አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በ2013 ራሳቸውን ከአሰልጣኝነት ሲያገልሉ ማን ያልደነገጠ ነበር? በኦልድትራፎርድ ደግሞ ይሄ ስሜት ፍፁም የተለየ ነበር፡፡ በማንችስተር ዩናይትድ ብቻ ሳይሆን በመላው እንግሊዝ እንደ ፈርጉሰን አይነት ውጤታማ አሰልጣኝ ፈልጎ ማግኘት አይቻልም፡፡
ሰር አሌክስ ጡረታ የመውጣት እቅድም ሆነ ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ ሆኖም የባለቤታቸው ካቲ መንትያ እህት -ብሪጌት ሮበርትሰን ህልፈተ ህይወት ይሄንን ውሳኔ እንዲያሳልፉ እንዳስገደዳቸው ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ያለጥርጥር በሥራዬ እቀጥል ነበር›› ብለዋል- ታላቁ አሰልጣን ከቴሌግራፍ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ‹‹በአንድ ምሽት ባለቤቴ (ካቲ ፈርጉሰን) ቴሌቪዝን እየተመለከተች ፊቷ ላይ ጥሩ ነገር አላስተዋልኩም፣ ከቴሌቪዥኑ ይልቅ የቤቱን ጣሪያ ስትመለከት አስተዋልኩኝ፣ የብቸኝነት ስሜት እንደተሰማት አውቃለሁኝ፣ እርሷ እና ብሪጌት መንትያ ነበሩ›› ብለዋል፡፡
የፈርጊ ባለቤት ካቲ አሰልጣኙ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ጥያቄ ያቀረቡላቸው በ2002 ነበር፡፡ በወቅቱ ታላቁ አሰልጣኝም ይሄንን ውሳኔ ለማሳለፍ ከውሳኔ ላይ ደርሰው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የኋላ ኋላ ውሳኔያቸውን ለውጠው በሚወዱት ሙያ ቀጠሉ እንጂ፡፡
‹‹ለሁለተኛ ጊዜ ይሄንን ጥያቄ ስታነሳልኝ ጥያቄውን ውድቅ ማድረግ አልቻልኩም፤ ከእውነተኛው ምክንያት ውጭ ሌላ ምክንያት ሊኖራት እንደማይችል አውቃለሁኝ›› የሚል አስተያት ሰጥተው በውሳኔያቸውን እንደማይፀፀቱ ገልፀዋል፡፡
የብሪጌት ህይወት ያለፈው በኦክቶበር 2012 ነበር፤ ፈርጊ የባለቤታቸው ስሜት ከመጥፎው አጋጣሚ በኋላ በጎ እንዳልሆነ ተገንዝበዋል፡፡ የአሁኑ ባለቤታቸውን ያገኙት በ1966 በግላስኮው ‹‹የአድማ ስብሰባ›› ላይ ነበር፡፡
ታላቁ አሰልጣኝ የግል ህይወታቸውን የሚተርከው መጽሐፍ ላይ በሰጡት አስተያየት ‹‹ባለቤቴ ሁልጊዜም ቢሆን የቤቱን በር ክፍት አድርጋ ትጠብቀኝ ነበር፤ ሌሊት 8፡00 እና 9፡00 ሰዓት ቤት ስመጣ እንኳን በር ስር ሆና ትጠብቀኝ እንደነበር መናገር አለብኝ፤ ስመጣ የሞቀ አቀባበል ታደርግልኝ ነበር›› ብለዋል፡፡
ፈርጊ ለመጨረሻ ጊዜ ለንባብ ያበቁትን መጽሐፍ ማስታወሻነቱን ለባለቤታቸው መንትያ እህት ብሪጌት አበርክተዋል፡፡ በአሰልጣኝነት ህይወታቸው ስኬታማ የሆኑት በባለቤታቸው ድጋፍ እንደሆነ ለመግለፅ ፍርሃት አልተሰማቸውም፤ ኧረ እንዲያውም ‹‹ቀዳሚዋ እርሷ ናት›› ለማለት አልሰነፉም፡፡
