሮችን ሊያፈናቅል ሲንቀሳቀስ የተቃወመውን ህዝብ በህጋዊ መንገድ ማስተናገድ ሲገባው ከፍተኛ የህወሓት ወታደራዊ ሃይል በመጠቀሙ ሽብር ፈጥሮ የብዙ ሰዎችን ህይወት እያጠፋና ንብረት እያወደመ ይገኛል፡፡ በዚህ ሁኔታ ከልብ እያዘን ከዚሁ የአገዛዙ ሽብር ጋር ተያይዞ በኦሮሞ አካባቢ የሚኖሩት የአማሮች ደህንነት ጉዳይ እጅግ በጣም አሳስቦናል። የአማራ ደም ሲፈስ ካላየ የማይረካው ወያኔ አጋጣሚውን በመጠቀም እንደለመደው አማራን ራሱ እዬገደለ “ኦሮሞ ገደለ” በማለት ላይ ነው። በጥብቅ መታወቅ እና መሰመር ያለበት ትልቅ ጉዳይ ግን ደማቸው የሚፈሰው ወገኖቻችን የሚገደሉት በወያኔ ብቻ መሆኑ ነው። ወያኔ ራሱ ባይገድላቸው እንዲሁ በግርግር መሃል ቢሞቱ እንኳ ተገቢውን ጥበቃ ስላላደረገ ዜጎቻችንን ሊጠብቅ ባለመቻሉ ለሚችል ሌላ አካል በቶሎ ስልጣን ማስረከብ አለበት ብለን አስረግጠን እንናገራለን። መልካም አስተዳደር ቢቀር የንጹሃን ዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ያልቻለ አገዛዝ አንድም ቀን ስልጣን ላይ ማደር የለበትም። መንግስት ነኝ ብሎ የተቀመጠው ወያኔ እንጅ የኦሮሞ ተማሪዎች እና ገበሬወች ስላልሆኑ ለእያንዳንዷ የአማራ ህይዎት መጥፋት ተጠያቂው ራሱ ወያኔ መሆኑ በሁሉም ዘንድ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ ማንኛውም የአማራ ተወላጅም በኦሮሞ ምድር ደም የሚያፈሰው ራሱ ወያኔ መሆኑን አውቆ ባመቸው መንገድ እንዲታገል እና ገዳዮችን ጊዜው ሲደርስ ለፍርድ ለማቅረብ ያመች ዘንድ ማስረጃ የመሰብሰብ ስራ መስራት አለበት፡፡ አሁን ወያኔ “የአማራ ክልል” ብሎ ባጠረው ምድር የሚኖረው አማራም በኦሮሞ አካባቢ ግፍ እየተፈጸመባቸው ለሚገኙ ወገኖቹ የወንድማዊነት አለኝታነቱን ማሳዬት ይጠበቅበታል፡፡ የኦሮሞን ህዝብ ትግል የሚመሩ አካላትም የገዳይ ወያኔዎችን ማስረጃ በመሰብሰብ ለአማራ ወንድሞቻቸው በማስተላለፍ እንዲተባበሩ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ አጋጣሚም ቤአን በመላ አገሪቱ የሚኖር አማራ ሁሉ ደህንነቱን የሚጠብቅለት መንግስት እንደሌለው አውቆ ራሱን እያሰባሰበና እያደራጀ ራሱ በሚመርጠው የጎበዝ አለቃ እየተመራ የራሱን ጠባቂ ጊዜያዊ የራስ አድን ኃይል እንዲያቋቁም ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

ድርቅ እና ርሃቡን በተመለከተ

የወያኔው ገዥ ቡድን የጭካኔው መገለጫ ብዙ ነው። አሁን እጃችን ላይ ያለው ማስረጃ እንደሚያረጋግጠው ደግሞ ሕዝባችን እጂግ የከፋ የርሃብ አደጋ ውስጥ ነው። ከ 15 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ እና ከነዚህም ውስጥ ብዙዎች በሞት እያሸለቡ ፣ ባእዳን መንግስታት ሳይቀሩ እርዳታ ለማቅረብ እየተሯሯጡ ባለበት ሰአት የማስተር ፕላን ፖለቲካ፤ የሱዳን ድንበር ማካለልና፣ የቅማንት ማንነት እያለ ህዝቡን እርዳታ አልባ ሆኖ እንዲያልቅ እያደረገው ይገኛል ። በመሰረቱ እነዚህ ነገሮች ረሃብ እና ቸነፈር በሌለበት ብሎም ሰላም በሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ ዜጎች ከላይ እስከታች መክረው እና ዘክረው የሚወስኗቸው ሁኔታዎች ሆነው እያሉ ግፈኛው አገዛዝ ግን በማናለብኝነቱ ቀጠለበት፡፡ ቤአን የወያኔው ገዥ ቡድ ከሽብር ተግባሩ ባስቸኳይ ታቅቦ በረሃብ ሰበብ በሞት አፋፍ ላይ ላሉ አማሮች እና ሌሎች ህዝቦች ተገቢውን የምግብ እርዳታ በጊዜ ማድረስ ግዴታው መሆኑን ያሳስባል።

ድል ለአማራ ህዝብ!
ቤተ አማራ ወደፊት!

የቤተ አማራ ንቅናቄ (ቤአን)

The post “በኦሮሚያ ክልል እየሞቱ ያሉት አማሮች ገዳይ ወያኔ ነው ፤ አማራው ከኦሮሞው ጋር መተባበር አለበት” – ከቤተ አማራ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ appeared first on Zehabesha Amharic.

የፍትሕ ጥያቄ ክልል የለውም! |ያሬድ ኃይለማርያም

0
0

በኦሮሚያ ክልል በሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን የግፍ እርምጃ ከማውገዝ ባለፍ ለፍትሕና ለነጻነት የሚደረገው ትግል ኢትዮጵያዊ መልክ ይያዝ!

abebe Gelaw

ታህሳስ 15፣ 2015 እ.አ.አ

“Injustice anywhere is a threat to justice everywhere” Martin Luther King Jr.   

Yared

Yared

ላለፉት ሦስት ሳምንታት አወዛጋቢውን የአዲሰ አበባ ማስተር ፕላን እቅድና የትግበራ ዝግጅት በመቃወም በአገራችን የተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ውስጥ የተቀሰቀሰው የተማሪዎች ተቃውሞ እያደር ወደ ሕዝባዊ ቁጣና አመጽ እየተቀይረ መምጣቱን በግልጽ እየተመለከትን ነው፡፡ አድሮ ጥሬ የሆነው የወያኔ አገዛዝ ሥርዓትም የተነሱትን ጥያቄዎች በወቅቱና ስልጡን በሆነ መልኩ ከመፍታት ይልቅ ላለፉት 24 አመታት እንደሚያደርገው ሁሉ ዛሬም የኃይል እርምጃ በመውሰድ በአስሮች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል፣ በርካቶችን ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት አድርሶባቸዋል፣ ቀላል ግምት የማይሰጠው የህዝብ ንብረትም እየወደመ ይገኛል፡፡ የህዝባዊ ተቃውሞው መንስዔ ተማሪዎቹ ያነሱትና በተቀረው የኅብረተሰብ ክፍል ዘንድ ብዥታን የፈጠረው የአዲሰ አበባ ከተማ የማስፋፊያ እቅድ ቢሆንም እያደር ግን መልኩን ቀይሮ ሥርዓቱ ለበርካታ አመታት ሊመልሳቸው ያልቻሉና በመላ አገሪቱ የተንሰራፋውን አፈና እና መሰረታዊ የፍትሕ፣ የሰብአዊ መብቶችና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን የሚያንጸባርቅ እየሆነ ነው፡፡

ከቅርብ ቀናቶች ወዲህ እየታየ ያለው ሕዝባዊ ቁጣና ንቅናቄ በክልሉ ውስጥ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሁሉ እያካተተ መምጣቱን እያስተዋልን ነው፡፡ ከገበሬው አንሶቶ አዛውንቶች፣ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ መምህራንና በተለያዩ የስራ መስክ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ የትምህርት ተቋማትና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዚህ ተቃውሞ ውስጥ እየተሳተፉ መሆናቸውን እየተከታተል ነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ የወያኔ ሥርዓት ስልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ አንስቶ ሰፊ የሆነና ከሳምንታት በላይ የቆየ ሕዝባዊ ተቃውሞ ስመለከት ይህ ሦስተኛው ነው፡፡ የመጀመሪያው እጅግ ብዙ የተወራለትና በእንጭጩ የተጨናገፈው የግንቦት 1997 ዓ›ም› ምርጫን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ቁጣ ነው፡፡በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው ‘ድምጻችን ይሰማ’ በሚል ላለፉት ሶስት አመታት የታየው እጅግ ስልጡንና ሰላማዊ የሆነው የሙስሊሙ ማሕበረሰብ የመብት ጥያቄ ነው፡፡ እነዚህ እንቅስቃሴዎች ሥርዓቱን በተወሰነ ደረጃ ከማሸበርና እንቅልፍ ከመንሳት ባለፈ የማስገደድ አቅም ስላልነበራቸው ወያኔ የሚፈጽመውን የመብት ጥሰት፤ እስር፣ ድብደባ፣ ግድያና የሃሰት ውንጀላ አላስቆመውም፡፡ የሥርዓቱን ብልግና እና ጭካኔ ግን በደንብ ያጋለጡ ንቅናቄዎች ናቸው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችለው ሰፊ የሆነ ሕዝባዊ ንቅናቄ አሁን በመካሄድ ላይ ያለው የኦሮሞ ሕዝብ ቁጣ ነው፡፡

የ1997ቱ ሕዝባዊ ቁጣ በመላ አገሪቱ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያቀፈና ያለምንም የዘር፣ የኃይማኖት፣ የጽዎታና ሌሎች ልዩነቶችን መነሻ ሳያደረግ በፍትሕ፣ በነጻነትና በዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ዙሪያ ያተኮረ ሰፊ እንቅስቃሴ ነበር፡፡  ሁለተኛው ንቅናቄ መሰረቱ የመብትና የፍትሕ ጥያቄዎች ቢሆኑም አንድን የኃይማኖት ክፍል ‘እስልምናን’ ማዕከል ያደረገ ንቅናቄ ሆኖ ነው የቆየው፡፡ ይሁንና በውስጡ የዘር፣ የጽዎታና ሌሎች ልዩነቶችን አሸንፎ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ያቀፈ ነበር፡፡ አሁን እየተካሄደ ያለው የሕዝብ እንቅስቃሴ ደግሞ ምንም እንኳን የተወሰኑ የፖለቲካ ድርጅቶች አጋርነታቸውን እየገለፁ ቢሆንም አሁን ባለበት ደረጃ የኦሮሚኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነውን የኅብረተሰብ ክፍል ብቻ ማዕከል ያደረገ ሆኖ ነው የቀጠለው፡፡ እነዚህ ሁለት በኃማኖትና በጎሳ የተወሰኑት ሕዝባዊ የፍትሕና የነጻነት ጥያቄዎችና ንቅናቄዎች ለምን ወደ አገር አቀፍ ንቅናቄነት እንዳላደጉ ወይም የማደግ ምልክት እንዳላሳዩ፣ ለምንስ ቀሪው የኅብረተሰብ ክፍል ሌሎቹ ወገኖቹ የሚያነሱትን የመብት ጥያቄ በጥርጣሬና የጎሪጥ ከማየት ባለፍ አጋርነቱን በተግባር ሊገልጽ አልቻለም? ለምን ልብ ለልብ ተራራቅን? በዛች አገር ውስጥ ማን በፍትሕ እጦት እየማቀቀና እየተሰቃየ ማንስ ደልቶትና ተረጋግቶ በሰላም መኖር ይችላል? ይህ አይነቱ የሕዝብ ክፍፍልስ ከምን መነጨ? ማንንስ ነው እየጠቀመ ያለው? እንደ አንድ አገር ሕዝብ የአንዳችን ሕመም እንደምንስ ለሌሎቻችንን ላይሰማን ቻለ ወይም ለምን እንዳልተሰማን ለማስመሰል እንሞክራለን? ከተሰማንስ ምን አደረግን? ምንስ ማድርግ እንችል ነበር? የሚሉና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ጥያቄዎች ማንሳትና በግልጽ መወያየት፤ ለችግሮቹም የጋራ መፍትሄ ማፈላለግ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ቁጭ ብሎ በሰለጠነ መልኩና በቅን ልቦና መነጋገርና መደማመጥ ካቃተንና ይህን ማድረግ ተራራ የመግፋት ያህል ከብዶ ከተሰማን ከተጫነን የረዥም ጊዜ መከራ፣ ስቃይ፣ ድህነት፣ አፈና እና አንባገነናዊው ሥርዓት መቼና በምን ሁኔታ ልንገላገለ እንችላለን?

ለእነዚህ ችግሮች መንስዔዎች ናቸው ከምላቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ጥቂቶቹን ልጥቀስ፡-

  • ለሃያ አራት አመታት በወያኔና መሰል ድርጅቶች ሲዘራ የቆየው ዘርንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገው የጥላቻ ቅስቀሳና የቅራኔን መርዝ ሲረጭ የነበረው የዘር ፖለቲካ ፍሬ አፍርቶ በግላጭ መታየት ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ ለዚህም በየጊዜው በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የተከሰቱትንና አሁንም እየተከሰቱ ያሉት፤ የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፉ የጎሣና የኃይማኖት ግጭቶችን በዋነኝነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
  • በእረዥም ጊዜ ታሪካችን ውስጥ የተፈጸሙ ክስተቶችን፣ አስነዋሪ ተግባራትንና ቅራኔ ሊፈጥሩና ሊያስፋፉ የሚችሉ ግድፈቶችን መዞ በማውጣት እሱኑ እያጦዙና እያራገቡ የፖለቲካ ትርፋቸውን የሚያሰሉ፤ ወይም በታሪክ ሂደት ውስጥ በአንድ ወይም በሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ የተፈጸሙ በደሎችንና  የግፍ ተግባራትን እንዳልተፈጸሙ በመካድ ወይም የሌሎችን በደል ችላ በማለትና ተገቢውን እውቅና በመንሳት ቅራኔዎችን የሚያሰፉ ግለሰቦች፣ ምሁር ተብዮዎች እና የፖለቲካ ድርጅቶች የተጠመዱበትን እኩይ አስተሳሰብ በሕዝቡም ዘንድ እንዲሰርጽ በማድረግ ቂምና ጥላቻን ያረገዘና ለበቀል የተዘጋጀ የኅብረተሰብ ክፍል እንዲፈጠር መደረጉን ማስተዋል ይቻላል፡፡
  • በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃንና በተለያዩ የመረጃ መረቦችም ተደጋግመው የሚሰራጩት ጭፍን እና የጅምላ ፍረጃዎችም በህብረተሰቡ ውስጥ አንዱ ሌላውን እንዲጠራጠርና እንዲሰጋ በማድረግ ወያኔ በሕዝቡ አበሮነት ላይ የፈጠረውን ስንጥቅ እንዲሰፋና ገደል እንዲሆን አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥረዋል፡፡
  • በዘር መድሎና ክፍፍል ላይ የተመሰረተው የአገዛዝ ሥርዓቱ የሥልጣን መዋቅር በሃያዎቹ አመታት ውስጥ ያፈራቸው የዛሬዎቹ ወጣቶች፤ በከፍተኛ የትምርት ተቋማቶች ውስጥ ያሉትን እና ባለፉት አሥር አመታት ውስጥ ተመርቀው በሥራ ገበታ ላይ የሚገኙትን አምራች ኃይሎች የዘር ፖለቲካው ሰለባዎች ለመሆናቸው የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለውን ድባብ ጠጋ ብሎ ማየት በቂ ነው፡፡ እነዛ ማንኛውም አገራዊ ጉዳይ ያገባኛል በሚሉና በኢትዮጵያዊነት ስሜት ያለምንም የዘር ልዩነት በጋራ ድምጻቸውን በሚያሰሙ ተማሪዎች ይናወጡ የነበሩት የትምርት ተቋማት ዛሬ በጎሣና በጎጥ ተቧድነው እርስ በእርሳቸው በሚቧቀሱና በሚወነጃጀሉ ተማሪዎች ተሞልተዋል፡፡ በአንድ የትምህርተ ተቋም ውስጥ፤ ከዛም አልፎ በአንድ ክፍል ውስጥ አብረው የሚያድሩና በአንድ ክፍል ቁጭ ብለው የሚማሩ ተማሪዎች እርስ በርስ እየተፈራሩ፤ ነገር ግን በቋንቋ ብቻ ከሚመሳሰላቸው ጋር ተቧድነው እርስ በርስ ሲደባደቡና የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሌላውን ሲያጠቁና ሲያገሉ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህ ትልቅ አገራዊ ኪሳራ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ በአንቦና በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተከሰቱት የእርስ በርስ ግጭቶች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ይህም የተቋሞቹን መክሸፍ ብቻ ሳይሆን የሚያሳየው እነዚህ ወጣት ተማሪዎች የነገዋ ኢትዮጵያ ተረካቢዎች እንደመሆናቸው መጠን ወያኔ የዛሬዋን ብቻ ሳይሆን የነገዋንም ኢትዮጵያን ለማክሸፍና ለማጨለም ተግቶ እየሰራ መሆኑን ነው የሚያሳየው፡፡

ወደ ተነሳሁበት ዋና ነጥብ ልመለስና ወያኔ ሥልጣን ከያዘ ወዲህ በቅርብ ጊዜ ከታዩት ሦስት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች መካከል የመጨረሻዎቹ ሁለቱ፤ ማለትም ‘ድምጻችን ይሰማ!’ በሚል መሪ መፈክር የተካሄደው የሙስሊሙ ማህበረሰብ ተቃዉሞና አሁን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰው የሕዝብ ቁጣና ንቅናቄዎች በግልጽ የሚያሳዩት በትምህርት ተቋማት ውስጥ ተወስኖ የቆየውና ስር የሰደደው የእርስ በእርስ መፈራራትና የክፍፍል ወረርሽኝ በሕዝብም ውስጥ ሰርጾ መግባቱን ነው የሚያመላክቱት፡፡

የሙስሊሙ ማኅበረሰብ መሰረታዊ የመብትና የነጻነት ጥያቄዎቹን በማንሳቱ ምክንያት መሪዎቹ ሲታሰሩበት፣ አባላቶቹ በገፍ ሲታሰሩ፣ ሲደበደቡና የስቃይ ሰለባ ሲሆኑ ከጥቂት አርቆ አሳቢና አስተዋይ የሆኑ የሌላ እምነት ተከታይ ግለሰቦችና በውጭ የሚኖሩ ጥቂት የኃይማኖት አባቶች በስተቀር በተቋም ደረጃም ሆነ በግል ተሰባስበውም በእነዚህ ወገኖች ላይ የደረሰውን የመብት ጥሰት የተቃወሙ፣ ያወገዙና  ያነሱትም መሰረታዊ የሆኑ የመብት ጥያቄዎች በጡንቻ ሳይሆን በሕግ አግባብ ሊመለስላቸው ይገባል ብለው ለፍትሕ ሲባል ከጎናቸው የቆሙ ወይም ድምጻቸውን ያሰሙ የሌላ ኃይማኖታዊ ተቋማቶች አላየሁም፡፡ ከዚያ ይልቅ በወያኔ ሚዲያዎች የሚሰራጩትን ፕሮፓጋንዳዎችና ቅስቀሳዎች፤ እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚዎች በአክራሪዎች የተሰነዘሩ ጥቃቶችን እያጣቀሱ የአገዛዙን የአፈና እርምጃ ተገቢነት አፋቸውን ሞልተው ይደግፉ የነበሩ ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ይህን በግልጽ ማስቀመጥ የሚያስፈልገው ሕዝብን ለማቃረን ሳይሆን የገባንበትን አዘቅት በቅጡ እንድናየው ለማሳሰብ ነው፡፡ እንዳበደ ውሻ ያገኘውን ሁሉ የሚናከሰው ወያኔ ብዙም ሳይቆይ የዋልድባን ገዳም ሲያተራምስና መነኮሳትን ሲያስር፣ ሲያዋርድና ሲደበድብ ከጥቂት እንዲሁ ለህሊናቸው ያደሩ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ አባላት በቀር በአብዛኛው የሙስሊሙና የሌላው እምነት ተከታይ ዘንድ የነበረው ምላሽ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ለነገሩ የወያኔ የዘር ፖለቲካ በደንብ ስር ሰዶ የተንሰራፋባትና የደቆሳት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አማኞችም ሳይቀሩ በዋልድባ ገዳም ለተፈጸመውም ሆነ በአዲሰ አበባ የጳጳሳቱ መኖሪያ ቤቶች በሌሊት በጠገቡ ጎረምሳ ደህንነቶች እየተሰበረ ሲደበደቡና ሲዋረዱ ድምጹን ያሰማ አልነበረም፡፡ የፍርሃት ቆፈኑና ጥበቱ የእምነት ተቋማትንም ሳይቀር ያደቀቃቸው መሆኑን እነዚህ የአደባባይ ኩነቶች በደንብ ያሳያሉ፡፡ በዚህ እረገድ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ በኩል የሚታየው ዘርና ቋንቋ የተሸገረው አብሮነት ያዝልቀው እንጂ በጥሩ ምሳሌነት ሲወሳ የሚኖር ነው፡፡

ሲፊዋን አገራቸውን ኢትዮጵያን እንዲረሱ ተደርገውና የተወለዱበትን ክልል ወይም የመጡበትን ጎጥ ወይም የዘር ምንጫቸው የሚገኝበትን ስፍራ ወይም በቋንቋ አሰፋፈራቸው የተካለለውን ሥፍራ ብቻ አገራቸው አድርገው እንዲያስቡና በዚህም ተወስነው ሌላውን ክፍል ባዳ ወይም ጠላት አድርገው እንዲያስቡ ተደርጎ ጭንቅላታቸው የተቀረጸው የዛሬዎቹ ወጣቶችና ‘የከፍተኛ’ ተቋማት ተማሪዎች የሚያነሱዋቸው የመብትም ሆነ ሌሎች ጥያቄዎች የመንደር ወንዝ የማይሻገሩ፣ ከቀበሌኛነት ያልዘለሉ ወይም በጎሣ፣ በሚናገሩት ቋንቋ ወይም በሚወግኑት ኃይማኖት ዙሪያ የታጠሩና የተወሰኑ መሆናቸው የሚያስገርም አይደለም፡፡ እነዚህን የመብት ጥያቄዎች ማንሳቱ ተገቢ መሆኑ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ መብትም ነው፡፡ ይሁንና ሁሉም እሱ ከመጣበት ክልል ወይም የዘር መስመር ውጪ ባለችዋ ኢትዮጵያና ሕዝብ ላይ የሚፈጸሙ በደሎች፣ የመብት ጥሰቶች፣ አገራዊ ጉዳዮችና ሌሎች ችግሮች አይመለከቱኝም ብሎ አይኑን ከጨፈነ እና ጆሮውን ከደፈነ፤ እሱም ሲጠቃና ሲበደል የሌላው አካባቢ ተወላጅ ይህንኑ አይነት ስሜት ካንጸባረቀ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እያከተመላቸው ነው ማለት ነው፡፡

የአፋር አርብቶ አደር ከቅዮው ሲሳደድና በታጣቂዎች ሲዋከብ፣ የኦጋዴን ሕዝብ በርሃብና በጥይት ሲቆላ፣ የጋንቤላ ገበሬ ከአካባቢው እየተፈናቀለ መሬቱ ለውጪ ቱጃሮች ተቸብችቦ በየጫካው ሲበተንና ሲሰቃይ፣ የአማራ ገበሬ ለዘመናት ያፈራውን ቅሪቱን ተዘርፎና ንብረቱ በእሳት ጋይቶ ለዘመናት ከኖረበት ስፍራና  ካለመው መሬት ላይ ቁራጭ ጨርቁን እንዳጣፋ አገር አይደለም እየተባለ ሲሳደድና ሚስትና ሴት ለጆቹ አይኑ እያየ ሲደፈሩበት፣ የትግራይ ገበሬ ስርአቱን ካልደገፍክ እየተባለ ሲዋከብ፣ የእርዳታ እህል ሲነፈግና በስሙ እየተነገደበት እሱ ግን ሚስትና ልጆቹን ይዞ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ፈሶ ለልመና ሲዳረግ፣ የኦሮሞ ገበሬዎች ለም መሬታቸውን እየተነጠቁ ለዘመኑ ከበርቴዎችና ለውጭ ባለሃብቶች እየተቸበቸበ እነሱ ከነቤተሰቦቻቸው የነጣቂዎቹ አገልጋይ እንዲሆኑ ለባርነት ሲገፉ፣ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ግፉዋን ላይ የሚፈጸሙ በደሎች የማይቆረቁሩት፣ እንቅልፍ የማይነሱት ትውልድና የህብረተሰብ ክፍል ሊፈጠር የሚችለው ከላይ በጠቀስኳቸው ችግሮች ነው፡፡

ዛሬ የኦሮሞ ተማሪዎች በየትምህርት ተቋማቱና በዝቅተኛ የትምህርት ደረጃዎች ሳይቀር ይመለከተናል ባሉት ጉዳይ ላይ ወደ አደባባይ ብቻቸውን የወጡት፤ ከዛም አልፎ ጠግቦ ባላደረ አንጀታቸው በሥርዓቱ ቅልብ ታጣቂዎች ሲደበደቡ፣ ሲታሰሩ፣ ሲሰቃዩና በግፍ በየአደባባዩ ሲገደሉ የሌላው ኢትዮጵያዊ ዝምታ የገባንበትን አዘቅት አመላካች ነው፡፡ ይህ በህዝብ መካከል ለክፉ ቀን እንኳን አብሮ በአጋርነት የመቆምና አንዱ ለአንዱ ደጀን የመሆን የቆየ ባህልና ማህበራዊ ትስስር ተቦርቡሮ ተቦርቡሮ ሊበጠስ አንድ ሃሙስ የቀረው በሚመስል ደረጃ ላይ መገኘቱ አሳሳቢ ነው፡፡ ይሁንና እስካሁን የኢትዮጵያን ሕዝብ አስተሳስረው የሚገኙት በርካታና ደንዳና ክሮች አሁንም እንዳያያዙን ስላሉ እነሱን ማጥበቅ የግድ ይላል፡፡ ለዚህም የሙስሊሙ ሕብረተሰብ ትስስርና አብሮነት ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ‘በድመጻችን ይሰማ’ ትግል ውስጥ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጎራጌ፣ ትግሬ፣ ከንባታ፣ ሃድያ፣ ወዘተ… ሳይል ሁሉም የእስልምና እምነት ተከታዮች በአንድ ላይ እየተሳሰቡና እየተደጋገፉ ለዲናቸው ሲቆሙ አይተናል፡፡

ይህን ሕዝብን አስተሳስረው የያዙ ክሮችን ለማሳሳት ወይም ለመበጣጠስ የሚተጋው ታዲያ ወያኔ ብቻ አይደለም፡፡ በያደባባዩ እራሳቸውን የሕዝብ ተወካይ አድርገው በማቅረብ የቅራኔን መርዝ የሚተፉ የፖለቲካ ድርጅቶችና አንዳንድ ስክነት የራቃቸው ግለሰቦችም የሚጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም፡፡ እነዚህ ኃይሎች በሕዝቡ መካከል ያሉ ጥቃቅን ልዩነቶችን የፖለቲካ ግብ ማሳለጫቸው እያደረጉ ታሪካዊ ትስስር ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች እያናቆሩ ዝናን ሊያተርፉና ድጋፍ ሊያሰባስቡ ሲጥሩ የሚታዩ ግለሰቦችን ሕዝቡ ሊገስጻቻው ይገባል፡፡ ሥልጡን ሕዝብ ካሳለፈው መጥፎም ይሁን ጥሩ የታሪክ ሂደት ውስጥ ለዛሬ ሕይወቱ የሚጠቅሙትን ነገሮች በይቅርታ መንፈስ፣ በእውቀትና በሳይንሳዊ ምርምሮች ተደግፎ እያነጸ የአብሮነት ጉዞውን እጅ ለእጅ ተያይዞ ያሰምራል፡፡ በእኩልነት መንፈስም አንገቱን ቀና አድርጎ ብሩህ የሆነ ነገን ያልማል እንጂ ከመቶ አመት በፊት የነበሩ የታሪክ ግድፈቶችን እየመዘዘ የዛሬና የነገውን ትውልድ የአብሮነት ተስፋ አያጨልምም፡፡ በመካከላችን የተፈጠሩት ገደሎች እርስ በእርስ እንዳንደማመጥና ተደጋግፈን እንዳንቆም፤ በተናጠል በሚያጠቃን ሥርዓትም ዘንድ ኮስሰን እንድንታይ እያደረገን ነውና ገደሉን ልናጠበው ይገባል፡፡ የፍትሕ ጥያቄ ዘር፣ ቀለም፣ ጾታ፣ ኃይማኖት ወይም ክልል አይገድቡትም፡፡ በማንም ሰው ላይ ይሁን በየትም ስፍራ የሚፈጽም ግፍና የፍትሕ መታጣት ሌላውን የሰው ዘር ሁሉ ሊቆረቁረውና እንቅልፍ ሊነሳው ይገባል፡፡ ለዛም ነው በአፓርታይድ ዘመን መላው አለም ከደቡብ አፍሪቃ ጥቁሮች ጎን ቆሞ ለፍትሕና ለሰው ልጆች እኩልነት የታገለው፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋውን የአንባገነናዊ ሥርዓቶች አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታሪክ አድርገን ለማስቀረት፡-

  • ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በየጊዜው የሚነሱ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችንና ቁጣዎችን በሰከነ መልኩ እየመዘነ ብሔራዊ ነጻነትን ሊያጎናጽፈን ወደሚችልበት አቅጣጫ እንዲያመራ የበኩላችንን ጥረት ሊያደርግ ይገባል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ‘እኔ’ ብለን ካጠርነው ጠባብ ምልከታ ውስጥ አራሳችንን አውጥተን ለፍትሕና ለነጻነት የሚደረጉ ሕዝባዊ እምቢተኝነቶችን ስንደግፍና አጋር ስንሆን ነው፡፡
  • ከላይ በዝርዘር ያነሳዋቸውን በሕዝቡ መካከል የተፈጠሩ ክፍፍሎች፣ ቅራኔዎችና እርስ በእርስ የመፈራራት ስሜቶች ለማጥፋትና ትግሉን በአገር ደረጃ ለመምራት የሚያስችል የድርጊት ግብረ ኃይል ለማቋቋም የሚያስችሉ የውይይት መድረኮችም በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በተደራጁ የህብረተሰብ ክፍሎች በኩሉ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
  • በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተጀመረው ሕዝባዊ ቁጣ ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ የሶስት እዮሽ ግጭት እንዳይሆን፤ ማለትም በመንግስትና በሕዝብ፤ እንዲሁም በሕዝቦች መካከል ተደጋግመው የተከሰቱትን አይነት ቅራኔዎችና የጎሳ ግጭቶች እንዳያስከትል ጉዳዮ የሚመለከታችው አካላት ሁሉ ከወዲሁ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡
  • በውጭ የምንገኝ ኢትዮጵያንም በወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለው የመብት ጥሰት፣ ግድያና አፈና ለመቃወምና ትግሉንም አገራዊ አቅጣጫ ለማዝያዝ የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይገባናል፡፡
  • ለበርካታ አመታት ይህን አይነት ሕዝባዊ ንቅናቄ የሚፈጠርበትን አንዳች ተአምር ወይም አጋጣሚ አድፍጠው ሲጠባበቁ የቆዩና ሕዝብ በራሱ ተነሳሽነት የጀመራቸውን ንቅናቄ በመጥለፍና አቅጣጫ በማሳት ለከፋፋይና ጠባብ ለሆነው የፖለቲካ አጀንዳቸው ማሳኪያነት ሊያውሉት የሚፈልጉ፤ እንዲሁም አገርንና ሕዝብን ለዳግም ደም አፋሳሽ እልቂት ሊዳርጉ ወደሚችሉ አቅጣጫዎች ትግሉን ሊገፉት የሚፈልጉ ኃይሎችን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የወያኔ አንድ አካል አድርጎ በመቁጠር ሊታገላቸውና ሊያስቆማቸው ይገባል፡፡

ባለፉት ሳምንታት በኦሮሚያ ክልልና በጎንደር በተቀሰቀሱት ግጭቶች ለተገደሉ ወገኖቻችን ቤተሰቦች ሁሉ መጽናናትን እመኛለሁ፡፡

ፍትህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

ያሬድ ኃይለማርያም                               https://humanrightsinethiopia.wordpress.com/

ከብራስልስ

The post የፍትሕ ጥያቄ ክልል የለውም! | ያሬድ ኃይለማርያም appeared first on Zehabesha Amharic.

መድረክ ባለ 6 ነጥብ መግለጫ አወጣ |“ሕዝቡ በጉልበትና በማጭበርበር የተቀማውን መብት ለማስመለስ በሰላማዊ መንገድ ይታገል”

0
0

Merera and Beyene

የሕዝቦችን ሕገመንግሥታዊ መብቶች በመጣስ የሚከናወኑ የኢህአዴግ ሕገወጥ እርምጃዎች ሕዝባችንን ለከፍተኛ ችግር፣ ሀገራችንንም ለአሳሳቢ ሁኔታ እየዳረጉ ስለሆነ በአስቸኳይ ሊቆሙ ይገባል!!
(ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የተሰጠ መግለጫ)
የኢህአዴግ አገዛዝ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በተግባር ሊያውላቸው ያልተዘጋጀባቸውን ድንጋጌዎች ከሀገሪቱ ሕገመንግሥት ጀምሮ ሲያውጅ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ያወጃቸውን ድንጋጌዎች በማፍረስና በተግባር እንዳይውሉ በማድረግ የዜጎችንና የሕዝቡን መብቶች የሚጥሱ ተግባራትን እየፈጸመ ይገኛል፡፡ ይህ ሁኔታ ከአንድ የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነት በጉልበትና በማጭበርበር ቀምቶ መንግሥት ነኝ ከሚል አምባገነን ቡድን የሚጠበቅ ቢሆንም፣ መዘዙ የሀገራችንን ደህንነትና የሕዝቦቻችንን እኩልነትና አንድነት ለማይሹ ኃይሎች አፍራሽ እንቅስቃሴ ቀዳዳ እየሰጣቸው መሆኑ መድረክን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡
ከእነዚህ ሕገመንገሥታዊ ድንጋጌዎች ጥሰት መነሻነት ከተፈጠሩት ውስብስብ ችግሮች ውስጥ አንዱ የአዲስ አበባ ከተማንና የኦሮሚያን ክልላዊ መንግሥት ግንኙነት በሚመለከት፣ በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 “የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል” የሚለውን በማንአለብኝነት ከመጣስ የመነጨ ችግር ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢህአዴግ ሥርዓተ-አልበኝነት መገለጫ ሆኖ የቆየው በሕገመንግሥቱ የሰፈረው ዝርዝር የአፈጻጸም ሕግ ሳይወጣ ከ21 ዓመታት በላይ መቆየቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ እንዲሁም በአዲስ አበባ አከበቢ የሚሠሩ የልማት ሥራዎችንም በሚመለከት ሕዝቡን በአግባቡ ሳያወያዩ ጥቂት እበላ ባይ ካድሬዎችን በአስፈጻሚነት በማሰማራት የእርሻ መሬታቸውን እየነጠቁ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የማካለል እንቅስቃሴ ላይ መሠማራቱ በተከታታይ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችንና ውዝግቦችን ከማስነሳቱም በላይ ለብዙ ዜጎች ሕይወት በኢህአዴግ መንግሥት አርመኔአዊ እርምጃ መቀጠፍ ምክንያት ሆኖአል፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንታት የአዲስ አበባ ከተማን ከሕግ አግባብ ውጪ ማማስፋት ጋር በተያያዘ በሕዝቡ ዘንድ ካደረው ስጋት በመነሳት የተቀሰቀሰውን ሰላማዊ ሕዝባዊ ተቃውሞን በኃይል ለማስቆም የኢህአዴግ መንግሥት በወሰደው እርምጃም በርካታ ተማሪዎችና ሌሎች ዜጎች መገደላቸውን መድረክ በእጀጉ ይኮንነዋል፡፡

የተገደሉት ዜጎችም

1ኛ፡- ተማሪ ካረሳ ጫላ ምዕራብ ወለጋ ጉልሶ ወረዳ፣

2ኛ፡- ተማሪ ጉቱ አበራ ምዕራብ ወለጋ ጉልሶ ወረዳ፣ 3ኛ፡- ተማሪ ሚፍታህ ጁንዲ በምዕራብ ሐረርጌ በደኖ ወረዳ፣

4ኛ፡- ተማሪ ገዘሃኝ ኦልሂቃ የሀራማያ ዩንቨርሲቲ ተማሪ፣

5ኛ፡- ተማሪ ደጀኔ ሰርቤሳ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ቶሌ ወረዳ፣

6ኛ፡- ተማሪ በቀለ ሰቦቃ አዳበርጋ ወረዳ ሙገር፣

7ኛ፡- ተማሪ በቀለ ሰይፉ አዳበርጋ ወረዳ ሙገር፣

8ኛ፡- ተማሪ ሙራዲ አብዱ የሀራማያ 2ኛ ደረጃ ተማሪ፣

9ኛ፡- አቶ ጫላ ተሾሜ ምዕራብ ሸዋ ጨለያ ወረዳ ባቢቻ ከተማ፣

10ኛ፡- ተማሪ አብደታ ባይሳ ምዕራብ ሸዋ ጫለያ ወረዳ ባብቻ ከተማ፣

11ኛ፡- ተማሪ ዱሌ ምዕራብ ሸዋ ጨለያ ወረዳ ጌዶ ከተማ፣

12ኛ፡- አቶ ታመነ ጸጋዬ ምዕራብ ሸዋ ጨለያ ወረዳ ጌዶ ከተማ፣

13ኛ፡-ተማሪ ደረጀ ጋዲሰ ምዕራብ ሸዋ ጨለያ ወረዳ ጌዶ ከተማ፣

14ኛ፡- ተማሪ ፈቃዱ ግርማ ምዕራብ ሸዋ ጨለያ ወረዳ ጌዶ ከተማ፣

15ኛ፡-ተማሪ ሉጫ ገማቹ ምዕራብ ወለጋ ኢናንጎ ወረዳ፣

16ኛ ተማሪ አያና ባንቲ ምዕራብ ወለጋ ኢናንጎ ወረዳ፣

17ኛ፡- ተማሪ አላዛር ምዕራብ ወለጋ ኢናንጎ ወረዳ ነዋሪ

18ኛ አቶ ኤብሰ ቱጆ ሆሮ ጉዱሩ ፍንጫ፣

19ኛ፡- አቶ ደበላ ጣፋ ጫንጮ ላይ ተገድሎ ተጥሎ የተገኘ፣

20ኛ ወ/ሮ ዲሶ ሚሊኬሳ ሕልፈታ ወረዳ

21ኛ፡- አቶ አበበ ቡሎ ወሊሶ ከተማ፣

22ኛ፡- አቶ ታዴ ሰፈራ አመያ ከተማ፣

23ኛ፡- አቶ ሌንጮ ሁንዴራ ወሊሶ ከተማ፣

24ኛ፡- አቶ ሰለሞን ሞገስ አማያ ከተማ፣

25ኛ፡- አቶ ታዴ አንዲሳ ወንጪ ከተማ፣

26ኛ፡- አቶ እናውጋው ኃይሉ ግንደበረት ወረዳ፣

27ኛ፡- ተማሪ አብደታ ለታ ግንደበረት ወረዳ

28ኛ፡-አቶ ባይኢሳ ገደፋ አቡና ግንደበረት

ወረዳ 29ኛ፡- ተማሪ አስቻለው ወርቁ ግንጪ ወረዳ፣

30ኛ፡- ተማሪ ሰይፉ ቱራ ግንጪ ወረዳ፣

31ኛ፡- ተማሪ አሸናፊ ግንጪ ወረዳ፣

32ኛ፡- አቶ ገላና ባቃና ጪቱ ከተማ ነዋሪ የነበሩ ስለመሆናቸው የደረሱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ከዚህም ሌላ ከመቶ ባለይ ዜጎች ቆስለዋል፣ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለእስራት ተዳርገዋል፡፡ ሰላማዊና ሕጋዊ ተቃውሞን ለማፈን በመንግሥት እየተወሰደ ያለው የኃይል እርምጃ እስከ አሁንም እንደቀጠለ በመሆኑ፣ በዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት መድረክን በእጅጉ እያሳሰበው ይገኛል፡፡ እንደዚሁም በቅርቡ በጎንደር ከተማ በሚገኘው ወሕኒ ቤት በእስረኞች ላይ የተፈጸመው ግዲያ መድረክን አሳስቦታል፡፡
ከዚህም ሌላ በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ “የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነፃ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ ነው” የሚለውንና በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 5 የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ለግጦሽም ሆነ ለእርሻ የሚጠቀሙበት መሬት በነፃ የማግኘት፣ የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብት አላቸው” ተብሎ የተደነገገውን በመተላለፍ፣ በከተሞችና በእንቨስትመንት ማስፋፋት ስም የአርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን መሬት እየቀሙ በማፈናቀል ለከፍተኛ የኑሮ ችግሮች እየዳረጉዋቸው ይገኛሉ፡፡ መድረክ ይህንን የኢህአዴግ መንግሥት የመሬት ቅሚያ እርምጃ ደጋግሞ ሲያጋልጥ የቆየ ሲሆን በእርምጃው ምክንያት በሕዝቡ ላይ እያደረሰ ያለው የጉዳት መጠን ከጊዜ ወደጊዜ በአሁኑ ወቅት እየሰፋ ስለመገኘቱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፤
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገዛዙ በርካታ የሀገሪቱን ከተሞች ለማስፋፋትና መሬቱንም በፌዴራል መንግሥት ቁጥጥር ሥር በመሬት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ለማስተዳደር፣ የማስተር ፕላንና የሪፎርም ከተሞች ብሎ በመሰየም፣ በየከተሞቹ አከባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ይዞታዎች አርሶ አደሩን ሳያማክሩና ተገቢውን ካሳ ሳይከፍሉ ወደ ከተማ ለማካለል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ነዋሪውን ሕዝብ ለከፍተኛ ስጋትና ጭንቀት እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡ ስለሆነም የኢህአዴግ አገዛዝ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ በማንአለብኝነት አምባገነናዊ ስሜት እየተመራ ፌዴራላዊ ሥርዓቱንና የዜጎችን ሕገመንግሥታዊ መብቶች በመጣስ እየፈጸመ ከሚገኘው ሕገወጥ ተግባር እንዲቆጠብ እንጠይቃለን፡፡ በተለይም፡-
1ኛ፡- ከአዲስ አበባ ከተማና ከኦሮሚያ ክልል ግንኙነት ጋር በተያያዘ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች ሕገመንግሥቱን ተግባራዊ ባለማድረግ ምክንያት እየተከሰቱ ስለሆኑ የሕገመንግሥቱን አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 ተግባራዊ የሚያድርግ ሕግ በአስቸኳይ ወጥቶ ተግባራዊ እንዲደረግና ለችግሩ ዘላቂ እልባት እንዲሰጥ፣ ለከተማዋ ልማት የሚወጡ እቅዶችም የሕገመንገሥቱን ድንጋጌ የሚያከብሩ ሆነው የአከባቢውን አርሶ አደሮች መብትና ጥቅም በሚገባ የሚያስጠብቅ እንዲሆኑ፣
2ኛ፡- በቅርቡም መንግሥት ሕገወጥ እርምጃ ለመውሰድ በተንቀሳቀሰበት ምክንያት በኦሮሚያ ክልል ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎችን ባደረጉና በሌሎችም ሰላማዊ ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው የኃይል እርምጃ በአስቸኳይ እንዲቆም፣
3ኛ፡- እስከአሁን የዜጎችን ሕይወት በሕገወጥነት ያጠፉና ሌሎች ጉዳቶችን ያደረሱ የመንግሥት አካላትም ለሕግ እንዲቀርቡና ለሟቾቹ ቤተሰቦችም ተገቢው ካሳ እነዲከፈላቸው እንዲደረግ፣

4ኛ፡- በመላ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ሕገመንግሥቱ ያረጋገጠላቸው ከመሬታቸው የያለመፈናቀል መብታቸው ተከብሮ፣ በየአከባቢያቸው በልማት ሥራዎች ሰበብ ኑሮአቸው እየተናጋ ለችግር የሚዳረጉበት ሁኔታ በአስቸኳይ ተወግዶ፣ የሚከናወኑት የልማት ሥራዎችም ቢሆኑ የአከባቢውን ሕዝብ ይሁንታ ያገኘና መብታቸውን የጠበቀ እንዲሆን እንዲደረግ፤

5ኛ፡- በተለይም በአሁኑ ወቅት ከተሞችን በማስፋፋት ስም የአርሶ አደሩን መሬቶች ወደ ከተማ ለማካለልና በከፍተኛ ዋጋ በሊዝ ለመሸጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ፣ አርሶ አደሩን በስጋት ውስጥ እየከተተው ስለሚገኝ፣ ኑሮአቸውን ለማሻሻል የሚበቃ በቂ ካሳ ሳይከፈል ይዞታቸውን ለመንጠቅ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲቆም እንዲደረግ፣

6ኛ፡- በቅርቡ በጎንደር ከተማ በሚገኘው ወሕኒ ቤት የተገደሉ በርካታ ዜጎች ጉዳይ በአስቸኳይ ተጣርቶ የሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት ያጠፉና ጉዳት ያደረሱ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡና ለሟቾቹ ቤተሰቦችም ተገቢው ካሳ እንዲከፈላቸው እንዲደረግ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
በመጨረሻም መድረክ በንጽሐን ዜጎቻችን ላይ በኢህአዴግ መንግሥት የተወሰደውንና እየተወሰደ ያለውን ኢሰብአዊ ግዲያ በጥበቅ እያወገዘ ለሟቾቹ ቤተሰቦች መጽናናትን ይመኛል፡፡ መላው ሕዝባችንም በኢህአዴግ በጉልበትና በማጭበርበር በተካሄዱት ምርጫዎች የተቀማውን ሕገመንግሥታዊ መብቶቹን ለማስከበር ሰላማዊ ትግሉን እንዲያጠናክር የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ጥሪ ያቀርባል፡፡
ድል ለሕዝባዊ ትግላችን !!
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ
ታህሳስ 5 ቀን 2008 ዓ ም
አዲስ አበባ

The post መድረክ ባለ 6 ነጥብ መግለጫ አወጣ | “ሕዝቡ በጉልበትና በማጭበርበር የተቀማውን መብት ለማስመለስ በሰላማዊ መንገድ ይታገል” appeared first on Zehabesha Amharic.

ሀሮማያ እና አወዳይ ከተማው በሕዝቡ ቁጥጥር ስር ውሏል |በሁለቱ ከተሞች 6 ሰዎች መሞታቸው ተዘገበ |ቪዲዮም ይዘናል

0
0


(ዘ-ሐበሻ) በሃሮማያ እና በአወዳይ ከተማ ዛሬ ቀጥሎ የዋለው የሕዝብ ቁጣ ከተማዋን መንገዶች እስከመዘጋጋት መድረሱ ተሰማ:: እንደ ዘ-ሐበሻ የዜና ምንጮች ዘገባ ሕዝቡ በተለይ በምስራቅ ሃረረጌ አወዳይ ከተማን ተቆጣጥሮ አደባባይ ወጥቷል::

በሁለቱ ከተሞች የፌደራል ፖሊስ በሕዝብ ላይ ባደረሰው ጥቃት 6 ሰዎች መሞታቸው ሲዘገብ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ከፍ እንደሚል እየተገመተ ነው::

harerege harerge

በሃሮማያ እና በአወዳይ እንደአዲስ በአገረሸው የሕዝብ ተቃውሞ; ሕዝቡ ወደከተማው የሚገቡና የሚወጡ መንገዶችን በተለይም ከሃረር እስከ ደንገጎ ያለውን መዝጋቱ ተሰምቷል:: በዚህ መንገድ የሚያልፉ መኪኖች መንገድ ስለተዘጋባቸው ወደ ጂጂጋ እና ድሬደዋ ለመመለስ መገደዳቸው ተዘግቧል::

The post ሀሮማያ እና አወዳይ ከተማው በሕዝቡ ቁጥጥር ስር ውሏል | በሁለቱ ከተሞች 6 ሰዎች መሞታቸው ተዘገበ | ቪዲዮም ይዘናል appeared first on Zehabesha Amharic.


የህወሃት እና የሱዳን ግንኙነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያለመ ነው። ”የአገሪቱ በጀት 100% ለመከላከያ ቢውልም አይበቃንም”አልበሽር ”ሱዳን 70% በጀት ለመከላከያ እና ፀጥታ ታውላለች”በሱዳን የእንግሊዝ አምባሳደር አሮን (ጉዳያችን ዜና)

0
0

ethiopia sudan Boarder

የህወሃት እና የሱዳን ግንኙነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያለመ ነው። ”የአገሪቱ በጀት 100% ለመከላከያ ቢውልም አይበቃንም” አልበሽር ”ሱዳን 70% በጀት ለመከላከያ እና ፀጥታ ታውላለች” በሱዳን የእንግሊዝ አምባሳደር አሮን (ጉዳያችን ዜና)

ከትናንት በስቲያ እሁድ ታህሳስ 3/2008 ዓም በሱዳን አየር ኃይል ማዘዣ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት አልበሽር ሱዳን ወደ ወታደራዊ ቴክኖሎጂ መሸጋገር አለባት ብለዋል።ከእዚህ በተጨማሪም እጅግ በፈጣን ሁኔታ የሱዳንን ደህንነት ሊያስከብር የሚችል የአየር ኃይል መገንባት አለብን ብለዋል።የሱዳኑ ፕሬዝዳንት አገራቸው ለመከላከያ የምታወጣው በጀት በዝቷል የሚሉ ተቺዎቻቸውን በቁጣ ተናግረዋል።በመቀጠልም ”በዙርያችን ያሉ ፀጥታቸው የተናጋ አገሮችን ተመልከቱ። የአገሪቱ በጀት 100% ለመከላከያ ቢውልም አይበቃንም።የእራሳችን የጦር መሳርያ ፋብሪካ ያስፈልገናል….እጅግ በፈጠነ ሁኔታ ትልቅ አቅም ያለው የአየር ኃይል መገንባት አለብን” ብለዋል ፕሬዝዳንት አልበሽር።በሌላ በኩል በሱዳን የእንግሊዝ አምባሳደር አሮን ”አሲያስ” ለተሰኘ ጋዜጣ ሲናገሩ ”የሱዳንን ዕዳ መቀነስ ፈፅሞ አይታሰብም።ምክንያቱም እስከ 70% በጀት ለመከላከያ እና ለፀጥታ ጉዳይ እንጂ ለሌሎች የልማት ዘርፎች እንደ ትምህርት፣ጤና ለመሳሰሉት አታወጣም።” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት አልበሽር ባለፈው ሳምንት ጋምቤላ ኢህአዴግ/ህወሃት ”የብሔር ብሔረሰቦች በዓል” የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ባደረጋት አገር በከፍተኛ ደረጃ የአገሪቱን ገንዘብ በሚያባክንበት ዝግጅት ላይ ተገኝተው ምሽቱን አዲስ አበባ መመለሳቸው እና ከህወሃት ባለስልጣናት ጋር መገናኘታቸውን የሱዳኑ ”ሱዳን ትሪቡን” መዘገቡ ይታወሳል።በአሁኑ ወቅት ህወሃት እና የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ በሚሰጥ እና ሕዝብን፣አገርንና ታሪክን በሚያዋርድ መልኩ በኢትዮጵያ ላይ በጥምር ሴራ እየሸረቡ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው።ህወሃት የኢትዮጵያ ህዝብን አንድነት በሚያናጋ መልኩ ጎሳ ከጎሳ የማጣላት እና ከውስጥ ሆኖ ኢትዮጵያን የማዳከም ሥራ እየሰራ ለመሆኑን ብዙ እማኞችን መጥቀስ ይቻላል።በአገሪቱ ላይ የታወጀው የጎሳ ፌድራሊዝም ለ25 ዓመታት ያክል ኢትዮጵያን ሰላም የነሳ መሆኑ እየታወቀ እና ውጤቱም በኦሮምያ እና በሌሎች ቦታዎች የበለጠ ፀጥታ የነሳ መሆኑ እየታየ ለችግሩ የበለጠ ”ቤንዚን የማርከፍከፍ” ሥራ አሁንም በህወሃት እየተፈፀመ ነው።በሰሜን ጎንደር የ”አማራ እና የቅማንት” ሕዝብ በሚል ሕዝቡን የመከፋፈል ‘መንግስታዊ የዘር ፍጅት’ እንዲፈፀም መደረጉን እና እስካሁን ከአንድ መቶ በላይ ሕዝብ ማለቁን ኢሳት ራድዮ በታህሳስ 4/2008 ዓም ከአካባቢው ያነጋገራቸውን ነዋሪዎች ጠቅሶ ገልጧል።

የእዚህ የ”አማራ እና የቅማንት” ሕዝብ በሚል የመከፋፈል ሥራ ላይ የሱዳን የሞራልም ሆነ የገንዘብ ድጋፍ ከወያኔ ጋር ሊኖርበት እንደሚችል የብዙዎች ጥርጣሬ ነው።ሱዳን ሰፊ የሆነውን የኢትዮጵያ ለም መሬት እና ወንዞች ወደ ግዛቷ ለማካለለ ከህወሃት ጋር መስማማቷ እና ሰሞኑን ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚችል ሲገለጥ ነው የሰነበተው። ዛሬ ታህሳስ 5/2008 ዓም በዋሽንግተን ኢትዮጵያውያን በሱዳን ኢምባሲ በር ላይ የድንበር ውሉን በመቃወም ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚደረግ ይታወቃል።

ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
ታህሳስ 4/2008 ዓም (December 15/2015)

Source:- Sudan Tribune December 13/2015

The post የህወሃት እና የሱዳን ግንኙነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያለመ ነው። ”የአገሪቱ በጀት 100% ለመከላከያ ቢውልም አይበቃንም” አልበሽር ”ሱዳን 70% በጀት ለመከላከያ እና ፀጥታ ታውላለች” በሱዳን የእንግሊዝ አምባሳደር አሮን (ጉዳያችን ዜና) appeared first on Zehabesha Amharic.

የህወሓቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በጎንደር ከፍተኛ ተቃውሞ ደረሰባቸው

0
0

12359849_553170274841462_5729451910503525948_nከአዲስ አበባ ጎንደር የገቡት የአገዛዙ ባለስልጣናት የህወሓቱ አባይ ፀሀዬ፣ የህወሓት ተላላኪ የሆነው ብአዴን ቁንጮዎች በረከት ስምዖንና አዲሱ ለገሰ ናቸው፡፡ የክልሉ ሹም ገዱ አንዳርጋቸውም በአጃቢነት ተገኝቷል፡፡
አባይ፣ በረከትና አዲሱ በትናንትናው ዕለት የዞኑን ካቢኔ አባላትና ጥቂት የስርዓቱ ደጋፊ የሆኑ የከተማው ነዋሪዎችን በጎሃ ሆቴል ሰብስበው በጎንደር ስለሰፈነው አለመረጋጋት፣ አመፅና ጦርነት ለማነጋገር ሞክረው “ይህ ሁሉ ችግር ከደረሰና ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ በኋላ ምትመጡ እስከ ዛሬ የት ነበራችሁ? የህዝብ ቁጣ ጫፍ ደርሷል አሁን እናንተ መጣችሁ አልመጣችሁ የምትፈይዱት ቅንጣት ታክል ነገር የለም…” የሚል ምላሽ ያለበት ከወትሮው ለየት ያለና ጠንካራ ተቃውሞ ከተሰብሳቢው ተሰንዝሮባቸዋል፡፡ በተለይም በባለስልጣናቱና በካቢኔው መካከል የተፈጠረው እሰጣገባና ንትርክ ወደ ከረረ ያለመግባባት ውስጥ እንደከተታቸው ታውቋል፡፡
እነበረከትና አባይ የጎንደርን ነዋሪዎች በየክፍለ ከተማው ሰብስበው ለማነጋገር መድረክ እንዲያመቻቹላቸው የዞኑን ካቢኔ አባላት ጠይቀው የካቢኔ አባላቱ በአሁኑ የትኩሳት ወቅት ህዝብ መሰብሰብ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ እና ባለስልጣናቱ ራሳቸው ወርደው ያሻቸውን ማድረግ እንደሚችሉ ቁርጥ ያለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በመሆኑም እነ በረከትና አባይ ፀሀዬ ከፍተኛ ብስጭት ውስጥ ወድቀው የሚያደርጉት ጭንቅ ጥብብ ብሏቸው አሁንም በጎንደር ከተማ ጎሃ ሆቴል ውስጥ ይገኛሉ፡፡

The post የህወሓቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በጎንደር ከፍተኛ ተቃውሞ ደረሰባቸው appeared first on Zehabesha Amharic.

