የሰባት ወር ህፃን ነበረች፡፡ በእናቷ እቅፍ ውስጥ ሆና በዕለተ ቅዳሜ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ ድንገተኛ ክፍላችን ከች አለች፡፡ እናት ‹‹ልጄን አድኑልኝ!›› እያለች መጮህ ጀመረች፡፡ ያው ድንገተኛ ክፍላችን ክፍል ውስጥ መስማት ከለመድናቸው ቃላቶች አንዱ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ንቁ ነበርን፡፡ ህፃናት ደርሰው ቅጠል የሚሆኑት ነገር ስላለ እንደ ሐኪም ህፃናትን የማናምነው ነገር አለ፡፡ ህፃኗን ተቀበልንና አልጋ ላይ ጋደም አደረግናት፡፡ ጥያቄዎች ቀጠሉ፡፡ ‹‹ምን ሆና ነው?›› እናት ፍርሃት በጠፈነገው አንደበት ‹‹ተቅማጥ! ትናንት እኮ ብዙ አልነበረም፡፡ ጠዋትም ሥራ ስገባ ሰላም ነበረች፡፡ ታዲያ ከስራ ስመለስ ሠራተኛዋ ተቅማጡ እየባሰባት መሆኑን ነገረችኝ፡፡ አንስቼ ሳያት ደካክማብኝ አገኘኋት›› እውነትም ሕጻኗ ሙሽሽ ብላ ነበር፡፡ ዓይኗ ሰርጉድ ብለዋል፤ ቆዳዋ ሲጨበጥ ዘግይቶ ነበር የሚለጠጠው፡፡ እጆቿና እግሮቿ እንቅስቃሴያቸው ተገተው ፍፁም መፍዘዝ ውስጥ ነበረች፡፡ ልቧ ሊወጣ ደርሷል፡፡ ትንፋሾቿ ቁርጥ ቁርጥ ይላሉ፡፡ ሞት ጥላውን ያጠላባት ምስኪን ህፃን!! አሁን ይህቺን ነፍስ ለማዳን ሩጫ ተጀመረ፡፡
አንዱ ክብደቷን ለካ፡፡ አንዱ የሚሰጣትን ፈሳሽ ያዘጋጃል፡፡ ሌላው የኦክስጂኑን ቱቦ ወደ አፍንጫዋ ከተተ፡፡ ደም ስሯን ማግኘት የደም ቧንቧዎች ሁሉ ደብዛቸው ጠፋ፡፡ ስለዚህ ወደ ሁለተኛው አማራች መሸጋገር ግድ ሆነ፡፡ የእግሯን አጥንት በስተን ህይወቷን ከሞት አፋፍ ሊነጥቅ የሚችለውን ፈሳሽ መስጠት የግድ ነበር፡፡ ነገሩ ሳይደግስ አይጣላም ሆነና ተሳካ፡፡
እነዚያ ህይወት አድን ጠብታዎች ወደ አጥንቷ እየተንዶለደሉ መግባት ቀጠሉ፡፡ የዚህችም ህጻን ነፍስ ደግሞ ኃይልን ነስታ ማንሰራራት ጀመረች፡፡ የተዘጋጀው ፈሳሽ በስድስት ሰዓታት ውስጥ አለቀ፡፡ በመትረፏ እርግጠኞች ሆንን፡፡ ሌሎች ተጓዳኝ ምርመራዎች ግን ቀጥለው ነበር፡፡ የደም ምርመራዋ መካከለኛ የሆነ ደም ማነስ እንዳለባት አሳበቀ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የብረት እጥረት መሆኑ ተደርሶበት ደሟን ሊተካ የሚችል ሽሮፕ ለሶስት ወራት ሰጠናት፡፡ የአመጋገቧን ነገር እናትን ጠየቅን፡፡ ጡት ብቻ እስከ ሶት ወር ጠባች፡፡ ከዚያ ጊዜ በኋላ እናት የመንግሥት ሠራተኛ ስለሆነች ጡት ማጥባት አመቺ ሆኖ ስላላገኘችው የላም ወተት ጀመረችላት፡፡
ብቻ ይገርማል! የሰው ህይወት በሰከንዶች ሽርፍራፊ ታሪኩ ሊለወጥ ነገሩ ሊገለበጥ የሚችል ፍጥረት መሆኑ፡፡ ታዲያ አንድ የጥያቄ እጅ የአዕምሮዬ በር ስታንኳኳ ሰማኋት፡፡