በ39 ዓመት የአሰልጣኝነት ቆይታቸው ላስመዘገቡት ስኬት ባለቤታቸውን ቀዳሚ ሲያደርጉ ብዙዎች ውስጣቸው ተነክቷል፤ ጥሩ ትምህርት እንዳገኙም ጥርጥር የለውም፤ አሰልጣኙ የስኬት እና በአንድ ክለብ ውስጥ ረጅም ዓመት የማሰልጠን ምልክት ናቸው፡፡
እርሳቸው በሜይ 2013 ለ13ኛ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ከሆኑ በኋላ የተሾሙት አሰልጣኞችም ቢሆኑ ከስኬት ጋር ተራርቀዋል፡፡ ከሳምንታት በፊት የኔቪል ወንድማማቾች ወላጅ አባት ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት ፈርጊ በስፍራው ደርሰው ከመኪናቸው ሲወርዱ እዚያ የነበሩ ደጋፊዎች በጣም በጩኸት ስሜት ውስጥ ሆነው ‹‹እናመሰግናለን፤ ሰር አሌክስ›› ብለዋቸዋል፡፡
በማንችስተር ዩናይትድ የነበራቸውን የ26 ዓመት ቆይታ አስመልክተው ‹‹ጡረታ እንደምወጣ እያወቅኩኝ እንኳን የክለቡን ደረጃ ለማስጠበቅ ጥረት ሳደርግ ነበር፤ ደካማ በሚባሉ ቦታዎች ላይ ተጨዋቾችን ማስፈረም ነበረብን፤ በምንም ነገር ዙሪያ ስለማንችስተር ዩናይትድ ስናገር የአውቶብሱ ጉዞ እንደሚቀጥል ገልጫለሁኝ፣ ማንም ወደ ኋላ አይቀርም፤ በቀጣይ መዳረሻችንን በተመለከተ ሁሉም አካል በእኛ ላይ ሙሉ እምነት ነበረው›› የሚል አስተያየትን ሰጥተዋል- ፈርጊ፡፡
ህይወት ከኦልድ ትራፎርድ በኋላ
ፈርጉሰን ውሳኔያቸውን ካሳለፉ በኋላ ወደ ኋላ አልተመለሱም፣ ውሳኔያቸውን ተከትሎ ቀጣይ ስራቸውን የወሰኑት ቀደም ብለው ነበር፡፡
‹‹ጡረታ ከወጣሁኝ በኋላ ዕድሜው እንደገፋ ሰው ያለ ሥራ መቀመጥን አልመረጥኩም›› ይላሉ- ቁጡው አሰልጣኝ፡፡
ጨምረውም ‹‹አባቴ ከመርከብ ሥራው ጡረታ የወጣው በ65 ዓመቱ ነበር፤ በግሌ እርሱ እንደሆነው መቀመጥን አልመረጠም፣ በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ (በትርፍ ጊዜያቸው በሃርቫርድ ቢዝነስ ስኩል ያስተምራሉ) መስራት ነበረብኝ፡፡…
…ከዚያ ውጭ በዩናይትድ እንደ ዳይሬክተር እና አምባሳደር እንዲሁም ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እና (ዩኒሴፍ) ጋር መስራትን መርጫለሁኝ፤ ከዩናይትድ ጋር በየዓለማቱ በመጓዝ ቡድኑ ሲጫወት መመልከት ያስደስተኛል›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የፈርጉሰን ስኬት ምስጢር