ማፈናቀል እንደገንዘብ –ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም

0
0

Pro Mesfinከ1966 ዓ.ም. በፊት መሬት አገር ነበር፤ ከዚያ በኋላ እስከ1983 መሬት የጋራ ሀብት ሆነ፤ ከ183 ወዲህ መሬት ገንዘብ ሆነ፤ ጡንቻ ገንዘብ ሆነ፤ መሬት ጡንቻና ገንዘብ ሆነ፤ አገር የት ደረሰ?
በጡንቻ ሀብታም መሆን ይቻላል፤ በጡንቻ ገበያውን መቆጣጠር ይቻላል፤ በጡንቻ ሻጩን መቆጣጠር ይቻላል፤ በጡንቻ ገዢውን መቆጣጠር ይቻላል፤ ገበያውን፣ ገዢውንና ሻጩን መቆጣጠር ከተቻለ ዋጋውን መቆጣጠር ይቻላል፤ እዚህ ደረጃ ላይ ከተደረሰ ምሥጢሩ ግልጽ ይሆናል፤ ምሥጢሩ ምንድን ነው? ዋናው ነገር ጡንቻ ነው፤ ጡንቻ የሀብት ምንጭ ነው፡፡
ጤንቻ ካለ ተማሪ ቤት ወይም ሀኪም ቤት፣ ወይም አንድ መሥሪያ ቤት ለመሥራት በሚል ሰበብ አንድ መቶ ቤተሰቦችን ከኑሮአቸው ማፈናቀል ሕጋዊ ያሆናል፤ አንድ መቶ ቤተሰቦች ሰፍረውበት የነበረው በአማካይ በነፍስ ወከፍ 100 ሜ.ካ. መሬት ነው እንበል፤ አንድ መቶ ቤተሰቦችን በማፈናቀል የተገኘው መሬት 100×100=10,000 ሜ.ካ. ይሆናል፤ በሊዝ ገበያ ላይ 10,000 ሜ.ካ. መሬት እንደሚከተለው ካሬ ሜትሩ በ20,000 ብር ይቸበቸባል፤ 10,000×20,000=200,000,000 ብር! ሳይሠሩ፣ ሳይለፉ፣ ሰዎችን በጡንቻ ትእዛዝ በማፈናቀል ብቻ የሚገኝ የጡንቻ ትርፍ!
አንድ ሺህ ቤተሰቦችን ማፈናቀሉ የበለጠ ትርፍን ያስገኛል፤ — 1,000x100x20,000=2,000,000,000 ብር! ምን የመሰለ ዘመናዊ ሰማይ-ጠቀስ ሕንጻ ይሠራል! ገንዘብ ካነሰም ማፈናቀል ነው!

The post ማፈናቀል እንደገንዘብ – ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም appeared first on Zehabesha Amharic.

የቀድሞው ጠ/ሚ/ር ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን የሰሞኑ ሕዝባዊ ቁጣ ለቤተሰቧና ለንብረቷ እንድታስብ እንዳደረጋት ገለጸች

0
0

azeb

(ዘ-ሐበሻ) በአንድ ወቅት “ደሃ ነኝ… ከዓለማችን የደሃ ሀገር መሪዎች መካከል እኛ አንደኞቹ ነን” ስትል የነበረችው የቀድሞው ሟች ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ሰሞኑን በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ በገንዘቧና በቤተሰቧ ላይ ያሳደረውን ስጋቷን በፌስቡክ ገጿ ገለጸች::

Screen Shot 2015-12-16 at 3.54.28 AM

ወ/ሮዋ በፌስቡክ ገጿ እንዳለችው “በሰሞኑ በሚሆነው ነገር በጣም በጣም የሚያሳዝን ነው። እኛ እንግዲህ አስራ ሰባት አመት ትግል ቦኅላ ለዚህ ድል በቅተን ደርግን ገርስሰን ለመላው ኢትዮጵያዊ ዲሞክራሲ ያለባት አገር መስርተናል። እና መለስ ልጅነቱን በሙሉ የለፋበትን አላማ ዛሬ በዚህ ብጥብጥ ባነሱ አደገኛ ቦዘኔዎች ከልማት ታቅበን መቀመጥ በጣም ያሳዝናል በእውነቱ። ስራ አቁሞ ሰልፍ ሲሰለፉ መዋል ምን ይባላል? ብንሰራ አይሻልም? እንደ የድሮ ስርአት ነፍጠኞች ያሁኑ አገር ባይበጠብጡ ይሻላል።”

ወ/ሮዋ አክላም ” ትልልቅ አዋቂ ሰዎች የመለስ አይምሮ ያፈለቀውን ራእይ የሚያስፈፅሙ አሉ ተመርጠው በህዝብ መቶ ድምፅ ተሰጥቷቸ እያሉ አሁን ለምን አገር ይረበሻል? እኔ በእውነቱ ከሆነ ለቤተሰብ ለንብረቴ ማሰብ ጀምሬያለሁ። እርግጠኛ ነኝ ብዙዎች እንደኔው ማሰብ መስጋት ጀምረዋል። ጥሩ አይደለም ሰላም እና መረጋጋት ያስፈልጋል በመጀመሪያ።” ብላለች::

ስለ ባሏ ራዕይ ከሞተ በኋላም እንዲነገር የምትፈልገው ወይዘሮ አዜብ ሕዝብ የመለስን ፓርክ በማቃጠሉ የተሰማትን ስሜት ስትገልጽም “የመለስ እሚያህል ትልቅ ሰው በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ እማይታወቅ ሰው፣ ከዚህ በፊትም እንዳልኩት በፔሮል የሚተዳደር ፕሬዚደንት በሶስት ሺህ ብር ደሞዝ የትም አለም የለም። እና ዛሬ ለመታሰቢያ አንድ ፓርክ ቢሰራ እነዚ ሰልፍ ወጡ የተባሉ አደገኛ ቦዘኔዎች አቃጠሉ አሉ። ሀዘኔ መሪር ነው በእውንት ከሆነ። መለስ ቢያየን ያፍርብናል። ራእይ ሰጥቶን ያ ሁሉ አይምሮ ጨምቆ አውጥቶ እኛ እንዲ ወደ ድንቁርና ስንሄድ ያሳዝነዋል። በቶሎ መንግስ ፀጥታ ሊያስከብር ይገባዋል። እነዚ ቦዘኔዎችም ለፍርድ መቅረብ አለባቸው።” ብላለች::

የቀድሞው ጠ/ሚ/ር ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን የሰሞኑ ሕዝባዊ ቁጣ ለቤተሰቧና ለንብረቷ እንድታስብ ካደረጋት ቀጣይ እቅዷ ገንዘቧን አሽሽታ ወደ ሌላ ሃገር መፈርጠጥ? ይህ የሕዝብ ጥያቄ ነው::

The post የቀድሞው ጠ/ሚ/ር ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን የሰሞኑ ሕዝባዊ ቁጣ ለቤተሰቧና ለንብረቷ እንድታስብ እንዳደረጋት ገለጸች appeared first on Zehabesha Amharic.

ፍልስፍና አልባ የሆነ አገዛዝና የፖለቲካ ትግል ዘዴ የአንድን ህብረተሰብ አስተሳሰብ ያዘበራርቃል- የመጨረሻ መጨረሻም አገርን ያወድማል!

0
0

 

ፈቃዱ በቀለ፣ ዶ/ር

ታህሳስ 15፣  2015

 

ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ

ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ

ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በብዙ አፍሪካ አገሮች የሚታየው የአስተዳደር ብልሹነት፣ የህዝቦች ኑሮ መዘበራረቅና ዓላማ-ቢስ መሆን፣ እንዲያም ሲል በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ በሃይማኖትና በጎሳ አሳቦ ርስ በርሱ እንዲጠላላ ማድረግና፣ የመጨረሻ መጨረሻም ወደ ርስ በርስ መተላለቅ እንዲያመራ መንገዱን ማዘጋጀት፣ በተራ አነጋገር ከመልካም አስተዳደር እጦት፣ ከአምባገነናዊ አስተዳደር መስፈንና ከዲሞክራሲ አለመኖር ጋር ሲያያዝ ይታያል። አንዳንዶች እንዲያውም እንደዚህ ዐይነቱን ዓላማ-ቢስ የህብረተሰብ ጉዞ የአፍሪካ መሪዎች ወይም የጥቁር ህዝብ ችግር አድርገው የሚመለከቱ አሉ።

በእርግጥ ለአንድ አገር ስርዓት ባለው መልክ መተዳደርና፣ ህብረተሰቡም በዕቅድና በዓላማ እንዲመራ ከተፈለገ በዚያ የሰፈነው አገዛዝ ህብረተሰቡን በማደራጀት ረገድ  የሚጫወተው ሚና አለ። ጥያቄው ግን አንድ ህብረተሰብ ዓላማ ባለው መልክ እንዳይደራጅና ቆንጆ ቆንጆ ስራዎችን እንዳይሰራ የሚያግዱት ነገሮች ምን ምን ናቸው? በስነ-ስርዓት እንዲደራጅስ ከተፈለገ መሪዎችም ሆነ ህብረተሰቡ መከተል የሚገባቸው ኖርሞች፣ ፍልስፍና፣ ሞራልና ስነ-ምግባር አሉ ወይ? ምንስ ይመስላሉ ? ወይስ አንድ ህዝብ እየተዋከበና ርስ በርሱ እየተፋጠጠ መኖሩ ተፈጥሮአዊ ግዴታ ነው ወይ ?  አንድ ህብረተሰብስ በምን መልክ ነው መታየት ያለበት? በሌላ አነጋገር፣ ለመብላትና ለመጠጣት ብቻ የሚኖርበት ?  ወይስ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ስነ-ምግባራዊ፣ ጥበባዊና ኢኮኖሚዊ፣ እንዲሁም ሌሎችም ነገሮች ተደራጅተው ህብረተሰቡ እንደሰውነታችን በብዙ ነርቮች ተሳስሮ፣ ልክ እንደደም ዝውውር ሳያቋርጥ፣ በተለይም ኢኮኖሚው አንድኛው መስክ ከሌላው ጋር በመያያዝ ውስጠ-ኃይሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለና እየተጠናከረ የሚጓዝበት መድረክ ነው ወይ ? የሚሉትን ጥያቄዎች ጠጋ ብሎ መመልከትና መመርመር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በተለይም በአሁኑ ዘመን የግሎባል ካፒታሊዝም አይሎ መውጣትና፣ የብዙ ህብረተሰቦችን ህይወት ወሳኝ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲያመሩ ማስገደድና ማዘበራረቅ፣ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ፈራቸውን እየሳቱና በቀላሉ የማይመለሱበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ማለት ይቻላል። በተለይም የየመንግስታቱ መኪና በከፍተኛ ደረጃ ሚሊታራይዝድ መሆንና ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የጦር ስልት ውስጥ እንዲካተት መደረጉ፣ በዚህም ላይ የስለላው ድርጅት መጠናከርና ህዝብን አላላውስም ማለት፣ ብዙ የአፍሪካ መንግስታት አንድ መንግስት ለአገሩና ለህዝቡ ምን መስራት እንዳለበት እንዳይገነዘቡና አትኩሮአቸውንም በሀገር ግንባታ ላይ እንዳያደርጉ አግዷቸዋል ማለት ይቻላል። የየመንግስታቱትም ሚና ህብረተሰቡን ከማደራጀት፣ ህብረ-ብሄርን ከመገንባት፣ በሳይንስና በቲክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የውስጥ ኢኮኖሚ ላይ ከመረባረብ ይልቅ፣ ራስን ወደ ማጠናከሪያና ሀብት ዘራፊነት ተለውጧል። በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ መንግስታትና አገዛዞች የህዝቦቻቸው ተጠሪዎች ሳይሆኑ፣ በውጭ ኃይሎች የሚታዘዙና፣ በተለይም ጦርነትንና ህዝባዊ ሀብትን ሊፈጥር የማይችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ የሚያደርጉ ናቸው።

ከዚህ ስንነሳ በፍጹም ልናልፈው የማንችለው ጥያቄ ከፊታችን ተደቅኖ ይገኛል።ይኸውም ብዙ የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮች ከሞላ ጎደል ስርዓት ባለው መልክ ተደራጅተው ሲጓዙና፣ የብዙ ሚሊያርድን ህዝቦች ዕድል ወሳኝ መሆን ሲችሉ፣ እንደኛ ያለውንስ ህዝብ ስነ-ስርዓት ያለው አደረጃጀት ለምን ተሳነው?  ስነ-ስርዓትስ ባለው መልክ ለመደራጀት  የሚጎድሉን ነገሮች ምንድናቸው? ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊ፣ ህብረተሰብአዊ ? ወይስ የፖለቲካ ፍልስፍና እጦትና መሪዎች የሚመሩበት አንዳች ፍልስፍና አለመኖር ?

ለአንድ ህብረተሰብ በስነ-ስርዓት መደራጀትን አስመልክቶ ከጥንት የግሪክ ስልጣኔ ጀምሮም ሆነ ከዚያም በፊት ህግና ስርዓት አስፈላጊ መሆናቸውን በብዙ ምርምር የተደረሰበትና በኢምፔሪካል ደረጃም የተረጋገጠ ነው። ይሁንና ግን በተለይም ፍልስፍናን ከፖለቲካ ጋር ማያያዝና፣ አንድም ህብረተሰብ ሚዛናዊ በሆነ መልክና በስነ-ስርዓት የማደራጀትን አስፈላጊነት በከፍተኛ ደረጃ ውይይት የተካሄደበት ከግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል። ከዚያ በኋላ የተነሱና ብዙም ምርምር የተካሄደባቸው የፖለቲካ ፍልስፍናዎች፣ ህብረተሰብን በአንድ ስርዓት ባለው መልክ ማደራጀት፣ በግሪኩ የተለያዩ ፍልስፍናዎች ላይ ተመርኩዞ ነው። እዚህ ላይ ሌላው የሚነሳው ጥያቄ፣ የተለያዩ የግሪክ ፈላስፋዎች አትኩሯቸውን ለምን በፍልስፍና ላይ፣ በተለይም በፖለቲካ ፍልስፍና ላይ አደረጉ ? የሚለው ከባድ ጥያቄ መመለስ ያለበት ይመስለኛል። እንደሚታወቀው የሰው ልጅ ለህይወቱ ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያና ራሱንም ለመከላከል መሳሪያዎች ቢያስፈልጉትም፣ ከዚህ ዘልቆ በመሄድ የማሰብ ኃይሉን በማዳበርና ራሱንም በማደራጀት ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ደረጃ በመሸጋገር የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤትም መሆን እንደሚችል የታወቀ ጉዳይ ነው። ከዚህ ስንነሳ ከላይ የተጠቀሱት መሰረታዊ ጉዳዮች በየጊዜው ሊሻሻሉና በቁጥር እየጨመረ ከሚሄደው ህዝብ ጋር ሊጣጣሙ የሚችሉት የሳይንስና የቴኮኖሎጂ ሚናነት በግልጽ ከተቀመጡና፣ በነዚህ ላይ ከፍተኛ ርብርቦሽ ከተደረገ ብቻ ነው።፡ይሁንና አንድ ህዝብ የማሰብ ኃይሉን እንዳያዳብር፣ አዳዲስ መሳሪዎችን በመፍጠር ከዝቅተኛ ህብረተሰብ ወደ ከፍተኛ እንዳይሸጋገር፣ ከቁም ነገር ስራ ይልቅ በሆነ ባልሆነው ነገር በመያዝ ወይም በጦርነት በመጠመድ ዝብርቅርቅ ኑሮ እንዲኖርና፣ በዚያው እንዲገፋበት የሚያደርጉትና፣ ይህ ዐይነቱም ኑሮ እንደ ባህልና እንደ ልማድ የሚወሰድበት ሁኔታ አለ። ይህንን ሁኔታ ጠጋ ብለው የተመራመሩት የግሪክ ፈላስፎች የሰው ልጅ ከእንስሳ የተለየ ከሆነና፣ ራሱንም ማደራጀትና በሰላም መኖር የሚችል ከሆነ ለምንድን ነው ወደ ጦርነት የሚያመራው? ለምንድን ነው የተዘበራረቀ ኑሮ የሚኖረው? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ነበረባቸው።

ሶክራተስና ፕላቶ ብቅ ከማለታቸው በፊት በስድስተኛው ክፍለ-ዘመንና ከዚያ በፊት የግሪክ ህዝብ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኝ ነበር። የርስ በርስ መተላለቅ፣ መጠን የሌለው ብዝበዛና ድህነት፣ የተፈጥሮ አደጋዎች መደጋገምና ሌሎችም የግሪክን ህዝቦች ኑሮ ያመሰቃቀሉና፣ ዕረፍትና ሰላም አንሰጥም ያሉ ሁኔታዎች የህዝቡ ዕጣዎች ነበሩ። እነዚህን የመሳሰሉ የኑሮን ትርጉም ያሳጡ ሁኔታዎች በእነ ሆሜርና በሄሲዮድም ሆነ በግሪክ ህዝብ ዕምነት የአምላኮች ድርጊት እንደነበሩና፣ ባስፈለጋቸው ጊዜ ህዝቡን ለመቅጣት ሲሉ የሚልኩት ውርጅብኝ እንደነበርና፣ ህዝቡም ካለ አምላኮች ፈቃድ በራሱ አነሳሽነት ምንም ሊያደረገው የሚችለው ነገር እንደሌለና፣ የነሱንም ትዕዛዝ መጠበቅ እንደነበረበት የታመነበት ጉዳይ ነበር። ከሶክራተስና ከፕላቶ በፊት የነበሩ የመጀመሪያዎቹ የተፈጥሮ ፈላስፎች ይህንን አስተሳሰብ ትክክል እንዳልሆነና፣ በተፈጥሮ ውስጥ ይከሰቱ የነበሩ አደጋዎች፣ ለምሳሌ እንደ ብልጭታና የመሬት መንቀጥቀጥም ሆነ ሌላ ነገሮች የአምላኮች ተልዕኮዎች ሳይሆኑ የተፈጥሮ ህግጋት እንደሆኑና፣ ማንኛውም ነገር ካለምክንያት እንደማይከሰት ለማመልከት ቻሉ። ይህ የመጀመሪያው የተፈጥሮ ፍልስፍናና፣ በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን በታላቁ የግሪክ መሪ በሶሎን ተግባራዊ የሆኑት የመጀመሪያው የፖለቲካ ሪፎርሞች በግሪክ ህዝብ አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስከተሉ። ህዝቡ ከማንኛውም የባርነት ማነቆዎች እንዲላቀቅ መደረጉ፣ የነበረበትን ዕዳ እንዳይከፍል መሰረዝና፣ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ እንደነፃ ዜጋ እንዲታይ መደረጉ ከፍተኛ የአስተሳሰብ ለውጥን ሊያመጣ ችሏል። ከፍተኛ የባህል ለውጥ የታየበትና ልዩ ልዩ የፍልስፍና አስተሳሰቦችና፣ የሂሳብ ምርምሮችና ሳይንሳዊ አስተሳሰብም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው በተለይም የግሪክን ምሁር ጭንቅላት መያዝ የጀመሩትና ዕውነተኛ ዕድገት የታየበት። በፒታኩስና በሶሎን የአገዛዝ ዘመን የግሪክ ህዝብ ከጦርነት ተላቆና በአጉል ጀግንነት ላይ የተመሰረተን ዝናን ጥሎ ራሱን በማግኘት ዕውነተኛ የሲቪክ አገዛዝን የተቀዳጀበት ዘመን ነበር። የማቴሪያል ደስተኛነት ብቻ ሳይሆን የመንፈስንንም ነፃትና ደስተኛነት በመቀዳጀት የመፍጠር ችሎታውን ያዳበረበት ዘመን ነበር። ከፒታኩስና ከሶሎን አገዛዝ በፊት የግሪክ ህዝብ በጦርነት የተጠመደና ይህንን እንደሙያው አድርጎ በመያዝ የሚዝናናበት ዘመነ ነበር።  ይሁንና ግን የፒታኩስና የሶሎን የፖለቲካ ሪፎርሞች በግሪክ ህዝብ ላይ መሰረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ቢያመጡም ይሁ ሁኔታ ግን በዚያው ሊገፋበት አልተቻለም። በመሆኑም  የስልጣን ሽግግር ሲካሄድና የኃይል አሰላልፍ ሲቀየር፣ የፖለቲካ ፍልስፍናና አደረጃጀት እነሶሎን በቀደዱት መልክ ሊጓዝ አልቻለም። በተለይም የስልጣንን ምንነት ከራሳቸው ዝናና ጥቅም አንፃር መተርጎምና ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት አንዳንድ የግሪክ መሪዎች የፖለቲካውን አቅጣጫ ይቀይራሉ። ህብረተሰብአዊ ስምምነትን የሚያጠነክር ፖለቲካዊ አካሄድ ሳይሆን ውዝግብነትን የሚፈጥር፣ የህዝቡን መንፈስ የሚረብሽና የጥቂት ኦሊጋርኪዎችንና ቡድኖችንም ሆነ ግለሰቦችን ጥቅም የሚያስቀድም ፖሊሲ መቀየስ ይጀምራሉ። በመሆኑም የኦሊጋርኪዎችን አመለካከት የሚያስተጋቡና ይህም ትክክል ነው ብለው የሚያስተምሩ ፈላስፋዎች፣ ሶፊስቶች ተብለው የሚጠሩ፣ የፖለቲካውን መድረክ እየተቆጣጠሩና ብዙ ወጣቶችንም በማሳሳት የበላይነትን እየተቀዳጁ በመምጣት በስምምነት የተመሰረተውና ለከፍተኛ ስልጣኔ የሚያመቸውን የእነሶሎን የፖለቲካ ፍልስፍናን ከመከተል ይልቅ ስግብግብነትንና ዝናነትን በማስቀደም ህብረተሰባዊ መዛባት እንዲፈጠር ያደርጋሉ። በተለይም የአቴን የበላይነትን መቀዳጀትና ከሌሎች ደሴቶች ጋር ሲወዳደር በስልጣኔ ቀድሞ መሄድ የግሪኩን የመጀመሪያውን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እየደመሰሰው ሊመጣ ቻለ። የመንፈስን የበላይነት፣ ጥበብና ህብረተሰብአዊ ስምምነትን የሚቀናቀነው የሶፊስቶች አመለካከት በመስፋፋት አገዛዙን ይበልጥ ለጦርነት የሚገፋፋና፣ የህዝቡን ሰላም የሚነሳ ስርዓት በመሆን በስንትና ስንት ጥረት የተገነባው ስልጣኔ በተሳሳተ ፍልስፍና መፈራረስ ይጀምራል።

በወቅቱ የተለያዩ የግሪክ ግዛቶች፣ በአንድ በኩል በራሳቸው ውስጥ በሚደረግ ሽኩቻ የተወጠሩ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ የፐርሺያ አገዛዝ አቴንና ሌሎችንም ግዛቶች በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ተደጋጋሚ ጦርነት ይከፍትባቸዋል። በፐሪክለስ የሚመራው አገዛዝ ሌሎችንም በማስተባበር ከፐርሺያ ወራሪ ጦር በኩል የተከፈተበትን ጦርነት መክቶ ይመልሳል።  ይሁንና ግን እነ ፐሪክለስ ሌሎችን ግዛቶች በማስተባበር በፐርሽያ ጦርነት ላይ ድል ከተቀዳጁ በኋላ  የጥጋብ ጥጋብ ይሰማቸዋል። ቀደም ብሎ የተደረሰበትን የእኩልነትና ስምምነት ውል  በማፍረስ በሌሎች የግሪክ ግዛቶች ላይ ወረራ ያደርጋሉ። እጅ አልሰጥም ያሏቸውን ግዛቶች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ተግባር  በማካሄድ በተለይም ወንድ ወንዱን በመጨረስ ሴቶችንና ህፃናትን ገባር ያደርጓቸዋል። ድርጊቱ እጅግ አሰቃቂ ነበር። የግሪክን ህዝብ ትርምስ ውስጥ የከተተ ነበር። ይሁንና ይህ የአቴን ጥጋብና ግፍ በስፓርታ የገዢ መደብ ሊከሽፍና ሊገታ ቻለ። በዚህ ድርጊቱ ፐሪክለስ አቴን ለሌሎች ግዛቶች በስልጣኔዋ ምሳሌ ትሆናለች ብሎ እንዳለተመጻደቀ ሁሉ፣ በተግባር ያሳየው ግን በኃይሉ በመመካት ወረራንና ጭፍጨፋን ነበር ያረጋገጠው።

እነ ሶክራተስና ፕላቶ ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻና፣ በአራተኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ላይ ብቅ ሲሉ ይህንን የወንድማማቾችን ርስ በርስ መተላለቅና፣ ህዝቡን ሰላም ማሳጣትና ኑሮውም ትርጉም እንዳይኖረው ማድረግ የተረጎሙት ከተሳሳተ ፍልስፍና ጋር የተያያዘ ስልጣን መሆኑን በማመልከትና፣ በአንድ ግለሰብ ላይ ብቻ የሚሳበብ ሳይሆን፣ ጠቅላላውን የፖለቲካ አወቃቀርና አገዛዙ የሚመራበትን ፍልስፍና በመመርመር ነበር። በሶክራተስ ዕምነትና አመለካከት፣ በጊዜው ፐሪክለስ ታላቅ መሪ ቢሆንም በሱ ዘመን አቴን ወደ ኢምፔርያሊስትነት የተለወጠችና፣ የአገዛዙም  ፖሊሲ ዝናን በማስቀደም ኃይልንና ስግብግብነትን(Power and Greed) ዋና ፍልስፍናው አድርጎ የተነሳ አገዛዝ መሆኑን በማመልከት ነበር። በመሆኑም ይላል ሶክራተስ፣ በፐሪክለስ ዘመን ወጣቱ ሰነፍ፣ ለፍላፊና አጭበርባሪ የሆነበት ዘመንና፣ አሳሳች አስተሳሰብ በማበብ በተለይም የወጣቱን ጭንቅላት በመያዝ ወደ ማይሆን አቅጣጫ እንዲያመራ የተደረገበት  ሁኔታ ነበር። ባህላዊ ኖሮሞችና መከባበር የጠፋበት፣ ሽማግሌ የማይከበርበትና፣ ህዝቡም  ይዞ የሚጓዘው አንድ ዕምነት አልነበረውም። አስተሳሰቡ ሁሉ የተዛበራረቀበት ነበር።