የዚህች ህፃን ችግር ከአንድ መሰረታዊ ጥያቄ ጋር የተያያዘ መሆኑን፡፡ ይኸውም የሚገባትን የእናት ጡት በየጊዜው አለማግኘቷ ከተፈጠረባት ችግር ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ የዛሬው ፅሑፍ የእናት ጡት ወተትን በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለመስጠት ይሞክራል፡፡
አንድ እውነት ልንገራችሁ፡፡ ሩሲያና አሜሪካ እንደ ድሯቸው አብረው ቢሰሩ እንኳን የእናትን ሁለት ጡቶች ያህል ለህፃኑ ጠቃሚ የሆነ ወተት ሊፈጥሩ አይችሉም፡፡ ዓለምን ሊያጠፋ የሚችል ሚሳኤል ፈጥረዋል፡፡ የመንታ ምንጮችን ያህል ግን የህፃኑን ጥያቄ አልመለሱም፡፡ ‹‹ለመሆኑ ምን አይተህበት ነው እንደዚህ እነዚህ ሁለት ሀገራቶችን የደፈርከው?›› በሉኝ፡፡ ምክንያቴን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
የእናት ጡት ወተት ለህፃናት የሚሰጠው ጥቅሞች
1. የጨጓራንና የአንጀትን ዕድገትና እንቅስቃሴ ያፋጥናል
የእናት ጡት ወተት የህፃኑን ጨጓራና አንጀት ከማጎልበት በተጨማሪ ውስጡ በሚይዛቸው ነገሮች የተነሳ አንጀትን በተለያዩ ተዋህስያን እንዳይወረሩ ማድረግ ይችላል፡፡ በዚያው ልክ ለሰውነታችን ተስማሚ የሆኑ ወዳጅ ባክቴሪያዎች እንዲያድጉ በማድረግ ከጠላት ባክቴሪያዎች የህፃኑን ጨጓራ እንዲጠብቁ ያደርጋል፡፡ ይሄ ነገር እምብዛም በላም ወተትም ሆነ በዱቄት ወተት ዳብሮ አይገኝም፡፡ በዚህ ምክንያት በህፃናት ላይ የሚከሰተውን የተቅማጥ በሽታ ይቀንሳል፡፡
2. ከትንፈሳ ጋር የተያያዙ በሽታዎችን ይቀንሳል፡፡
3. ዱቄት ከሚጠቀሙ ሰዎች ይልቅ የእናት ጡት ወተት የሚጠቀሙ ህፃናት ለጆቾ ቁስለት በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው አናሳ ነው፡፡ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንንም ቢሆን በመቀነሱ ረገድ የማይናቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡
4. የእናት ጡት ወተት ወደ ፊት የሚፈጠርን ቅጥ ያጣ ውፍረት ይቀንሳል፡፡
5. ከልብና ቧንቧ ጋር የተያያዙ በሽታዎችንም ቢሆን ይቀንሳል፡፡
6. ለስኳር በሽ ያላቸውን ተጋላችነትም ይቀንሳል፡፡ ለምሳሌ፣ የላም ወተትን የሚጠቀም ህፃን ካለበላም ወተት ውስጥ ለሚገኘው ቤታ ካሴይን ለተባለው ፕሮቲን የሚለቀቀው የሰውነት መከላከያ ኢንሱሊን አምራች የሆነውን መረጭ ስለሚጎዳው ህፃኑ ለስኳር በሽታ የመጋለጥ ዕድሉ ይጨምራል፡፡