የዘመኑ እግርኳስ እንደ ሰር አሌክስ አይነት ስኬታማ አሰልጣኝ ተመልክቶ አያውቅም፤ ፈርጊ ሁልጊዜም አንድን አሰልጣን ለስኬት የሚያበቃው ‹‹ስብዕናው፣ በውስጡ ያለው ኃይል፣ ውሳኔ ሰጪነቱ (የውሳኔ ሰው መሆን)፣ አስተውሎቱ እና ግንኙነቱ ነው›› የሚል መረጃን ሰጥተው ‹‹ይህ በኬብል ካምፓኒ አልያም ባርክሌይስ ባንክ ለሚሰራ ሰው ሳይቀር ይሰራል፣ ሁልጊዜም ቢሆን የምትገናኘው ከሰው ልጅ ጋር ነው፣ ከሰው ልጅ ጋር ስትገናኝ ደግሞ ቀጥተኛ መሆን እና ተነሳሽነት መፍጠር ግድ ይልሃል፣ በአለቃቸው ላይ ከፍተኛ እምነት ሊኖራቸው ይገባል›› በማለት ምስክርነታቸውን ገልፀዋል፡፡
ፈርጊ በመጽሐፋቸው ላይ የስኬታማነታቸውን ምስጢር በግልፅ ዘርዝረዋል፣ ወደ ኋላ መለስ ብለውም ‹‹ምንም ነገር ለማድረግ አልፈራም ነበር፤ ተጋጣሚዬን ለማሸነፍ ምንም አይነት ሪስክ ከመውሰድ ወደኋላ አልልም፤ ከዚህ በተጨማሪም በወጣት ተጨዋቾች መጠቀም ያስደስተኛል›› የሚል አስተያየትን ሰጥተው ‹‹በወጣበት ተጨዋቾች ላይ ከፍተኛ እምነት አለኝ፤ በአበርዲንም ሆነ ሴይንት ሜሪን ወጣት ተጨዋቾችን ለታላቅ ስኬት የማብቃት ችግር አልነበረብኝም፤ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ከመጣሁኝ በኋላ በ1950ዎቹ ሰር ማት በስፒ የሰራውን ነገር መድገም ነበረብኝ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ወጣት ተጨዋቾች የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው፡፡ ይሄ እውነታ ለግማሽ ምዕተ ዓመት በኦልድ ትራፎርድ ሲተገበር ነበር›› በማለት የክለቡን ባህል ለማስቀጠል ባደረጉት ጥረት እንደሚኮሩ ገልፀዋል፡፡
ማንችስተር ዩናይትድ ለሁለት አስርት ዓመታት በባለግርማ ሞገሱ አሰልጣን ተመርቷል፤ በጎቫን በአስቸጋሪ ውጣ ውረድ ያለፉት ፈርጊ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ ከመምጣታቸው በፊት በስኮትላንድ በተጨዋችነት እና አሰልጣንነት አገልግለዋል፡፡ በተጨዋችነት ዘመናቸው ኃይል እና ጉልበትን ቀላቅለው የተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮችን ስቃይ ውስጥ ይከትቱ ነበር፤ በአሰልጣንነት ዘመናቸው ደግሞ ቁጡነታቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡
‹‹የመጣህበት መንገድ ለአለሰልጣኝነት ህይወቴ ጠቅሞኛል፤ ጥቂት እድለ ቢስ የሆኑ ሰዎችን ስናግዝ ቆይተናል፡፡ ለምሳሌ በጀማሪ ሰራተኞች አድማ ላይ መሳተፍ አያስፈልገኝም፣ አልያም እነኚህ ጀማሪ ሰራተኞች በአድማ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማበረታታት አይጠበቅብኝም፡፡ እኛ (የፋብሪካ ሠራተኞች) ጥሩ ክፍያ ይከፈለን ነበር፤ ችግር አልነበረብንም›› የሚል አስተያየትን ሰጥተው ‹‹የአሰልጣኝነት ፍቃድ ያገኘሁት በ24 ዓመቴ ነበር፡፡ ዕድሜዬ 