በጊዜው የነበረው ትግል ይህንን አቅጣጫ የሌለውን ጉዞና በስልጣን መባለግ አስመልክቶ በሶክራተስና በፕላቶ በአንድ ወገን፣ በሌላ ወገን ደግሞ በሶፊስቶች መሀከል የጦፈ ትግል ይካሄድ ነበር ። ሶፊስቶች የእነ ፐሪክለስን የአገዛዝ ፍልስፍናን ሲደግፉ፣ መሰረተ-ሃሳባቸውም በጊዜው የነበረውን ሁኔታ መቀበልና ይህም ትክክል መሆንኑ ማስተማር ነበር። ሶፊስቶች በአነሳሳቸው ተራማጅ ቢሆኑም፣ ፍልስፍናቸው በቀጥታ በሚታይ ነገር ላይ ተመርኩዞ ትንተና መስጠትና፣ በጣፈጠ ግን ደግሞ በተሳሳተ አቀራረብና አነጋገር የሰውን ልብ መማረክ ነበር። ስለዚህም በሶፊስቶች ዕምነት ስልጣን ላይ ያለው የገዢ መደብ የሚያወጣውን ህግ አምኖ መቀበልና፣ ከዚህ ሌላ አማራጭ ነገር እንደሌለ ሲከራከሩና ለማሳመን ሲጥሩ፣ እነሶክራተስና ፕላቶ ደግሞ፣ በተለይም ፕላቶ በሶክራተስ በመመሰል ይሉት የነበረው የጠቅላላውን የፖለቲካ አወቃቀር ለመረዳት ከነበረው ሁኔታ አልፎ(Trnascedental) መሄድና መመርመር እንደሚያስፈልግ ያመለክቱ ነበር። በሌላ አነጋገር፣ ሶፊስቶች ኃይልንና ለስልጣን መስገብገብን ትክክል ነው ብለው ሲሰብኩ፣ እነሶክራተስና ፕላቶ ደግሞ እንደዚህ ዐይነቱ ጉዞ እጅግ አደገኛ እንደሆነና፣ የመጨረሻ መጨረሻም አንድ ህብረተሰብ ሊወጣ የማይችልበት ማጥ ውስጥ የሚከተው ነው ብለው በጥብቅ ያሳስቡ ነበር። ካሊክለስ የሚባለው አንደኛው የሶፊስቶች መሪ የእነሶክራተሰን በአርቆ አስተዋይነትና በሚዛናዊነት ላይ የተመረኮዘ የፖለቲካ ፍልስፍናን ሞኞች ብቻ ናቸው የሚከተሉት ብሎ በመስበክና በማንቋሸሽ፣ ፖለቲካ በስምምነት ላይ ሳይሆን በአሽናፊና በተሽናፊነት ላይ የተመረኮዘና፣ የመጨረሻ መጨረሻም ኃይል ያለው ብቻ ነው ሊገዛ የሚችለው በማለት ሽንጡን ገትሮ ይከራከር ነበር። በተጨማሪም በሶፊስቶች ዕምነት አንድ ሁሉንም ሊያሰተባብርና፣ ሁሉም ሰው ሊቀበለው የሚችለው ዕውነት ነገር የለም። ሁሉም ሰው አንድን ነገር እንደፈለገው ሊተረጉምና ሊረዳ ይችላል። ፕሮታጎራስ የሚባለው የሶፊቶች  ሌላው መሪ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱ የዕውነት መለኪያ አለው፤ (Man is the Measure of Everything) አንድ ሁሉንም ሊያሰተባብርና ተቀባይነት ሊኖረው የሚገባው ዕውነት የለም በማለት የሶፊስቶችን የተሙለጨለጨ አመለካከት ያስተጋባ ነበር።

በሶክራተስና በፕላቶ የፍልስፍና ዕምነት ግን ማንም ሰው ዓላማና ተግባር ሲኖረው፣ በመጀመሪያ ከትክክለኛ ዕውቀት ጋር ነው የሚፈጠረው። ይሁናን ግን እያንዳንዱ ግለሰብ በዚህች ዓለም ላይ ሲወረወር እንደየህብረተሰቡ ሁኔታ ከተፈጠረበት ዕውቀት ጋር እየራቀ ይሄዳል። በአንድ ወቅት ነገሮች ርስ በራሳቸው እንደተያያዙና የተወሳሰቡ መሆናቸውን ይገነዘብ የነበረው ጭንቅላት፣ የተያያዙ ነገሮችን እየበጣጠሰ መመልከት ይጀምራል። ነገሮች ሁሉ ብዥ ይሉበታል። ዕውነትን ከውሽትን ለመለየት ይቸገራል። ከዚህም በላይ ለአንድ ችግር መነሻ የሆነውን ዋና ምክንያት ለመረዳት ችግር ውስጥ ይወድቃል። በሶክራተስም ሆነ በፕላቶ ዕምነት ወደ ጥንቱ ሁኔታ ለመመለስ ማንኛውም ሰው ሀቀኛውን መንገድ ለመፈለግ የማያቋርጥ ትግል ማድረግ አለበት። እየመላለሰ ራሱን መጠየቅ አለበት። በቀላሉ በሚታዩ ነገሮች ላይ መማረክና እነሱን ትክክል ናቸው ብሎ መቀበል የለበትም። ስለሆነም፣ በሁለቱ ዕምነት የሰው ልጅ ሁሉ ጠላት ከመንፈስ ተነጥሎ የሚታየው አካል ነው። ሰዎች ራሳቸውን ለማጎልመስ ሲሉ በሆነው ባልሆነው ነገር ይታለላሉ። አስተሳሰባቸው በማቴርያል ነገር ላይ ሲጠመድ ስግብግብነትንና አብጦ መገኘትን፣ ሌላውን ሰው ደግሞ ማንቋሸሽና መናቅን እንደ ዋና የኑሮ ፍልስፍናቸው አድርገው ይመለከታሉ። ይህ ዐይነቱ አመለካከትና ከቆንጆ ስራ እየራቁ መሄድና በራስ ዓለም ውስጥ መኖርና መሽከርከር ለጦርነትና ለአንድ ህብረተሰብ መመሰቃቀል ምክንያት ነው ብለው ያስተምሩናል።  በሌላ አነጋገር የሰዎች ንቃተ-ህሊና ዝቅ እያለ ሲሄድ፣ ወይንም ደግሞ በተሳሳተ ኢንፎርሜሽንና ዕውቀት በሚመስል ነገር በሚጠመድበት ጊዜ እያንዳንዱ ግለሰብ የህብረተሰቡ አካል መሆኑን ይዘነጋል።  እንደዛሬው ባለው ሁኔታ ደግሞ ሃይማኖትንና ጎሳነትን በማሰቀደም እያንዳንዱ ግለሰብ የእኔ ሃይማኖት ወይም ጎሳ ከሌላው ይበልጣል በማለት ሰብአዊነትን ከማስቀደም ይልቅ ወደ አለመተማመንና እንዲያም ሲል ወደ ርስ በርስ መጨራረስ ያመራል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ብልጥ ነን ለሚሉና ለስልጣንና ለገንዘብ በሚሽቀዳደሙ ጥቂት ኃይሎች እንደመሳሪያነት በማገልገል አንድ ህዝብ በዘለዓለማዊ ትርምስ ውስጥ እንዲኖርና፣ ድህነትና ረሃብ እጣው እንዲሆን ይደረጋል።

በሶክራተስም ሆነ በፕላቶ ዕምነት የሰው ልጅ ሁሉ ችግር የማሰብ ኃይል ችግር ወይም የዕውቀት ችግር ነው። ዕውነተኛ ዕውቀትን የምንጎናጸፈው ትምህርት ቤት በምንማረው ወይም እንደ ዳዊት ሸምድደን በምንደግመው ዐይነት የሚገለጽ አይደለም። በሁለቱም ዕምነት ሆነ ኋላ ብቅ ላሉት የአውሮፓ ፈላስፋዎችና ተመራማሪዎች፣ ዕውነተኛ ዕውቀት ማለት ራሳችንን እንድናውቅ የሚያደርገን፣ ወደ ውስጥ ራሳችንን ለመመልከት እንድንችል ግፊት የሚያደርግብን፣ የበለጠ ራሳችንን እንድንጠይቅ የሚያስችለን፣ የተፈጥሮን ህግጋት ጠለቅ ብለን እንድንረዳ የሚያስችለንና፣ በጥንቃቄም በተፈጥሮ ውስጥ ያሉትን ነገሮች በማውጣትና ቅርጻቸውን በመለወጥ እንድንጠቀምባቸው የሚያግዘን፣  ህብረተሰብን በስነ-ስርዓትና መልክ ባለው ሁኔታ እንድናደራጅ የሚረዳን፣ ከሰውነታችን ፍላጎት ይልቅ የመንፈስን የበላይነት በማረጋገጥ በመንፈስ ኃይል በመመራት ከሌላው ተመሳሳይ ወንድማችን ጋር ተሳስቦ መኖር መቻል፣ በፍጹም የራስን ጥቅም በማስቀደም ዓላማ አለመመራት…ወዘተ. ናቸው። ለተንኮልና ለምቀኝነት ተገዢ አለመሆንና ወደ ብጥብጥ አለማምራትና፣ ህብረተሰብአዊ ምስቅልቅልነት እንዲፈጠር ሁኔታዎችን አለማዘጋጀት፣ የማንኛውም የሰው ልጅ ፍጡር ጥረት አርቆ በማሰብ ኃይል በመመራት ወደ እግዚአብሄር ለመጠጋት መጣር ነው። በፕላቶ ዕምነት ሌላው ለአንድ ህብረተሰብ ምስቅልቅል ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ወይም ለጦርነት ምክንያት የሚሆኑ ከሰብአዊነትና ከወንድማማችነት ይልቅ የብሄረ-ሰብ/ጎሳ አድልዎነት(Ethnic Solidarity) ምልክት የሆኑ ቅስቀሳዎች ቦታ ከተሰጣቸው ነው። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ለሚከሰት ችግር ዋናው ምክንያት የተለያዩ ብሄረሰቦች በመኖራቸው፣ ወይም አንደኛው ብሄረሰብ በሌላው ላይ ጫና ስለሚያደርግ ሳይሆን፣ በስልጣን ላይ ያሉ ኃይሎች ራሳቸው በሚፈጥሩት ልዩነትና ስልጣን ላይ ለመቆየትና ህዝቡን አደንቁረው ለዘለዓለም ለመግዛት እንዲችሉ የብሄረሰብን ጥያቄንና ሃይማኖትን የፖለቲካ መሳሪያ አድርገው  ሳይንሳዊውንና የስልጣኔውን ፈር ያሳስታሉ። ስለዚህም ለአንድ ህብረተሰብ ችግር ዋናው መፍትሄ እያንዳንዱ ግለሰብ ከሌላው የማይበልጥ መሆኑን ሲረዳና፣ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የተለያዩ ብሄረሰቦች መኖር የታሪካዊ ግዴታ እንጂ እንደክፋት መታየት የሌለባቸው መሆኑን ሲገነዘብ ነው። የእያንዳንዱም ግለሰብ ግንዛቤ የሰውን ልጅ ሁኔታ ልክ እንደተፈጥሮ ህግ መረዳት ሲሆን፣ ተፈጥሮ ውስጥ የተለያዩ ነገሮች፣ ለምሳሌ የተለያዩ አበባዎች፣ የተለያዩ ዛፎችና የተለያዩ ከብቶች መኖር የተፈጥሮን ውበት እንደሚያመለክቱና፣ የተፈጥሮም ግዴታ የሆኑትን ያህል፣ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥም የተለያዩ ብሄረሰቦች፣ ጥቁርና ቀይ መልክ  ያለው ሰው፣ ረዥምና አጭር ሰው… ወዘተ. መኖር እንደ ውበት መታየት ያለባቸው ነገሮች እንጂ መበላለጥን የሚያረጋግጡ አይደሉም። ስለሆነም ልዩ ልዩ ነገርችና አንድነት(unity in muliplicity) እዚያው በዚያው መኖር የተፈጥሮ ህግጋት መሆናቸውን በመረዳት ልዩነት ለጠብ ምክንያት ሊሆን እንደማይችል እንደመሰረተ ሃሳብ መወሰድ ያለበት መመሪያ ነው። ስለዚህም በአንድ ህብረተስብ ውስጥ የሚከሰቱ ብጥብጦች የተፈጥሮን ውስብስብነትና ውበት ለመረዳት ካለመቻልና ጠለቅ ብሎ ለማየት ካለመፈለግ የተነሳ ወይም በተሳሳተ ዕውቀት በመመራት አንድን ህብረተሰብ ለመግዛት መቻኮል ነው። ለዚሁ ሁሉ መፍትሄው ይላል ፕላቶ፣ ማንኛውም ግለሰብ አርቆ አሳቢነትን በማስቀደም በመፈቃቀር ላይ የተመሰረተ ህብረተሰብ ለመግንባት መጣር አለበት። ማንኛውም ግለሰብ ይህንን የዩኒቨርስ ህግ ሲረዳና  ስምምነትንና ስርዓትን(Harmony and Order) በጭንቅላቱ ውስጥ ሲቀርጽ በምድር ላይ ዕውነተኛውን ገነት ይመሰርታል ይላል።

ወደድንም ጠላንም ከብዙ ሺህ ዐመታት ጀምሮ በዓለም ላይ የተከሰቱ የርስ በርስ መተላለቆች፣ በአገሮች መሀከል የተካሄዱ ጦርነቶች፣ ረሀብና የወረርሽኝ በሽታዎች፣ በዘመነ-ሳይንስ እሰካዛሬም ድረስ ዘልቆ ብዙ የሶስተኛውን ዓለም አገሮች የሚያምሰውና፣ የአንድ አገር ህዝብ እየተሰደደ እንዲኖር የሚያደርግ፣ ጊዜ ያመጣላቸው ኃይሎች ድንበር እየጣሱ የሌላውን አገር የሚወሩ፣ እነ ሶክራተስና ፕላቶ ከፈለሰፉት የሰብአዊነት(Rational Humanism)  ይልቅ ሳይንሳዊ „አርቆ-አሳቢነትን“(Scientific Rationalism) በማስቀደምና በበላይነት በመመካት ነው። ለምሳሌ ሜስትሮቪክ  „The Barbarian Temperament“ በሚለው እጅግ ግሩም መጽሀፉ ውስጥ የሚያረጋግጠው፣ በሃያኛውና በሃያአንደኛው ክፍለ ዘመን የምዕራቡ ዓለም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ቢራቀቀም፣ እንዲሁም ደግሞ የሊበራል ዲሞክራሲን አስፍኛለሁ ቢልም የተወሳሰቡ የጦር መሳሪያዎችን፣ የኬሚካልና የባዮሎጂ መርዞችን በመስራት በሚያስፈልገው ጊዜ ጠላቴ ነው በሚለው ላይ እንደሚበትንና፣ ብዙ ሺህ ህዝቦችን መጨረስ እንደሚችል ነው። ይህ ዐይነቱ ዕልቂት በፋሺዝም ዘመን በጉልህ የታየና የተረጋገጠ ነው። እንደዚህ ዐይነቱ ድርጊት እንደገና ሊከሰት የሚችልበትም ሁኔታ አለ። በኢራቅ ህዝብ ላይ የደረሰው ግፍ፣ በየቀኑ በአፍጋኒስታን ህዝብ ላይ የሚደርሰው ዕልቂት፣ ከአራት ዐመት በፊት ደግሞ አንድን አምባገነን ገዢ አዳክማለሁ ወይም ጥላለሁ ብሎ በዚያውም አሳቦ በሊቢያ ህዝብ ላይ የወረደው የቦንብ ናዳ የምዕራቡን ዕውነተኛ ገጽታ የሚያሳየን ነው። እንደዚሁም ከአራት ዐመት ጀምሮ በውጭ ኃይሎች በተጠነሰሰ ሴራና በገንዘብና በመሳሪያ በመደገፍ በሶሪያ ህዝብ ላይ የደረሰውና የሚደርሰው ዕልቂትና የታሪክ ቅርስ መፈራረስ በዘይት ሀብትና በመሳሪያ እንዲሁም በስልጣን በተመኩና ስልጣንን መባለጊያ ባደረጉ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች አማካይነት ነው። በአሜሪካ የኒዎ-ኮም(Neo-Com) አራማጆችም ሆነ በጠቅላላው የአሜሪካ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የሚሊታሪና የኢንተለጀንስ ኤሊት ዘንድ ያለው ስምምነት ዓለምን ለመግዛት ከተፈለገና፣ የሶስተኛው ዓለም አገሮችም በቴክኖሎጂና በሳይንስ ላይ የተመሰረተ የተረጋጋ ህብረተሰብ እንዳይገነቡ ከተፈለገ የተለያዩ ሰበቦችን በመፈለግ እርስ በርሳቸው ማጫረስ ነው የሚል ነው። ይህንንም በገሃድ ይናገራሉ። ከዚህም ስንነሳ ጠቅላላው የአሜሪካ የፖለቲካ ኤሊት ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ቢኖረው ኖሮና፣ ስልጣኔንም ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ የሚያስብ ቢሆን ኖሮ የፖለቲካ ስሌቱ የተለየ መሆን ነበረበት። በኢራቅ፣ በሊቢያና በሶሪያ አገሮች አምባገነን አገዛዞች ቢኖሩም፣ የእነዚህን አገዛዞች አስተሳሰብ መቀየርና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ማስፈን የሚቻለው ጥቂት ኃይሎች እንዲያምጹ እነሱን በመርዳት ሳይሆን የፖለቲካ ውይይት እንዲካሄድ በማድረግ ብቻ ነበር። በሌላ አነጋገር መሆን የነበረበት የፖለቲካ ስሌት እነዚህ አምባገነን አገዛዞች የሰለጠነ ፖለቲካ እንዲያራምዱ ማስተማር ነበር።  በሌላ ወገን ደግሞ በአንድ ሀብረተሰብ ውስጥ አምባገነናዊ አገዛዝ አለ ከተባለ ከውስጥ በሚደረግ ምሁራዊና ሳይንሳዊ ግፊት ብቻ ነው ሁኔታዎችን መለወጥ የሚቻለው። እንደምናየው የውጭ አገሮች ጣልቃገብነት በሶስቱም አገሮች የነበረውን ሁኔታ የበለጠውን አዘበራረቀው እንጂ መሻሻልን በማምጣት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍን አላደረገም። ስለሆነም በእንደዚህ ዐይነቱ ቅጥ ያጣ የቦምብ ውርጅብኝ እነዚህ አገሮች እንደገና በእግራቸው ሊቆሙ ወደማይችሉብት ሁኔታ ወስጥ መወርወር ቻሉ።  ሃምሳና ስድሳ ዐመታት ያህል የሰሯቸው ስራዎች፣ የገነቧቸው ከተማዎችና የመሰረቷቸው ህብረተሰቦች ከፈራረሱና ከተመሰቃቀሉ በኋላ እንደገና እነሱን መልሶ ለመገንባት እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። የህዝቡም አቅም የሚፈቅድና አስተሳሰቡም የተዳከመ ስለሆነ ህልሙ ከቀን ተቀን ችግር አልፎ ህብረተሰብአዊ ግንባታ ላይ ሊያተኩር አይችልም።፡  በሌላ ወገን ደግሞ የሰለጠንኩኝ ነኝ የሚለውን የምዕራቡን የካፒታሊስት የገዢ መደቦችና ጠቅላላውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖኢና የሚሊታሪ ኤሊት ተንኮል የማይረዱ የሶስተኛው ዓለም አገዛዞችና መንግስታት የማያስፈልግ ቀዳዳ በመስጠት ሁኔታውን ያባብሱታል። የኢራቅ፣ የሊቢያና የሶሪያ አገዛዞቹ ብልሆች ቢሆኑ ኖር ከውስጥ ተቃውሞ ሲነሳ ነገሩ እንዳይባባስ በውይይትና በስምምነት መፍታት በቻሉ ነበር። በፖለቲካ ጥበብ ያልተካኑት እነዚህ መሪዎች ግን ነገሩን ረገብ ለማድረግ ከመሯሯጥ ይልቅ የእልክ ፖለቲካ በመከተላቸው አገራቸው እንዲፈራርስና የብዙ መቶ ሺህ ሰው ህይወት እንዲጠፋ ለማድረግ በቁ።  በዚህም የተነሳ አንዳንድ ነፃ አውጭ ነኝ የሚሉ ድርጅቶች የማያስፈልግ እሳት እየጫሩ መጨረሻ ላይ ማቆም የማይቻል እሳት እየሆነ በመምጣት ታሪክን አውዳሚና ህዝብን ጨራሽ ለመሆን በቅቷል።

የዚህ ሁሉ ችግር ዋናው ምንጭ ምንድነው? ቢያንስ ባለፉት 70 ዐመታት የዓለምን ፖለቲካ የሚቆጣጠረው የምዕራቡ ዓለም ስለዲሞክራሲ ይዘትና አመለካከት ያለው አካሄድና ግንዛቤ ለየት ያለ መሆኑን ነው። የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጥያቄዎች ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ቢኖራቸውም ዕድገታቸውና ተቀባይነታቸው እንደየአገሮቹ ታሪክ፣ ህብረተሰብ አወቃቀርና የማቴሪያል ሁኔታና እንዲሁም ንቃት-ህሊና የሚወሰን ነው። ዲሞክራሲን ከላይ ወደ ታች ወይም በጠብመንጃ ኃይል የሚተከል ሳይሆን ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከንቃተ-ህሊና ዕድገት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነው። ችግሩ ግን የምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም አካሄድ ዲሞክራሲን በየአገሮች ውስጥ ለማስፈን ሳይሆን እንዴት አድርጌ አገሮችን አተረማምሳለሁ የሚል ነው። የዕድገት ሂደታቸውን አዛባለሁ የሚል ነው አካሄዱና የፖለቲካ ስሌቱ። የዚህ ሁሉ ችግር  ታላቁ ሺለር እንደሚለን፣ የሰው ልጅ ከአርስቲቶለስ ጀምሮ ዲሞክራሲ የሚለውን ፅንሰ-ሃሳብ ሰምቷል፤ ሆኖም ግን በመሰረቱ ከአረመኔ ባህርዩ አልተላቀቀም። ፍሪድርሽ ሺለር፣ ታሪክ ማለት ምን ማለት ነው፣ ለምንስ ዓላማ የዓለምን ታሪክ ማጥናት አለብን  በሚለው እጅግ ግሩም ስራው ውሰጥ የሰውን ልጅ እጅግ አስቸጋሪ ጉዞ ከመረመርና፣ የግሪክን ስልጣኔና የአውሮፓን የህብረተሰብ ታሪክ ካጠና በኋላ የደረሰበት ድምዳሜ፣ የሰው ልጅ ህብረተሰብአዊ ባህርይ እንዲኖረውና ታሪክን እንዲሰራ ከፈለገ የግዴታ ውጣ ውረድን ማሳለፍና ከፍተኛ የጭንቅላት ስራ መስራት እንዳለበት በጥብቅ ያሳስባል። ይሁንና ግን የሰው ልጅ ሙሉ በሙሉ ሰብአዊነትን ሊጎናፀፍ የሚችለው መንፈሱን ከልቡ ጋር ያገናኘ እንደሆነ ብቻ ነው ይላል።  ሺለር እንደዚህ ዐይነቱ ድምደማ ላይ የደረሰው በአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን በአውሮፓ ምድር ውስጥ በፕሮቴስታንትና በካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎች የተለኮሰውንና፣ ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች ዕልቂት ምክንያት የሆነውን ሰላሳ ዐመት ያህል የፈጀውን ጦርነት በሰፊው ከመረመረና፣ የመሪዎችን የተሳሳተ ፖለቲካ በጥልቀት ካጠና በኋላ ነው። በአስራአራተኛው ክፍለ-ዘመንም በጣሊያን ሰፍኖ የነበረውም ሁኔታ የሚያረጋግጠው የአሪስቶክራሲውንና የቀሳውስቱን ቅጥ ያጣ ፖለቲካና፣ ህዝቡም ራሱን በራሱ ማግኘት አቅቶት የሆነ ያልሆነውን የሚሰራበት ወቅት ነበር። አንድ ህዝቡን የሚያግባባ ቋንቋ ባለመኖሩም ለስራና ለሃሳብ ልውውጥ የማያመችና ለስልጣኔ እንቅፋት የሆነበት ወቅት ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳና በገዢ መደቦች ቅጥ ያጣ ኑሮ ህዝቡ በረሃብ፣ በድህነትና በልዩ ልዩ በሽታዎች ይሰቃይና ህይወቱ ይቀሰፍ ነበር። ይህንን በጥብቅ የተከታተለው ዳንቴ በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ህዝቡን የሚያግባባ ቋንቋ ይፈጥራል። ቀጥሎም  የአምላኮች ኮሜዲ በመባል የሚታወቀውን ትልቁን የሌትሬቸር ስራ በመጻፍ፣ አንድ ህዝብ እንዴት አድርጎ ከጨለማ ኑሮው ተላቆ የብርሃኑን ዓለም እንደሚጎናጸፍ ያመለክታል። ዳንቴ በዚህ ስራው ለተከታዩ ትውልድ መነሻ የሚሆን ትልቅ ስራ ሰርቶ ያልፋል። በመሆኑም ሬናሳንስ የሚባለው የግሪኩን ዕውቀት እንደገና ማግኘትና ከጊዜው ሁኔታ ጋር ማቀናጀት የተጀመረው እነዳንቴ በቀደዱት የብርሃን መንገድ አማካይነት ነው ማለት ይቻላል። ይህም ማለት ጭንቅላትን ለማደስና፣ ከኋላ ቀር አስተሳሰቦች ለመላቀቅ፣ ፍልስፍናን፣ ሳይንስን፣ ጥበብን፣ ግጥምንና አርክቴክቸርን የጭንቅላት ተሃድሶ መመሪያ ማድረግ ለአንድ ህዝብ ስልጣኔን መስራትና ተስማምቶ መኖር አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር የዳንቴ ስራዎችና በሬናሳንስ ዘመን ተግባራዊ የሆነው ስልጣኔ ያረጋግጣል።  ስለዚህም አንድ ግለሰብም ሆነ ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነቱን ሊቀዳጅ የሚችለውና፣ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስም ተፈጥሮን  በመቆጣጠር፣ ተፈጥሮ ውስጥ ያሉትን ነገሮች ለራሱ መጠቀሚያ በማድረግ ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊሽጋገር የሚችለው፣ የሬናሳንስ ወይም የግሪኩን ፍልስፍናና፣ በኋላ ደግሞ የጀርመን አይዲያሊስቶች፣ማለትም ሺለር፣ ጎተ፣ኸርደር፣ ዊንክልማንና፣ በተጨማሪም ላይብኒዝና ካንት ያዳበሩትን ፍልስፍናና የሳይንስ መሰረት መመሪያ ማድረግ የተቻለ እንደሆን ብቻ ነው።

ከዚህ ስንነሳ  ማቅረብ ያለብን ጥያቄ፣ በተለይም አገርን አስተዳድራለሁ የሚል አንድ መሪ ወይም አገዛዝ እንዴት አድርጎ ነው ጭንቅላቱን በአዲስ ዕውቀት በማነፅ ህብረተሰብአዊ ስምምነትና ስርዓት እንዲፈጠር የሚያደርገው? እንዴትስ አድርጎ ነው ቆንጆ አስተሳሰብን ከጭንቅላቱ ጋር በማዋሃድ የራሱን ጥቅም ሳያስቀድምና አድልዎን የፖለቲካ ዘይቤው ሳያደርግ፣ እንዲሁም ደግሞ የርዕዮተ-ዓለም ሰለባ ሳይሆን አገር ማስተዳደር የሚችለው? እንዴትስ ለስልጣኔና ለቆንጆ ስራዎች ታጥቆ ሊነሳ ይችላል? የሚሉትን ጥያቄዎች በዝርዝር እንመልከት።