7. የእናት ጡት ወተት ህጻናት በደም ካንሰርና ለሌላ በልጆች ላይ የሚከሰትን ካንሰር የመቀነስ አቅም አለው፡፡
እናት ልጇን ጡት በማጥባቷ ለራሷ የምታገኛቸው ጥቅሞች
1. ከወለደች በኋላ ያለው የማህፀን ደም መፍሰስን ይከላከላል፡፡
ምክንያቱም ህፃነት በሚጠቡበት ጊዜ ኦክሲቶሲን የተሰኘው ሆርን ይመነጫል፡፡ ይህ ሆርሞን ደግሞ የማህፀን ጡንቻ እንዲኮማተር በማድረግ የማህፀን መሸብሸብ በማምጣት የደም መፍሰስን ይቀንሳል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ሆርሞን ነው ምጥን የሚያመጣው፡፡ ህዝባችን በተለምዶ የምጥ መርፌ ይለዋል፡፡ በጉልኮስ ውስጥ ተጨምሮ በነጠብጣብ መልኩ ወደ እናትየዋ ደም ሲገባ ምጥ ከተደበቀበት ከች ይላል፡፡ ምክንያቱም ማህፀንን ማኮማተር ደስ ይለዋል፡፡
2. የእርካታዋን ጊዜ ያሰምርላታል
ኦክሲቶሲን የተሰኘው ሆርሞን በፍቅር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ሚና እንዳለው ተገልፆልናል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ጥንዶች ሩካቤ በሚፈፅሙበት ጊዜ ይህ ሆርን መንጭቶ ደስታን ያጎናፅፋቸዋል፡፡ ልክ እንደዚህ ሁሉ ህፃኑ በሚጠባበትም ጊዜ ይህ ሆርሞን ይመነጫል፡፡ አንዱ ዓላማው ወተቱን ማፍለቅ ሲሆን ሁለተኛ አላማው ደግሞ በእናትና በህፃኑ መካከል ያለውን ትስስር ማጠንከር ነው፡፡ እጅግ ደስተኛ ያደርጋታል፡፡ ለልጇ ያላትን ጉጉት ይጨምረዋል፡፡
3. እንደ ወሊድ መቆጣጠሪያ ያገለግላታል
የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ባደረገው ጥናት ጡት ብቻ ለስድስት ወር የሚያጠቡ እናቶች በስድስቱ ወር ውስጥ የማርገዝ ዕድላቸው 1.2 በመቶ ነው፡፡ ከ100 እናቶች ውስጥ አንዷ ብቻ ታረግዛለች እንደ ማለት ነው፡፡ እስከ ስድስት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ጡት ማጥባትን ለወሊድ መቆጣጠሪያ መጠቀም የምትፈልግ ካለች ልጇን ለስድስት ወር መደበኛ በሆነ ጊዜ ውስጥ ጡት ብቻ ማጥባት ይኖርባታል፡፡
ቢሆንም ግን ያለውን ችግር ማለት አንድ ፐርሰንቷንም ቢሆን ለመቀነስ አብዛኛው የህክምና ባለሙያዎች ለሶስት ወር ብቻ ይህን ስልት እንዲጠቀሙ ይመክራሉ፡፡
4. ጡት የምታጠባ እናት በጡትና በእንቁልጢ (Ovary) ካንሰር የመጠቃት ዕድሏን በእጅጉ ትቀንሳለች፡፡
5. ከወጪ አንፃርም ቢሆንም ጡት ማጥባት እጅጉን ተመራጭ ነው፡፡ አሜሪካ ውስጥ በተደረገ ጥናት ዱቄት ወተት ከሚጠቀሙት ይልቅ የሚያጠቡት እናቶች 1000 ዶላር በየዓመቱ ይቆጥባሉ ተብሏል፡፡
እንዴት እናጥባቸው?
የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ህፃናት የመጀመሪያ ስድስት ወር ምግባቸው ጡት ብቻ እንዲሆን ደንግጓል፡፡ እናትን ሌሎች ምክንያቶች ካልገደቧት በቀር፡፡ ለምሳሌ ከ6 ወር በፊት የላም ወተት ቢጀምሩ የህጻናቱ አንጀት ያልዳበረ ስለሆነ የሚገባው የላም ወተት የአንጀት ግድግዳቸውን ጎድቶ ለአንጀት ኢንፌክሽን ከማጋለጡ በተጨማሪ የብረት ማዕድን በሚገባ እንዳይመጠጥ ስለሚያግድ ለደም ማነስ ያጋልጣቸዋል፡፡ መግቢያችን ላይ ያላቸውን ህፃንን አስታውሷት! ስለዚህ በመጀመሪያው ስድስት ወር ጡት ብቻ መጥባት ይኖርባቸዋል፡፡ ራሳቸውን ከደም ማነስና ከአንጀት ኢንፌክሽን ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ከጡት ወተት የሚገኘውን ጥቅም ለማግኘት ሲሉ የእናት ወተት ብቻ በዚህ ጊዜ እንዲጠቡ ይመከራል፡፡
ህፃናት መጥባት መጀመር ያለባቸው በተወለዱ በአንድ ሰዓት ውስጥ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ይህም የመጥባት አቅማቸውን ያሳድገዋል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን የእናትየዋ ገላ ከህፃኑ ገላ ጋር መነካካት የራሱ የሆነ በጎ ጎን አለው፡፡ በ‹‹ኦፕሬሽን›› የሚወልዱ እናቶች ህፃናቱ በተወሰነ መልኩ ለጊዜው ፍዘት ሊያጋጥማቸው ይችላሉ፡፡ ይኸውም የማደንዘዣው ተፅዕኖ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ የሚከሰተው ለኦፕሬሽ ግልጋሎት የዋለው ጠቅላላ ማደንዘዣ ከሆነ ነው፡፡ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ከእንብርት በታች የሚያደነዝዘውን መንገድ ስለሆነ የሚጠቀሙት ህፃናት በማደንዘዣው ተጽዕኖ ስር አይወድቁም፡፡ ይህም ቢሆን ቶሎ መጥባት እንዲጀምሩ ማበረታት የተገባ ነገር ነው፡፡
የአጠባባቸው መንገድ
ለመጀመሪያ ጊዜ የምትወልድ እናት የማጥባት ችግር ያጋጥማታል፡፡ በደንብ ማጥባት ካልቻለች ደግሞ ለእርሷም ሆነ ለልጇ ሰላም አይሰጥም፡፡
– በመጀመሪያ ህጻኑን እንዴት አድርጋ በእጇ ይዛ ማጥባት እንደምትችል (Posioning) እገልፀዋለሁ፡፡
– ሁለተኛው ደግሞ ህፃኑ እንዴት አድርጎ የጡቷን ጫፍ መያዝ እንዳለበት እንመለከታለን፡፡
1. ህጻኑ በታችኛውና በላይኛው ከንፈሩ መካከል አፉን ሲከፍት 120 ዲግሪ መስራት አለበት፡፡
2. የታችኛው ከንፈሩ ወደ ውጪ መገልበጥ አለበት፡፡
3. የህፃኑ አገጭና አፍንጫ ከጡቱ ጋር በጣም መቀራረብ አለበት፡፡
4. ጉንጩ ሙሉ ሆኖ መታየት አለበት፡፡
5. የህፃኑ ምላስ ከታችኛው ድዱ ወይም ጥርሱ በላይ ሆኖ ወደፊት ትንሽ መውጣት አለበት፡፡
ህፃኑ የጡቱን ጫፍ በስርዓት ላለመያዙ ምልክቶች፡-
1. የላይኛውና የታችኛው ከናፍር በአፍ ጠርዝ (comer of mouth) መገኛነት፡፡
2. የሰረጎደ ጉንጭ
3. የምላሱ ጫፍ ከእናትየዋ ጡት ጫፍ በታች አለመታየት፡፡
4. ካጠባች በኋላ የማሸብሸብ የጡት ጫፍ፡፡
ምን ያህል ጊዜ በቀን ይጥቡ?