32 ሲሞላ ለአሰልጣኝነት ዝግጁ ነበርኩኝ፤ እየተጫወትኩኝ አሰለጥን ስለነበር ለመወሰን አልቸገርኩም፡፡ በእግር ኳሱ ኢንዱስትሪ መማር አለብህ፣ አለበለዚያ በስራው መቆየት አትችልም›› በማለት አሰልጣኝነት ፈታኝ ሙያ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በቁጣ ተጨዋቾችን የሚያርዱት ታላቁ አሰልጣኝ በግላስኮው ቡና ቤት ከፍተው ይሰሩ ነበር፡፡ ወደኋላ ተመልሰው ‹‹ቡና ቤት አስቸጋሪ ስራ ነው፣ ይሰለቻል፣ ቅዳሜ ማታ ያለው ግርግር ይፈትናል፣ ሰዎች ይወጣሉ- ይገባሉ፡፡ የአሰልጣኝነት ዕድል ሳገኝ ስኬታማ መሆን እንደምችል ለራሴ ነገርኩት፣ እርግጥ ነው አሰልጣኝነት የውድቀት ስጋት አብሮ ያስከትላል፣ ነገር ግን ወደ ቡና ቤት ከመመለስ በአሰልጣኝነት ሙያ ስኬታማ መሆን እንዳለብኝ ቁርጠኛ ሆንኩኝ፣ በጭራሽ ወደኋላ ማሰብ እና መመለስ አላስፈለገኝም›› የሚል መረጃን ይሰጣሉ፡፡
በመጀመሪያ ክለባቸው ፈርጊ ተቸግረው ነበር፤ ያገኙት ባጀት እና የተጨዋቾች ቁጥር አነስተኛ መሆን አሰልጣኙን ፈትኗቸዋል፡፡
‹‹በአበርዲን በጣም ብዙ ነገሮችን ተምሬያለሁኝ፤ በመልበሻ ክፍል ውስጥ ጠንካራ ማንነት ይዞ መቅረብ እና በወጣት ተጨዋቾች ላይ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ ተገነዘብኩኝ›› የሚል አስተያየትን የሚሰጡት ፈርጉሰን በማንችስተር ዩናይትድ ተመሳሳይ የሆነ አካሄድን ተጉዘው እንደ ብሪያን ሮብሰን፣ ብሪያን ማክሌር፣ ማርክ ሂዩስ፣ ስቲቭ ብሩስ፣ ፖል ኢንስ እና ሮይ ኪንን የመሳሰሉ ተጨዋቾች ከታች አንስተው ለታላቅነት ለማብቃት አልተቸገሩም፡፡
ግልፅ የሆነ የመሪነት መርህ ያላቸው ቁርጠኛው አሰልጣኝ ‹‹ተጨዋቾቹ የማይደሰቱበትን ነገር በጠንካራ ማንነት መለወጥ ይቻላል፤ የዚህ አይነት ሰብዕና የተጨዋቾችን ማንነት ይለውጣል፤ ቁርጠኛ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ የአሸናፊነት መንፈስ ያሰርፃል፣ በቃ ነገሩ ይህን ያህል ቀላል ነው›› የሚል አስተያየትን ይሰጣሉ፡፡
እርግጥ ነው ከሰራተኛው መደብ መገኘታቸው በስልጠናው ውጤታማ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፤ ‹‹ከንጋቱ 11፡00 እና 12፡00 ላይ ከእንቅልፋቸው ተነስተው የማሽን ስራዎች ላይ የሚጠመዱ ሰዎችን መመልከት ለስራ ያነሳሳል፣ ሥራዎች የሚሰሩት በጋራ በመሆኑ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ይኖረዋል›› ይላሉ፡፡
የመጨረሻዎቹ ዓመታት ፈተና