በብዙዎቻችን ዕምነት ትምህርት ቤት የተማረና ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ኢኮኖሚክስም ሆነ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት አጠናቆ በማስትሬት ወይም በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቀ አገርን በስነስርዓት ማስተዳደርና፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በማድረግ ሚዛናዊ ዕድገት በማምጣት በስልጣኔ እንድትታወቅና ህዝቦቿም በደስታና በስምምነት እንዲኖሩ ሊያደርግ የሚችል ይመስለን ይሆናል። የሶክራተስን፣ የፕላቶንና፣ እንዲሁም በኋላ የተነሱትን፣ ሃይማኖትን ከፍልስፍና ጋር በማጣመር በአውሮፓ ምድር ስልጣኔ እንደገና እንዲያንሰራራ ከፍተኛ አስተዋፅዖ  ያደረጉትን የታላላቅ ቀሳውስት ስራዎች ስንመለከት፣ እንዲሁም ከአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን በኋላ ብቅ ብቅ ያሉትን ሳይንቲስቶችንና ለሰው ልጅ  ያስተላለፉትን  ዕውቀት ስንመረምር፣ በግጥምና በቲያትር እንዲሁም  የፖለቲካ ተዋንያንን አእምሮ በፍልስፍና ለመቅረጽ የታገሉትን እንደ ሺለር፣ ላይብኒዝና ካንት እንዲሁም ጎተን ስራዎች ስንመለከት እኛ ትምህርት ቤት ገብተን የተማርነው ትምህርት፣ ከነዚህ ጠቢባን ጋር በፍጹም የሚጣጣሙ አይደሉም። ከነዚህ የፍልስፍና ምሁራንና ሳይንቲስቶች ጽሁፎች መገንዘብና መማር የምንችለው በአንድ አገር ውስጥ ስልጣኔ ማምጣት ከተፈለገና ህዝቡም በስምምነት እንዲኖር ከተፈለገ የግዴታ የማያቋርጥ ትግል ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ነው። ስለዚህም ልክ እንደ ግሪክ ፈላስፋዎች ኋላ ላይ ብቅ ያሉት የአውሮፓ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች ለሌላ ነገር ሳይሆን ለአዕምሮና መንፈስ ከፍተኛ ቦታ በመስጠት ምርምራቸውን አካሄዱ።

በአጠቃላይ ሲታይ የሰው ልጅ አዕምሮ/መንፈስ ጥሩ ወይም መጥፎ አስተሳሰብ ይዞ ሊቀረጽ ይችላል። ጥሩ አስተዳደግ ካለውና አዕምሮው በጥሩ ዕውቀት የተገነባ ከሆነ ሰብአዊ ባህርይ ሊኖረውና ታሪክንም ሊሰራ ይችላል። በአንፃሩ ደግሞ አንድ ሰው በልጅነቱ በጥሩ ሁኔታ ካልተያዘና ጭንቅላቱ በጥሩ ዕውቀት ካልተገራ ሃሳቡና ተግባሩ ተንኮልን ማውጠንጠንና የታሪክን ሂደት ማጣመም ይሆናል። ይሁንና ግን አንድ ሰው ራሱን በራሱ ለማግኘት ከፈለገ ጭንቅላቱ በጥሩ ዕውቀት የተገራውም ሆነ የተዛባ አስተሳሰብ ያዳበረው በየጊዜው የጭንቅላት ጂምናስቲክ መስራት አለባቸው። የሰው ልጅ አስተሳሰብ የሚለዋወጥ በመሆኑ አርቆ አሳቢ የሆነውም ቢሆን አልፎ አልፎ ኢራሽናል ስለሚሆን ወደ መጥፎ ተግባር እንዳያመራ ከፈለገ ሰውነቱ ጂምናስቲክ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ጭንቅላቱም በስራ መወጠር አለበት። ስለዚህም አንድ ግለሰብም ሆነ የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ታሪክን ይሰሩ ዘንድ ራሳቸውን ከጥሩ ነገር ጋር ማገናኘት መቻል አለባቸው። ከአንድ አካባቢ የሚመጡ ግፊቶችን ለመቋቋም የሚችሉና በክርክር ለማሳመንና ቆንጆ ቆንጆ ነገሮች ተግባራዊ እንዲሆኑ የማያቋርጥ ትግል ማድረግ አለባቸው። ለዚህም ደግሞ በተከታታይ ደቀ-መዝሙራንን ማስለጠን በአውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ የተለመደ አሰራር ነበር። እንደኛ አገር ያለው ጋ ስንመጣ ተከታታይነት ያለው ሃሳብ ማዳበር ያለመቻልና ደቀ-መዝሙሮችንም አለማሰልጠንና ዝግጁም አለመሆን ነው። ከዚህ ስንነሳ  በዛሬው የግሎባል ካፒታሊዝም ዘመን አንድ ሰው ቀና አስተሳሰብ ቢኖረውምና ለስልጣኔ የቆመ ቢሆንም ባለው የላላና የሳሳ ምሁራዊ ኃይል ምክንያት ከውጭ የሚመጣውን ግፊት ሊቋቋም የማይችልበት ሁኔታ ይፈጠራል። በአካባቢውም ተንሸራታች ኃይሎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ሳይወድ በግድ ስልጣኔን የሚቀናቀነውን ሬል ፖለቲካ የሚባለውን እንዲቀበልና እንዲያራምድ ይገደዳል። ይህም ማለት ዕውነተኛ ዕውቀትና ሀቀኝነት በራሳቸው የሚበቁ መመዘኛዎች አይደሉም። ከውጭ የሚመጣውን ግፊት ለመቋቋም ዋናው መፍትሄ በራስ መተማመንና ለውጭ ኃይል መግቢያ ቀዳዳ አለመስጠት ነው። ስልጣንን የሚይዙ ኃይሎች የሚሰሩትን የሚያውቁና ለአንድ ዓላማ የተሰለፉና በአንድ ራዕይ የሚመሩ መሆን አለባቸው። ከዚህ በሻገር በአገር ውስጥ በተለያየ ዘርፍ ሊንቀሳቀስ የሚችል ሰፋ ያለ ምሁራዊ ኃይል እንዲሰለጥን አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ትችታዊ አመለካከት በዳበረበት አገርና፣ ምሁሩም ለውጭ ኃይል ሳይሆን ለአገሩ ህዝብ ብቻ ጥብቅና የቆመ መሆኑን በሚያረጋግጥበት አገርና ህዝቡንም የሚያስተምር ከሆነ የውጭ ኃይሎች እንደፈለጋቸው እየገቡ ሊያሳስቱና በአገዛዛዙ ላይ ግፊት ሊያደርጉ አይችሉም።

በሌላ ወገን ግን ዛሬ በሁላችንም ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር ሁላችንን ሊያስማማንና እንደመመሪያ ሊሆነን የሚችል ፍልስፍናና ራዕይ አለመኖሩ ነው። የፖለቲካ ድርጅቶች ነን የሚሉትም ሆነ ለመጽሄትም ሆነ ለድህረ-ገጾች በየጊዜው በተለያዩ አርዕስቶች ላይ የሚጽፉ ምሁራን እንደፈለጋቸው የሚጽፉ እንጂ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መለኪያን እንደመመርኮዢያ በማድረግ አይደለም ሃሳባቸውን ለመግለጽ የሚሞክሩት። ስለሆነም በየጊዜው የሚቀርቡት ጽሁፎች ከምን ተነስተው እንደሚጻፉ አይታወቅም። አቀራረቦችም በጣም ተደጋጋሚ ከመሆናቸው የተነሳ በአገራችን ምድር ያለውን የህዝባችንን የቀን ተቀን ኑሮ የሚዳስሱና የችግሮችንንም ዋና ምክንያቶች እንድንረዳና መፍትሄም እንድንፈልግ የሚጋብዙን አይደሉም።  ሁሉም የፈለገውን የሚጽፍ ከሆነና ራሱን እንደመለኪያ አድርጎ የሚቆጥር ከሆነ ደግሞ ይህ ዐይነቱ አካሄድ ሶፊስታዊ ነው የሚሆነው። ስለዚህም ነው ሶክረተስና ፕላቶ እንደዚህ ዐይነቱን አመለካከትና አካሄድ አጥብቀው የታገሉት። ምክንያቱም እያንዳንዱ ምሁር ራሱን እንደዋና መለኪያ የሚቆጥርና፣ ከሌላውም የተለየ መሆኑን ለማረጋግጥ የሚጥር ከሆነ አንድን ህዝብም ሆነ ታዳጊ ወጣት ሃሳቡን ሊሰበስብለትና እንደመመሪያም አድርጎ ሊወስደው የሚችለው ሳይንሳዊ ፈለግ አይኖረውም ማለት ነው። ስለሆነም ለአንድ አገርና ህዝብ እታገላለሁ የሚል ምሁር ኃላፊነቱ ተጨባጩን ሁኔታ በጥልቀትም ሆነ በስፋት መረዳት ብቻ ሳይሆን ችግሩ ሊቀረፍ የሚችልበትን ዘዴ መጠቆም ነው። ለዚህ ደግሞ አንድ የሚመራበት ግልጽ ፍልስፍናና ሳይንሳዊ የአሰራር ዘዴ እንዲኖረው ያስፈልጋል።  እኔ እስከማውቀው ድረስም በአውሮፓ የህብረተሰብ ትግል ታሪክ ውስጥ እያንዳንዱ ምሁር፣ ምሁር ነኝ ብሎ ዝም ብሎ ይታገል የነበረ ሳይሆን በምን ዐይነት ፍልስፍናና ነው በጊዜው የነበረውን ችግር መረዳትና  መፍትሄስ ማግኘት የሚቻለው ብሎ ነበር ራሱን ያስጭንቅ የነበረው። በዚህም ምክንያት ነው በአውሮፓ ምድር ውስጥ ፍልስፍናዊ አመለካከት ስር ሊሰድ የቻለውና፣ አገሮችም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የተወሳሰበ፣ የጠራና ግልጽ የሆነ ህብረተሰብ መገንባት የቻሉት።

ሌላው በአገራችንም ሆነ ውጭ አገር በኢትዮጵያዊ ኮሙኒቲ ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር አካዳሚክ ዕውቀትን ሰፋ ካለው ምሁራዊ ዕውቅት ነጥሎ ለማየት አለመቻል ነው። ሁሉም ሰው ትምህርትን ለመቅሰም የሚያስችለው ውስጣዊ ኢንተለጀንስ ቢኖረውም፣ ምሁራዊነትንና(Intellectualism)ሎጂካዊ አስተሳሰብን ሊጎናጸፍ የሚችለው ስርዓት ያለው ጥናት(systematic reading)ሲያካሂድና፣ በምድር ላይ የሚታየውን ነገር ለመረዳት ራሱን ሲያስጨንቅ ነው። ለዚህ ነው አብዛኛውን ጊዜ በንጹህ አካዳሚ ትምህርት የሰለጠኑ ሰዎች በምድር ላይ ያለውን ነገር በሚገባ ማንበብ የማይችሉትና የችግሩንም ዋና ምንጭ ለመረዳት የሚያስችል መሳሪያ የማይኖራቸው።  ስለሆነም አንድ ሰው በትምህርት ጎበዝ  ቢሆን እንኳ  የስልጣኔ ትርጉምን እስካልተረዳ ድረስና፣ ለስልጣኔና ለእኩልነትም ሽንጡን ገትሮ ሊታገል እስካልቻለ ድረስ ለህብረተሰብ ግንባታ የሚያደርገው አስትዋፅዖ ከቁጥር ውስጥ የሚገባ አይሆንም። አንድ ወጥ አስተሳሰብ ይዞ ያደገ በመሆኑም የአንድን ነገር ሂደት ከሁሉም አቅጣጫ የመመርመርና የማመዛዘን ኃይል ሊኖረው በፍጹም አይችልም። እንደዚህ ዐይነቱ ሰው ከራሱ ጥቅም ተሻግሮ የዕውነት ጠበቃ ሊሆን በፍጹም አይችልም። ስለሆነም አንድ ሰው በዚህ ወይም በዚያኛው ርዕዮተ-ዓለም እመራለሁ ቢልም እንኳ ይህ ማለት ግን ቀናና ጥሩ ሰው፣ ወይም ደግሞ ምሁራዊ ኃይል ያለውና ከተንኮል የጸዳ ነው ማለት አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ ርዕዮተ-ዓለም ሽፋን እንጂ የአንድን ሰው ምንነት መግልጫ አይደለም። አንድ ሰው ማርክሲስት ነኝ ወይም ሊበራል ነኝ  ወይም ደግሞ ይህንኛውን ወይም ያኛውን የፖለቲካ ዕምነትና ሃይማኖት እከተላለሁ ቢልም እነዚህ ሽፋኖች ድብቅ ዓላማውን የሚገልጹ ወይም ማንነቱን የሚያሳዩ አይደሉም። ወይም አንድ ሰው ሊበራል ነኝ ስላለ የተቀደሰ ዓላማ፣ ማርክሲስት ነኝ የሚለው ደግሞ የሰይጣን ዓላማ አለው ማለት አይደለም። እነዚህ ዐይነቱ ግለሰቦች በተናጠልም ሆነ በፓርቲ ደረጃ ተደራጅተው ለዚህ ወይም ለዚያኛው ርዕዮተ-ዓለም እንታገላለን ቢሉም የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ተግባራዊ ለማድረግ የሚታገሉባቸው መሳሪያዎች እንጂ በራሳቸው ዕውነተኛ ስልጣኔ አጎናጻፊ አይደሉም። እንዲያውም የዕውነተኛውን የስልጣኔ መንገድ የሚያደናቅፉና ወደ ሌላ ውዝግብ ውስጥ የሚከቱን ናቸው። ዛሬ በንጹህ የካፒታሊዝም ሊበራል ስርዓት ውስጥ እያለን እንኳ ዓለም ወደ ሰላም እያመራች አይደለችም፤ እንደምናየው የዓለም ህዝብም ብልጽግናን እያየ አይደለም። ጦርነትና ድህነት በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ የሀብት ዘረፋና በጥቂት ሰዎች እጅ የሀብት ክምችት የሰው ልጅ እጣ ሆነዋል። በየአገሮችም ውስጥ ህብረተሰብአዊ ውዝግብ የመከሰቱ ሁኔታ እያደገ በመምጣቱ የየመንግስታቱ ሚና ጦርነትን ዓለም አቀፋዊ ማድረግና ህዝብን ማሳሳትና አትኩሮውን ወደ ውጭ ማድረግ ነው።

እዚህ ላይ መቅረብ ያለበት ጥያቄ የምዕራቡ ካፒታሊዝም በአሸናፊነት ከወጣ በኋላ ለምንድነው አሁንም ቢሆን የሰው ልጅ ዕጣ ጦርነትና መፈናቀል፣ እንዲሁም መበዝበዝ የሆነው? ካፒታሊዝም ከፊዩዳሊዝም ጋር ሲወዳደር ተራማጅ ስርዓት ቢሆንምና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ምጥቀት ቢታይበትም፣ ከ17ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ ቀስ በቀስ እያለ የበላይነትን እየተቀዳጀ የመጣው ኢምፔሪሲስታዊ ወይም ሶፊስታዊ አስተሳሰብ የየመንግስታቱ መመሪያ ሆነ። በመሆኑም ከ13ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ሰብአዊነትን ሙሉ በሙሉ ለማስፈን የተደረገውን ትግልና አስተሳሰብ በመደምሰስ በነፃ ገበያ ስም የሚመራን፣ የአንድን ህዝብ አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ ወደ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ የሚቀይር ርዕዮተ-ዓለም በማዳበርና በማስፋፋት ካፒታሊዝም የበላይነትን ተቀዳጀ። የሰው ልጅም ኑሮ ንጹህ በንጹህ ኢኮኖሚያዊ ነው የሚለውን በማስፋፋት፣ የኑሮው ፍልስፍናም ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ሞራላዊና ስነ-ምግባራዊ እንዳይሆን ለማድረግ በቃ።  በዚህ ምክንያት በሰብአዊነት ፈንታ የብዝበዛ ስርዓት ሊፈጠር ቻለ። ይህ ሁኔታ ከሰላሳኛው ዐመት ጦርነት በኋላ በ1648 ዓ.ም በዌስት ፋልያ ላይ የየአገሮችን ነፃነት የሚያውቅ ስምምነት ሲደረስበትና ተቀባይነትን ሲያገኝ፣ በብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ውስጥ የብሄረተኝነት ስሜት ማየል ጀመረ። ከውስጥ የአገርን ኢኮኖሚ በሰፊ መሰረት መገንባትና ወደ ውጭ ደግሞ ያላደጉ አገሮችን የጥሬ ሃብት አምራች አገሮችና አቅራቢዎች የሚሆኑበትን ሁኔታ ታለመ። በተለያዩ አውሮፓ አገሮች መሀከል እሽቅድምደም በመጀመር የሶስተኛው ዓለም አገሮች በካፒታሊዝም ሎጂክ ውስጥ ሊገቡና እጣቸውም በዚያው የሚወሰን እንዲሆን ተደረገ።

ከዚህ አጭር ትንተናና በመነሳት ከአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በአሽናፊነት የወጣውንና እየተወሳሰበ የመጣውን ካፒታሊዝም በተለይም በአፍሪካ አህጉር ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖና እስካሁን ድረስም አላላቅቅ ያለንን የጭቆና፣ የብዝበዛና እንዲሁም የምስቅልቅል ሁኔታ የፈጠረብንን ስርዓት ጠጋ ብለን እንመልከት። ከአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ካፒታሊዝም የበላይነትን እየተቀዳጀ ሲመጣ የስልጣኔው ፕሮጀክት እየተደመሰሰና የዓለም አቀፍ ህብረተሰብ፣ በተለይም የአፍሪካ ሁኔታ እየተበላሽና እየተዘበራረቀ ይመጣል። የካፒታሊዝም ተልዕኮ  በዓለምአቀፍ ደረጃ ስልጣኔን ማስፋፋት ሳይሆን በጉልበት ላይና በስግብግብነት እንዲሁም በማጭበርበር ላይ በመመርኮዝ በተለይም የአፍሪካን አህጉር ንጹህ የጥሬ ሀብት አምራችና አቅራቢ ማድረግ ነበር ዋናው ፕሮጀክቱ። በመጀመሪያ  በ15ኛው ክፍለ-ዘመን የባርያን ንግድ ማስፋፋት፣ በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ደግሞ የቅኝ ግዛት አስተዳደር በመመስረት ከውስጥ ቀስ በቀስ እያለ የሚያድግ ስርዓት እንዳይፈጠር ሁኔታውን ያዘባራርቃል። በተለይም በቅኝ ግዛት ዘመን የተቋቋሙት አስተዳደሮች ከቅኝ ገዢዎች አገሮች ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ወደ ውስጥ የስራ ክፍፍል እንዳይዳብርና የውስጥ ገበያም እንዳይስፋፋ እንቅፋት ይፈጥራል። ወደ ቅኝ ግዛትነት የተለወጡ አገሮችም የተወሰኑ የጥሬ-ሀብትና የእርሻ ምርት ማውጣትና ማምረት፣ እንዲሁም ውጤቱንም ወደ ውጭ መላክ ስለነበረባቸው በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የስራ ክፍፍል በማዳበር ወደ ውስጥ ሰፋ ያለ ገበያ ለመገንባት እንዳይችሉ ታገዱ። ይህ ሁኔታ በራሱ መንደሮችን፣ ትናንሽና ትላልቅ ከተማዎችን በስነስርዓት በመገንባት ወደ ህብረተሰብ እንዳይለወጡ እንቅፋት ሆነባቸው። የተተከሉትም የባቡር ሃዲዶች የጥሬ-ሀብት የሚወጣባቸውን ቦታዎች ከወደብ ጋር ማገናኘት ሰለነበር ወደ ውስጥ ህዝቡን የሚያስተሳስር የመመላለሻ መንገድና የባቡር ሃዲድ እንዳይሰራ ታገደ። በዚህም ምክንያት ህብረተሰብዊ ውህደት እንዳይፈጠር መሰረት በመጣል፣ በአንድ አገር ውስጥ ጎሳዎች በጎሳ ደረጃ ሊደራጁ የሚችሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታና፣ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ እንቅፋት የሆነን እንደ ስርዓት ሊቆጠር የማይችል ሁኔታን በመፍጠር የሰዎች አትኩሮ ጠባብ እንዲሆን ለማድረግ በቃ።

ከፖለቲካ ነፃነት „መቀዳጀት“ ከ50ኛዎቹ ዐመታት መጨረሻና ከ60ሳዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ የብዙ አፍሪካ አገሮች ዕድል በሌላና በረቀቀ መልክ ህብረተሰብአዊ ዝብርቅርቅነት የሚኖርበትና ብዝበዛው የሚቀጥልበት ሁኔታ በመፍጠር በየጊዜው የሚነሱ አገዛዞች አስተሳሰብ በትናንሽ ነገሮች እንዲጠመዱ ተገደዱ። አስተሳሰባቸው ብሄራዊ አጀንዳ እንዳይኖረው ተቆለፈ። የተለየ አስተሳሰብ ያላቸውና ወደ ህብረ-ብሄር ግንባታ እንሸጋገራለን ያሉትን ደግሞ በመንግስት ግልበጣ አማካይነት በመጣል የአገዛዝ አለመረጋጋትና አለመተማመን ሊፈጠር ቻለ። ስልጣን ላይ የሚወጣው መሪ ከዚህ ወይም ከዚያኛው የምዕራብ አገር መንግስታት ጋር በማበርና ታዛዥ በመሆን አገሩን ሊገነባ እንዳይችል ተደረገ። በዚህ ላይ ደግሞ  ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠሩት ኢንስቲቱሽኖችና፣ በአዲስ መልክ የተከሰተው የኃይል አሰላለፍ የብዙ አፍሪካ አገሮችን የወደፊት ዕድል የሚወስኑ ነበሩ። ከ1945 ዓ.ም በኋላ ሁለት ዐይነት የኃይል አሰላለፎች ቢከሰቱም፣ በመሰረቱ ግን በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚመራው የካፒታሊስቱ ጎራ ነበር/ነውም ዓለምአቀፍ ኢንስቲቱሹኖችን በመቆጣጠር የአብዛኛዎቹን የሶስተኛው ዓለም አገሮችን፣ በተለይም ደግሞ የአፍሪካን ህዝብ ዕድል ይወስን የነበረውና ዛሬም የሚወስነው። በዚህ ላይ ደግሞ ዶላር ዋናው ዓለምአቀፋዊ የንግድ መገበያያና የሀብት ማከማቻ ገንዝብ በመሆኑ አብዛኛዎቹ አገሮች የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት ሲሉ የግዴታ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴያቸውን በተወሰነ መስክ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ተገደዱ። በዚህም ምክንያት የአገር ውስጥ ገበያን ማዳበር ባለመቻላቸው በገንዘብና በምርት፣ እንዲሁም በገንዘብ አማካይነት የሚካሄደው የንግድ ልውውጥ ውስን በመሆኑ፣ የየአገሮቹ የገንዘብ ኃይል ሊዳከም በቃ። በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ ሊሆንና ተቀባይነትም ሊያገኝ የማይችል ሆነ። በሌላ አነጋገር፣ የአንድ አገር የገንዘብ ጥንካሬ ሊወሰን የሚችለው ወደ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ ሲዳብርና፣ በየኢኮኖሚ መስኮችም መሀከል የንግድ ልውውጥ ሲኖርና፣ በዚህም አማካይነት በኢኮኖሚው ውስጥ የሚሽከረከረው ገንዘብ ፍጥነቱ ሲጨምር ነው። ከዚህም በላይ አንድ አገር ገንዘቧ ጠንካራና ዓለምአቀፋዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ከተፈለገ ወደ ውጭ የምትልከው ምርት በፋብሪካ የተፈበረከና ያለቀለት ምርት መሆን አለበት። በሌላ አነጋገር፣ አንድ አገር ለዓለም ገበያ የምታቀርበው ምርት የእርሻ ምርት ውጤት ወይም ያልተፈበረከ የጥሬ ሀብት ብቻ ከሆነ ገንዘቧ ደካማ ይሆናል፤ ተቀባይነትም አያገኝም።  ከዚህ አጭር ትንተና ስንነሳ የካፒታሊዝም ውስጣዊ ሎጂክና እንቅስቃሴን መገንዘቡ ከባድ አይሆንም። ወደ ሌሎች ነገሮችም ስንመጣ አካሄዱ ለየት ያለ ቢመስልም ዋናው ባህርዩ ግን የበላይነትን(Dominanz) መቀዳጀት ነው። ይህም ማለት እያንዳንዱ የአፍሪካ አገር ኢትዮጵያንም ጨምሮ እንደ ነፃ አገር መታየት የለባቸውም። በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካርና በራሱ የሚተማመን ህብረተሰብ መገንባት የለባቸውም። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ወደ ውስጥ ህብረተሰብአዊ ስምምነትና ውህደትን ስለሚያመቻችና ብሄራዊ ስሜትን ስለሚያጠናክር የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠርና ግፊት በማድረግ የየመንግስታቱ አጀንዳ አትኮሮአቸው በትናንሽ ነገር ላይ መጠመድ አለበት። እንዲያም ሲል ወደ ጦርነት እንዲያመራ ይደረጋል።

በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት መፈጸሚያ በኋላ ሙሉ በሙሉ በአሽናፊነት የወጣው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ተልዕኮው ህብረተሰቦችን ማዘበራረቅና፣ በህብረተሰቦች ውስጥ ግጭት እንዲፈጠር ሁኔታውን ማመቻቸት ሆነ ተግባሩ። ለዚህ ደግሞ የትምህርት መስኩ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል። የአንድን ሰው አእምሮ ስትቆጣጠረውና በገንዘብ ስትገዛው የህብረተሰቡንም አቅጣጫ ታዛንፋለህ። የስልጣኔውን መንገድ ሁሉ ታጨልምበታለህ። አብዛኛው ህዝብ የማሰብ ኃይሉ ሲዳከም በቀላሉ ወደ ባርነት ይለወጣል፤ በራሱ ላይ ዕምነት አይኖረውም። የዓለም ገበያና የዓለም ንግድ እንዲሁም ለዚህ እንዲያመች ተብሎ የረቀቀው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ዋናው ዓላማቸው የብዙ አፍሪካ ህዝቦችን ዕድል በዚህ ዐይነት የካፒታሊስት ሎጂክ ውስጥ እንዲሽከረከሩ በማድረግ ለዝንተዓለም ባርያ አድርጎ ማስቀረት ነው። ለምሳሌ ለትምህርት ቤትና ለዩኒቨርሲቲ ተብሎ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተዘጋጀውን የኢኮኖሚክስ መማሪያ መጽሀፎችን ለተመለከተ፣ እንደዚህ ዐይነቱ ተቀባይነት ያገኘ(Conventionalism or normative positivism) የመማሪያ መጽሀፍ በራሱ አርቀን እንዳናስብና የዕውነተኛውን ስልጣኔን ትርጉም እንዳንረዳ ሊያደርገን የቻለ ነው። ዕድገትንና ስልጣኔን ከህብረተሰብ አወቃቀርና ከታሪክ አንፃር፣ እንዲሁም የተለያዩ አገሮችን ልምድ መሰረት አድርጎ እንደመነሻና እንደመማሪያ ከመወሰድ ይልቅ፣ ርዕዮተ-ዓለምንና የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍል ጥቅሞችን የሚያንፀባርቅ ትምህርት በመማር የታሪክ ወንጀል ተሰራ፤ እየተሰራም ነው። የሳይንስና የቴክኖሎጂን ዕድገት ስንመለከት ግን ንፁህ የምርምርና የጭንቅላት ውጤት መሆናቸውን መገንዘብ እንችላለን። ኢኮኖሚክስ ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው ከፊዚክስ፣ ከኬሚስትሪና ከባዮሎጂ ጋር ሲያያዝ ብቻ ነው። ይህንን መሰረተ-ሃሳብ ያላካተተ የኢኮኖሚክስ ትምህርት የመጨረሻ መጨረሻ አገሮችን መቀመቅ ውስጥ ነው የሚከታቸው። ለምሳሌ በኢኮኖሚክስ ታሪክ ውስጥ መርካንትሊዝም፣ ፊዚዮክራሲ፣ በእነ አዳም ስሚዝና ፔቲ ኢንዲሁም ሪካርዶ የሚወከለው ክላሲካል ኢኮኖሚክስ፣ ይህንን እያረመ ወይም እያስተካከለ የወጣው የማርክሲስት ኢኮኖሚክስ፣ ከዚያ በኋላ ማርክሲዝምን በመቃወም የወጣው የማርጂናሊስት ወይም የኒዎ-ክላሲክል፣ ዛሬ ደግሞ ኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ ተብሎ የሚታወቀው፣ በእነ ሹምፔተር የሚወከለው ኢቮሉሺናሪ ኢኮኖሚክስ፣ በቬብለን ቶርስታይን የሚወከለው የኢንስቲቱሽን ኢኮኖሚክስ፣ ብዙ የምዕራብ አውሮፓ ኢኮኖሚዎች የተገነቡበት፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ፊዚካል ኢኮኖሚክስ እየተባለ የሚታወቀው በጣም ጠቃሚ ዕውቀት፣ እነዚህ ሁሉ የኢኮኖሚክስ ዘርፎች ናቸው። ተማሪው ይህንን ሁሉ እንዳያውቅና፣ በተለይም ምዕራብ አውሮፓ የአደገበትን ምስጢር እንዳይገነዘብ በሃያኛው ክፍል-ዘመን በእነሳሙኤልሰንና በሌሎች የተደረሱት እንደ መመሪያ በመውሰድና እነሱን በመሸምደድ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠር የአፍሪካ ምሁራን ሊሳሳቱና ለየአገራቾቻው መቆርቆዝና ድህነት እንደ ዋና ምክንያት ሊሆኑ  በቅተዋል። ዛሬ በአፍሪካ ውስጥ ለሚታየው መዝረክረክና ድህነት ዋናው ምክንያት ፖሊሲ አውጭዎቹ ሳይሆኑ በመሰረቱ በርዕዮተ-ዓለም ላይ የተመሰረተው ለምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም የሚያመቸው የኢኮኖሚክስ ትምህርት እንደመመሪያ በመወሰዱ ነው። ከዚህም በላይ በየአገሮቹ የሰፈነው መንግስታዊ አወቃቀርና የፖለቲካ ኤሊት ለዕድገትና ለስልጣኔ ሽንጡን ገትሮ እንዳይታገል በመኮላሸቱ በቀላሉ የዕድገትን ፈለግ ማጣመም ተቻለ። ኒዎ-ሊበራሎች የበላይነትን በመቀዳጀት ከዩኒቨርሲቲ አልፈው ኢንስቲቱሽኖችን ሁሉ በመቆጣጠር አብዛኛው ተማሪ ዐይኑን እንዳይከፍትና፣ የዕውነተኛ ዕድገትንና ስልጣኔን ትርጉም እንዳይረዳ ሊደረግ በቃ። ለዚህም ነው ሶክራተስ፣ ፕላቶና የእነሱን ፈለግ ይዘው የተነሱት ምሁራን ተቀባይነት ያገኘን ዕውቀት መሳይ ነገር አጥብቀው የታገሉት። ምክንያቱም ተቀባይነት ያገኘ ነገር ሁሉ ካለንበት ቦታ ርቀን እንዳንሄድ ያደርገናል። በማሰብ ኃይልና በኮመን ሴንስ ልንፈታ የምንችላቸውን ችግሮች እንዳንፈታ መንገዱን ሁሉ ይዘጋብናልና።