የአመጋገቡ መጠን እንደ እናትየዋ የጡት ወተት መጠንና የህጻኑ የመጥባት አቅም ሊወሰን ቢችልም በተለይ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከ8-12 ጊዜ በቀን ሊጠቡ ይገባል፡፡ እናትየው በምታጠባበት ጊዜ የመጨረሻው ወተት እስኪወጣ ድረስ በደንብ ማጥባት አለባት፡፡ ምክንያቱም የመጨረሻው ወተት በስብ ፀጋ የተጥለቀለቀ ስለሆነ ፈጣን የሆነ ዕድገት ለህፃኑ ያጎናፅፈዋል፡፡ ስለዚህ በአንድ ጊዜ አንደኛዋን ጡት ብቻ እንዲጠባ በማድረግ የመጨረሻ ወተቱን እንዲያገኝ ማድረግ አለባት፡፡
የእናት ጡት ወተት በባህሪው ህጻኑን እንቅልፋም የማድረግ አቅም አለው፡፡ ስለዚህ ህፃናት እንቅልፋቸውን በመለጠጥ ይታወቃሉ፡፡ ወደው አይደለም፡፡ እንቅልፍን እየጠጡ ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ህፃኑ በእንቅልፍ ምክንያት ሳይጠባ አራት ሰዓት ካለፈው እናቴ ሆይ! ቀስቅሺና አጥቢው፡፡
ህጻኑ መራቡን እንዴት ልወቀው?
ህፃኑ መራቡን እንዴት ልወቀው የሚል ጥያቄ ተነስቷል፡፡ ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ህፃናት እየተራቡ የሚግደረደሩት ጉድ የላቸውም፡፡ እንደ እኛ ይሉኝታ የለባቸውም፡፡ ግን አፍ አውጥተው ራበን አይሉም፡፡ ስለዚህ ምን እናድርግ?
የመራብ ምልክቶች (Feeding Cues)
1. እጃቸውን ወደ አፋቸው ማስጠጋት ወይም ማንቀሳቀስ
2. እጃቸውን መጥባት
3. መነጫነጭ
4. እጅና እግራቸውን ማወዛወዝ ወይም የመቅዘፍ አይነት እንቅስቃሴ ማሳየት፡፡
5. ማሚ በእነዚህ አራት ምልክቶች የማትረዳ ከሆነ የመጨረሻ ምልክታቸውን ያሳያሉ፡፡ ‹‹እሪ›› ብሎ ማልቀስ! መቼስ እናት ልጇ ስታለቅስ ተረት አታነብለትም፡፡ በልዩ ፍቅሯ ከመንታ ምንጮቿ በአንደኛው የልጇን ጥም ታረካለች እንጂ፡፡
የመጥገብ ምልክቶች
‹‹ልጅ ሆዴን አመመኝ እንጂ ጠገብኩኝ አያውቅም›› የሚል ብሂል አለን፡፡ ይሄ ተረት አፉን ለፈታ ህጻን ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ ለተለወደው ህፃንስ ምን መፍትሄ አለ ካላችሁ የሚከተለውን ነገር አስታውሱ፡፡
1. ህፃኑ በራሱ ጊዜ የጡቱን ጫፍ ይለቃል፡፡
2. የፊቱና የእጆቹ ጡንቻዎች ሲረግቡ ይስተዋላል፡፡
3. ከሁለትና ሶስት ወር በታች የሆኑ ህፃናት ወደ እንቅልፍ አለማቸው ይመለሳሉ፡፡
በቂ የሆነ የጡት ወተት እያገኙ መሆናቸውን በምን እንወቅ?