ሰር አሌክስ ጡረታ ከመውጣታቸው በፊት የነበሩት የመጨረሻዎቹ ዓመታት ከተለያዩ ስመጥር ተጨዋቾች ጋር መጋፈጥ ነበረባቸው፤ ዴቪድ ቤካም በማንቸስተር ዩናይትድ የስኬት ዘመን ቁልፍ ከሚባሉ ተጨዋቾች መሀከል አንዱ ቢሆንም የኋላ ኋላ በሁለቱ ግለሰቦች መሀከል አለመግባባት ተፈጥሮ እንግሊዛዊው ለስንብት ተዳርጓል፡፡ አሰልጣኙ በ2003 ወደ ሪያል ማድሪድ እንዲያመራ ቢያደርጉም አሁን ግን ሁሉም ነገር አልፎ በድጋሚ ወዳጅነት መስርተዋል፡፡
‹‹ነገሮችን መቆጣጠር ያስፈልጋል፤ ለራስ የሚራ ከፍ ያለ ዓት መቆጣጠር አያስቸግረኝም፤ (ክርስቲያኖ) ሮናልዶ ከመስታወት ፊት ቆሞ ሊቀነጃጅ ይችላል፡፡ ይህንን የምመለከተው በበጎ ስሜት ነው፡፡ የተጋጣሚ ቡድን ተጨዋቾች እርሱን ለማቆም የመሰላቸውን ጥፋት ሊፈፅሙ ይችላሉ›› ይላሉ፡፡
‹‹አንድ ተጨዋች ፌራሪ መኪና እየነዳ ለምን ይሄንን የመኪና ሞዴል እንደመረጠ ራሳችሁን ለትጠይቁ ትችላላችሁ፤ ሆኖም ይህ የእርሱ ምርጫ ነው፡፡ በሊጉ መጨረሻ ወይም በወረደ ክለብ ውስጥ የሚገኝ ተጨዋች ያንን መኪና ይዞ ከተማ ውስጥ ሊያሽከረክር አይችልም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ይህንን መተግበር ይከብዳቸዋል፣ እውነተኛ ተጨዋቾች በዚህ ረገድ አይቸገሩም››
ኤሪክ ካንቶናን ተቆጣጥሮ ለስኬት መብቃት የቻለ አሰልጣኝ ምንም ነገር የሚሳነው አይመስልም፣ ‹‹ከካንቶና ጋር በየዕለቱ አወራ ነበር፤ የሚገባውን ክብር ያላገኘ መሳጭ ሰው ነው፣ በትክክለኛ ክለብ ውስጥ ስለነበር የሚፈልገው የሚያበረታታው ሰው ነበር፤ በልምምድ ሜዳ ላይ ተዳክሞ እና ዓይኑ ጠብቦ ልትመለከቱት ትችላላችሁ፣ የድብርት ስሜት ተጫጭኖት ምንድነው የሆነው? እንድትሉ ያደርጋል፡፡ ሆኖም አንድ ጊዜ ልምምድ ከጀመረ በኋላ ሁሉም ነገር ያስተካክላል›› የሚል መረጃን ሰጥተው ‹‹ሮናልዶ ሌላው ታላቅ ተጨዋች ነበር፣ ግን ደግሞ ፍፁም ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋች ነው፣ ሁሉንም ነገር በአግባቡ ይፈፅማል›› በማለት ከትልልቅ ተጨዋቾች ጋር በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ አልፈው እንደሰሩ ይናገራሉ፡፡
በአሰልጣኝነት ዓለም የፈርጉሰን ቀዳሚ መርህ ሌሎችን ማመን ነው፡፡ ነገሩ በሁለቱም መንገድ ይገለፃል፤ ይህንን መርህ እንዲያብራሩ ጥያቄ ስታቀርቡላቸው ‹‹በአሰልጣኝነት ቁልፉ ነገር በተጨዋቾቹ ላይ ከፍ ያለ እምነት መጣል ነው፡፡ እምነት ስትጥል ምንም ነገር ፈልገህ ሊሆን አይገባም፤ ለአንተ በመጫወታቸው የምቾት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ ግድ ነው፡፡ ራስህን ለእነርሱ አሳልፈህ መስጠት አለብህ፤ ሁልጊዜም ቢሆን ‹‹ይኸውላችሁ፤ እዚህ የተገኘሁት በአንድ ምክንያት ነው፡፡ ያላችሁን ምርጥ ብቃት አውጥታችሁ እንድትጠቀሙ እሻለሁኝ፣ ይህ ምርጥ ሰው እንድትሆኑ ያስችላችኋል፤ በዚህ ላይ ጥሩ ክፍያ ታገኛላችሁ እላቸዋለሁኝ፣ በማንቸስተር ዩናይትድ ይህንን ስፈፅም ነበር፡፡ ተጨዋቾቹ የራሴ ናቸው፣ ስኬታማ እንድሆን አግዘውኛል፣ ስለዚህ ለእነርሱ ታማኝ መሆን ነበረብኝ›› የሚል ምላሽ ይሰጣሉ፡፡