ዛሬ  አገራችንና የሌሎች አፍሪካ አገሮችን ያሉበትን ሁኔታ ለመረዳትና ምክንያቱንም ለመገንዘብ የምንፈልግ ከሆነ ከሞላ ጎደል የላይኛውን ትንተና ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያለብን ይመስለኛል። ሌላው ችግራችን ደግሞ የኛንም ሆነ የሌሎች አፍሪካ አገሮችን የተወሳሰበ ችግር ለመረዳት በሚሞከርበት ጊዜ አውሮፓውያን እስከ አስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የተጓዙበትን የምሁር ውይይትና ክርክር እንደልምድና ትምህርት አድርገን ለመውሰድ አንቃጣም። ያም ሆነ ይህ በአውሮፓ የህብረተሰህብ አወቃቀርና በአፍሪካ አገሮች የህብረተሰብ ሂደት መሀከል ያለውን ልዩነት ትንሽም ቢሆን ጠጋ ብለን እንመልከት። ይህ ዐይነቱ ግምገማ ከሞላ ጎደል ዛሬ ብዙ አፍሪካ አገሮች ለምን በዚህ ዐይነቱ የተመሰቃቀለና ደካማ የሆነ የኢኮኖሚ ክንዋኔ ውስጥ ለመገኘት እንደተገደዱ የተወሰነ ግንዛቤ ሊሰጥን የሚችል ይመስለኛል። አንደኛ፣ የብዙ አፍሪካ አገሮች ህብረተሰብ አወቃቀር ከብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ጋር ሲነፃፀር ይለያል። አበዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች በፊዩዳሊዝም ስርዓት ያላለፉ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አወሮፓው ህብረተሰብ የርዕዮተ-ዓለም ግጭት አልተካሄደባቸውም። ሁለተኛ፣ ብዙ የአፍሪካ ህብረተሰቦች ከሌላው ዓለም ጋር የነበራቸው በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ግኑኝነት እጅግ የላላ ነበር። ለምሳሌ የግሪክ ስልጣኔ በአረቦችና በአይሁዲዎች አማካይነት ከግሪክ ቋንቋ ወደ ላቲን እየተተረጎመ ወደ አውሮፓ ሲገባና ሲስፋፋ፣ ብዙ አፍሪካ አገሮች ይህ ዕድል አላጋጠማቸውም። ሶሰተኛ፣ የብዙ ምዕራብ አውሮፓ የህብረተሰብ አወቃቀር በሩቅ ንግድ አማካይነት ሲበለጽግና ውስጠ-ኃይል በማግኘት ወደ ተሻለ የህብረተሰብ አወቃቃር ሲሸጋገር፣ አብዛኛዎቹ አፍሪካ አገሮች ይህ ዐይነቱ ዕድል አላጋጠማቸውም። አራተኛ፣ በአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን በባርያ ንግድና፣ በአስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ደግሞ በቅኝ አገዛዝ አማካይነት ህብረተሰብአዊ አወቃቀራቸው ይበላሻል። በማበብ ላይ የነበረው የስራ ክፍፍል ይኮላሻል። አብዛኛዎቹ አፍሪካ አገሮች ለምዕራብ አውሮፓ ጥሬ-ሀብት አቅራቢ ብቻ እንዲሆኑ ይፈረድባቸዋል። ለዚህም የየመንግስታቱ አወቃቀር ወደ ውስጥ ዕድገትንና ስልጣኔን እንዳያመጣ ሆኖ ይዘጋጃል። አምስተኛ፣ ከቅኝ አገዛዝ መላቀቅ በኋላ በዓለም አቀፍ ላይ አዲስ የተፈጠረው የኃይል አሰላለፍ የአፍሪካን ዕድገት የሚጻረር ነበር። ስደስተኛ፣ ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓው ምድር ፍጻሜ ያገኘው ጦርነት ወደ አፍሪካና ወደ ሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች ይሸጋገራል። አንጎላንንና ሞዛቢክን፣ ከብዙ ዐመታት ጀምሮ በኮንጎ/ዛየርና በማዕከለኛው አፍሪካ የሚካሄደውን ጦርነት ስንመረመር፣ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ጦርነት ፍጻሜን ሲያገኝና የተደላደለ ህብረተሰብ ሲመሰርቱ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ግን በጦርነት መድማት ነበረባቸው፤ አለባቸውም። አውሮፓውያን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ሲበለጽጉ አፍሪካ በጦርነት መድማት አለባት፤ ህዝቦቿም የሰከነና የሰለጠነ ኑሮ መኖር የለባቸውም፤ መዋከብና መበዝበዝ ዕጣቸው መሆን አለብት። ሰባተኛ፣ ለዚህ ደግሞ ፍልስፍና አልባ የሆኑ መሪዎች እንደ አሻንጉሊት በየቦታው መቀመጥ ቻሉ። በተዋቀራላቸው የስለላ መሳሪያ፣ በሰለጠነላቸው ወታደርና የፖሊስ ሰራዊት አማካይነት ማንኛውንም ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ማፈንና ብልጽግና እንዳይመጣ ማድረግ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጠረላቸው። በአገራችንና በሌሎች አፍሪካ አገሮች የተቋቋሙት የወታደር ተቋሞች፣ የስለላ መዋቅሮችና የፖሊስ ሰራዊት በመሰረቱ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረውን ኃይል አሰላለፍ የሚያንፀባርቁና፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዘረጋውን የአገዛዝ ሰንሰለት አጋዦችና ታዛዦች እንጂ ከየህብረተሰቦቻቸው ፍላጎት አንፃር ከታች ወደ ላይ ቀስ በቀስ እየተደራጁና ሲቪክ የሆነ ባህርይ እንዲኖራቸው ሆነው የሰለጠኑ አይደሉም። በዚህም ምክንያት በብዙ የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያንም ጨምሮ የሲቪልና የወታደሩ ቢሮክራቶች እጅግ አረመኔና ህብረተሰብአቸውን ለውጭ ኃይሎች አሳልፈው እንዲሰጡ የተዘጋጁ ናቸው ማለት ይቻላል።

በዘመነ-ግሎባላይዜሽን ሁኔታው ምስቅልቅልና ለብዙ ምሁራንና የፖለቲካ ተዋናዮች ግልጽ ያልሆነ ሁኔታ የተፈጠረበት ዘመንን እንመለከታለን። በተለይም ከ1989 ዓ.ም በኋላ የተፈጠረው አዲስ ሁኔታ ካፒታሊዝም ለጊዜውም ቢሆን በአሸናፊነት እንዲወጣና ሁሉም አገሮች ቢያንስ በመርህ ደረጃ የነጻ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲን እንዲከተሉ አስገደዳቸው። አብዛኛዎቹ አገሮች ወደ ውስጥ ከማተኮር ይልቅ ይበልጥ ወደ ውጭ በማተኮር በማኑፋክቱር ላይ የተመረኮዘ ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ እንዳይገነቡና እንዳያስፋፉ አገዳቸው። አብዛኛዎች አገሮች በተለይም  የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተልና ተግባራዊ በማድረግ ከአገርና ከህብረተሰብ ግንባታ ይልቅ የአገልግሎት መስኩ እንዲስፋፋ ሁኔታዎችን አመቻቹ። ስለሆነም ከዚህ ጋር ተያይዞ የውጭ ኤክስፐርቶች በየአገሩ በመሰማራትና በየመንግስታቱ ላይ ግፊት በማድረግ የተዛባና ሀብት ሊፈጥር የማይችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ አደረጉ። ይህ ዐይነቱ አካሄድ በአንድ አገር ውስጥ ያልተመጣጠነ ዕድገትና የሀብት ፍሰት በማስከተል በየአገሮች እየተሰፋፋ ለመጣው ድህነት ዋና ምክንያት ሆነ። በዚህ መልክ ግሎባል ካፒታሊዝም በልዩ ልዩ መስኮች በመሰማራትና በየመንግስታቱ ላይ ግፊት በማድረግ መንግስታቶችን የበለጠ ከህዝቦቻቸው እንዲርቁና ወደ ጨቋኝነት እንዲለወጡ ሁኔታው ገፋፋቸው። በዚህም መሰረት አገር፣ ህብረ-ብሄር(Nation-State)፣ ብሄራዊ ኢኮኖሚና ብሄራዊ ነፃነት፣ እንዲሁም የመንግስት  ትርጉምና ሚና በአንድ አገር ዕድገት ውስጥ የሚኖረው መሰረታዊ ተግባር፣ ህብረተሰብአዊ እሴትና ህብረተሰቡን ሊያቅፍና የመፍጠር ኃይሉን ሊያዳብር የሚችል ብሄራዊ ባህል፣ የግለሰብ ነፃነትና ሚና፣ የሚያድጉ ልጆች ሁኔታና እንክብካቤ፣ እንዲሁም ጤናማ የሆነ የቤተሰብ ምስረታና፣ ይህም የአንድ አገር ምሰሶ መሆን… ወዘተ… ወዘተ. ቦታና ትርጉም እንዳይኖራቸው ተደረገ። አንድ አገር ማንም እየመጣ የሚፈነጭበትና ከየመንግስታቱ ጋር በመቆላለፍና በመባልግ ሀብት የሚዘርፍና ህብረተሰባዊ እሴቶች የሚበጣጠሱበት መድረክ ሆነ። ይህ ሁኔታ በየአገሮች ውስጥ የሴተኛ አዳሪዎችን መስፋፋት፣ ህጻናትን ማባለግና ከሰው ልጅ ጤናማና ተፈጥሮአዊ ኖርም የራቁ ግኑኝነነቶች በመፍጠርና በማስፋፋት ህዝቡ ስለ ህብረተሰብ ትርጉም ደንታ እንዳይኖረው ተደረገ። ስለሆነም በብዙ የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያንም ጨምሮ፣ እነዚህ አገሮች እንደ አገሮች ቢታዩም፣ ህዝቦች ግን ህበረተሰብአዊ ንቃተ-ህሊና(Social Consciousness) እንዳይኖራቸው ተደረጉ።

ዛሬ በብዙ የአፍሪካ አገሮች አምባገነንነት ሰፍኗል፤ ዲሞክራሲ የለም እየተባለ የሚለፈፈውና የሚወደሰው ይህንን ውስብስቡን የዓለም ሁኔታ ለመመርመር ካለመቻል የተነሳ ይመስለኛል። የብዙ የአፍሪካ አገሮች ችግር ፕላቶ እንደሚለን ዕውነትን ከውሸት ለመለየት የሚያስችል ዕውቀት ለመስፋፋት አለመቻሉና፣ ዕውነተኛ ሁለ-ገብ የሆነ ምሁራዊ እንቅስቃሴ አለመኖሩ ነው። ሰፋ ያለ የዳበረ ምሁራዊ እንቅስቃሴና፣ በሁሉም አቅጣጫ የሚገለጽ ብሄራዊ ባህርይ ያለው ምሁራዊ እንቅስቃሴ በሌለበት አገር የውጭ ኃይሎች ከውስጡ ኃይል ጋር በማበር የጨለማውን ዘመን ያራዝማሉ። የጭቆና መሳሪያዎችን እየላኩና እያስታጠቁ የጸጥታ ኃይል በሚሉት አማካይነት አንድ ህብረተሰብ ተዋክቦ እንዲኖር ያደርጋሉ። ህብረተሰቦች ታሪክ የሚሰራባቸው፣ ህዝብ ተረጋግቶ እንዲኖር ነገሮች በስነስርዓት ከሚዘጋጅባቸው ይልቅ ወደጦርነት አውድማ እንዲቀየሩ ይገደዳሉ። ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ  ሀብትን በማይፈጥር በተራ ሸቀጣ ሸቀጥ አማካይነት ህብረተሰብን ማዋከቡ በከፍተኛ ፍጥነት መካሄድ አለበት። እንደ አገራችን ባሉት ደግሞ ከሌሎች ነገሮች ጋር ተደምሮ የኮሞዲቲ ገበያ የሚባል በማቋቋም ሰፊው ገበሬ አመለካከቱን ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲያዞር በማድረግ ለዓለም ገበያ የቡናና የሰሊጥ ምርት አቅራቢ፣  ለውስጥ ገዢዎች ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንዲሆን ተደርጓል። ከውጭ ሰልጥነው የገቡትና ዝናን ያገኙት አዲሶቹ ኤሊቶች ዋና ተግባር ህዝባችንን ወደ ባርነት መለወጥ ነው። ይህ በግሎባልይዜሽን ዘመን ንቃተ-ህሊናቸው የደከሙ ህብረተሰቦችንና፣ በኒዎ-ሊበራል ርዕዮተ-ዓለም የሰለጠኑ ተውረግራጊዎችን እየፈለጉና እያሰለጠኑ በአንድ በኩል ህብረተሰቦች ርካሽና የቆሻሻ ፍጆታ ዕቃ መጣያ ሆነዋል፤ በሌላ ወገን ደግሞ አብዛኛው ህዝብ ብዙ ቀናትና ወራት የለፋበትን የቡናም ሆነ የሰሊጥ ምርት በርካሽ ዋጋ እንዲሸጥ በመገደድ ወደ ባርነት እንዲለወጥ ተደርጓል። በዚህ መልክ ባለፈው ሃያ አራት ዐመታት በህብረተሰብአችን ውስጥ አዲስ ድህነትን ፈልፋይና የአገራችንን አቅጣጫና ዕድገቷን ያጣመመ እጅግ አደገኛ የህብረተሰብ ክፍል ብቅ ሊል ችሏል። ይህ የህብረተሰብ ክፍል በዓለም አቀፍ ደረጃ በተዋቀረው የፊናንስ ሰንሰልት ውስጥ በመካተት በካፒታሊስት አገሮች የሚካሂደውን የሀብት ክምችት(Capital Accumulation) አጋዥ ሆኗል። ወደ ውስጥ ደግሞ የህብረተሰቡን ሀብት በመምጠጥና የተንደላቀቀ ኑሮ በመኖር ለከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ምክንያት ሆኗል። በራሱ ዓለም ውስጥ የሚኖር፣ ዐይን ያወጣና ህብረተሰቡም ወደ ጥፋት መንገድ ሲያመራ ማየት የማይችልና፣ ማየት ቢችል እንኳ ደንታ የሌለው የህብረተሰብ ክፍል ሊሆን በቅቷል። ፍልስፍና አልባ የሆነና ህብረተሰብአዊ ኖርሞችን መከተል የማይችል፣ ወይም ህብረተሰቡ በተወሰኑ ኖርሞች ላይ እንዲተዳደር ማድረግ የማይችል ከሰፊው ኢትዮጵያ ህዝብ ተነጥሎ የሚኖር፣ የራሱ መዝናኛና ልዩ የመገበያያ ቦታ(Shoping Center) ያለው  ኃይል ብቅ ብሏል። በዚህ መልክ ብቻ ነው የዓለም አቀፍ ካፒታሊዝም ብዙ የሶስተኛውን ዓለም አገሮችን የሚቆጣጠረውና ለመቆጣጠር የሚችለው።

ዛሬ በአገራችን ምድር የሰፈነውን ፍልስፍና አልባ ፖለቲካና ህዝብን ማዋከብ ከዚህ ቀላል ሁኔታ በመነሳት ነው መመርመር መቻል ያለብን። በቀላል የሊበራል ዲሞክራሲና የነፃ ገበያ ፎርሙላ፣ ወይም በአምባገነን ስርዓት መስፈንና በዲሞክራሲ እጦት የህብረተሰብአችንን የተወሳሰበ ችግር ለመገንዘብ አንችልም። የአገዛዙ ችግር የፖለቲካ ፍልስፍና አልባነት ችግር ነው ስል ምን ማለቴ ነው? በመጀመሪያ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር አለ። ይኸውም ወያኔ/ኢህአዴግ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ውስጥ የፈለቀና የፊዩዳሊዝምና እጅግ የተዘበራረቀው ካፒታሊዝም ውጤት አገዛዝ ነው። በተለይም በአርባዎቹ መጨረሻና በሃምሳዎቹ መጀመሪያ ላይ የተተከሉት በፍጆታ ምርትና አጠቃቀም ላይ የተመሰረቱት፣ ግን ደግሞ የውስጥ ገበያን ማስፋፋትና ማዳበር የማይችሉት ኢንዱስትሪዎች ለዛሬው አገዛዝም ሆነ ቀደም ብለው ለነበሩት ቢሮክራሲያዊ መዋቅሮች የባህርይና የአሰራር መሰረቶች ሆነዋል። ከአዋቂነትና ከብልህነት፣ ከጥበብና ከቆንጆ ቆንጆ ስራዎች ይልቅ ተንኮለኛ፣  ዳተኛና አራዳ እንዲሁም አገር ከፋፋይ  ሆነው ብቅ ሊሉ የቻሉት አርቆ ባለማሰብ በተዋቀረው በተቆራረጠና ህብረተሰብአዊ መተሳሰርን በማያጠናክር የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ነው።  የዛሬውን የወያኔ አገዛዝ  ከተቀሩት ለየት የሚያደርገው የብሄረሰብን ወይም የጎሰኝነትን ጥያቄ አንግቦ በመነሳቱና፣ የተለየም መሆኑን ለማረጋገጥ መሞከሩ ብቻ ነው። የጎሰኝነትን ወይም የብሄረሰብ ፖለቲካንም የሚጠቀመ ለከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው እንጂ ለየብሄረሰቦቹ ነፃ መውጣት በማሰብ አይደለም። ይህ ዐይነቱ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ በምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም የሚደገፍ ሲሆን፣ በተለይም እንግሊዝና ሌሎች የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮች ደጋፊዎች ናቸው። ስለሆነም ከራሱ ባሻገር ማሰብ የማይችለው አገዛዝ ለስልጣንና ለሀብት ክምችት በማለት ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር የዘጠና ሚሊዮንን ህዝብ ዕድል ማጨለም ችሏል። የባርነቱንና የድህነቱን፣ እንዲሁም የጥገኝነቱን ዘመን ለብዙ መቶ ዐመታት ማራዘም ችሏል። ሁኔታው የባሰ እንዲመሰቃቀልና መጠገኛና መፍቻ መንገድም እንዳይገኝ ማድረግ ችሏል። በተለይም  የአገዛዙ መሪዎች ያደጉበት ሁኔታና ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ጋር ለመቀላቀል አለመቻል የተለዩ መሆናቸውን በማስመሰል በእንደዚህ ዐይነት አገርን ከውስጥ የሚያስቦረቡርና ለውጭ ጠላት ደግሞ ካለምንም መከላከል ትጥቅን ፈቶ እጅ የሚያሰጥ ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል።

ከዚህም ስንነሳ በአስተሳሰባቸው አንድ ወጥና ድርቅ ማለት፣ በምንም ዐይነት ለሰው ልጅ አለማሰብ፣ ወይም ህብረተሰብአዊ ፍቅር አለመኖር፣ አሁንም ቢሆን ጦርነትንና ድንፋታን ማስቀደም፣ ሶክራተስና ፓላቶ እንዳሉት ከህዝባዊ ስነ-ምግባርነት(Civic Virtue) ይልቅ፣ ህብረተሰቡን ማመሰቃቀል፣ ታዳጊው ትውልድ ኃላፊነት እንዳይኖረው ማድረግና ቀማኛ እንዲሆን ሁኔታውን ማመቻቸት፣ ከፋፋይነትና ለውጭ ኃይሎች ሰጥ ለጥ ብሎ መገዛትና፣ ይህንን እንደትልቅ ፈሊጥ አድርጎ መያዝ ዋናው የፖለቲካ „ፍልስፍናቸው“ በመሆን አገራችንን ከሁሉም አቅጣጫ ለማዳከም ችለዋል።  ይህ ዐይነት የፖለቲካ ዘይቤ ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ሲወዳደሩ ልዩ ሊያስመስላቸው ይችል ይሆናል፤ ነውም። በአንዳንድ ነገሮች ከቀደመው የኃይለስላሴና የደርግ አገዛዝ ቢሮክራቶች የሚመመሳሰሉበትም ሁኔታ አለ። ይኸውም ብሄራዊ ባህርይ ማጣት፣ በተለይም ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ሰጥ ለጥ ብሎ ማጎብደድ፣ ወይም አሜሪካንን እንደ አምላክ ማየትና አገርን መካድና የአገርን ምስጢር አሳልፎ መስጠት፣ ሰፊውን ህዝብ መናቅና ተንኮሎኝነት፣ በዚህ የሚመሳሰሉ ናቸው። ይህንን በጭንቅላታችን ውስጥ ስንቋጥር ነው የነገሮችን ሂደት መገንዘብ የምንችለው። ዝም ብሎ ግን አገዛዙ ለኢትዮጵያ አጀንዳ የለውም፤ ማርክሲስት ነው፤ የአልባንያውን ዐይነት ሶሻሊዝም ነው የሚያካሂደው፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ነው የሚያራምደው፤ ህገ-መንግስቱ ስታሊኒስታዊ ነው፤ የሚሉት አነጋገሮች የህብረተሰብአችንና የአገዛዙን የህሊና አወቃቀር፣ እንዲሁም ደግሞ የታሪክን ሂደት እንዳንረዳ የሚያደርገን አይደለም። በተጨማሪም የተበላሹ ማቴሪያላዊ(Socio-economic formation) አወቃቀሮች በሰው ልጅ አስተሳሰብ ላይ የሚኖራቸውን ተጽዕኖ ባለመገንዘብ የሚሰነዘሩ መንፈሰ ሀተታዎች እንጂ ሀቁን የሚነግሩን አይደሉም። ስለዚህም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ተንታኝ ከራሱ ስሜት በመነሳት እንጂ አንዳች ፍልስፍናንና ስልትን(Methodology) በመከተል አይደለም የዛሬውን አገዛዝ ባህርይና ፖለቲካ የሚባለውን ፈሊጥ ለመተንተን የሚሞክረው። እንደዚህ ዐይነቱ በአንዳች ፍልስፍናና ስልት ላይ ያለተደገፈ አቀራርብ ደግሞ የችግሩን ዋና ምንጭ እንዳንረዳ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ ፍቱንና ህብረተሰብአችንን ሊያረጋጋና ወደስልጣኔ ሊያመራው የሚያስችል መፍትሄ እንዳንሰጥ ያግደናል። ለመጻፍ ተብሎ የሚጻፍ፣ ወይም ደግሞ ቁጭትን ለመወጣት ተብሎ የሚጻፍ ነገር የለም። ስለሆነም የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታም ሆነ አጠቃላዩን የህዝባችንንና የአገዛዙን የህሊና አወቃቀር ለመረዳት፣ በፍልስፍና፣ በህሊና ሳይንስ፣ በህብረተሰብ ሳይንስና እንዲሁም በተነፃፃሪ የታሪክ ምርምር(Comparative studies) የሚደገፍ ጥናት ቢካሄድ ተቀራራቢ መልስና መፍትሄ ማግኘት የሚቻል ይመስለኛል።

ያም ሆነ ይህ የዛሬው የወያኔ/የኢህአዴግ አገዛዝ የፖለቲካ ስልጣንን ሲጨብጥ ሜዳው ክፍት ነበረለት።  የሚጋፈጠውን ሲያጣ ፍቅርና ሰላምን ከማስቀደም ይልቅ እንደልቤ መፈንጫ አገኘሁ በማለት ህብረተሰቡን ማዋከብ የፖለቲካው ዘይቤው አድርጎ ተያያዘው። የህብረተሰቡን ሀብት በመንጠቅና ጥቂቶችንም በማባለግ እያበጠ መምጣት ጀመረ። ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ዕርዳታ ሲፈስለት እኔ ነኝ ብቸኛው ኃይል በማለት በግሎባላይዜሽን ጉያ ስር በመውደቅና በመታሸት የህብረተሰቡን ችግር ውስብስብ አደረገ። ለዚህም ደግሞ  መለሰ ወዳጃችን ነው፤ በአካባቢውም ሰላምንና መረጋጋትን የሚያመጣ ነው እየተባለ መወደስ ቻለ። በሌላ ወገን ግን የምዕራቡ ዓለም የተከተለውና ዛሬም የሚከተለው ፖለቲካ ከአጭር ስሌት አንፃር የተተለመ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ጋር የቆመና እሱንም የደገፈ፣ ራሱም እንደ ዋና ጠላት መታየቱ በፍጹም አልገባውም። ስለሆነም መለስ ከመሞቱ በፊትና ስልጣን ላይ 20 ዐመታት ያህል በቆየበት ዘመን፣ ልክ ሶክራተስ ፐሪክለስን እንደወነጀለው፣ ሰነፍ፣ ለፍላፊ፣ አጭበርባሪ፣ አገር ሻጭና ከሃዲ፣ በዝሙት ዓለም ውስጥ የሚዋኝ፣ ዕውነትን ከመፈለግ ይልቅ ለውሸት ጠበቃ የቆመ ትውልድ፣ በግልጽ የሚታዩ ነገሮችን የሚክድና፣ ተቀባይ ሲያጣ ደግሞ ቃታ የሚሰነዝር ትውልድ ለማፍራት በቅቷል። ይሁንና ግን መለስ ከፐሪክለስ ጋር ሊወዳደር የሚችል መሪ አልነበረም። ፐሪክለስ በሌሎች የግሪክ ግዛቶች ላይ የአቴንን የበላይነት ለማስፈን የታገለና በአቴን ስልጣኔ የሚኮራ ነበር። በመለስ ይመራ የነበረው የወያኔ አገዛዝና የዛሪው ወያኔ ግን „ከአሜሪካን ጋር እየተመካከርን ነው የምንሰራው“ በማለት የበታችነቱን ያረጋገጠንና የሚያረጋግጥ፣ ለስልጣኔ ጠንቅ የሆነ አገዛዝ ነበር፤ ነውም። ብሄራዊ አጀንዳ የሌለውና ኢትዮጵያችንን ከውስጥ በማዳከም የሚደሰት ነበር፤ ነውም። የዓለም የገንዘብ ድርጅትንና የዓለም ባንክን የኒዎ-ሊበራል አንጀት አጥብቅኝ የሞኔተሪ ፖሊሲ በመከተልና በዚህ በመዝናናት ድህነትን የፈለፈለ ነው። የዚህ ሁሉ ዋናው ምክንያት ደግሞ በስልጣን መታወርና የማንአለብኝ ብሎ እየተመጻደቁ መኖር ነው። በዚህ ዐይነት በውሸት ላይ በተመሰረተ አገዛዝ ግን ደግሞ ነገ እንደዱቄት የሚበን፣ አገዛዙ መግቢያና መውጫ የሚያጣበት ቀን መምጣቱ አይቀሬ ነው። በታሪክ ውስጥ አንድ ጨቋኝ አገዛዝ ለብዙ ዘመናት የቆየበት ጊዜ የለም። በሌላ ወገን ግን በህዝባችንና በአገራችን ላይ ያደረሰው አደጋ በቀላሉ ተገልጾ የሚያልቅ እይመስለኝም። ብዙ ጥናትንና ምርምርን የሚጠይቅ ነው። በአጭሩ ግን አገዛዙ ህዝባችንን በሀዘን ዓለም ውስጥ እንዲኖር አድርጎታል፤ ግራ የገባው፣ ለምን እንደሚኖርና ወዴት እንደሚጓዝ የሚያውቅ አይመስልም። ለማኝ እንዲሆን ተደርጓል። በራሱ ላይ ዕምነት እንዲያጣ ሆኗል። ተፈጥሮአዊ ነፃነቱ ተገፏል። ወጣት ልጆቹን ለውጭ ከበርቴዎች ካለ ዕድሜያቸው ለጋሽ እንዲሆን ተደርጓል። ብሄራዊ ነፃነታችን ተገፏል። በአንድ በኩል አሽረሽ ምችው፣ በሌላው ወገን ደግሞ ተስፋ መቁረጥና መዘናጋት የህብረተሰብአችን ልዩ ባህርይ ሆነዋል።