1. የሚወስዱት መጠን
ከላይ እንደተገለፀው በመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት ከ8-12 ጊዜ በቀን መውሰድ ሲኖርባቸው የመጥባት ችሎታቸው እየዳበረ በሚመጣበት ሶስተኛና አራተኛ ሳምንታት ከ7-9 ሊቀንስ ይችላል፡፡ አንዴ በሚጠቡበት ጊዜ ከ10-15 ደቂቃ በመጀመሪያው ሁለት ሳምንታት ሊወስድ ይችላል፡፡ ወራቸው እየገፋ ሲመጣ ግን ከ8-10 ደቂቃ በቂ ሊሆን ይችላል፡፡
2. ክብደታቸውን በተመለከተ
ህፃናት ገና እንደተወለዱ ባለው የመጀመሪያ ሳምንት ከ5-7 በመቶ የሚደርስ የክብደት መቀነስ ይገጥማቸዋል፡፡ ለምሳሌ፣ ሶስት ኪሎ የሆነ ህፃን ሩብ ኪሎ ሊቀንስ ይችላል፡፡ ከሁለተኛው ሳምንት ጀምሮ ግን ከ15-40 ግራም የሚደርስ ጭማሬ በየቀኑ ያገኛል፡፡ ነገር ግን ከ7 በመቶ በላይ ቅናሽ እያመጣ ያለ ህፃን ልዩ የሆነ ምርመራ ያስፈልገዋል፡፡
3. የሽንታቸው መጠን
የሽንታቸው መጠን ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ይመጣል፡፡ በመጀመሪያው 24 ሰዓት አንድ ጊዜ ሲሸኑ፣ በሁለተኛው ቀን ከ2-3ጊዜ፣ በ3ኛውና በ4ኛው ቀን ከ4-6 ጊዜ፣ ከ5ኛው ቀን በኋላ ከ6-8 ጊዜ ይሸናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ የሽንታቸው ድግግሞሽ ከቀነሰ፣ ደማቅ ቢጫ ሽንት ከሸኑ ወይም ቀያይ ጠብ የሚመስሉ ደቃቅ ነገሮች፣ ከሽንታቸው ጋር ተቀላቅሎ ከወጣ እየወሰዱት ያለው የጡት መጠን በቂ አለመሆኑን ጠቋሚዎች ናቸው፡፡
4. ካካቸውን በተመለከተ
የመጀመሪያው ሶት ቀኖች ካካቸው ደማቅ ጎመኔ ቀለም ይኖረዋል፡፡ ከአራተኛው ቀን ጀምሮ ቢጫና የተፈረፈረ ወደ መሆን ይቀየራል፡፡ ነገር ግን ጥቁር እንደሆነ የሚቀጥል ከሆነ የአጠባቡ ችሎታው ገና ያልዳበረ መሆኑን ወይመ በቂ ጡት እየመነጨለት አለመሆኑን ሲያመለክት፣ ሲከፋ ደግሞ የአንጀት መዘጋትን ሊያመለክት ይችላል፡፡
አረንጓዴ ካካ፡- አንዳንዴ ህጻናት አረንጓዴ ካካ ይኖራቸዋል፡፡ መቼስ ጡት ብቻ የሚጠባ ህጻንን ካካው አረንጓዴ የሆነው ጎመን በልቶ ነው ብለን ስሙን አናጠፋም፡፡ ምክንያቱ እንዲህ ነው፡፡ ቅድም ስለመጨረሻው ወተት ሲያነቡ ነበር፡፡ የዚህ ወተት ሌላው ጥቅሙ ከፍተኛ የሆነ ስብ በውስጡ ስለያዘ የአንጀትን እንቅስቃሴ በማዘግየት ወተቱ ትንሹ አንጀት ላይ ላክቶስ የተባለው ካርቦ ሃይድሬት በደንብ እንዲፈጭ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን እናትየው የአንዱ ጡቷ ወተት በደንብ ተጠብቆ ሳያልቅ የምትቀይረው ከሆነ የመጨረሻውን ወተት ህጻኑ ሳያገኝ ይቀራል፡፡ ስለዚህ የአንጀት እንቅስቃሴው ፈጣን ስለሚሆን ብዙ ላክቶሶች /ወተት ውስጥ ያለ ካርቦሃድሬት/ ትልቁ አንጀት ላይ እንዲደርሱ ያደርጋል፡፡ እዚያ የሚገኙት ባክቴሪያዎች ደግሞ የሚፈጥሩት ጋዝ ካካውን አረንጓዴ ቀለም ይዞ እንዲወለድ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ እናቶች በዚህ ሊደነግጡ አይገባም፡፡ ይልቁንም ጡታቸውን በሚገባ ማጥባት ይኖርባቸዋል፡፡
በአጠቃላይ ህፃናት በቀን ከሶስት ጊዜ በላይ ካካ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ እስከ ስድስት ወር ጡት ብቻ ለህፃኑ መስጠት ቁርጥንና ክትፎን ያስንቃል ተብሎ ይታመናል፡፡ ነገር ግን በቂ የሆነ የጡት ወተት ማመንጨት ካልቻለች የዱቄቱን ወተት ልትጠቀም ትችላለች፡፡ በቂ አለመሆኑንም ልታውቅ የምትችልበት መንገዶች እነኚህ ናቸው፡፡
1. ከ7% በላይ ክብደት መቀነስ ካለው
2. የሽንቱ ወይም የሰገራው መጠን መቀነስ ካለው ዱቄቱን በጥብጣ ልትሰጠው ትችላለች፡፡
የዱቄት ወተት እየበጠበጠች በምትሰጥበት ጊዜ ግን የጡቷን ወተት ያገኘችውን ያህል መስጠት ይኖርባታል፡፡ ምክንያቱም የጡት ወተት በወጣ መጠን የመተካቱና፣ የቀጣዩ ጡት ወተት የመጨመር መጠኑ እየጨመረ ስለሚመጣ ነው፡፡
ጡት ማጥባት የሚከለከልበት ጊዜ አለወይ?