‹‹ፀጉር አድርቅ›› ቁጣ
የፈርጉሰን ቁጣ አስፈሪ ነው፡፡ ኧረ እንዲያውም የሚያስበረግግ በመሆኑ ‹‹ፀጉር አድርቅ›› ቁጣ እስከመባል ደርሷል፤ ‹‹ይሄ የማይረባ ስም ለረጅም ዓመታት አብሮኝ ኖሯል፣ ሆኖም ቡድኔ በጭራሽ በፍርሃት ስሜት ተሸብቦ አልተጫወተም፣ አንድ ተጨዋች እንኳን በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኖ አልተጫወተም፡፡ ተጨዋቾቼ በሙሉ ያላቸውን አቅም አውጥተው ሲጫወቱ ቆይተዋል፣ ሁልጊዜም ቢሆን ጀብደኛ ነበሩ፤ በቃ መልሱ ይኸው ነው›› ይላሉ፡፡
‹‹እርግጥ ነው በትክክለኛ ምክንያት ስሜትን መቆጣጠር አለመቻል ወይም መበሳጨት ክለቡ ማንችስተር ዩናይትድ እንደሆነ መታወቅ አለበት፤ ይሄ ነገር ካልረዳነው ትርጉሙ አይገባንም፡፡
‹‹አንድ አባባል አለን፤ ማንም በርህን አንኳኩቶ ገንዘብ አይሰጥህም፡፡ በሩን አንኳኩተህ አንድ የሆነ ነገር ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ወደ ሜዳ ውስጥ ገብተህ ጨዋታውን በማሸነፍ ገንዘብ ማግኘት አለብህ››
ሰር አሌክስ ተጨዋቾቻቸውን ለተደራራቢ ስኬት ያበቁበት የራሳቸው አካሄድ አላቸው፡፡ ‹‹ብዙዎቹን ምን ያህል ሜዳልያ አንገታቸው ላይ እንዲጠብቁ እጠይቃቸዋለሁኝ፤ (ራያን) ጊግስ ላይ ደርሳችኋል? የሚል ጥያቄ አነሳላቸዋለሁኝ፤ ስንቶቻችሁ ዘጠኝ ጊዜ አሳክታችኋል? ለ10ኛ ጊዜ ይህንን ክብር ማግኘት አትፈልጉም? እላቸዋለሁኝ›› ይላሉ፡፡
ከፈርጉሰን ስኬት በርካታ ነገሮች መማር ይቻላል፤ ጡረታ መውጣት ከክለብ ባለቤቶች፣ ሊቀመንበሮች እና ስራ አስኪያጆች ጋር በምን አይነት መልኩ ‹‹ንግግር ማድረግ›› እንዳለባቸው እንደተረዱ የገለፁት አሰልጣኝ ‹‹ዓለምን መቆጣጠር እችላለሁኝ›› የሚል አስተሳሰብ ጤናማ አይደለም፡፡ ከሜዳ ላይ ሰራተኞች እንዲሁም ከፅዳት እና ሻይ ቤት ሰራተኞች ጋር መነጋገር ተገቢ ነው›› የሚል አስተያየትን ይሰጣሉ፡፡
በስፒ፣ ጃክ ስቴይን እና ቢል ሻንክሌ ስኬታማ አሰልጣን ነበሩ፤ ‹‹ንግግርህ ግልፅ መሆን አለበት፤ ትክክለኛውን መረጃ ለተጨዋቾቹ በማስተላለፍ የምትፈልገውን ነገር ማግኘት ይቻላል›› ይሄ የፈርጊ የመጨረሻ ቃል ነው፡፡
The post Sport: ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ጡረታ የወጡት ለሚስታቸው ሲሉ መሆኑን ይፋ አደረጉ appeared first on Zehabesha Amharic.