በዛሬው ወቅት ወደ አስራ አራት ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝባችንን የሚያሰቃየው ረሃብ ከአገዛዙ ባህርይ፣ አወቃቀር፣ ብሄራዊ ባህርይ ማጣትና በዘረፋ ላይ የተመሰረተ አገዛዝ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። በተጨማሪም የረሃቡና የድህነቱ መስፋፋት የሚያመለክተው አገራችን የቱን ያህል በውጭ ኃይሎች መዳፍ ቁጥጥር ስር እንደወደቀች ነው። የአገዛዙ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከውጭ የመጣና በውጭ ኃይሎች የተደነገገ በመሆኑ ወደ ውስጥ፣ በተለይም ሰፊውን አምራች ገበሬ ሊያግዝ የሚችል የማምረቻ መሳሪያና ማዳበሪያ እንዲመረት ማድረግ የሚያስችልና፣ ቀስ በቀስ ደግሞ ህብረተሰብአዊ ሀብት እንዲፈጠር የሚያደርግ ባለመሆኑ ሰፊው ህዝባችን የግዴታ እንደገና ለረሃብና ለድህነት ተጋልጧል።  የአገዛዙ የሃሳብ ድህነትና ህዝብን መናቅ ህዝባችን ሊወጣው የማይችለው ፍዳ ውስጥ ከቶታል። ይህ በብዙ ድሮች የተቆላለፈው ችግርና የህብረተሰቡና የገዢው መደብ አስተሳሰብ በከፍተኛ ደረጃ መዳከም፣ 70% በመቶ የሚሆነው የአገራችን ምድር ለእርሻ የሚያገልግል ቢሆንምና፣ አገራችንም በውሃ ብዛት ክምችት በዓለም አቀፍ ደረጃ አምስተኛ ቦታን ብትይዝም፣ አሁንም ቢሆን በረሃብ የምትታወቅና ህዝባችንም በልመና እንዲኖር የተገደደ ነው። በአገራችን ምድር ውስጥ እየተደጋገመ ረሃብ መከሰት በዛሬው አገዛዝ ብቻ የሚሳበብ አይደለም። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በአገራችን ምድር የተከሰተውን ህብረተሰብአዊ አወቃቀር ለተከታተለና ላጠና፣ አዲስ የተፈጠረው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊት ብሄራዊ ባህርይ የነበረውና ያለው አልነበረም። በመሆኑም እንደዚህ ዐይነቱ ኤሊት ከሰፊው ህዝብ ርቆና ተገልሎ የሚኖርና፣ ፈጣሪም ባለመሆኑ በየጊዜው በአገራችን ምድር ረሃብ እንዲከሰት አድርጓል። ይህ ሁኔታ እንደባህል በመወሰዱና እስከዛሬ ድረስ በመዝለቁ በሰፊው ህዝብና በየጊዜው ብቅ በሚለው አዳዲስ ኤሊት መሀከል ምንም ዐይነት ግኑኝነት እንዳይፈጠር ተደርጓል። አዲስ አበባ የተቀመጠው ኤሊትና የገዢው መደብ ገበሬው በስንትና ስንት ልፋት በብርድና በጠራራ በባዶ ሆዱና ካለጫማ እያረሰ እንደሚያቀርብለት የገባው አይመስልም። ስለሆነም የአስተሳሰብ ለውጥ እስካልተደረገ ድረስና፣ ሃላፊነትን ሊቀበልና ብሄራዊ ስሜት ሊኖረው የሚችል አዲስ የህብረተሰብ ኃይል እስካልተፈጠረ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ እጣ ለሚቀጥሉት ሰላሳና ሃምሳ ዐመታት ድህነትና ረሃብ ይሆናል ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።

የወያኔን አገዛዝ የተበላሸና ህዝብን ለዝንተዓለም የሚያወዛግብ ፖለቲካን ስንመለከት በጣም የሚያሳዝኑና የሚያስቁ ሁኔታዎችን እንመለከታለን። ወያኔ ለዘለዓለም ስልጣን ላይ ለመቆየት ባለው ፍላጎት መሰረት ከውስጥ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ገንዘብ ከኢኮኖሚው ዕድገት ሁኔታ ጋር እየተመጣጠነ እንዲታተም ከማድረግ ይልቅ፣ በብዛት እንዲታተም በማድረግና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ በማድረግ ሊያደልብ ችሏል፤ አባልጓልም። ይህ አዲሱ መጤ የህብረተሰብ ክፍል አምራችና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመትከል የስራ መስክ የሚፈጥር ሳይሆን፣ በተለይም በአገልግሎት መስክ ላይ በመረባረብ በከፍተኛ ደረጃ የፍጆታ ዕቃ ተጠቃሚና የህብረተሰቡን ሀብት የሚመጥ ሊሆን ችሏል። ይህ በራሱ አገራችን ውስጥ መረን በለቀቀ መልክ ለተስፋፋው ድህነትና ድብቅ ረሃብ እንደ አንድ ዋና ምክንያት ሊቆጠር የሚችል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔ ራሱ የሚቆጣጠረው የኢንዱስትሪ መስክና አዳዲስ የሚተከሉት ኢንዱስትሪዎች በመሰረቱ ወደ ውስጥ ህዝባዊ ሀብትን(National and Social Wealth) ለመፍጠር የሚያስችሉና የስራ መስክ ለመከፍት የሚበቁ አይደሉም። በዚህም ምክንያት የውስጥ ገበያው ሊስፋፋና ሊዳብር የቻለበትን ሁኔታ አንመለከትም። በየቦታው ያሉ የቢሮክራሲው ማነቆዎች ደግሞ ህዝቡን የሚያሰሩና ወደ ውስጥ የጥሬ-ሀብት እንዲወጣና ሰፊው ህዝብ ወደ ስራ ዓለም እንዲሰማራ ለማድረግ የሚያስችሉ አይደሉም። በዚህም ምክንያት አገዛዙና ቢሮክራሲያዊ ማነቆዎች፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ሚኒስትሪዎች የሰፊው ህዝብ ተጠሪዎች ሳይሆኑ የህዝብን ሀብት የሚዘርፉና ህዝቡ በራሱ አነሳሽነት ችግሩን እንዳይቀርፍ ትልቅ እንቅፋት ለመሆን የቻሉ ናቸው። የኢኮኖሚና የኢንዱስትሪ ሚኒስተሮችን ዋና ተግባር በምንመረምርበት ጊዜ በመሰረቱ በየክፍለ ሀገራት ወይም በየክልሉ እየተዘዋወሩ የየአካባቢውን የኢኮኖሚና የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ማጥናትና፣ ከዚህ በመነሳት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ የሚገባቸው ነበሩ።  ሁኔታውን ስንመረምር ግን ሁሉም ሚኒስተሮች ማለት ይቻላል፣ ከህዝቡ ርቀው የሚኖሩና በየክፍላተ ሀገራት ምን ምን የስራ ክፍፍል እንዳለና፣ የገበያውም ሁኔታ በምን መልክ የተደራጀ መሆኑን ለመቃኘት የሚጥሩ አይደሉም፤ ፍላጎትም የላቸውም። ይህ እንግዲህ የአገዛዙን ፖሊሲ ሲመለከት፣ በሌላ ወገን ደግሞ አገዛዙ ለረጅም ዘመናት በስልጣን ላይ ለመቆየት ካለው ፍላጎት የተነሳ በህብረተሰቡ ውስጥ ባሉት ኢንስቲቱሽኖችና እስከመጠጥ ቤት ድረስ ሰርጎ በመግባት ህዝቡን ፍዳ እያሳየ ነው። ምንም የፖለቲካ ዕውቀት የሌላቸውን ሁሉ ደጋፊዎች በማድረግ ፖለቲካን ወደ ርካሽነት የለወጠ አገዛዝ ነው ማለት ይቻላል። ይሁ ጉዳይ እስከውጭ ድረስ በመዝለቅና አንዳንድ በኢትዮጵያውያን የሚተዳደሩ ቡና ቤቶችን በማቀፍ በውጭ አገር ያለው ኢትዮጵያዊ እንዲቃቃርና እንዳይቀራረብ እያደረገ ነው። በተለይም በብዛት ለትምህርት እየተባሉ የሚላኩ ምንም ነገር የማይገባቸው ልጆች በካድሬነት በመመልመል  የማይሆን ነገር እየሰሩ ነው። ስለሆነም እነዚህ ወጣት ትግሬዎች/ኢትዮጵያውያን በማያውቁት ነገር ውስጥ በመግባት በሌላው ወያኔን በሚጠላው ኢትዮጵያዊ እንደጠላትነት እየታዩ ነው። አገዛዙ ህብረተሰቡን በመከፋፈልና የተወሰነውን ህብረተሰብ ክፍል በጥቅም በመደለል የሚያካሂደው ፍልስፍናዊ አልባ ፖለቲካ በቀላሉ ልንወጣው የማንችለው ማጥ ውስጥ እየከተተን ማለት ነው። ኢትዮጵያን እንደ አገርና እንደ ህብረ-ብሄር በጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረተ ላይ የመገንባቱ ሁኔታ ለብዙ መቶ ዐመታት እንዲተላለፍ እየሆነ በመምጣት ላይ ነው። ይህ ዐይነቱ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ለራሱ ለአገዛዙ ብቻ ሳይሆን ለትግሬ ብሄረሰብም የሚያመች አይሆንም። ወያኔ ቢወድቅ እንኳ የተቀሩት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ እንዲሁም አባቶቻችንና እናቶቻችን የሆኑት የትግሬ ብሄረሰብ ተወላጆች በጥርጣሬ እየታዩ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚገለሉበት ሁኔታ ይፈጠራል። ስለዚህ የዚህን የተወሳሰበና አደገኛ ሁኔታ በመረዳት አዲስ የትግል አቅጣጫ መቀየስ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ከዚህ ስንነሳ የተቃዋሚውን ኃይል የትግል ስትራቴጂ ወይም ፍልስፍና በጥቂቱም ቢሆን መቃኘቱ አስፈላጊ ይመስለኛል።

አጠቃላዩንና የተወሳሰበውን የአገራችንን ሁኔታ ስንመረመር ተቃዋሚ ነኝ በሚለው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ይህንን የተወሳሰበ ሁኔታ ለመረዳት የሚያስችል ትንታኔ ሲሰጥ አይታይም። በብዙዎቻችን ዕምነት የዛሬው የወያኔ አገዛዝ ብቻውን የሚጓዝና፣ የተከተላቸውና የሚከተላቸውም ፖሊሲዎች ከውጭው ዓለም ጋር በተለይም፣ ኢንተርናሽናል ኮሙኒቲ ከሚባለው ጋር  የሚያያዙ አይደሉም። የዓለም አቀፍ የገንዘብ ደርጅት(IMF)፣ የዓለም ባንክ፣ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የአውሮፓ አንድነት በአገራችን የኢኮኖሚ ፖሊስና ተግባራዊ መሆን ላይ ምንም ዐይነት ተፅዕኖ የላቸውም።  ስለዚህም ትግሉ ከወያኔ ጋር ብቻ ነው። ሌላው ቀርቶ በሳይንስና በቲዎሪ እንዲሁም በፍልስፍና ደረጃ ዓለም አቀፍ ኮሙኒቲ የሚባለውን መጋፈጥ አያስፈልግም። የኢትዮጵያ ህዝብ ከወያኔ አገዛዝ ከተላቀቀ ሁሉ ነገር ይሰተካከላል የሚል ከዓለምና ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም አመለካከት በተቃዋሚው ኃይል ጭንቅላት ውስጥ የተቋጣረ ይመስላል።፣ ይህ ዐይነቱ አመለካከትና የትግል ስትራቴጂ ከታሪክ ልምድና በሳይንስና በፍልስፍና መነፅር የሚደገፍ አይደለም።

እኔ እስከተከታተልኩትና እስካጠናሁት ድረስ 1ኛ­) ተቃዋሚው ነኝ የሚለው ኃይል ብሄራዊ አጀንዳ ያለው አይመስለኝም። አገር ወዳድነቱና ብሄራዊ ስሜቱም ያጠራጥራል። ምክንያቱም ሳይንቲስቱ ላይብኒዝ እንደሚለው አንድ ግለሰብም ሆነ ድርጅት ህዝብ ወዳድና ለአገሩ የሚቆረቆረው በሳይንስና በፍልስፍና ላይ የተመረኮዘ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ብቻ ነው። 2ኛ) ፍልስፍናዊ መሰረት የለውም ወይም ደግሞ በምን ዐይነት ፍልስፍና እንደሚመራ ግልጽ አይደለም። 3ኛ)ባለፉት 24 ዐመታት በአገራችን ምድር የተፈጠረውን እጅግ አስቸጋሪ የኢኮኖሚ፣ የህብረተሰብና የማህበራዊ እሴቶች መበጣጠስና፣ የህዝባችንንም ኑሮ የመረመረና ለነዚህም ዋናው ምክንያት ምን እንደሆነ ጠጋ ብሎ ለመገንዘብ የቃጣና፣ የሚቃጣ አይደለም። በየጊዜው ንግግር ለማድረግ ተጋብዘው እዚህ አውሮፓ የሚመጡትን የተቃዋሚ ተጠሪዎች ንግግር ለተመለከተ በምድር ላይ ያለውን ሁኔታ በቅጡ የተገነዘቡ አይመስሉም።  አነጋገራቸው በነፃነት እጦት፣ በዲሞክራሲ አለመኖርና ምርጫ በስነ-ስራዓት አለመካሄድ አኳያ የሚደረጉ ንግግሮች እንጂ፣ ሰፊና ጠለቅ ያሉ ትንተናዎችን ሲሰጡ አይታዩም። ውጭ አገር ያለውም ችግሩን በምርጫና በህገ-መንግስት ዙሪያ ከማየት አልፎ በህብረተሰብአችን ውስጥ የቱን ያህል የአዕምሮ መዛባት(Austim) እንደሰፈነና፣ ለዚህም ደግሞ ልዩ ጥናትትና መፍትሄ እንደሚያስፈልገው ጥናት ሲያቀርብ አይታይም። 4ኛ) በአጠቃላይ ሲታይ የተቃዋሚው ኃይል ነኝ የሚለው በአገራችን ውስጥ የምዕራቡን ዓለም፣ በተለይም ደግሞ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን ጣልቃ-ገብነት ከምንም አይቆጥረውም፤ ወይም ደግሞ ከፖለቲካ ስሌቱ ውስጥ የለም። አንዳንዶች ይህንን ጉዳይ ሲያነሱ አይ ግራ ቀደም ተብለው ይወነጀላሉ፤ ከወዳጃችን ከአሜሪካን ጋር አታጣሉን ይባላሉ። እነዚህ ሰዎች ወደ ውስጥ በአማርኛ ቋንቋ እንኳ ውይይት እንዳይካሄድ  በሩን በመዝጋት ምሁራዊና ሳይንሳዊ ክርክር እንዳይደረግ ለማድረግ በቅተዋል። 5ኛ)ሌላው ትልቁ ችግር የብሄረሰብ ነፃ አውጭ ነኝ የሚባሉት ምሁራዊ ሁኔታና፣ የአንዳንዶችም በየጊዜው የመለዋወጥ አስተሳሰብና አካሄድ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ እየፈጠረ መጥቷል ማለት ይቻላል። በመሰረቱ በአገራችን ያለው ችግር የብሄረሰብ ችግር ወይም ጭቆና አይደለም። የንቃተ-ህሊና ጉድለትና የታሪክንና የህብረተሰብን ዕድገትና ሂደት ያለመረዳት ጉዳይ ነው። ከዚህ ስንነሳ እዚህና እዚያ እንቀሳቀሳልን የሚሉት የነፃ አውጭ ድርጅቶች ነን ባዮች ፍልስፍናቸው ምን እንደሆነ አይታወቅም። ተበድሏል የሚሉትን ወገናቸውን እንዴትስና በምን መንገድ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የጥበብና የኢኮኖሚ ዕድገት ባለቤትና ተጠቃሚ ለማድረግና ቆንጆ ኑሮ ሊኖር የሚችልበትን  መንገዱን ሲያሳዩን አንመለከትም። የዲሞክራሲና የነፃነት እጦት መፈክሮች ብቻ የትም አያደርሱትም። ከሌሎች አገሮች ልምድ እንደምናየው፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የአንጎላና የሞዛምቢክ፣ እንዲሁም የዚምባብዌ ህዝቦች የነፃነት ትግሉ ተጠቃሚዎች ሊሆኑ በፍጹም አልቻሉም። በድሮው አገዛዝ አዲስ የገዢ መደቦች በመቀመጥና ከውጭው ዓለም ጋር በመቆላለፍ ሀብት ዘራፊዎችና አቆርቋዦች ሆኑ እንጂ ህዝቦቻቸውን ተጠቃሚ ሊያደርጉ አልቻሉም። እንደምናየው በእነዚህ አገሮች ሁሉ በተለይም ወጣቱ ስራ አጥ በመሆንና የማስለጠኛ ቦታ በማጣቱ ተፈጥሮአዊ ችሎታውን ተግባራዊ እንዳያደርግ ተገዷል። ስለሆነም በዚህም ሆነ በዚያ መስክ ብሄረሰባችንን ነፃ እናወጣለን የሚሉት ቡድኖች በመሰረቱ ከነዚህ የሚለዩ አይሆኑም። ምናልባትም እንደጆከር በመቀመጥ ማስፈራሪያ የሚሆኑና፣ የድህነቱንም ዘመን የሚያራዝሙ ይሆናሉ። ከዚህ ስንነሳ ከፍልስፍና፣ ከሳይንስ፣ ከቲዎሪና ከጥበብ፣ እንዲሁም ከህብረተሰብ ሳይንስ ውጭ በነፃነት ስም ብቻ የሚካሄዱ ትግሎች የትም አያደርሱም። የዛሬው አገዛዝ ቢወድቅ እንኳ ምናልባት የደቡብ ሱዳን ዐይነት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ስለሆነም እያንዳዱ የነፃ አውጭ ድርጅት ነኝ የሚል እዚህና እዚያ ከመሯሯጡና ከምዕራቡም ምክር ከመጠየቅ ይልቅ እስቲ በአንድነት ተቀምጠን በየአንዳንዱ ጥያቄ ላይ ክርክርና ውይይት እናድርግ። እስከምረዳው ደረስ የአንደን አገር ችግር፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ህብረተሰብአዊና ማህበራዊ፣ እንዲሁም ባህላዊ ችግሮች በፖለቲካ ዲስኮርስና በዲሞክራሲያዊ ውይይት ብቻ ነው መፍታት የሚቻለው። ስለሆነም ለስልጣን ከመቻኮል ይልቅ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታና የዓለም አቀፍ የፖለቲካን፣ የሚሊታሪ፣ የርዕዮተ-ዓለምና የኢኮኖሚ አወቃቀር ጠጋ ብለን እንመርምር፤ አብረን ተቀምጠንም እናጥና። ለዚህም ደግሞ ድፍረቱ ይኑረን። ለብቻችን መሯሯጥና ለአውሮፓው አንድነትም ሆነ ለአሜሪካ መንግስት ተጠሪዎች እሮሮ ማሰማቱ ትክክለኛው የትግል ዘዴ አይደለም። እንዲያውም ራስን አለመቻልና የነፃነቱንም መንገድ ውስብስብ የሚያደርገው ነው። የአውሮፓንና የአሜሪካንን መንግስታት በዲፕሎማሲ ማሳመን አይቻልም።  የአሜሪካም ሆነ የምዕራብ አውሮፓ መንግስታቶች ተቃዋሚውን ኃይል እንዲደግፉ ከተፈለገ ተቃዋሚው ኃይል ከወያኔ የተሻለ የሚሰራ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። ይህም ማለት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይሰፍንና ጠንካራ ህብረተሰብ እንዳይመሰረት ጠንክሮ መስራት አለበት።

ከዚህ አጭር ሀተታ ስነሳ፣ ከዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበና አገርን ለማውደም ከተቃረበ ችግር እንዴት እንወጣለን ? የሚለው ነው ዋናው ጥያቄያችንና መመለስ ያለብን ጉዳይ። በተራ የነፃ ገበያና የሊበራል ዲሞክራሲ ፎርሙላ ወይስ አስቸጋሪ በሆነው ግን ደግሞ ፍቱን በሆነው በሬናሳንስ ፍልስፍና አማካይነት ነው የተወሳሰበውን የህብረተሰብአችንን ችግር ልንፈታ የምንችለው። በእኔ ዕምነት ተራ የሊበራል ዲሞክራሲና የነፃ ገበያ ፎርሙላዎች ለኛ ብቻ ሳይሆኑ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ችግር በፍጹም መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ አይደሉም። መፍትሄው የመንፈስን የበላይነት የሚያስቀድመውን የሬናሳንስን ሁለ-ገብ የህብረተሰብን ችግር መፍቻ ስልት የተከተለን እንደሆን ብቻ ነው። እኛ ብቻ ሳንሆን ዛሬ የተቀረው የዓለም ህዝብ የሚመኘው የመንፈስን የበላይነት የሚያስቀድምና የኑሮን ትርጉም እንድንረዳ የሚያደርገንን መንገድ ነው። በእርግጥ ይህ አካሄድ ከአገራችን ሁኔታ ጋር የሚጣጣምበትን ዘዴ መፈለግ የሚያሻ ይመስለኛል። ለማንኛውም ከየት እንደመጣን፣ በዚህ ዓለም ላይ ለምን እንደምንኖርና፣ ምንስ ማድረግ እንዳለብንና ወዴትስ እንደምናመራ የተገነዘብን እንደሆን ብቻ ተቀራራቢ መፍትሄ ማግኘት የምንችል ይመስለኛል። ለዚህ ሁሉ መፍትሄውም የፒታጎራስን፣ የሶክራተስንና የፕላቶንን ወንድማዊ ወይም የእህትማማች ፍቅር እንደመመሪያ አድርገን የወሰድን እንደሆን ብቻ ነው። ይህ ፍቅር ግን በዕውቀት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። ምሁራዊ ፍቅር ማለት ነው። ዕውነትን ለመፈለግ የሚረዳንና ሶፊስታዊውን የመሙለጭለጭ መንገድ አሽቀንጥረን የሚያስጥለን መሆን አለበት። በሃሳብና በልብ እንድንገናኝ የሚያደርገንና፣ ራሳችንን አውቀንና ለውጠን ህብረተሰብአችንን ከገባበት ማጥ ውስጥ እንዲወጣ የሚያስችለው ፍልስፍናና መመሪያ መሆን አለበት።

ፈቃዱ በቀለ

fekadubekele@gmx.de

 

 

 

The post ፍልስፍና አልባ የሆነ አገዛዝና የፖለቲካ ትግል ዘዴ የአንድን ህብረተሰብ አስተሳሰብ ያዘበራርቃል- የመጨረሻ መጨረሻም አገርን ያወድማል! appeared first on Zehabesha Amharic.

ጎንደር‬ የሚገኙት ባለስልጣናት ለሁለት ተከፍለው በመተማ ሸዲና አርማጭሆ ህዝቡን በመማፀን ላይ ናቸው

0
0

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ) በጎንደር‬ የሚገኙት የህወሓት አገዛዝ ከፍተኛ ባለስልጣናት በአሁኑ ሰዓት ለሁለት ተከፍለው ወደ መተማ ሸዲና አርማጭሆ አቅንተው ህዝቡን በመማፀን ላይ ናቸው፡፡

በትናንትናው ዕለት በጎንደር ጎሃ ሆቴል በነበረው ስብሰባ ላይ ገዱ አንዳርጋቸው የጎንደር ህዝብ በስርዓቱ ላይ ማመፁን ባፋጣኝ የማያቆም ከሆነ የክልሉ ልዩ ኃይል እና ፌደራል ፖሊስ ጦር ተቀናጅተው የማያዳግም የኃይል እርምጃ እንደሚወስዱ እሱ የሚመራውን ክልል አስተዳደር አቋም አስታውቋል፡፡

abay Tsehaye
በዛሬው ዕለት አባይ ፀሐዬ፣ ደመቀ መኮንን እና አምባቸው /የክልሉ ምክትል አስተዳዳሪ/ ወደ መተማ ሸዲ አምርተው በቦታው ያገኙትን ጥቂት ህዝብ ከአንገት በላይ የሆነ ጉንብስ ለመዋረድ እየጣሩ ይገኛሉ፡፡


በተመሳሳይ ሁኔታም እንዲሁ በረከት ስምዖን፣ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ሙሉጌታ ወርቁ /የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር/ እና የክልሉ ልዩ ሃይል አዛዥ የሆነው ሰው ወደ አርማጭሆ ዘልቀው ከህዝብ ጫማ ስር በመውደቅ ላይ ናቸው፡፡

The post ጎንደር‬ የሚገኙት ባለስልጣናት ለሁለት ተከፍለው በመተማ ሸዲና አርማጭሆ ህዝቡን በመማፀን ላይ ናቸው appeared first on Zehabesha Amharic.

ሕወሃት የሚመራው መንግስት በኦሮሞ ህዝብ ላይ ጦርነት ማወጁን ኦነግ አወገዘ –መግለጫውን ይዘናል

0
0

abebe Gelaw

ላለፉት 25ዓመታት በኦሮሞ ህዝብ ላይ ጦርነት በማወጅ ሲገድድና ሲያስር የነበረው የወያኔ ኣናሳ ቡድን መንግስት ታህሳስ 15 ቀን 2015ዓም ለሁለተኛ ጊዜ ኣዋጁን በማደስ የኦሮሞ ህዝብ በሰላማዊ መንገድ እያካሄደ ያለውን ተቃውሞ ለማፈን የጦር ሃይሉ የፈለገውን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ስልጣን ሰጥቶታል። ይህ በኦሮሞ ህዝብ ሊይ የታወጀው ይህ የጦርነት ኣዋጅ ኣዲስ ባይሆንም ከቀድሞዎቹ በበለጠ የንጹሃን ዜጎችን እልቂት የሚያስከትል መሆኑ ኣያጠራጥርም።

[ሙሉውን መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ]

The post ሕወሃት የሚመራው መንግስት በኦሮሞ ህዝብ ላይ ጦርነት ማወጁን ኦነግ አወገዘ – መግለጫውን ይዘናል appeared first on Zehabesha Amharic.