መልሳችን አዎ ነው፡፡
1. የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ በደሟ ያለ እናት ጡት ብቻ የምታጠባ ከሆነ እስከ ስድስት ወር ድረስ ማጥባት ትችላለች፡፡ ተጨማሪ ምግብ መስጠት ስትጀምር ግን ሙሉ ለሙሉ ማጥባቷን ማቆም ይኖርባታል፡፡
2. እናትየዋ የቲቢ በሽተኛ ከሆነች መድሃኒቱን ከጀመረች እስከ ሁለት ሳምንት ድረስ ማጥባት አትችልም፡፡ ምክንያቱም በምታስልበት ጊዜ ባክቴሪያው ወደ ህፃኑ እንዳይተላለፍበት ነው፡፡ በሌላ አባባል እናትና ልጅ መገናኘት አይችሉም፡፡ ጡቷ ግን እየታለበ ህጻኑ ሊጠቀምበት ይገባል፡፡
3. የጡት ቁስለት ሊያመጣ የሚችል ኸርፐስ የተባለ በሽታ አለ፡፡ ከህጻኑ አፍ ጋር ሲነካካ ቫይረሱ ሊተላለፍበት ይችላል፡፡ በሽታው በባለሙያ ይታወቃል፡፡ በዚህ ጊዜ በጥንቃቄ ወተቷን አልባ ልትሰጠው ይገባል፡፡
4. አልኮል የጡት ወተት ምርትን ከመቀነሱም በላይ የልጁን የነርቭ ዕድገት ሊያቀጭጭ ይችላል፡፡ ስለዚህ አቁሚ ባንልም የአልኮል መጠጧን ልትቀንስ ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አልኮል ከወሰደች ልጇን ከሁለትና ሶስት ሳታት ቆይታ በኋላ ብታጠባው መልካም ነው፡፡
5. ሲጋራ የምታጨስ እናት ጡት አታጥቢ ማለት ቢከብድም ሲጋራ የሚያጨሱ አጥቢ እናቶች ጤነኛ መስለው ድንገት የሚሞቱ ህፃናት ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ ማጨስ ማቆም ለእርሷም ለልጇም መልካም ነው፡፡
6. አንዳንድ መድሃኒቶች፡፡ ይሄ መድሃኒቱን የሚያዘው የህክምና ባለሙያ የትኞቹን መድሃኒት ሲወስዱ ማጥባት እንደሚከለክል ይገልፅልሻል፡፡
ጡት ማጥባት መቼ ይቁም (Weaning)?
የአሜሪካ የህፃናት አካዳሚ (American Academy of pediatrics- AAP) ለአንድ ዓመት ያህል ከተቻለም ከዚያ ቢያልፍ ጥሩነቱን መስክሯል፡፡ ስለዚህ መቼ ይቁም የሚለውን የእናትዬዋ ምርጫ ነው፡፡ ከቻለች ልጇ አቅመ አዳምና ሔዋንን እስኪርስ ማጥባት መብቷ ነው፡፡ ግን እንዴት ይቁም የሚለውን ትንሽ ነገር ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ጡት ማጥባት ለማቆም ግራዋና ሬት መጠቀም በእኔ ይብቃ እላለሁ፡፡ እንደውም ጡቷ ጫፍ ላይ ፕላስተር ለጥፋ ልጇን አስደንግጣ ጡት ያስተወች ዘመድ አለችኝ፡፡ ስለዚህ እንዴት ይቁም? ድንገት ማቆም ለልጅም ዱብ ዕዳ ይሆንበታል፡፡ ለእናትየዋም ጥሩ አይሆንም፡፡ ለምሳሌ፣ እናትየው በጡት መወጠር እንዲሁም የወተት ትኩት ‹‹Milk fever›› ለተሰኘ መገለጫው ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለትና ደስ የማይል ስሜት ለሆነ በሽ ልትጋለጥ ትችላለች፡፡ ስለዚህ ማቆም ያሰበች እናት እንዲህ አድርጋ ልታቆም ትችላለች፡፡
1. ሲጀመር ህፃኑ ተጨማሪ ምግብ ሲጀምር ለጡት ያለው ፍላጎት እየቀነሰ ይመጣል፡፡
2. ለሁለት ወይም ለአምስት ቀን አንዴ ጡት መከልከል፡፡
3. የምታጠባበትን ደቂቃ ማሳጠር፡፡ ለምሳ ከ8-10 ደቂቃ በአንድ ጊዜ የምታጠባ ከሀነ ወደ 5 ወይም 3 ደቂቃ መቀነስ፡፡
4. የምታጠባበትን ጊዜ ማራራቅ፡፡ ለምሳሌ፣ በፊት በየሁለት ሰዓት የምታጠባ ከሆነ በየ 4 ሰዓቱ ማጥባት፡፡
5. ተጨማሪ ምግቡን ሌሎቹ የቤተሰቡ አባላት እንዲሰጡ ማድረግ፡፡ ከእናትም ውጭ ምግብ ሊሰጠው የሚችል አካል እንዳለ ማስለመድ፡፡ ህጻኑም ‹‹ለካም እንዲህ አለ!›› ማለት ይጀምራል፡፡ ይሄን ስል ግን እናትየዋ ሌላ ሀገር ትሂድ ማለቴ አይደለም፡፡ ስትርቀውም ደግሞ ሌላ ችግር ነው፡፡
6. ከጡት ወደ ጡጦ መሸጋገር ለህጻናት በመጀመሪያ ጊዜ ሞታቸው ነው፡፡ እርግጥ ከጡጦ ይልቅ በስኒ ቢጋቱ ተመራጭ ነው፡፡ እምቢ ካሉ ግን ጡጦውን መጠቀም ነው፡፡ ስለዚህ የጡጦውን ጫፍ ለህፃናቱ በሚሆናቸው መጠን መፈለግ ግድ ነው፡፡
በዚህ ጊዜ እናትየዋ ጡቷ እየተወጠረ ካስቸገራት ትንጥዬ ጨምቃ ልታፈስ ትችላለች፡፡ ብዙ ካለበችው ግን ወዲያውኑ መልሶ ይተካል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቀዝቃዛ ነገር ለምሳሌ በረዶ ልታስቀምጥበት ትችላለች፡፡ ህመሙ በጣም የሚያስቸግራት ከሀነ ፓራሴታሞል ወይም አይቡፕሮፊን ልትጠቀም ትችላለች፡፡
በአጠቃላይ የእናት ጡት ወተት በዚህች ምድር ላይ ለህፃኑ የተዘጋጀ ምርጥ ስጦታ ነው፡፡ እናቶች አምጠው መውለድ ብቻ ሳይሆን ከመንታ ጡታቸውም አመንጭተው ህፃናቶቻቸውን ንጉስ ማድረግም ያውቁበታል፡፡ እናቶች ሆይ የመጀመሪያውን ስድስት ወሮች ለልጆቻችሁ የምግብ ምርጫ የራሳችሁ መንታ ምንጮች ይሁን፡፡
The post Health | መንታ ምንጮች | የእናት ጡት ወተት ለጤናማ ልጆች ዕድገት (ልዩ ዘገባ) appeared first on Zehabesha Amharic.