በጎንደር ጭልጋና አካባቢው (ጮንጮቅ) በሕወሓት ታጣቂዎች እና በገበሬዎች መካከል የተከፈተው ደም ያፋሰሰው ጦርነት ቀጥሏል

0
0

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ) በጮንጮቅ እየተካሄደ በሚገኘው ከባድ ውጊያ አረጋዊያን ሴቶችና ህፃናት የዕልቂቱ ሰለባ በመሆን ላይ ናቸው፡፡ የህወሓት ታጣቂዎች በጮንጮቅና አካባቢው የሚኖሩ ገበሬዎችን የእህል ክምሮችና መኖሪያ ቤቶችን በእሳት አጋይተዋል፡፡

Zehabesha News
በጮንጮቅ እየተካሄደ የሚገኘውን ህዝባዊ ትግል የህወሓት/ብአዴን ሰዎች አማራና ቅማንት በሚል አቅጣጫ በማስቀየር በውሸት ህዝቡን ጎራ ለይቶ እርስበርሱ ተሰላልፎ እንዲጨራረስ ለማድረግ እየተጉ ነው፡፡


ከጎንደር መተማ የሚያደርሰው አውራ ጎዳና በመዘጋቱ ምክንያት እንደ አማራጭ የተያዘው ከጎንደር በሁመራ መስመር በኩል በስናር አልፎ መተማ የሚያስገባው መንገድ ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል፡፡


በሌላ በኩል ደግሞ ከሳምንታት በፊት በኦሮምያ የፈነዳው የህዝብ ቁጣ ማዕበል አድማሱን እያሰፋ የህወሓትን አገዛዝ እስከ አንገቱ ድረስ አጥልቆታል፡፡ ህወሓትም በምላሹ ወደ ህዝቡ መተኮሱን ገፍቶበት እስካሁን ከ30 በላይ ንፁሃን ሰዎች ህፃናትን ጨምሮ መጨፍጨፋቸው ተረጋግጧል፡፡

The post በጎንደር ጭልጋና አካባቢው (ጮንጮቅ) በሕወሓት ታጣቂዎች እና በገበሬዎች መካከል የተከፈተው ደም ያፋሰሰው ጦርነት ቀጥሏል appeared first on Zehabesha Amharic.

የመጨረሻው ድል የፍትህ: የሰላም፡የፍቅር ነው። በዘር በክልል መከፋፈል ከመለስ ጋር ሞቷል!

0
0

ቢላል አበጋዝ / ዋሽግተን ዲ ሲ

ረቡዕ ፣ ዲሴምበር 16 ቀን 2015

2312 (1)እንደዛሬው ወያኔ ኢህአዴግ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ግልጽ በሆነ መንገድ ፍላጎቱን በትክክል፤ የሚሄድበትን መንገድ ወለል አርጎ ያሳየበት ጊዜ የለም።ፍላጎቱ ስልጣን፤ዘዴው በጭካኔ መርገጥ፤ ይህ ካልሰራ አገር መበተን ነው።ይህን ማንም አሽቃባጩ ማንም ይቅርታ ጠያቂው ሊከላከልበት የሚችለው አይደለም።ከዚህ ወዲያ በጭካኔ የመርገጥ ተግባሩን ይበረታበታል እንጂ የሚቀንስው አይደለም።የህዝቡን እምቢተኝነት “የሽብርተኛ” ማለቱ የምዕራቡን ዓለም እገዛ ለማግኘት፤ከተጠያቂነትም የሚድን መስሎት ነው።

የህወሃት ማከላዊ ኮሚቴ በሁለት ተከፍሎ ይህም ማለት ለህዝቡ እምቢተኝነት ፖለቲካዊ መፍትሄ መስጠትና እንደወትሮው በጭካኔ መርገጥ ላይ ቢዶልት፤ጨፍጭፍ፤ እርገጥ የሚለው ክፍል ያቸነፈ መሆኑ በኦሮሚያ ወታደራዊ አዋጅ መታወጁ አመላካች ነው።የሚሄድበትን መንገድ ወለል አርጎ ያሳየበትም ይኸው ነው።

ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሀይሎች ዛሬ የሚሰሩት ስተት ቢኖር በኦሮሞ ኢትዮጵያ የተነሳውን አመጽ አንዱ ክፍል የተወሰነ፤የኦሮሞ ብቻ አድርጎ ማሰብ፤ኦሮሞች የሆኑ ደግሞ የብቻ ትግላቸው አድርገው ካዩት ነው።እኒህ ዳር ና ዳር ያሉ የጽንፈኝነት ሰለባ አመለካከቶች ለወያኔ የሚመቹ የኢትዮጵያን ህዝብ ለቀጣይ ባርነት ይሚዳርጉ ናቸው።የወያኔ ኢህአዴግ ፍላጎቶችች ጋር የሚናበቡ ጽንፎች ናቸውና።

የህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ትግል መራመድ እነዚህን ከላይ ያነሳኋቸውን ጽንፈኝነቶች እያከሸፈ ወያኔ ጋር መጋፈጥ ይኖርበታል። ደስ የሚያሰኘው ወጣቱ እኒህን ጽንፎች እያከሸፈ መሆኑ ነው። እኒህ ጽንፎች በኦሮሞው በኩል የዛሬው ጉዳት፤ሞትና ስቃዩ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ያለፈ ታሪክን ይዘው ለጥርጣሬ በር ይከፍታሉ።በአማራው በኩል ያሉት ጽንፈኞች ደግሞ አማራው ሲበደል ኦሮሞው መቸ አገዘ ይላሉ።በዚህ ክርክር የጋምቤላው የአፋሩ የሶማሉ የደቡቡ በደል መነሳቱ ይቀራል።በዚህ መሃል ወያኔ ኢህአዴግ ፋታ ያገኛል ማለት ነው።ወያኔ ኢህአዴግን የሚጥለው አገር አቀፍ ህዝባዊ አመጽ ነው።አንድ ባንድ ተራ በተራ ለገጠሙት ብርታት የለውም ማለት ወያኔ ላይ የዋህ ግምት ማድረግ ነው።

ወያኔ ኢህአዴግ በህዝቦች መካከል ክፉ ልዩነቶችን ቢያጣ እራሱ በጥረቱ ያሰናዳቸዋል።ይቀምማቸዋል።በጎንደር እያደረገ ያለውን በክልል ውስጥ ክልል መፍጠርን፤የቅማንት ህዝብን ጥያቄ ማራገብን ማመልከት ብቻ ይበቃል።እንዲህ ያሉትን ዘዴዎች ትቶ ለምን ከነጭርሱ ኤርትራ ወረረችኝ አይልም ?ይህንም ይላል።ግን ትልቅ ካርዱ ሰለሆነ ያቆየዋል። ኤርትራን ይተነኩስ እንደሆን እንጂ ኤርትራ ኢትዮጵያን የምትወርበት ምክንያት ዛሬ የለም።ኤርትራ የኢኮኖሚ ችግርዋን መልክ ማስያዝ ላይ እንዳለች እየተነገረ ከሆነ ቆይቷል።

አፍጥጠው ያሉት የቀይ ባህር ባሻገር ሀብታም አረብ አገሮች ዛሬ ወያኔን በገለልተኝነት አቌም ያዩታል እንጂ ለወያኔ ኢህአዴግ መሰናበት አይጨነቁም።እንዲያውም በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አገር ወዳድ መንግስት ሳይቆም የኔ የሚሉት ሀይል ከዚህ ወያኔ ሊያራግበው ከሚመኘው እሳት መሃል እንዲወጣላቸው የኢትዮጵያን ጉዳይ መያዣ እዲኖራቸው ይፈልጋሉ።ይህን ደግሞ የሚገልጸው ከየመን በኋላ ሀብታም አረብ አገሮች ፈርተዋል።ሰግተዋል።ምንም ከማድረግ አይመለሱም።ኢትዮጵያ የወትሮ ምኞታቸው፤የወትሮም ስጋታቸው ናትና። የህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ትግሉን የሚያዛንፉ ሌላ ሀይሎች እነሱ ናቸው እላለሁ።ጠላት ወያኔ ኢሃዴግ ብቻ አይደለም።

ዛሬ በኢትዮጵያ ወያኔ ህወሃት በግድያ፤ በድብደባ ሊገታው የማይችለው አመጽ ተነስቷል።ከኢትዮጵያ ውስጥም ይሁን ከውጭ ዜጎች ስጋት ባለበት መንፈስ ሁኔታውን እየተከታተሉ ነው። የወያኔ የፖሊስና ወታደራዊ ሀይል በትንሹ እንኳን ቢነቃነቅ የወያኔ ህልውና የመጨረሻዎቹ ሰዓቶች መድረሳቸው አመላካች ነው።ወያኔ ይህን ያህል በቋፍ ነው። ያውቀዋል።ጥያቄው የአሁኑ የየካቲት 1966 ዓም ድጋሚ ይሆን ? ነው።

ወያኔ መግደል ይችላል።የኢትዮጵያ ህዝብ የነጻነት የዴሞክራሲ ትግል ሊገታ ግን አይችልም።የፋሺስት ኢጣሊያ ጭፍጨፋን ታዝቦ ለታሪክ ያቆየው አንድ የሁንጋሪያ ሰው የፋሺስ ኢጣልያ የአረመኔ ድርጊት ኢትዮጵያ በሚለው መጽሀፉ መጨረሻ እንዲህ ብሏል “በደምና በስቃይ ላይ የተገነባ፤በደምና በገጠጠ ውሸት ላይ የተመረኮዘ ይወድቃል።ከመቸውም ጊዜ በበለጠ የመጨረሻው ድል የፍትህ: የሰላም፡የፍቅር ነው።”

 

 

ድል ለዲሞክራሲያዊ  ሀይሎች ሁሉ!

ኢትዮጵያ በአንድነትዋ በነጻነት ለዘለዓለም ትኑር!

The post የመጨረሻው ድል የፍትህ: የሰላም፡የፍቅር ነው። በዘር በክልል መከፋፈል ከመለስ ጋር ሞቷል! appeared first on Zehabesha Amharic.

የኢትዮጵያ ህዝብ አጋንት፣ ጠንቋይ፤ ተብለው ዛሬም በወያኔዎች ተሰደቡ። –ከተማ ዋቅጅራ

0
0
ከተማ ዋቅጅራ

ከተማ ዋቅጅራ

ወያኔ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ መቼስ የማንሰማው ነገር የለም 25 አመት ሙሉ በትግዕስቱ ታግሶዋቸው  የተቀመጠውን ህዝብ በየተራ እየተነሱ ማንቋሸሽ፣ መስደብ አላቆሙም። አሁንም እንኳን ሞት በራፋቸው ላይ ቆሞ መጥፊያቸው ግቢያቸው ገብቶ ስድባቸውን ቀጥለዋል። ይሄ የሚያሳየው ደግሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያላቸው ጥላቻ ካልጠፉ በስተቀር እንደማይተውት የሚያሳይ ነገር ነው።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር የኢትዮጵያን ወጣቶች ቦዘኔ፣ ፍንዳታ፣ በማለት ሲያጥላሉ እና ሲሳደቡ አሻንጉሊቶቹ  የፓርላማ  አባላት ያጨበጭቡና ይስቁ ነበር። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ባገኘው አጋጣሚ እንደማይፈልጋቸው ሲነግራቸው ኖሯል። ህዝቡ እንዳልመረጣቸው ቢያስውቃቸው ምን ታመጣላችሁ በሚል እያንቋሸሹ፣ እየሰደቡ የጭቆና አገዛዛቸውን ቀጥለውበታል። ህዝብን የሚያክል ነገር መሪ በተባሉት አካል ቦዘኔ እየተባሉ በአደባባይ ሲሰደቡ የሚያሳፍር ቢሆንም ህዝቡ ግን ቦዜኔ ያለው ቤተ መንግስት ነው በማለት የቦዘኔ ጥርቅም ያለው ያለ እውቀታቸው እና ያለ ህዝብ ፍላጎት ተመርጠናል በማለት የተሰገሰጉበት መሆናቸውን ይነግራቸው ነበር።

በ97 የቅንጅት ሰልፍ ግዜ አጋዚ በሰላማዊ ሰው ላይ በወሰደው ኢሰባአዊ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ወያኔዎች የተወሰደው እርምጃ ትክክል ነው ባንክ ሊዘርፉ ሲሉ የነበሩ እና የተለያየ የሽብር ስራ ሊሰሩ የነበሩት ናቸው እርምጃ የተወሰደባቸው በማለት ከመጸጸት ይልቅ ያልተገባ ስም እየሰጡ መግደላቸውን እንደ ትክክለኛ ስራ አድርገው ሲነግሩን ህዝባችን ጥርሱን ነክሶ ዝም ከማለት ውጪ ምንም ያደረገው ነገር አልነበረም። ወያኔዎች የኢትዮጵያ ህዝብን በማንቋሸሽ እና በመስደብ የታወቁ ናቸው። በተቃራኒው ደግሞ የትግራይ ህዝብ ደግሞ በወያኔዎች አገላለጽ ወርቅ ትውልድ እንደሆኑ ይነግሩናል። ይሄ ደግሞ አንደኛ ዜጋ እና ሁለተኛ ዜጋ እንደሆንን አልገባን ከሆነ በግልጽ ነግረውን  እየሰሩበት ይገኛሉ።ለዚህ ነው ህዝባችንን ወራዳ፣ ፍንዳታ፣ ቦዘኔ ሌላም ሌላም እያሉ የሚሰድቡት። ዛሬ ደግሞ  በለመደው የስድብ አፋቸው አጋንት፣ጠንቋይ ብለው  ህዝባችንን በግልጽ በአደባባይ ሰድበውታል። ይሄ የሚያሳየው ለወያኔዎች የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ሰው አለመቁጠራቸው ነው። የሰው ልጅን አጋንት ተብሎ መሳደብ ያስቀጣል ወደፊትም ተጠያቂም ያደርጋቸዋል። ዛሬ ስልጣን ላይ ነይ ብለው በስልጣናቸው ተጠቅመው የፈለጉትን መናገርና መስራት እንችላለን ተብሎ ህዝብን የሚያል ማዋረድ ህዝብን ማንቋሸሽ አቋማቸው ሁሌም የማይለወጥ መሆናቸውን አሳውቀውናል እኛም ካወቅን ሰነበትን።  ህዝቡ ሲነሳ ነደድ እሳት እንደሆነ አልተገነዘባችሁ ይሆንን? ህዝብ ሆ ብሎ ተነስቶ እንደሚያጠፋችሁ ዘንግታችሁታል። ህዝብን ንቆ፣ አዋርዶ፣ አንቋሾ መኖር እንችላለን ብላችሁ ካሰባችሁ ዶክተር መራራ ጉዲና እንደተናገሩት እነሱ ከጫካው ወጡ እንጂ ጫካው ከነሱ አልወጡም የሚለው አገላለጽ ይገልጻችኋዋል። ዛሬም ከ25 አመት በኋላ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያላችሁ ጥላቻ አለመጥፋቱን በግልጽ ነግራችሁናል። ዛሬም የኢትዮጵያን ህዝብ ለመስደብ እና ለማጥፋት  እንደማይመለሱ በእርገጠኝነት አሳይታችሁናል።

እንግዲህ ዛሬ ያልነቃህ ካለህ ንቃ ያልተነሳህ ካለህ ተነስ። ኦፒዲኦ፣ ብአዴን፣ ደህዴን የሚባሉት ድርጅቶች ቀድመን እንደተናገርነው ደግመንም ደግመንም እንዳሳሰብነው የወያኔ መጠቀሚያ እንጂ ምንም የማይሰሩ በአገሪቷ ላይ ስልጣን የሌላቸው የሆድ አደር ጥርቅም እንደሆኑ ብዙሃኖቹ አስረግጠው ተናግረዋል። በየትኛውም አካባቢ ትዕዛዝ የሚያስተላልፉት ውሳኔ የሚሰጡት የክልሎች መንግስት ተብዬዎች ሳይሆን ወያኔዎች ናቸው። ከዚህ  መስመር በኋላ ኦፒዲኦ ነው የሚመለከተው ከዚህ መስመር በኋላ ብአዴን ነው የሚመለከተው ከዚህ መስመር በኋላ ደህዴን ነው የሚመለከተው በማለት ሁሉም አንድ ሆነው እንዳይሰሩ ለመለያየት የተጠቀመበት እንጂ ምንም የማይፈይዱ የወያኔ መጠቀሚያ የሆኑ አጥር እና ድርጅቶች ናቸው። ይሄንን አጥር እና የወያኔ ሴራ  ለአንደ እና ለመጨረሻ ግዜ መሰበሪያው ሰአት አሁን ነው። በአጥር ከልሎ አንዱ ወደ ሌላው እንዳይመጣ አንዱ ለአንዱ አጋር እንዳይሆን እናንተ አይመለከታችሁም ሁሉም የራሳቸው አስተዳዳሪ ስላላቸው ማንም ከራሱ ክልል ውጪ አይመለከታችሁም በሚል ሰበብ አራርቆ ወያኔ ግን ሁሉም ክልሎች ውስጥ በዋነኝነት እየሰራ ህዝባችንን አለያይቶ በተነጠል እያጠፋን ስለሆነ ነገሮችን በጥልቀት እና በብልጠት የምናይበት ግዜ ነው። ወያኔ ያስቀመጠው አጥር በማፍረስ ፍቅር አሸናፊ ነው አንድነት ሃይል ነው የኛ ጠላት ወያኔ ነው ብለን የከፋ ነገር ሳይመጣ አንድነታችንን በግልፅ እናውጅ። በአገር ቤትም በውጪም የምትኖሩ የተቃዋሚ ኃይሎች አንድ ነን ብላችሁ በአንድነት ተሳሰሩ በአንድነት ቁሙ ስለ አንድነት ዘምሩ ያኔ በአንድነት የተሳሰረ ህዝብ በአንድነት የፍቅር መዝሙርን ሲያሰሙ የወያኔ ምሶሶዎች ይፈርሳሉ ዛሬ አጋንት ብሎ ህዝባችንን የሰደቡ በፍቅር እና በአንድነት ስንቆም የእግዚአብሔር ኃይል ለብሰን የተሳዳቢዎችን አፋቸውን የመዝጋት ስልጣን እናገኛለን። የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ንቁ እንንቃ ሁሉም ህብረተሰብ አንዱ ለአንዱ ዘብ ይቁም አንዱ ለአንዱ መከታው ይሁን። ሁላችንም ሳንለያይ በመደጋገፍ ለወያኔ ሴራ ክፍተት ባለመስጠት ብንሰራ በአጭር ግዜ ድሉን በእጃችን ማስገባት ይቻላል ሰላምን ለኢትዮጵያ ማስፈን ይቻላል።

የወያኔን ፉከራ ባዶ ፉከራ ማድረግ የምንችለው ሳንከፋፈል ስንታገል ብቻ ነው። ስድባቸውን ማጥፋት የምንችለው በአንድነት ስንነሳ ብቻ ነው። ይሄ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ መልዕክቴ ነው። ህዝባችንን ለጭፍጨፋ አናጋልጥ ለህዝባችን ነጻነትን ለማምጣት በረሃ የወረዱትንም አሰልቺ ትግል እንዲጋፈጡ አናድርጋቸው። ነጻነት ማግኘት የምንችለው በረሃም ያሉት ከተማም ያሉት በውጪም ያሉት የአንድነት ድምጽ ሲኖረን ነው። ይሄ ካልሆነ ግን ትላንትና በአደባባይ ቦዘኔ፣ ፍንዳታ፣ ወራዳ ተብለን ተሰድበንና ተገድለን በመከራ እንዳለፍን ሁሉ ዛሬም አጋንት፣ ጠንቋይ ብለውን እየሰደቡን እየገደሉን እያዋረዱን ነው። በአደባባይ እየተሰደብን በአገራችን እየተገደልን ከቄአችን ላይ እየተፈናቀልን እንዳንኖር ሰላማችንን ማምጣት የምንችለው እኛው ነን። ወያኔ እንደሆነ መቼም መለወጥ የማይችሉ ናቸው። መለወጥ ያለብን እኛው ለውጥን ፈላጊ ሰላምን ናፋቂዎቹ ነን።

ከተማ ዋቅጅራ

17.12.2015

Email – waqjirak@yahoo.com

 

 

The post የኢትዮጵያ ህዝብ አጋንት፣ ጠንቋይ፤ ተብለው ዛሬም በወያኔዎች ተሰደቡ። – ከተማ ዋቅጅራ appeared first on Zehabesha Amharic.

የመጨረሻው ድል የፍትህ: የሰላም፡የፍቅር ነው። በዘር በክልል መከፋፈል ከመለስ ጋር ሞቷል!

0
0

ቢላል አበጋዝ
ዋሽግተን ዲ ሲ
ረቡዕ ፣ ዲሴምበር 16 ቀን 2015

እንደዛሬው ወያኔ ኢህአዴግ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ግልጽ በሆነ መንገድ ፍላጎቱን በትክክል፤ የሚሄድበትን መንገድ ወለል አርጎ ያሳየበት ጊዜ የለም።ፍላጎቱ ስልጣን፤ዘዴው በጭካኔ መርገጥ፤ ይህ ካልሰራ አገር መበተን ነው።ይህን ማንም አሽቃባጩ ማንም ይቅርታ ጠያቂው ሊከላከልበት የሚችለው አይደለም።ከዚህ ወዲያ በጭካኔ የመርገጥ ተግባሩን ይበረታበታል እንጂ የሚቀንስው አይደለም።የህዝቡን እምቢተኝነት “የሽብርተኛ” ማለቱ የምዕራቡን ዓለም እገዛ ለማግኘት፤ከተጠያቂነትም የሚድን መስሎት ነው።

abebe Gelaw
የህወሃት ማከላዊ ኮሚቴ በሁለት ተከፍሎ ይህም ማለት ለህዝቡ እምቢተኝነት ፖለቲካዊ መፍትሄ መስጠትና እንደወትሮው በጭካኔ መርገጥ ላይ ቢዶልት፤ጨፍጭፍ፤ እርገጥ የሚለው ክፍል ያቸነፈ መሆኑ በኦሮሚያ ወታደራዊ አዋጅ መታወጁ አመላካች ነው።የሚሄድበትን መንገድ ወለል አርጎ ያሳየበትም ይኸው ነው።

ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሀይሎች ዛሬ የሚሰሩት ስተት ቢኖር በኦሮሞ ኢትዮጵያ የተነሳውን አመጽ አንዱ ክፍል የተወሰነ፤የኦሮሞ ብቻ አድርጎ ማሰብ፤ኦሮሞች የሆኑ ደግሞ የብቻ ትግላቸው አድርገው ካዩት ነው።እኒህ ዳር ና ዳር ያሉ የጽንፈኝነት ሰለባ አመለካከቶች ለወያኔ የሚመቹ የኢትዮጵያን ህዝብ ለቀጣይ ባርነት ይሚዳርጉ ናቸው።የወያኔ ኢህአዴግ ፍላጎቶችች ጋር የሚናበቡ ጽንፎች ናቸውና።

የህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ትግል መራመድ እነዚህን ከላይ ያነሳኋቸውን ጽንፈኝነቶች እያከሸፈ ወያኔ ጋር መጋፈጥ ይኖርበታል። ደስ የሚያሰኘው ወጣቱ እኒህን ጽንፎች እያከሸፈ መሆኑ ነው። እኒህ ጽንፎች በኦሮሞው በኩል የዛሬው ጉዳት፤ሞትና ስቃዩ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ያለፈ ታሪክን ይዘው ለጥርጣሬ በር ይከፍታሉ።በአማራው በኩል ያሉት ጽንፈኞች ደግሞ አማራው ሲበደል ኦሮሞው መቸ አገዘ ይላሉ።በዚህ ክርክር የጋምቤላው የአፋሩ የሶማሉ የደቡቡ በደል መነሳቱ ይቀራል።በዚህ መሃል ወያኔ ኢህአዴግ ፋታ ያገኛል ማለት ነው።ወያኔ ኢህአዴግን የሚጥለው አገር አቀፍ ህዝባዊ አመጽ ነው።አንድ ባንድ ተራ በተራ ለገጠሙት ብርታት የለውም ማለት ወያኔ ላይ የዋህ ግምት ማድረግ ነው።

ወያኔ ኢህአዴግ በህዝቦች መካከል ክፉ ልዩነቶችን ቢያጣ እራሱ በጥረቱ ያሰናዳቸዋል።ይቀምማቸዋል።በጎንደር እያደረገ ያለውን በክልል ውስጥ ክልል መፍጠርን፤የቅማንት ህዝብን ጥያቄ ማራገብን ማመልከት ብቻ ይበቃል።እንዲህ ያሉትን ዘዴዎች ትቶ ለምን ከነጭርሱ ኤርትራ ወረረችኝ አይልም ?ይህንም ይላል።ግን ትልቅ ካርዱ ሰለሆነ ያቆየዋል። ኤርትራን ይተነኩስ እንደሆን እንጂ ኤርትራ ኢትዮጵያን የምትወርበት ምክንያት ዛሬ የለም።ኤርትራ የኢኮኖሚ ችግርዋን መልክ ማስያዝ ላይ እንዳለች እየተነገረ ከሆነ ቆይቷል።

አፍጥጠው ያሉት የቀይ ባህር ባሻገር ሀብታም አረብ አገሮች ዛሬ ወያኔን በገለልተኝነት አቌም ያዩታል እንጂ ለወያኔ ኢህአዴግ መሰናበት አይጨነቁም።እንዲያውም በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አገር ወዳድ መንግስት ሳይቆም የኔ የሚሉት ሀይል ከዚህ ወያኔ ሊያራግበው ከሚመኘው እሳት መሃል እንዲወጣላቸው የኢትዮጵያን ጉዳይ መያዣ እዲኖራቸው ይፈልጋሉ።ይህን ደግሞ የሚገልጸው ከየመን በኋላ ሀብታም አረብ አገሮች ፈርተዋል።ሰግተዋል።ምንም ከማድረግ አይመለሱም።ኢትዮጵያ የወትሮ ምኞታቸው፤የወትሮም ስጋታቸው ናትና። የህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ትግሉን የሚያዛንፉ ሌላ ሀይሎች እነሱ ናቸው እላለሁ።ጠላት ወያኔ ኢሃዴግ ብቻ አይደለም።

ዛሬ በኢትዮጵያ ወያኔ ህወሃት በግድያ፤ በድብደባ ሊገታው የማይችለው አመጽ ተነስቷል።ከኢትዮጵያ ውስጥም ይሁን ከውጭ ዜጎች ስጋት ባለበት መንፈስ ሁኔታውን እየተከታተሉ ነው። የወያኔ የፖሊስና ወታደራዊ ሀይል በትንሹ እንኳን ቢነቃነቅ የወያኔ ህልውና የመጨረሻዎቹ ሰዓቶች መድረሳቸው አመላካች ነው።ወያኔ ይህን ያህል በቋፍ ነው። ያውቀዋል።ጥያቄው የአሁኑ የየካቲት 1966 ዓም ድጋሚ ይሆን ? ነው።

ወያኔ መግደል ይችላል።የኢትዮጵያ ህዝብ የነጻነት የዴሞክራሲ ትግል ሊገታ ግን አይችልም።የፋሺስት ኢጣሊያ ጭፍጨፋን ታዝቦ ለታሪክ ያቆየው አንድ የሁንጋሪያ ሰው የፋሺስ ኢጣልያ የአረመኔ ድርጊት ኢትዮጵያ በሚለው መጽሀፉ መጨረሻ እንዲህ ብሏል “በደምና በስቃይ ላይ የተገነባ፤በደምና በገጠጠ ውሸት ላይ የተመረኮዘ ይወድቃል።ከመቸውም ጊዜ በበለጠ የመጨረሻው ድል የፍትህ: የሰላም፡የፍቅር ነው።”

ድል ለዲሞክራሲያዊ ሀይሎች ሁሉ!
ኢትዮጵያ በአንድነትዋ በነጻነት ለዘለዓለም ትኑር!

The post የመጨረሻው ድል የፍትህ: የሰላም፡የፍቅር ነው። በዘር በክልል መከፋፈል ከመለስ ጋር ሞቷል! appeared first on Zehabesha Amharic.

ዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቁጥር 81 – PDF

Viewing all 15006 articles
Browse latest View live